Site icon Ethiopian Legal Brief

አንታራም ህጎቸ፤ ከዓለም ዙሪያና ከአገራችን

አንዳንዴ በየአገሩ የሚወጣው ህግ ይዘት ያስገርማል፡፡ ህግ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሰላም ስርዓትና ፀጥታ እንዲሰፍን የሚረዱ ደንቦችን በመደንገግ የጠቅላላውን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጠቅለል ባለ መልኩ ይቆጣጠራል፡፡ የአንድ አገር ህጎች ከአገሪቱ እድገት ጋር እያደጉ ሲመጡ በህግ ጥላ ስር የሚወደቀው የሰው ልጆች ባህርይ ድርጊትና እንቅስቃሴም እየሰፋ ይመጣል፡፡
ለምሳሌ በእኛ አገር መንገድ ላይ ወይም ሰው ፊት መትፋት ነውር ቢሆንም በህግ ግን በግልጽ የሚያስቀጣ ድርጊት አይደለም፡፡ በአሜሪካ በሚገኙ ብዙ ግዛቶች ይህን መሰሉ ነውር ድርጊት ለሥነ-ምግባር የተተወ ብቻ ሳይሆን በህግ ያስቀጣል፡፡ እንስሳትን መጠጥ ማጠጣት እንዲሁ በሀገራችን ድርጊቱ ያልተለመደ ከመሆኑም በላይ /ለዛውም በተወደደ ቢራ!/ በማህበረሰቡም ዘንድ ብዙም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች እንስሳትን መጠጥ ማጠጣት የሚከለክል ግልጽ ህግ አላቸው፡፡
በእኛ አገር ሰንበት ይከበራል፡፡ ያም ሆኖ ግን በሰንበት ቀን ስራ መስራትን የሚከለክል ህግ በእኛ አገር የለም፡፡ በአሜሪካ የተወሰኑ ግዛቶች በሰንበት ቀን የተወሰኑ ስራዎች /በህግ በተወሰነ ጊዜና ቦታ/ ለምሳሌ መኪና መሸጥ፣ መኪኖችን ለሽያጭ ማሳየት፣ የአልኮል መጠጥ መሸጥ በህግ የተከለከሉ ናቸው፡፡
ከላይ የጠቃቀስናቸው ህጎች ሁሉም በዋናው የየግዛቶቹ ህግ አውጪ የወጡ ሳይሆኑ በእኛ አገር ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ እንደምንለው በንዑስ መስተዳደሮች የወጡ ደንቦ ናቸውው፡ እነዚህ ደንቦች ሲወጡ የራሳቸው መነሻ ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ የፈለገውን ያህል አሳማኝ ምክንያት ቢኖርም ግን ግርምት ማጫራቸው አይቀርም፡፡
ከዚህ በታች በምሳሌነት የምናቀርብላችሁ በዓለማች ዙሪያ ያሉ ህጎች በይዘታቸው ዝርዝር ጉዳዮችን የሚመለከቱ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ይዘታቸው በራሱ ግርምትን ይፈጥራል፡፡ በተለይ በአሜሪካ ከድሮ ጊዜ ጀምሮ በተለያ ግዛቶች እና ንዑስ ክፍለ ግዛቶች የወጡት ደንቦችና ድንጋጌዎች ከአገራችን ህጎች ጋር ብናነፃፅራቸው ተመሳሳይ ቀርቶ ተቀራራቢ ህግ ለማግኘት እንቸገራለን፡፡
እነዚህን ህጎች ፈረንጆቹ /Dumb laws/ በጥሬው ሲተረጎም ደነዝ ህጎች እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ደነዝ የሚለው ቃል ለሰውም ለህግም ስለሚከብደኝ ግጥም ካልሆነ ግጥም መጠሪያ ስሙን ተውሼ አንታራም ህጎች ብላቸው እወዳለሁ፡፡ እስቲ ከወደ አሜሪካ የተወሰኑትን እንጠቃቅስላችሁ፡፡

አንታራም ህጎች ከወደ አሜሪካ

• ሳሙና ሲሰርቅ የተያዘ ሰው ሳሙናው እስኪያልቅ ድረስ መታጠብ ግዴታው ነው፡፡
• እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶችና ሴቶች በሚስቁበት ጊዜ የሚታይ ከአንድ በላይ ወላቃ ጥርስ እንዲኖራቸው አይፈቀድም፡፡
• በፍርድ ቤት የምስክር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ማልቀስ ክልክል ነውው፡
• በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ብስክሌት መንዳት ህገወጥ ነው፡፡
• ባገለገለ ፓንት መኪና መጥረግ ወይም ማጠብ ክልክል ነው፡፡
• ለውሻ ውስኪ መስጠት ህገ-ወጥ ነው፡፡
• በቀጭኔ ጀርባ ላይ ሆኖ አሳ ማጥመድ ክልክል ነው፡፡
• መንገድ ላይ መትፋት የሚያስቀጣ ድርጊት ነው፡፡
• አንድ ፀጉር ቆራጭ ፀጉሩን የሚቆርጠው ህፃን ልጅ “ጆሮህን እቆርጣሃለሁ!” ቢለው አባባሉ ለቀልድ ቢሆንም እንኳን ድርጊቱ ህገ-ወጥ ነው፡፡
• አንድ ሰው ነጭ ሽንኩርት ከበላ በኋላ አራት ሰዓት ያህል ሳይቆይ ሲኒማ ቤት ወይም ትያትር ቤት መግባት አይችልም፡፡
• አንበሳ ሲኒማ ቤት ይዞ መግባት ህገ-ወጥ ነው፡፡
• እጅጌ የሌለው ሸሚዝ አድርጎ ፓርክ ውስጥ መገኘት 10 ዶላር ያስቀጣል፡፡
• በእግር ኳስ የጎል ብረት ላይ ጉዳት ማድረስ 200 ዶላር ያስቀጣል፡፡
• ሁሉም የመኝታ ቤት መስኮቶች ጥርቅም ብለው በደንብ ካልተዘጉ በስተቀር ማንኮራፋት ክልክል ነው፡፡
• በፖሊስ ላይ ማፍጠጥ ክልክል ነው፡፡
• ፀጉር ቆራጮች ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ ነጭ ሽንኩርት መብላት አይችሉም፡፡
• በአውራ ጎዳና መሃል ፂም ወይም ፀጉር መላጨት ያስቀጣል፡፡
• ከአራት በላይ እርስ በእርስ ዝምድና የሌላቸው ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ መኖር አይችሉም፡፡

