Articles

በአንድ ውሳኔ ሁለት ጊዜ የፍርድ ባለዕዳ! (የሰበር መ/ቁ. 19205)

በአንድ ውሳኔ ሁለት ጊዜ የፍርድ ባለዕዳ! (የሰበር መ/ቁ. 19205)
አመልካች አቶ ሽኩር ሲራጅ
መልስ ሰጪ አቶ ሙላት ካሣ
ሰ/መ/ቁ. 19205
መጋቢት 25/1999 ዓ.ም.
የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ 4

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በፍርድ ቤት የተወሰነበትን ገንዘብ በአፈጻጸም እንዲከፍል አቤቱታ የቀረበበት የፍርድ ባለዕዳ እንደፍርዱ ሊፈጽም ባለመቻሉ ቤቱ ተሽጦ ለዕዳው መክፈያነት እንዲውል አፈጻጸሙን የሚያየው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ሆኖም በትዕዛዙ መሰረት ቤቱ ከመሸጡ በፊት የፍርድ ባለዕዳው 20,000 ብር (ብር ሃያ ሺ) በሞዴል 85 ያስይዛል፡፡ በመቀጠል የፍርድ ባለመብቱ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ እንዲለቀቅለት ለፍርድ ቤቱ አመለከተ፡፡

ገንዘብ በሞዴል 85 ከተያዘ በኋላ አፈጻጸም ቀላልና ያለቀለት ጉዳይ ቢሆንም የፍርድ ባለመብት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት የተያዘውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም፡፡ ምን ተፈጠረ? መጀመሪያ አፈጻጸም የተከፈተበት መዝገብ ጠፋ ተባለ፡፡ ተባለ ብቻ ሳይሆን በቃ ጠፋ! በመዝገብ መጥፋት የትኛውም ፍርድ ቤት ቢሆን ስሙ መነሳት ባይኖርበትም መልካም የፍርድ ቤት አስተዳደር ባለበት ፍርድ ቤት ውስጥ እንኳን ሳይቀር የመዝገብ መጥፋት አንዳንዴ ይከሰታል፡፡ ደግነቱ የጠፋው መዝገብ የአፈጻጸም በመሆኑ ሌላ የአፈጻጸም መዝገብ መክፈት የሚቻል በመሆኑ በፍርድ ባለመብት ላይ ከሚያስከትለው አላስፈላጊ ወጪና መጉላላት በቀር የከፋና የማይመለስ ጉዳት የማድረስ ውጤት የለውም፡፡ እናም በዚህኛው በጠፋው የአፈጻጸም መዝገብ ምትክ በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ ሌላ የአፈጻጸም መዝገብ እንዲከፈት ተደረገ፡፡

ሆኖም ነገሩ በዚህ አላበቃም፡፡ የመዝገቡ መጥፋት ሳያንስ ሌላ ጉድ የሚያሰኝ ነገር ተከሰተ፡፡ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ ጠፋ!! አዲስ በተከፈተው መዝገብ ላይ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ገንዛብ ወጪ ሆኖ ለፍርድ ባለመብት እንዲከፈል ትዕዛዝ ሲሰጥ ትዕዛዙ የደረሰው የፋይናንስ ቢሮ በሞዴል 85 ተይዞ የነበረው ገንዘብ ፍርድ ቤቱ ራሱ በ5/5/89 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ገንዘቡ አቶ ኤልያስ አርአያ ለተባለ ግለሰብ መከፈሉን በመግለፁ ነገሩ ሁሉ “ፍጥጥ ቁልጭ” ሆነ፡፡

