Articles

ሰራተኛው በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ስለሚሰናበትበት ሁኔታ፡ የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ

ሰራተኛው በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ስለሚሰናበትበት ሁኔታ፡ የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ

መግቢያ

የንብረት ትርጉም

የአሰሪው ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት

ጉዳት ማድረስ እና ጉዳት መድረስ

ከባድ ቸልተኝነት

 

መግቢያ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 27(1) አነጋገር ሰራተኛው ከስራ የሚሰናበተው ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ሲያደርስና ጉዳቱም የደረሰው በአሰሪው ንብረት ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባለው ማናቸውም ንብረት ላይ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አራት የጥፋቱ ማቋቋሚያዎች አንድ ላይ ተሟልተው መገኘት እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ ይኸውም፤

 • አንደኛ ጉዳት ደረሰበት የተባለው ነገር “ንብረት” መሆን አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ህጉ ለንብረት የሰጠውን ፍቺ ማሟላት ይኖርበታል፡፡
 • ሁለተኛ ንብረቱ የአሰሪው ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት ሊሆን ይገባል፡፡
 • ሶስተኛ አሰሪው በንብረቱ ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ብሎም በጉዳቱና ጉዳት አደረሰ በተባለው ሠራተኛ መካከል የምክንያትና ውጤት ግንኙነት ስለመኖሩ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት ሲባል ሠራተኛው ማድረግ የሌለበትን በማድረጉ ወይም ማድረግ ያለበትን ባለማድረጉ ምክንያት ጉዳት መከሰቱን ለማመልከት ነው፡፡
 • አራተኛ ሠራተኛው ጉዳቱን ያደረሰው ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

እነዚህን አራት ነጥቦች የሰበር ችሎት ለድንጋጌው ከሰጠው ትርጉምና ተፈጻሚ ካደረገበት መንገድ አንጻር እንደሚከተለው እናያለን፡፡

የንብረት ትርጉም

በአንቀጽ 27(1) ሸ አነጋገር ንብረት ለሚለው ቃል ፍቺ ለመስጠት የሰበር ችሎት በአንዳንድ ውሳኔዎች ላይ በፍትሐ ብሔር ህጉ ላይ የተቀመጠውን የንብረት ትርጓሜ በማጣቀስ እልባት የሰጠ ቢሆንም በሌሎች ውሳኔዎች ግን ለቃሉ ሰፊ ትርጉም በመስጠት የ27(1) ሸ ተፈጻሚነት የተለጠጠ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በሰ/መ/ቁ 17189 (አመልካች የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ንጉሴ ዘለቀ ጥቅምት 17 ቀን 1998 ዓ.ም. ቅጽ 2)[1] በነበረው ክርክር ተጠሪ ከስራ የተሰናበተው በቅርንጫፍ ስራ አስሊያጅነቱ የየዕለቱ ገቢ ተሰብስቦ ባንክ መግባቱ ማረጋገጥ ሲገባው በጊዜው ገንዘብ ያዥ የነበረው ሰራተኛ ባዘጋጀው የገንዘብና የባንክ መዝገብ ላይ በመፈረም ወይም ሳይፈርም በመተው ጉድለት እንዲፈጽም ረድቶታል በሚል ሲሆን ስንብቱን በመቃወም ያቀረበው ክስ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤት ጉድለቱ ሲደርስ ተጠሪ ስራ ላይ አልነበረም በሚል የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ ውጪ ስለሆነ ተጠሪ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለስ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎትም “ጉድለቱ ሲደርስ ተጠሪ ስራ ላይ የነበረ መሆኑ አላከራከረም” በማለት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

ችሎቱ ማስረጃን መሰረት አድርጎ ከደረሰበት ድምዳሜ በተጨማሪ የሥራ ውሉ የተቋረጠበትን ድንጋጌ [አዋጅ ቁጥር 42/85 አንቀጽ 27(1) በ] ይዘት በስፋት መርምሯል፡፡

ችሎቱ ከመረመራቸው ነጥቦች አንዱ “ገንዘብ” የንብረትን ትርጉም ማሟላት ስለመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ በአሰሪው ላይ ደረሰ የተባለው ጉድለት የገንዘብ ጉድለት ነው፡፡ ስለሆነም በ27(1) በ መሰረት የተደረገን የስራ ውል ማቋረጥ ህጋዊነት ለመወሰን ገንዘብ የሚለው ቃል በንብረት ትርጉም ውስጥ መጠቃለል ይኖርበታል፡፡ ይህን አስመልክቶ ችሎቱ ጉዳዩን ከፍትሐ ብሔር ህግ አንቀጽ 1126 እና 1127 ጋር አገናዝቦ በማየት ገንዘብ አንዱ ግዙፍነት ያለው ተንቀሳቃሽ ንብረት እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የተማሪዎችን ውጤት በወቅቱ አለማስገባትና በዚህ የተነሳ አሰሪውን ድርጅት በድጋሚ ፈተና ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ 377/96 አንቀጽ 27(1) ሸ አነጋገር በአሰሪ ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ በመሆኑ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያሰናብት ጥፋት ነው፡፡ (አመልካች አድማስ ኮሌጅ እና ተጠሪ ሰለሞን ሙሉዓለም // 34669 ታህሳስ 2 ቀን 2001 .. ቅጽ 8) የስር ፍርድ ቤቶች የተጠሪ ድርጊት በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 27 ስር የሚወድቅ አይደለም በማለት የስራ ውሉ መቋረጥ ህገ-ወጥ ነው በማለት ውሳኔ ቢሰጡም የሰበር ችሎት ድርጊቱ በአንቀጽ 27(1) ስር እንደሚሸፈን በማተት ሽሯቸዋል፡፡

ችሎቱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በቀዳሚነት በአንቀጽ 27(1) ሸ አነጋገር ንብረት ለሚለው ቃል ፍቺ ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ በሰ/መ/ቁ. 17189 እንዳደረገው በፍትሐ ብሔር ህጉ በንብረት ህግ ላይ የሚገኙትን ድንጋጌዎች ከማጣቀስ ይልቅ የራሱን ፍቺ መስጠትን መርጧል፡፡ ለቃሉ ፍቺውን ከማስቀመጡ በፊትም “ንብረት” ለሚለው ቃል ሁሉንም የሚያስማማ ወጥ ትርጉም ለመስጠት ያለውን ችግር በእንዲህ መልኩ ገልጾታል፡፡

