Articles

በአሉታ ማመዛዘን -ክፍል 1

ያልተከለከለ ሁሉ የተፈቀደ ነው? ያልተፈቀደ ሁሉ የተከለከለ ነው? ጀማሪ የህግ ተማሪዎች እንዲሁም በህግ ሙያ ያልተሰማሩ ሰዎች በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የጦፈ ክርክር ሲገጥሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በህግ ዘርፍ ተመርቀው የበቁ፣ የነቁ ባለሞያዎች ሳይቀር እይታቸው በጥያቄዎቹ ተጽዕኖ ስር ሲወድቅ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ፍርድ ቤቶች አልተከለከለም/አልተፈቀደም በሚል ዘይቤ እየተመሩ ትዕዛዝ፣ ብይንና ፍርድ የሚሰጡበት አጋጣሚ ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡

‘አልተከለከለም/አልተፈቀደም’ መነሻው ከላቲን አባባሎች (Latin Maxims) ሲሆን ሙሉ አገላለጹ በላቲን Tout ce que la loi ne defend pas est permis በእንግሊዝኛ ደግሞ Everything that the law does not forbid is permitted. የሚል ነው፡፡ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ‘ህጉ ያልከለከለው ሁሉ የተፈቀደ ነው’ የሚል ይዘት አለው፡፡

ይሄንን ጨምሮ በርካታ የላቲን አባባሎች ለአገራችን የህግ ባለሞያዎች እንግዳ አይደሉም፡፡ በህግ ትምህርት፣ መጣጥፎችና ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ የላቲን አባባሎችን መጠቀም ብልህ ባያስብልም ብዙም አያስወቅስም፡፡ በእርግጥ ለማስታወስ ምቹ ከመሆናቸውና እምቅ ሀሳብ በቀላሉ ለማስተላለፍ ካላቸው ሀይል አንጻር በህግ ጽሑፎችና መጻህፍት ላይ እንደ አግባብነቱ ጥቅም ላይ ቢውሉ ፀሐፊን አያስተችም፡፡ ሆኖም ህጉን ለመረዳት ወይም ለማብራራት እንጂ ለመተርጎም ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ በተለያዩ የህግ ስርዓቶች ያሉ የህግ ምሁራን በላቲን አባባሎች ላይ ፊታቸውን ባያዞሩም ብዙም ለህግ ትርጉም ተጠቃሽ መሆናቸውን ይቃወማሉ፡፡

James Fitzjames Stephen የተባለ አንድ የ19ኛ ክፍለ ዘመን የህግ ምሁር እንዳለው፤

It seems to me that legal maxims in general are little more than pert headings of chapters. They are rather minims than maxims, for they give not a particularly great but a particularly small amount of information. As often as not, the exceptions and disqualifications to them are more important than the so-called rules

የላቲን አባባሎችን እያጣቀሱ ህግ መተርጎም በተለይ በሰበር ችሎት ዘንድ በስፋት ተቀባይነት ያገኘ የአተረጓጎም ስልት ሆኗል፡፡ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ከህጉ መንፈስና ይዘት ይልቅ በአባባል መመራት ከህግ አውጪው ሀሳብ በግልጽ የማፈንገጥ ያክል ነው፡፡ በውጤቱም ወጥነትንና ተገማችነትን ያዳክማል፡፡

