Articles

የሰበር ችሎት የህግ ቃላት መፍቻ

የሰበር ችሎት የህግ ቃላት መፍቻ

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጠው የህግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኙ የክልል እና የፌደራል ፍ/ቤቶች የአስገዳጅነት ውጤት እንዲኖረው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 454/1997 ከተደነገገበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ችሎቱ ካከናወናቸው አመርቂ ስራዎች መካከል ለህግ ቃላት ፍቺ ማበጀት አንዱና ዋነኛው ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ፈታኝ በሆነው ህግን የመተርጎም ስራ ውስጥ የቃላትንና ሐረጋትን ትክክለኛ ይዘት መወሰን እና የህግ ዕውቀት የሌለው ሰው በሚገባው ቀላልና አጭር አገላለጽ ትርጓሜያቸውን ማስቀመጥ ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡

አንዳንድ ቃላት ከህግ ጋር በተያያዘ ካልሆነ በቀር በዕለት ተዕለት የማህበረሰቡ የቋንቋ አጠቃቀም ግልጋሎት የላቸውም፡፡ ለምሳሌ ህግ ጠቀስ ባልሆነ ንግግር “እከሊት/ሌ እኮ ዳረገኝ/ችኝ” አንልም፡፡ መዳረግ፣ ዳረጎት ትርጉም የሚኖረው በህግ ግንኙነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ለእነዚህና መሰል ቃላት በቀላሉ የሚገባ ፍቺ ካልተበጀ በስተቀር ህግ አዋቂውና የህግ ዕውቀት በሌለው የህብረተሰብ ክፍል መካከል መግባባት፣ መደማመጥ አይኖርም፡፡ አንዳንዴ በህግ ሙያተኛው ዘንድ ራሱ የህግ ቋንቋ የባቢሎን የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ አንዳንድ ቃላት በህግ አውጪው ሆነ ተርጓሚው ቁርጥ ያለ ትርጓሜ ስለማይሰጣቸው በአጠቃቀም ረገድ ልዩነት ይከሰታል፡፡ ለምሳሌ ከህግ ውጭ፣ ህገ-ወጥ፣ ህግ መጣስ፣ ህግ መተላለፍ፣ ህጋዊ ያልሆነ፣ የህግ መሰረት የሌለው የሚሉ ቃላትና ሐረጋት ጥቅም ላይ የሚውሉበት ሁኔታ ወጥነት አይታይበትም፡፡

ወጥነትን በማስፈን ረገድ ትልቁን ሚና መጫወት ያለባቸው ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ የፍ/ቤቶች የህግ ቃላት ፍቺ በሌላው ዓለም ዘንድ በህግ መዝገበ ቃላት ዝግጅት ውስጥ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ብቻቸውን የዳኝነት መዝገበ ቃላት (Judicial Dictionary) ሆነው ይጠናቀራሉ፡፡ በዚህ ረገድ Stroud’s Judicial Dictionary እና West Publishing Company ያዘጋጀው Judicial and Statutory Definitions of Words and Phrases ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሰበር ችሎት የህግ ቃላት ፍቺዎች ወደፊት የአማርኛ የህግ መዝገበ ቃላት ቢዘጋጅ በዋነኛ ምንጭነት በማገልገል ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡

በግሌ ከለቀምኳቸው ከቅፅ 1 እስከ 19 ድረስ በታተሙት የሰበር ውሳኔዎች (በከፊልም ባልታተሙት) ውስጥ የሚገኙ የህግ ቃላት ፍቺዎች መካከል የከፊሎቹ በዝርዝር ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡ ሁሉም ቃላት በመደበኛ መዝገበ ቃላት እንደምናገኘው ዓይነት ትርጓሜ አልያዙም፡፡ ስለሆነም ከአገባብ በመነሳት ለፍቺ እንዲያመቹ ተደርገው ተሰካክተዋል፡፡ የተወሰኑ ቃላት ደግሞ ህግ አውጭው ትርጓሜያቸውን የወሰናቸው ሆኖም ግን በችሎቱ ተጨማሪ ማብራሪያ የዳበሩ ናቸው፡፡

