Uncategorized

የአስተዳደር ህግ ንድፈ ሃሳባዊ አቅጣጫዎች

የአስተዳደር ህግ ንድፈ ሃሳባዊ አቅጣጫዎች

በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የህግ ሚና ውስብስብ ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በመንግስት አስተዳደር ስራ ወይም በአስተዳደራዊ ሂደት ውስጥ ሊኖረው የሚችለው አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ እና ውጤት ተግባራዊ የሆነ ጥናትና ትንተና የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ከተግባራዊ መመዘኛው በተጨማሪ ዓይነተኛ ሚናና ተግባሩን በተመለከተ የሚቀረጽበት ማዕዘን ወይም እይታ በተለያዩ ወገኖች የተለያየ አቋም ተይዞበት ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበት ግን የአስተዳደር ህግ ለብቻው ተነጥሎ የሚጠና የህግ ክፍል ሳይሆን መሰረት ከሆኑት ነባራዊ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ግንኙነት፤ ግጭትና ስምምነት እንዲሁም መስተጋብራዊ ውጤት አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡

ምንም እንኳን የአስተዳደር ህግን በተመለከተ ጐራ ለይቶ የተቀመጠ ፍንትው ያለ ንድፈ ሀሳብ ባይኖርም ጠቅለል ባለ መልኩ ሁለት የአቅጣጫ መስመሮችን ይዞ ይገኛል፡፡ ሃርሎው እና ሮውሊንግ የተባሉ የአስተዳደር ህግ አጥኝዎች እነዚህን ሁለት ንድፈ ሀሳባዊ አቅጣጫዎች በመለየት ‘የቀይ መብራት’ (የቁም ንድፈ ሀሳብ) እና ‘የአረንጓዴ መብራት’ (የእለፍ ንድፈ ሀሳብ) የሚል ስያሜ በመስጠት የሚያንፀባርቁትንና የሚወክሉትን አቋም በተመለከተ ትንተና አቅርበዋል፡፡[1]

በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው የቁም ንድፈ ሀሳብ በአቀራረቡ ወግ አጥባቂ ሲሆን ቁጥጥርን አይነተኛ የአስተዳደር ህግ ሚና አድርጐ ይወስዳል፡፡ ንድፈ ሀሳቡ ከአስተዳደር ህግ መጸነስና መወለድ ጋር አብሮ የዳበረ የኋለኛው ዘመን (traditional) እይታን ያንጸባርቃል፡፡ ይህ ሲባል ግን ታሪካዊ ውልደቱንና አመጣጡን ለማሳየት እንጂ በአሁኑ ወቅት በተግባር የሚገለፅ አቀራረብ እንዳልሆነ ለመጠቆም አይደለም፡፡ የአስተዳደር ህግ የተነሳበት ዋነኛ አጀንዳ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ስልጣን በቅጡ መቆጣጠርና በዚህም የዜጐች መብትና ጥቅም እንዳይጣስ መከላከል ነው፡፡ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የመንግስት ተቋማትና ባለስልጣናት ከስልጣናቸው ገደብ አልፈው በሚፈፅሙት ድርጊት በዜጐች ላይ በደል እንዳይደርስ ስልጣናቸው እንደፈረስ ልጓም መቆጣጠሪያ መሳሪያ ያስፈልገዋል፡፡

በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት ይህ መሳሪያ የአስተዳደር ህግ ነው፡፡ በአስተዳደር ህግ የቁጥጥር መሳሪያ ከሆኑት መንገዶች አንዱ አስተዳደራዊ ድርጊትና ውሳኔ ህጋዊነቱን በተመለከተ በፍ/ቤቶች የሚታረምበት የፍርድ ምርመራ ስርዓት ሲሆን የቁም ንድፈ ሀሳብ ፍ/ቤቶች አስተዳደራዊ ተቋማትን የመቆጣጠር ጠንካራ ሚና እንዲኖራቸው በአጽንኦት ይከራከራል፡፡[2]

