Articles

ህገ መንግስታዊ መብት ይቃጠላል?—የዓመት ፈቃድ መተላለፍ ውጤት

አንቀጽ 77 ንዑስ አንቀጽ 5 በአማርኛውና በእንግሊዝኛው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“በዚህ አዋጅ መሰረት የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛው ያልወሰደው የዓመት ፈቃድ ታስቦ በገንዘብ ይከፈለዋል”

A worker whose contract of employment is terminated under this proclamation is entitled to his pay for the leave he has not taken

ድንጋጌውን በአማርኛ ሆነ በእንግሊዘኛ ለሚያነብ ሰው ይዘቱ እንከን የማይወጣለትና ትርጉም የማይሻ ስለመሆኑ መረዳት አይሳነውም፡፡ ሠራተኛው ያልወሰደው የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ሲባል ያልተጠቀመበት፣ ዕረፍት ያልወጣበት፣ ሳይሰጠው የቀረ ፈቃድ ማለት ነው፡፡ ግልጽ ህግ ትርጉም እንደማያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም “ለሠራተኛው የሚከፈለው ያልወሰደው ሳይሆን ከሁለት ዓመት በላይ ያልተላለፈው የዓመት ፈቃድ ነው” ወደ ሚል አቅጣጫውን የሳተ መደምደሚያ የሚያደርሰን ምክንያት የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ የዓመት ፈቃድ ከተላለፈ ወይም ካልተወሰደ “ሠራተኛው ውሉ ሲቋረጥ ሊያገኝ በሚገባው የክፍያ መብት ላይ ገደብ ይጥላል” የምንል ከሆነ ይህንኑ አቋማችንን ከዓመት ፈቃድ አስፈላጊነት፣ ከአሠሪና ሠራተኛ ህጉ መሰረታዊ ዓላማና ተዛማጅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ጋር ልናስታርቀው ይገባል፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ የተላለፈ የዓመት ፈቃድ “ይቃጠላል” የሚል አመለካከት የሕጉን መሠረታዊ ዓላማዎች የሚሸረሽር እንደመሆኑ ከህግና ከስነ-አመክንዮ ሊታረቅ የሚችልበት መንገድ የለም፡፡

የዓመት ፈቃድ የማግኘት መብት በሥራ ውል ሆነ በህብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ እና በመሳሰሉት ሊጠብ ሆነ ሊገደብ የማይችል በህግ የተደነገገ፤ በህገ መንግስቱ የታወቀ አነስተኛ የስራ ሁኔታ ነው፡፡ የዓመት ፈቃድን ጨምሮ ሌሎች አነስተኛ የስራ ሁኔታዎችን በህግ መደንገግ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት አነስተኛ የመደራደር አቅም ያለውን ሠራተኛ ከአሠሪ ኢ-ፍትሐዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ሲባል ነው፡፡ አነስተኛ የስራ ሁኔታዎች ባልተከበሩበት ሁኔታ የኢንዱስትሪ ሰላም ሊሰፍን አይችልም፡፡

ከስራ ሰዓት ጋር በተያያዘ በአሠሪና ሠራተኛ ህጉ የተደነገጉት አነስተኛ የስራ ሁኔታዎች የአጠቃላዩን ሠራተኛ ጤንነት፣ ደህንነት እና የሰውነት ክብር (human dignity) ጥበቃና ከለላ የሚሰጡ መሠረታዊ ደንቦች ናቸው፡፡ ሠራተኛው ሰውነቱ በድካም ዝሎ ጤናው እንዳይቃወስ የተወሰነ የእረፍት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰው በመሆኑ ብቻ ማረፍ አለበት፡፡ የዓመት ፈቃድ መሠረታዊ ዓላማ መቃኘት ያለበትም ከዚህ አንጻር ነው፡፡ በመሰረታዊ ግቡ ላይ የጠራ አቋም ከተያዘ የተዛነፈ የህግ ትርጉም አይፈጠርም፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጥቅምት 30 ቀን 1998 ዓ.ም በሰጠው አንድ ውሳኔ (አመልካች የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ተጠሪ አቶ ጌታሁን ሀይሌ ሰ/መ/ቁ 14057 ቅጽ 3) የዓመት ፈቃድን አስፈላጊነት አስመልክቶ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡

“ሠራተኛው ለስራ ብቂ በሆነ የአዕምሮና የአካል ሁኔታ በስራ ላይ መገኘት ይጠበቅበታል፡፡ የአመት እረፍት ከሚሰጥባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ሰራተኛውን ይህን የሚጠበቅበትን ግዴታ ማሟላት እንዲችል ነው፡፡” (ሰረዝ የተጨመረ)

በሰ/መ/ቁ 27959 (አመልካች የኢት/ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና ተጠሪ አቶ አሊ መሐመድ አሊ ኅዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 6) ላይም ችሎቱ ተመሳሳይ አቋሙን እንደሚከተለው አንጸባርቋል፡፡

“…የሣምንት ወይም የአመት እረፍት የሚሠጠውም ሆነ በቀን የተወሰነ ሰዓት ብቻ እንዲሠራ ሕጉ የሚያስገድደው ሠራተኛው በሥራ የደከመ አእምሮውንና አካሉን በማሣረፍ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነቱን በመጠበቅ የሥራ ውጤታማነቱ እንዲጨምር ለማድረግ ነው፡፡” (ሰረዝ የተጨመረ)

የዓመት ፈቃድን የምንቃኝበት መነጽር ራሱን ችሎ እንደቆመ መብት ሳይሆን ሠራተኛው ግዴታውን እንዲወጣ እንዲሚያግዝ መሳሪያ ከሆነ ወደ ተሳሳተ ንድፈ ሃሳባዊ ጎዳና ማምራታችን አይቀርም፡፡ ከታሪካዊ መሠረቱ ብንነሳ የዓመት ፈቃድን ጨምሮ የስራ ሰዓት እና ሌሎች አነስተኛ የስራ ሁኔታዎችን በሀገራት ህግ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መደንገግ ያስፈለገበት ታሪካዊ መነሻ አሠሪዎች የነጻ ገበያ ሰርዓትን ተገን በማድረግ በሠራተኞች ላይ የሚፈጽሙትን የጉልበት ብዝበዛ እና የመብት ረገጣ ለመግታት እንጂ “ሠራተኛው ለሥራ ብቁ በሆነ የአዕምሮና የአካል ሁኔታ” በስራ ላይ ባለመገኘቱ ምክንያት የአሠሪው ምርታማነት እና ትርፍ ስለቀነሰ ወይም እንዳይቀንስ አሊያም አነስተኛ የስራ ሁኔታዎች ለአሠሪው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ስላላቸው አይደለም፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ ህግ እድገት ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ኢኮኖሚክስንና ሰብዓዊ መብትን መሠረት ያደረጉ ሁለት ግዙፍ የአስተሳሰብ አቅጣጫዎች በተለያየ ደረጃ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ኢኮኖሚክስን መነሻ በማድረግ የተቃኙ አስተሳሰቦች የአሠሪና ሠራተኛ ህግን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት መነጽር ምርታማነትንና የነጻ ገበያ ውድድርን ማዕከል ያደርጋል፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ቀንደኛ አራማጆች ከሆኑት መካከል ኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች (neoclassical economists) አነስተኛ የሥራ ሁኔታዎችን የሚያዩት እንደ ጫና (ሸክም) ነው፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛው እረፍት ሲወጣ አሠሪው ስራ ለማይሰራ ሠራተኛ ደመወዝ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ እረፍት በወጡ ሠራተኞች ምክንያት ትርፍና ምርታማነት እንዳይቀንስ አሠሪው የሚኖረው አማራጭ በስራ ገበታ ያሉትን ሠራተኞች ስራውን ደርበው እንዲሰሩ ማድረግ ወይም አዲስ ምትክ ሠራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት ነው፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ምርታማነትን ይቀንሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋል፡፡

በሁለተኛው አማራጭ አሠሪው ለምትክ ሠራተኞች በሚከፍለው ደመወዝ የተነሳ ለተጨማሪ ወጪ ስለሚዳረግ በሚያመርተው ምርት ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ይገደዳል፡፡ ዋጋ በጨመረ ቁጥር በገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ያቅተዋል፡፡ ስለሆነም በኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አመለካከት በመንግስት የሚደነገጉ አነስተኛ የስራ ሁኔታዎች በምርታማነት ላይ ደንቃራ እንቅፋት በመፍጠር ጤናማ የገበያ ውድድርን ስለሚያዳክሙ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያስከትላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ እነዚህ ኢኮኖሚስቶች የዓመት ፈቃድን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሁኔታዎች አስገዳጅ በሆነ መልኩ በህግ መደንገግ እንደሌለባቸው ይሟገታሉ፡፡