ንብረት ለሚለው ቃል በአዋጁ ስር የተመለከተ ትርጓሜ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ከአዋጁ አላማና ከአሰሪው ድርጅት ባህርይ እንዲሁም ከንብረት ህግ ጽንሰ ሀሳቦች ጋር በማዛመድ ለቃሉ ትርጉም መስጠት ፍትሐዊነት ይኖረዋል ምክንያቱም ንብረት ለሚለው ጽንሰ ሀሳብ ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም ለመስጠት የሚቻል አይደለምና፡፡

በመቀጠልም ንብረት ለሚለው ቃል የሚከተለውን ፍቺ ሰጥቷል፡፡

“የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅን አጠቃላይ አላማም ሆነ የንብረት ህግ ጽንሰ ሀሳቦች ባህርያት ግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ ንብረት ማለት ዋጋና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው እንዲሁም በአብዛኛው ሀብትነት ሊያዝ የሚችል ነገር መሆኑን ለመገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡”

ችሎቱ ይህንን ትርጉም ከጉዳዩ ጋር በማዛመድ እንዳለው፤

“ዋጋና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሆኖ በባለሀብትነት ሊያዝ የሚችል ነገር ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ያደረሰ ሰራተኛ ከሆነ በአሰሪው ንብረት ላይ በህጉ አነጋገር ጉዳት አድርሷል ለማለት የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡”

ችሎቱ ትርጉም ለመስጠት የተጠቀመበት ለአሰሪው “ዋጋና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነገር” የሚለው አገላለጽ በይዘቱ ሰፊ መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ በዚህ ትርጓሜ መሰረት ማናቸውም የአሰሪውን ጥቅም የሚመለከት ነገር ሁሉ እንደ አሰሪ ንብረት መቆጠሩ አይቀርለትም፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ 64988 (አመልካች ዳሽን ባንክ አክስዮን ማህበር እና ተጠሪ አቶ ሀይሉ ሽመልስ ግንቦት 30 ቀን 2003 .. ቅጽ 11) በጋዜጣ ሀሰተኛ መግለጫ መስጠት በአንቀጽ 27(1) ሸ አነጋገር በአሰሪ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ስለመሆኑ በሰበር ችሎት አቋም ተወስዶበታል፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ ተጠሪ በአመልካች የስራ ውላቸው መቋረጡን በመግለጽ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሏቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ ውሳኔ ይሰጣቸው ዘንድ ክስ ያቀረቡ ሲሆን አመልካችም በመልሱ ላይ ተጠሪ መግለጫ የመስጠት ስልጣን ሳይኖራቸው በጋዜጣ አሉታዊ የሆነ መግለጫ በመስጠት በባንኩና በሰራተኞች ላይ መረበሽን፤ በደንበኞች ላይ ደግሞ መደናገጥን ለወደፊቱ የባንኩ ደንበኞች ሊሆኑ በሚችሉት ላይም ጥርጣሬና አመኔታ የሚያሳጣ ተግባር የፈጸሙ በመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት ስንብቱ በአግባቡ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡

ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም አመልካች ስለጉዳዩ ማስረጃ አለማቅረቡንና በስንብት ደብዳቤው ላይ የተገለጹት ድርጊቶችም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ስር እንደማይወደቁ በማተት የተጠሪ የስራ ውል መቋረጥ ከህግ ውጭ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔው ቅር በመሰኘት አመልካች የይግባኝ አቤቱታ ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 337 መሰረት ተሰርዟል፡፡

አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ባለመስማማት የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን በአቤቱታውም ላይ የተጠሪ ድርጊት በአመልካች ባንክ ስምና ክብር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ በባንኩ ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ሊቆጠር ይገባዋል በማለት ተከራክሯል፡፡ ክርክሩም በችሎቱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ችሎቱ ውሳኔ ሲሰጥ በሰ/መ/ቁ. 34669 “ንብረት” ለሚለው ቃል የሰጠውን ፍቺ ከሞላ ጎደል በመድገም የአሰሪው መልካም ስምna ዝና እንደ አሰሪ ንብረት እንደሚቆጠር ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በዚሁ መሰረት “ንብረት” ለሚለው ቃል የሚከተለው ፍቺ ተሰጥቷል፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅን አጠቃላይ አላማም ሆነ የንብረት ህግ ጽንሰ ሀሳቦች ባህርያት እንዲሁም የንግድ ህጉ ስለመልካም ስም (Good will) የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ ንብረት ማለት ዋጋና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው እንዲሁም በአብዛኛው ሀብትነት ሊያዝ የሚችል ነገር መሆኑን ለመገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ችሎቱ የሰጠው ፍቺ ይዘት ሲታይ ትርጉም በመስጠት ረገድ በንግድ ህጉ ስለመልካም ስም (Good will) የተመለከቱት ድንጋጌዎች ግምት ውስት መግባት እንዳለባቸው ከማሳሰብ ባለፈ በተለየ መልኩ በችሎቱ የተሰጠ ትርጓሜ የለም፡፡