የንድፈ ሀሳቡን ዳራ በቅጡ ለመረዳት ከምንጩ የፖለቲካዊ ፍልስፍና አንፃር መመርመሩ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ እይታ ምርጥ መንግስት ማለት በስሱ የሚገዛ፣ የታቀበ መንግስት ነው፡፡ ፒተር ለይላንድ እና ቴሪ ውድስ ይህንኑ በማጉላት እንዲህ ይላሉ፤

የቁም ንድፈ ሀሳብ አመጣጡ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የነፃ ገበያ የፖለቲካ ስርዓት ነው፡፡ ነፃ ገበያ ለግለሰለቦች ነፃነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአንፃሩ ግን የመንግስትን ስልጣን በጥርጣሬ በማየት ውስን አገዛዝን በዋነኛነት ይደግፋል፡፡[3]

የነፃ ገበያ ስርዓት ነፀብራቅ የሆነው የቁም ንድፈ ሀሳብ የመንግስትን እጆች ለማሳጠር የአስተዳደር ህግን እንደ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ይጠቀምበታል፡፡ ጠንካራ መንግስት በግለሰቦች እንቅስቃሴ ውስጥ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ ስለሚያስቸግር የግለሰቦች ነፃነት ጠር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በተግባር እንደታየው ግን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የመንግስት ስልጣንና ጡንቻ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እያደገ መጥቷል፡፡ የተለያየ ተግባራትን የሚያከናውኑ የአስተዳደር ተቋማት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት በህግ አውጭው በሚሰጣቸው ስልጣን መሰረት መጠነ ሰፊ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በቁም ንድፈ ሀሳብ መሰረት በታሪክ ሂደት እያደገ የመጣውን የመንግስት ስልጣንና በየጊዜው የሚፈጠሩትን የአስተዳደር ተቋማት ከግለሰቦች ነፃነት ጐን ለጐን አጣጥሞ መሄድ የሚቻለው በህግ ማዕቀፍ ጠንካራ ቁጥጥር ሲደረግባቸው ነው፡፡ የአስተዳደር ህግ በዋነኛነት ይህን የቁጥጥር ተግባር ማከናወን አይነተኛው ተልእኮው ነው፡፡

ሁለተኛውን የእለፍ ንድፈ ሀሳብ ያየን እንደሆነ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ለመንግስት ስልጣንና ለአስተዳደር ተቋማት የአረንጓዴ መብራት ማለትም የእለፍ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ በዚህ ንድፈ ሀሳብ መሰረት የአስተዳደር ህግ ዋነኛ ሚና የመንግስት ስራን ማቀላጠፍ ነው፡፡ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ሲቀር የመንግስት ቢሮክራሲ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይሰራል፡፡ ስለሆነም የአስተዳደር ህግ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማነትን ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ አስተዳደር በቁጥጥር ሰበብ እጆቹ የሚታሰሩ ከሆነ ተጨማሪ አስተዳደራዊ በደልን ከማስከተል በቀር ፋይዳ የለውም፡፡

ፖለቲካዊ ዳራውን ያየን እንደሆነ የማህበራዊ ዲሞክራሲ (social democracy) ንድፈ ሀሳብ ነፀብራቅ ነው፡፡[4] በዚህ ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ መሰረት መንግስት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመሳተፍ አቅም ለሌለው ህብረተሰብ ማህበራዊ አገልግሎትን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት የአስተዳደር ህግ የ‘መንገድ ጠራጊነት’ ሚና ሊኖረው ይገባል፡፡

[1] Carol Harlow and Richard Rawlings, Law and Administration (The Law in Context Series, 3rd edn, Cambridge University Press: Cambridge, 2009) ገፅ 1-48

[2] Peter Leyland & Gordon Anthony, Textbook on Administrative Law (7th edn, Oxford University Press, 2013) ገፅ 6

[3] ዝኒ ከማሁ ገፅ 5

[4] ዝኒ ከማሁ ገፅ 7

1 reply »

  1. hi abrish peace new. let me ask u a question what is z similarity & difference b/n directory vs circular? what is its status? can we say circular is binding before a court of law? thank u.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.