Articles

አስተዳደራዊ ድንጋጌ የማውጣት (ከፊል የህግ አውጭነት) ስልጣን ምንነት፣ ባህርይ እና አስፈላጊነት

ምንነት እና ባህርይ

የአስተዳደር መ/ቤቶች ከመደበኛው የማስፈጸም ስልጣናቸው በተጨማሪ በህግ አውጭው በሚሰጣቸው ውክልና መሰረት አስተዳደራዊ መመሪያ የማውጣት ስልጣን አላቸው፡፡ የሚኒስትሮች ም/ቤት እንዲሁ ከተወካዮች ም/ቤት በሚሰጠው የውክልና ስልጣን ደንቦችን ይደነግጋል፡፡ ብቁና ውጤታማ አስተዳደር እንዲሰፍን የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን፣ ተግባርና ግዴታ በተጨባጭ ማሳካት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስኬት እንዲኖር ደግሞ የማስፈፀም ስልጣን ብቻውን አይበቃም፡፡ ጠቅለል ያለ ይዘት ያላቸው በፓርላማ የሚወጡ ህጐች የፖሊሲ ደንቦችን ከማስቀመጥ ባለፈ ቴክኒካልና ዝርዝር ጉዳዮችን ስለማይዳስሱ በየጊዜው ለሚነሱ ችግሮች በዓይነትና በጥራት ምላሽ መስጠት ይሳናቸዋል፡፡ ስለሆነም በውክልና አስተዳደራዊ ድንጋጌዎችን የማውጣት ስልጣን አስፈላጊነት ከሁለት አቅጣጫዎች ማለትም ከአስተዳደር ስራ ውጤታማነት እና ከህግ አውጭው ውስንነት አንፃር ሊቃኝ ይችላል፡፡

አስተዳደራዊ ደንብና መመሪያ ማውጣት የአስተዳደር ህግ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ ከነፃ ገበያ መከሰት በኃላ ተከትሎ የመጣው ዘመናዊው የማህበራዊ ዋስትና መንግስት (welfare state) ካስመዘገባቸው እድገቶች አንዱ የስራ አስፈፃሚው አካል ህግ የማውጣት ስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ነው፡፡

በውክልና ህግ ለማውጣት ዋናው የስልጣን ምንጭ ህግ አውጭው እንደመሆኑ የተወካዮች ም/ቤት በማያወላውልና ግልጽ በሆነ መልኩ ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ወይም ለአስተዳደር መ/ቤቶች ካልሰጠ እነዚህ አካላት ደንብ ሆነ መመሪያ ለማውጣት ከህገ መንግስት የመነጨ ስልጣን የላቸውም፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የሚኒስትሮች ም/ቤት ሆነ የአስተዳደር መ/ቤቶች ደንብና መመሪያ እንዲያወጡ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ስልጣን አይሰጣቸውም፡፡ በፌደራል ደረጃ ህግ የማውጣት ስልጣን የተወካዮች ም/ቤት ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ የየክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ህግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል በህገ-መንግስቱ ላይ የለም፡፡

ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣን ምንጩ የተወካዮች ም/ቤት ብቻ ነው ከተባለ ይህ አካል ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ማስተላለፍ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመርመሩ ተገቢ ሆናል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ላይ የተወካዮች ም/ቤት ህግ የማውጣት ስልጣኑን በውክልና እንዲያስተላልፍ የሚፈቅድለት ግልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ ብዙዎች የመስኩ ምሁራን እንደሚስማሙበት ግን ህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል በውክልና ለማስተላለፍ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ስልጣን (inherent power) አለው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ያለገደብ ከህዝብ የተሰጠውን ስልጣን በውክልና ስም ሊያስተላልፍ አይችልም፡፡

