Articles

ሶስተኛ ወገን ተከሳሽ—የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

ሶስተኛ ወገን ተከሳሽ—የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

ከተከሳሽ ጋር ኃላፊነት ሊወስድ ወይም ሊካፈል የሚችል ሦስተኛ ወገን በተከሳሽ ጠያቂነት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደ ክርክሩ የሚገባ ተከራካሪ

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 43/1/ “…ሌላ ሦስተኛ ወገን ከእኔ ጋር ድርሻ ካሣውን መክፈል አለበት…” በሚል ይቀመጥ እንጂ ከዚህ የሕግ አነጋገር ድርሻ ካሣውን የሚለውን ሐረግ ካየነው ትርጉም የሚሰጥ መስሎ አይታይም፡፡ ለምን ቢባል ድርሻ እና ካሣ የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው፡፡ አንዱ ቃል ሌላውንም ሊተካ አይችልም፡፡ ምንጫቸውም የተለያየ ነው፡፡ በተለይም “Where a defendant claims to be entitled to contribution or indemnity from any person . . .” ከሚለው የዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዘኛ ግልባጭ ጋር ከላይ የተመለከተውን ሐረግ ከተመለከትነው “ድርሻ” እና “ካሣ” የተለያዩ ሆነው “ወይም” በሚለው ምህፃረ ቃል የተያያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ድርሻ (Contribution) የሚለው ቃል ለክሱ ምክንያት በሆነው ጉዳይ ከተከሳሹ ጋር የአንድነትና የነጠላ ግዴታ ያለባቸው ወገኖች ኖረው ከሳሽ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1897 መሠረት አንደኛውን ባለዕዳ ብቻ ነጥሎ በከሰሰ ጊዜ ተከሳሹ ከእኔ ጋር ድርሻውን መክፈል ያለበት ሌላ ሦስተኛ ወገን ስላለ የክርክሩ ተካፋይ ይሁንልኝ በማለት በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን በማድረግ፤ እንዲሁም ካሣ (indemnity) የሚለው ቃል ደግሞ ተከሳሹ በተከሰስኩበት ጉዳይ ኃላፊ የምሆን ከሆነ የሚፈረድብኝ ክፍያ እኔን ተክቶ የሚሸፍን ወገን /እንደ ኢንሹራንስ ባለ ጉዳይ/ ስለአለ ጣልቃ ገብቶ ይከራከራር በማለት የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን በማድረግና የሚመለከታቸው ወገኖች በአንድ ፋይል እንደተገናኙ ጉዳዩ የሚያልቅበትን ሥርዓት በመዘርጋት ተከታይ ክስን ለማስቀረት ታስቦ የተቀመጠ ድንጋጌ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ይህ ባይሆን ኖሮ ድርሻ የሚከፍል ወገን እያለ ከተከሳሽ ላይ ብቻ ሲፈረድበት እርሱም በተራው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1908 እና 1909 መሠረት በብልጫ በከፈለው መጠን በሌሎች የጋራ ባለእዳዎች ላይ ክስ ማቅረቡ አይቀሬ ይሆናል፡፡

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 43 አስፈላጊነት ተከታይ ክስ ሳይኖር በክርክርና በማስረጃ አቀራርብ ረገድ ጉዳዩን በአንድ ፍ/ቤት እንዲታይ በማድረግ ኃላፊነት ያለባቸውን እና ሊከፈል የሚገባውን የካሣ መጠን በመወሠንና በመጨረሻም የሚከፍለውን ወገን በመለየት በአጭር ጊዜ በአነስተኛ ወጭ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡

በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 43/2/ ሦስተኛው ወገን በክሱ ውስጥ እንዲገባ ፍ/ቤቱ የፈቀደ እንደሆነ የክሱ ማመልከቻ ግልባጭና ለክሱ የተሠጠው የመከላከያ መልስ እንዲደርሰው ይታዘዛል ተብሎ ከተደነገገው “…በክሱ ውስጥ እንዲገባ…” የሚለው ሐረግ ይህ ሦስተኛ ወገን የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆን መደረጉንና የክርክሩ ተካፋይ (a party to the suit) ከሆነም ስለ ጉዳዩ የሚያቀርበው ክርክር ድርሻ ወይም ካሣ ክፍያ የመክፈል ግዴታ ያለበት መሆኑን በሚመለከት ክርክር ካለው ከተከሳሽ ጋር ክርክር ለማድረግ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ከሳሹ ያቀረበውን ክስ አስመልክቶ በኃላፊነትና በካሣ መጠን ረገድ ክርክር ማቅረብ የሚችል መሆኑን አመልካች ነው፡፡