የአሰሪው መልካም ስምና ዝና እንደ ንብረት የሚታይ በመሆኑ የሰራተኛው ድርጊት በአሰሪው መልካም ስምና ዝና ላይ ጉዳት አድርሷል ወይም ለአደጋ አጋልጧል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አሰሪው ድርጅት በተሰማራበት የንግድ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ (አመልካች ወሰኔ የህክምና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ተጠሪ / ክብረወሰን አለማየሁ //. 77134 ጥቅምት 8 ቀን 2005 .. ቅጽ 14) በዚህ ጉዳይ ተጠሪ በተደጋጋሚ የስራ ሰዓት አያከብርም፤ በሚያክማቸው ህሙማን ላይ የመሳደብና የጠብ ጫሪነት ተግባር ፈጽሟል እንዲሁም የህክምና ስነ-ምግባር ደንብን በመተላለፍ የታካሚዎችን የግል ሚስጥር ለሶስተኛ ወገኖች አሳልፎ ሰጥቷል በሚል የስራ ውሉ በአመልካች በመቋረጡ ስንብቱ ህገ-ወጥ እንደሆነ በመግለጽ ክስ አቅርቦ ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የተጠሪ ጥፋት በማስረጃ መረጋገጡን በማመለከት ስንብቱ ህጋዊ ነው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ በተደጋጋሚ የስራ ሰዓት ባለማክበሩ በስራው ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሷል የሚለው አተረጓጎም የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1) ሀ እና ለ አቀራረጽ የተከተለ አይደለም እንዲሁም የህክምና ዲሲፕሊን አለማክበር በተጠሪ የስራ ውል በግልጽ ካልተመለከተ በስተቀር የስራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል ምክንያት አይደለም የሚሉ ምክንያቶችን በመስጠት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎት የይግባኝ ሰሚውን ውሳኔ በመሻር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡

ችሎቱ ተጠሪ የፈጸማቸው ድርጊቶች ክሱን በሰማው ፍርድ ቤት በማስረጃ መረጋገጣቸውንና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም በማስረጃ ምዘና ውድቅ እንዳላደረጋቸው በመግለጽ እነዚህ ድርጊቶች የስራ ውልን ለማቋረጥ በቂ ምክንያት መሆን አለመሆናቸውን ጭብጥ ይዞ መርምሯል፡፡ ለተያዘው ጭብጥ እልባት ለመስጠት አመልካች ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ባህርይና ካለበት ሀላፊነት፤ ተጠሪ በአሰሪና ሰራተኛ ህግና በሙያ ስነ-ምግባር ደንቡ ከተጣለበት ግዴታና ኃላፊነት እንዲሁም የተጠሪ አድራጎት በአመልካች ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር መመዘን እንዳለበት ችሎቱ በውሳኔው ላይ ካመለከተ በኋላ እነዚህን ነጥቦች ከተጠሪ ድርጊት አንጻር በዝርዝር መርምሯል፡፡

በዚሁ መሰረት ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተጣለበት ግዴታ የሙያውን ስነ-ምግባር አክብሮ ህሙማንን በአክብሮት የማነጋገርና የግል ሚስጥራቸውን የመጠበቅ ግዴታን እንደሚያካትት በመግለጽ የተጠሪ ድርጊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 174/1986 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት አመልካች የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ የተሰጠውን ፍቃድ ለማሳገድ ወይም ለማሰረዝ የሚችል ምክንያትና በወንጀል ህግ አንቀጽ 399 እና 400 መሰረትም የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ በችሎቱ ውሳኔ ላይ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የተጠሪ ድርጊት የአመልካችን መልካም ስምና ዝና በማጉደል ፈቃድ ባገኘበት የህክምና አገልግሎት የመስጠት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆን የማድረግ ውጤት እንዳለው ችሎቱ አስምሮበታል፡፡

የተጠሪ ድርጊት በየትኛው ጥፋት ስር ይወድቃል የሚለውን በተመለከተ የተጠሪ ጥፋቶች በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1) ረ እና ሸ ስር እንደሚወደቁ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በተለይ የአንቀጽ 27(1) ሸ አፈጻጸምን በተመለከተ ድንጋጌው ከምን አንጻር መቃኘት እንዳለበት የተገለጸው በሚከተለው መልኩ ነበር፡፡

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1) ድንጋጌም አመልካች ከሚሰጠው የህክምና ግልጋሎት ልዩ ባህርይና ተጠሪ ከሚጠበቅበት ከፍተኛ የሆነ የስነምግባር ብቃት አንጻር ባለማክበሩ፤ በአመልካች ላይ የደረሰውን ወይም ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በማያሻማ ሁኔታ መተርጎም ያለበት መሆኑን ከአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ አላማ ከድንጋጌው ይዘትና ስለህክምና ፈቃድ አሰጣጥ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን ይዘት በመመርመር ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

ከመልካም ስምና ዝና በተጨማሪ የአሰሪው ጸጥታና ደህንነት እንደ ንብረት ተፈርጆ በሰበር ችሎት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ (አመልካች የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት እና ተጠሪ አቶ በሪሁን በላይ // 90389 ጥቅምት 16 ቀን 2006 .. ቅጽ 15) ተጠሪ በአመልካች ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ተጠሪ ተረኛ በነበሩባቸው በተለያዩ ሁለት ቀናት የተለያዩ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች ወደ ድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተው ተገኝተዋል፡፡ በተለይ በመጀመሪያው ቀን የገባው ግለሰብ አውሮፕላኖች በሚቆሙበት ቦታ ላይ በመገኘቱ በፖሊሶች ተይዟል፡፡ እነዚህ ፍሬ ነገሮች በማስረጃ ቢረጋገጡም ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት በአመልካች ላይ የደረሰበት የጸጥታና ደህንነት ችግር የለም በማለት የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ ውጭ ነው የሚል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የስራ ውል መቋረጥን በተመለከተ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቷል፡፡

የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎትም የተጠሪ ተግባር በአንቀጽ 27(1) ሸ ብሎም በአንቀጽ 27(1) ቀ እና 14(2) ሀ ስር እንደሚወድቅ በማተት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሽሯል፡፡

የአሰሪው ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት

በአንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት የስራ ውልን በህጋዊ መንገድ ለማቋረጥ ጉዳት ደረሰበት የተባለው ነገር የንብረትን ትርጉም ማሟላቱ ብቻ ሳይሆን ንብረቱ የአሰሪው ወይም ከድርጅቱ ስራ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በእህት ድርጅት ንብረት ላይ በሰራተኛው የደረሰ ጉዳት በአሰሪ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አይደለም፡፡ ንብረቱ የአሰሪው ካልሆነ ከድርጅቱ ስራ በቀጥታ ግንነኙነት ያለው (ለምሳሌ አሰሪው ተከራይቶ ለስራ የሚጠቀምበት) ስለመሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ (አመልካች ግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሺያል /የተ/የግል/ማህበር እና ተጠሪ አቶ ኃይሉ ናርዬ //. 7440 መጋቢት 24 ቀን 2001 .. ቅጽ 13)

