Articles

የህግ ትርጉም መለወጥ እና ተለውጧል ስለሚባልበት ሁኔታ

የህግ ትርጉም መለወጥ

የህግ ትርጉም አስገዳጅነቱ ለስር ፍ/ቤቶች እንጂ ለራሱ ለችሎቱ አይደለም፡፡ ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ አቋም ሊይዝ ይችላል፡፡ የትርጉም መለወጥ በጠባቡ ካልተተገበረ በስር ፍርድ ቤቶች ዘንድ ሊኖረው የሚገባውን የተሰሚነትና የተቀባይነት ደረጃ በእጅጉ ያሳንሰዋል፡፡ መረሳት የሌለበት ነገር ወጥነት ለበታች ፍ/ቤቶች ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለችሎቱም በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ በአንድ ጭብጥ ላይ በየጊዜው የሚቀያየር የህግ ትርጉም ተቀባይነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ወዲያው ወዲያው አቋም ሲለዋወጥ ፍርድ ቤቶችን ያደናግራል፡፡

በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም መስጠት እጅግ አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች መኖራቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ በአንድ ወቅት የተሰጠ ትርጉም ፀንቶ ሊቆይ ይገባል፡፡ የተለየ ትርጉም ሲያስፈልግ ለውጥ ማድረግ የተፈለገበትን ምክንያት በአዲሱ ውሳኔ ላይ በግልጽ ማመልከትና የበፊቱን ውሳኔ በማያሻማ መልኩ በግልጽ መሻር ያስፈልጋል፡፡ በግልጽ የሚደረግ የትርጉም ለውጥ ያልተገባ ውዥንብርን ያስወግዳል፡፡ በአነስተኛ ወጪ ፍትሕ በቀላሉ እንዲሰፍንም ያደርጋል፡፡

የቀድሞ የህግ ትርጉም በግልጽ ቀሪ ተደርጎ አዲስ አቋም ከተያዘባቸው መዝገቦች መካከል ሰ/መ/ቁ 42239 ቅጽ 10፣[1]  43821 ቅጽ 9[2]  እና 36730 ቅጽ 9[3] ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሰ/መ/ቁ 42239 የግልግል ዳኝነት ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ እንዲሆን ስምምነት ከተደረገ በሰ/ችሎት ሊታይ አይችልም በማለት በሰ/መ/ቁ 21849 ተሰጥቶ የነበረው የህግ ትርጉም ተሽሯል፡፡ በተለወጠው ትርጉም መሰረት የጉባዔው ውሳኔ በሰበር ስልጣን ስር እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ በሰ/መ/ቁ 43821 ዳኝነት እንደገና እንዲታይ ጥያቄው መቅረብ ያለበት ከይግባኝ በፊት እንደሆነ በሰ/መ/ቁ 16624 ተሰጥቶ የነበረው የህግ ትርጉም ተለውጦ ከይግባኝ በኋላም ሊቀርብ እንደሚችል አቋም ተይዞበታል፡፡ የሰመ/ቁ 36730 የይርጋ ማቋረጫ ምክንያትን የሚመለከት ሲሆን ከዚህ ቀደም በሰ/መ/ቁ 16648 ስልጣን ለሌለው የዳኝነት አካል ክስ ማቅረብ የይርጋ ጊዜን እንደማያቋርጥ ተደርጎ ህጉ መተርጎሙ አግባብነት እንደሌለው ታምኖበት የቀድሞው ትርጉም ተቀይሯል፡፡

ሶስቱም መዝገቦች ውሳኔ ያገኙት ሰባት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት ነው፡፡ ይህም የትርጉም ለውጥ ከሚደረግበት ስርዓት ጋር በተያያዘ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ሰባት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የተሰጠ የህግ ትርጉም ከሰባት ያነሱ ለምሳሌ አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት ሊለወጥ ይችላል? የዳኞች ቁጥር እንደተጠበቀ ሆኖ በሙሉ ድምጽ የተሰጠ ውሳኔ በአብላጭ ድምጽ ሊለወጥ የመቻሉ ጉዳይም ሌላው በጥያቄነት መነሳት ያለበት ነው፡፡

