Site icon Ethiopian Legal Brief

ስለ ውክልና- የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

ውክልና

ተወካይ የሆነ ሰው ወካዩ ለሆነው ሌላ ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ስራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን የሚገባበት ውል

አንድ ተወካይ የውክልና ስራ በሚፈጽምበት ጊዜ የወካዩን ህጋዊ ሁኔታዎችን የመለወጥ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህም በመሆኑ ተወካዩ ለወካዩ ፍጹም ታማኝ የመሆን እና የወካዩን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ የማስጠበቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ስለሆነም ተወካዩ ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው የወካዩን ጥቅም ብቻ በመሆኑ የጥቅም ግጭት ባለበት ሁኔታ ተወካዩ በስራው አፈጻጸም ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የጥቅም ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ተወካይ ከራሱ ጥቅም ይልቅ የወካዩን ጥቅም ሊያስቀድም ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህም ተወካዩ የራሱን ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ ሲያጋጥመው ሁኔታውን ለወካዩ ሳያሳውቅና ወካዩ ሳይስማማ ስራውን እንዳይፈጽም ይከለከላል፡፡

ስለወኪልነት የተደነገጉትን የፍ/ብሔር ድንጋጌዎች ስንመለከትም ተወካዩ ከወካዩ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው እንደሚገባ እና የውክልና ስልጣኑን የሚያስቀሩ ምክንያቶች ለወካዩ ማስታወቅ እንዳለበት፤ ተወካዩ ስራውን የሚፈጽመው በተለይ ለወካዩ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ተወካዩ በራሱ ስም ከወካዩ ጋር የሚያደርገው ውል ወካዩ ካላጸደቀው በቀር ሊፈርስ እንደሚችል መደንገጋቸው ተወካዩ ለወካዩ ፍጹም ታማኝ መሆን እንዳለበት እና ለወካዩ ጥቅም ብቻ መስራት እንዳለበት፣ የጥቅም ግጭት ባለበት ጊዜ ሁሉ ሁኔታውን ለወካዩ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም አንድ ተወካይ የጥቅም ግጭት ባለበት ጊዜ ለወካዩ ሳያሳውቅ የሚያከናውነውን ስራ ወካዩ ሊቃወመው የሚችል መሆኑን እና በዚህ ሁኔታ የተከናወነው ስራም ወካዩ ካላፀደቀው በቀር ወካዩ ራሱ እንደፈጸመው ሊቆጠር እንደማይገባ ከውክልና ግንኙነት አጠቃላይ ዓላማ እና ከፍ/ብ/ህጉ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 14974 ቅጽ 1፣[1]  ሰ/መ/ቁ. 50440 ቅጽ 10፣[2] ሰ/መ/ቁ. 67376 ቅጽ 13፣[3] ፍ/ህ/ቁ 2198፣ 2208፣ 2209(1)፣ 2188

የአፃፃፍ ስርዓት

የውሉ አጻጻፍ በተለየ ቅርፅ እንዲደረግ ሕጉ የማያስገደድ ከሆነ ይህን ውል እንዲፈጽም በቃል የሚሰጥ የውክልና ስልጣን በወካዩ ላይ ሕጋዊ አስገዳጅነት አለው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 68498 ቅጽ 13፣[4] ፍ/ህ/ቁ. 2180

የወካይ መሞት

በወካይ መሞት ምክንያት ቀሪ በሆነ የውክልና ስልጣን ተወካይ ከነበረው ሰው ጋር በወካዩ ስም የሚደረግ ውል ከጅምሩ ፈራሽና ህጋዊ ውጤት የሌለው ነው፡፡

ወካዩ የሞተ እንደሆነ፣ በሥፍራው አለመኖሩ የተረጋገጠ እንደሆነ፣ ለመስራት ችሎታ ያጣ እንደሆነ ወይም በንግድ መውደቅ ኪሣራ ደርሶበት እንደሆነ ለጉዳዩ ተቃራኒ የሚሆን ውል ካልተገኘ በቀር የውክልና ሥልጣኑ ወዲያውኑ የሚቀር መሆኑን የፍታብሓር ሕ/ቁጥር 2232 ንዑስ አንቀጽ 1 ይደነግጋል፡፡

የውክልና ስልጣን መሻር ውጤት

እንደራሴው ቀሪ በሆነው ሥልጣን መሠረት በሌላ ሰው ስም ወይም ወካይ በነበረው ሰው ስም በሠራ ጊዜ በስሙ የተሠራበት ስው እንደፈቃዱ በስሙ የተሠራውን ሥራ ለማጽደቅ፣ ለመቀበል ወይም ለመሻር መብት አለው፡፡ በማለት በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2191/2/ ከተደነገገ በኋላ በዚሁ በተሰጠው መብት ተጠቅሞ አንዱን መንገድ እንዲከተል ወይም እንዲመርጥ ከእንደራሴው ጋር የተዋዋሉት ሦስተኛ ወገኖች ለማስገደድ እንደሚችሉ እና ሿሚው ከሦስተኛ ወገኖች በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ወዲያውኑ ካላስታወቃቸው እንደራሴው የሠራውን ሥራ እንዳልተቀበለው ሕጉ ግምት የወሰደ ለመሆኑ ተከታይ በሆነው ድንጋጌ ተመልክቷል፡፡ እንግዲህ ሿሚው በግልጽም ይሁን በዝምታ እንደራሴው ሥልጣኑ ቀሪ ከሆነ በኋላ የሠራውን ሥራ ያልተቀበለው መሆኑ ከተረጋገጠ የዚሁ ያለመቀበል ውጤት በቁጥር 2193 ተደንግጓል፡፡