በሰ/መ/ቁ 74400 ተጠሪ ሲያሽከረክሩት በነበረው የአመልካች ድርጅት ንብረት ላይ በግጭት ጉዳት አድርሰዋል በሚል በአመልካች የተወሰደባቸውን የስንብት እርምጃ በመቃወም የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈላቸው በመጠየቅ ክስ ያቀረቡ ሲሆን አመልካችም ስንብቱ በአንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት ህጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡ ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ማስረጃ ሲመረምር ጉዳት ደረሰበት የተባለው ተሸከርካሪ ባለቤትነቱ የአመልካች እህት ኩባንያ የሆነው የግዮን ጋዝ ኃ/የተ/የግል/ማህበር እንደሆነ በማረጋገጡ የስራ ውሉ መቋረጥ ከህግ ውጭ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው የአመልካችና የግዮን ጋዝ ኃ/የተ/የግል/ማህበር ባለቤት አንድ ቢሆኑም ድርጅቶቹ የራሳቸው የተለያየ የህግ ሰውነት ያላቸው በመሆኑ ተጠሪ በአመልካች ንብረት ላይ ጉዳት አድርሳል ለማለት አልተቻለም፡፡ አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ብሎም ለሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ቢያቀርብም ሁለቱም የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንተውታል፡፡ የሰበር ችሎት ከስር ፍርድ ቤት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በውሳኔው ላይ የሚከተለውን ሐተታ አስፍሯል፡፡

አንድ የተፈጥሮ ሰው ከአንድ በላይ /የተወሰነ የግል ማህበሮች ባለቤት ሁኖ መገኘት በአንዱ ድርጅት ውስጥ ያለ ሰራተኛ በሌላኛው እህት ድርጅቱ ንብረት ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት በሌላኛው ድርጅት በህጉ አግባብ የተቀጠረውን በድርጅቱ ንብረት ላይ ጉዳት አደርሰሃል በማለት የስራ ውሉን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 27/1// መሰረት ያለማስጠንቀቂያ የሚያስችለው ህጋዊ ምክንያት አይደለም፡፡

ምንም እንኳን ችሎቱ በውሳኔው ላይ በቀጥታ ትርጉም የሰጠው ለ”አሰሪ ንብረት” ቢሆንም እግረመንገዱን “ከድርጅቱ ስራ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት” የሚለው አገላለጽ በምን መልኩ መተርጎም እንዳለበት ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ ተጠሪ የስራ ውል ያደረጉት ከአመልካች ጋር መሆኑን ከገለጸ በኋላ አመልካች ተሽከርካሪውን ለስራ ምክንያት ተኮናትሮ ሲጠቀምበት የነበረ ስለመሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ አለመረጋገጡን በውሳኔው ላይ ጠቅሶታል፡፡ ያ ማለት ፍሬ ነገሩ ቢረጋገጥ ኖሮ አሰሪው ለስራ ጉዳይ በኪራይ የሚጠቀምበት ንብረት ከድርጅቱ ስራ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ንብረት በመሆኑ የስራ ውሉ መቋረጥ ህጋዊ ይሆን ነበር፡፡

ጉዳት ማድረስ እና ጉዳት መድረስ

የአንቀጽ 27(1) ሸ ድንጋጌ የሰራተኛውን የሀሳብ ክፍል ብቻ ሳይሆን የድርጊት ክፍሉንም ከነውጤቱ ጠቅልሎ ይዟል፡፡ ስለሆነም ለድንጋጌው አፈፃፀም የሰራተኛው ድርጊት (commission) ወይም አልድርጊት (omissim) መኖሩ ብቻ ሳይሆን ጉዳቱ በዚህ የተነሳ ስለመከሰቱ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ በጉዳት አድራሹና በደረሰው ጉዳት መካከል የምክንያትና ውጤት ግንኙነት በሌለበት በድንጋጌው የተገለፀው ጥፋት ተፈፅሟል ለማለት አይቻልም፡፡

ሰራተኛው ማድረግ የሌለበትን ድርጊት በመፈፀሙ በአሰሪው ንብረት ላይ ተጨባጫነት ያለው ቀጥተኛ ጉዳት ካደረሰ የምክንያትና ውጤት ግንኙነቱን ሆነ የሀሳብ ክፍሉን ለመወሰን አይከብድም፡፡ በሰ/መ/ቁ 42873 (አመልካች የባህል ማዕከል እና የስዕል ጋለሪ .የተ.የግል ማህበር እና ተጠሪ ቢንያም ክፍሌ ሰኔ 17 ቀን 2001 . ያልታተመ) ተጠሪ የሚያሽከረክረውን የአመልካች አውቶቡስ በመኪኖች መውጪያ በር በኩል ማውጣት ሲገባው በመኪኖች መግቢያ በር መኩል በማውጣቱ በአውቶቡሱ ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህ መልኩ በአሰሪው ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት እና የጉዳት አድራሹ ድርጊት በማስረጃ የተረጋገጠ ቢሆንም የስር ፍ/ቤቶች ተጠሪ ጉዳቱን ያደረሰውን ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ስለመሆኑ አመልካች አላስረዳም በማለት የስራ ውሉን መቋረጥ ከህግ ውጭ አድርገውታል፡፡ የሰበር ችሎት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ ሲሽር በውሳኔው እንዳመለከተው ተጠሪ የፈፀመው ድርጊት እና በአሰሪው ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በማስረጃ ከተረጋገጠ ተጠሪ ቸልተኛ መሆኑ የሚያሳየው ድርጊቱ ራሱ እንጂ በምስክር በሚነገር ቸልተኛ ነው በሚል ቃል ወይም አገላለጽ አይደለም፡፡

