Articles

ማጣቀሻዎች እና ህግ አተረጓጎም

ማጣቀሻዎች እና ህግ አተረጓጎም

በህግ የተደነገጉ ወይም በልማድ የዳበሩ የህግ አተረጓጎም ስልቶችን በመጠቀም አግባብነት ያለውን የህግ ትርጉም ማበጀት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ከተጻፈው ህግ ወጣ ብሎ አግባብነት ያላቸውን ምንጮች መዳሰስ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ውጫዊ ማጣቀሻዎችን /Extrinsic Aids/ የመጠቀም ፍላጎታቸውና ልማዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር አሳይቷል፡፡[1] በስፋት ተቀባይነት ካገኙ ማጣቀሻዎች መካከል ሐተታ ዘምክንያት፣ /Legislative History/ የህጉ ታሪካዊ ዑደት /Legislative Evolution/ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች፣ /International Agreements/ የሌሎች አገራት ህግ እና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች እንዲሁም የምሁራን ስራዎች ሰፊ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡[2]

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በበርካታ መዝገቦች በማጣቀሻ የታገዙ ውሳኔዎች ሰጥቷል፡፡ በእርግጥ ጥቅም ላይ የዋሉበት መንገድ ሲታይ ግልጋሎታቸው እንደ ደጋፊ ማለትም እንደ ማጠናከሪያ ምክንያት ነው፡፡ የሚጠቀሱት ምንጮች አከራካሪ የህግ ጭብጦችን ለመፍታት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አላደረጉም፡፡ ሁሉንም ውሳኔዎች ማካተት ባይቻልም በተወሰኑት ላይ የተደረገው ከፊል ዳሰሳ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

የሌሎች አገራት ተሞክሮና ልምድ

የአገራችን የተጠናቀሩ ህጎች የተለያዩ አገራት ህጎች አሻራ አርፎባቸዋል፡፡ የአንድ የህግ ክፍል ለምሳሌ የውል ህግ ወይም ከውል ውጪ ኃላፊነት ህግ በስራቸው የተካተቱት ዝርዝር ድንጋጌዎች ሳይቀር ምንጫቸውን ለማወቅ አዳጋች አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር ፈታኝ ሁኔታ ሲፈጠር ህጉ የተቀዳበትን አገር የህግ ስርዓትና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በማጣቀሻነት መጠቀም የአገራችንን የህግ አተረጓጎም በእጅጉ ያጎለብተዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ጠለቅ ያለ ፍተሻ የተደረገባቸው መዝገቦች ባይኖሩም በጥቅል አገላለጽ “ሌሎች አገራት” “በርካታ አገራት” “የዳበረ የህግ ስርዓት ያላቸው አገራት” ወዘተ…በሚል ማጣቀስ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ለአብነት ያክል በሁለት መዝገቦች የሰፈረውን ገለጻ እናያለን፡፡

ሰበር መ/ቁ/ 23632 ቅጽ 5 አመልካች ወ/ት ፀዳለ ደምሴ እና ተጠሪ አቶ ክፍሌ ደምሴ ጥቅምት 26 ቀን 2000 ዓ.ም.

እንደሚታወቀው የልጆቻቸውን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ከወላጆቻቸው የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሰው ሊኖር ስለማይችል ሕግ አውጭው 
በመርህ ደረጃ የተቀበለው በመሆኑ በሕይወት ያለው አባት ወይም እናት የሕፃን ልጁ ሞግዚት እና አስተዳዳሪ አድርጎ የመሾሙ አሠራር አገራችንን ጨምሮ 
የበርካታ አገራት ተሞክሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 14981 ቅጽ 12 አመልካች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ተጠሪ ወ/ሮ ሃዋ መሐመድ ግንቦት 04 ቀን 1998 ዓ.ም.

በአገራችን ራሱን የቻለ የማስረጃ ሕግ ባለመኖሩ በዚህ ጉዳይ በቀጥታ ተፈፃሚነት ያለው ድንጋጌ ሊጠቀስ ባይችልም በሌሎች አገሮች ተቀባይነት ካገኘው 
የማስረጃ ሕግ መርህ ግን መረዳት የሚቻለው የባለሙያ አስተያየት ብቻውን ለመቆም የሚችል ወይም በተቃራኒ ማስረጃ ሊስተባበል የማይችል ሳይሆን 
ይልቁንም ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ተገናዝቦ ብቃቱና ተአማኒነቱ ሊመዘን የሚገባ መሆኑን ነው፡፡

በሁለት መዝገቦች ላይ ደግሞ እስራኤል እና ሩስያ በስም ተለይተው ተጠቅሰዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ.112091 ቅጽ 18 አመልካች አንድነት ለፍትህና ለዱሞክራሲ ፓርቲ እና ተጠሪዎች ሠማያዊ ፓርቲ ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

