Site icon Ethiopian Legal Brief

የትምህርት ውሎችና የሠራተኛው የማገልገል ግዴታ

ይህ ጽሑፍ የተወሰደው ‘አሠሪና ሠራተኛ ህግ’ ከሚለው በህትመት ላይ ከሚገኝ መጽሐፌ ሲሆን 
የእንግሊዝኛውን ቅጂ ‘The Duty to serve: Cassation Bench on the legal effects of 
employer-sponsered Tuition Assistance’ በሚል ርዕስ በዚሁ ብሎግ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

‘አሠሪና ሠራተኛ ህግ’ የሚለው መጽሐፍ በተያዘለት የህትመት ሰሌዳ መሰረት ከ20 ቀናት በኋላ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ 
በዚህ አጋጣሚ ከዚህ ቀደም ስለመጽሐፉ በሰጠሁት መግለጫ መነሻነት በስልክና በኢሜይል ‘መጽሀፉ የት ደረሰ?’ እያላችሁ 
ላበረታታችሁኝ ውድ የብሎጉ ጎብኚዎች እጅግ የከበረ ምስጋናዬን ልገለፅ እወዳለው፡፡ 
ስለ መጽሐፉ በተነሳ ቁጥር ስምህን ሳላነሳ የማላልፈው ውድ ወዳጄ ታሪኩ አዱኛ ለህትመቱ እውን መሆን 
ስላደረግካቸው ነገሮች ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለው፡፡

የትምህርት ውሎችና የሠራተኛው የማገልገል ግዴታ

በአዋጁ ላይ የአሠሪና ሠራተኛ ግዴታዎች መዘርዘራቸው ተጨማሪ ግዴታዎችን በስምምነት የመወሰን ነጻነትን አይገድብም፡፡ ከህግና ከህብረት ስምምነት ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ ተጨማሪ ግዴታዎችና ማዕቀቦች በሥራ ውል ወይም በሌላ ተጨማሪ ውል ሊወሰኑ ይችላሉ፡፡ በብዙ አገራት የሥራ ውሉ ጸንቶ ባለበት ጊዜ ሆነ ከተቋረጠ በኋላ ሠራተኛው ከድርጅቱ የንግድ ሥራ ጋር ተመሳሳይነት ባለው ንግድ ውስጥ እንዳይሰማራ ወይም ለሌላ ተወዳዳሪ ድርጅት እንዳይቀጠር አስቀድሞ በውል ማሰር የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ግዴታ የመስራት ነጻነትን የመገደብ ውጤት ስላለው የስምምነቱ ይዘትና የተፈጻሚነት ወሰን የህግ ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡[1]

አሁን ላይ ተፈጻሚነታቸው በሥራ መሪዎች ላይ ብቻ ተወስኖ በቀረው የፍትሐብሔር ህግ ላይ በሚገኙት የሥራ ውል ድንጋጌዎች ላይ ከአሠሪው ጋር ‘መወዳደር እንዳይደረግ የሚደረግ የውል ቃል’ በግልጽ ዕውቅና አግኝቶ ህጋዊ ውጤቱና የተፈጻሚነቱ አድማስ ተለይቶ ቢቀመጥም በዚህ ጉዳይ ላይ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ዝምታን መርጧል፡፡ በእርግጥ በተግባርም ሲታይ እንዲህ ዓይነት ውሎች ብዙም አልተለመዱም፡፡ ለሰበር ችሎት ቀርበው የህግ ትርጉም የተሰጠባቸው ክርክሮችም የሉም፡፡ ከተጨማሪ ውሎች ከሚመነጩ ግዴታዎች መካከል በሰበር ችሎት የህግ ትርጉም የሚፈልግ ጉዳይ ሆኖ በተደጋጋሚ እየቀረበ ያለው በትምህርትና ስልጠና ውሎች በሠራተኛው ላይ የሚጣለው የማገልገል ግዴታ ነው፡፡ ይህን ግዴታ የሚፈጥሩትና አፈጻጸሙን የሚወስኑት ውሎች በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ሆነ በሌላ ህግ ቁጥጥር አይደረግባቸውም፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ የህጉን ትኩረት የሚሻ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ የሰበር ችሎትን አቋም ማስቃኘቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ግልጽ ስምምነት ስለማስፈለጉ

