Articles

የሰበር ውሳኔዎች ግጭት

የሰበር ውሳኔዎች ግጭት

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጥ የህግ ትርጉም ለበታች የክልልና የፌደራል ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት እንዲኖረው አስገዳጅ ህግ ከወጣ (አዋጅ ቁጥር 454/1997) ከአስር ዓመት ዓመት በላይ አልፎታል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ህጉና አፈጻጸሙ ለፍትህ ስርዓቱ ያበረከተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እና ያስከተለው ችግር በተመለከተ የዳሰሳና የክለሳ ጥናት ተደርጎ ውጤቱ ይፋ የሆነ ሪፖርት እስካሁን ድረስ የለም፡፡ እስከ አሁን ድረስ የህጉ አጠቃላይ ተቀባይነት መሰረት ያደረገው አሰራሩ ወጥነትን ያመጣል ከሚል በሀሳብ ደረጃ ሊያሳምን የሚችል አመለካከት እንጂ በተግባር ተፈትኖ እየታየ ያለ ሀቅ አይደለም፡፡

ተግባራዊ የመለኪያ ሚዛንን ለጊዜው ወደ ጎን እንተወውና ወጥነት የአዋጁ ዋና ዓላማና ግብ ነው ብለን እንነሳ፡፡ ችግሩ ግን ከዚህ ይጀምራል፡፡ አዋጅ ቁጥር 454/1997 ወጥነትን እንደ ዋና ሆነ ተጓዳኝ ዓላማና ግብ ይዞ ስለመነሳቱ በግልጽ ሆነ በተዘዋዋሪ የሚናገር ድንጋጌ አልያዘም፡፡

በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 454/1997 ሊወጣ የቻለው ስለፌደራል ፍርድ ቤቶች የወጣውን አዋጅ ቁጥር 25/88 (እንደተሻሻለ) እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የአስፈላጊነቱ መሰረት ምን እንደሆነ በግልጽ የተመለከተ ነገር የለም፡፡

አዋጁ ዝምታን ቢመርጥም ህጉ ሊያሳካ የፈለገው ቀዳሚ ግብ የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ወጥነት እንዲኖራቸውና ተገማች እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ ግምት ቢወሰድ በመርህ ደረጃ አሳማኝና አስማሚ ሀሳብ ነው፡፡ እንግዲህ ወጥነትና ተገማችነት የአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ዋነኛው ገጽታ እንዲሆን ከታለመ ከብዙ ነገሮች መሐል ቢያንስ አንድ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ ይገኝ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ይኸውም የሰበር ውሳኔዎች ራሳቸው ወጥነት ዐቢይ መገለጫቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ግልጽ የአቋም ለውጥ በሌለበት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ እርስ በእርስ የማይጣጣምና የሚጋጭ የህግ ትርጉም በሚኖርበት ጊዜ በበታች ፍርድ ቤቶች ላይ ውዥንብር በመፍጠር ተገማችነትን አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ አዋጅ ቁጥር 454/1997 ይፋ ህግ ሆኖ ከታወጀ ወዲህ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ዓመት እየጠበቁ ከመታተማቸው ውጪ በአንድ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚ የተደረገውን የህግ ትርጉም በቀላሉ መለየትና ማግኘት የሚያስችል የውሳኔዎች ጥንቅር (Codification) አሁን ድረስ አልተዘጋጀም፡፡ በዚህ የተነሳ በበታች ፍ/ቤቶች ይቅርና በራሱ በችሎቱ ዘንድ እንኳን ወጥነትን ማስፈን አልተቻለም፡፡

እርስ በእርስ ከሚጋጩ የሰበር ውሳኔዎች መካከል ለአብነት ያህል የሚከተሉት በአስረጂነት ይጠቀሳሉ፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ 47495 ያልታተመ እና ሰ/መ/ቁ. 47139 ቅጽ 11

በሰ/መ/ቁ 47495 ያልታተመ[1] ችሎቱ ህጉን በመተርጎም በደረሰበት ድምዳሜ መሰረት በሟች ስም ተመዝግቦ የነበረ የውርስ ሀብት በሽያጭ፣ በውርስ፣ በስጦታ ወይም በሌላ ህጋዊ መንገድ መተላለፉ ሳይረጋገጥ ውርሱ በሚጣራበት ጊዜ በአንደኛው ወራሽ ስም ተመዝገቦ እንደሚገኝ ከተረጋገጠ የውርሱ ሀብት ተደርጎ ሊጣራ አይገባውም፡፡ በዚህ ንብረት ላይ መብት አለኝ የሚል ወራሽ የባለቤትነት ምዝገባው ስርዓቱን ጠብቆ ያልተከናወነ ስለመሆኑ ሳያስረዳ እንዲሁም የባለቤትነት ምስክር ወረቀቱን ስልጣን ባለው አካል ሳያሰርዝ ንብረቱን በስሙ ያስመዘገበው ወራሽ እንዴት እንዳፈራው ሊረጋገጥ ይገባል በሚል የሚያነሳው ቅሬታ የሕግ መሰረት ያለው አይደለም፡፡