ሰራተኛው አንድን ድርጊት በቀጥታ በመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ባለማድረጉም በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ሆኖም ቢዚህ መልኩ የሚደርስ ጉዳት የአልድርጊት (omissim) ውጤት መሆኑ በማያሻማ መልኩ ካልተረጋገጠ በቀር የሰራተኛውን የተጠያቂነት አድማስ አለአግባብ ያሰፋዋል፡፡ ስለሆነም ሰራተኛው ጥፋተኛ ተብሎ የስራ ውሉ በህጋዊ መንገድ ሊቋረጥ የሚገባው በስራ ውል፣ በህብረት ስምምነት፣ በስራ ደንብ ወይም በአዋጁ መሰረት ማድረግ ሲኖርበት ባለማድረጉ የተነሳ ጉዳት ሲደርስ እንጂ ከስራ ግዴታው በመነጨ ስራውን በትጋት ባለመፈጸሙ ወይም ጉዳቱ እንዳይደርስ ባለማድረጉ ሊሆን አይገባም፡፡ በሌላ አነጋገር ግልጽ የሆነ የስራ ግድፈት ከስራ ግዴታ አለመወጣት መለየት ይኖርበታል፡፡ በሰበር ችሎት በተሰጡት ውሳኔዎች ሁለቱ ሳይለዩ አንድ ላይ ተጨፍልቀዋል፡፡

በሰበር ችሎት በተሰጡ ውሳኔዎች አልድርጊት በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት ለስራ ውል መቋረጥ ህጋዊ ምክንያት ከተደረገባቸው ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • በሰ/መ/ቁ 34669 (ቅጽ 8) ሰራተኛው የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች የፈተና ወረቀት በጊዜ አርሞ ባለመመለሱ አሰሪውን በድጋሚ ፈተና ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ ዳርጐታል፡፡
 • በሰ/መ/ቁ 37615 (አመልካቸ ጊጋ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር እና ተጠሪ ከበደ ዓለሙ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ) ሰራተኛው ይሰራበት የነበረውን ማሽን ቁልፍ ማስረከብ ሲገባው ሳያስረክብ እረፍት ስለወጣ አሰሪው መጠነኛ የገንዘብ ወጪ እንዲያወጣ አድርጐታል፡፡
 • በሰ/መ/ቁ 86284 (አመልካች ሆራይዘን አዲስ ጐማ (.) እና ተጠሪ አቶ መኮንን አለሙ መጋቢት 13 ቀን 2005 . ቅጽ 15) ተጠሪ የድርጅቱን ጆንያ ተቆጣጥሮና ተከታትሎ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ለሌሎች የቀን ሰራተኞች ኃላፊነቱን በመተዉ ምክንያት 390 (ሶስት መቶ ዘጠና) ጆንያ ነው ተብሎ የተጫነው በመውጫ በር ላይ ሲቆጠር 580 (አምስት መቶ ሰማንያ) ሆኖ ተገኝቷል፡፡
 • በሰ/መ/ቁ 90389 (ቅጽ 15) ሰራተኛው በጥበቃ ስራ ላይ እያለ ማንነታቸው የማይታወቅና ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ወደ አሰሪው ድርጅት ግቢ (የአውሮፕላን ማረፊያ) ገብተዋል፡፡
 • በሰ/መ/ቁ 39650 (አመልካች የየረር በር ምሰራቅ ፀሐይ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን እና ተጠሪዎች እነ ቄስ ሰፊነው ደሳለኝ ግንቦት 27 ቀን 2001 . ቅጽ 8) ተጠሪዎች በጥበቃ ስራ ተረኛ በነበሩበት ጊዜ ብር 15,000 (አስራ አምስት ሺ ብር) የያዘ ሙዳየ ምጽዋት ተሰርቋል፡፡
 • በሰ/መ/ቁ 17189 (ቅጽ 2) ሰራተኛው የመቆጣጠር ግዴታውን አልተወጣም በሚል በአሰሪው ድርጅት ገንዘብ ያዥ ለደረሰ የገንዘብ ጉድለት ተጠያቂ ሆኖ የስራ ውሉ መቋረጥ ህጋዊ እንደሆነ በሰበር ችሎት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

በእነዚህ በተጠቀሱት መዝገቦች እያንዳንዱ ሰራተኛ በአንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል የስራ ውሉ መቋረጥ ህጋዊ አንደሆነ በሰበር ችሎት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ 17189 በህጉ አተረጓጐም ላይ በአንደኛው የችሎቱ ዳኛ የተለየ ሀሳብ የሰፈረ ቢሆንም በመደምደሚያ ሀሳቡ ላይ ልዩነት አልታየም፡፡ የተለየው ሀሳብ የስራ ተግባርን በመጣስ የሚፈጸሙ የገንዘብ ብክነቶች በአዋጁ አንቀጽ 27(1) ሸ ስር እንደማይሸፈኑ አቋም የተንጸባረቀበት ሲሆን ይኸው ልዩነት በመደምደሚያ ሀሳቡ ላይ ልዩነት አለማምጣቱ ያስገርማል፡፡ ከምክንያት እና ውጤት ግንኙነት አንፃር ብሎም ከአንቀጽ 27(1) ሸ ድንጋጌ ይዘት አንፃር በከፊል ጠለቅ ያለ ትንተና ቢታከልበት ኖሮ ልዩነቱ ከህግ አተረጓጐም ባለፈ ውጤቱንም ባካተተ ነበር፡፡

በሰ/መ/ቁ 17189 መልስ ሰጪ (ሰራተኛው) ጥፋተኛ የተደረገው ጥቅል በሆነ አነጋገር በስሩ ያለውን ገንዘብ ያዥ በተገቢው ሁኔታ አልተቆጣጠረም በሚል እንጂ ተለይቶ የታወቀና ማድረግ ሲኖርበት ያላደረገው ነገር ስለመኖሩ ባለማድረጉ ምክንያትም ጉዳቱ ስለመድረሱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ነው፡፡ በእርግጥ ስራውን በትጋት የማይሰራ ሰራተኛ በአዋጁ አንቀጽ 13(1) የተጣለበትን ግዴታ አልተወጣም፡፡ ይሁን እንጂ የስራ ግዴታን አለመወጣት ከአንቀጽ 27(1) ሸ ጋር ማገናኘት ድንጋጌውን አለአግባብ ለጥጦ ራሱን የቻለ ትርጉም እንዳይኖረው ያደርገዋል፡፡