የማገልገል ግዴታ ከሥራ ውል በቀጥታ አይመነጭም፡፡ የትምህርት ወጪ መሸፈኑ ብቻውን የማገልገል ግዴታን አይፈጥርም፡፡ ሠራተኛው በአሠሪው የተሸፈነለትን የትምህርት ወጪ መልሶ ሊከፍል ካልከፈለ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ አሠሪውን ሊያገለግል ግዴታ የሚገባበት ተጨማሪ ውል ያስፈልጋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ውል የአሠሪው ዋነኛ ግዴታ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መሸፈን ነው፡፡ የትምህርት ዕድሉ በአሠሪው በኩል ከተገኘ ወጪው በሶስተኛ ወገን መሸፈኑ ውሉን የጸና ከመሆን አያስቀረውም፡፡ በአመልካች ወ/ሮ ሃርሴማ ሰለሞን እና መልስ ሰጪ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (ኅዳር 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ. 33473 ቅጽ 8) መካከል በነበረው ክርክር የኔዘርላንድስ መንግስት በሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል መልስ ሰጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሚ እንዲሆን ከትምህርት ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ መነሻነት አመልካች እንዲወዳደሩ ተደርጎ የትምህርት ዕድሉን አግኝተዋል፡፡ አመልካች በዕድሉ ለመጠቀም እንዲችሉ መልስ ሰጭ የዕረፍት ፈቃድ የሰጣቸው ሲሆን የድጋፍ ደብዳቤም ጽፎላቸዋል፡፡

ከፍቃዱና ከደብዳቤው አስቀድሞ አመልካች ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ ለአራት ዓመታት መልስ ሰጭን ለማገልገል ግዴታ ገብተዋል፡፡ ግዴታቸውን ባይወጡ ደግሞ መልስ ሰጭ ወይም ሶስተኛው ወገን የከፈለላቸውን የትምህርት ወጪ ለመክፈል ተስማምተዋል፡፡ አመልካች በሰበር አቤቱታቸው ላይ “ውሉን ልፈርም የቻልኩት ካልፈረምሽ የዓመት ፈቃድና የድጋፍ ደብዳቤ አይሰጥሽም ስለተባልኩ ነው” በማለት ቢገልጹም የፈቃድ ጉድለት መኖሩን ማስረዳት ባለመቻላቸው ክርክራቸውን ውድቅ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ዕድሉን የሰጠው አካል ያወጣውን ወጪ ሊከፍሉ እንደማይገባ ያቀረቡት ክርክር በችሎቱ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

በሰ/መ/ቁ 40325 (አመልካች የትምህርት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ወሰን አሰፋ ሐምሌ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ) ከመደራደር አቅም ልዩነት ጋር ተያይዞ መጎዳትን መሰረት በማድረግ በፍ/ህ/ቁ. 1710(2) ውሉ ውጤት እንዳይሰጠው ጥያቄ ቢቀርብም ችሎቱ አልተቀበለውም፡፡ ተጠሪ በአመልካች የትምህርት ወጪ ተሸፍኖላቸው በሁለት ዓመት ጊዜ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓመት ሶስት ዓመት በድምሩ ስድስት ዓመት አመልካችን ለማገልገል ግዴታ ገብተዋል፡፡ ውሉን የፈረሙት የመጀመሪያውን የትምህርት ዓመት ካጠናቀቁ በኋ ነው፡፡

ተጠሪ በውላቸው መሰረት ባለመፈጸማቸው ስድስት ዓመት እንዲያገለግሉ ወይም ወጪውን እንዲከፍሉ በአመልካች ክስ ሲቀርብባቸው ውሉ ከጊዜ በኋላ መፈረሙና ለሁለት ዓመት ትምህርት ስድስት ዓመት እንዲያገለግሉ የገቡት ውል ከአመልካች ጋር በነበራቸው የበላይና የበታች ግንኙነት ተገደው የፈረሙት በመሆኑ በፍ/ህ/ቁ. 1710(2) መሰረት ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሰባቸው ፈራሽ እንዲባልላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸው ክሱን ባስተናገደው ፍ/ቤት ተቀባይነት አግኝቶ በፍ/ህ/ቁ. 1710(2) አግባብ ፈራሽ ተደርጓል፡፡