በመሰረቱ በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ ከመንግስት አስተዳደር እየተለጠጠ መምጣት ጋር ተያያዥ የሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡት ክስተት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ልዩ ሁኔታ እንጂ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ ህግ አውጭው ምንም እንኳን በከፊል ስልጣኑን ማስተላለፍ ቢኖርበትም የፖሊሲ ጥያቄዎችን የሚነኩ መሰረታዊ ጉዳዩች በደንብ ወይም በመመሪያ እንዲወሰኑ ውክልና መስጠት የለበትም፡፡ የተፈጻሚነቱ ወሰኑ በህግ አውጪው በሚወጣው ህግ ላይ የሚታዩ ቀዳዳዎችን ለመድፈን ብሎም የፖሊሲ ጥያቄዎችን በማይነኩ ዝርዝርና ጥቃቅን ቴክኒካል ጉዳዮች መገደብ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር አፈጻጸሙ በጠባቡ ሊሆን ይገባዋል፡፡

        አስፈላጊነት

በተለያዩ አገራት እንደታየው ህግ አውጭው ከሚያወጣቸው ህጐች በበለጠ የአስተዳደር መ/ቤቶች የሚያወጧቸው መመሪያዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ በየጊዜው እያደገና እየተወሳሰበ የመጣው የመንግስት አስተዳደር ስራና የህግ አውጭው ለዚህ ስራ ውጤታማነት የሚያግዙ ህጐችን በዓይነትና በጥራት ለማቅረብ አለመቻል በውክልና ስልጣን የሚወጣ ህግ አማራጭ ሳይሆን የግድ መሆኑን ያሳየናል፡፡

አስፈላጊነቱ ጎልቶ ቢታይም በመስኩ ሊቃውንት ጠንካራ ተቃውሞ ሳይገጥመው አልቀረም፡፡ እንደብዙዎች እምነት የአስተዳደር መ/ቤቶች ህግ የማውጣት ስልጣን በዜጐች መብት ላይ በሩን ዘግቶ ለአምባገነናዊነት በሩን የሚከፍት አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ የተቃውሞው መሰረቱ ንድፈ ሀሳባዊ ሲሆን የስልጣን ኢ-ተወካይነት ንድፈ ሀሳብ (theory of non delegability of power) አንዱ ነው፡፡ በላቲን (potestas delegari non potest delegare) ተብሎ ሲጠራ በእንግሲዝኛው (power once delegated should not be re-delegated) የሚል መልእክት አለው፡፡ ይህም ወደ አማርኛ ሲመለስ በውክልና የተሰጠ ስልጣን እንደገና በውክልና ሊተላለፍ አይችልም እንደ ማለት ነው፡፡ በአጭር አገላለፅ ህግ አውጭው ህግ የማውጣት ስልጣኑን የሚያገኘው ከመራጩ ህዝብ እንደመሆኑ ይህን በአደራ የተቀበለውን ስልጣን እንደገና (በድጋሚ) ለአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና ማስተላለፍ የለበትም ማለት ነው፡፡

የህግ አውጭነት የስልጣን ምንጩ ህዝብ ነው፡፡ የአንድ አገር ህዝብ ተወካዮቹን ሲመርጥ ችሎታና ብቃታቸውን መሰረት አድርጐ ያስተዳድሩኛል፤ ለእኔ ይሰሩልኛል፣ ትክክለኛውን ህግ ያወጡልኛል በሚል እምነት ጥሎባቸው ነው፡፡ ህግ አውጭው በውክልና በአደራ ከህዝቡ የተሰጠውን ስልጣን በአግባቡ በመገልገል ልማት፤ እድገት፤ ፍትህ፣ መልካም ስርዓትና ሰላም የሚያሰፍኑ ህጐችን ማውጣት አለበት፡፡ ህዝቡ ድምፁን ሰጥቶ ተወካዮቹን ሲመርጥና ስልጣን ሲሰጥ ይህን የህግ አውጭነት ስልጣን ላልተመረጡ ግን ለተሾሙ ስራ አስፈፃሚዎች በውክልና እንዲያስተላልፉት አይደለም፡፡ ከዚህ ሀሳብ በተቃራኒ ስልጣን በውክልና ከተላለፈ ህዝቡ ድምፅ ሰጥቶ ባልመረጣቸው (ስራ አስፈፃሚዎች) እየተገዛ ነው፡፡