በሰራተኛው የሚፈጸም ጥፋት በአዋጁና በህብረት ስምምነቱ አግባብነት ካለው ድንጋጌ ስር እየተነፃፀረ በድንጋጌው በተቀመጠው መለኪያ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ለተከታታይ አምስት ቀናት የቀረ ሰራተኛ ከስራ በመቅረቱ ምክንያት በአሰሪው ንብረት ላይ ቀጥተኛ ባይሆንም ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ሆኖም ከስራ ሲሰናበት የስንብቱ ህጋዊነት የሚለካው በአንቀጽ 27(1) ለ ስር እንጂ በአንቀጽ 27(1) ሸ አይደለም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሰ/መ/ቁ 39650 በመዝገቡ ላይ ተጠሪዎች የነበሩት ሰራተኞች በጥበቃ ስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ስርቆት ሲፈጸም ጥፋተኛ የተደረጉት የመጠበቅ ግዴታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ጥቅል ምክንያት እንጂ ማድረግ ያለባቸውን ባለማድረጋቸው ምክንያት ስርቆት መፈጸሙ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ነው፡፡ ተጠሪዎች ስርቆት በተፈጸመበት እለት የተወሰኑት ወይም ሁሉም የስራ ቦታቸውን ለቀው ስለመሄዳቸው፣ ከጥበቃ ተግባራቸው ተዘናግተው በወሬ መጠመዳቸው ወይም ሌላ በግልጽ የፈጸሙት የስራ ግድፈት በሌለበት ሁኔታ የተፈጸመው ስርቆት በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ ብቻ ተጠሪዎችን የጉዳቱ አድራሾች አያደርጋቸውም፡፡ ከዚያም አልፎ ተረኛ በነበሩበት ጊዜ ስርቆት መፈጸሙ ብቻውን የስራ ተግባራቸውን በአግባቡ አልተወጡም ሊያስብላቸው እንኳን አይችልም፡፡ ከፍተኛ የስራ ትጋትና የተጠናከረ ጥበቃ መኖር በራሱ ስርቆትን አያስቀርምና፡፡ በመሰረቱ ሰራተኛው በአንቀጽ 27(1) ሸ መሰረት የስራ ውሉ የሚቋረጠው በአሰሪው ንብረት ላይ ሊደርስ የነበረን ጉዳት ባለማክሸፉ ወይም ጉዳቱ እንዳይደርስ ባለማዳኑ ሳይሆን አንድን ተለይቶ የሚታወቅ ተግባር በማድረጉ ወይም ባለማድረጉ ምክንያት ጉዳት ሲደርስ ነው፡፡ ተጠሪዎችም ስርቆቱ እንዳይከሰት ማድረግ አለመቻላቸው በድንጋጌው መሰረት ጥፋተኛ አያሰኛቸውም፡፡

በሰ/መ/ቁ 90389 እንዲሁ ተጠሪ (ሰራተኛው) የጥበቃ ተረኛ በነበረበት ጊዜ ማንነታቸው የማይታወቅ ሰዎች ወደ ድርጀቱ ግቢ መግባታቸው በራሱ ግለሰቦቹን አስገብቷል የሚያስብል አይደለም፡፡

ከላይ በሰ/መ/ቁ 17189፣ 39650 እና 90389 ካየነው በተቃራኒ በሰ/መ/ቁ 34609፣ 37615 እና 86284 ሰራተኛው የስራ ግዴታው አካል የሆነና ተለይቶ የሚታወቅ የስራ ግድፈት በመፈጸሙ ምክንያት በአሰሪው ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ግልጽ የሆነ የምክንያትና ውጤቱ ግንኙነትን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሰራተኛው፤

 • ሲሰራበት የነበረውን የማሽን ቁልፍ ማስረከብ ሲኖርበት አለማስረከቡ (ሰ/መ/ቁ 37615)
 • የተማሪዎችን ፈተና በጊዜ አለመመለሱ (ሰ/መ/ቁ 34669)
 • በአዋጁ በተጣለበት ግዴታ እና አሰሪው በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ስራውን በግሉ አለመስራቱና በተቃራኒው ያለአሰሪው ፈቃድ የስራ ግዴታውን ለሌሎች ሰራተኞች ማስተላለፉ (ሰ/መ/ቁ 86284)

በአጠቃላይ መደረግ የነበረበት ተለይቶ የሚታወቅ ድርጊት ባለመደረጉ የተነሳ የአሰሪው ንብረት ለጉዳት ተዳርጓል፡፡ በዚህ መልኩ አንድን ነገር ባለማድረግ የሚገለጽ ጉዳት የማድረስ ተግባር ግልጽ የሆነ የስራ ግድፈት በመሆኑ የስራ ግዴታን ካለመወጣት (ሰራን በአግባቡ ካለማከናወን) ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ጐልቶ ይታያል፡፡

በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሰራተኛው ጉዳት የማድረስ ተግባር ፈጽሟል የሚባለው የአሰሪው በሆነ ንብረት ላይ በእርግጥም ጉዳት ሲደርስ ነው፡፡ የደረሰው ጉዳት በተጨባጭ የሚታይ በሚሆንበት ጊዜ (ለምሳሌ በአሰሪው አውቶብስ ላይ በግጭት የሚደርስ ጉዳት፤ ተጨማሪ የገንዘብ ወጪ፣ የገንዘብ ምዝበራ ወይም ስርቆት) ጉዳት ስለመድረሱ አካራካሪ አይሆንም፡፡