ውሳኔው በይግባኝ በመጽናቱ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን የሰ/ችሎት በተጠሪ የቀረቡትን ምክንያቶች በፍ/ህ/ቁ 1710(2) ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች አንጻር በመመርመር ተጠሪ ከአመልካች ጋር ያደረጉት ውል የሚያስከትለውን ህጋዊ ውጤት ለመገንዘብ በቂ የትምህርት ደረጃና እውቀት እንዳላቸው በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት ስድስት ዓመት ለማገልገል ግዴታ መግባታቸው አሠሪውን ይጠቅማል ተብሎ ቢወሰድ ውሉ ለአንደኛው ተዋዋይ ወገን የበለጠ ጥቅም መስጠቱ በፍ/ህ/ቁ. 1710(1) የውል ማፍረሻ ምክንያት እንደማይሆን የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ እንደ ችሎቱ አስተያየት ተጠሪ ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ውሉን እንዲፈርሙ መደረጉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመሆናቸው ተገደው መፈረማቸውን አያሳይም፡፡

ሠራተኛው ለማገልገል የገባውን ግዴታ ሳይፈጽም ቢቀር ለትምህርቱ የወጣውን ወጪ እንደሚመልስ አማራጭ ግዴታ ሆኖ በውሉ ላይ ይመለከታል፡፡ ሆኖም የማገልገል ግዴታ በግልጽ በውሉ ላይ እስከሰፈረ ድረስ ወጪ የመመለስ ግዴታ በዝምታ ቢታለፍም ከመክፈል ኃላፊነት ነጻ አያደርግም፡፡ አሠሪው በውሉ መሰረት ለትምህርትና ለመሳሰሉት አስፈላጊ የሆኑትን ወጪዎች ከሸፈነ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ የሚቀረው የሠራተኛው የማገልገል ግዴታ ነው፡፡ ግዴታውን ካልፈጸመ በፍ/ህ/ቁ 1771(2) እና 1790(1) መሰረት ኪሳራ የመክፈል ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ (አመልካች የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንቲትዩት እና ተጠሪ አቶ ተፈሪ ማሞ (በሌለበት) ግንቦት 19 ቀን 2002 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 49453 ቅጽ 10)

አማራጭ ግዴታ

ከላይ በተጠቀሱት የሰበር ውሳኔዎች (ሰ/መ/ቁ 33473 እና 40325) ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ መዝገቦች ከማገልገል ግዴታ ጋር በተያያዘ ክስ የሚቀርበው በአማራጭ ዳኝነት በመጠየቅ ነው፡፡ ክስ የሚቀርብለት ፍ/ቤትም ሠራተኛው የማገልገል ግዴታውን በውሉ መሰረት እንዲፈጽም፣ የማይፈጽም ከሆነም ለትምህርት የወጣውን ወጪ እንዲመልስ በአማራጭ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ሠራተኛው ፈቃደኛ ካልሆነ አሠሪውን ለማገልገል አይገደድም፡፡ ተገዶ እንዲፈጽም ማድረግ የግል ነጻነቱን የሚነካ ስለሆነ የፍ/ህ/ቁ 1776 ተፈጻሚነት እንደሌለው በሰ/መ/ቁ 33473 ሆነ በሌሎችም መዝገቦች ወጥና ጽኑ አቋም ተይዞበታል፡፡ ሠራተኛው በገባው ግዴታ መሰረት እንደ ሙያው አሠሪውን ለማገልገል የሚገደደው የፈቀደ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ለማገልገል ፈቃደኛ ካልሆነ ግን በአማራጭ ለትምህርቱ የወጣውን ወጪ ለመተካት ይገደዳል፡፡

