Articles

ተቃርኖ ንባብ

እጅግ በርካታ በሆኑ የሰበር ውሳኔዎች የህግ ትርጉም ለማበጀት ተመራጭ ሆኖ የተወሰደው የአተረጓጎም ስልት ሁለት እና ከዚያ በላይ ድንጋጌዎችን በማነጻጸር ቅራኔያቸውን መፍታት ነው፡፡ ይህ የህግ አተረጓጎም ዘዴ ልዩ ሕግ ከአጠቃላይ ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል (The special prevails over the general) እየተባለ የሚጠራው ሲሆን ተፈጻሚ ሲደረግ በጠቅላላ ህግ የሚገኘው ድንጋጌ ተትቶ በተቃራኒው በልዩ ህግ ያለው ድንጋጌ ውጤት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ መልኩ ህጉን መተርጎም ትክክል ቢሆንም የትክክለኛነቱ መሰረት የተቃርኖ መኖር ነው፡፡ የሚነጻጸሩት ድንጋጌዎች በውስጣቸው ሊታረቅ የማይችል ተቃርኖ እንዳላቸው ሳይረጋገጥ ልዩ ህግ ከአጠቃላዩ ህግ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ይህ በብዙ የሰበር ውሳኔዎች ላይ የሚንጸባረቅ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ ማዛመድና ማቃረን ከሌለ ህግ መተርጎም የማይቻል ነው የሚመስለው፡፡ አርፈው በሰላም የተቀመጡ፣ ሊጋጩ ቀርቶ የማይነካኩ፣ እርስ በእርስ የማይደራረሱ አንቀጾች በግድ እንዲቃረኑ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ለልዩ ህግ ዕውቅና በመስጠት የማስታረቅ ስራ ይሰራል፡፡ ሆኖም ተቃርኖ በሌለበት ልዩ ሕግ ከአጠቃላይ ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል (The special prevails over the general) የሚለው መርህ ሁለት ያልተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ የመዳከር ያክል ትርጉም የሌለው ህግ የመተርጎም ስራ ነው፡፡

በአስረጂነት በአንድ መዝገብ ላይ በሰበር ችሎት የተሰጠውን የህግ ትርጉም እና አተረጓጎም እናያለን፡፡

በሰ/መ/ቁ. 24703 ቅጽ 7[1] የመድን ገቢው ፊርማ ሳይኖር በአንድ ወገን በመድን ሰጪው ብቻ የተፈረመ የመድን ውል በስር ፍርድ ቤት ዋጋ በማጣቱ ችሎቱ ይህን ስህተት ለማቃናት የፍ/ብ/ሕ/ሥ/ቁ.1725 እና 1727 ድንጋጌዎችን ከን/ህ/ቁ. 657 ጋር በማነጻጸር የተገኘውን ‘ተቃርኖ’ ልዩ ህግ የሆነውን የኋለኛውን ድንጋጌ ተፈጻሚ በማድረግ ‘ለማስታረቅ’ ችሏል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ በችሎቱ በተደረሰበት መደምደሚያ፤