በሰበር ችሎት ከተሰጡት ውሳኔዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የጉዳት መድረስ ሰፋ ያለ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ 80284 የተረጋገጠና ሊደረሰ የነበረ ጉዳት በአንቀጽ 27(1) ሸ ስር እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህ መዝገብ በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል ከስራ የተሰናበተው ሰራተኛ የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በሚገባ ባለመወጣት የስራ ግዴታውን ለሌሎች ሰራተኞች አሳልፎ በመስጠቱ በመኪና ላይ እንደተጫነ ማረጋገጫ ከሰጠበት ጆንያ ውስጥ 190 የድርጅቱ ጆንያ በትርፍነት በጥበቃ ሰራተኞች ተይዟል፡፡ ሊደርስ የነበረው ጉዳት ከሰራተኛው ውጪ ባለ ምክንያት ሳይደርስ መቅረቱ ከአንቀጽ 27(1) ሸ አንፃር ትርጉም ባይሰጥበትም ችሎቱ ስንብቱን በአንቀጽ 27(1) ሸ ስር ህጋዊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

በሰ/መ/ቁ 90389 እና 64988 የሰበር ችሎት ለአሰሪ ንብረት የተለጠጠ ትርጉም በመስጠቱ የጉዳት ትርጉምም በዛው ልክ ሰፍቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ 90389 በአሰሪው ላይ ደረሰ የተባለው ጉዳት የአሰሪው ደህንነትና ፀጥታ ለአደጋ መጋለጡ ሲሆን በሰ/መ/ቁ 64987 ደግሞ ሰራተኛው በጋዜጣ ሰጠ በተባለው ሀሰተኛ መግለጫ ምክንያት አሰሪው በመልካም ስሙና ክብሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት አቋም ተይዟል፡፡ በተለይ በዚህኛው መዝገብ ላይ ችሎቱ የተጠሪ (ሰራተኛው) ተግባር በአሰሪው መልካም ስምና ዝና ላይ ወዲያውኑ ወይም ወደፊት ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ተግባር እንደሆነ በመግለፅ ወደፊት ሊደርስ የሚችል ጉዳትም በአንቀጽ 27(1) ሸ ስር እንዲወድቅ አድርጐታል፡፡

ከባድ ቸልተኝነት

የሰበር ችሎት የከባድ ቸልተኝነትን መለኪያ በሰ/መ/ቁ 41115 (አመልካች ሜድሮክ ኮንስትራክሽን ኃላ.የተ.የግል ማህበር እና ተጠሪ አቶ ሞገስ ሽፈራው የካቲት 26 ቀን 2001 . ቅጽ 8) እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡

ከባድ ቸልተኝነት የሚለውን ቃል መለኪያ በተመለከተ ህጉ በግልጽ አያሳይም፡፡ ይሁን እንጂ ቸልተኝነት የጥንቃኔ ጉድለት እንደመሆኑ መጠን የጥንቃቄ አይነትና ደረጃ እንደየድርጊቱና አድራጊው የስራ ድርሻ አኳያ በመመልከት ምላሽ ለማግኘት አያዳግትም

በሰ/መ/ቁ 41115 ተጠሪ በሚያሽከረክሩት የአመልካች ድርጅቱ መኪና ላይ ቁልፉን ትተው በመሄዳቸው ረዳታቸው መኪናውን አንቀሳቅሶ በማጋጨቱ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህም የተነሳ ከስራ ተሰናብተዋል፡፡ ስንብቱን በመቃወም ተጠሪ ክስ ሲያቀርቡ ጉዳዩን የመረመረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተጠሪ ተግባር ከባድ ሊባል የሚችል ቸልተኝነት ሆኖ ስላላገኘው ስንብቱ ከህግ ውጭ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የይግባኝ አቤቱታ የቀረበለት የከ/ፍ/ቤትም ይግባኙን ሰርዞታል፡፡ በመጨረሻም አመልች የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ የተጠሪ አድራጐት በከባድ ቸልተኝነት ስር ሊወድቅ ስለመቻሉ በጭብጥነት ተይዞ ችሎቱ ከላይ ባስቀመጠው መለኪያ መሰረት የተጠሪ የጥፋት ደረጃ ከባድ ቸልተኝነትን ሊያቋቁም የሚችል መሆኑ አለመሆኑ ከስራቸው ባህርይ አንፃር ተመልክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ተጠሪ በስራቸው ሹፌር ከመሆናቸው አንፃር ጥንቃቄ ማድረግ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ የመኪናቸውን ቁልፍ አያያዝ በመሆኑ ቁልፉን በመኪናው ላይ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ትተው ሊወርዱ እንደማይገባ በመጠቆም የቸልተኝነት ደረጃው ግን ከባድ ተብሎ እንደማይፈረጅ ችሎቱ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ የሰጠው ምክንያት የሚከተለው ነው፡፡

“…መኪናው ቁሞ የነበረበት ቦታ አመልካች ድርጅት ግቢ ውስጥ ከመሆኑ እና ቁልፉን አንስተው መኪናውን በማንቀሳቀስ በሌላ መኪና ላይ ጉዳት እንዲደርስ በቀጥታ አስተዋጽኦ [ያደረገው] የመኪናው ረዳት መሆኑ መረጋገጡ ከረዳቱ አስፈላጊነት አንፃር ሲታይ የተጠሪ የጥንቃቄ ጉድለት የከባድ ቸልተኝነት መለኪያ ሊያሟላ ይችላል ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ተጠሪ ቁልፉን በመኪናው ውስጥ ረዳቱ ባለበት ሁኔታ ትቶ መውረዱ ትክክለኛ አዕምሮ ባለው ሰውና በተጠሪ የግል ሁኔታ መመዘኛ መሰረት ከባድ ቸልተኝነትን ሊያሳይ የሚችል አይደለም፡፡

ከባድ ቸልተኝነት ተለይቶ በተቀመጠ መለኪያና ሚዛን መሰረት የሚወሰን እንደመሆኑ በማስረጃ የሚረጋገጥ የፍሬ ነገር ጥያቄ አይደለም፡፡ በማስረጃ የሚረጋግጠው መለኪያውን የሚያቋቁሙት ፍሬ ነገሮችን እንጂ ከባድ ቸልተኝነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የተጠሪ የስራ ድርሻ ሹፌርነት መሆኑ፣ የመኪናውን ቁልፍ ረዳታቸው መኪናው ውስጥ እያለ ትተው መውረዳቸው፤ መኪናው በአመልካች ድርጅት ግቢ ውስጥ መቆሙ እንዲሁም ጉዳት አድራሹ የተጠሪ ረዳት መሆኑ ሁሉም በማስረጃ የሚረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፍሬ ነገሮች በመነሳት ከባድ ቸልተኝነት ስለመኖሩ (ስላለመኖሩ) ድምዳሜ ላይ መድረስ ደግሞ በቀጥታ በማስረጃ የማይረጋገጥ የህግ ጥያቄ ነው፡፡

