Articles

እንግሊዝኛ በሰበር ችሎት

የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች፣ ሐተታዎችና ትንታኔዎች በእንግሊዝኛ ቃላት ተወረዋል፡፡ አንዳንዶቹ አማርኛ ጣል ጣል ያረገባቸው የመመረቂያ ጽሑፍ ይመስላሉ፡፡ በጥቂቶቹ ላይ ደግሞ እንግሊዝኛ አብዛኛውን የውሳኔ ክፍል እንደ አረም ወሮት ሲታይ አማርኛ ለማመሳከሪያ ብቻ የገባ ይመስላል፡፡ ግልፅነት አንኳር ከሆኑት የፍርድ አጻጻፍ ስርዓት መርሆዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህም የቋንቋውን የሰዋሰው ስርዓት ጠብቆ ተከራካሪ ወገኖች በሚገባቸው ቀላል አገላለጽ መጠቀምን ይጠይቃል፡፡ እንግሊዝኛን ከአማርኛ ጋር እያቀላቀሉ ፍርድ መጻፍ ግልፅነትን ከማደፍረስ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ተከራካሪ ወገኖች የአማርኛውን ዓረፍተ ነገር ሰምተው የተረዱት ሀሳብ እንግሊዝኛ ሲታከልበት ያደናግራቸዋል፡፡ ምን ለማለት ይሆን? በሚል ጥርጣሬና ብዥታ በሀሳብ ማዕበል እንዲቃትቱ ያደርጋቸዋል፡፡

እንግሊዝኛ በሰበር ውሳኔዎች ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግልፅ የሆነው የአማርኛ ዓረፍተ ነገር ወይም ሐረግ በቅንፍ የእንግሊዝኛ ፍቺ ይታከበልበታል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የአማርኛ ፍቺ ሳይከተለው እንግሊዝኛው ብቻውን የፍርዱ አካል ሆኖ ይካተታል፡፡ የመጀመሪያው ትርፍ መልዕክት ሁለተኛው ደግሞ ጎዶሎ መልዕክት በመፍጠር በሁለቱም ግልፅነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

የአማርኛውን ሀሳብ ለመግለጽ

በሚከተሉት የሰበር ውሳኔዎች ላይ የእንግሊዝኛው አገላለጽ ትርፍና አላስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በተወሰኑት ላይ የአማርኛውን ሀሳብ አዛብቶታል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 42239 ቅጽ 10

የሰበር ስርዓት አይነተኛ አላማ ከሆኑት አንዱ በአንድ ሀገር ውስጥ ወጥ የሆነ የሕግ አተረጎጎም እና አፈጻጸም (Uniform interpretation and application of the law) መኖሩን ማረጋገጥ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ 45548 ቅጽ 13

ከተያዘው ጉዳይ ጋር ስናያይዝ ሁለቱ ሚስቶች ናቸው እስከ ተባለ ድረስ በሕጉ መንፈስና ሃይል (by operation of the law) ከባለቤታቸው ጋር ያፈሩትን ንብረት ከባለቤታቸው ጋር እኩል የመካፈል መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 35946 ቅጽ 8

ነገር ግን በተያዘው ጉዳይ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ተቃዋሚ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱ ተቃዋሚው በምስክሮች አመሰካከር ላይ የሚያነሳውን ክርክር /The right to confront witnesses/ የሚያጠብና ጉልህ የሆነ የሥነ- ሥርአት ጉድለት መፈጸሙን የሚያመለክት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 08751 ቅጽ 6

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ የተገኘው ማስረጃ የውሣኔውን መሠረታዊ ይዘት የሚነካ /Substantially affects the merit of the case/ መሆን አለበት፡፡

እንግሊዝኛ ፍቺው ሳይጠቀስ

ሰ/መ/ቁ. 65930 ቅጽ 12

በአንድ የፍትሃብሄር ጉዳይ ልዩ አዋቂዎች /Experts/ እና ልዩ አዋቂዎች ያልሆኑ ምስክሮች ቀርበው በተሰሙ ጊዜ “In the civil context … lay evidence should not be preferred to expert evidence with out good reason” የሚለውን የማስረጃ ምዘና መርህ መከተል ይገባል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 11924 ቅጽ 3