አንታራም ህጎች ከአለም ዙሪያ

እንደ አሜሪካ የበዛ ባይሆንም በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ አገራት በአንታራምነት የተፈረጁ ህጎች አሏቸው፡፡ ለአብነት የተወሰኑትን እንመልከት፡፡
ታይላንድ
• ፓንት፤ የውስጥ ልብስ ወይም የጡት ማስያዣ ሳያደርጉ ከቤት ወጥቶ መሄድ ክልክል ነው፡፡
ስዋዚላንድ
• ሴቶች ፓንት መልበስ አይችሉም፡፡ ፓንት ለብሳ የተገኘች ሴት የለበሰችው ፓንት በፖሊስ እንዲወልቅ ተደርጎ ከፊቷ ይቀደዳል፡፡
ሲንጋፖር
• ቆሻሻ መንገድ ላይ በመጣል ሶስት ጊዜ ጥፋተኛ ተብሎ በተደጋጋሚ የተቀጣ ሰው ‹‹እኔ ቆሻሻ ጣይ ነኝ!›› የሚል ጽሁፍ ያለበት ልብስ ለብሶ መንገድ እንዲያፀዳ ይገደዳል፡፡
አውስትራሊያ
• የመብራት አምፖል መቀየር የሚችሉት ፍቃድ የተሰጣቸው የኤሌትሪክ ባለሙያዎች ብቻ ናቸው፡፡
ዝምባቡዌ
• ፕሬዚዳንቱን ያጀበው የመኪና ትዕይንት ሲያልፍ ደስ የማይል የፊትና የሰውነት ንቅናቄ ወይም እንቅስቃሴ (offensive gesture) ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
ፈረንሳይ
• ዓሳማን ናፖሊዮን ብሎ መሰየም ሆነ መጥራት ህገ-ወጥ ነው፡፡
• ካለመቀበሪያ ቦታ መሞት ክልክል ነው፡፡

አንታራም ህጎች ከአገራችን

በአገራችን ከላይ እንዳየናቸው ዓይነት ፈገግታን የሚያጭሩ አንታራም ህጎች እስካሁን አልገጠመኝም፡፡ ሆኖም ከህገ-መንግስታዊነት መለኪያ አንጻር አንታራምነታቸው ጎልተው የወጡ የህግ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ እኔ የሚከተሉትን መርጫለው፡፡ ማብራሪያ አልተጨመረም፡፡

• “ክልሎች የራሳቸውን ህግ እስኪያወጡ ድረስ የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች ትራንፖርት ነክ በሆኑት ጉዳዮች ላይ በክልሎች ውስጥ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡”
(የትራንፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997 አንቀጽ 27(2)

• 37 በልዩ ሁኔታ ሰራተኞችን ስለማሰናበት
1) በዚህ ደንብ በሌላ ሁኔታ የተደነገገው ቢኖርም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ሰራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈፃፀም ስርዓት ሳይከተል ከስራ ማሰናበት ይችላል
2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከስራ የተሰናበተ ሰራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ስራ የመመለስ መብት አይኖረውም፡፡
(የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩል ባለስልጣን ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37)

• “ለባንክ ወይም ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ብድር መያዣነት የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በሚመለከት የተደረገ ውል በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1723 መሰረት በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ስልጣን በተሰጠው አዋዋይ ፊት አልተደረገም በሚል ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ይህ አዋጅ ከመጽናቱ በፊት በማናቸውም ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ አይጸናም፡፡”
(የፍትሐ ብሔር ህግ እንደተሻሻለ አዋጅ ቁጥር 639/201)

• እንደ ልዩ ጥቅምና ለሙያ ልቀት ማበረታቻ እንዲሆን አንድ አካዳሚክ ሰራተኛ ቋሚ ቅጥር ሊደረግ ይችላል፡፡ የአካዳሚክ ሰራተኛ ቋሚ ቅጥር የሚሆነው በሰጠው አገልግሎትና ባበረከተው የማስተማር እና/ወይም የምርምር ምሁራዊ አስተዋጽኦ ወይም ባስመዘገበው የተቋም መሪነት ብቃት ላይ ተመስርቶ ይሆናል፡፡
(የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁ. 650/2001)
የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 ተፈጻሚነቱ በቋሚ የመንግስት ሰራተኖች ላይ ብቻ እንደመሆኑ (አንቀጽ 2(1) እና 3(1) የአካዳሚክ ሰራተኛ ቋሚ ቅጥር እስኪሆን ድረስ የጡረታ መብት የለውም ማለት ነው፡፡

• “የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት፣ ማንኛውም አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም እንዲከፋፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን በዚህ አዋጅ ተሰጥቶታል፡፡”
(የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁ. 691/2003)

Exit mobile version