Articles

ማመሳሰል/መለየት እና የህግ ትርጉም አስገዳጅነት

አዋጅ ቁ. 454/1997 በስር ፍ/ቤቶች ላይ ድርብ ግዴታዎችን ይጥላል፡፡ የመጀመሪያው አግባብነት ባላቸው ሁኔታዎች የሰበር ችሎትን የህግ ትርጉም መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን የዚሁ ግዴታ ግልባጭ ገፅታ የሆነው ሁለተኛ ደግሞ አግባብነት በሌላቸው ሁኔታዎች ተፈጻሚ ከማድረግ መቆጠብ ናቸው፡፡ ለግዴታዎቹ ውጤታማነት ፈቃድ ብቻ ሳይሆን እውቀት ጭምር ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤት በበፊተኛው የማመሳሰል በኋለኛው የመለየት ክህሎት ሊኖረው ይገባል፡፡

የሰበር ችሎት ትርጉም በሁሉም እርከን ላይ በሚገኙ ፍ/ቤቶች አስገዳጅነት እንዲኖረው ህግ አውጪው በአዋጅ ቁ. 454/1997 ሲደነግግ የአስገዳጅነት የተፈጻሚነት ወሰኑ በምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ሊሆን እንደሚገባ ብዙም አላስጨነቀውም፡፡ እናም እንደዋዛ በዝምታ አልፎታል፡፡ ይህን ችግር ችሎቱ አስቀድሞ የተገነዘበው ይመስላል፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ቢሆንም በአስገዳጅነት እና በጉዳዮች ዓይነት መካከል ያለውን ዝምድና በሰ/መ/ቁ. 61221 ቅጽ 14[1] ለመለየት ተሞክሯል፡፡

በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) ስር እንደተመለከተው ከአምስት ያላነሱ የዚህ ችሎት ዳኞች ተሰይመው የሚሰጡት የሕግ ትርጉም ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማናቸውም እርከን የሚገኝን ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ ነው፡፡ አንድ የሕግ ትርጉም ለተመሳሳይ ጉዳይ ገዥነት እንዲኖረው ለማድረግ ደግሞ በመሰረታዊ ነጥቦች ላይ ጉዳዮቹ መመሳሰል ያለባቸው ስለመሆኑ ከአስገዳጅ የሕግ ትርጉም ፅንሰ ሀሳብ የምንገነዘበው ነው፡፡

የትኞቹ ናቸው መሰረታዊ ነጥቦች የሚባሉት? የተሟላ ባይሆንም ለጥያቄው በሰ/መ/ቁ. 67924 ቅጽ 13[2] ምላሽ ቀርቧል፡፡ በዚሁ መሰረት፤

በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የህግ አተረጓጎምና አፈጻጸም ማስፈን ይቻል ዘንድ እንደ አንድ ስልት ተቆጥሮ በወጣው በአዋጅ ቁጥር 454/97 ድንጋጌ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች ተሰይመው የሰጡት የህግ ትርጉም በበታች ፍ/ቤቶች የአስገዳጅነት ኃይል ወይም ባህርይ የሚኖረው ትርጉም በተሰጠበት እና ዳኝነት እንዲሰጥበት [በቀረቡት] ጉዳዮች መካከል የተነሳው የፍሬ ነገርና የህግ ጥያቄ የተመሳሰለ ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ ህግና ፍሬ ነገር መመሳሰል አለባቸው፡፡ ፈታኙ ጥያቄ ምን ያህል መመሳሰል አለባቸው ነው፡፡ ሙሉ በሚሉ መመሳሰል አለባቸው ወይስ በአብዛኛው መመሳሰል አለባቸው? በአብዛኛው ከተባለስ መመሳሰሉ ሊኖር የሚገባው ለህግ ትርጉም ቀጥተኛ ተዛምዶ ያላቸው ጥቂት ግን ደግሞ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች መመሳሰል ነው ወይስ በቁጥር የሚበዙት ፍሬ ነገሮች መመሳሰል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች እጥር ምጥን ያለ ምላሽ ማስቀመጥ ይከብዳል፡፡ ከማመሳሰል ጋር የተያያዙ ተያያዥ ጥያቄዎች የብዙ ዘመናት የዳበረ ልምድ ባላቸው የኮመን ሎው አገራት ሳይቀር በአንድ ቀመር አልተፈቱም፡፡ እያንዳንዱ ክርክር የግል ባህርያት አሉት፡፡ ተመሳሳይ ጉዳዮችን በተመሳሳይ መንገድ የመወሰን ስርዓት ከዓላማው አንጻር (ወጥነትና ተገማችነት) ብቻ እየተመነዘረ ከታየ የሚያስጎመጅ ገጽታ ቢላበስም አደጋዎችም እንዳሉት መዘንጋት የለበትም፡፡ ይሄን ጠቃሚ ነጥብ የሰበር ችሎት ሳይቀር አምኖ ተቀብሎታል፡፡

