Articles

ወደ ስራ በመመለስ ፋንታ ካሳ ከፍሎ ማሰናበት፡ የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ

ወደ ስራ በመመለስ ፋንታ ካሳ ከፍሎ ማሰናበት፡ የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ

1.  መግቢያ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(3) እንደተደነገገው ከህግ ውጭ የስራ ውሉ የተቋረጠበት ሰራተኛ ወደ ስራ የመመለስ ጥያቄ በግልጽ ቢያቀርብም ጉዳዩን የሚያየው የስራ ክርክሮችን የሚወስነው አካል ጥያቄውን ባለመቀበል ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት ማዘዝ ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ከስራ ግንኙነቱ ጠባይ የተነሳ የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል ከፍተኛ ችግር ያስከትላል ብሎ ከታመነ ነው፡፡ ትዕዛዙ ዋናው ክርክር በሚታይበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአፈጻጸም ወቅትም ሊሰጥ ይችላል፡፡

ለመሆኑ ይህን መሰሉ ትዕዛዝ ለመስጠት አሳማኝ የሆኑት ሁኔታዎች ምንድናቸው? በሰበር ችሎት በኩል ያለው አቋምስ ምን ይመስላል? እነዚህን ጥያቄዎች የሰበር ውሳኔዎችን መሰረት በማደረግ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

2.  መለኪያው

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(3) ድንጋጌ ሊተረጎም የሚገባው “በአንድ በኩል የሰራተኛውን የስራ ዋስትና በሌላ በኩል ደግሞ የኢንዱስትሪን ሰላም በማመዛዘን ሊሆን ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ሰራተኛው ወደ ስራ መመለሱ የአሰሪውን ስራ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ የሚችል መሆኑ ካልተረጋገጠ በቀር ሰራተኛው በሆነው ባልሆነው ከስራ እንዲሰናበት ማድረጉ ተገቢ አይሆንም” (አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል እና አቶ ዘላለም መንግስቱ ሰ/መ/ቁ 55189 ሰኔ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9)

ሰበር ችሎት በሌላ ውሳኔው (የአብጃታ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማህበር እና ወ/ሮ ማርታ አበበ ሰ/መ/ቁ. 82336 ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 14) ላይ እንዳመለከተው የድንጋጌው መንፈስ ከአሰሪና ሰራተኛ ህግ አጠቃላይ ዓላማና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ 42 ስር ከተቀመጠው ድንጋጌ አንጻር ተዳምሮ ሲታይ እንደሚያስገነዝበው አንቀጽ 43(3) ተግባራዊ ሲደረግ የስራ ዋስትና ዋጋ በማያጣበት አግባብ ሊከናወን ይገባዋል፡፡

መለኪያውን ከማስቀመጥ ባሻገር የስራ ክርክሮችን የሚወስነው አካል ድንጋጌውን ተፈጻሚ ሲያደርግ የስራ ግንኙነቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃል ብሎ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ ባለፈ የስራ ግንኙነቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ (የጎሽና እርግብ መለስተኛና አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር እና አቶ ተሰማ ኃይሉ ሰ/መ/ቁ. 49931 ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9) በችሎቱ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው “ያለ በቂ ማስረጃና ምክንያት አሰሪው የስራ ግንኙነቱ ችግር ላይ ሊወድቅ ይችላል ብሎ ስለተከራከረ ብቻ ድንጋጌውን ተግባራዊ ማድረግ የስራ ዋስትናን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል፡፡”