በውል ውስጥ አማራጭ ግዴታ ሲኖር ባለዕዳው በውሉ ከተመለከቱት ሁለት አይነት ግዴታዎች አንዱን መርጦ በመፈጸም ከሁለቱም ግዴታዎቹ ነጻ ይሆናል፡፡[2] ከማገልገል ወይም ወጪ ከመክፈል ግዴታዎች ከሁለቱ አንዱን በመወጣት ውሉን መፈጸም የሚቻል በመሆኑ ከትምህርት ውል የሚመነጭ የማገልገል ግዴታ አማራጭ ግዴታ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ሆኖም ግዴታው ባለመፈጸሙ ክስ ሲቀርብ አማራጭ መሆኑ ይቀራል፡፡ በዚህን ጊዜ ወጪ የመተካት ግዴታ የውሉ አለመፈጸም ውጤት እንጂ በአማራጭ የሚፈጸም ግዴታ አይደለም፡፡ ትምህርቱን አጠናቆ በዛው የቀረ ሠራተኛ ወይም የማገልገል ግዴታውን አቋርጦ ሥራውን የለቀቀ ሠራተኛ በውሉ የተጣለበትን ግዴታ አላከበረም፡፡ ግዴታውን ካላከበረ በሰ/መ/ቁ 49453 እንደተመለከተው በፍ/ህ/ቁ 1771(2) እና 1790(1) መሰረት ኪሳራ ለመክፈል ይገደዳል፡፡

ስለሆነም የማገልገል ግዴታውን አልተወጣም በሚል ክስ ከቀረበበት በአማራጭ ግዴታውን ለመፈጸም የሚያቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በክሱ ላይ በአማራጭ ዳኝነት መጠየቁ ግዴታውን አማራጭ አያደርገውም፡፡ ሲጠቃለል ሠራተኛው በማገልገል ወይም ወጪውን በመክፈል ከሁለቱ በአንዱ በአማራጭ ውሉን የመፈጸም መብት ያለው ቢሆንም አንዴ ግዴታውን አላከበረም ተብሎ ክስ ሲቀርብበት ግን ይህን መብቱን ያጣል፡፡ የማገልገል ግዴታ እያለበት ሥራውን ጥሎ የሄደ ሠራተኛ ክስ ሲቀርብበት “ተመልሼ አገለግላለው” ለማለት አይችልም፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው አሠሪው እስከፈቀደ ድረስ ብቻ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 32769 (አመልካች የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ተጠሪ እነ ሙሉቀን ፍስሐ (2 ሰዎች) ህዳር 9 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ) የሰጠው የህግ ትርጉም ከላይ የተነሳውን ሀሳብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ ሠራተኛው የማገልገል ግዴታውን ባለመወጣቱ አሠሪው ያወጣውን ወጪ እንዲከፍል፣ ዋሱም በዋስትና ግዴታው መሰረት ክፍያ እንዲከፍል በሁለቱም ላይ ክስ የቀረበ ሲሆን ጉዳዩን ያየው ፍ/ቤት ሠራተኛው ለማገልገል ፍቃደኝነቱን ስለገለጸ ክፍያው ሊከፈል እንደማይገባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይግባኙን ያው ፍ/ቤትም ግራ ቀኙን አከራክሮ ውሳኔውን አጽንቷል፡፡ የሰበር ችሎት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሲሽር እንዳለው ሠራተኛው፤

“…አገልግሎት መስጠቱን ማቋረጡን ካመነ ሲመቸኝ አገልግሎቱን መስጠት እችላለው በሚል መከራከር አይችልም፡፡”

ግዴታው ተፈጻሚ መሆን የሚጀምርበት ጊዜ

በአንድ የትምህርት መስክ ለመመረቅ የሚፈጀው ጊዜ ውሱን በሆኑ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር ትምህርቱ ከመጀመሩ በፊት ይታወቃል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ በአብዛኛዎቹ የትምህርት ውሎች ላይ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ የሚፈጀው ጊዜ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡ ትምህርቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የማገልገል ግዴታ ተፈጻሚ መሆን ይጀምራል፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የማጠናቀቂያ ጊዜው ሊራዘም ይችላል፡፡

ለምሳሌ ተማሪውን በማይመለከቱ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ትምህርቱ በተያዘለት ሰሌዳ የማይጠናቀቅበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ወይም ደግሞ ተማሪውን በሚመለከቱ (ለምሳሌ የጤና ማጣት፣ ዝቅተኛ ውጤት፣ የዲሲፕሊን እርምጃ ወዘተ…) ምክንያቶች ወደ ኋላ መጎተት ይከሰታል፡፡

አንዳንዴ ጊዜ ደግሞ ትምህርቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ ትምህርት የማግኘት ዕድል ይፈጠራል፡፡ በዚህን ጊዜ የማገልገል ግዴታ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው የመጀመሪያው ትምህርት ሲጠናቀቅ ነው ወይስ ሁለተኛው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በሰ/መ/ቁ 46574 (አመልካች ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ተጠሪዎች እነ ዮናስ ካሳ (ሁለት ሰዎች) መጋቢት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 12) የተሰጠው ውሳኔ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፡፡