አልተከለከለም/አልተፈቀደም እያሉ ማመዛዘን በከፊልም ቢሆን ተገቢነት የሚኖረው በአንድ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አጠቃላይ ስለ ህግ ያለንን ግንዛቤ ከማንፀባረቅ የዘለለ በፍርድ ቤት አከራካሪ የሆነ ጭብጥ ለመፍታት የሚያስችል የአተረጓጎም ስልት አይደለም፡፡ ለግለሰባዊ መብቶች ቅድሚያ በሚሰጡ እንደ እንግሊዝ ባሉ አገራት በመርህ ደረጃ በህግ ክልከላ ያልተደረገባቸው ነገሮች ሁሉ ለዜጋው እንደተፈቀዱ ግምት የሚወሰድበት ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ዜጎች ግልፅ ክልከላ በሌለበት ያለ ስጋትና መሸማቀቅ በነፃነት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ‘በግልፅ ያልተፈቀደ ሁሉ የተከለከለ ነው’ የሚለው አመላከከት ተፈጻሚነቱ ከመንግስት ስልጣን ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር አካላት፣ ሹመኖች፣ ባለስልጣናት እና ሌሎች ከህግ የመነጨ ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት በህግ ተለይቶ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ማናቸውንም ውሳኔ ሆነ እርምጃ ከመውሰድ እንደተከለከሉ ግምት ይወሰድበታል፡፡ ይህ አመለካከት የመንግስትን ስልጣን ግልፅ በሆነው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ በመገደብ ለዜጎች መብትና ነፃነት ከለላ ይሰጣል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው ጠቅለል ያለ የህግ አመለካከት ውጪ በፍርድ ቤት በሚካሄድ ሙግት ላይ የስነ-ስርዓት ወይም የስረ-ነገር ህጉን ለመተርምና ተፈጻሚ ለማድረግ አለመከልከል ሆነ አለመፈቀድ አንደኛውን ተከራካሪ ረቺ ሌላኛውን ተረቺ የሚያደርገው አይሆንም፡፡ አልተከለከለም/አልተፈቀደም በህግ አተረጓጎም ውስጥ ሰርጎ ከገባ በአሉታ የማመዛዘን አባዜን ያነግሳል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ዳኞች አንዴ አልተከለከለም አንዴ አልተፈቀደም እያሉ ለውሳኔያቸው ምክንያት በመስጠት ህግን ከመተርጎም ሚናቸው እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ይግባኝ ስለሚባልባቸው/ስለማይባልባቸው ጉዳዮች አስመለክቶ በሁለት ሰበር መዝገቦች የተሰጡ ውሳኔዎችን እናያለን፡፡

በወንጀል ጉዳይ የትዕዛዛ ይግባኝ ስላለመኖሩ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 184 ተደንግጓል፡፡ ይግባኝ የማይባልባቸው ትዕዛዞች በድንጋጌው ስር ተዘርዝረዋል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተተ ጉዳይ ይግባኝ ሊባልበት የሚቻል ስለመሆኑ ለመወሰን አልተፈቀደም/አልተከለከለም በማለት በአሉታ በማመዛዘን ፍሬያማ ውጤት ላይ አንደርስም፡፡ ምክንያቱም አልተከለከለም የሚለውን አባባል ከተከተልን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 184 ስር ያልተዘረዘሩ በርካታ ትዕዛዞች ዋናው ክርክር ከመቋጨቱ በፊት ለይግባኝ ምክንያት ስለሚሆኑ ፍትሕ መፋጠኑ ይቀርና ይንዛዛል፡፡ በተቃራኒው አልተፈቀደም የሚለው አሉታዊ የማመዛዘን ዘይቤ የምንከተል ከሆነ መሰረታዊና ህግ መንግስታዊ መብቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሳይቀር ይግባኝ ስለሚከለከል ፍትሕ ይዛባል፡፡ ሆኖም በአሉታ የማመዛዘን አባዜ የሚያስከትለው ችግር ከፍትሕ መንዛዛትና መጓደል የዘለለ ነው፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በአሉታ የማመዛዘን አባዜ ሲነግስ ፍርድ ቤቶች አልተከለከለም አሊያም አልተፈቀደም በማለት እያማረጡ ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ስልጣን ስለሚኖራቸው ከትክክለኛው ህግን የመተርጎም ሚናቸው እንዲሸሹ ያደርጋቸዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 93234 ቅጽ 17[1] /አልተከለከለም/