እንግዲህ ያለው መፍትሄ ምንድነው? በአንድ በኩል የፍርድ ባለመብት መብቱን በህግ ሀይል ለማስከበር ክስ አቅርቦ ተከራክሮ አሸንፎ ተፈርዶለት የፍርዱን ፍሬ በአፈጻጸም እንዲከፈለው ከችሎቱ ፊት ቆሟል፡፡ በሌላ በኩል የፍርድ ባለዕዳው መጀመሪያ በቀረበበት ክስ በመረታቱ እንደ ፍርዱ ፈጽም ሲባል የሚፈለግበትን ገንዘብ በተለመደው ህጋዊ ስነ ስርዓት መሰረት ‘አድርግ!’ እንደተባለው ገንዘቡን በሞዴል 85 ገቢ አድርጓል፡፡ የፍርድ ባለዕዳ ሆነ የፍርድ ባለገንዘብ በዚህ መዝገብ ላይ በተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚ ስህተትም ሆነ ጥፋት የለባቸውም፡፡ ጥፋቱ ግራ ቀኙን አይቶ ፍትህ በሚያጎናጽፈውና ዳኝነት የሚሰጠው የራሱ የፍርድ ቤቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

በመጨረሻ ወደ ሰበር ያመራው ጉዳይ አመጣጥና የታሪኩ መነሻ ከላይ የተገለጸው ሲሆን የተፈጠረው ክስተት ጉዳዩን ትኩረት የሚስብ አድርጎታል፡፡ የበለጠ ትኩረትን የሚስበው ግን ክስተቱ ሳይሆን ለክስተቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በየደረጃው ጉዳዩ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች መፍትሄ ይሆናል በሚል የሰጡት ትዕዛዝ እና ውሳኔ ነው፡፡
በመጀመሪያ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ ለሌላ ሰው መከፈሉን ያወቀው አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት “የፍርድ ባለዕዳ ገንዘቡን በፍርድ ቤት ካስያዘ በፍርድ ቤት እንደተቀመጠ ስለሚቆጠር የፍርድ ባለመብት ጉዳዩን ተከታትሎ ገንዘቡ ለሌላ 3ኛ ወገን እንዲከፈል ምክንያት የሆነውን አካል ጠይቆ ገንዘቡን ከሚቀበል በቀር ከፍርድ ባለዕዳ ድጋሚ መጠየቅ አይችልም” በማለት ወሰነ፡፡ ይህ ውሳኔ በይግባኝ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተሻረ ሲሆን የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤት መልሶ ሽሮታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲሽር የሰጠው ምክንያት “የፍርድ ባለዕዳ በሞዴል 85 ያስያዘውን ገንዘብ በፍትሃብሄር ስነ ስርዓት ህግ ቁ. 395 መሰረት እንደተከፈል ይቆጠራል” የሚል ሲሆን በይዘቱ አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤት ከሰጠው ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ በመጨረሻ ጉዳዩ ሰበር ደረሰ፡፡ የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክርና የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ጭብጥ በመያዝ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ሰበር ችሎቱ ምላሽ ያሻዋል በሚል የያዘው ጭብጥ “በሞዴል 85 ተይዞ የነበረው ገንዘብ ለሌላ 3ኛ ወገን ቢከፈልም ለአሁን አመልካች እንደተከፈለ መቆጠሩ አግባብ ነው ወይስ አይደለም?” የሚል ነው፡፡ ችሎቱ ለተያዘው ጭብጥ ምላሽ ለመስጠት የራሱን ትንተና ከሰጠ በኋላ በመጨረሻ ላይ የደረሰበት ድምዳሜ የሚከተለው ነበር፡፡

“በፍርድ ቤት ገንዘብ ገቢ በማድረግ እዳ መክፈል አንድ አማራጭ መንገድ ቢሆንም የፍርድ ባለእዳው እዳውን ጨርሷል መባል ያለበት ይህ ሂደት ተጠናቆ የፍርድ ባለመብቱ ገንዘቡን ሲረከብ ሊሆን ይገባል፡፡”

ሰበር ችሎቱ ይህን አቋሙን ሲያጠናክር በተጨማሪነት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

“የፍርድ ባለመብቱ ገንዘቡን ባልተረከበበት ሁኔታ የፍርድ ባለዕዳው እንደከፈለ መቁጠሩ አግባብ አይደለም፡፡ የፍርድ ባለዕዳው ያስያዘው ገንዘብ ፍርዱ ከመፈጸመ በፊት ተመልሶ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተከፈለ ባለዕዳው ገንዘብ እንዳስያዘ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ያስያዘው ገንዘብ ሳይኖር በፍትሃብሔር ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 395(2) መሰረት ፍርዱ እንደተፈጸመ ሊቆጠር አይገባውም፡፡”