በዚህ መዝገብ 1ኛ ተጠሪ ቤልጂየም አገር ሄዶ ለሁለት ዓመት የማስትሬት ትምህርት ሊማርና ትምህርቱን አጠናቆ ሲመለስ ለስድስት ዓመታት አመልካችን ሊያገለግል ግዴታውን የማይፈጽም ከሆነም ለትምህርት የወጡ ወጪዎችን ሊከፍል ከአመልካች ጋር ውል ገብቷል፡፡ 2ኛ ተጠሪም 1ኛ ተጠሪ ግዴታውን ባይወጣ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት ወጪውን ለመክፈል ግዴታ ገብታለች፡፡ በዚሁ መሰረት 1ኛ ተጠሪ በአመልካች ድጋፍና ፈቃድ የማስትሬት ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ በመቀጠል ተጨማሪ የፒ.ኤች.ዲ የትምህርት ዕድል አሜሪካን አገር በማግኘቱ ትምህርቱን ለመከታተል ሄዷል፡፡

ይህን ተከትሎ አመልካች ለትምህርት የወጣ ወጪ እንዲመለስለት በ1ኛ ተጠሪ እና በዋሱ በ2ኛ ተጠሪ ላይ ክስ አቅርቦ ጉዳዩን ያስተናገደው የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ተጠሪ በመማር ላይ እንደሆነ በማስረጃ ማረጋገጡን በመጥቀስ 1ኛ ተጠሪ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመለስ አመልካች መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብቱን ጠብቆ በትዕዛዝ ዘግቶታል፡፡ በትዕዛዙ ላይ የይግባኝ አቤቱታ የቀረበለት የፌ/ከ/ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ትዕዛዙን አጽንቶታል፡፡

የሰ/ችሎት በበኩሉ ክርክሩ ሊወሰን የሚገባው አመልካችና ተጠሪ ያደረጉትን ውል ይዘትና ውሉ ለተዋዋይ ወገኖች የሰጠውን መብትና የጣለውን ግዴታ በመመርመር እንደሆነ በመጠቆም 1ኛ ተጠሪ ግዴታውን ስላለመወጣቱ የሚከተለውን ሐተታ በማስፈር ትዕዛዙን ሽሮታል፡፡

“1ኛ ተጠሪ በውሉ መሠረት ትምህርቱን ጨርሶ የማስተርስ ዲግሪውን ያገኘ ቢሆንም ወደ አገሩ በመመለስ ለአመልካች አገልግሎት አልሰጠም ወይም ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይህም ማለት ውሉ በሰጠው መብት የተጠቀመ (ትምህርቱን የተማረ) ሲሆን፤ ግዴታውን ግን አልፈጸመም፡፡ [የፒ. ኤች ዲ.] ትምህርት እንዲቀጥል የሚያስችለው ተጨማሪ ስምምነትም ከአመልካች አላገኘም፡፡”

የወጪው መጠን

በአብዛኛዎቹ የትምህርት ውሎች ላይ የማገልገል ግዴታን ባለመወጣት ምክንያት ሊከፈል የሚገባው የክፍያ መጠን በቅድሚያ በውሉ ላይ ይገለጻል፡፡ ክስ የሚቀርበውም ሠራተኛው በውሉ ላይ የተመለከተውን ገንዘብ እንዲከፍል ነው፡፡ ሆኖም የሰ/ችሎት በሰ/መ/ቁ 33473 እና 49453 ግልጽ እንዳደረገው ሊከፈል የሚገባው በእርግጥ የወጡ ወጪዎችን እንጂ በውሉ ላይ የሰፈረውን የገንዘብ መጠን አይደለም፡፡ እነዚህም ወጪዎች በቀጥታ ለትምህርትና ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች (ለምሳሌ ትራንስፖርት፣ መመረቂያ ጽሑፍ ለማዘጋጀት፣ ደመወዝ ወዘተ) የወጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወጪዎች ስለመውጣታቸው በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በሰ/መ/ቁ 33473 በሶስተኛ ወገን የተከፈሉ በማስረጃ የተረጋገጡ ክፍያዎች ‘በአሠሪው ወጪ’ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ ችሎቱ በሰጠው አስተያየት ግዴታን ባለመወጣት የሚከፈለው የገንዘብ መጠን በአሠሪው ወይም በሶስተኛ ወገን ለትምህርቱ ሲባል በተጨባጭ የወጣውን ነው፡፡