የህግ ትርጉም ተለወጠ ስለሚባልበት ሁኔታ

የህግ ትርጉም ተለውጧል የሚባለው በግልፅና በማያወላዳ አነጋገር የቀድሞው ትርጉም ተሽሮ በአዲስ ሲተካ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ለውጥ የተደረገባቸው የሰበር ውሳኔዎች በቁጥር ኢምንት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ግልፅ የሆነ አነጋገር በሌለበት በበርካታ መዝገቦች የሰበር ችሎት አቋሙን ቀይሯል፡፡ በዚህ መልኩ በዝምታ የሚደረግ ለውጥ በቁጥር እየበዙ ለመጡት የሚጋጩ ውሳኔዎች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ የግጭት መኖር ከትርጉም መለወጥና አስገዳጅነት ጋር ተያይዞ መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ለዚህ አንገብጋቢ ጥያቄ አሁንም ድረስ በችሎቱ ሆነ በህግ አውጪው መላ አልተዘየደለትም፡፡

ከግጭት ባሻገር የትርጉም መለወጥ መኖሩን ለመረዳት አደናጋሪ የሆነባቸው ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡ ሁኔታዎቹ የስር ፍ/ቤትን አደናግረው ፍትሕ ፈላጊውን ዜጋ ላልተገባ መንገላታት ዳርገውታል፡፡

ውርስ እንዲጣራ የሚቀርብ አቤቱታ ለማየት የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው ፍርድ ቤቶችን አስመልክቶ በሰበር ችሎት የተፈጠረ ድንገተኛ ስህተት ተጠቃሽ የችግሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሰ/መ/ቁ. 35657 ቅጽ 9[4] እና በሌሎችም መዝገቦች የአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታን ለመቀበልና ለመዳኘት ስልጣን እንደሌላቸው ተመልክቷል፡፡ ሆኖም በሰ/መ/ቁ. 36205 እነዚህ ፍርድ ቤቶች የውርስ ማጣራት አቤቱታ በማስተናገዳቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል የሚል አቤቱታ ለሰበር ችሎት ቀርቦ ችሎቱ ግን አቤቱታውን ባለመቀበል የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡ ይህም በአንድ ጉዳይ ላይ በይዘታቸው የማይጣጣሙ ሁለት ውሳኔዎች መፈጠር ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡

በማይጣጣሙ ውሳኔዎች የተነሳ በአንድ በኩል የአዲስ አበባ ፍ/ቤቶች በሰ/መ/ቁ. 35657 የተሰጠውን የህግ ትርጉም ዋቢ እያደረጉ በሌላ በኩል የፌደራል ፍርድ ቤቶችም በሰ/መ/ቁ. 36205 የተሰጠውን ውሳኔ እያጣቀሱ የውርስ ማጣራት አቤቱታ ለማየት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ተመሳሳይ አቤቱታዎች ወደ ሰበር መጉረፍ ጀመሩ፡፡[5]

