Site icon Ethiopian Legal Brief

በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ–የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ

በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ–የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ
1. መግቢያ

በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ዋነኛ ከሚባሉት የአሰሪ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ከስራው ጋር በተያያዘ የሰራተኛውን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅና ከአደጋ ለመከላከል የሚያስፈልጉትን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ ይገኝበታል፡፡ ግዴታው በአዋጁ አንቀጽ 12(4) ላይ በጥቅሉ የተቀመጠ ሲሆን በአንቀጽ 92 ላይ ደግሞ ግዴታዎቹ በዝርዝር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ከሙያ ደህንነት፤ ጤንነትና የስራ አካባቢ ጋር በተያያዘ ግዴታ የተጣለው በአሰሪው ላይ ብቻ ሳይሆን በሰራተኛውም ላይ ጭምር ነው፡፡ (አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 13(4) (5) እና አንቀጽ 93)
ሰራተኛው ሆነ አሰሪው በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ ቢወጡም ያልተጠበቀ አደጋ መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በስራ ላይ በሚደርስ አደጋ ሰራተኛው ጉዳት ሲደርስበት የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ እንደ ጉዳቱ መጠን እንዲካስ ከሞተም በስሩ የነበሩ ጥገኞች ክፍያ እንዲከፈላቸው በአሰሪው ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡
ህጉ በፍርድ ቤቶች ተፈጻሚ ሲደረግ በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ ትርጉምና የተፈጻሚነቱ ወሰን፤ የአሰሪው ኃላፊነት፤ የአካል ጉዳት ምንነትና መጠን፤ የጉዳት መጠን ደረጃ እና የካሳ ስሌት በተመለከተ የህግ ትርጉም የሚሹ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ይህ ዳሰሳም የሰበር ችሎት በስራ ላይ የሚደርስ አደጋን በተመለከተ በምን መልኩ የህግ ትርጉም እንደሰጠ የሚቃኝ ይሆናል፡፡
2. የአሰሪው ኃላፊነት
2.1. በጥፋት ላይ ያልተመሰረተ ኃላፊነት

በህጉ አነጋገር በሰራተኛው ላይ በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ የደረሰበት መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ለአደጋው መድረስ የአሰሪው ጥፋት መኖሩን ማሳየት አስፈላጊ አይደለም፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 96(1) ላይ እንደተመለከተውም አሰሪው ጥፋት ባይኖረውም ሰራተኛው በስራ ላይ ሳለ ለሚደርስበት ጉዳት ኃላፊ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 47807 (ቅጽ 9) እንዳለው የአሰሪው ኃላፊነት በጥፋት ያልተመሰረተ ጥብቅ (strict) ስለሆነ ካሳ ጠያቂው ወገን ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ማሳየት ብቻ እንጂ ከዚህ አልፎ የጉዳት አድራሹን ወይንም የአሰሪውን የአእምሮ ሁኔታ (state of mind) ማስረዳት አይጠበቅበትም፡፡
ይሁን እንጂ አሰሪው ኃላፊ ለመሆን በመጀመሪያ ደረጃ በህጉ ትርጓሜና አነጋገር በስራ ላይ የደረሰ አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ መኖር አለበት፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 68138 ቅ13)

2.2. ከኃላፊነት ነጻ ስለሚያደርጉ ምክንያቶች

በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ የደረሰው በሰራተኛው ጥፋት ከሆነ በተለይም ሰራተኛው በስራው ላይ ሰክሮ ከነበረ እንዲሁም መስከሩን ተከትሎ ስራ እንዳይሰራ ከአሪው ትዕዛዝ ተሰጥቶት ይህንኑ በመተላለፍ አደጋ የደረሰበት እንደሆነ አሰሪው ኃላፊነት የለበትም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 67201 ቅ13)
ሰራተኛው በስራ ላይ አደጋ ደርሶበት የጉዳት መጠኑን በሐኪሞች ቦርድ ከተረጋገጠ በኋላ ተሽሎት ድሮ ሲሰራ የነበረው ስራ መስራት መቀጠሉ አሰሪውን ከኃላፊነት ነጻ አያደርገውም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 43370 ቅ8)
2.3. የአሰሪው ከውል ውጨ ተጠያቂነት