እንደሚታወቀው ክርክሮች የሚወሰኑት እንደ የግል ባህሪያቸው እየታየ ነው፡፡ በአንድ ጉዳይ የተነሣውን ክርክር እልባት ለመስጠት የተሰጠ ውሣኔ በሌላ ጉዳይ ለተነሣው ክርክርም እልባት ለመስጠት ያስችላል ብሎ ሙሉ በሙሉ መደምደም ትክክልም ተገቢም አይይደም፡፡[3]

በችሎቱ የ10 ዓመት ጉዞ በበርካታ ውሳኔዎች የተሰጡ የህግ ትርጉሞች በስር ፍ/ቤት በቀዳሚነት ብሎም በደጋፊነት እየተጠቀሱ አከራካሪ የህግ ጭብጦችን ለመፍታት የማይናቅ ፋይዳ ማበርከታቸው ባይካድም ተጨማሪ የክርክር ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውም በገሀድ የሚታይ ሐቅ ነው፡፡ በታተሙት 19 ቅጾች ውስጥ የስር ፍ/ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የሰበር መዝገብ ከተያዘው ጉዳይ ጋር አግባብነት የለውም ተብሎ በችሎቱ የተተቸበት አጋጣሚ በየጊዜው መጨመር እንጂ መቀነስ አላሳየም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አግባብነት ያለው የህግ ትርጉም ሳይጠቀስ በዝምታ ታልፎ የሚሰጥ ውሳኔ ሰበር ደርሶ የሚታረምበት ክስተት ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በአዋጅ ቁ. 454/1997 በቸልታ የታለፈው የጉዳዮች መመሳሰል አሁን አሁን ትኩረት የሚያሻው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሰበር ችሎት ህግ በመተርጎም ብቻ ሳይሆን የራሱን ውሳኔዎች በመተርጎም ስራ መጠመዱ አይቀሬ ነው፡፡

የስር ፍ/ቤቶች በጥረትና በጥናት የታገዘ ልምድ እያካበቱ ሲመጡ የማመሳሰል ብቃታቸው በጊዜ ሂደት መዳበሩ አይቀርም፡፡ ሆኖም ማመሳሰል በቅንነትና በታማኝነት ካልታገዘ ውጤታማነቱ ይኮላሻል፡፡ ዳኞች ዳኝነት በሚሰጡበት መዝገብ ላይ ያሉትን ፍሬ ነገሮችና የህግ ነጥቦች ተመሳሳይ ይዘት ካለው የሰበር ውሳኔ ጋር በማነጻጸር የልዩነት ነጥቦችን ለማግዘፍ፤ የማይቀራረቡትን ደግሞ እንደምንም አጠጋግቶ ለማመሳሰል ሰፊ ስልጣን አላቸው፡፡ ከዚህ አድራጎት የሚገድባቸው ለዳኝነታዊ ስነ ምግባራቸው ያላቸው ተገዢነት ብቻ ነው፡፡ ዳኞች መሰረታዊ የህግ ስህተት የሚሰሩት ባለማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ ከፊሎቹ በፍርድ ቤት የሚፈጸሙ ስህተቶች አንደኛውን ተከራካሪ ወገን ለመጥቀም ሆነ ተብሎ በማወቅ የሚሰሩ ስህተቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስህተቶች ሰበር ችሎት ብቻውን አያቃናቸውም፡፡ ልክ እንደ ህግ መተርጎም ሁሉ ማመሳሰልም ነጻ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓት ካልሰፈነ አያብብም፡፡ ይልቅስ በአጭር ይቀጫል፡፡

