Site icon Ethiopian Legal Brief

ዳግም ዳኝነት—የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

ዳግም ዳኝነት—የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

የመጨረሻ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ውሳኔው ወይም ትዕዛዙ ሐሰተኛ ማስረጃን መሰረት በማድረግ መሰጠቱ ሲረጋገጥ ጉዳዩ በድጋሚ /እንደገና/ የሚታይበት ስርዓት

በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 6(2) ይግባኝ ሊቀርብበት የሚችል የመጨረሻ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ውሳኔው ወይም ትዕዛዙ የተሰጠው በሃሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሰነድን፣ ሃሰተኛ የምስክርነት ቃልን፣ ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቅሶ የሆነ ተግባርን መሰረት አድርጎ መሆኑን አቤት ባዩ ሲረዳው ጉዳዩ በይግባኝ ከመታየቱ በፊት[1] ውሳኔውን የሰጠው ፍ/ቤት ራሱ ዳኝነቱን በድጋሚ እንዲያይ ጥያቄ ለማቅረብ መብት የሚሰጠው ነው፡፡ የድንጋጌው ሙሉ ይዘትና መንፈስ የሚያሳየው የመጨረሻው ፍርድ ከተሰጠ በሁዋላ ሀሰተኛ ሰነድ ወይም ሀሰተኛ የምስክርነት ቃል ወይም መደለያ እንደተደረገና አቤት ባዩም ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ለማወቅ ያለመቻሉን በሚገባ ለማስረዳት የሚችል የሆነ እንደሆነ፣ እነዚህ ጉዳዮች መኖራቸው ወይም መፈጸማቸው ታውቆና ተገልጾ ቢሆን ኖሮ ለፍርድ መለወጥ ወይም መሻሻል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችል እንደነበር ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ፣ የተሰጠ ፍርድ ሊያስለውጥ የሚችል አዲስ ማስረጃ ማግኘቱ ብቻ ፍርድ እንደገና እንዲታይ የማያደርግ መሆኑን፣ ማስረጃው ፍርዱን በማሳሳት ውጤቱን ያበላሸና ተገቢ ያልሆነ ድርጊትን የሚያሳይ መሆን ያለበት መሆኑን ነው፡፡

በመሆኑም ማስረጃው በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሰነድን፣ ሀሰተኛ የምስክርነት ቃልን ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ ተግባርን መሰረት ያደረገ መሆንና ማስረጃው ፍርዱ በሚሰጥበት ጊዜ ፍርዱ እንደገና ይታይልኝ የሚለው ተከራካሪ ወገን ማስረጃው መኖሩን ያውቀው የነበረ ያለመሆኑ፣ ይግባኝ ቀርቦበት ከሆነ አዲስ ማስረጃው ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ግምት ውስጥ እንዲያስገባ ይግባኙ ለቀረበለት ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ፣ የተገኘው አዲስ ማስረጃ የሀሰት ሰነድን፣ ሀሰተኛ ምስክርነትን፣ መደለያንና የመሳሰሉትን የሚመለከት ለመሆኑ ማረጋገጫ መኖሩን በሚጠቅስ ቃለመሐላ የተደገፈና ማስረጃው አስፈላጊው ትጋት የተደረገበት ቢሆንም ፍርዱ በተሰጠ ጊዜ በአመልካቹ ያልታወቀ መሆኑን የሚገልፅ መሆን ያለበት መሆኑ በቅድመ ሁኔታነት ሊሟሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ድንጋጌው ያስገነዝባል፡፡

የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ጥብቅ መለኪያዎች ያሉት መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት መንፈስ መገንዘብ የምንችለው ጉዳይ ሲሆን የድንጋጌው ጥብቅ የመሆን አይነተኛ አላማም የተሰጡ ውሳኔዎችን አጣራጣሪነት ለማስወገድ መሆኑ ይታመናል፡፡ ስለሆነም የዳግም ዳኝነት ጥያቄ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለውሳኔው መሰረት የሆነው ሰነድ ወይም ማስረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሕጉ የተመለከቱት ሁሉም መመዘዎችን አቤቱታ አቅራቢው ማሟላቱን በቅድሚ ሊያረጋገጥ ይገባል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 104028 ቅጽ 17፣[2] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 6