ሰራተኛው በስራ ላይ እያለ ለሚደርስበት ጉዳት የአሰሪው ኃላፊነት በጥፋት ላይ ያልተመሰረተ ስለመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 96(1) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት አሰሪው ጥፋት ባይኖርበትም ሰራተኛ በስራ ላይ ሆኖ ጉዳት እስከደረሰበት ድረስ በአዋጁ መሰረት የመካስ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ሰራተኛው በአሰሪው ጥፋት የተነሳ በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ሲደርስበት አግባብ ባለው ህግ መሰረት ካሳ የመጠየቅ መብቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ የአሰሪው ጥፋት ሲኖር ሰራተኛው መብቱን የሚጠይቅበት አግባብ በአሰሪና ሰራተኛ ህጉ በግልጽ አልተመለከተም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 80343 (ቅ15) አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ እያለ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲከፈለው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 96(1) መሰረት አሰሪውን በጥፋት ላይ ባልተመሰረተ ኃላፊነት ከሶና አስፈርዶ ክፍያ ከተቀበለ በኋላ በዚያው ጉዳት የአሰሪውን ጥፋት መሰረት በማድረግ የጉዳት ካሳ ክፍያ እንዲከፈለው ከውል ውጭ ኃላፊነት መሰረት በተጨማሪ እንዲከፈለው በፍትሐብሔር ችሎት ክስ ማቅረብ ይችላል? የሚለው ጥያቄ በሰበር ችሎት ተመርምሯል፡፡ ይሁን እንጂ በሰበር ችሎት ለጥያቄውም አሉታዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሰበር ችሎት በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ እያለ ለደረሰበት ጉዳት የአሰሪና ሰራተኛ ህጉን መሰረት አድርጎ ክስ አቅርቦ ከተፈረደለትና ካሳ ከተቀበለ በኋላ በድጋሚ ያንኑ ጉዳት በሚመለከት በጥፋት ላይ በተመሰረተ ኃላፊነት የጉዳት ካሳ ክፍያ ከውል ውጪ ባለው ህግ ድንጋጌዎች መሰረት በፍትሐ ብሔር ችሎት ታይቶ እንዲወሰንለት የሚያቀርበው ክስ ተገቢነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ በሌላ አኳኋንና መልክ ይዞ ቢሆንም አስቀድሞ ውሳኔ እንዳገኘ የሚቆጠር ነው፡፡
3. በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ ትርጉም

• በስራ ላይ የደረሰ አደጋ አለ ለማለት ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡ ይኸውም አንደኛ ሰራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ወይም ስራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት ጉዳት የደረሰ ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ የምክንትና ውጤት ግንኙነት (proximate cause and effect relationship) መኖር አለበት፡፡ ስለሆነም ሰራተኛው ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ ቢሆንም በተፈጥሯዊ ምክንያት የሞት አደጋ የደረሰበት እንደሆነ አሰሪው ኃላፊነት የለበትም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 47807 ቅጽ 9)
• በአሰሪው መጓጓዣ አደጋ ሲደርስ አደጋው ከስራ መልስ ወይም ወደ ስራ ሲኬድ መሆን አለበት፡፡ ከስራ ቦታ ውጪ በመሄድ ላይ የደረሰ አደጋ በስራ ላይ የደረሰ አደጋ ባለመሆኑ አሰሪው ኃላፊነት የለበትም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 68138 ቅ13)
• መስሪያ ቤቱ ለሰራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው መጓጓዣ የሚለው የህጉ አነጋገር ሰራተኞች በጋራ የሚጠቀሙበትን ሰርቪስ ብቻ ሳይሆን ለሰራተኛው ለስራ ጉዳይ በግሉ የተሰጠውን መጓጓዣም ይጭምራል፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 61717 ቅ13)
• አሰሪው ድርጅት ለሰራተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ በመደበው መጓጓዣ አደጋ ሲደርስ አደጋው በስራ ላይ እንደደረሰ ተቆጥሮ አሰሪው ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ አሰሪው የመደበው የመጓጓዣ አገልግሎት አደጋው የደረሰበት በአሰሪው ስር ባለ ሌላ ሰራተኛ ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን ከሆነ አሰሪው ለተጎጂው ሰራተኛ የጉዳት ካሳ ኃላፊነት የሌለበት ስለመሆኑ አያሳይም፡፡ ሶስተኛ ወገኖች ለአደጋው ያደረጉት አስተዋጽኦ ለአሰሪው መከላከያ ሊሆን አይችልም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 36194 ቅጽ 8)
4. የአካል ጉዳት ትርጓሜ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 99(1) የአካል ጉዳት ማለት የመስራት ችሎታ መቀነስን ወይም ማጣትን በሚያስከትል ሁኔታ በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደሆነ ፍቺ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ የመስራት ችሎታ መቀነስ የሚለው አገለላጽ ወሰኑ በትክክል አልተመለከተም፡፡ የመስራት ችሎታ መቀነስ ሲባል ሰራተኛው ሲሰራ የነበረውን ስራ የመስራት ችሎታ መቀነስ ነው? ወይስ ሰራተኛው ወደፊትም በሌላ የስራ መስክ ተሰማርቶ ለመስራት ያለውን ችሎታ መቀነስን ያጠቃላል?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሰበር ችሎት የድንጋጌውን የእንግሊዝኛ ቅጂ መሰረት በማድረግ ከመረመረ በኋላ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ በዚሁ መሰረት የመስራት ችሎታ መቀነስ ማለት ሰራተኛው ይሰራ የነበረውን ስራ ለመስራት የሚያስችለውን የተወሰነ ችሎታውን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በአጠቃላይ ወደፊትም ሰራተኛው በሌሎች የስራ መስኮች ተሰማርቶ ሌሎች ስራዎችንም ለመስራት የሚያስችለውን ችሎታ (capacity to work) የሚመለከት ነው፡፡ ስለሆነም በስራ ላይ በሚደርስ አደጋ የደረሰበት ሰራተኛ የጉዳት መጠኑ በሐኪሞች ቦርድ ተረጋግጦ ማስረጃ ከተሰጠው በኋላ ተሽሎት ቀድሞ ሲሰራ የነበረውን ስራ ያለምንም ችግር መስራት ቢቀጥልም ጉዳቱ ወደ ፊት በሌላ የስራ መስክ ተሰማርቶ ለመስራት ያለውን ችሎታ የሚቀንስበት በመሆኑ ከአሰሪው ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 43370 ቅ8)