የጉዳዩ ጭብጥ እንዲሆን ያስቻለውን ክርክር ያቀረበው አሰሪው ከሆነ ደግሞ ይህን ክርክሩን በቅድሚያ ያስረዳ ዘንድ የግድ ይሆንበታል፡፡ ይህም the one who alleges in the affirmative shall prove it ከሚለው አገላለጽ ጋር የተስማማ ይሆናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 36730 ቅጽ 9

ይህ አተረጓጎም እኛ ብቻ ሣንሆን የዳበረ የሕግ ሥርአት ያላቸው አገሮች “Limitation periods are to be construed strictly so as not to take away the right of the plaintiffs” በሚል መንገድ የሚከተሉት አተረጓጎም ነው፡፡

እነዚህ ውሳኔዎች በችሎት ሲነበቡ ጆሮውን ቢቆርጡት እንግሊዝኛ የማይሰማው ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ዓይኖቹ አምስት ዳኞች ላይ ተተክለው ምን እንደሚያስብ አስቡት፡፡ ምን ይባል ይሆን? እያለ በተደጋጋሚ በየቀጠሮው ሲመላላስ የከረመው ተከራካሪ የውሳኔ ቀን በደስታ ይሁን በሀዘን እፎይታ ይሰማው ዘንድ /ቁርጥን ማወቅ የመሰለ ነገር የለም እንዲሉ/ ተገቢ ቢሆንም እንግሊዝኛ አያውቅምና በውሳኔ ቀን፣ በቁርጡ ቀን ግራ ተጋብቷል፡፡

አማርኛ እና እንግሊዝኛ ቅጂ

የአማርኛና እንግሊዝኛ ቅጂዎችን ጎን ለጎን መጥቀስ አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው በሁለቱም ቋንቋዎች መካከል የይዘት ልዩነት ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ ተገቢ ቢሆንም የይዘት ልዩነት ሳይፈጠር ብሎም የሚነጻጸር ቃል፣ ሐረግ ወይም ድንጋጌ ሳይኖር አማርኛውን በእንግሊዝኛ ማጀብ የበርካታ የሰበር ውሳኔዎች ላይ መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በሰ/መ/ቁ. 74530 ቅጽ 13 እና በሰ/መ/ቁ. 89276 ቅጽ 15 ላይ የሰፈረውን እንመልከት፤

የእንግሊዘኛውን ቅጅ ስንመለከት- Breach of Trust የሚል ርዕሥ ያለው አንቀጽ 675 Whoever, with intent to obtain for himself or to procure for a third person an unjustifiable enrichment, appropriates, or procures for another, takes or causes to be taken, misappropriates, uses to his own benefit or that of a third person, or disposes of for any similar act, in whole or in part, a thing or a sum of money which is the property of another and which has been delivered to him in trust or for a specific purpose, is punishable, according to the circumstances of the case, with simple imprisonment, or with rigorous imprisonment not exceeding five years. በማለት በንዑስ አንቀጽ1 የሚደነግግ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ3 The intent to obtain for himself or to procure for third person an unjustifiable enrichment shall be presumed where the criminal is unable upon call, to produce or repay the thing or sum entrusted, or at the time when he should have returned it or accounted there for. በማለት ይደነግጋል፡፡

“የእንግሊዝኛውን ቅጅ ስንመለከት” በሚል ጀምሮ “በማለት ይደነግጋል” በሚል የተቋጨው የወ/ህ/ቁ. 675 ንዑስ ቁ. 1 እና 3 የእንግሊዝኛ ድንጋጌ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት መዝገቦች ላይ ለማብራሪያነት ሆነ ለትርጉም አላገለገለም፡፡ ይዘቱም ከአማርኛው ጋር አልተራራቀም፡፡