በእርግጥ በፍ/ብሄር ሕጉ በተለየ የአጻጻፍ ሥርአት መደረግ ከሚገባቸው ውሎች መካከል አንዱ የኢንሹራንስ ውል ሲሆን የዚህ ዓይነት ውሎችም በተዋዋይ ወገኖች መፈረም እንዳለባቸውና በሁለት ምስክር ፊትም መረጋገጥ እንዳለባቸው በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1725 እና 1727 ላይ የተመለከተ ቢሆንም የግራ ቀኙን ግንኙነት በተለይ የሚገዛው ልዩ ሕግ የሆነው የንግድ ሕጉ ስለሆነና በጠቅላላ ሕግና በልዩ ሕግ መካከል አለመጣጣም በሚኖርበት ጊዜ ልዩ ሕግ የበላይነት እንደሚኖረው /The special prevails over the general/ ከሕግ አተረጓጐም መርህ መገንዘብ የሚቻል እንደመሆኑ በዚሁ መሰረትም መድን ሰጪው በሚያዘጋጀው ፖሊሲ ላይ መድን ሰጭው መፈረም እንዳለበት በን/ህ/ቁ. 657 ከመመልከቱ በስተቀር መድን ገቢው መፈረም እንደሚገባው ያልተመለከተ በመሆኑ በውል ማቅረቢያ /offer/ ሰነዱ ላይ መድን ገቢው ከፈረመና በፖሊሲው ላይ ደግሞ መድን ሰጭው ከፈረመ በሁለቱ መካከል የመድን ውል ስለመደረጉ በቂ አስረጂ እንደሆነ ከንግድ ህጉ አኳያ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መዝገቦች ችሎቱ የተጠቀመው የህግ አተረጓጎም ስልት እና መጨረሻ የደረሰበት ግኝት (የህግ ትርጉም) ሙሉ በሙሉ ያረፈው በተነጻጸሩት ድንጋጌዎች መካከል ስለመኖሩ ግምት የተወሰደበት ተቃርኖ ነው፡፡ ሆኖም ከችሎቱ ግምት በስተቀር በተጨባጭ ተቃርኖ ስለመከሰቱ አሳማኝ ምክንያት አልቀረበም፡፡ ሊቀርብም አይችልም፡፡ ምክንያቱም በተጠቀሱት ድንጋጌዎች ስምምነት እንጂ ተቃርኖ የለም፡፡ በን/ህ/ቁ. 657 ላይ መድን ገቢው መፈረም እንደሚገባው አለመመልከቱ በጠቅላላ የውል ህግ ድንጋጌዎች (ፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1725 እና 1727) ሊደፈን የሚገባው ክፍተት ነው፡፡ ክፍተት ከተቃርኖ ይለያል፡፡ ለምሳሌ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 ስለ ተዋዋይ ወገኖች ችሎታ አለመመልከቱ ከጠቅላላ የውል ህግ ድንጋጌዎች ጋር አይቃረንም፡፡ ይልቅስ ይጣጣማል፡፡ የጠቅላላ ድንጋጌዎች ዓይነተኛ ፋይዳም ይኸው ነው፤ በሁሉም ልዩ ውሎች ላይ ተፈጻሚነት ያላቸውን የጋራ ደንቦች መወሰን፡፡

የልዩ ህግ የአተረጓጎም መርህ ቁልፍና ቀዳሚ ሁኔታ ከመነሻው ተቃርኖ ስለመኖሩ በጥልቀትና በጥንቃቄ ማጣራት ነው፡፡ ቁም ነገሩ ያለው የሚጣጣመውን ከሚቃረነው አበጥሮ መለየት መቻሉ ላይ ነው፡፡ ይህ አንኳር ነጥብ ችሎቱ ራሱ በሰ/መ/ቁ/ 21448 ቅጽ 4[2] በቀላል ግን ደግሞ ጥልቅ መልዕክት ባዘለ አገላለጽ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡

በተለያዩ የሕጉ ክፍሎች በሚገኙ ድንጋጌዎች መካከል ቅራኔ ከማፈላለግ ይልቅ ተደጋጋፊ ሆነው የጋራ ዓላማ የሚያሳኩበትን የሕግ ትርጉም መሻት የሕግ ባለሙያዎች ሊመርጡት የሚገባ የሕግ አተረጓጎም ዘይቤ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ ሕግ ጠቅላላ ዓላማ ካለው ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል የሚለውን ዘይቤ ተከትሎ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት በእርግጥ የማይታረቅ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ በላቀ የሕግ አውጪው ፍላጐት የተደገፈ ግጭት መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈጋል፡፡

ችሎቱ በዚሁ መዝገብ ላይ የተፈጻሚነት ወሰንኑን አስመልክቶ በአጽንኦት እንዳሰመረበት ልዩ ሕግ ከአጠቃላይ ሕግ ቅድሚያ ይሰጠዋል የሚለው የአተረጓጐም ስልት፤

…ተግባራዊ የሚሆነው ሁለት የህግ ድንጋጌዎች የሚጋጩ ሲሆንና ሁለቱም ድንጋጌዎች አንድ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ብቻ ተፈፃሚነት የሚኖረው የአተረጓጐም ዘይቤ በመሆኑ ይህን ዘይቤ ለመምረጥ በቅድሚያ በሁለቱም ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ መኖሩን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡

ይህ መሪ ሀሳብ አከራካሪ ሆኖ ከተነሳው ጉዳይ አንጻር በአንድ በኩል ልዩ የሆነው የሽያጭ ሕግ የሚፀና ውል እንዲኖር የሽያጭ ውል ጽሑፍ ያስፈልጋል ማለቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላላ ደንቦችን የሚገዛው የውል ሕግ ለሚፀና የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ከጽሑፍ በተጨማሪ አዋዋይ ፊት መከናወኑ አስፈላጊ መሆኑን ከሚገልፀው ጋር ይጋጫል? ሁለቱንም ማጣጣምስ አይቻልም? የሚለው ጥያቄ ተመርምሯል፡፡ በዚህ ረገድ የተደረሰበት ድምዳሜ የሚከተለው ነው፡፡

የሕጉ አንቀጽ 2877 የሽያጭ ውል በጽሑፍ ካልሆነ በቀር አይፀናም ከማለት ሌላ በአዋዋይ ፊት መከናወን አያስፈልግም የሚል ድንጋጌ የለውም፡፡ በመሆኑም የሽያጭ ሕግ በውልም ሕግ ለተጠቀሰው የጽሑፍ አስፈላጊነት አፅንኦት ከመስጠቱ ሌላ የመረጋገጥን (authentication) አስፈላጊነት አላስቀረም በማለት የሁለቱን ድንጋጌዎች ላይ ላዩን የሚታይ ቅራኔ (apparent contradiction) ማስታረቅ ይቻላል፡፡

የችሎቱ ሀሳብ ቅራኔ አለመኖሩን በድፍረት አያስረግጥም፡፡ ቅራኔ ላይና ታች አያውቅም፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የጠቅላላ ህግ ፋይዳ ድግግሞሽን በማስቀረት በእያንዳንዱ ልዩ ህግ ላይ የጋራ ተፈጻሚነት ያላቸውን ደንቦች መወሰን ነው፡፡ ስለሆነም የሕጉ አንቀጽ 2877 ከቁጥር 1723 ጋር ቢነጻጸር ‘ላይ ላዩን የሚታይ’ ቅራኔ እንኳ የለውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 24703 የተጠቀሱት ድንጋጌዎች እንዲሁ የሚስማሙ እንጂ የሚጋጩ አይደሉም፡፡ ለመድገም ያክል የማይቃረኑ ድንጋጌዎችን ማስታረቅ ያልተጣሉ ሰዎችን የማስታረቅ ያክል ትርጉም የሌለው የህግ አተረጓጎም ነው፡፡

[1] አመልካች የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ተጠሪ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብ/ክ/መ/ት ቢሮ ሚያዝያ 9 ቀን 2000 ዓ.ም.

[2] አመልካች ወ/ሮ ጎርፌ ወርቅነህ እና መ/ሰጭዎች እነ ወ/ሮ አበራሽ ደባርጌ ሚያዚያ 30 ቀን 1999 ዓ.ም.

2 replies »

  1. መምህር ኣብረሃም እንደምን ነህ ማንኛውም ህግ ነክ ጉዳዮች ስለምትልክልኝ ምስጋናየ ወደር የለዉም ቀጣይነት እንደሚነሮው ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ፤እንደሚታወቀዉ ኣሁን የኣሰሪና ሰራተኛ ህግ እንደወጣ ግልፅ ነው ፡፡ ስለሆነም በህግ ኣተረጋገም መርህ ከሆኑ ኣንደኛው (The special prevails over the general) መሆኑን ግልፅ ነው ከዚህ ቀደም የተሰጡ የሰበር ውሳኔዎች ኣሁን ከወጣው ኣዲሱ የኣሰሪና ሰራተኛ ህግ ኣለመጣጣም ካለው ወይ የሚጋጭ ከሆነ የሰበር ውሳኔዎቹ ተፈፃሚነት እንደሌላቸው እምነት ኣለኝ ስለዚህ በዚህ ላይ ያለህ ኣስተያየት ብታስቀምጥልኝ፡፡
    ኣመሰግናለሁ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.