በዚሁ መሰረት የሰበር ችሎቱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማጽናት የፍርድ ባለዕዳው ለብር 20,000 (ሃያ ሺ ብር) ተጠያቂ ነው የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ለመሆኑ በሞዴል 85 የተያዘው ገንዘብ እንዴት ለሌላ ግለሰብ ሊከፈል ቻለ? ለዚህ ጥያቄ በሰበር ችሎቱ ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ በዚህ ረገድ በውሳኔው ላይ እንዳሰፈረው በሞዴል 85 ተይዞ የነበረውን ገንዘብ ወሰደ የተባለው ግለሰብ በምን ምክንያት እንደወሰደ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደተለቀቀለት ችሎቱ ከፍርድ ቤቶቹ መዝገብ እንደተረዳ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡ በዚህ መልኩ የተገለጸውና ያልተገለጸው ከተለየ በኋላ ከሁለቱ ውጪ የሆነ ሌላ ፍሬ ነገር ደግሞ በራሱ በችሎቱ ታከለበት፤ እንዲህ የሚል፡፡

“…ይህ ገንዘብ ለአሁን መልስ ሰጪ እዳ መክፈያ ውሎ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል”

ግምት ነው እንግዲህ!
ሲጠቃለል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፤ በፍርድ ቤት ስህተት፤ በፍርድ ቤት ጥፋት ለተከፈለው ገንዘብ ተጠያቂ ነህ የተባለው ፍርድ ቤቱ ሳይሆን የፍርድ ባለዕዳው ነው፡፡ የሰበር ችሎትን ጨምሮ በየደረጃው ጉዳዩን ያዩት ፍርድ ቤቶች በፍትሃብሄር ስነ ስርዓት ህግ ቁ. 395 የህግ ትርጉም ላይ በመሽከርከር ከመሰረታዊው ጥያቄ (በሚያስተዛዝብ መልኩ) ሸሽተዋል፡፡ ፍርድ ቤት የሰው ገንዘብ አላግባብ ለማይገባው ሰው ከከፈለ ዋነኛ እና ብቸኛ ተጠያቂውም ፍርድ ቤት እንጂ የፍ/ባለመብት ሆነ የፍ/ባለዕዳ አይደሉም፡፡

ለመሆኑ የትኛው ይሻል ነበር? ፍርድ ቤቱን ከሃያ ሺ ብር ተጠያቂነት ከለላ መስጠት ወይስ ለፍርድ ቤት ተዓማኒነትና ፍትሐዊነት ዘብ መቆም? ሲሆን ሲሆን መዝገብ ጠፍቶ እያለ፤ በሞዴል 85 የተያዘ ገንዘብ ጠፍቶ እያለ ይህን ጉድ አገር ሳይሰማው በአስተዳደራዊ መንገድ ፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነት ከራሱ በጀት ቀንሶ ጠፋ የተባለውን ገንዘብ መተካት ይጠበቅበት ነበር:: እንግዲህ በሞዴል 85 ገንዘብ የሚያስይዝ የፍርድ ባለዕዳ ዋስትናው ምን ይሆን? ችሎቱ ይህ ጥያቄ አላሳሰበውም፡፡ ሆኖም ከፍርድ ቤት ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው አገልግሎት ለሚጠብቀው ዜጋ ሁሉ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡

21 replies »

 1. በጣም ያሳዝናል እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በመስማታችን፡፡ ፍትህ ፍርድ ብቻ ሳይሆን ርትዕም ነው፡፡ እኔ የማዝነው በዚህ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በዚህ አተረጓጎም ችግር ምክንያት ከዚህ በኋላ የሚከተለው ጥፋት ነው፡፡

 2. ወደ ህገ-መንግሰት አጣሪ ጉባኤ እነድሄድ ንገሩትና….. የሰበሩን ውሳኔ ድብን ያስደርገው

 3. dear aberish
  endet nehe sera endet yezohale 384/96 be wonjele hegu tesherewale endie! be 384/96 kese makerebe yechalale woye

 4. andit mekina beyazat shufer tifat gudat biderisibat.shufarun lemeteyek yeseber wisane yinor yihon????

