Articles

የስራ መሪ መታገድ እና የስራ ውል መቋረጥ፡ የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ

ተፈጻሚ ስለሚሆነው ህግ

የስራ መሪዎችን የስራ ሁኔታ የሚገዛ የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ ካለ በስራ መሪውና በአሰሪው መካከል ያለው ግንነኙነት የሚመራው በዚሁ መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ ይህን ነጥብ አስመልክቶ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 60489 (አመልካች አቶ አምባዬ ወ/ማርያም እና ተጠሪ የኢትዮጵያ የእህል ንግድ ድርጅት ጥር 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ቅጽ 13) የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቷል፡፡

“በግራ ቀኙ መካከል ስራ ላይ ያለው ልዩ ህግ (የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ) እስካለ ድረስ እና ያለው ደንብ ደግሞ ለሞራልና ለህግ ተቃራኒ ነው ወይም ተፈጻሚነት ሊኖረው የማይገባበትን ህጋዊ ምክንያት እስካልቀረበ ድረስ ተፈጻሚነት የሚኖረው ይሄው ልዩ ህግ በመሆኑ ወደ አጠቃላይ የፍታሐብሔር ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ያላቸውን የህግ ማዕቀፍ ፍለጋ የሚኬድበት አግባብ የለም፡፡”


የመተዳደሪያ ደንቡ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 ተፈጻሚነት እንዲኖረው የሚፈቅድ ሲሆን አዋጁ በስራ መሪም ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ (አመልካች አቶ ዳዊት ሸዋቀና እና ተጠሪ ስኳር ኮርፖሬሽን መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 84661 ቅጽ 15)

የስራ መሪ መታገድ እና ውጤቱ

የስራ መሪ ለተወሰነ ጊዜያት ከስራና ከደመወዝ ታግዶ መጨረሻ ላይ ቢሰናበት የታገደው ካለበቂ ምክንያት ቢሆንም እንኳን ለታገደበት ጊዜ ደመወዝ አይከፈለውም፡፡ (አመልካች ንብ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር እና መልስ ሰጭ አቶ ተገኑ መሸሻ ሰ/መ/ቁ 18307 ጥቅምት 25 ቀን 1998 ዓ.ም ቅጽ 2) በዚሁ ጉዳይ ላይ የሰበር ችሎት ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የፍ/ህ/ቁ 2541(1) ድንጋጌን ሲሆን ለድንጋጌው ትርጉም ከመስጠቱ በፊት የድንጋጌውን ይዘት እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡

“…ሠራተኛው አንድም የስራ አገልግሎት ባይሰጥም እንኳን ይኸው ሁኔታ አሰሪው ስራ ሳይሰጠው በመቅረቱ ወይም እንዳይሰራ በመከልከሉ የተነሳ እንደሆነ ደመወዙን ለማግኘት መብት አለው…”

ምንም እንኳን የድንጋጌው መልእክት ግልፅ ቢሆንም ችሎቱ በፍ/ህ/ቁጥር 2541(1) የተቀመጠው ድንጋጌ የሚያገለግለው “የስራ መሪው የስራ ውሉ ባልታገደበት ወይም ባልተቋረጠበት ጊዜ ሥራ ላይ ሆኖ ነገር ግን አሰሪው ስራ ሳይሰጠው ወይም እንዳይሰራ በከለከለው ጊዜ ነው፡፡” በማለት ተርጉሞታል፡፡ በዚህም የተነሳ የፍ/ህ/ቁ 2541(1) የስራ መሪው ከስራና ከደመወዝ ታግዶ የስራ አገልግሎት ላልሰጠባቸው ጊዜያቶች ደመወዝ እንዲከፈለው የሚፈቅድ ድንጋጌ እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