ሁለተኛው የውክልና ህግ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞ ከስልጣን ክፍፍል መርህ (separation of powers) የሚነሳ ሲሆን ዞሮ ዞሮ መሰረቱ ለአምባገነናዊነት ያጋልጣል የሚል ነው፡፡ በስልጣን ክፍፍል መርህ መሰረት ህግ ማውጣት ለህግ አውጭው፤ ህግ መተርጐም ለፍርድ ሰጭው፤ ህግ ማስፈፀም ለአስፈጻሚ ተብሎ የእያንዳንዱ የመንግስት አካል ስልጣኑ ተመድቦና ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ አንድ የመንግስት አካል በተደራራቢነት ከአንድ በላይ ስልጣን የያዘ እንደሆነ ከራሱ በላይ ተቆጣጣሪ የሌለው ስልጣኑን በዘፈቀደ የሚጠቀም አምባገነን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስራ አስፈፃሚው ከተመደበለት ህግ የማስፈፀም ተግባር በተጨማሪ በደንብና መመሪያ ስም ህግ የሚያወጣ ከሆነ ሁለት የመንግስት ስልጣናትን ደርቦ ስለመያዙ ያም የስልጣን ክፍፍል መርህን መጣሱ ግልጽነቱ ጐልቶ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ንድፈ ሀሳብ ተቃውሞዎች መሰረት በውክልና የሚወጣ ህግ አስተዳደራዊ አምባገነናዊነት፤ የበዘፈቀደ አሰራር እና በስልጣን አለአግባብ መገልገል እንዲስፋፋና ስር እንዲሰድ ያደርጋል በሚል ከመስኩ ባለሙያዎች የሰላ ሂስና ትችት ሲገጥመው ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝ አገር ውስጥ ሎርድ ሄዋርት የተባሉ የተከበሩ ዳኛና ምሁር በአገራቸው በየጊዜው በፍጥነት እያደገ የመጣውን የአስተዳደር መ/ቤቶች በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣንና አሰራር The New Despotism በሚለው መጽሀፋቸው እ.ኤ.አ. በ1931 ዓ.ም. ያቀረቡት ጠንካራ ተቃውሞ የእንግሊዝ ፓርላማ ስለጉዳዩ የሚያጠና አጣሪ እንዲሾምና ውሳኔ እንዲያሳልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ከምርመራው በኋላ የኬሪ ሪፖርት ተብሎ የሚታወቀው የምርመራ ሪፖርት የደረሰበት ድምዳሜ የውክልና ህግ እንግሊዝ ውስጥ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ይህም በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ተቀባይነት እንደሌለው ካተተ በኋላ በተግባር ግን የግድ አስፈላጊና መቅረት የሌለበት አሰራር መሆኑን በአጽንኦት ገልጿል፡፡

ስለሆነም ከላይ የቀረቡት ንድፍ ንድፈ ሀሳባዊ ተቃውሞዎች አሳማኝ የመሆናቸውን ያህል እየተወሳሰበ ከመጣው የመንግስት አስተዳደር ስራ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ተግባራዊ ምክንያቶች አስፈላጊነቱን አይቀሬና የበለጠ አሳማኝ አድርገውታል፡፡ የአስተዳደር መ/ቤቶች በህግ አውጭው በሚወጡት አዋጆች ላይ ብቻ ተንተርሰው ውጤታማ አስተዳደር ማስፈን አይቻላቸውም፡፡ ማህበራዊ አገልግሎት ለማቅረብ ሆነ መሰረተ ልማት ለመገንባት በአጠቃላይ በቅርበት ለሚታዩና በየጊዜው ተለዋዋጭ ለሆኑ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ቢያንስ የተወሰኑ ጉዳዮች ለአስተዳደር መ/ቤቶች ሊተዉ ይገባል፡፡ ለዚህም ይመስላል ታዋቂው የአስተዳደር ህግ ምሁር ዌድ (H.W.R. wade) የውክልና ህግን “መጥፎ ግን አስፈላጊ” (Necessary evil) ሲል የሚገልፀው፡፡ የውክልና ህግን በተግባር አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ሀ. የጊዜ እጥረት