5. የአካል ጉዳት መጠን ደረጃ

ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ለመባል የጉዳት መጠኑ በሀኪሞች ቦርድ 100% መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ስለሆነም የጉዳት መጠኑ ከ100% በታች ስለመሆኑ ከሐኪሞች ቦርድ ማረጋገጫ ቢቀርብም ጉዳቱ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ተብሎ ሊመደብ ይችላል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 49273 (አመልካች አቶ ደረጀ ውለታው እና ተጠሪ ዋሊያ ሌዘርና ሌዘር ፕሮዳክትስ ኃ/የተ/የግ/ማ) በስር ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት አመልካች በስራ ላይ በደረሰ አደጋ የቀኝ እጃቸው አራት ጣቶችና የግራ እጃቸው ሶስት ጣቶች ተቆርጠዋል፡፡

የጉዳት መጠኑን አስመልክቶ የሐኪሞች ቦርድ የጉዳት መጠኑ 65% መሆኑን የገለጸ ሲሆን ክሱ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ የደረሰው ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት በመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 109(3)(ሀ) መሰረት የአምስት ዓመት ደመወዛቸው ብር 24900 (ሃያ አራት ሺ ዘጠኝ መቶ ብር) እንዲከፈላቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በውሳኔው ቅር በመሰኘት በመልስ ሰጭ የይግባኝ አቤቱታ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሐኪሞች ቦርድ የተለጸውን የጉዳት መጠን መሰረት በማድረግ የጉዳት ካሳው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 109(3)(ለ) መሰላት እንዳለበት በማተት አመልካች የአምስት ዓመት ደመወዛቸው በ65% ተባዝቶ ብር 16185 (አስራ ስድስት ሺ አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ብር) እንዲከፈላቸው የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማሻሻል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በመቀጠልም ስሌቱ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 109(3)(ሀ) ሊሆን እንሚገባውና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን በመግለጽ አመልካች የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መሰረታዊው ጭብጥ የአካል ጉዳት መጠኑ እንደመሆኑ የሰበር ችሎቱ በአመልካች ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ነው ወይስ ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት በሚል ጭብጥ በመመስረት የግራ ቀኙን ክርክር መርምሯል፡፡

የሰበር ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ ለህጉ ማለትም ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት አወሳሰን በተመለከተ በተለምዶ በስር ፍርድ ቤቶች ህጉ ተፈጻሚ ሲደረግ የነበረበትን መንገድ የሚቀይርና ፈር-ቀዳጅ ሊባል የሚችል ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ይኸውም በአብዛኛዎቹ ፍርድ ቤቶች የጉዳት መጠንን ለመወሰን መሰረት ይደረግ የነበረው ከሐኪሞች ቦርድ የሚሰጠውን ማስረጃ ሲሆን ከዚህ አንጻር የሰበር ችሎቱ እንዳለው በሐኪሞች ቦርድ ጉዳት የሚለካው ከአጠቃላይ የሰውነት ሁኔታ ጋር በማነጻጸር እንጂ የደረሰው ጉዳት ከመስራት ችሎታ ጋር ተነጻጽሮ አይደለም፡፡

ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 110(2) አነጋገር ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ ማናቸውም ደመወዝ የሚያስገኝ ስራ ለመስራት የሚከለክለው የማይድን በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው፡፡ ስለሆነም በሐኪሞች ቦርድ ማስረጃ የጉዳት መጠኑን ከ100% የሚያንስ ቢሆንም እንኳን በሰራተኛው ላይ የደረሰው ጉዳት ማናቸውንም ስራ የሚከለክለው ከሆነ የጉዳት መጠኑ ዘላቂ መሉ የአካል ጉዳት ነው፡፡ የአካል ጉዳት ሙሉና ከፊል ተብሎ የሚከፈለው ከመስራት ችሎታ ጋር በማነጻጸር እንጂ ከአጠቃላይ ከሰውነት አካል ጉድለት ጋር ተነጻጽሮ አይደለም፡፡ በዚሁ መሰረት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሽሮ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸንቷል፡፡
6. የጉዳት ካሳ አሰላል
6.1. የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኛ—በጡረታ የተሸፈነና የመድን ዋስትና ያልተገባለት ሲሆን
በመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ በስራ ላይ አደጋ ሲደርስበት ድርጅቱ የመድን ሽፋን ካልገባ የካሳ መጠኑን ለመወሰን ተፈጻሚ የሚሆነው በመንግስት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ላይ የተመለከተው የካሳ መጠን ነው፡፡ ይህ የሰበር ውሳኔ ሲሰጥ ጡረታን በተመለከተ ተፈጻሚነት የነበረው ህግ አዋጅ ቁጥር 345/95 ነው፡፡ በውሳኔው ላይ እንተመለከተው በአዋጁ አንቀጽ 33 መሰረት ጉዳት ለደረሰበት ሰራተኛ የሚከፈለው የካሳ መጠን ሰራተኛው ጉዳት ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈለው የነበረው መደበኛ የወር ደመወዝ 45% በአምስት ዓመት ተባዝቶ የሚገኘው ሂሳብ በሰራተኛው ላይ በደረሰው ጉዳት በመቶኛ ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 43370 ቅጽ 8)
6.1.1. ማስታወሻ

በአሁኑ ወቅት ፀንቶ ያለው የመንግስት ሰራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 ሲሆን የጉዳት ካሳ መጠኑን በተመለከተ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ማሻሻያው ግን የሰራተኛውን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሳይሆን በጣም በሚጎዳ መልኩ የተደረገ ነው፡፡
ይህን ለመረዳት መጀመሪያ የቀድሞውን አዋጅ ቁጥር 345/95 ከአሰሪና ሰራተኛ ህግ ጋር ማነጻጸር ያስፈልጋል፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት ሰራተኛው ከዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ያነሰ ጉዳት ሲደርስበት የሚከፈለው ካሳ የአምስት ዓመት ደመወዙ በደረሰበት ጉዳት በመቶኛ ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው፡፡ ለምሳሌ ከጉዳቱ በፊት አንድ ሺ ብር ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ በግለሰብ ወይም በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ በስራ ላይ በሚደርስ አደጋ 30 ፐርሰንት የአካል ጉዳት ሲደርስበት የሚከፈለው የካሳ መጠን 1000 ሲባዛ በ12 ሲባዛ በአምስት ሲባዛ በ30/100 =18000 ብር ነው፡፡
ተመሳሳይ ደመወዝ ኖሮት ተመሳሳይ የጉዳት መጠን የደረሰበትና የመድን ሽፋን በሌለው የመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ በአዋጅ ቁጥር 345/95 አንቀጽ 33 መሰረት የሚከፈለው የካሳ መጠን ደግሞ 1000 ሲባዛ በ12 ሲባዛ በአምስት ሲባዛ በ45/100 ሲባዛ 30/100 = 8100 ብር ነው፡፡
ከንጽጽሩ እንደምንረዳው በመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ሰራተኛ በግለሰብ ወይም በግል ድርጅት ተቀጥሮ ከሚሰራው ሰራተኛ በ55% ያነሰ ካሳ ያገኛል፡፡ ከላይ በተሰጠው ምሳሌ ላይ የግል ሰራተኛው ብር 18000 ክፍያ ሲያገኝ የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኛው ግን የሚያገኘው ከዚህ እጅጉን ያነሰ ማለትም 8100 ብር ብቻ ነው፡፡
በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ የሚታየው ልዩነት (discrimination) እና የልዩነቱ መስፋት የሚያሳዝንና የህግ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ ግልጽ ቢሆንም አዲሱ የጡረታ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 714/2003 ግን ልዩነቱን እዚህ ግባ የማይባል ከፊል ማሻሻያ ብቻ በማድረግ የቀድሞውን አዋጅ ግድፈት ሳያርመው ቀርቷል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 38(1) ላይ እንደተመለከተው ከአስር በመቶ ያላነሰ ከስራ የመጣ ጉዳት ደርሶበት ስራ ለመስራት የሚችል ከሆነ የጉዳት ዳረጎት በአንድ ጊዜ የሚከፈለው ሲሆን መጠኑም በአንቀጽ 39 ላይ እንደተመለከተው ሰራተኛው ጉዳት ከደረሰበት ወር በፊት ይከፈለው የነበረው የወር ደመወዙ በ47 በመቶ ተባዝቶ የሚገኘው ሂሳብ በ60 ከተባዛ በኋላ እንደገና በደረሰበት ጉዳት በመቶኛ ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው፡፡
ስሌቱን ይበልጥ ለመረዳት ከላይ በተሰጠው ምሳሌ አንጻር እናያለን፡፡ ስለሆነም 30 በመቶ የአካል ጉዳት የደረሰበትና ከአደጋው በፊት ብር 1000 ደመወዝ ሲከፈለው የነበረ የመድን ሽፋን በሌለው የመንግስት የልማት ድርጅት ውሰጥ ተቀጥሮ ሲሰራ የነበረ ሰራተኛ በስራ ላይ አደጋ ሲደርስበት በአዋጅ ቁጥር 714/2003 መሰረት ሊያገኘው የሚችለው ካሳ 1000 ሲባዛ በ47 ፐርሰንት ሲባዛ በ60 እንደገና ሲባዛ በ30 ፐርሰንት = 8460 ብር ነው፡፡
ከቀድሞው አዋጅ ቁጥር 345/95 ጋር ሲተያይ በአዋጅ ቁጥር 714/2003 የተደረገው ማሻሻያ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ በምሳሌው መሰረት ሰላሳ ፐርሰንት የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰራተኛ በአዋጅ ቁጥር 345/95 መሰረት 8100 ብር ካሳ የሚያገኝ ሲሆን በበአዋጅ ቁጥር 714/2003 ደግሞ 8460 ብር ያገኛል፡፡ ልዩነቱ 360 ብር ብቻ ነው፡፡
መሰረታዊው ቁምነ ነገር በማሻሻያው የተደረገው የጭማሪ መጠን አይደለም፡፡ ከመነሻው ያልተጠበቀ አደጋ ደርሶ ለሰራተኛው በሚከፈለው ካሳ ላይ የመንግስትና የግል ብሎ ልዩነት መፍጠር ልዩነት ለመፍጠር ከመፈለግ የተፈጠረ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የሚያሳምን ቀርቶ የሚያከራክር ምክንያት እንኳን ሊቀርብበት የሚችል አይደለም፡፡ ስለሆነም ከቁንጽል ማሻሻያ ባለፈ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ሊደረግበትና ከግል ሰራተኛች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የካሳ መጠን በህግ ሊደነገግ ይገባል፡፡
6.2. የመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኛ—በጡረታ የተሸፈነና የመድን ዋስትና የተገባለት ሲሆን