ሀብትሽ በሀብቴ

ባልና ሚስት ከጋብቻ በፊት ያፈሩትን የግል ንብረት የጋራ ለማድረግ የሚስማሙበት የጋብቻ ውል

“ሀብትሽ ሀብቴ ነው” የሚለው የአማርኛ ሐረግ የሚታወቀው ተጋቢዎች በግል የነበራቸውን ሀብት የጋራ ለማድረግ በማሰብ የሚጠቀሙበት ስለመሆኑ ከነባራዊ ሁኔታ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 98029 ቅጽ 18፣[1] ፍ/ህ/ቁ. 1732፣ 1734-1738

መሠረታዊ የህግ ስህተት

ስህተቱ ሳይታረም በመቅረቱ ምክንያት ውጤቱ ሊለወጥ ያልቻለ ወይም በተከራካሪው ወገን ፍትህ የማግኘት መብት ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ

ሰ/መ/ቁ. 86187 ቅጽ 15፣[2] ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3) ሀ፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1998 አንቀጽ 10፣ 22፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 207

መስቀለኛ ይግባኝ

በይግባኝ ክርክር መልስ ሰጪ የሆነው ወገን በቀጥታ ይግባኝ ሳያቀርብ ተገቢውን ዳኝነት ከፍሎ ይግባኝ ባዩ ባቀረበው 
የይግባኝ ክርክር በመልስ ሰጪነት ከሚያቀርበው ክርክር ጋር በፍርዱ ቅር በመሰኘት የሚያቀርበው ይግባኝ

መስቀለኛ ይግባኝ ስለሚስተናገድበት ስርዓት በሕጉ በተለየ ሁኔታ በግልጽ የተመለከተ ነገር እስከሌለ ድረስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 እና 338 ድንጋጌዎች የተመለከተው የክርክር አመራር ስርዓት ለመስቀለኛ ይግባኝም በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚነት የሚኖረው በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 340(2) በተመለከተው መሰረት መልስ ሰጪው ወገን የሚያቀርበው የይግባኝ ማመልከቻ ግልባጭ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ.ቁ. 338 መሰረት ለይግባኝ ባዩ እንዲደርስ ሊደረግ የሚችለው ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/.ቁ. 337 መሰረት ያልተሰረዘ በሆነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም መልስ ሰጪው ወገን ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ከተሰማ በኋላ የሌላኛውን ወገን ክርክር መስማት ሳያስፈልግ ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሰረት እንዲሰረዝ የሚሰጥ ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 340(2) የተመለከተውን የክርክር አመራር ስርዓት የሚቃረን ነው ለማለት አይቻልም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 92043 ቅጽ 16፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 337፣ 338፣ 340/2/

መቀበር መብት(የ—)

በአንድ ወቅት የአንድ ሃይማኖት ተከታይ የነበረ ሰው ከሃይማኖት ተቋሙ በተሰጠው ልዩ ፈቃድ 
ለስርዓተ ቀብሩ መፈጸሚያ እንዲሆነው በቅጥር ግቢ ውስጥ የመቃብር ቤት አሰርቶ ከመሞቱ በፊት
ሃይማኖቱን ቢቀይር ባሰራው መቃብር ቤት “የመቀበር መብት” አይኖረውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 85979 ቅጽ 15፣[4] ፍ/ህ/ቁ. 1179፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 13፣ 27/1/፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁለተናዊ መግለጫ አንቀጽ 18፣ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 18(1)

መብት መርጋት(የ—)

የመብት መፅናት፣ በህግ ዕውቅና ማግኘትና መረጋገጥ

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1168/1/ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለእጅ /ባለይዞታ/ የሆነ ሰው የዚሁኑ ንብረት ግብር ባለማቋረጥ 15 ዓመት በሥሙ ከከፈለ የዚሁ ሀብት ባለቤት ይሆናል በሚል ደንግጐ ይገኛል፡፡ ሕጉ ይርጋ አዘል ስለሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለእጅ /ባለይዞታ/ የሆነው ሰው የዚህን ንብረት ግብር ባለማቋረጥ ለ15 ዓመት በሥሙ ከከፈለ ሌላ ይገባኛል የሚል ሰው እንዲሰጠው ሊጠይቀው አይችልም፡፡ በሕጉ ለባለይዞታው መብቱ ይረጋለታል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 15631 ቅጽ 3፣[5] ፍ/ህ/ቁ. 1168(1)