3.  ማሰናበት ስለሚቻልባቸውና ስለማይልባቸው ሁኔታዎች

አንድን ሰራተኛ ወደስራ ከመመለስ ይልቅ ካሳ ከፍሎ ለማሰናበት በዋነኛነት ምላሽ የሚፈልገው ጥያቄ በምክንያትነት የተሰጠው ሁኔታ የስራ ግንኙነቱን ከፍተኛ ችግር ውሰጥ የሚጥል መሆኑና ያለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደየጉዳዩና እንደየሁኔታው የሚታይ እንጂ ነባራዊ የሆነ ወጥ መስፈርት ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ከግምት መግባት ያለባቸው ነጥቦችና ሊመዘኑ ስለሚገባቸው ተነጻጻሪ የአሰሪና ሰራተኛ ጥቅሞች በተመለከተ የሰበር ችሎት ለስር ፍርደ ቤቶች ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የሰበርን አቋም በግልጽ ለመረዳት ማሰናበት ስለሚቻልባቸውና ስለማይቻልባቸው ሁኔታዎች በተመለከተ በችሎቱ የተሰጡ ውሳኔዎችን መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡

ጠቅለል ባለ አነጋገር ይህንን ነጥብ አስመልክቶ ለሰበር ችሎት ከቀረቡ ጉዳዮች ለመረዳት እንደሚቻለው ተቀራራቢነት ባለው መልኩ ተፈርጀው ሊቀመጡ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዚሁ መሰረት ሰራተኛው ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ሊያሰናብቱ በሚችሉ ምክንያቶች (አንቀጽ 27) ከስራ ተባሮ አሰሪው ማስረዳት ባለመቻሉ የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ-ውጭ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ካሳ ከፍሎ ማሰናበት ከሞላ ጎደል ተቀባይነት አለው፡፡ ከዚህ በተቀራኒ ለስራ ውሉ መቋረጥ በአሰሪው የተሰጠው ምክንት ከህመምና ከብቃት ማነስ (አንቀጽ 28) ጋር በተያያዘ ሆኖ የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ ውጭ ሆኖ ሲገኝ ሰራተኛውን ካሳ ተከፍሎት ማሰናበት አግባብነት የለውም፡፡

3.1.   ማሰናበት ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች

3.1.1.የአሰሪ የንብረት ደህንነት

አብዛኛዎቹ ወደ ስራ በመመለስ ፈንታ ሰራተኛው ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት የተፈቀደባቸው ሁኔታዎች ሰራተኛው በጥፋት ላይ በተመሰረተ ከስራ ተሰናብቶ ስንብቱ ከህግ ውጭ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡

በሰላም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል እና አቶ ከበደ ሰይፉ (ሰ/መ/ቁ. 37454 ታህሳስ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ቅጽ 8) መካከል በሰበር በታየ ክርክር ተጠሪ ከስራ የተሰናበቱት የዘብ ስራቸውን ሲያከናውኑ የቅርብ አለቃቸውን ትዕዛዝ ባለመቀበላቸው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ በቅርብ አለቃቸው ላይ ዝተዋል በሚል ሲሆን ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ ያየው የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ከሚያሳዩ የጽሁፍ ማስረጃዎች በስተቀር ተጠሪ አምባጓሮ ስለመፍጠራቸው ማስረጃ አልቀረበም በሚል የስራ ውሉ የተቋረጠው ከህግ ውጭ ነው የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም ፍርድ ቤቱ መልስ ሰጭ ወደ ስራ ለመመለስ ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ካሳና የተለያዩ ክፍያዎች ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በውሳኔው ላይ ሁለቱም ወገኖች ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን በአመልካች የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ አመልካች ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ፍርድ ቤቱ መልስ ሰጭ የስምንት ወር ደመወዝ ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም አመልካች በስንብቱ ህጋዊነትና በፌ/ከ/ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ የሰበር አቤቱታ አቅርቦ ችሎቱ ስንብቱ ከህግ ውጭ ነው በማለት የተሰጠውን ውሳኔ ሳይነካ ተጠሪ ወደ ስራ ይመለሱ በማለት በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