ፍርድ በድጋሚ እንዲታይ የሚጠይቅ ሰው ሀሰተኛ መረጃ የተሰጠው መንግስት በኃላፊነት ቦታ ላይ ባስቀመጠው ባለስልጣን እና በመንግስት አካል መሆኑን ከማስረዳት አልፎ የመንግስት ባለስልጣን ይህንን ህገወጥ ተግባር የፈፀመበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ሊጠየቅ አይገባውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 91968 ቅጽ 15፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 6፣ ወ/ህ/ቁ. 403፣ 405

የተፈጻሚነት ወሰን

አንድ ተከራካሪ ጠበቃ ወክሎ እንዲከራከር እንጂ የውርስ ሀብት ንብረት ስምምነት ለማድረግ የውክልና ስልጣን አልተሰጠውም በሚል ዳግም ዳኝነት እንዲታይ የሚቀርብ አቤቱታ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 6 ስር አይሸፈንም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 45839 ቅጽ 9[4]

የማስረዳት ግዴታ

በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 6(1)(ሀ) መሰረት ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የሚኖረው የመጨረሻው ፍርድ ወይም ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ የተሰጠው በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሰነድ ወይም ሀሰተኛ የምስክርነት ቃልን ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ የሆነ ተግባርን መሰረት በማድረግ ሲሆን አቤት ባዩም ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ለማወቅ አለመቻሉን ማስረዳት የሚጠበቅበት ከመሆኑም በላይ በፊደል (ለ) እንደተጠቀሰውም እነዚህ የተዘረዘሩት ተግባሮች መፈጸማቸው ቢገለጽ ኖሮ ለተሰጠው ፍርድ መለወጥ ወይም መሻሻል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር አቤት ባዩ የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡

ሰ/መ/ቁ 89641 ቅጽ 15[5]

የሚቀርብበት ጊዜ

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሔ/ቁ. 6 ተጨባጭ ውጤት ሊሰጥ በሚችል አኳኋን ሊተገበር የሚችለው ውሣኔው ሐሰተኛ እና ወንጀል ጠቀስ የሆኑ ተገባሮችን መሰረት በማድረግ የተሰጠ ነው የሚል አቤቱታ እስከቀረበበት እና በቂና አሣማኝ መሆኑን ፍ/ቤቱ እስካመነበት ድረስ ይግባኝ ይባልበትም አይባልበትም ያለልዩነት ሥራ ላይ እንዲውል በሚያስችል ሁኔታ ሲተረጎም ነው፡፡

ዳኝነት እንደገና እንዲታይ (Review of judgement) በሚል የሚቀርብ አቤቱታ አስቀድሞ በተሰጠ ውሣኔ ላይ ይግባኝ የተባለበት ነው በሚል ምክንያት ብቻ ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባ ሰ/መ/ቁ. 16624 ተሰጥቶ የነበረው ትርጉም ተለውጧል፡፡ ስለሆነም ጥያቄው ጉዳዩ በይግባኝ ታይቶ ውሳኔ ከተገኘ በሁዋላም ቢሆን በቁጥር 6 ስር የተመለከቱት መመዘኛዎች ተሟልተው እስከተገኙ ድረስ መቅረብ ይችላል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 43821 ቅጽ 15[6]

የሚቀርብበት ፍርድ ቤት

ማንኛውም ውሳኔ የተሰጠበት ሰው በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6(1)(ሀ) እና (ለ) ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎች ወይም ከእነዚህ አንዱን መሰረት በማድረግ የዳግም ዳኝነት አቤቱታውን ማቅረብ የሚችለው ፍርዱን ለፈረደው ወይም ትዕዛዙን ወይም ውሳኔውን ለሰጠው ፍ/ቤት ስለመሆኑ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6(1) ስር በግልጽ ተመልክቶአል፡፡

የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ሐሰተኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ ሰጥቷል በሚል የዳግም ዳኝነት ጥያቄ ሊቀርብ የሚገባው ለሰበር ችሎቱ ሳይሆን መጀመሪያ ፍርዱን ለፈረደው የስር ፍ/ቤት ነው፡፡

የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ዓይነተኛ ዓላማ ተገቢ ሁኔታዎችና ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸው ሲረጋገጥ በሀሰተኛ ማስረጃ፣ በመደለያና በመሰል ወንጀል ጠቀስ ድርጊቶች ምክንያት የተዛነፈውን ፍትሕ ወደነበረበት መመለስ ነው፡፡ ይህ ሂደት ከሰበር ችሎቶች የስልጣን ወሰን ውጪ የሆነው ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ተግባራት የሚከናወንበት በመሆኑ ምክንያት በሰበር ችሎት ሊስተናገድ የሚችልበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ የተጠቀሰውን የስነ ስርዓት ድንጋጌ ዓላማ ለማሳካት ይቻል ዘንድ የሚኖረው አማራጭ የዳግም ዳኝነት አቤቱታው ፍሬ ነገር የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ተግባራትን የማከናወን ስልጣን ባላቸው የስር ፍ/ቤቶች እንዲስተናገድ ማድረግ ይሆናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 93137 ቅጽ 15[7]

ማስታወሻ

የችሎቱ አቋም በተመሳሳይ ጉዳይ በሰ/መ/ቁ. 08751 ቅጽ 6[8] ከሰጠው ውሳኔ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡

በዚህ መዝገብ ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ በተጭበረበረ ሰነድ ላይ በመመስረት እንደሆነ በመግለጽ አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ተቀብሎ ግራ ቀኙን በማከራከር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን እንደገና እንዲታይ አቤቱታ የቀረበበት የችሎቱ ውሳኔ ተጭበረበረ በተባለው ሰነድ ይዘት ላይ ተመርኩዞ ባለመሰጠቱ የተነሳ አቤቱታው ውድቅ ቢደረግም በሰ/መ/ቁ. 93137 ከተያዘው አቋም አንጻር አቤቱታው ከጅምሩ ሊስተናገድ የሚገባው አልነበረም፡፡

ይግባኝ

ዳኝነት በድጋሚ እንዲታይ በሚቀርብ አቤቱታ ዳኝነቱ በድጋሚ ሊታይ አይገባውም ወይም ይገባዋል? በማለት ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ ወይም ብይን ላይ ይግባኝ ማቅረብ አይቻልም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 42871 ቅጽ 9፣[9] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 6(3) እና (4)

 

[1] በሰ/መ/ቁ 43821 (አመልካች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ አቶ አማረ ገላው ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ. 43821 ቅጽ 9) ዳኝነት እንደገና እንዲታይ ጥያቄው መቅረብ ያለበት ከይግባኝ በፊት እንደሆነ በሰ/መ/ቁ 16624 ተሰጥቶ የነበረው የህግ ትርጉም ተለውጦ ከይግባኝ በኋላም ሊቀርብ እንደሚችል አቋም ተይዞበታል፡፡

[2] አመልካች ወ/ሮ ብዙአየሁ ያለው እና ተጠሪ አቶ ሲሳይ ካሴ የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም.

[3] አመልካች አቶ ግርማ ሰንበት አልቀረቡም እና ተጠሪ፡- ወ/ሮ አልማዝ ገብረየስ ታህሳስ 15 ቀን 200 ዓ.ም.

[4] አመልካች ወ/ሮ ይርጋአለም ከበደ ድና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ፅጌ ሚካኤል / 5 ሰዎች/ ሚያዝያ 5 ቀን 2002 ዓ.ም

[5] አመልካቾች እነ ወ/ሮ ሐረገወይን ብርሃኑ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አዜብ ብርሃኑ /2 ሰዎች/ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም.

[6] አመልካች ወ/ሮ ትርሐስ ፍስሐዬ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዘነበች በሪሁን ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም.

[7] አመልካች ወ/ሮ ብጥር ታገለ እና ተጠሪ ወ/ሮ አገር ተሰማ የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

[8] አመልካች ወ/ሮ አበበች በጅጋ እና ተጠሪ እነ ዶ/ር ተስፋዬ አካሉ /2 ሰዎች/ ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም.

[9] አመልካች የቀድሞ ወረዳ 07 ቀበሌ 32 አስተዳደር ጽ/ቤት እና ተጠሪ ወ/ሮ ጆሮ ዋቅጅራ ጥር 12 ቀን 2002 ዓ.ም.

Exit mobile version