የማገልገል ግዴታ በከፊል ተፈጽሞ ከሆነ የወጪው መጠን ሲሰላ አገልግሎት የተሰጠበት ጊዜ ከግምት ውስጥ ይገባል፡፡ ስሌቱ ሲሰራ በአገልግሎት ዘመኑ ልክ ወጪውም ተቀናሽ ይደረጋል፡፡ በሰ/መ/ቁ 40325 ተጠሪ ለማገልገል ግዴታ የገቡት ለስድስት ዓመት ሲሆን ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለአንድ ዓመት አመልካችን አገልግለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት እንዲከፍሉ ከተጠየቁት ወጪ ውስጥ አንድ ዓመት ያገለገሉበት ጊዜ ታስቦ ተቀንሶላቸዋል፡፡

የግዴታው አለመፈጸም ተጨማሪ ውጤቶች

የማገልገል ግዴታን አለመፈጸም ለትምህርት የወጣውን ወጪ የመተካት ኃላፊነት ያስከትላል፡፡ ይህ ዋነኛ ውጤቱ ቢሆንም በዚህ ብቻ አይገደብም፡፡ የመጀመሪያው ውጤት ከስንብት ክፍያ ጋር የተያያዘ ሲሆን የማገልገል ግዴታውን ያልተወጣ ሠራተኛ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅ የስንብት ክፍያ የማግኘት መብቱን ያጣል፡፡ አምስት ዓመት የአገልግሎት ጊዜ ኖሮት ሥራውን በገዛ ፈቃዱ የሚለቅ ሠራተኛ የስንብት ክፍያ የሚያገኘው ሥራው ላይ የሚያስቆይ ከሥልጠና ጋር የተያያዘ ለአሠሪው የውል ግዴታ[3] የሌለበት እንደሆነ ነው፡፡

በተጨማሪም የማገልገል ግዴታን አለመወጣት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ ክሊራንስ የማግኘት መብትን ያሳጣል፡፡ ሆኖም የሥራ ልምድ የምስክር ወረቀት ሊያስከለክል አይገባም፡፡ በሰ/መ/ቁ 48476 (አመልካች የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እና ተጠሪ አቶ ደረጀ መኮንን ሚያዝያ 12 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9) ለትምህርት የወጣ ወጪን አለመክፈል በሥራ ልምድ እና ክሊራንስ ላይ ያለውን ህጋዊ ውጤት በተመለከተ የሰ/ችሎት የህግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ክርክሩ የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 መሰረት በማድረግ የቀረበ ሲሆን ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለም ሆነ በማናቸውም ምክንያት የሥራ ውሉ ሲቋረጥ የሥራ ልምድ የምስክር ወረቀት ሊሰጠው እንደሚገባና ዕዳ አለበት በሚል ሆነ በሌላ በማናቸውም ምክንያት ሊከለከል እንደማይገባ በማተት ችሎቱ የጸና አቋሙን አንጸባርቋል፡፡ በሌላ በኩል መልቀቂያ (clearance) ሠራተኛው ዕዳ እንደሌለበት ማረጋገጫ በመሆኑ አሠሪው ከሠራተኛው የሚፈልገው ዕዳ መኖሩን ከገለጸ በዚህ ረገድ ማስረጃ እንዲሰጥ አይገደድም፡፡