የዕገዳው ከፍተኛ ጊዜ በስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ በግልጽ ሰፍሮ እያለ አሰሪው በዚህ ጊዜ ውስጥ የዲሲፕሊን እርምጃ ካልወሰደ በደንቡ ላይ ከተቀመጠው የእገዳ ጊዜ በላይ ላሉት ጊዜያት አሰሪው ደመወዝ ለመክፈል ይገደዳል፡፡ በሰ/መ/ቁ 37982 (አመልካች የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ታደሰ ዘነበ ሐምሌ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ቅጽ 8) የአመልካች ድርጅት የስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ በጥፋት ምክንያት አንድ የሥራ መሪ ታግዶ ሊቆይ የሚችለው ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ ሲሆን ተጠሪ የአንድ ወር ጊዜው ካበቀ በኋላ ለሰባት ወራት ከስራና ከደመወዝ በመታገዳቸው አመልካች የሰባት ወራት ደመወዝ ለተጠሪ የመክፍል ግዴታ እንዳለበት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የውሳኔ ክፍል በሰበር ችሎትም ጸንቷል፡፡

የስራ ውል መቋረጥ እና ውጤቱ  

በስራ መሪነት ደረጃ ላይ በማገልገል ላይ ያለ ሰራተኛ ያለበቂ ምክንያት ቢሰናበት ኪሳራ ወይም ካሳ ከማግኘት ያለፈ መፍትሔ በህጉ ላይ አልተቀመጠለትም ፡፡ የስራ ውላቸው በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ 377/96 ከሚመራ ሰራተኞች አንፃር ሲታይ የስራ ውል ከህግ ውጪ መቋረጥ በተመለከተ የስራ መሪ የሆነ ሰራተኛ በሁለት መልኩ ተጠቃሚ አይደለም ይህም

ሀ. ውዝፍ ደመወዝ አይከፈለውም
ለ. ወደ ስራ የመመለስ መብት የለውም

ወደ ስራ የመመለስ መብት

በውስጥ ደንብ በግልጽ ካልተመለከተ በስተቀር ከህግ ውጭ የተሰናበተ የስራ መሪ ወደ ስራ የመመለስ መብት የለውም
ፍርድ ቤት ከህግ ውጭ ከስራ የተሰናበተን የስራ መሪ ወደ ስራ እንዲመለስ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው የስራ መሪዎችን በተመለከተ በአሰሪው መስሪያ ቤት የአስተዳደር የውስጥ መመሪያ ሲኖርና ይህ መመሪያ ከስርዓቱ ውጭ የተሰናበተ የስራ መሪ ወደ ስራው እንዲመለስ የሚፈቅድ ሲሆን ነው (አመልካች የአርሲ እርሸ ልማት ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ሰለሞን አበበ ታህሳስ 10 ቀን 1998 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 15815 ቅጽ 3)  

የሰበር ችሎት በውሳኔው ላይ እንዳተተው ፍርድ ቤቶች የስራ መሪ ወደ ስራው እንዲመለስ ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት ለውሳኔያቸው መሰረት ያደረጉትንና ይህንኑ የሚቅድ የውስጥ ደንብ ስለመኖሩ በግልጽ ማመልከትና የደንቡን ድንጋጌ መጥቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ለውሳኔያቸው መነሻ የሚሆን ደንብ በሌለ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነው ህግ የፍትሀ ብሔር ህግ ነው
በሰበር ውሳኔው ላይ እንደተመለከተው የስራ መሪ የስራ ውሉ ከህግ ውጭ ያለበቂ ምክንያት የተቋረጠ ቢሆንም እንኳን ካሳ ከማግኘት ባለፈ ወደ ስራ የመመለስ መብት አይኖረውም፡፡ በሰ/መ/ቁ 15815 ተጠሪ ወደ ስራ እንዲመለስ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ተሸሮ ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጠው የሁለት ወር ደመወዝ እንዲሁም ስንብቱ በበቂ ምክንያት ያልተደገፈ በመሆኑ የሶስት ወር ደመወዙ በካሳ መልክ እንዲከፈለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