እዚህ ላይ የሰበር ችሎቱን ሚና ማውሳት ያስፈልጋል፡፡ ግልፅና ጥራት ያለው ውሳኔ ከሌለ ማመሳሰልን ይበልጥ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ በስር ፍ/ቤቶች የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች አገላለጽ፣ መሰረታዊ የፍሬ ነገር እና የህግ ጥያቄዎችን በአግባቡ መለየት፣ ህጉ የተተረጎመበትን መንገድ ሳያወሳስቡ ማመልከት፣ መሰረታዊ የህግ ጥያቄው በየትኛው የህግ አተረጓጎም ስልት እንደተፈታ ማብራራት፣ የቋንቋውን የሰዋሰው ስርዓት የጠበቀ ቀላልና ሁሉም የሚረዳው አገላለጽ መጠቀም፣ አስገዳጅ የሆነውን ገዢ ደንብ (የህግ ትርጉም) አሳጥሮ ማጠቃለል በአጠቃላይ ለውሳኔው ይዘት ብቻ ሳይሆን ለውሳኔ አጻጻፍ መርሆዎችና ደንቦች ተገቢውን ቦታ መስጠት ወዘተ…ሁልጊዜ ከችሎቱ የሚጠበቁ ናቸው፡፡

ሰበር ችሎት የህግ ትርጉም ሰጠ ማለት የተተረጎመው ድንጋጌ አከራካሪነቱ ይቀራል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በችሎቱ ትርጉም ላይ የአረዳድ ልዩነት ይፈጠራል፡፡ ለዚህም ነው ችሎቱ በሰ/መ/ቁ. 80350 ቅጽ 14[4] የጥንቃቄ መልዕክት ለማስተላለፍ የተገደደው፤

ይሁን እንጂ ይህ የሰበር ሰሚ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መንፈሱ በጥንቃቄ ታይቶ ግንዛቤ ካልተወሰደበት ከሕጉ ዓላማና መንፈስ ጋር የማይሄድ ውጤትን ማስከተሉ የማይቀር መሆኑ እሙን ነው፡፡

 

[1] አመልካች አቶ አከለ ምህረቱ እና ተጠሪ ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መስከረም 22 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.

[2] አመልካች ወ/ሮ ምንያ ገ/ሥስሴ እና ተጠሪዎች ወ/ሪት መሠረት ዓለማሁ መጋቢት 26 ቀን 2004 ዓ.ም.

[3] ሰ/መ/ቁ. 41535 ቅጽ 12 አመልካች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተጠሪዎች እነ ግሎሪ ኃላፊነቱ/የተ/የግል ማህበር /4 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.

[4] አመልካች ሸራተን አዲስ እና ተጠሪ እነ አቶ ገናናው ከበደ /51 ሰዎች/ ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.

1 reply »

 1. tnx ma best

  2017-02-25 17:28 GMT+03:00 Ethiopian Legal Brief :

  > Abrham Yohannes posted: “አዋጅ ቁ. 454/1997 በስር ፍ/ቤቶች ላይ ድርብ ግዴታዎችን ይጥላል፡፡
  > የመጀመሪያው አግባብነት ባላቸው ሁኔታዎች የሰበር ችሎትን የህግ ትርጉም መቀበልና ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን የዚሁ ግዴታ
  > ግልባጭ ገፅታ የሆነው ሁለተኛ ደግሞ አግባብነት በሌላቸው ሁኔታዎች ተፈጻሚ ከማድረግ መቆጠብ ናቸው፡፡ ለግዴታዎቹ
  > ውጤታማነት ፈቃድ ብቻ ሳይሆን እውቀት ጭምር ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ”
  >

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.