ሰበር በውሳኔው ትኩረት ሰጥቶ ያየው የተጠሪ የስራ ባህሪና የአመልካች ድርጅት የንብረት ደህንነት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት “የተጠሪ የስራ ባህሪ የአመልካች ድርጅት ጠቅላላ ንብረት ፀጥታና ደህንነት መጠበቅ ከመሆኑ አንጻር ይህም በአሰሪውና በሰራተኛው መካከል የሚጠይቀውን ከፍተኛ የሆነ መተማመን የሚያሻክረውና ግንኙነቱ ቢቀጥል በአመልካች ድርጅት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳትና ችግር ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ” የሚል ምክንያት በመስጠት የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮታል፡፡

3.1.2.እምነት የሚጠይቅ ስራ

በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት የሰራተኛው ታማኝነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 13 የተመለከቱት የሰራተኞች ግዴታዎች ውጤታም በሆኑ መልኩ ተግባራዊ የሚሆኑት ሰራተኛው ለስራውና ለአሰሪው ታማኝ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ስለሆነም ሰራተኛው የተመደደበት ማንኛውም የስራ መደብ በባህርዩ እምነት የሚጣልበት ስራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ የስራ ዘርፎች ከመደበኛው በተለየ ልዩ እምነትን ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ ከገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ስራዎች፤ ከአሰሪው ድርጅት መረጃ አያያዝ ጋር የተገናኙ ስራዎች እንዲሁም ከደርጅቱ የፍርድ ቤት ጉዳዩች ጋር የተያያዙ ስራዎች ከፍተኛ እምነትን ይጠይቃሉ፡፡ ስለሆነም በአንድ ልዩ እምነት በሚጠይቅ ስራ ላይ የተመደበ ሰራተኛ ስንብቱ ከህግ-ውጭ ቢሆንም ወደ ስራ ተመልሶ የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ስለመሆኑ መረዳት አይከብድም፡፡ ያም ሆኖ እምነት በሚጠይቅ ስራ ላይ ሁል ጊዜ ሰራተኛውን ካሳ ተከፍሎት ማሰናበት አግባብነት ያለው አይደለም፡፡ ስራው እምነት የሚጠይቅ መሆኑ ፍርድ ቤቱ እንደ አንድ ነጥብ ግምት ውስጥ ከማስገባት ባለፈ እንደ ወሳኝ ነጥብ ሊወስደው አይገባም፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና አቶ ጌትነት መኮንን (ሰ/መ/ቁ. 64079 ግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 11) መካከል በሰበር በታየ ክርክር ተጠሪ የመብራት ቢል ሰብሳቢ ሆኖ ሲሰራ ገንዘብ ለግል ጥቅሙ አውሏል በሚል የኦዲተር ሪፖርት ቀርቦበት በዚሀ ምክንያት ከስራ በመባረሩ የስራ ውሌ ከህግ ውጭ ተቋርጧል በሚል ወደ ስራ እንዲመለስ እንዲወሰንለት ክስ አቅርቧል፡፡ የስራ ውሌ ከህግ ውጭ ተቋርጧል በማለት ለክሱ መሰረት ያደረገውም አመልካች ጥፋት መፈጸሙን ባወቀ በሰላሳ ቀናት ውስጥ የስንብት እርምጃ አልወሰደም በሚል ነው፡፡

ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም ተጠሪ ገንዘብ ማጉደሉን በተመለከተ በዋናው ፍሬ ጉዳይ ላይ ጭብጥ ሳይዝ በ30 ቀናት ውስጥ የስራ ውሉ አለመቋረጡን ካረጋገጠ በኋላ ተጠሪ የስድስት ወር ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔው ቅር በመሰኘት አመልካች ለጅማ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ሰርዞታል፡፡