በሁለቱም ቅጂዎች መካከል የሚፈጠር የይዘት ልዩነት

በሁለቱ ቅጂዎች መካከል አለመጣጣም ሲኖር ለእንግሊዝኛው ቅድሚያ መስጠት ተቀባይነት ያለው የህግ አተረጓጎም እየሆነ ነው፡፡ በብዙ ውሳኔዎች ላይ አማርኛው ተገቢውን ቦታ ያጣበት ምክንያት አይገለፅም፡፡

ለአብነት ያክል በሶስት መዝገቦች ላይ የይዘት ልዩነት የተፈታበትን መንገድ እንመልከት፤

ሰ/መ/ቁ. 19258 ቅጽ 7

በንግድ ሕግ ቁጥር 121 ሥር የአክሲዮኖች ድርሻ መዝገብ ምን ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት ከተዘረዘሩት መካከል በንዑስ ቁጥር 1(ለ) “እያንዳንዱ ማህበርተኛ ማግባት ያለበትን የመዋጮዎች ግምት” የሚለው መዋጮው [ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር] ከተቋቋመም በኋላ ወደ ፊት መግባት እንደሚችል በሚገልጽ አኳኋን የተፃፈ ቢሆንም “the value of all contributions made by the members” ከሚለው የእንግሊዝኛ ግልባጭ ጋር አጠቃለን ስናየው መዋጮ አስቀድሞ መግባት ያለበት መሆኑን የሚያመለከት ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 97094 ቅጽ 17

ይህ ከሆነ የዚሁ አንቀጽ 418(3) የአራተኛው ቅጂ ባለይዞታነትን ለማስረዳት የፅሁፍ ማስረጃ መቅረብ እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም የእንግሊዘኛው ቅጂ የስነ- ስርዓት ህጉ ደግሞ ይህንኑ አንቀጽ ሲገልጽ The Claimant or 0bjector Shall adduce evidence to Show that and the date of the attachment he had Some interest in or was possessed of the property attached ይላል፡፡ እንግዲህ ከዚህኛው የእንግሊዘኛ ቅጂ የምንረዳው ማስረጃ በማቅረብ ለአፈጻጸም የቀረበውን ንብረት ማስረዳት እንደሚቻል የሚገልጽ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 38935 ቅጽ 8

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2893 ንዑስ አንቀጽ 3 “ስለሆነም ሻጭ ውሉን እንደውሉ ቃል ለመፈፀም መዘግየቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሉ እንዲፈፀምለት ካልጠየቀ በቀር ገዢው ውሉ በግዴታ እንዲፈፀም የማድረግ መብቱን ያጣል” በማለት ይደነግጋል፡፡ እዚህ ላይ በአማርኛው “መዘግየቱን ከተረዳበት” በሚለው ቁልፍ በእንግሊዘኛው “ascertained” በሚለው ቃል መካከል ልዩነት ያለመሆኑን ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ የድንጋጌው መንፈስ ገዥ በአንድ ዓመት ውስጥ ውሉ እንዲፈፀምለት ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ያለበት ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሠረት ለመፈፀም ፈቃደኛ አለመሆኑን ካረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የእንግሊዘኛውን የቃል አጠቃቀም በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡

በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2 ንዑስ ቁ. 4 እንደተመለከተው ማናቸውም በፌደራል መንግስት የሚወጡ ህጎች በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች መታተም ይኖርባቸዋል፡፡ በአገራችን የእንግሊዝኛው ቅጂ ከአማርኛው ጎን ለጎን የመካተቱ ምክንያት በሌሎች አገራት (ለምሳሌ ካናዳ) ካለው የሁለትዮሽ ቋንቋ (Bijural Legislation) አስፈላጊነት የተለየ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የቅጂዎች አለመጣጣም ሲኖር የምንከተለው የህግ አተረጓጎም ስልት ከእነዚህ አገራት አይመሳሰም፡፡