ጉዳት የደረሰበት የመንግስት ልማት ድርጅት ሰራተኛ በጡረታ የተሸፈነ ሆኖ በአሰሪው የመድን ዋስትና የተገባለት ከሆነ የጉዳት ካሳው የሚወሰነው በመድን ሽፋኑ መሰረት ነው፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 65427 ቅጽ 11) በዚህ ጉዳይ አመልካች ተጠሪን ጨምሮ ሰራተኞቹ ለሚደርስባቸው ጉዳት የመድን ዋስትና ገብቷል፡፡ ተጠሪ ደግሞ በስራ ላይ በሚደርስ አደጋ 7% የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አመልካችም በገባው የመድን ዋስትና መሰረት ለአመልካች ካሳ ከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ ተጠሪ የተከፈለኝ ክፍያ ከደረሰብኝ ጉዳት ያነሰ ነው በሚል በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በአመልካች ላይ ክስ አቅርበው የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክሱን ውድቅ በማድረጉ ተጠሪ ይግባኝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም መዝገቡን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 377/96 109(1) ድንጋጌ መሰረት ለሰራተኛ የሚከፈል የጉዳት ካሳ አሰሪው በገባበት የመድን ዋስትና ተፈጻሚ ይሆናል ተብሎ የተገለጸው የመንግስት ሰራተኞችን የሚመለከት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በ1ኛ መልስ ሰጨ (በአሁን አመልካች) እና 2ኛ መልስ ሰጭ (የኢትዮጵያ መድን ድርጅት መካከል የተደረገው የመድን ሽፋን ውል ህግ ሆኖ የሚገዛው ሁለቱን ተዋዋይ ወገኖች እንጂ ይግባኝ ባይ (የአሁን ተጠሪን) የውሉ ተገዢ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ የሚያስገድድ አይደለም፡፡
ፍርድ ቤቱ ይህን ካለ በኋላ የአሁን አመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/96 109(3)(ለ) መሰረት ቀሪውን ካሳ እንዲከፍል ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ የሰበር አቤቱታ በአመልካች የቀረበለት የሰበር ችሎት ለክርክሩ ተፈጻሚነት ያለው ህግ አዋጅ ቁጥር 377/96 109(3)(ለ) ሳይሆን 109(1) እንደሆነ በመግለጽ የመጀመሪያ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮታል፡፡
ችሎቱ በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 109(1) መሰረት የመንግስት ልማት ድርጅት አሰሪ በሰራተኛው ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ የሚከፍለው በገባበት የመድን ዋስትና ወይም በመንግስት የጡረታ ህግ መሰረት ሲሆን ይህ ሊቀየር የሚችለው አሰሪውና ሰራተኛው በህብረት ስምምነታቸው በተቃራኒ ተስማምተው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሰረት የጡረታ ህግ ተፈጻሚ የሚሆነው የመድን ዋስትና ሽፋን ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡
6.2.1. ማስታወሻ