መከላከያ ማስፈቀጃ (የ-)

በአጭር ስነ ስርዓት ታይቶ እንዲወሰን ክስ በሚቀርብበት ጊዜ ተከሳሹ ክሱን ለመከላከል እንዲፈቀድለት የሚያቀርበው አቤቱታ

በአጭር ሥነ ሥርዓት እንዲታይ በሚቀርብ ክስ አመራር ሥርዓት ተከሳሽ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በፍ/ቤቱ አግኝቶ የተጠየቀውን ገንዘብ ላለመክፈል በቂ ምክንያት መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው ፍ/ቤቱ ከአጭር ሥነ ሥርዓት ወደ መደበኛ የክርክር ሥነ ሥርዓት ውስጥ በመግባት ግራ ቀኙን በአግባቡ በማስረጃ ካከራከረ በኋላ ነው፡፡

የፈቃድ ጥያቄ ደረጃ ላይ የቼክ ባሕርይ ሳይሆን መታየት ያለበት ተከሳሽ ለመከላከል እንዲፈቀድለት ያቀረበው ምክንያት ፈቃድ የሚያሰጥ መሆን አለመሆኑን ነው፡፡ የፍሬ ነገር ክርክር ከፈቃድ በኋላ የሚታይ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 43315 ያልታተመ፣[6] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 284-286

መድን ጥቅም(የ—)

የመድን ጥቅም /insurable interest/ ያለው ሰው ሲባል በደረሰው አደጋ ወይም ጉዳት በትክክል የተጎዳ ወይም ሊጎዳ የሚችል ሰው ማለት ነው፡፡

መድን ሰጪው ካሣ የሚቀበለው ጉዳት በደረሰበት ወቅት ጉዳት በደረሰበት ንብረት ወይም እቃ ላይ የመድን ጥቅም ያለው ሰው ሲሆን የመድን ጥቅም የሌለው ሰው ካሣ ለመጠየቅ የሚያስችለው የሕግ መሰረት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 47004 ቅጽ 13[7]

ረቂቅ ውል

የተዋዋይ ወገኖች ፊርማ ያላረፈበት ወይም ስምምነታቸው ተሞልቶ ያልተጻፈበት ውል

በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1720 ንኡስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ መሰረት አንድን ውል እንደረቂቅ የሚያስቆጥረው የውሉ በሚገባ አኳኋን በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1726 መሰረት የተስማሙበትን ሞልተው አለመፃፋቸው፣ በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1727/1/ መሰረት ተዋዋዮች ያልፈረሙበት ሲሆንና በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1728 ንኡስ አንቀጽ 1 እና ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት ተዋዋዮቹ ፊርማቸውን ያላስቀመጡ ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ውሉ የተዋዋዮቹን ስምምነት በሚገልጽ መንገድ በጽሐፍ ተዘጋጅቶ ተዋዋዮቹ ከፈረሙበት በኋላ ምስክሮች ሣይፈርሙበት ቢቀሩ የውሉን ሰነድ እንደረቂቅ የሚያስቆጥር ጉድለት እንዳልሆነ ከፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1727 ንኡስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተዋዋዮቹ የተፈረመው ውል ላይ ምስክሮች ሣይፈራረሙ ቢቀሩ ውሉ እንደረቂቅ የሚታይ ሣይሆን ውሉን ውጤት አልባ የሚያደርግ ጉድለት ስለመሆኑ ከፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1727/2/ ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በልዩ ሁኔታ የቤት ሽያጭ ውል በጽሑፍ ሳይይደረግ ቢቀር እንኳን እንደረቂቅ የሚታይ ሣይሆን ውሉ ፈራሽ እንደሚሆን ከፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2877 ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 34803 ቅጽ 8[8]

(የአንድ ዳኛ የልዩነት ሀሳብ)

ባልና ሚስትነት ሁኔታ(የ—)

ሁለት ሰዎች የባልና ሚስትነት ሁኔታ አላቸው የሚባለው ባልና ሚስት ነን እየተባባሉ አብረው 
የሚኖሩ እንደሆነና ቤተዘመዶቻቸውና ሌሎች ሰዎች በዚሁ ሁኔታ መኖራቸውን ሲያረጋግጡላቸው ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 21740 ቅጽ 5፣[9] ፍ/ህ/ቁ. 699፣ 708