በካናዳ በፌደራል መንግስት፣ በኩቤክ እና ሌሎች ሁለት ግዛቶች የሚወጡ ህጎች በሙሉ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ መዘጋጀትና መታተም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ህዝቡ ከሁለቱ የአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ቅጂዎች መካከል የይዘት መፋለስ እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ እንደዛም ሆኖ የይዘት ልዩነት ከተከሰተ አንደኛውን ቅጂ ከሌላኛው ማበላለጥ ሳይኖር ህጉ ይተረጎማል፡፡ በቅጂዎቹ መካከል የእኩልነት ሚዛን ለመጠበቅ ሲባል ፍርድ ቤቶች “የጋርዮሽ ትርጓሜ ደንብ” (Shared Meaning Rule) የሚባለውን የአተረጓጎም ስልት ይከተላሉ፡፡ በዚህ ስልት መሰረት ሁለቱም ቋንቋች የሚጋሩት ትርጓሜ ውጤት ይሰጠዋል፡፡

ሁለቱም ቅጂዎች የሚጋሩት ትርጓሜ በማይኖርበት ጊዜ የህጉ ዓይነተኛ ዓላማና ህጉ ሊያሳካ ያሰበው ፖሊሲ አስፈላጊ ከሆነም ውጫዊ ማመሳከሪያዎች (ሐተታ ዘምክንያት፣ በህግ አወጣጥ ሂደት የቀረቡ ማብራሪዎችና ውይይቶች፣ የምሁራን ስራዎች እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ህጎች) ግምት ውስጥ በማስገባት የአንደኛው ቅጂ ትርጓሜ ብቻ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ወደ አገራችን ስንመጣ ህጉ በሁለት ቋንቋች አይዘጋጅም፤ ይታተማል እንጂ፡፡ በህጉ ላይ የሚደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶችና በህግ አውጪው የሚካሄዱ ክርክሮች በሙሉ የሚከናወኑት በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ እንግሊዝኛው አማርኛውን ከመተርጎም (translate) የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ አስፈላጊነቱም በአገሪቱ የህግ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዚኛ ቋንቋ በመሆኑ እግረ መንገድም የውጭ አገር ዜጎች እንዲያውቁት በሚል ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የምንከተለው የአተረጓጎም ስልት በአዋጅ ቁ. 3/1987 አንቀጽ 2 ንዑስ ቁ. 4 ላይ በግልፅ እንደሰፈረው የአማርኛው የበላይነት ደንብ (Paramountcy Rule) ነው፡፡ ስለሆነም በሁለቱም ቅጂዎች መካከል የይዘት ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ የአማርኛው የበላይነት ይኖረዋል፡፡

እዚህ ላይ የአማርኛው ቅጂ ይዘት አንዳችም ስሜት የማይሰጥ ይልቁንም ግራ የሚያጋባ በሚሆንበት ጊዜ እንግሊዝኛው ተፈጻሚ ሊደረግ እንደሚገባ ክርክር ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ክርክሩ በአዋጅ ቁ. 3/1987 በግልጽ አነጋገር ከሰፈረው የአማርኛ የበላይነት ደንብ አንጻር አያስኬድም፡፡ አንድ ህግ ትርጉም የሚያስፈልገው ግልፅነት ሲጎድለው ነው፡፡ ትርጉም በማበጀት ሂደት ውስጥ የተለያዩ የአተረጓጎም ስልቶች ተርጓሚው አካል ለሚደርስበት ድምዳሜ አጋዥ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በዚህ አካሄድ ስሜት አይሰጥም የተባለው ድንጋጌ ጣዕም እንዲሰጥ ሆኖ ይተረጎማል፡፡ ግራ የሚያጋባውም የሚያግባባ ይዘት እንዲላበስ ይደረጋል፡፡ በሂደቱ መጨረሻ ላይ የሚደረስበት ግኝት ከእንግሊዝኛው ቅጂ ይዘት ጋር ሊጣጣም ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ ግን እንግሊዝኛው የበላይነት እንደተሰጠው አያሳይም፡፡ ይልቅስ የትርጉም መገጣጠም ነው የሚፈጠረው፡፡ ስለሆነም የቅጂዎች ልዩነት ሲኖር ትርጉም የሚያስፈልገውና ሊተረጎም የሚገባው የአማርኛው ብቻ ነው፡፡ አማርኛው የበላይነት ይኖረዋል ሲባል ግልፅነት ሲኖረው ብቻ ሳይሆን ግልፅነት ሲጎድለው ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ጉድለቱ ተቃንቶ ሲነበብ የሚኖረው ይዘት የበላይ ሆኖ ውጤት ይሰጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሱት ሶስት መዝገቦች ብሎም በሌሎች መዝገቦች ላይ የእንግሊዝኛው ቅጂ ከአማርኛው የተለየ ይዘት ሲኖረው የእንግሊዝኛው ይዘት ተቀባይነት ያገኛል፡፡ ሆኖም ለዚህ ዓይነቱ የህግ አተረጓጎም የሚሰጥ አሳማኝ የህግ ምክንያት የለም፡፡ በዚህ መልኩ የሚሰጥ ትርጉም በስር ፍ/ቤቶች ላይ አስገዳጅነት አለው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም የሰበር ችሎት “የእንግሊዝኛውን ቅጂ ስንመለከት..” በማለት ውሳኔ እንደሰጠው ሁሉ የስር ፍ/ቤቶችም “የአማርኛውን ቅጂ ስንመለከት…” እያሉ ውሳኔ ከመስጠት የሚከለክላቸው አጥጋቢ ምክንያት አይኖርም፡፡