በስራ ውሉ መቋረጥና ተጠሪ ካሳ ተክፍሎት እንዲሰናበት በአመልካች በአማራጭ በቀረበው ጥያቄ ላይ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎት የመጀመሪያውን ጥያቄ ውደቅ በማድረግ በአማራጭ የቀረበውን ጥያቄነት መርምሯል፡፡ ችሎቱም ተጠሪ ሲሰራበት የነበረው የስራ መደብ ከፍተኛ እምነት የሚጠይቅ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት በዚህ ሁኔታ ተጠሪ ወደ ስራ ቢመለስ በአመልካችና ተጠሪ መካከል የመተማመን መንፈስና የመልካም የስራ ግኑኝነት ይኖራቸዋል ብሎ መደምደም እንደማይቻል በመግለጽ የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ካሳ ተክፍሎት እንዲሰናበት በአመልካች በአማራጭ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት እንደሆነ በማተት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በማሻሻል ተጠሪ ካሳ ተክፍሎት እንዲሰናበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ምንም እንኳን በውሳኔው ላይ በሰበር በዋነኛነት የተሰጠው ምክንያት የተጠሪ የስራ መደብ ከፍተኛ እምነት የሚጠይቅ መሆኑ ቢሆንም ገንዘብ ስለመጉደሉ የኦዲተር ሪፖርት ቀርቦ ስንብቱ በስነ-ስርዓት ቅድመ-ሁኔታ አለመሟላት (ስንብቱ በሰላሳ ቀናት ውስጥ አለመፈጸሙ) ምክንያት ከህግ ውጭ መሆኑ ችሎቱ ለደረሰብት ድምዳሜ በውሰጠ ታዋቂነት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ይህንን የሰበር ውሳኔ መሰረት በማድረግ ገንዘብ አጉድሏል የተባለና ስንብቱ ከህግ ውጭ የሆነ ሰራተኛ ሁሉ ካሳ ተከፍሎት መሰናበት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ አይሆንም፡፡

3.2.   ማሰናበት ስለማይልባቸው ሁኔታዎች

3.2.1. የብቃት ማነስ

ግልጽ የሆነ የስራ ብቃት መቀነስ የስራ ውልን በማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ስለመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 28(1)(ሀ) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ መልኩ ሰራተኛውን ለማሰናበት ግልጽ በሆነ የአፈጻጸም መመዘኛ ሰራተኛው ተገምግሞ ስራው የሚጠይቀውን የሰራ ብቃት የሌለው ስለመሆኑ በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ አሰሪው በቂ ማስረጃ ሳያቀርብ በስራ ብቃት ማነስ በሚል የስራ ውሉ መቋረጡ ከህግ ውጭ በሚሆንበት ጊዜ ሰራተኛው ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት የሚቀርብ ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ (የጎሽና እርግብ መለስተኛና አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር እና አቶ ተሰማ ኃይሉ ሰ/መ/ቁ. 49931 ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9) ሰበር በዚህ መዘገብ ላይ በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው የስራ ግንኙነቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ሰራተኛው ካሳ ተከፍሎት ሊሰናበት አይገባም፡፡

3.2.2. የጤና መታወክ እና የአካል ጉዳት

የጤና መታወክና የአካል ጉዳት ሌላው የስራ ውልን በማስጠንቀቂያ ሊያቋርጡ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ (የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 28(1)(ለ) ይሁን እንጂ ሰራተኛውን በዚህ ምክንያት ለማሰናበት የጤና መታወኩ ወይም የአካል ጉዳቱ ሰራተኛው በስራ ውሉ የተጣለበትን ግዴታ ከመፈጸም ለዘለቄታው የሚገድበው ደረጃ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡ ጊዜያዊ ወይም ከፊል የጤና መታወክ ወይም የአካል ጉዳት በሚኖርበት ጊዜ አሰሪው ሰራተኛው በሚመጥነው ቦታ ላይ መድቦ የማሰራት ግዴታ አለበት፡፡

ዘለቄታዊ ውጤት ሳይኖረው ሰራተኛን በጤና ችግር ወይም በአካል ጉዳት ምክንያት ማሰናበት ከህግ ውጭ ከመሆኑም በላይ ሰራተኛው ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት የሚቀርብ ጥያቄም ተቀባይነት የለውም፡፡ (የአብጃታ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማህበር እና ወ/ሮ ማርታ አበበ ሰ/መ/ቁ. 82336 ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 14)