የክሱ ማመልከቻና ለክሱ የተሰጠው የመከላከያ መልስ እንዲደርሰው የሚደረገውም የሦስተኛ ወገን ተከሳሹ ክርክር እንደአስፈላጊ’ቱ ከተከሳሹ ጋር ሊሆን እንደሚችልና በተካሹ እንደተገለፀው ድርሻ ወይም የካሣ ክፍያ ካለበት ደግሞ ተከሳሹ ለከሣሽ ኃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም? ካለበትስ ለደረሰው ጉዳት ሊከፈል የሚገባው የካሣ መጠን ምን ያህል ነው የሚለውን በሚመለከት በተከሳሽ እግር ተተክቶ ከከሳሹ ጋር መሟገት እንዲችል ነው፡፡ በዚሁ በቁጥር 43/2/ “…በክሱ ውስጥ እንዳለ ይቆጠራል” የሚለውና የዚህ ግልባጭ የሆነው የእንግሊዝኛው ንባብ “…shall be deemed to be in the same position as a defendant” የሚለው አነጋገር ይህንኑ አባባል የሚደግፍ ነው፡፡

እንዲሁም ይህ ሦስተኛ ወገን ተከሣሽ ቀርቦ በክርክሩ ውስጥ ገብቶ እንዲከራከር ጥሪ ተደርጐለት ያልቀረበ እንደሆነ ምን ውጤት እንደሚያስከትል በሚደነግገው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 76 ላይ፤

“…ይህ ሦስተኛ ወገን ቀርቦ በክርክሩ ውስጥ በመግባት መልስ እንዲሰጥ ፍ/ቤቱ አዞ መጥሪያው ከደረሰው በኋላ ቀርቦ መልስ ሳይሰጥ ወይም አላፊ የማይሆንበትን ምክንያት በማስረዳት ሳይከራከር የቀረ እንደሆነ…” /ሰረዝ የተጨመረ/

የሚለውን የሕግ አነጋገር፤

“Where a third party duly summoned to appear under Art. 43(2) fails without good cause to appear for the purpose of disputing the plaintiff’s claim against the defenders on whose behalf the summon was issued, or his own liability to the defendant…” (emphasis added.)

ከሚለው የእንግሊዘኛ ግልባጭ ጋር አያይዘን ከተመለከትነው ሦስተኛው ወገን ተከሳሽ በክርክሩ ውስጥ እንዲገባ ከተፈቀደ የክርክሩ ተካፋይ ሆኖ የሚያቀርበው ክርክር ሁለት ፈርጅ ሊይዝ የሚችል መሆኑን የሚያሣይ ነው፡፡ ይኸውም፤

  • 1ኛው ከተከሳሽ ጋር ሆኖ ድርሻ ክፍያ ወይም ስለተከሣሽ ሆኖ የካሣ ክፍያ የመክፈል ግዴታ ያለበት መሆኑን ተቀብሎ በተከሳሽ እግር በመተካት ተከሳሽ ለከሳሽ ኃላፊነት የማይኖርበት መሆኑን፤ ኃላፊነት አለበት ንኳ ቢባል ሊከፈል በሚገባው የካሣ መጠን ላይ ከከሳሽ ጋር ክርክር በማድረግ መሟገት የሚችልበት ክርክር ሲሆን
  • ሁለተኛው ደግሞ ድርሻ ወይም ካሣ ለመክፈል ለተከሳሽ ከህግ ወይም ከውል የመነጨ ግዴታ የለብኝም በማለት መከራከር የሚችልበት መንገድ ነው፡፡

ስለሆነም የድንጋጌው ይዘት ብቻ ስንመለከተው እንኳ በክርክር ውስጥ ገብቶ እንዲከራከር የተጠራ ሦስተኛ ወገን ተከሣሽ በክርክሩ ከገባ በኋላ መሟገት የሚችለው ከተከሳሽ ጋር እንጂ ከከሣሽ ጋር ለመከራክር የሚያስችለው መብት የለውም የሚለው መደምደሚያ ህጋዊ ድጋፍ ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 23692 ቅጽ 6፣[1] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 43፣ 76፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ 1908፣ 1909