ተከሳሽ ከሳሽነት ክስ(የ—)

ተከሳሽ የሆነ ወገን በተከሰሰበት መዝገብ ላይ በተራው በከሳሹ ላይ የሚያቀርበው ክስ

ንብረት ለማስመለስ በቀረበ ክስ ላይ ንብረቱ የሚመለስ ከሆነ ተከሳሽ በንብረቱ ላይ ያፈሰሰውን ሀብት /ያወጣውን ወጪ/ መጠየቅ የሚችለው በተከሰሰበት መዝገብ ተገቢውን ዳኝነት ከፍሎ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ /ወይም ሌላ አዲስ ክስ/ በማቅረብ እንጂ በመከላከያ መልሱ ላይ በሚያቀርበው መከራከሪያ አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 86454 ቅጽ 15[10] ፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 234(1) ረ፣ 215(2)

አመዛኝ ግዴታ

የውል አብዛኛው ወይም መሰረታዊ ግዴታ፣ ዓይነተኛ ግዴታ

ዓይነተኛ የሆነ ወይም መሰረታዊ የውል ግዴታ መጣስ ከሌለ በቀር ተዋዋይ ወገኖች ጥቃቅን ምክንያቶችን ብቻ በመስጠት ውሉ እንዲፈርስ ማድረግ አይችሉም፡፡ የቤት ሽያጭ ውል አመዛኙ ግዴታ በተፈጸመ ጊዜ የተወሰነ ቀሪ ገንዘብ አለመከፈሉ ውሉን ለማፍረስ የሚያበቃ መሠረታዊ የግዴታ መጣስ አልተፈጸመም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 18768 ቅጽ 4፣[11] ሰ/መ/ቁ. 57280 ቅጽ 13፣[12] ፍ/ህ/ቁ. 1771(1)፣ 1785(2)፣ 1789

አር.ቲ.ዲ. (RTD)

የተፋጠነ የወንጀል ክርክር ስርዓት

የጉዳዮችን መራዘም ለማስቀረት የተቀየሰው የተፋጠነ የወንጀል አሰጣጥ (RTD) መሰረታዊ ዓላማ በማስረጃ ደረጃ ውስብስብነት የሌላቸውን ጉዳዮች በቀላሉ ለመወሰን አዲስ አሠራር ለመዘርጋት ማስቻል ከሚሆን በስተቀር በሕገ መንግስቱና በሌሎች ተፈጻሚነት ባላቸው ሕጎች የተጠበቁትን የተከሳሽን መብቶች በሚጎዳ አኳኃን ለመተግበር አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በሕጉ የተጠበቁት መብቶችና የዳኝነት አካሄዶች በሕጉ አግባብ ተተግብረው ዳኝነት ከሚሰጥ በስተቀር አንድ ጉዳይ የተፋጠነ የወንጀል አሰጣጥን (RTD) መሰረት አድርጎ በመቅረቡ ብቻ ቀሪ የሚሆኑ አይደሉም፡፡ የተፋጠነ የወንጀል አሰጣጥ (RTD) አሰራርን መሰረት አድርጎ የሚታይ ጉዳይ የተከሳሹን የመከላከል መብት ለመተው የሚያስችለው ተከሳሹን ይህንኑ መብቱን በማሻያማ አኳኃን የተወው መሆኑን ሲያረጋገጥ ነው፡፡

የተከሳሽ ክስን የመከላከል መብት ሊታለፍ የሚገባው ተከሳሹ መብቱን የማይጠቀምበት መሆኑን በግልፅ ለፍርድ ቤቱ ሲያረጋግጥለት ብቻ ነው፡፡ ተከሳሹ መብቱን ስለመተዉ ባልተረጋገጠበት አግባብ ግን የተከሳሽን የመከላከል መብት ተከሳሹ ትቷል የሚል አገላለፅ በፍርድ ሐተታው ላይ በማስፈር ብቻ ዳኝነት መስጠት ተገቢነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ 100712 ቅጽ 17፣[13] ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 9/4/፣ 13/1/ እና /2/፣ 20/4/

አቤቱታ ፅሁፍ(የ—)