4.  በአፈጻጸም ውቅት ስለሚነሱ ችግሮች

4.1.   በስንብት ፋንታ ካሳ ተከፍሎ መሰናበት የሰራተኛው ምርጫ ስለመሆኑ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 43(3) ከህግ ውጭ የስራ ውሉ የተቋረጠበት ሰራተኛ ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት ትዕዛዝ ለመስጠት እንደየጉዳዩ ደረጃ ሁለት የተለያዩ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ በዋናው የክርክር መዝገብ ላይ ጥያቄው በፍርድ ቤቱ አነሳሽነት አሊያም በአሰሪው አመልካችነት የተነሳ ከሆነ የስራ ግንኙነቱ ቢቀጥል ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳይ አሳማኝ ምክንያት ሊኖር ይገባል፡፡ በአንጻሩ ጥያቄው በሰራተኛው በራሱ የተነሳ በሚሆንበት ጊዜ ሰራተኛው የሚጠይቀውን ዳኝነት መርጦ መጠየቅ የሚችል እንደመሆኑ ብሎም ዳኝነት ባልቀረበበት ጉዳይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ሊሰጥ ስለማይችል ሰራተኛው እንደምርጫው ሊስተናገድ ይገባል፡፡ ስለሆነም የስራ ውሌ ከህግ ውጭ ስለተቋረጠ ካሳና ሌሎች ክፍያዎች ተከፍለውኝ ልሰናበት በማለት ሰራተኛው ዳኝነት የጠየቀ እንደሆነ ወደ ስራ መመለስ ጭብጥ ሊሆን አይችልም፡፡

ጥያቄው የተነሳው ፍርድ ከተሰጠ በኋላ በአፈጻጸም ወቅት ከሆነስ? አሁንም ምርጫው የሰራተኛው ነው? የሚለው ጥያቄ ከህጉ አነጋገገር አንጻር ምላሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ምክንያቱም አንቀጽ 43(3) ለሰራተኛው ያልተገበደ የመምረጥ ነጻነት አይሰጥም፡፡ በዚህ ድንጋጌ ላይ እንደተመለከተው አንድ ሰራተኛ ወደስራው እንዲመለስ ከተፈረደለት በኋላ ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆን ቢቀር የሥራ ክርክሮችን የሚወስነው አካል የስራውን ጠባይና ሌሎችንም ሁኔታዎች በማመዛዘን ለሰራተኛው ሙሉ ካሳ ወይም ለደረሰበት መጉላላት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ ተከፍሎት ከስራ እንዲሰናበት ሊወስን ይችላል፡፡ ህጉ የስራው ጠባይና ሌሎችም ሁኔታዎች መመዘን እንዳለባቸው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ይህ ሚዛን የሚያገለግለው ካሳ ተከፍሎኝ ልሰናበት በሚል የቀረበውን ጥያቄ ለመቀበልና ላለመቀበል ይሁን የካሳ መጠኑን ለመወሰን ግልጽ አይደለም፡፡