ከእነዚህ ኢኮኖሚስቶች ጎራ የወጡትና ኒው ኢንስቲቱሸናሊስት (new institutionalist) በመባል የሚጠሩት ደግሞ በመነሻው ባይሆንም በመድረሻው ላይ የተለያ አመለካከት አላቸው፡፡ ሀሳባቸው ሲጠቃለል አነስተኛ የሠራተኛ መብቶች ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር አሠሪውን ተጠቃሚ ያደርጉታል የሚል ነው፡፡ ስለሆነም በስራ ሰዓት ላይ የሚደረግ ገደብ ምርታማነትን የሚቀንስ ሳይሆን በተቃራኒው ስለሚጨምር ከዚህ አንጻር ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ለቁፋሮ የተቀጠረ ሠራተኛ በተከታታይ ያለ ዕረፍት ለአስራ ስድስት ሰዓታት ከሚቆፍር ይልቅ በቀን ስምንት ሰዓት ቢቆፍር በስራው የበለጠ ውጤት ያስገኛል፡፡ በቀን፣ በሳምንትና በዓመት የተወሰነ ዕረፍት ቢሰጠው ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ኒው ኢንስቲቱሺናሊስቶች በህግ የሚደነገጉ አነስተኛ የሠራተኛ መብቶች አስፈላጊነት ይቀበላሉ፡፡ አስፈላጊነታቸውን የሚመዝኑት ግን ከምርታማነት ማለትም ለአሠሪው ከሚያስገኙት ጥቅም አንጻር ነው፡፡ ስለሆነም የዓመት ፈቃድ የሚያስፈልግበት ምክንያት ሠራተኛው አካሉ እና አዕምሮው ታድሶ በብቃት ለመስራት እንዲያስችለውና በዚህም ውጤታማነቱ እንዲጨምር ነው፡፡

ከላይኞቹ አስተሳሰቦች በተቃራኒ የሚገኘው ሰብዓዊ መብትን ማዕከል ያደረገ አቀራረብ መነሻውም ሆነ መድረሻው ሠራተኛው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለሠራተኞች መብቶች በህግ ዕውቅና መስጠት የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት ሠራተኛው ሰብዓዊ ክብሩ እና ጤንነቱ በአሠሪው እንዳይጣስ ከለላ ለመስጠት ነው፡፡ አነስተኛ የሥራ ሁኔታዎች የአሠሪውን ምርታማነት አሳደጉም አላሳደጉም ለሠራተኛው በህግ ሊታወቁለት ይገባል፡፡ ሠራተኛው በቀን አስራ ስድስት ሰዓት መስራት የማይኖርበት በስራው ውጤታማ ስለማይሆን አይደለም፡፡ ይልቅስ አስራ ስድስት ሰዓት ማሰራት ኢ-ሰብዓዊ የጉልበት ብዝበዛ በመሆኑ ነው፡፡ በቀን፣ በሳምንት፣ በዓመት ዕረፍት ያስፈለገበት መሰረታዊ ምክንያት የበለጠ ለስራው ብቁ ስለሚያደርገው በዚህም የአሠሪው ምርታማነት እንዲጨምር አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ መሰረታዊ ምክንያቱ ካለዕረፍት ማሰራት የሠራተኛን ሰብዓዊ ክብር የሚንድ ተግባር በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ በሁለተኛው የአስተሳሰብ መስመር አስገዳጅነት ያላቸውን አነስተኛ ሁኔታዎች በመወሰን ከአሠሪ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች ከለላ እና ጥበቃ የሚያደርግ ህግ ሊኖር ይገባል፡፡

ከላይ ወደ ተነሳው ጉዳይ ስንመለስ ፍ/ቤቶቻችን አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት በኒው ኢንስቲቱሺናሊሰቶች የአስተሳሰብ መስመር እየተጓዙ ስለመሆናቸው ለመረዳት አይከብድም፡፡ የዓመት ፈቃድ ከአሠሪው ምርታማነት አንጻር ሲታይ ከሁለት ዓመት በላይ ሲተላለፍ ይቃጠላል ከሚል ልስልስ አቋም ጋር በእርግጥም ይጣጣማል፡፡