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 43 መሰረት ወደ ክርክሩ እንዲገባ የሚጠራ ጣልቃ ገብ ተከራካሪ ወገን ከመነሻውም ከተከሳሹ ጋር የሕግ ወይም የውል ግንኙነት የለኝም በማለት ክርክር ከአቀረበ የክርክሩ ተሳታፊ የሚሆንበት አግባብ የለም፡፡ እንዲህ አይነት ክርክር እልባት ማግኘት ያለበት በተለየ ክስ እና የክርክር መዝገብ እንጂ ከሳሽ ባቀረበው መዝገብ ሊሆን አይገባም፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 43 ድንጋጌ አላማም እንዲህ አይነት ክርክሮችን ሁሉ በአንድ አይነት መዝገብ አጠቃልሎ ለመወሰን ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይልቁንም ጣልቃ ገብ ከመነሻውም ክዶ በተከራከረበት ጉዳይ የተከሳሽንና የጣልቃ ገብን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ ውሳኔ መስጠት ከሳሽ ያቀረበው ክስ ያላግባብ ጊዜና ወጪን እንዲጨምር የማድረግ ውጤት የሚኖረው ይሆናል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 79465 ቅጽ 14፣[2] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 43

በግጭት ምክንያት በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ መኪና ባለቤት ካሳ እንዲከፍል ክስ በቀረበበት ጊዜ መኪናው በመሸጡ ገዢው ወደ ክርክሩ እንዲገባለት ከጠየቀ የባለቤትነት ስሙ ወደ ገዢው ባይዘወርም ግጭቱ በደረሰበት ጊዜ ገዢው መኪናውን ተረክቦ በይዞታ ሥር ከነበረ ገዢው ወደ ክርክሩ መግባት አለበት፡፡ የመኪናው ባለቤትም ሆነ ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ መኪናውን ሲጠቀምበት የነበረ ሰው ሁለቱም ኃላፉነት ቢኖርባቸውም የመጨረሻው የመካስ ኃላፊነት የሚወድቀው መኪናውን ይዞ ሲገለገልበት የነበረው ሰው ላይ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 41544 ቅጽ 8[3]

የዳኝነት ስልጣን

አንድን ክርክር በማስተናገድ ላይ ያለ የክልል ፍ/ቤት በፌዴራል መንግስት የተመዘገበ ተቋም (ድርጅት) አግባብነት ያለው የጣልቃ ገብ አቤቱታ በቀረበለት ጊዜ ጉዳዩን ጣልቃ ገቡን ወደ ክርክሩ በማስገባት አይቶ ለመወሰን ስልጣን የሌለው በመሆኑ ክርክሩ ጣልቃ ገብን ባካተተ መልኩ ለማየት ወደሚችለውና ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ጉዳዩ ቀርቦ ሊታይ የሚገባ መሆኑን ገልጾ መዝገቡን መዝጋትና ተከራካሪዎችን ማሰናበት ይገባዋል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 90920 ቅጽ 15፣[4] ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(4)፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስት አንቀጽ 64(4)፣ ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 9፣ 231(1) ለ፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1998 አንቀጽ 5(6)፣ 14

ይሁን እንጂ በአንድ ክርክር ሂደት ወደ ክርክሩ እንዲገባ የተደረገ ተከራካሪ ወገን ጉዳዩን የፌዴራል የሚያደርገው የነበረ ሁኖ እያለ ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት ስልጣን ሳይኖረው ስረ ነገሩን አስተናግዶ ዳኝነት ከሰጠ በኋላ ይኼው ተከራካሪ ወገን በይግባኝ ደረጃ በነበረው ክርክር የተሠጠውን ዳኝነት ተቀብሎ ከወጣ በኋላ በሌሎች ጉዳዩን የፌዴራል ሊያደርጉ በማይችሉ ተከራካሪ ወገኞች መካከል የተሰጠው ውሳኔ ከመነሻውም የፌዴራል ጉዳይ ነው ብሎ መወሰን አግባብነት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 95033 ቅጽ 16፣[5] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 43(1)

 

[1] አመልካች አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና መልስ ሰጭዎች እነ አሊ መሐመድ ሐምሌ 03 ቀን 1999 ዓ.ም.

[2] አመልካች ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ አ/ማ እና ተጠሪ እነ አቶ አገኘው ገረመው /2 ሰዎች/ ጥር 14 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.

[3] አመልካች ሠላም የሕዝብ ማመለለሻ አ/ማ እና ተጠሪ ኒያላ ኢንሹራንስ አ/ማ ሀምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም.

[4] አመልካች ዓባይ ኢንሹራንስ አ.ማ እና ተጠሪዎች አቶ አለማየሁ አሰፋ ህዳር 06 ቀን 2006 ዓ.ም.

[5] አመልካች አቶ ስንታየሁ ተፈሪ እና ተጠሪ ወ/ሮ ማርታ በቀለ መጋቢት 25ቀን 2006 ዓ.ም.

1 reply »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.