በአቶ ደሬሳ ኮቱ እና የአምቦ ገሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየን (ሰ/መ/ቁ. 53064 ግንቦት 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9) መካከል በሰበር በታየ ክርክር የሰበር ችሎቱ ከውሳኔ በኋላ ካሳ ተከፍሎ መሰናበት የሰራተኛው ምርጫ ስለመሆኑ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ስለሆነም ከህግ-ውጭ የስራ ውሉ የተቋረጠበት ሰራተኛ ከፍርድ በኋላ ወደስራ ለመመለስ ካልፈለገ ህጉ በምትክነት የሰጠው መብት እንደመሆኑ ምርጫውም የሰራተኛው ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ አመልካች የስራ ውላቸው ከህግ ውጭ በመቋረጡ ከልዩ ልዩ ክፍያዎች ጋር ወደስራ እንዲመለሱ ውሳኔ ተሰጥቷቸው በአፈጻጸም ወቅት ግን ወደ ስራ ለመመለስ እንደማይችሉ በመግለጽ ካሳ ተከፍሏቸው እንዲሰናበቱ አቤቱታ አቅርበው አፈጻጸሙ የቀረበለት ፍርድ ቤት አመልካች ካሳ እንዲከፈላቸው የተወሰነ ነገር የለም በማለት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ በትዕዛዙ ቅር በመሰኘት በየደረጃው ለሚገኙ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትና የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመጨረሻም መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ያቀረቡት አቤቱታ በሰበር ሰሚ ችሎት ተቀባይነት አግኝቶ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሯል፡፡ በፍርዱ ሐተታ ላይ እንደተመለከተው ከፍርድ በኋላ ካሳ ተክፍሎኝ ልሰናበት በሚል የሚቀርብን ጥያቄ ማስተናገድ ያለበት መጀመሪያ ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት ሳይሆን አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ከሁለቱ አንዱን መምረጥም የሰራተኛው መብት እንደመሆኑ ፍርድ ቤቱ ካሳን አስመልክቶ የተሰጠ ውሳኔ የለም በሚል ጥያውን ውድቅ ሊያደርገው አይችልም፡፡

4.2.   ውዝፍ ደመወዝና ሌሎች ክፍያዎችን መውሰድ መብቱን ቀሪ የሚያደርገው ስለመሆኑ

ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለስ ውሳኔ ያገኘ ሰራተኛ በአፈጻጸም ወቅት ካሳ ተከፍሎት ለመሰናበት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የሚኖረው ሰራተኛው በፍርዱ መሰረት በከፊል ያልተፈጸመለት ከሆነ ነው፡፡ (አበባ ትራንስፖርት ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና ዓለምሰገድ ኃይሉ ሰ/መ/ቁ. 38255 ታህሳስ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ቅጽ 8) በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠሪው በስር ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ የአራት ወራት ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለስ ተወስኖለታል፡፡ አመልካችም በፍርዱ መሰረት ወጪና ኪሳራን ጨምሮ የአራት ወር ደመወዝ ለተጠሪ የከፈለ ሲሆን ወደ ስራ እንዲመለስም በደብዳቤ አሳውቆት ሂደቱ በርክክብ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ተጠሪ ክፍያውን ከወሰደ በኋላ ወደ ስራ መመለስ እንደማይፈልግ በመግለጽ ካሳ ተከፍሎት እንዲሰናበት አፈጻጸሙን ለያዘው ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ተጠሪ ወደ ስራ መመለስ እንዳልፈለጉ በመቁጠር መዝገቡን ዘግቶታል፡፡ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ተጠሪ ይግባኝ አቅርበው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ተጠሪ ወደ ስራ መመለስ አልፈለጉም በሚል በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ በመሻር ውዝፍ ደመወዛቸውን ይዘው ወደ ስራ እንዲመለሱ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም አመልካች ባቀረበው የሰበር አቤቱታ ጉዳዩን የመረመረው የሰበር ችሎት ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 43(3) ከተቀመጠው ልዩነት እንዳለው በሐተታው ላይ ካሰፈረ በኋላ የድንጋጌውን ተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ የሚከተለውን ብሏል፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 43(3) ድንጋጌ ላይ “የተቀመጠው መብት ተግባራዊ የሚሆነው ተጠሪው በፍርዱ መሰረት የተወሰነለትን ውዝፍ ደመወዝና ሌሎቸንም ክፍያዎች ሳይወስድ ቢሆን ኖሮ ነው፡፡”