ከክፍያ ጋር የዓመት ፈቃድ የማግኘት መብት በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 42 ንዑስ ቁጥር 2 ዕውቅና አግኝቷል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ድንጋጌዎች ለዚህ መብት መከበር ውጤት እንዲሰጡ ተደርገው መተርጎም ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ መስመር የምንጓዝ ከሆነ ከሁለት ዓመት በላይ የተላለፈ የዓመት ፈቃድ ህጋዊ ውጤቱን መወሰን የሚከብድ ስራ አይሆንም፡፡ የዓመት ፈቃድ ከህገ መንግስቱ የመነጨ መብት በመሆኑ አሠሪው ለሠራተኛው ሊሰጠው ይገደዳል፡፡ ከዚህ ግዴታው ሊያመልጥ የሚችልበት ምንም ቀዳዳ የለም፡፡ አዋጁ በመብቱ አፈጻጸም ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀዳዳዎችን በአጥጋቢ መንገድ ደፍኗቸዋል፡፡ አሠሪው የአመት ፈቃድ መውጫ ፕሮግራም አውጥቶ በየዓመቱ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑ (አንቀጽ 78(1) እና (2))፣ በዓመት ፈቃድ ፈንታ ገንዘብ መክፈል መከልከሉ (አንቀጽ 76(2)፣ በማናቸውም ሁኔታ የዓመት ፈቃድ መብትን ለመተው የሚደረግ ስምምነት በህግ ፊት የማይጸናና ዋጋ አልባ መሆኑ (አንቀጽ 76(1) ሁሉም ተጠቃለው ሲነበቡ ህጉ ለዓመት ፈቃድ ጥበቃና ከላለ እንደሰጠ ያረጋግጣሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እንደ መብት ገደብ ተደርጎ እየተተረጎመ ያለው የዓመት ፈቃድን ከሁለት ዓመት በላይ ማስተላለፍን የሚከልክለው የህጉ ድንጋጌ ተቃንቶ ሲነበብ ከገደብ ይልቅ ለሠራተኛው መብት ጥበቃ የሚደርግ ስለመሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ በማስተላለፍ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሠራተኛው በየዓመቱ እረፍት እንዲያገኝ ዋስትና ይሰጣል፡፡ የጊዜ ገደቡ በአሠሪው ላይ ክልከላ በመጣል የሠራተኛውን መብት ያጸናል፡፡ ህጉ አሠሪውን እያለው ያለው “አስገዳጅ የሥራ ሁኔታ ከገጠመህ የዓመት ፈቃድ ማስተላለፍ ትችላለህ፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በላይ ማስተላለፍ አትችልም” ነው፡፡ ግልጽ የሆነው የህጉ መልዕክት በዚህ መልኩ መነበብ ይኖርበታል፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ካስተላለፈውስ? ካስተላላፈ ህግ ጥሷል፡፡ ህግ የጣሰ ሰው ደግሞ ይቀጣል እንጂ አይሸለምም፡፡ ስለሆነም በድርጊቱ ጥፋተኛ ተብሎ በአዋጁ አንቀጽ 184(1) ለ መሰረት እስከ አምስት መቶ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ስምምነት ቢኖርስ? ሠራተኛውና አሠሪው የዓመት ፈቃድ ከሁለት ዓመት በላይ እንዲተላለፍ ቢስማሙ ውጤቱ ምን ይሆናል? ጥያቄውን ለመመለስ መጀመሪያ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የተደረገ የማስተላለፍ ስምምነት ውጤት ምን እንደሆነ መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሠራተኛው የዓመት ፈቃድ ይተላላፍልኝ ብሎ በግልጽ ሲጠይቅና ጥያቄውም በአሠሪው ተቀባይነት ሲያገኝ የዓመት ፈቃድ ወደሚቀጥለው ዓመት ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረግ ስምምነት እንደማንኛውም ውል ህጋዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡

ህጉ ለዚህ ስምምነት ዕውቅና የሚሰጠው እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ብቻ ነው፡፡ ስምምነቱ ቢኖርም የዓመት ፈቃድ ከሁለት ዓመት በላይ ሊተላለፍ አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ከሁለት ዓመት በላይ ለማስተላለፍ ስምምነት ሊደረግ አይችልም፡፡ እንደዛም ሆኖ ቢስማሙስ? በግልጽ በህግ በተከለከለ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ስምምነት ህገ ወጥ ስለሆነ ህጋዊ ውጤት አይኖረውም፡፡ ስለዚህም የዓመት ፈቃድን ወደ ሶስትኛ ዓመት ወይም ከዛ በላይ ለማስተላለፍ ስምምነት ተደርጎ ከሆነ ሠራተኛው በዚህ ስምምነት አይገደድም፡፡ በዚህ መሠረት ፈቃድ የተላለፈበት ዓመት እስስኪደርስ ድረስ መጠበቅ ሳይስፈልገው ወዲያውኑ ህገ ወጥ ስምምነቱ በተደረገበት ዓመት ፈቃድ እንዲሰጠው የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው፡፡ ህጉ የዓመት ፈቃድ ስምምነት እንዳይተላለፍ የከለከለበት ምክንያት በአሠሪው እና በሠራተኛው መካከል ካለው የመደራደር አቅም ልዩነት የተነሳ ጥበቃ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ አነስተኛ የሥራ ሁኔታዎች በስምምነት የሚወሰኑ ጉዳዮች አይደሉምና፡፡