በዚህ መዝገብ ዓቃቤ ህግ በሚያቀርበው የክስ ማሻሻል ጥያቄ ይግባኝ እንዳልተከለከለ አቋም ተይዞበታል፡፡ ለዚህ አቋም እንደ ማሳመኛ የተጠቀሰው ምክንያት ህጉ ያልከለከለው መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ሐተታው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት ወይም ነፃ በመልቀቅ ወይም ለጊዜው በመልቀቅ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ በዋናው ጉዳይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ከሚቀርበው ይግባኝ ጋር በአንድነት ካልሆነ በቀር በቁጥር 94 መሰረት ቀጠሮ መስጠትን ወይም አለመስጠትን ወይም በቁጥር 131 መሰረት የሚቀርብ መቃወሚያን ወይም በቁጥር 146 መሰረት ማስረጃን መቀበልን ወይም አለመቀበልን አስመልክቶ በሚሰጡ ትዕዛዞች ላይ ይግባኙን ነጥሎ ማቅረብን የሚከለክል ነው፡፡

እንደሚታየው ይህ ድንጋጌ ትዕዛዞቹ መሰረት የሚያደርጓቸውን ድንጋጌዎች ጭምር በመጥቀስ ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊት የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ የተጣለባቸውን ጉዳዮች የሚዘረዝር ሲሆን ከዝርዝሩ ውስጥ የክስ ማሻሻል ጉዳይም ሆነ የክስ ማሻሻል ጉዳይ መሰረት የሚያደርጋቸውን ቁጥር 118 እና 119 ድንጋጌዎች አልተካተቱም፡፡ ይህም ሕጉ የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ በግልጽ ከጣለባቸው ውጪ በሆኑ የመጨረሻ ትዕዛዝ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ (የክስ ማሻሻል ጥያቄን አልተካተቱም፡፡ ይህም ሕጉ የትዕዛዝ ይግባኝ ክልከላ በግልጽ ከጣለባቸው ውጪ በሆኑ የመጨረሻ ትዕዛዝ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ (የክስ ማሻሻል ጥያቄን ውድቅ ከማድረግ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን ጨምሮ) ከስረ ነገሩ ፍርድ በፊትም ቢሆን ይግባኝ ማቅረብን አስመልክቶ የስነ ስርዓት ሕጉ ያስቀመጠው ክልከላ አለመኖሩን መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ)

ሰ/መ/ቁ 74041 ቅጽ 13[2] /አልተፈቀደም/

ሆኖም የሰበር ችሎት ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 184 እና 185 ጣምራ ንባብ በመነሳት ህጉን እንደተረጎመው ተከሳሽ እንዲከላከል በተሰጠበት ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ማቅረብ አይችልም፡፡ እንደዛም ሆኖ በትዕዛዙ ላይ ይግባኝ ቀርቦ ከፀና ጉዳዩ ከመነሻው ይግባኝ እንዲባልበት በህግ ስላልተፈቀደ በማጽናት የተሰጠው ውሳኔ እንደ መጨረሻ ፍርድ ተቆጥሮ ለሰበር ለመቅረብ ብቁ አይደለም፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የሰፈረው አስተያየት እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነሥርዓት እና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አዋጅ አንድ ሰው በሙስና ወንጀል ተከሶ የኮሚሽኑ አቃቤ ሔግ ማስረጃ እንደክሱ ያስረዳ ስለመሆኑ ፍ/ቤቱ አምኖ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ቢሰጥ በዚህ ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ለማቅረብ የሚቻል ስለመሆኑ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ)

በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 184 እና 185 ስር የተመለከቱት ድንጋጌዎች አንድ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 142(1) መሰረት ብይን ሲሰጥ ይግባኝ ለማቅረብ የሚቻል መሆኑን አያሳዩም፡፡ (ሰረዝ የተጨመረ)

[1] አመልካች የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ እና ተጠሪ አቶ ኃይለኪሮስ ወልደብርሃን ካሕሳይ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

[2] አመልካች እነ አንተነህ መኮንን እና ተጠሪ የፌደራል ስነ-ነግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ሰኔ 4 ቀን 2004 ዓ.ም.

4 replies »

  1. I relly appreciate your recent posts and critical view on the decisions of Court of Cassation.

    Kenenissa Ketema

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.