ምንም እንኳን የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ. 65427 የሰጠው ውሳኔ በአግባቡ ቢሆንም ለውሳኔው መሰረት በሆነው የህግ ድንጋጌ ላይ ያለው ችግር ግን ሳይነሳ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ከላይ እንዳየነው ለሰራተኞቹ የመድን ዋስትና ባልገባ የመንግስት የልማት ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ በስራ ላይ አደጋ ሲደርስበት ተፈጻሚ በሚሆነው የጡረታ ህግ መሰረት የሚያገኘው የጉዳት ካሳ በግለሰብ ወይም በግል ድርጅት ተቀጥሮ ተመሳሳይ የጉዳት ደረጃ ከደረሰበት ሰራተኛ የጉዳት ካሳ ክፍያ እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ ይህ የተጋነነ ልዩነት የመድን ሽፋን በሚኖርበት ጊዜም የሚታይ ነው፡፡ በሰ/መ/ቁ. 65427 አንሶብኛል በሚል ክስ ያቀረቡት ተጠሪ ለክሳቸው መሰረት የሚሆን ህግ ባይኖርም ገዝፎ የሚታይ እውነት ግን አለ፡፡ ይኸውም ተጠሪ በመድን ሽፋኑ መሰረት የተከፈላቸው ብር 7500 (ሰባት ሺ አምስት መቶ ብር) ሲሆን በግለሰብ ወይም በግል ድርጅት ተቀጥረው ተመሳሳይ የጉዳት መጠን ቢደርስባቸው ኖሮ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ካሳው የሚሰላው በአንቀጽ 109(3)(ለ) በመሆኑ ተጨማሪ ብር 8649 ብር (ስምንት ሺ ስድስት መቶ አርባ ዘጠኝ ብር) ያገኙ ነበር፡፡ በመርህ ደረጃ ሲታይ የመድን ሽፋን መኖሩ ለሰራተኛው የበለጠ ዋስትና መሆን ሲገባው አሰሪውን መጥቀሚያ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የልማት ድርጅት ለሰራተኞቹ የመድን ዋስትና ሲገባ አነስተኛው የጉዳት ካሳ መጠኑ በአንቀጽ 109(3)(ለ) የተመለከተው መሆን እንዳለበት በሚደነግግ መልኩ ህጉ መሰረታዊ ለውጥ ሊደረግበት ይገባል፡፡
6.3. የጉዳት ክፍያ—በመንግስት የጡረታ ህግ ላልተሸፈኑ ሰራተኞች