ከዚህ በተቃራኑ “ይቃጠላል” የሚል አቋም እርስ በርሱ የሚጣረስ ውሉ የጠፋበት አቋም እንደሆነ ማየት እንችላለን፡፡ በስምምነት ከሁለት ዓመት በላይ የተላላፈ የዓመት ፈቃድ “ይቃጠላል” ማለት የስምምነቱ ውጤት መብቱን ቀሪ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ መብትን ቀሪ ለማድረግ የሚደረግ ስምምነት መብትን ለመተው የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ ሆኖም ስምምነቱ ዋጋ እንደሌለው የአንቀጽ 76(1) ድንጋጌ እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡

“አንድ ሠራተኛ የዓመት ፈቃድ ለማግኘት ያለውን መብት በማናቸውም ሁኔታ ለመተው የሚያደርገው ስምምነት ውድቅ ይሆናል፡፡”

በማናቸውም ሁኔታ፤ ከሁለት ዓመት በላይ ለማስተላለፍ በመስማማትም ቢሆን፡፡

14 replies »

 1. የኮንትራት ሠራተኛ ወይም የፕሮጄክት ሠራተኛ የዓመት እረፍት አለው ወይ

 2. በበጀት ዓመቱ የሚለው ግን ግልፅነት የጎደለው ወይም ሰራተኛው አንድ ዓመት ካገለገለ በሗላ ይዘት እረፍት ይወስዳል ከሚለው ጋር አይጣረዝም? ስለ በጀት ዓመት የሚያወራው የሲቪል ሰርቫንት አዋጅ ለ መንግስታዊ ላልሆነ ድርጅት ይሰራል?

 3. በቀን ሰራተኛነት የተቀጠረ ሰራተኛ የአመት ፈቃድ የማግኘት መብት አለው

 4. Dear Sir,
  I am following what you are striving to reach the people.
  Thanks a lot, for me you are my teacher in this regard.
  Thanks once again

 5. አብርሃም ለምታደርገው ሁሉ አመሠግናለሁ።
  ጥያቅይ አለኝ፥
  አንድ ሠራተኛ ያዓመት ፍቃዱን የሚወስድበትን ወር ከመረጠ በኃላና ድርጅቱም ፈቃዱን እንዲወስድ ብጽሁፍ
  ካሳወቀው ፤ ካልምንም ምክንያት ሳይወስድ ቢተው፤ ፍቃዱን እንደተወ አይቆጠርም፧

 6. የአመት ፈቃድ በሁለት መንገዶች እንደሚተላለፍ የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ አንቀፅ 79 ንኡስ አንቀፅ 2 እና 3 ያመለክታሉ፡፡ እንግዲህ በነዚህ ሁለት መንገዶች የተላለፈ የአመት ፈቃድ ከሁለት አመት በላይ እንዳይራዘም ንኡስ አንቀፅ 5 ክልከላ አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል አንቀፅ 76 ንኡስ አንቀፅ 2 ስንመለከት በህጉ ከተፈቀደው በስተቀር በአመት ፈቃድ ፈንታ ለሰራተኛው ገንዘብ መክፈልን ይከለክላል፡፡ ይህውም የሰራተኛው የስራ ውል ሲቋረጥና ብዙም በማያጋጥመው አንቀፅ 80 ንኡስ አንቀፅ 2 ምክንያት በገንዘብ ተለውጦ ይከፈላል፡፡ ህጉ ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚያደርገው ሰራተኞች ጊዜያዊ ችግራቸውን በማየት በእረፍት ፈንታ ገንዘብ እንዳይመርጡና በስራ የደከመ አካልና አእምሮአቸውን የባሰ እንዳይጎዱ ነው፡፡ ስለዚህ ሰራተኞች መብታቸውን አውቀው የአመት እረፍታቸው ከሁለት አመት በላይ እንዳይጠራቀም መጠበቅም መጠቀምም አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የስራ ውላችን ሲቋረጥ በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈለናል በሚል እሳቤ ሰራተኞች የአመት እረፍታቸውን የማይወሰዱበት አዝማሚያ ይበዛል፡፡ አሰሪውም ከተሰጠው ጊዜ ገደብ በላይ እረፍትን ማከማቸት እንደሌለበት ሰራተኞችም ከተባለው ጊዜ በላይ ያለእረፍት መስራት እንደሌለባቸው ማወቅና መተግበር አለባቸው፡፡ በህጉ የተቀመጠው የአመት ፈቃድ አሰጣጥ ስርአት ሰራተኞች እረፍታቸውን በወቀቱ እንዲጠቀሙ አሰሪዎችንም ለሰራተኞች እረፍት በጊዜው እንዲሰጡ የሚስገድድም ነው፡፡ የአመት ፈቃድ ዋናው አላማም ማከማቸት ሳይሆን እረፍቱን ተጠቅሞ በታደሰ መንፈስ ስራ ላይ መገኘት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከተቀመጠው ገደብ በላይ የተከማቸ የአመት እረፍት አለመከፈሉ ምክንታዊ ነው እላለሁ፡፡