በምርጫ ወቅትና ከተመረጡ በኋላ የፓለቲካ ድርጅቶች አባላት የሚፈጽሙትን የክደት ተግባር ለመቆጣጠርና ለማስቀረት የዳበረ ዲሞክራሲ ሥርዓት ያላቸው 
እንደ እስራኤል ያሉ ሌሎች አገሮች በሕገ መንግስታቸውና በሌሎች የሕግ ማዕቀፍች ከልካይ የሆኑና ይህንን ተግባር በሚፈፅሙ ላይ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ 
የህግ ድንጋጌዎችን በመደንገግ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 44561 ቅጽ 10 አመልካች ወ/ሮ ገነት በላይ እና ተጠሪ አቶ ፈኔት ተክሉ /ሞግዚት/

በርካታ አገሮች ለምሣሌ ሩስያ ከሟች ወደ ወራሾች በውርስ ሊተላለፉ የሚችሉ ንብረቶችና መብቶች በዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡

የምሁራን ስራዎች

ከውል ውጭ የሚደርስ ኃላፊነት ሕጎች ግቦችን በተመለከተ በሶስት መዝገቦች[3] ላይ የፕሮፌሰር ጆርጅ ቺቺኖቪች The Ethiopian law of compensation for damages መጽሐፍ በምንጭነት ተጠቅሷል፡፡

በሶስቱም መዝገቦች ላይ የፕሮፌሰር ጆርጅ ቺቺኖቪች ስራ የተጠቀሰው በተመሳሳይ ነጥብ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም በሰ/መ/ቁ. 35034 ቅጽ 9 የሰፈረውን ገለጻ ማየቱ ይበቃል፡፡

በፍትሐብሔር ሕጋችን ከውል ውጪ አላፊነትን በሚመለከት የተቀመጡ ድንጋጌዎች ጉዳት የደረሰበት ሰው የሚካስበትን ሥርዓት የዘረጉ ናቸው፡፡ 
የእነዚህ ድንጋጌዎች ዓይነተኛ ግባቸውም ጉዳትን የመካስና የጥፋት ባህርይን የመግታት ስለመሆኑ በድንጋጌዎቹ ላይ ማብራሪያ ጽሑፍ ያበረከቱት 
በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ክፍል አስተማሪ የነበሩት ጆርጅ ቺቺኖቪች ገልፀውታል፡፡

በሶስቱም መዝገቦች ላይ የምሁራ ስራ ለውሳኔ መነሻ የሚሆን ግንዛቤ ከማስጨበጥ የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ለአከራካሪ የህግ ጭብጥ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ምሁራዊ ስራ እንደ ህግ ትርጉም ዕውቅና ያገኘው ሮበርት አለን ሴድለር “Ethiopian civil procedure” በሚል ርእስ ያዘጋጁት መጽሐፍ ሲሆን ምሁሩ ለክስ ምክንያት የሰጡት ፍቺ በችሎቱ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ችሎቱ የምሁሩን ስራ በምንጭነት ሲጠቅስ እንዳመለከተው፤

ሮበርት አለን ሴድለር "Ethiopian civil procedure" በሚል ርእስ ባዘጋጁት መጽሀፍ ላይ "የክስ ምክንያት" አለ ብሎ ለመወሰን የሚቻለው በክሱ ላይ የቀረበው 
ነገር ቢረጋገጥ ከሣሹ የጠየቀውን ዳኝነት ለማግኘት ሕግ ይፈቅደሉታል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ሲቻል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡[4]

ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች

ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የህግ ስርዓት በተለይም በፍርድ ቤቶች ዘንድ ያላቸው ቦታ አናሳ ነው፡፡ ለተፈጻሚነታቸው ውስንነት ምክንያት ከሆኑት መካከል ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ እና ሌሎች የክልል የስራ ቋንቋዎች አለመተርጎማቸው እንዲሁም በቀላሉ ሊገኙ አለመቻላቸው በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም በበታች ፍ/ቤቶች የሚስተዋለው የመዝገብ መጨናነቅ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የመጠቀም ልማድ አመንምኖታል፡፡

የሰበር ችሎት የአገሪቱ የመጨረሻው የዳኝነት አካል እንደመሆኑ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ የህግ ጭብጦች አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፋዊ ገፅታቸውን ጭምር በጥልቀት መዳሰስ ይኖርበታል፡፡ ይህም ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በችሎቱ ዘንድ የተለየ ትኩረት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ በአንጻራዊነት ሲታይ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮቹ በሰበር ችሎት ጎልተው አይታዩም፡፡ ስለሆነም በስር ፍ/ቤት ውሳኔዎች ላይ ደብዛቸው የማይታየው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በሰበር ችሎት አልፎ አልፎ መጠቀሳቸው ብዙም የሚገርም አይሆንም፡፡

በህግ አተረጓጎም ሂደት የዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ሚና በተመለከተ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 44101 ቅጽ 10 (አመልካች ሚስስ ፍራንሱዊስ ፖስተር እና ተጠሪ እነ ሚስተር ዱከማን ቬኖ (2 ሰዎች) የካቲት 24 ቀን 2002 ዓ.ም.) በሐተታው እንዳሰመረበት ኢትዮዽያ ያፀደቀቻቸው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል መሆናቸውን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 9(4) ስር የተደነገገ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ በስፋት ሽፋን የተሰጣቸው መሠረታዊ የመብቶችና የነጻነቶች ድንጋጌዎች ሀገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋትና ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም ይኖርባቸዋል፡፡ አለመጣጣሙ የሚፈታበት መንገድ ግን አሁንም ድረስ ቁርጥ ያለ ምላሽ አላገኘም፡፡