በሰ/መ/ቁ 42873 (ያልታተመ) ተጠሪ የነበረው ሰራተኛ የሚያሽከረክረውን የአመልካች መኪና በመኪኖች መውጪያ በር በኩል ማውጣት ሲገባው በመኪኖች መግቢያ በር በኩል በማውጣቱ በአውቶቡሱ ላይ ጉዳት ማድረሱ በማስረጃ ቢረጋገጥም ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው ፍ/ቤት ተጠሪ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረሱን አመልካች አላስረዳም በማለት ከባድ ቸልተኝነትን እንደ ፍሬ ነገር ጥያቄ በመቁጠር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የሰበር ችሎት ውሳኔውን ሲሽር ቸልተኝነት በምስክር ቃል የሚረጋገጥ ፍሬ ነገር አለመሆኑን በሚከተለው መልኩ ገልጾታል፡፡

“[ተጠሪ] ቸልተኛ መሆኑ የሚያሳየውም ድርጊቱ እራሱ እንጂ በሌላ ሰው (ምስክር) በሚነገር ቸልተኛ ነው በሚል ቃል ወይም አገላለጽ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን በሰ/መ/ቁ 41115 እና 42873 ወጥነት ባለው መልኩ ከባድ ቸልተኝነት የህግ ጥያቄ ስለመሆኑ በችሎቱ አቋም የተያዘበት ቢሆንም በሰ/መ/ቁ 52181 (አመልካች የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ተጠሪ አቶ ዳምጠው አንጐ ግንቦት 23 ቀን 2002 . ያልታተመ) የተሰጠው ውሳኔ ከሁለቱ ማፈንገጥ ታይቶበታል፡፡ በዚህ መዝገብ ተጠሪ የሻንጣ መጐተቻ ታግ ከአውሮፕላን ጋር በቸልተኝነት አጋጭተዋል በሚል ከስራ የተሰናበቱ ሲሆን ስንብቱን ተከትሎ ክስ በማቅረባቸው ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤት፤

አሠሪ ሠራተኛውን ያለ ማስጠንቀቂያ ለማሰናበት የሚችለው ጉዳት ያደረሰው በቸልተኝነት የተለመደ አሰራርን ወይም ደንብን [የጣሰ] የሆነ እንደሆነ ነው፡፡

የሚል ምክንያት በመስጠት ስንብቱን ከህግ ውጭ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ይግባኝ የቀረበለት የከፍተኛው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠሪ በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ያደረሰ ስለመሆኑ አመልካች የማስረዳት ሸክሙን አልተወጣም በሚል የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡

የስር ፍ/ቤቶች ከባድ ቸልተኝነትን እንደ ፍሬ ነገር በመቁጠር የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ቢሆንም የሰበር ችሎት ስህተቱን ከማረም ይልቅ የስር ፍ/ቤቶችን ስህተት ደግሞታል፡፡ ችሎቱ በቀረበለት የሰበር አቤቱታ መነሻነት ጉዳዩን የመረመረው ተጠሪ ሲያሽከረክረው በነበረው የእቃ መጫኛ ታግ አውሮፕላኑን የገጨው በከባድ ቸልተኝነት ነው ወይስ አይደለም? የሚል ጭብጥ በመመስረት ሲሆን ለጭብጡ ምላሽ የሰጠው ግን ተለይቶ በተቀመጠ የከባድ ቸልተኝነት መለኪያ ሳይሆን በማስረጃ ላይ ነው፡፡ በጭብጡ ላይ የችሎቱ ሐተታ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“…ስለአደጋው ምርመራ እንዲያደርግ የተቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርት በህብረት ስምምነቱ መሰረት የተቋቋመው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የአመልካች ዋና ስራ አስፈጻሚ ያልተቀበለው ቢሆንም ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና የመመዘን ስልጣን ያላቸው /ቤቶች የአደጋ ምርመራ ሪፖርት ያቀረበው ኮሚቴና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረቡትን ሪፖርት ታዓማኒነትና ክብደት ያለው ማስረጃ መሆኑን በመመዘን አደጋው በተጠሪ ከባድ ቸልተኝነት ሳይሆን []ስራ መደራረብ ምክንያት ተጠሪ አጋጥሞት በነበረው ተፈጥሯዊ የሰውነት መድከም የመጣ ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ በከባድ ቸልተኝነት አውሮፕላኑ ላይ አደጋ ያደረሰ መሆኑን አላስረዳም በማለት ወስነዋል፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያ /ቤትና የከፍተኛ /ቤት ፍሬ ጉዳይ በማጣራትና ማስረጃ በመመዘን የደረሱበት ድምዳሜ የማጣራት ስልጣን ለሰበር ችሎት በፌደራል ህገ መንግስት አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3() እና በአዋጅ . 25/88 አንቀጽ 10 ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በመሆኑ አደጋው የደረሰው በተጠሪ ከባድ ቸልተኝነት ነው በማለት አመልካች ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡

[1] ውሳኔ የተሰጠው በተሻረው አዋጅ ቁጥር 42/85 መሰረት ቢሆንም ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የድንጋጌው ይዘት ያልተለወጠ በመሆኑ በሰ/መ/ቁ. 18419 ችሎቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 377/96 ለሚነሱ ተመሳሳይ ጥያቄዎችም ተፈጻሚነት አለው፡፡

9 replies »

 1. Ethiopia has limited number of matured lawyer, highly professional lawyers, qualified lawyers …..among them you are the one, I know you ,giving many law courses in haramaya university

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.