4.3.   በአፈጻጸም ወቅት ሊከፈሉ ስለሚችሉ ክፍያዎች

በአፈጻጸም ወቅት ወደ ስራ ለመመለስ የማይፈልግ ሰራተኛ ሊከፈለው የሚችለው ክፍያ ሙሉ ካሳ ወይም ለደረሰበት መጉላላት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 43(3) ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከስራ ውል ከህግ ውጭ መቋረጥ የሚነጩ ክፍያዎች አፈጻጸምን የተገደበ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ከህግ ውጭ የስራ ውሉ የተቋረጠበት ሰራተኛ በዋናው ክስ ላይ ወደ ስራ ለመመለስ ባይፈልግና በዚህ መልኩ በግልጽ ዳኝነት ከጠየቀ ሊያገኝ የሚችለው ካሳ ብቻ ሳይሆን የስንብት ክፍያ ጭምር ነው፡፡ ካሳና የስንብት ክፍያ ከስራ ውሉ ከህግ ውጭ መቋረጥ በቀጥታ የሚመነጩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከስራ ውሉ ከህግ ውጭ መቋረጥ በቀጥታ ባይመነጭም ያልወሰደው የዓመት ፍቃድ ካለውም የስራ ውል ሲቋረጥ የሚቀርብ ጥያቄ እንደመሆኑ አሰሪው የዓመት ፍቃድ መውሰዱን በማስረጃ ካላረጋገጠ በአዋጀ መሰረት የሚገባው የዓመት ፍቃድ ያገኛል፡፡ የፕሮፊደንት ፈንድም እንዲሁ የስራ ውል ሳይቋረጥ ሊጠየቅ አይችልም፡፡

ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ ለመመለስ ጥያቄ የሚያቀርብ ሰራተኛ የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ ውጭ ሆኖ ሲገኝ የስንብት ክፍያ፤ የፕሮፊደንት ፈንድና የዓመት ፍቃድ በተመለከተ ውሳኔ አያርፍባቸውም፡፡ ስለሆነም ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለስ የተወሰነለት ሰራተኛ በአፈጻጸም ወቅት ወደ ስራ መመለስ ባይፈልግ ከካሳ በተጨማሪ የስንብት ክፍያ፤ የፕሮፊደንት ፈንድና የዓመት ፍቃድ ያገኛል? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋል፡፡

ለዚህ ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ምላሽ የተሰጠው በወ/ት ትዕግስት ንጉሴ እና ኤስ.ኦ.ኤስ ኢንፋንት ኢትዮጵያ (ሰ/መ/ቁ. 42361 ጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9) መካከል በነበረው ክርክር በሰበር የተሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ በአፈጸጻም ወቅት ተጠይቀው ሊከፈሉ ስለሚችሉና ስለማይችሉ ክፍያዎች በተመለከተ በግልጽ ተለይቶ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በተመሳሳይ የክፍያ ጥያቄዎች ላይ የሰበር ችሎት አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ በክርክሩ ላይ አመልካች በስር ፍርድ ቤት የፍርድ ባለመብት የነበረች ሲሆን የስራ ውሏ ከህግ ውጭ ስለተቋረጠ ወደ ስራ እንድትመለስ በሚል ተወስኖላት በአፈጻጸም ለህገ-ወጥ ስንብት የሚከፈሉ ክፍያዎችና የፕሮፊደንት ፈንድ ተከፍሎኝ ልሰናበት በማለት አቤቱታ አቅርባ ፍርድ ቤቱም የካሳ፤ የስንብትና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ እንዲከፈላት ትዕዛዝ ሰጥቶ ፕሮፊደንት ፈንድን አስመልክቶ የቀረበውን ጥያቄ ግን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት የከፍተኛው ፍርድ ቤትም ይግባኙን አልተቀበለውም፡፡

በመጨረሻም አመልካች የሰበር አቤቱታ አቅርባ የሰበር ችሎቱም ጥያቄውን ባለመቀበል የስር ፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ አጽንቶታል፡፡ የአፈጻጸም አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤት የአመልካችን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው የፕሮፊደንት ፈንድ ውሳኔ ያላረፈበት በመሆኑ በአፈጻጸም ሊጠየቅ አይችልም በሚል ነው፡፡ የሰበር ችሎትም የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 371ን በመጥቀስ ውሳኔ ያላረፈበት ነገር በአፈጻጸም ሊጠየቅ እንደማይችል በሐተታው ላይ አስፍሮታል፡፡ ይሁን እንጂ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 43(3) አንጻር ውሳኔ ባላረፈበት ጉዳይ በአፈጻጸም ሊጠየቅ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