ሆኖም በሰ/መ/ቁ. 47139 ቅጽ 11[2] የተሰጠው የህግ ትርጉም በግልጽ እንደሚያስገነዝበን አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት በስሙ የተመዘገበ ሰው ንብረቱ በእጁ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ማስረዳት ካልቻለ ህጋዊ ወራሽ እንዳያስረክበው ሲጠይቅ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ 49239 ያልታተመ እና ሰ/መ/ቁ. 114669 ቅጽ 19

በአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ውስጥ በወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ ሳይኖር አንድ ሠራተኛ ለሰላሳ ወይም ከዚያ በላይ ቀናት ከታሰረ ውጤቱ ምንድነው? ለጥያቄው ምላሽ ከሰ/መ/ቁ 49239 ያልታተመ[3] አንጻር ካየነው ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከስራ እንደቀረ ተቆጥሮ የሥራ ውሉ በህጋዊ መንገድ ይቋረጣል፡፡

ይሁን እንጂ በሰ/መ/ቁ. 114669 ቅጽ 19[4] ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 49239 ይዞት የነበረውን አቋም መሻሻሉን በግልጽ ሳይጠቁም የህጉን ትርጉም ቀይሮታል፡፡ በዚህ መዝገብ ተጠሪ የአመልካችን መኪና ሲያሽከረክሩ ግጭት በመከሰቱ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ለአራት ወር ከአስር ቀናት በጊዜ ቀጠሮ በእስር ከቆዩ በኋላ ዓቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ለመቀጠል የሚያስችል ነገር ባለማግኘቱ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

ተጠሪ ከሰላሳ ቀናት በላይ ከስራ ቀርተዋል በሚል ከስራ ሲሰናበቱ የውሉን መቋረጥ አስመልክቶ ጉዳዩን ያዩት ፍርድ ቤቶች የእስራት ፍርድ ሳይኖር በጊዜ ቀጠሮ መታሰር የሥራ ውል ለማቋረጥ በቂ ምክንያት እንዳልሆነ ወጥ አቋም ላይ ደርሰዋል፡፡ የሰበር ችሎትም ከስር ፍ/ቤቶች አልተለየም፡፡ አከራካሪውን ጭብጥ አስመልክቶ ለህጉ በተሰጠው አስገዳጅ ትርጉም መሰረት፤

“በፍርድ ቤት ውሳኔ ከ30 ቀን በላይ ከስራ [መቅረቱ] ተረጋግጦ ያልተወሰነበት ሰራተኛ ያለማስጠንቀቂያ ከስራ ማሰናበት የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 /1/በ/ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ነው፡፡”

  1. ሰ/መ/ቁ. 25005 ቅጽ 5 እና ሰ/መ/ቁ. 26839 ቅጽ 5

የማይንቀሳቀስ ንብረት (መኖሪያ ቤት) ግንባታ ከጋብቻ በፊት ቢጀመርም ግንባታው የተጠናቀቀው ባልና ሚስት በጋብቻ ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ ውስጥ ከሆነ በተለይም አንደኛው ወገን ለቤቱ ግንባታ የገንዘብ አስተዋጽኦ አድርጎ ከሆነ በፍቺ ጊዜ ሁለቱም የቤቱን እኩል ድርሻ የማግኘት መብት እንዳላቸው የህግ ትርጉም የተሰጠው በሰ/መ/ቁ. 25005 ቅጽ 5[5] ነው፡፡ ይህ ትርጉም ግን ፀንቶ መቆየት የቻለው ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻ ነው፡፡

ኀዳር 10 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰ/መ/ቁ. 26839 ቅጽ 5[6] በተመሳሳይ ጉዳይ በተሰጠ የሰበር ውሳኔ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት (መኖሪያ ቤት) ግንባታ ከጋብቻ በፊት ተጀምሮ ባልና ሚስቱ በትዳር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ከተጠናቀቀ በፍቺ ወቅት ለንብረቱ መገኘት ተጋቢዎቹ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተመርምሮ እንደነገሩ ሁኔታ የግል ወይም የጋራ ሊባል ይገባል፡፡ ይህንንም ለመወሰን በንጽጽር ሲታይ አብዛኛው መዋጮ የተደረገው ከግል ነው ወይስ ከጋራ? የሚለውን ከግምት ማስገባቱ ተገቢ እንደሚሆን በውሳኔው ላይ ተመልክቷል፡፡ የንብረት ክፍፍሉን በተመለከተም ንብረቱ በአብዛኛው ከጋራ ሃብት መዋጮ የተገኘ ከሆነና የግል ንብረቱ ትንሽ ከሆነ ንብረቱ የጋራ ሆኖ እንደሚቆጠር፤ በንብረቱ ላይ የተቀላቀለውን የግል ሃብት በተቀላቀለው መጠን የግሉ የሆነው ተጋቢ ሊወስድ እንደሚገባ ከሰ/መ/ቁ. 25005 ያፈነገጠ አቋም ተይዞበታል፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ. 33200 ያልታተመ እና ሰ/መ/ቁ. 44025 ቅጽ 10

በሰ/መ/ቁ. 44025 ቅጽ 10 ንብረት በወራሾች በጋራ ከተያዘ የይርጋ ደንብ ተፈጻሚነትን እንደሚያስቀር ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በሰ/መ/ቁ. 33200[7] በተሰጠ ውሳኔ ግን የጋራ ይዞታ ይርጋን ተፈጻሚ ላለማድረግ በምክንያትነት ሊጠቀስ እንደማይገባው ጠንካራ አቋም ተይዞበት ነበር፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የችሎቱ ሐተታ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

ንብረቱ በጋራም ተያዘ በተናጠል የተጠየቀው ዳኝነት የውርስ አጣሪ ተቋቁሞ ንብረት ለመከፋፈል እስከሆነ ድረስ ይሄው ጥያቄያቸው በሕግ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ካልቀረበ በይርጋ የማይታገድበት ምክንያት አይኖርም ጥያቄው ይርጋ የለውም ማለትም የይርጋን ዓላማ ውጤት አልባ ከማድረግ የተለየ አይሆንም፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ. 17937 ቅጽ 4 እና ሰ/መ/ቁ. 33200 ያልታተመ

በወራሽና ወራሽ መካከል የሚነሳ የንብረት ማስመለስ ክርክር በ3 ዓመት ይርጋ እንደሚታገድ በሰ/መ/ቁ. 17937 ቅጽ 4[8] እና በቀጣይነት ከተሰጡ በርካታ ውሳኔዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በሰ/መ/ቁ. 33200[9] አንድ በወራሽና ወራሽ መካከል የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታ ላይ በሚያቀርበው ክስ ላይ ተፈጻሚነት ያለው ልዩ የይርጋ ድንጋጌ እንደሌለ ተጠቀሶ ይርጋው በፍ/ህ/ቁ. 1845 መሰረት በ10 ዓመት እንደሚታገድ የህግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ. 32013 ቅጽ 6፣ ሰ/መ/ቁ. 44237 ቅጽ 10 እና ሰ/መ/ቁ. 40418 ቅጽ 10

የውርስ ሃብት ክፍፍል ጥያቄ በፍ/ብ/ሕግ ቁ. 1000/1/ በተመለከተው የሦስት ዓመትም ሆነ በፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 974/2/ በተቀመጠው የአምስት ዓመት የጊዜ ገደብ በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን በሰ/መ/ቁ. 32013 ቅጽ 6[10] ትርጉም ከተሰጠ ከሁለት ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ይዘት ባለው ጉዳይ ግልጽ የአቋም ለውጥ ሳይደረግ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ ይርጋ አያግደውም ተብሏል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 44237[11] አመልካች የጠየቁት ዳኝነት ወራሽነታቸውን ማረጋገጣቸውንና የውርሱን ሀብት ተጠሪ ይዘው እየተጠቀሙበት በመሆኑ እንዲያካፍሏቸው ቢጠይቋቸው ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የውርስ ሀብት አጣሪ በፍርድ ቤት እንዲሾምላቸው ነው፡፡ የሰበር ችሎት አመልካች የጠየቁት ዳኝነት የውርስ ሀብት ክፍፍል እንደሆነ በመጠቆም በፍ/ህ/ቁ. 1062 በማናቸውም ጊዜ ሊቀርብ የሚችልና በይርጋ የማይታገድ እንደሆነ በማተት የፍ/ህ/ቁ. 1000/1/ ድንጋጌን ተፈጻሚ በማድረግ የስር ፍ/ቤቶች ክሱን በይርጋ ውድቅ በማድረግ የሰጡትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡

ጥቅምት 10 ቀን 2002 ዓ.ም. በተሰጠ ሌላ ውሳኔ ደግሞ የችሎቱን አቋም ለመጨበጥ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከሰ/መ/ቁ. 40418 ቅጽ 10[12] የህግ ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው የውርስ አጣሪው ባቀረበው ሪፖርት መሰረት የቀረበ የንብረት ልካፈል ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1080/3/ በተደነገገው የአንድ ዓመት የጊዜ ውስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡

  1. ሰ/መ/ቁ. 08751 ቅጽ 6 እና ሰ/መ/ቁ. 93137 ቅጽ 15

የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ሐሰተኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ሰጥቷል በሚል የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ሊቀርብ የሚገባው ለሰበር ችሎቱ ሳይሆን መጀመሪያ ፍርዱን ለፈረደው የስር ፍ/ቤት ነው፡፡ ይህ በሰ/መ/ቁ. 93137 ቅጽ 15[13] የተያዘው የችሎቱ አቋም በተመሳሳይ ጉዳይ በሰ/መ/ቁ. 08751 ቅጽ 6[14] ከተሰጠው ውሳኔ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ በዚህ መዝገብ ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ በተጭበረበረ ሰነድ ላይ በመመስረት እንደሆነ በመግለጽ አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ተቀብሎ ግራ ቀኙን በማከራከር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

[1] አመልካች ወ/ሮ ፈለቀች ሽፈራው እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ በቀለች መንግስቱ /2 ሰዎች/ መጋቢት 20 ቀን 2002 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ የሱፍ ሁሴን እና ተጠሪ አቶ አደን አብደላ ኅዳር 30 ቀን 2003 ዓ.ም.

[3] አመልካች የአ/አ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ፍቅሩ ከበደ የካቲት 3 ቀን 2002 ዓ.ም.

[4] አመልካች የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የደብረማርቆስ መንገዶች ጥገና ዲስትሪክት እና አቶ አስማረ ፈጠነ ጥቅምት 24 ቀን 2008 ዓ.ም.

[5] አመልካች መኮንን በላቸው እና ተጠሪ ወ/ሮ አለሚቱ አደም ኀዳር 3 ቀን 2000 ዓ.ም.

[6] አመልካች ወ/ሮ አስካለ ለማ እና ተጠሪ ሣህለ ሚካኤል በዛብህ ኀዳር 10 ቀን 2000 ዓ.ም.

[7] አመልካች አቶ አወል አማን እና ተጠሪዎች እነ አቶ ናሥር አማን /2 ሰዎች/ ያልታተመ ህዳር 11 ቀን 2001 ዓ.ም

[8] አመልካች ወ/ሮ ድንቄ ተድላ እና ተጠሪ እነ አቶ አባተ ጫኔ መጋቢት 20 ቀን 1999 ዓ.ም.

[9] ዝኒ ከማሁ

[10] አመልካች ደምስ ጥበበሥላሴ እና ተጠሪ ቴዎድሮስ ጥበበሥላሴ መጋቢት 25 ቀን 2000 ዓ.ም.

[11] አመልካች ወ/ሮ ሙለሸዋ ቦጋለ – በራሳቸውን እና ወኪል ለሆኑላቸው /4 ሰዎች/ እና ተጠሪ ወ/ሮ ፈልቃ ቤኛ ሰ/መ/ቁ. 44237 ቅጽ 10 መጋቢት 20 ቀን 2002 ዓ.ም.

[12] አመልካች ተስፋዬ ሞላ እና ተጠሪዎች እነ እሸቱ ሞላ /3 ሰዎች/ ጥቅምት 10 ቀን 2002 ዓ.ም.

[13] አመልካች ወ/ሮ ብጥር ታገለ እና ተጠሪ ወ/ሮ አገር ተሰማ የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

[14] አመልካች ወ/ሮ አበበች በጅጋ እና ተጠሪ እነ ዶ/ር ተስፋዬ አካሉ /2 ሰዎች/ ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም.

2 replies »

  1. Daer Abrham ,as I read most of your articles they are scholarily and well researched.It is not usual to have a writer like you who boldly challenges ad criticizes the decesions of the uighest organ of the country.keep it up.

  2. Thank you, dear Abrham. You’re doing well in raising our awareness regarding legal issues. I would like to encourage you to keep up eroding ignorance & putting the cornerstone of knowledge where others to build on it & give the correct shape to be. You carrying out your civic responsibility & it is on the right track. May the Almighty God Bless You!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.