ከሳሽ የሚጠይቀውን ሁሉ ዘርዝሮ የሚገልፅ ፅሁፍ፣ ተከሳሽ የሚሰጠው የመከላከያ ፅሁፍ፣ 
የተከሳሽ ከሳሽ የሚያቀርበው ፅሁፍ፣ የይግባኝ ማቅረቢያ ፅሑፍ ወይም በሌላ አይነት 
ተፅፎ ለፍርድ ቤትና ክስ መነሻ ወይም ለዚሁ መልስ የሚመለከት ማናቸውም ፅሑፍ

የባልና ሚስትነት የምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚቀርብ አቤቱታ፣ ባል ወይም ሚስት ነኝ በማለት አንድ ሰው የሚያቀርበውን ማመልከቻና መግለጫ ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የባልና ሚስትነት ምስክር ወረቀት ለማግኘት በሚቀርብ አቤቱታ ማናቸውም ያገባኛል የሚል ሰው ባል ወይም ሚስት አይደለም በማለት የሚያቀርበውን ተቃውሞና ክርክርን ይጨምራል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 75560 ቅጽ 17፣[14] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. አንቀጽ 80

(የአንድ ዳኛ የልዩነት ሀሣብ)

አንቀጽ ማገጣጠም”

1. የህጉን ዓላማና ግብ በጥልቀት ሳይፈትሹ ላይ ላዩን በማየት መተርጎም
2. የህብረተሰቡን ችግር የማይፈታ በተቃራኒው ችግር የሚፈጥር የህግ አተረጓጎም

“ተያያዣነት ያላቸው ነጥቦች በጥልቀት ሣይታዩ ሶስትና አራት የሚሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች በማገጣጠም የሚሰጥ ውሣኔ ከችግር ፈችነቱ ይልቅ ችግር ፈጣሪነቱ የሚያመዝን እንደሚሆን ለመገንዘብ ይኸ[15] የህግ አተረጓጎም ከተሰጠ በኋላ እየተፈጠረ ያለውን የተመሠቃቀለ ሁኔታ በማየት በቂ ትምህርት ለመውሰድ ይቻላል፡፡”

ሰ/መ/ቁ. 34803 ቅጽ 8[16]

(የአንድ ዳኛ የልዩነት ሀሳብ)

ይርጋ መተው

አንድ ሰው የይርጋ ጊዜውን ትቶታል የሚባለው ለዕዳው ምንጭ የሆነውን ግዴታ በማመን 
አዲስ መተማመኛ ሰነድ የሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ ይርጋን መተው ውጤቱ ይርጋን የሚያቋርጥ ሳይሆን 
አዲስ የይርጋ ጊዜ መቆጠር እንዲጀምር ያደርጋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 90361 ቅጽ 6[17]

ድምር ውጤት የቅጣት አወሳሰን መርህ(የ—)

አንድ ሰው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎችን ከፈጸመና 
ወንጀሎቹ ነጻነትን በሚያሳጣ ቅጣት የሚያስቀጡ ከሆነ ለእያንዳንዱ ወንጀል 
ሊቀጣ የሚገባውን ቅጣት በመደመር በወንጀለኛው ላይ የሚወሰነውን ቅጣት ለማስላት የሚያስችል የቅጣት አወሳሰን መርህ

ሰ/መ/ቁ. 92296 ቅጽ 17፣[18] ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ፣ 61(ሀ)፣ 65፣ 248(ለ)፣ 184(1) ለ፣ 187(1)፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁ. 652/2001 አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 4

ጋብቻ

አንድ ወንድና ሴት ባልና ሚስት ሆነው አንድ ላይ ለመኖር የሚያደርጉት ሕጋዊ ስምምነት

በኢትዮጵያ ጋብቻ በሶስት ዓይነት መንገድ ሊፈፀም እንደሚችል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 1 ያመለክታል፡፡ በነዚህ ስርዓቶች በአንደኛው ጋብቻ ከተፈፀመ በድጋሚ በሌላኛው ስርአት ሊፈጸም የሚገባበት የሕግ ምክንያት አይኖርም፡፡ ድጋሚ ተደርጎ እንኳን ቢገኝ ጋብቻው ፀንቶ የሚቆየው የመጀመሪያው ጋብቻ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በአንድ ወንድና ሴት በመሃከል የሚደረግ ጋብቻ ፈርሶ እንደገና ካልተፈፀመ በቀር ጋብቻ አንድ እንጂ ሁለትና ከዚያ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡

አንድ ወንድ እና ሴት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጋቡ በኋላ በድጋሚ በውጭ አገር ጋብቻ ቢፈጽሙ አንድ ጊዜ ጋብቻ ከተመሰረተ ሁለተኛ ጋበቻ የሚፈፀምበት የሕግ መሠረት የሌለ በመሆኑ ጋብቻው ውጤት የሚኖረው የመጀመሪያው ጋብቻ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 40781 ቅጽ 8[19]

ጳጉሜ

እንደ አስራ ሦስተኛ ወር /እንደ ወር/ የማይቆጠር ጊዜ

ህጉ የይርጋ ጊዜውን በወር ወይም ወራት ከወሰነ ጊዜው የሚቆጠረው በጳጉሜ ውስጥ ያሉት ቀናት ታሳቢ ሳይደረጉ ነው፡፡

በፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 1860(3) በተመለከተው የጊዜ አቆጣጠር ደንብ መሰረት ጳጉሜ እንደወር አይቆጠርም፡፡ ጳጉሜ እንደ አስራ ሦስተኛ ወር የማትቆጠር መሆኑ ከታወቀና የሀገራችን የአንድ አመት ጊዜ 12 ወራቶች ከሆኑ ከዚህ አቆጣጠር ውጭ ያሉት ቀናት በተዋዋይ ወገኖች መካከል መብትም ሆነ ግዴታ ሊፈጥሩ አይገባም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 96458 ቅጽ 16፣[20] ፍ/ህ/ቁ. 1860(3)

ፈቃጅ የውል ህግ ድንጋጌዎች

ሰፊ ነፃነት ለተዋዋይ ወገኖች የሚሰጡ የውል ህግ ድንጋጌዎች

ተዋዋይ ወገኖች ህግ አውጭው በፈቃጅነት የደነገጋቸውን የውል ድንጋጌዎች መከተል ካልፈለጉ የመተው ነፃነት አላቸው፡፡ የፈቃጅ የህግ ድንጋጌዎች አለመሟላት በውሉ ህጋዊነት ላይ የሚያስከትለው ምንም አይነት ተጽዕኖ የለም፡፡ እነዚህ የህግ ድንጋጌዎች በተዋዋይ ወገኖች ፍላጎትና ፈቃድ ተጠቃሽና ተፈፃሚ የሚሆኑ ሲሆኑ ተዋዋይ ወገኖች በዝምታ ያለፉት ነገር ሲኖርና በዚያም ምክንያት ክፍተት ሲፈጠር ክፍተቱን ለመሸፈን ሊጠቀሱና ሊፈፀሙ የሚችሉ የህግ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፈቃጅነት ያላቸው የውል ህግ ድንጋጌዎች የተዋዋዮቹን የመዋዋል ነፃነት (Freedom of contract) በማክበር ህግ አውጭው በአስገዳጅነት ሣይሆን በአማራጭነት የደነገጋቸው ናቸው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 34803 ቅጽ 8[21]

(የአንድ ዳኛ የልዩነት ሀሣብ)

ፍቺ

የሁለት ተጋቢዎችን የትዳር ግንኙት በሕግ መሠረት ማቋረጥ

ጋብቻ ከሚፈርስባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው የፍቺ ውሣኔ ሲሰጥ መሆኑ የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 75/ሐ/ ያመለክታል፡፡ ጋብቻ አንድ እንደሆነ ሁሉ ጋብቻው በፍቺ ሊፈርስ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሁለት የጋበቻ ስርአቶች መከናወናቸውም ሁለት ጊዜ የፍቺ ውሣኔ እንዲሰጥ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ተጋቢዎቹ ግንኙታቸውን ማቋረጥ ከፈለጉ ጋብቻው በሁለት አይነት ስርአት ስለተፈፀመ ግንኙቱን ለማቋረጥ እያንዳንዱን ጋብቻ አስመልክቶ የፍቺ ውሣኔ ሊሰጥ የሚገባው አይሆንም፡፡ የሕጉም አላማ ይህ አይደለም፡፡