ህግ አውጭው ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በውክልና ለማስተላፍ ከሚገደድባቸው ምክንያቶች አንዱ ከራሱ ከህግ አውጭነቱ የሚመነጭ ችግር ነው፡፡ አንድን አዋጅ ለመደንገግ ከሚወስደው ረጅም ጊዜና ተፈፃሚ ከሚሆነው የጠበቀ የስነ-ስርዓት አካሄድ አንፃር ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉ ህጐችን በብዛትና በጥራት ለማውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ የተወካዮች ም/ቤትን ያየን እንደሆነ ለሁለት ወራት የክረምት የእረፍት ጊዜና በመካከል ለአንድ ወር ለእረፍት ከተበተነ ጠቅላላ የስራ ጊዜው ከዘጠኝ ወራት አይበልጥም፡፡ ከዘጠኙ ወራት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ተቀንሰው በሚቀሩት የስራ ቀናት ባሉት አጭር የስራ ሰዓታት ለአገሪቱ አስፈላጊ አዋጆችን ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ማውጣት አዳጋች ነው፡፡ የመስኩ ባለሞያዎች እንደሚናገሩት የአንድ አገር ፓርላማ ለተከታታይ 365 ቀናት፣ ድፍን 24 ሰዓታት በስራ ላይ ቢቆይ እንኳን በብዛትና በጥራት ለአገሪቱ አስፈላጊ የሆኑ ህጐችን ማቅረብ ይሳነዋል፡፡

ለ. የእውቀት እጥረት

የህዝብ ተመራጮች ለመመረጣቸው ምክንያት እውቀት ወይም ብቃት አንዱ መለኪያ ቢሆንም ዋናው መስፈርት ግን በህዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታና ተቀባይነት ነው፡፡ በጠቅላላ ጉዳዮች ጠቅላላ እውቀት ይኖራቸዋል ብለን ብንገምት እንኳን ከመንግስት አስተዳደር ውስብስብነት አንፃር ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ የበለጠ እውቀትና ችሎታ ያለው በስራ አስፈፃሚው ዘንድ ነው፡፡ ስለሆነም ፓርላማው ትኩረቱን በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ዝርዝር የአፈፃፀም ስልት የሚጠይቁ ቴክኒካል ጉዳዮች በደንብና በመመሪያ እንዲወሰኑ ስልጣኑን በውክልና ማስተላለፍ የግድ ይለዋል፡፡ በፓርላማው ዘንድ የእውቀት እጥረት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር መ/ቤቶች በተቋቋሙለት ዓላማ ስር ልዩና ብቁ የሰው ኃይል ያላቸው መሆኑ ስልጣንን በውክልና ማስተላለፍ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ተመራጭም ያደርገዋል፡፡

ሐ. ተለዋዋጭ ሁኔታ

አንድ ህግ ፀድቆ ከወጣ በኃላ ወደፊት ለሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ በቂ ምላሽ አይሰጥም፡፡ መሰረታዊው ችግር እልባት ቢያገኝ እንኳን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጠሩ የአፈፃፀም ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የህግ አውጭው የህግ አወጣጥ ስነ-ስርዓት የጠበቀና ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ አንፃር በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ከተለዋዋጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች አንጻር በተከታታይ አዋጅ በማውጣት ምላሽ መስጠት አይታሰብም፡፡ በተቃራኒው ደንብና መመሪያ የማውጣት ስነ-ስርዓት እጅጉን የቀለለ እንደመሆኑ ችግሮችን እየተከታተሉ አግባብነት ያለው መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል፡፡ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መፍትሔ ለመስጠት አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

መ. አስቸኳይ ሁኔታ

አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ባጋጠመ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት ከሚያስፈልገው ረጅም ጊዜ አንፃር ፈጣን ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንፃሩ ደንብና መመሪያ በአንድ ሳምንት ምናልባትም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ሊወጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም ልዩና አስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ከፓርላማው ይልቅ ስራ አስፈፃፀሚው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ በውክልና ህግ የማውጣት ስልጣን አስፈላጊ ነው፡፡

 

4 replies »

  1. thank you Abrhish, i have been using your blog from 2015, I am not a law professional but becoming lawyer due to you blog.

    thank you ended and keep it up.

  2. thanku so much abreham please about annual leave from 14 days, 15 ,16 upto which the last increment days please help i understand the last day 35 day the long year service but another information or civil servant low please sent. thanku somuch

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.