 7. የአመት ፈቃድ በሁለት መንገዶች እንደሚተላለፍ የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ አንቀፅ 79 ንኡስ አንቀፅ 2 እና 3 ያመለክታሉ፡፡ እንግዲህ በነዚህ ሁለት መንገዶች የተላለፈ የአመት ፈቃድ ከሁለት አመት በላይ እንዳይራዘም ንኡስ አንቀፅ 5 ክልከላ አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል አንቀፅ 76 ንኡስ አንቀፅ 2ን ስንመለከት በህጉ ከተፈቀደው በስተቀር በአመት ፈቃድ ፈንታ ለሰራተኛው ገንዘብ መክፈልን ይከለክላል፡፡ ይህውም የሰራተኛው የስራ ውል ሲቋረጥና ብዙም በማያጋጥመው አንቀፅ 80 ንኡስ አንቀፅ 2 ምክንያት በገንዘብ ተለውጦ ይከፈላል፡፡ ህጉ ይህን ሁሉ ጥበቃ የሚያደርገው ሰራተኞች ጊዜያዊ ችግራቸውን በማየት በእረፍት ፈንታ ገንዘብ እንዳይመርጡና በስራ የደከመ አካልና አእምሮአቸውን የባሰ እንዳይጎዱ ነው፡፡ ስለዚህ ሰራተኞች መብታቸውን አውቀው የአመት እረፍታቸው ከሁለት አመት በላይ እንዳይጠራቀም መጠበቅም መጠቀምም አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የስራ ውላችን ሲቋረጥ በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈለናል በሚል እሳቤ ሰራተኞች የአመት እረፍታቸውን የማይወሰዱበት አዝማሚያ ይበዛል፡፡ አሰሪውም ከተሰጠው ጊዜ ገደብ በላይ እረፍትን ማከማቸት እንደሌለበት ሰራተኞችም ከተባለው ጊዜ በላይ ያለእረፍት መስራት እንደሌለባቸው ማወቅና መተግበር አለባቸው፡፡ በህጉ የተቀመጠው የአመት ፈቃድ አሰጣጥ ስርአት ሰራተኞች እረፍታቸውን በወቀቱ እንዲጠቀሙ አሰሪዎችንም ለሰራተኞች እረፍት በጊዜው እንዲሰጡ የሚስገድድም ነው፡፡ የአመት ፈቃድ ዋናው አላማም ማከማቸት ሳይሆን እረፍቱን ተጠቅሞ በታደሰ መንፈስ ስራ ላይ መገኘት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ከተቀመጠው ገደብ በላይ የተከማቸ የአመት እረፍት አለመከፈሉ ምክንታዊ ነው እላለሁ፡፡

 8. Wow how important this issue is to us poor workers. Let me tell you my own experience. once I was working in a government office. I had 58 days accumulated leave. I asked two days permission that may later be deducted from my leave just to visit. Unfortunately the boss rejected my request. I submitted a written application for 20 days leave for the management committee. after many debates I have been given 5 days. Then I left the work that way. all the rest leave days wasted. I have not used my right because I don’t know the proclamation. So would you please dispatch this lesson.
  Thank you Abrsh.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.