በመንግስት የጡረታ ህግ ላልተሸፈኑ ሰራተኞች የጉዳት ክፍያ አሰላል በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 109(3) ላይ የተመለከተ ሲሆን ድንጋጌውም የህግ ትርጉም በማይፈልጉ መልኩ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የጉዳት ክፍያው የአካል ጉዳት መጠንን መሰረት ያደረገ እንደመሆኑ ጭብጥ ሆኖ ሊነሳ የሚችለው የጉዳት መጠኑን በመወሰን ላይ እንጂ የጉዳት ክፍያ መጠኑን በመወሰን አይደለም፡፡ በመሆኑም በአንቀጽ 109(3)(ሀ) መሰረት የጉዳት መጠኑ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ከሆነ የክፍያ መጠኑ የሰራተኛው የዓመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ነው፡፡ የጉዳት መጠኑ ከዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት በታች ከሆነ ደግሞ ክፍያው በአንቀጽ 109(3)(ሀ) ላይ የተመለከተው ሆኖ ከአካል ጉድለት ደረጃው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ይሆናል፡፡ [አንቀጽ 109(3)(ለ)] በሌላ አነጋገር የክፍያ መጠኑ የሰራተኛው የዓመት ደመወዝ ሲባዛ በአምስት ሲባዝ የአካል ጉዳት በመቶኛ ሲባዛ የሚገኘው መጠን ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ግን የአካል ጉዳት መጠን ከመቶ ፐርሰንት ማነሱ ብቻውን የጉዳት መጠኑ ከዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት መጠን በታች መሆኑን የሚያሳይ አለመሆኑን ነው፡፡ በሰራተኛው ላይ የደረሰው ጉዳት በመቶኛ ሲቀመጥ ከመቶ ፐርሰንት በታች ቢሆንም ጉዳቱ ሰራተኛውን ምንም ዓይነት ስራ እንዳይሰራ የሚያደርገው ከሆነ ሙሉ ዘላቂ የአካል ጉዳት ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 49273 ቅጽ 9 ላይ በሰራተኛው ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት መጠን 65% ቢሆንም ጉዳቱ ሙሉ ዘላቂ የአካል ጉዳት ነው ሲል ሰበር ውሳኔ ሰጥቶ ክፍውም በዚሁ መሰረት ተሰልቷል፡፡ (የበለጠ ለመረዳት ከላይ ስለየአካል ጉዳት መጠን ደረጃሌቀረበውን ዳሰሳ ይመልከቱ)
6.4. የጉዳት ክፍያን በርትዕ ስለሚወሰንበት ሁኔታ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ላይ የጉዳት ካሳ ክፍያ በርትዕ ስለሚወሰንበት ሁኔታ በግልጽ አልተመለከተም፡፡ ይሁን እንጂ በአመልካች የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ግርማ ወዮሳ መካከል በነበረው ክርክር (ሰ/መ/ቁ. 60464 ቅጽ 11) የሰበር ችሎቱ ተጠሪ የሚገባውን የክፍያ መጠን በርትዕ ወስኖታል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ እንደሚከተለው ነው፡፡ ተጠሪ ስራ በመስራት ላይ እያለ ድንጋይ ወድቆበት ሁለት የእግሮቹ ጣቶች በመቆረጣቸው ዘላቂ የአካል ጉዳት ደርሶበታል በሚል ክሱ የቀረበለት የግራር ጃርሶ ወረዳ ፍርድ ቤት ብር 57442.66 (ሃምሳ ሰባት ሺ አራት መቶ አርባ አራት ብር ከ66 ሳንቲም) እንዲከፈለው ውሳኔ ከሰጠ በኋላ አመልካች የይግባኝ አቤቱታ ለኦሮሚያ ዞን ሰሜን ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጉድለት የለበትም በሚል አቤቱታውን ውደቅ አድርጎታል፡፡ በመቀጠልም አመልካች የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል በሚል የሰበር አቤቱታ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ችሎቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡
በመጨረሻም አመልካች ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን በዋናነት ያቀረበው መከራከሪያም ተጠሪ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉድለት የደረሰበት ስለመሆኑ የህክምና ማስረጃው ስለማያስረዳ በዚሁ መልኩ ክፍያ እንዲፈጸም በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው የሚል ነው፡፡
ችሎቱ ጉዳዩን ሲመረምር በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ በተጠሪ ላይ ደረሰ የተባለውን የአካል ጉዳት እና ቀረበ የተባለውን ማስረጃ በተመለከተ የተምታታ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ተጠሪንም በችሎት አስቀርቦ የደረሰበትን ጉዳት በተመለከተ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ ተጠሪ በችሎት ሲታይ ብሎም ስለደረሰበት ጉዳት ሲያስረዳ ጉዳት የደረሰበት የግራር ጃርሶ ወረዳ ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው ተጠሪ የተቆረጠው ሁለት የእግሮቹ ጣቶቹ ሳይሆን የግራ እጁ ሁለት ጣቶች ናቸው፡፡ እግሩም ላይ ስብራት ደርሶበታል፡፡ ከመዝገቡ ጋር የተያያዘው ከሐኪሞች ቦርድ የተሰጠው ማስረጃም ጉዳቱ ተጠሪ የገለጸውን የሚደግፍ ነው፡፡ ሆኖም ቦርዱ የጉዳት መጠኑን በፐርሰንት ከማስቀመጥ ይልቅ ተጠሪ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ድሮ ሲሰራ የነበረውን የአናጺነት ስራ መስራት እንደማያስችለው በመግለጽ ማስረጃ ሰጥቷል፡፡
የሰበር ችሎቱም የአካል ጉዳት መጠኑን በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት መዝገብ ውስጥ ያሉትን ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ በተጠሪ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉደት ሳይሆን ጊዜያዊ የአካል ጉዳት እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፤
የክፍያ መጠኑን በተመለከተም ችሎቱ በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው ክፍያው የሚወሰነው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጀ አንቀጽ 109(3)(ለ) እንደሆነ ካመለከተ በኋላ በዚህ ድንጋጌ ላይ ተመጣጣኝ በሚል የተቀመጠውን ቃል ሰፋ አድርጎ በመተርጎም ተጠሪ በርትዕ 24000 (ሃያ አራት ሺ ብር) እንዲከፈለው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔው ላይ “ሕጉ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም የካሳውን መጠን በርትዕ መሰረት አይቶ መወሰን ስለሚፈቅድ…” የሚል ሐተታ ይገኝበታል፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ በስራ ላይ ለደረሰ አደጋ ክፍያ በርትዕ እንዲወሰን የሚፈቅድ መሆኑ አከራካሪ ቢሆንም የተጠሪ ጉዳይ ሶስት ፍርድ ቤቶች አልፎ ሰበር ደርሶ እንደገና የጉዳት መጠኑ በሐኪሞች ቦርድ እንዲወሰን መዝገቡን ጉዳዩን መጀመሪያ ላየው ፍርድ ቤት መመለሱ ከፍትሕ አንጻር ተገቢነት የሌለው ነው፡፡
7. ስለጥገኞች
7.1. የጥገኞች ትርጉም