በሰ/መ/ቁ. 52530 ቅጽ 11፣ በሰ/መ/ቁ 44750 ያልታተመ፣ በሰ/መ/ቁ. 35657 ቅጽ 9 እና በሌሎች ተመሳሳይ የሰበር ውሳኔዎች ውርስ ማጣራት የፌደራል ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን እንደሆነ ወጥ አቋም ቢያዝበትም ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 36205 ስህተት መስራቱን አምኖ ማስተካከያ ወይም ማሻሻያ አላደረገም፡፡ ከዚያ ይልቅ የሰ/መ/ቁ. 35657 የህግ ትርጉም በሰ/መ/ቁ. 36205 አለመለወጡ በተደጋጋሚ እየተገለጸ የችግሩን ምንጭ ወደ ስር ፍ/ቤቶች የማሸሽ አዝማሚያ ታይቷል፡፡ ችሎቱ ስህተቱን በከፊል በማመን ዕውቅና የሰጠው በሰ/መ/ቁ 52892 ያልታተመ[6] ነው፡፡ በዚህ መዝገብ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ማጽናት በህግ አስገዳጅነት ሆነ በትርጉም መለወጥ ረገድ የሚኖረው ውጤት የችሎቱን ትኩረት ሳያገኝ በዝምታ ታልፏል፡፡ በተቃራኒው በሰ/መ/ቁ. 36205 የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የጸናበት መንገድ ከሌላው ‘ማጽናት’ እንደሚለይ ማስተባበያ የሚመስል ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“…በዚህ ረገድ ይህ ሰበር ችሎት በበርካታ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ለውሳኔው መሠረት ያደረገው የአ/አ ከተማ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን በአዋጅ 408/96 ላይ
 ስለወራሽነት ማስረጃ የመስጠት ሥልጣን በተመለከተ የተደነገገው ቢኖርም የውርስ ማጣራት ተግባር ሊያስከትል ከሚችለው ውስብስብ የሕግ ጥያቄ አንፃር በተለየ
 ሁኔታ መታየት እንዳለበት በማገናዘብ ይህ ጥያቄ በቀረበ ጊዜ መታየት ያለበት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሊሆን ይገባል ሲል በሰበር መ/ቁ 35657 ትርጉም
 ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግን የአ/አ ከተማ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ በሰበር ሰሚ ችሎት አስቀርቦ ካከራከረ በኋላ ስሕተት የለውም ተብሎ የዚህ 
ፍ/ቤት ሰበር መ/ቁ 36205 ውሳኔው መፅናቱ ይታወሳል፡፡ በኋለኛው መዝገብ የተሰጠው ውሳኔ በፎርም ብቻ የፀና በመሆኑ የቀድሞውን የሰበር አቋም የለወጠ 
ስለመሆኑ አመልካች ምክንያት አልተሰጠበትም፡፡” (ሰረዝ የተጨመረ)

በፎርም ብቻ ማጽናት? በፎርም ሆነ ያለ ፎርም ሰበር ያጸናው የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ለተከራካሪ ወገኖች መብት ይፈጥራል፡፡ ግዴታ ያቋቁማል፡፡ በየትኛውም መልኩ ቢሆን የማጽናት ውሳኔ ለስር ፍ/ቤቶች የህግ ትርጉም ይሁንታ ይሰጣል፡፡ ስለሆነም የሰበር ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት እንዳልተሰራ ማረጋገጫ እየሰጠ የስር ፍ/ቤቶች ተቃራኒ አቋም ማንጸባረቅ አይችሉም፡፡ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ቢፈጸምበትም ባይፈጸምበትም ለችሎቱ ውሳኔ መሰረት የሆነውን የህግ ትርጉም አስገዳጅነት አያስቀረውም፡፡

 

[1] አመልካች ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ኃላ.የተ. የግል ኩባንያ እና ተጠሪ ዳኒ ድሪሊንግ ኃላ.የተ. የግል ኩባንያ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም.

[2] አመልካች ወ/ሮ ትርሐስ ፍስሐዬ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዘነበች በሪሁን ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም.

[3] አመልካች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ አቶ አማረ ገላው ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም.

[4] ጥቅምት 13 ቀን 2001 ዓ.ም. አመልካቾች እነ ወ/ሮ እመቤት መክብብ እና ተጠሪ አቶ በድሉ መክብብ

[5] ለምሳሌ ሰ/መ/ቁ. 52530 ቅጽ 11 ኀዳር 14 ቀን 2003 ዓ.ም. አመልካች እነ አቶ ሰናይ ልዑልሰገድ /2 ሰዎች) እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ትእግስት ኃይሌ እና ሰ/መ/ቁ 44750 ያልታተመ አመልካች አቶ መለሰ ደጀኑ እና ተጠሪ ወ/ሮ ወይንሸት ታደሰ መጋቢት 07 ቀን 2002 ዓ.ም. ይመለከቷል፡፡

[6] አመልካች ወ/ሮ ብዙነሽ ዘለቀ እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አሰገደች ጥላሁን /2 ሰዎች/ ሐምሌ 26 ቀን 2002 ዓ.ም.

2 replies »

  1. Dear Abreham,you deserve sincerest thanks as you are doing the most interesting and beneficial task by sharing your knowledge and skills.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.