የዚህን ድንጋጌ ይዘት ስንመለከት ሿሚው ይህንኑ የእንደራሴውን ሥራ ካልተቀበለው ምን ጊዜም ይኸው ውል ፈራሽ ነው የሚል አይደለም፡፡ ይልቁንም ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1808 እስከ 1818 ድረስ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተከትሎ የውሉ መፍረስ ወይም መሰረዝ ሊወሰን የሚችል መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም እነዚህኑ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በመከተል ውሉ ሊፈርስ የማይችልበት አጋጣሚ ያለ መሆኑን የሚያሳይና ነገር ግን ውሉ የሚፈርስ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በቅን ልቦና ከእንደራሴው ጋር በተዋዋሉት 3ኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት መንገድ የሚያመቻች ድንጋጌ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 26399 ቅጽ 5፣[5] ፍ/ህ/ቁ. 1808—1818፣ 2191(2)፣ 2193

ስለማፅደቅ

የውክልና ስልጣን አገልግሎት ውክልናው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ለሚከናወኑ ሕጋዊ ተግባራት እንጂ ከመሰጠቱ በፊት ተወካዩ ለፈጸማቸውን ተግባራት ሕጋዊ ውጤት አይፈጥርም፡፡

ዘግይቶ የተሰጠ የውክልና ስልጣን ተወካዩ የፈጸማቸውን ተግባራት የማጽደቅ ውጤት የለውም፡፡ ምክንያቱም አግባብነት ያላቸው የፍ/ህ/ቁ. 2190 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉት የውክልና ስልጣን ኖሮ ተወካዩ ከውክልና ስልጣኑ በላይ አሳልፎ ለፈጸማቸው ተግባሮች እንጂ ፈጽሞ የውክልና ስልጣን በሌለበት በወካዩ ለተከናወኑ ተግባራት አይደለም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 74538 ቅጽ 13፣[6] ፍ/ህ/ቁ. 2190

ልዩ የውክልና ስልጣን

የአንድ ንብረት ባለሃብትነት በውል ለሌላ ሰው የሚተላለፈው ባለሃብት ወይም ባለሃብቱ የንብረቱን ባለቤትነት በውል ለሌላ እንዲያስተላልፍ የፀና ልዩ የውክልና ስልጣን ባለው ሰው እንደሆነ የህገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1፣ የፍትሐብሓር ህግ ቁጥር 1204 ንዐስ አንቀጽ 2፣ የፍታብሓር ህግ ቁጥር 2005 ንዐስ አንቀጽ 2 እና የፍትሐብሓር ህግ ቁጥር 2232 ንዐስ አንቀጽ 1 ድንጋጌዎችን በጣምራ በማንበብ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 73291 ቅጽ 13፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 40(1)፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1204፣ 2232(2)፣ 2015(ሀ)፣ 2005(2)

የማይንቀሳቀስ ንብረት የመሸጥ፣ የመለወጥና የንብረቱን ባለቤትነት ለሦስተኛ ወገን የማስተላለፍ ስልጣን ያለው ተወካይ ንብረት በመያዣ አስያዞ በወካዩ ስም ከባንክ የመበደር ስልጣን አለው፡፡

የውክልና ማስረጃ ለተወካዩ ልዩ የውክልና ስልጣን የሚሰጥ ከሆነ ሕጋዊ ውጤቱ በውክልና ማስረጃው ላይ ከተጻፉት ተግባራት በተጨማሪ በውክልና ማስረጃው የተገለፁትን ጉዳዮችና እንደ ጉዳዩ ክብደትና እንደ ልምድ አሰራር በውክልና ማስረጃው የተገለጹትን ጉዳዮች ተከታታይና ተመሣሣይ የሆኑ አስፈላጊ ተግባራትን የመፈፀም ስልጣንን የሚያካትት መሆኑ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2206 ንዑስ አንቀጽ 1 ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም በውክልና ማስረጃ ቤት የመሸጥ፣ የመለወጥና ለሦስተኛ ወገን የማስተላለፍ ስልጣን ያለው ሰው ከዚህ መለስ የሆኑ ተግባራትን የመፈፀም ችሎታ እንዳለውና በተለይም ንብረቱን በመያዣነት ለማስያዝ የሚያስችል ስልጣን እና ችሎታ እንዳለው “ለራሱ ዕዳ ዋስትና እንዲሆን አንዱን የማይንቀሣቀሥ ንብረትን በእዳ መያዣነት አድርጎ ለመስጠት የሚችለው የማይንቀሣቀሰውን ንብረት ለመሸጥ ችሎታ ያለው ሰው ነው” ከሚለው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 3049 ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 17320 ቅጽ 5፣[7] ፍ/ህ/ቁ. 2026/1/፣ 3049/2/

ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራ በቀር ሌላ ሥራ ለመስራት የሚያስፈልግ ሲሆን ልዩ ውክልና እንዲኖረው አስፈላጊ መሆኑንና ተወካዩ ልዩ የውክልና ሥልጣን ከሌለው በቀር የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ለመሸጥ ወይም አስይዞ ለመበደር የማይችል መሆኑ በፍታብሔር ህግ ቁጥር 2205 ንዑስ አንቀፅ 1 እና ንዑስ አንቀፅ 2 ተደንግጓል፡፡

በወካዩ ስም ማናቸውንም ፎርማሊቲ እያሟላ ንብረት እንዲያዛውር፣ በስሙ እንዲዋዋል የውክልና ስልጣን የተሰጠው ተወካይ በወካዩ ስም የሚገኝ የማይንቀሳቀስ ንብረት የመሸጥ፣ የመለወጥ ስልጣን የለውም፡፡

በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2205 መሠረት የሚሰጥ ልዩ ውክልና በይዘቱ በልዩ ውክልና የሚፈፀሙ እያንዳንዳቸውን ተግባሮች በግልፅ የሚያመለክት መሆን ይገባዋል፡፡

የውክልና ስልጣን የሚተረጎመው ሳይስፋፋ በጠባቡ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 50985 ቅጽ 13፣[8] ፍ/ህ/ቁ. 2204፣ 2205፣ 2181/3/

የውክልና ሰነዱ ይዘት በግልፅ ውክልና ተቀባዩ የተሰጠው ስልጣን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ የሚያስችል ስለመሆኑ እየገለፀ ስለልዩ ውክልና አስፈላጊነት የተቀመጠው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2205 በውክልና ስልጣን ሰነዱ ያለመጠቀሱ ውክልናው ልዩ የውክልና ስልጣን አይደለም ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ስለመሆኑ የሚያሳይ የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡ ዋናውና ቁልፉ ነገር ለውክልና ተቀባዩ የተሰጡት ተግባሮች በዝርዝርና ግልጽ ሁኔታ ተጠቅሰው በውክልና ሰነዱ ላይ መገኘት እንጂ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ያለመጠቀሳቸው አይደለም፡፡ የሰነዱ ይዘት ግልጽ መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች በውክልና ስልጣን ሰጪውና በውክልና ስልጣን ተቀባዩ አልተጠቀሱም ተብሎ ሰነዱ ዋጋ እንዲያጣ ማድረግ የተዋዋዮችን ሐሳብ ውጤት እንዳይኖረው የሚያደርግ በመሆኑ በውል አተረጓጎም ደንቦችም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው የሚሆነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 72337 ቅጽ 13፣[9] ፍ/ህ/ቁ. 2199፣ 2055

 

[1] አመልካች ወ/ት ማህሌት ገ/ስላሴ እና ተጠሪ እነ አቶ መንግሥቱ ኃብ /2 ሰዎች/ ሐምሌ 28 ቀን 1997 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ ሃብቱ ወልዱ እና እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ መሰሉ ደስታ/ 2 ሰዎች/ ግንቦት 16 ቀን 2002 ዓ.ም.

[3] አመልካቾች እነ ወ/ሮ ንግስት ኪዲኔ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ አቶ በለጠ ወልደሰማያት /2 ሰዎች/ ሀምሌ 30 ቀን 2004 ዓ.ም.

[4] አመልካች አቶ ገብረ ክርስቶስ ገብረ እግዛብሔር እና ተጠሪ ሳባ እምነበረድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሰኔ 07 ቀን 2004 ዓ.ም.

[5] አመልካች አቶ ኃ/ማርያም ባዩ እና ተጠሪ እነ አቶ ሳሙኤል ጎሳዬ /5 ሰዎች/ ኅዳር 5 ቀን 2000 ዓ.ም.

[6] አመልካች ወ/ሪት አሊያት ይማም ሙዘይን እና መልስ ሰጭ አቶ እምነቴ እንደሻው ሐምላ 20 ቀን 2004 ዓ.ም.

[7] አመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ እነ ዶ/ር ሻውል ገብሬ /2 ሰዎች/ መጋቢት 18 ቀን 2000 ዓ.ም.

[8] አመልካች እነ አቶ ስሻህ ክፍሌ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ አፀደ ደቤ /2 ሰዎች/ ሕዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም.

[9] አመልካች ወ/ሮ ንግስቲ እምነት እና ተጠሪ ቴዎድሮስ ተክሌ የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም.

Exit mobile version