የውስጥ መተዳደሪ ደንብ ወደ ስራ መመለስን የሚፈቅደ ሲሆን 

የስራ መሪ በፍትሐብሔር ህጉ መሰረት ወደ ስራ የመመለስ መብት ባይኖረውም ከአሰሪው ጋር ያለውን ግንኙነት የሚገዛ መተዳደሪ ደንብ ወደ ስራ የመመለስ መብትን በግልፅ የሚፈቅድ ከሆነ ከህግ ውጭ የመሰናበቱ አንዱ ውጤት ወደ ስራ መመለስ ነው፡፡ (አመልካች የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽ ኮፖሬሽን እና ተጠሪ እነ አቶ በቀለ ኩምሳ (3 ሰዎች) ጥቅምት 10 ቀን 2000 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 21329 ቅጽ 6) በዚህ መዘገብ ጉዳዩ በተጀመረበት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ አመልካች መልስ ሰጭዎችን ከተሰናበቱበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ስራ እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደ ስራ እንዲመልሳቸው ሲሆን ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጉድለት የለበትም በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
አመልካች በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን የክርክሩም ነጥብ ሁለቱም የውሳኔ ነጥቦች ማለትም ውዝፍ ደመወዝ እና ወደ ስራ መመለስን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ በሰበር ያስቀርባል የተባለበት ነጥብ ወደ ስራ መመለስን በተመለከተ ሳይሆን ውዝፍ ደመወዝ ይከፈል በሚል በተሰጠው የውሳኔ ክፍል አግባብነት ለመመርመር ነው፡፡ ወደ ስራ መመለስን በተመለከተ ያስቀርባል ባለመባሉም የስር ፍርድ ቤቶች ይህን አስመልክቶ የሰጡት ውሳኔ መጽናቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ካሳና ሌሎች ክፍያዎች  

ከላይ በሰ/መ/ቁ 21329 የተገለፀው ሁኔታ የስራ መሪው ወደ ስራ እንዲመለስ ከተወሰነ በኃላ ሊከፈለው ስለሚገባ ክፍያ በተመለከተ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በዚሁ መዝገብ ላይ ተጠሪዎች ስራ ካቋረጡበት ጊዜ ጀምሮ ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፈላቸው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተወሰነ ሲሆን ይግባኝ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ አፅንቷል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የሰበር ችሎት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ከሻረ በኃላ የስራ መሪ ከህግ ውጪ ቢሰናበትም ወደ ስራው ሲመለስ ውዝፍ ደመወዝ ሊከፈለው እንደማይገባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ሰበር ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የፍ/ህ/ቁ 2573 ድንጋጌ አፈፃፀምን አስመልክቶ በሰጠው ሀተታ በድንጋጌው መሰረት ካሳ የሚከፈለው ከስራ ለተሰናበተ (እንዲመለስ ላልተወሰነለት) የስራ መሪ እንጂ ወደስራው እንዲመለስ ተወስኖለት ወደስራ ለተመለሰ አይደለም፡፡ ከህግ ውጭ የተሰናበተ የስራ መሪ ወደ ስራ የማይመለስ ከሆነ በዋነኛነት በፍ/ህጉ አንቀጽ 2573 እና 2574(2) መሰረት ከሶስት ወር ደመወዙ የማይበልጥ ካሳ፤ በአንቀጽ 2570(2) መሰረት ከሁለት ወር የማይበልጥ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ እና በተለየ መልኩ ገደብ የሚያደርግ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር ያልተጠቀመበት የዓመት እረፍት በሙሉ በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈለዋል፡፡ (አመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ አቶ አሰበወርቅ ዘገየ ታህሳስ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ. 23609 ቅጽ 7)

5 replies »

  1. don’t understand about my idea. Tolesa is employee of my organization. tolesa is contract base employee in case of more than 65 years old. tolesa from salary he paid Employee Income tax or withholding tax

  2. Abrish,1st of all I thank U so much for Ur I can say continuous or sustainable endeavor U’ve been making to prove or assure an accessibility of golden legal articles,concepts,&…as well as building capacity….

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.