• ጥገኞች የሚለው ቃል ከሟች የምግብ፤ የመጠለያ፤ የልብስና ለጤናው አጠባበቅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዲሟላላቸው የሚጠይቁትን ወገኖች የሚመለከት ስለመሆኑ ተንዝበናል፡፡ ስራ ሰርቶ ማስተዳደር የሚችልና ችግረኛ መሆኑ በቅድሚያ ያልተረጋገጠበት ወገን የሟች ሰራተኛ ባል ወይም ሚስት በመሆኑ ብቻ የጉዳት ካሳ የሚያገኝበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከጉዳት ካሳ ዓላማ ጋርም አንድ ላይ ይሄዳል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም የሟች ሰራተኛ ባል ወይም ሚስት መተዳደሪያ የሚሆነው በቂ ሀብት ካለው ጥገኛ ሊባል አይችልም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 36194 ቅጽ 8)
• የህብረት ስምምነቱ በስራ ላይ በሚደርስ የሞት አደጋ ካሳው ለወራሾች ይከፈላል ቢልም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ አንቀጽ 110(1) ከተመለከቱት ጥገኞች ውጪ ከሆኑ የካሳ ክፍያ አያገኙም፡፡ (ሰ/መ/ቁ. 72645 ቅጽ 13)
7.2. ለጥገኞች የሚከፈል ካሳ ስሌት

አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 110 ንኡስ አንቀጽ 3 በመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ህግ ላልተሸፈኑ ሰራተኞች ጥገኞች የሚሰጠው የካሳ መጠን የሰራተኛው የዓመት ደመወዝ በአምስት ተባዝቶ የሚገኘው ክፍያ እንደሆነ የሚደነግግ ሲሆን ክፍያው ለነዚህ ጥገኞች የሚከፋፈልበትን ሁኔታም ለሶስት በመክፈል ድርሻቸውን ይወስናል፡፡ በዚሁ መሰረት ለሟች ሰራተኛ ባል ወይም ሚስት ሃምሳ በመቶ፤ አካለመጠን ላላደረሱ የሟች ልጆች ለእያንዳንዳቸው አስር በመቶ እንዲሁም በሟች ሰራተኛ ድጋፍ ይረዱ ለነበሩ የሟች ወላጆች ለእያንዳንዳቸው አስር በመቶ ይከፈላል፡፡ የሟች ሰራተኛ ወላጆች በህይወት ካሉና ሶስት ልጆች ካሉት እንዲሁም አንደኛው ተጋቢ በህይወት ካለ ለልጆች በጠቅላላው ሰላሳ በመቶ ለሁለቱም ወላጆች በድምሩ ሃያ በመቶ እንዲሁም ለባል/ሚስት ሃምሳ በመቶ ተከፍሎ ጠቅላላ ድምሩ አንድ መቶ ፐርሰንት ስለሚሆን ክፍያውን በመሸንሸን ረገድ ችግር አይገጥምም፡፡ በተጨማሪም በአንቀጽ 110(4) መሰረት የጥገኞች ቁጥር ሲቀንስና ሲጨምርም የክፍፍሉ መጠን መቶ በመቶ እስኪሆን ድረስ ከእያንዳንዱ ጥገኛ ላይ በመጠኑ ይቀነሳል ወይም ለእያንዳንዱ ጥገኛ ድርሻ ክፍፍሉ መቶ በመቶ እስኪሆን ድረስ ይጨምራል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ሟች አንድ ጥገኛ ብቻ ትቶ የሞተ እንደሆነ ክፍፍሉ በምን መልኩ እንደሚፈጸም ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአመልካች የህጻን ዮናታን ነጋ ተሻገር ሞግዚት እና በተጠሪ አቶ አበራ ለገሰ (ሰ/መ/ቁ. 40529 ቅጽ 9) መካከል በነበረው ክርክር የሰበር ችሎት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 110(3) እና 110 (4) ድንጋጌዎች ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ውሳኔ በመስጠት የክፍያ ስሌቱን በተመለከተ ለህጉ ትርጉ ሰጥቷል፡፡
“በስራ አደጋ የሞተ ሰራተኛ ትቶት ያለፈው ጥገኛ አንድ ብቻ በሚሆንበት ጊዜ ሊከፈል የሚገባው የካሳ መጠን የጠቅላላውን አሰር መቶኛ ሳይሆን ሙሉውን መቶ ፐርሰንት ነው፡፡

Exit mobile version