በሰበር ችሎት በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች በቁጥር ውስን ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል፤

 • ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት[5]
 • የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብት ቻርተር[6]
 • የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር[7]
 • የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን[8]
 • ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ /The Universal Decleration of Human Rights)[9]

ከእነዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች አከራካሪውን የህግ ጭብጥ ለመፍታት በቀጥታ ተፈጻሚ ተደርገዋል፡፡

 • የዓለም የፖስታ ሕብረት ስምምነት /ኮንቬንሽን/[10]
 • የተባበሩት መንግስታት ቻርተር[11]

[1] Ruth Sullivan, Statutory Interpretation, (2nd, Toronto: Irwin Law Inc., 2007) ገፅ 279

[2] ዝኒ ከማሁ ገፅ 279-302

[3] ሰ/መ/ቁ. 19338 ቅጽ 5 አመልካች ዘይነባ ሐሰን እና ተጠሪ ፍሬው ተካልኝ መጋቢት 2 ቀን 2000 ዓ.ም. ፣ ሰ/መ/ቁ. 34138 ቅጽ 5 አመልካቾች እነ ሲስተር ገነት ጌታቸው /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ ወንድወሰን ኃይሉ ወልደማርያም ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. እና አመልካቾች እነ ወ/ሮ ጥሩቀለም ደሴ እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ ጽጌ ከፍያለው ጥቅም ዐ6 ቀን 2ዐዐ1 ዓ

[4] ሰ/መ/ቁ. 16273 ቅጽ 2 አመልካች የኢት/ቴሌኮሙኒኬሽነ ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ አቶ ገንታ ገምአ ጥቅምት 22/98 ዓ.ም.

[5] ሰ/መ/ቁ. 73514 ቅጽ 14 አመልካች ተስፋዬ ጡምሮ እና ተጠሪ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ህግ ህዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

[6] ሰ/መ/ቁ. 42150 ቅጽ 12 አመልካች የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና ተጠሪዎች እነ አቶ ዲንኤሌ ካሣ /ሃያ ሁለት ሰዎች/ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. በልዩነት ሀሳብ የተጠቀሰ

[7] ሰ/መ/ቁ. 35710 ቅጽ 8 አመልካች ወ/ሮ እፀገነት እሸቱ እና ተጠሪ ወ/ሮ ሰላማዊት ንጉሴ ታህሣሥ 16 ቀን 2001 ዓ.ም.

[8] ዝኒ ከማሁ

[9] ሰ/መ/ቁ 57632 ቅጽ 12 አመልካች ሰማኸኝ በለው እና ተጠሪ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ታህሳስ 25 ቀን 2003 ዓ.ም.

[10] ሰ/መ/ቁ. 24173 ቅጽ 5 አመልካች የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እና ተጠሪ ወ/ሮ አይዳ ሐሰን ጥቅምት 21 ቀን 2000 ዓ.ም.

[11] ሰ/መ/ቁ/ 98541 ቅጽ 17 አመልካች አቶ አለማየሁ ኦላና እና ተጠሪ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

3 replies »

 1. Thanks Abresh dear

  2017-02-06 23:09 GMT+03:00 Ethiopian Legal Brief :

  > Abrham Yohannes posted: “ማጣቀሻዎች እና ህግ አተረጓጎም በህግ የተደነገጉ ወይም በልማድ የዳበሩ የህግ
  > አተረጓጎም ስልቶችን በመጠቀም አግባብነት ያለውን የህግ ትርጉም ማበጀት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ከተጻፈው ህግ
  > ወጣ ብሎ አግባብነት ያላቸውን ምንጮች መዳሰስ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ፍርድ ቤቶች
  > ውጫዊ ማጣቀሻዎችን /Extrinsic Aids/ የመጠቀም ፍላጎታቸውና ልማዳቸው ከጊዜ ወደ ጊ”
  >

 2. thank you for the attachments!!

  2017-02-06 23:09 GMT+03:00 Ethiopian Legal Brief :

  > Abrham Yohannes posted: “ማጣቀሻዎች እና ህግ አተረጓጎም በህግ የተደነገጉ ወይም በልማድ የዳበሩ የህግ
  > አተረጓጎም ስልቶችን በመጠቀም አግባብነት ያለውን የህግ ትርጉም ማበጀት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ከተጻፈው ህግ
  > ወጣ ብሎ አግባብነት ያላቸውን ምንጮች መዳሰስ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ፍርድ ቤቶች
  > ውጫዊ ማጣቀሻዎችን /Extrinsic Aids/ የመጠቀም ፍላጎታቸውና ልማዳቸው ከጊዜ ወደ ጊ”
  >

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.