አንድ ወንድ እና ሴት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጋቡ በኋላ በድጋሚ በውጭ አገር ጋብቻ መስርተው በዛው አገር በፍርድ ቤት ፍቺ ከፈጸሙ በግራ ቀኙ መሐከል የነበረው ጋብቻ አንድ ብቻ በመሆኑ በውጭ አገር የተሰጠው የፍቺ ውሣኔ ይህን በመካከላቸው የነበረውን አንድ ጋብቻ እንዳፈረሰ ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል፡፡ ግራ ቀኙ ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ ሌላ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መፈፀማቸው ሁለት ትይዩ /Parallel/ ትዳር ውስጥ ነበሩ ሊያሰኛቸው አይችልም፡፡ በመሆኑም በመካከላቸው የነበረው የጋብቻ ግንኙነት አንድ የመሆኑን ያሕል የሚፈርሰውም በአንድ የፍቺ ውሣኔ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 40781 ቅጽ 8[22]

ፍቺ ሁኔታ(የ-)’ (Defacto divorce)

በራሱ ጊዜ የፈረሰ ጋብቻ

ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ በሆነ መንገድ በተግባር የተከናወነ ፍቺ (Defacto divorce)

ሰ/መ/ቁ. 61357 ቅጽ 13[23]

ፖሊስ አባል(የ—)

መሠረታዊ የሆነ የፖሊስ ሙያ ስልጠና ተሰጥቶት በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተቀጥሮ የሚሠራ የፌዴራል ፖሊስ አባል

በሕጉ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ አንድ ሰው የፖሊስ ቅጥር ፎርም የሚል ስያሜ የያዘ ሰነድ ስለሞላ ወይም በቅጥር ፎርሙ በሕጉ አግባብ የሚገኙት ማዕረጎች ተሰጥተውት የጥቅማ ጥቅሙ ተጋሪ መሆን እንደ ሕጉ አነጋገርና ይዘት ፖሊስ ነው ብሎ ትርጉም ለመስጠት አያስችልም፡፡

በኮንስታብል ማእረግ በመለዮ ለባሽነት ቅጥር ፈጽሞ በፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ ሲያገለግል የነበረ ሐኪም ለፖሊስነት የሚያበቁትን የምልመላና የፖሊሳዊ ስልጠና ወስዶ ቃለ መሀላ ፈጽሞ በአባልነት ካልተመዘገበ በስተቀር የፖሊስ አባል አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 99367 ቅጽ 16፣[24] የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 720/2004 አንቀጽ 2(1)፣ 14፣ የፌደራል ፖሊስ  አባላት መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ. 268/2005 አንቀጽ 5(1)፣ 6(1)፣ 7(1)

 

[1] አመልካች ወ/ሮ ልዩሴት ሥዩም እና ተጠሪ አቶ ሸዋፈራ ንጉሴ ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በተጨማሪ አመልካች የወ/ሮ ብሬ አያና ወራሾች /እነ አሰገደች በቀለ/ 4 ሰዎች/ እና ተጠሪዎች እነ ዓለማየሁ አየለ /6 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁ. 36ዐ6ዐ ሚያዝያ 29 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ያልታተመ ይመለከቷል፡፡

[2] አመልካች ዳንኤል ዘሚካኤል እና ተጠሪ ቢሃሪ ባቡላል ሞዲ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] አመልካች ቱሌን ዩኒቨርሲቲ አሲስታንስ ፕሮግራም ኢትዮጵያ እና ተጠሪ ዶ/ር ዮዲት አብርሃም መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.

[4] አመልካች የሐረር (ደ/ሳ) ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እና ተጠሪዎች ወ/ሮ ማንያህልሻል አበራ መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

[5] አመልካቾች እነ የሻረግ መንግሥቱ እና ተጠሪ እማሆይ የሻረግ ፈረደ ታህሣስ 17 ቀን 1998 ዓ.ም.

[6] አመልካች ብራንድ ኒው የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል ኃ/የተ/የግ/ማኀበር እና ተጠሪ አቶ መስፍን ታደሰ ግንቦት 18 ቀን 2001 ዓ.ም.

[7] የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ተጠሪ ባሌ ገጠር ልማት ድርጅት መጋቢት 11 ቀን 2004 ዓ.ም.