ችሎቱ እንዳለው “በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43(3) ስር የተመለከተው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ በግልጽ ዳኝነት ተጠይቆበት ውሳኔ ሳይሰጥ ከተጠየቁት ዳኝነቶች መካከል ወደ ስራ የመመለስ ጥያቄ ላይ ብቻ ውሳኔ ከተሰጠ እና ሰራተኛው ወደ ስራ መመለስ ሳይፈልግ ሲቀር ቀድሞ ዳኝነት በጠየቀባቸው ነገር ግን ውሳኔ ባላረፈባቸው ነጥቦች ላይ ዳኝነት ሊጠየቅ እንደሚችል ያስረዳል፡፡”

እዚህ ላይ ከአጻጻፍ ስህተት ይሁን ከሌላ አገላለጹ በከፊል ግልጽ ባይሆንም (ቀድሞ ዳኝነት በጠየቀባቸው ነገር ግን ውሳኔ ባላረፈባቸው በሚል የተቀመጠው ቀድሞ ዳኝነት ባልጠየቀባቸው እንዲሁም ውሳኔ ባላረፈባቸው በሚል መስተካከል አለበት) ፍሬ ሓሳቡን ለመረዳት ግን አይከብድም፡፡

የሰበር ችሎት የፕሮፊደንት ፈንድ ጥያቄውን ያልተቀበለው በደፈናው እንደ ስር ፍርድ ቤት አገላለጽ ውሳኔ ያላረፈበት በመሆኑ ሳይሆን ከህገ-ወጥ ስንብት በቀጥታ አይመነጭም በሚል ነው፡፡ ለዚህም የተሰጠው ምክንያት የፕሮፊደንት ፈንድ ጥያቄው በተጠሪ በኩል ክርክር የቀረበበት ከመሆኑም በላይ በአሰሪና ሰራተኛ ህግ የይርጋ ድንጋጌዎች ሳይሆን በፍ/ህ/ቁ. 1845 መሰረት በ10 ዓመት በይርጋ የሚታገድ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄው በአፈጻጸም ወቅት የሚቀርብ ሳይሆን ራሱን የቻለ መዝገብ ተከፍቶለት ክርክር ተደርጎበት ውሳኔ ማግኘት አለበት፡፡

3 replies »

  1. በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 43(3) ከተቀመጠው ልዩነት እንዳለው በሐተታው ላይ ካሰፈረ በኋላ የድንጋጌውን ተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ የሚከተለውን ብሏል፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 43(3) ድንጋጌ ላይ….other than editing works such as mentioned as an example the article was so marvelous. Because there are so many problems in interpreting article 43 of the labour law in courts and there is also a problem of understanding this article among legal scholars. In a nut shell it was a wonderful work.

  2. dear sir, thank you so much for your wonderful explanation. but i have one more question, may be i don’t understand it…. let us say, there is a responsible person in a position which is leading to corruption. but that person is not involved in that corruption, but others are using his/her name. which means, there is a working procedure posted in the internet to those guests what to fullfill before they are appearing to the department. now, some of the employees are cheating them by saying,” they don’t process it even if you bring all the necessary documents, so that bring this much money and i shall help you..blabla…bla….” but that person in that position doesn’t know this, he/she sees what they brought to start the process. if they bring all the necessary documents, they will get what they have to get. if not, thier request will be rejected. now, what should the person in that position do if he/she is accused without his/ her problem? what does the law says about it? what is the protection of the law? i thank you so much for your positive guidance and answers in advance. big love for you. AZEB

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.