አሠሪው ለትምህርት ያወጣውን ወጪ ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ክስ አቅርቦ ከመጠየቅ ውጪ ለሠራተኛው መስጠት ያለበትን የሥራ ልምድ የውሉ መያዣ ሊያደርገው እንደማይችል በሰ/መ/ቁ 48476 አቋም የተያዘበት ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በሰ/መ/ቁ 59666 (አመልካች የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ አቡ ጎበና ግንቦት 4 ቀን 2003 ዓ.ም.ቅጽ 11) አሠሪው ለትምህርት አወጣሁት የሚለውን ወጪ በራሱ ቀንሶ የማስቀረት መብት እንደሌለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ አመልካች ከተጠሪ ጋር የነበረው የሥራ ውል ሲቋረጥ ተጠሪ ከሚከፈለው የዓመት እረፍት እና ስንብት ክፍያ ላይ ለተጠሪ ትምህርት ወጪ ሆኗል ያለውን ገንዘብ በራሱ ስልጣን ቀንሶ ያስቀረ ሲሆን ገንዘቡን ለተጠሪ እንዲመልስ የስር ፍርድ ቤቶች በሰጡት ውሳኔ ላይ ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በችሎቱ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 59(1) መሰረት ደመወዝ ለመቀነስ በአሠሪው ስልጣን ላይ የተቀመጠው ገደብ በተመሳሳይ ሁኔታ የሥራ ውል ሲቋረጥ በሚከፈሉ ክፍያዎችም ላይ ተፈጻሚነት አለው፡፡

የዋስ ግዴታ

ወጪው በአሠሪው ተሸፍኖለት በምላሹ ለተወሰነ ጊዜ ለማገልገል ግዴታ ለገባ ሠራተኛ ዋስ መሆን በብዙ መልኩ የከበደ ነው፡፡ በተለይ ትምህርቱ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚሰጥ ከሆነ በሚፈጠረው የግንኙነት ክፍተት የተነሳ ሠራተኛው ግዴታውን እንዲወጣ በቅርብ ርቀት ሆኖ ለመከታተልና ለመወትወት ያስቸግራል፡፡ ዋሱ በገባው ግዴታ መሰረት እንዲከፍል ሲገደድም በከፈለው ልክ በአሠሪው እግር ተተክቶ የከፈለውን ለማስመለስ ያለው ዕድል ጠባብ ነው፡፡

ግዴታው የሚቆይበት ጊዜ ርዝመት በዋሱ ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ ሁለት ዓመት ተምሮ ስድስት ዓመት ለማገልገል ግዴታ ለገባ ሠራተኛ ዋስ የሆነ ሰው ከግዴታው ነጸ ለመሆን ስምንት ዓመት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ አገልግሎቱ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ዋሱ ሀሳቡን ቀይሮ ከግዴታው ነፃ የሚወጣበት መንገድም የለም፡፡ ዋሱ በፍ/ሕ/ቁ 1925 በተመለከተው መሰረት የዋስትና ግዴታን ማውረድ የሚቻልበት መንገድ ቢኖርም የድንጋጌው ተፈፃሚነት ግን የባለዕዳው ግዴታ ወደፊት ይደርሳል ተብሎ ለሚታሰብ ሁኔታ ሆኖ ዋስትናው ለስንት ጊዜ እንደሚረጋ በዋስትና ስምምነቱ ላይ ሳይወሰን ከቀረ ነው፡፡ የትምህርት ወጪ ለመመለስ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ለማገልገል ግዴታ የሚገባበት ውል በፍ/ሕ/ቁ 1925 በተመለከተው መልኩ ወደፊት የሚሆን ግዴታ ወይም በአንድ ዓይነት ሁኔታ የሚመጣ ግዴታ እንዳልሆነ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 49041 (አመልካች የአ/አ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና ተጠሪዎች እና አቶ ኤሣው መዓዛ (3 ሰዎች) ህዳር 2 ቀን 2003 ዓ.ም ቅጽ 12) የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ዋሱ በቁጥር 1925 (2) መሰረት የዋስትና ግዴታውን ማውረድ የሚችልበት እድል የለውም፡፡

 

[1] ለምሳሌ ቻይና ወደ ገበያ ኢኮኖሚ መሸጋገሯን ተከትሎ ሠራተኛው አሠሪውን እንዳይወዳደር ገደብ ለሚጥሉ ስምምነቶች ዕውቅና የሰጠች ሲሆን በሠራተኛው ላይ የሚያሳደረውን ኢኮሚያዊ አሉታዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችልና ተፈጻሚነቱ ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍም ዘርግታለች፡፡ የበለጠ ለመረዳት Ronald C. Brown, Understanding Labor and Employment Law in China (Cambridge, New York: Cambridge University Press, 2010) ገፅ 163-5 ይመለከቷል፡፡

[2] የፍ/ህ/ቁ 1880

[3] የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ /ማሻሻያ/ አዋጅ ቁጥር 494/1998 አንቀጽ 2(2) ሸ

Exit mobile version