[8] አመልካች መ/ር መኳንንት ወረደ እና ተጠሪዎች የእነ መስከረም ዳኛው /4 ሰዎች/ ሞግዚት አቶ ጥጋቡ መኮንን ጥቅምት 27 ቀን 2001 ዓ.ም.

[9] አመልካች ወ/ሮ አስረስ መስፍን እና ተጠሪ ወ/ሮ ውብነሽ ታከለ ጥቅምት 28 ቀን 2000 ዓ.ም.

[10] አመልካቾች እነ ወ/ት ፍሬወይኒ አለም /3 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ አለም መሐሪ ግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም. በተጨማሪ አመልካቾች የእነ ህጻን ሲኢድ ዘውዴ /3 ሰዎች/ ሞግዚት እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ጥሩሰው ሞሳ /9 ሰዎች/ ሰ/መ/ቁ. 94713 ቅጽ 17 መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ይመለከቷል፡፡

[11] አመልካች ወ/ሮ አለሚቱ አግዛቸው እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ዝናሽ ኃይሌ ሚያዝያ 18 ቀን 1999 ዓ.ም.

[12] አመልካች እነ ሴንትራል ቬኑ ኃላፉነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /4 ሰዎች/ እና ተጠሪዎች እነ አቶ ሰለሞን ከተማ /2 ሰዎች/ ጥር 3 ቀን 2004 ዓ.ም.

[13] አመልካች አቶ ሽብሩ ጌቱ ሴንጫ እና ተጠሪ የፌዴራል አቃቤ ሕግ መጋቢት 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

[14] አመልካች ወ/ሮ ኪሮስ ገ/ማሪያም እና ተጠሪ አቶ ገብረ ስላሴ ሃይሌ ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓ.ም.

[15] በሰ/መ/ቁ. 34803 የተሰጠውን የህግ አተረጓም ይጠቅሳል፡፡

[16] አመልካች መ/ር መኳንንት ወረደ እና ተጠሪዎች የእነ መስከረም ዳኛው /4 ሰዎች/ ሞግዚት አቶ ጥጋቡ መኮንን ጥቅምት 27 ቀን 2001 ዓ.ም.

[17] አመልካቾች እነ ወ/ሮ አለዊያ ዑመር /7 ሰዎች/ እና ተጠሪ አቶ ሐሺም ሁሴን የካቲት 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

[18] አመልካቾች እነ አንዱዓለም አራጌ (3 ሰዎች) እና ተጠሪ የፌደራል ዓቃቤ ህግ

[19] አመልካች አቶ ፍቅረሥላሴ ካህሳይ እና ተጠሪ ወ/ሮ ሮማን ታደሰ ሐምሌ 3ዐ ቀን 2001 ዓ.ም.

[20] አመልካች ኢትዮጵያ የርቀት ትምህርት ኮሌጅ እና ተጠሪ ዶ/ር ደሣለኝ ተመስገን ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም.

[21] አመልካች መ/ር መኳንንት ወረደ እና ተጠሪዎች እነ መስከረም ዳኛው /4 ሰዎች/ ጥቅምት 27 ቀን 2001 ዓ.ም.

[22] አመልካች አቶ ፍቅረሥላሴ ካህሳይ እና ተጠሪ ወ/ሮ ሮማን ታደሰ ሐምሌ 3ዐ ቀን 2001 ዓ.ም.

[23] አመልካች አቶ ፍቅሬስላሴ እሽቴ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዋጋዬ ጋይም ሕዲር 22 ቀን 2004 ዓ.ም.

[24] አመልካች ዶ/ር ሕሊና ፍቅሬ እና ተጠሪ የፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም.

3 replies »

 1. Well done. I appreciate your …

  2017-01-31 19:12 GMT+03:00 Ethiopian Legal Brief :

  > Abrham Yohannes posted: “የሰበር ችሎት የህግ ቃላት መፍቻ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት
  > የሚሰጠው የህግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኙ የክልል እና የፌደራል ፍ/ቤቶች የአስገዳጅነት ውጤት እንዲኖረው
  > የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 454/1997 ከተደነገገበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር
  > ዓመታት ውስጥ ችሎቱ ካከናወናቸው አመርቂ ስራዎች መካከል ለህግ ቃላት ፍቺ ማበጀት አን”
  >

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.