 5. ምንም አዲስ ነገር የለም በፍርድ ቤት በእኔ ላይ የተፈፀመ ብዙ ብዙ ዘግናኝ በደሎችን ማቅረብ እችላለሁ በሰነድ አስደግፌ .!!!

 6. በመሰረቱ ሰበር ህግ እየተረጎመ ነው ወይስ ህግ እያወጣ? ሕግ በመተርጎም ሰበብ ፍትሃዊ ያልሆነ;አመክንዮን ያልተከተለለ;ገለልተኛ ያልሆነ ህግ እያወጣ ይመስለኛል::

 7. በሞዴል 85 የተየያዘው ገንዘብ በፍ/ባለእዳው እና በፍ/ባለ መብት መካከልባለ ጉዳይ እንደሆነ በሁለቱም ወገን ማለትም በታችኛው ፍ/ቤት እና ፋይናስ መ/ቤት የሚታወቅ በመሆኑ ሁለቱም መጠየቅ ያለባቸው ሲሆን በይበልጥ ፍ/ቤቱ ላይ የፋይልም የመጥፋት ሁኔታ ስላለ ጠበቅ ያለ ምርመራ በማድረግ በጥፋተኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል

 8. Abrish asgerami eyita new yayehew
  gin seber halafinetun judgment debtor yiwused yalew may be this judgment debtor can claim his money back by filing a suit against the one who got the money by mistake bilo yihon ende? Hahhaaaa
  Ewunetim ASASABI new
  tanxs for your deep review

 9. አገልግሎት አሰጣጥና ፍትህ እንዲህም ይሆናል!አገልግሎት አሰጣጥና ፍትህ እንዲህም ይሆናል!

 10. በመሰረቱ ፍ/ቤቶቻችን ላይ ብዙ የአሰራር ግድፈቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ እገምታለሁ ሆኖም ሊገባኝ ያለቻለው ጥፋቱን ለይቶ እርማት የሚወሰድበት ስርዓት ካልተበጀለት ከዚህም የበለጠ ነገር ሊከሰት ስለሚችል ትኩረት ቢሰጠው የተሸለ ነው እያልኩኝ አሁን በተፈጠረው ነገር ላይ ያለኝ አስተያዬት ግን ፈጽሞ የፍ/ባለእዳው ተጠያቂ ሊደረግ አይገባውም ነበረ ምክንያቱም ገንዘቡን በሞዴል 85 ያሲያዘው ፍ/ቤቱ ላይ በመሆኑ አሁንም ቢሆን ይህ ግልሰብ ፍ/ቤቱን ገንዘቤን ይመልስልኝ ብሎ መክሰስ ይገባዋል ብዬ አስባለሁ አመሰግናለሁ

 11. Dear Abrish,

  Greetings!

  It is very nice and beautifully written article showing how much injustice
  is being done by the organs established to serve justice,i.e courts.

  Kind regards,

 12. በጣም አሳፋሪ የፍትሕ አካሉን ተአማኒነት የጣለ ውሣኔ ነው ።ከፈጣሪ በታች ሊታመን አና ለዜጎች ሳያዳላ ለሌላው ፈፃሚ አካልም የሥነምግባርና የሞራል አረአያ እንዲሆን የሚጠበቅበት አካል ይህንን ከፈፀመ ፍትህን የሚሹ ዜጎች ወደየት ይሆን የሚሔዱት?
  የፍትህ አሥተዳደሩ ጉዳዩን በዝርዝር አይቶ ተጠያቂውን አንጥሮ በማውጣት ተገቢውን ቅጣት በማሳረፍ በአደራየተቀመጠውን ገንዘብ ለማይመለከተው የከፈለውን ከራሱ እንዲከፍል ተደርጎ የፍቤቱን ታማኒነት መመለስ ይቻላል። አለበለዚያ ፍትሕ አዲዮስ።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.