6 replies »

 1. Really I have a greate appreciation for you!

  2017-01-30 14:38 GMT-08:00 Ethiopian Legal Brief :

  > Abrham Yohannes posted: “የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች፣ ሐተታዎችና ትንታኔዎች በእንግሊዝኛ ቃላት
  > ተወረዋል፡፡ አንዳንዶቹ አማርኛ ጣል ጣል ያረገባቸው የመመረቂያ ጽሑፍ ይመስላሉ፡፡ በጥቂቶቹ ላይ ደግሞ እንግሊዝኛ
  > አብዛኛውን የውሳኔ ክፍል እንደ አረም ወሮት ሲታይ አማርኛ ለማመሳከሪያ ብቻ የገባ ይመስላል፡፡ ግልፅነት አንኳር ከሆኑት
  > የፍርድ አጻጻፍ ስርዓት መርሆዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህም የቋንቋውን የሰዋሰው ስርዓት ጠብቆ ”
  >

 2. I don’t have words to say for your contribution availing legal materials and your valuable comments and views. Great!!

 3. Interesting insight John. You are the first in kind in a legal profession contribution. keep it up!!

 4. እግዜር ይስጥልን፡ አቦ! እንዳንተ በየዘርፉ ያሉትን ያትጋልን!!! በርታ!!!+ ኣክባሪህ

  From: Ethiopian Legal Brief To: etyopya@yahoo.com Sent: Tuesday, January 31, 2017 1:38 AM Subject: [New post] እንግሊዝኛ በሰበር ችሎት #yiv0486714333 a:hover {color:red;}#yiv0486714333 a {text-decoration:none;color:#0088cc;}#yiv0486714333 a.yiv0486714333primaryactionlink:link, #yiv0486714333 a.yiv0486714333primaryactionlink:visited {background-color:#2585B2;color:#fff;}#yiv0486714333 a.yiv0486714333primaryactionlink:hover, #yiv0486714333 a.yiv0486714333primaryactionlink:active {background-color:#11729E;color:#fff;}#yiv0486714333 WordPress.com | Abrham Yohannes posted: “የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች፣ ሐተታዎችና ትንታኔዎች በእንግሊዝኛ ቃላት ተወረዋል፡፡ አንዳንዶቹ አማርኛ ጣል ጣል ያረገባቸው የመመረቂያ ጽሑፍ ይመስላሉ፡፡ በጥቂቶቹ ላይ ደግሞ እንግሊዝኛ አብዛኛውን የውሳኔ ክፍል እንደ አረም ወሮት ሲታይ አማርኛ ለማመሳከሪያ ብቻ የገባ ይመስላል፡፡ ግልፅነት አንኳር ከሆኑት የፍርድ አጻጻፍ ስርዓት መርሆዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህም የቋንቋውን የሰዋሰው ስርዓት ጠብቆ ” | |

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.