Articles

የዕድሜ ልክ እስራት 25 ዓመት ነው?

አንዳንዴ እንደ ቀላል የሚወሰዱ የህግ ጉዳዮች የክርክር ምንጭ ይሆናሉ፡፡ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ትርጓሜን በተመለከተ ከአንድ በላይ የህግ ባለሞያ ጋር ክርክር ገጥሜ አውቃለው፡፡ ጭብጡ ይህን ይመስላል? ‘የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቅጣት የተፈረደበት ሰው ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚቆየው ለ25 ዓመታት ነው? ወይስ ዕድሜ ልኩን ማለትም እዛው ማረሚያ ቤት ውስጥ እስኪሞት ድረስ?’

በወንጀል ህጉ ላይ ነጻነትን የሚያሳጡ አራት ዓይነት ቅጣቶቸ ተቀመጠዋል፡፡ እነሱም፤

ቀላል እስራት ከ10 ቀን እስከ 3 ዓመት በልዩ ሁኔታ እስከ 5 ዓመት /አንቀጽ 106/

ጽኑ እስራት

 • ከአንድ ዓመት እስከ 25 ዓመት አንቀጽ /አንቀጽ 108(1)/
 • በህግ በግልፅ በተደነገገ ጊዜ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት /አንቀጽ 108(1)/

የሞት ቅጣት

የሞት ቅጣት ሲወሰን ህጉ የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ያስገድዳል፡፡

 • ወንጀሉ እጅግ ከባድ ወንጀለኛውም በተለይ አደገኛ ሲሆን
 • ለወንጀሉ ቅጣት እንዲሆን በህጉ በግልጽ ከተደነገገ
 • ወንጀለኛው ቅጣት ማቅለያ የሌለው ሲሆን
 • ዕድሜው ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ ሲሆን
 • ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኘ ሲሆን

የወ/ህ/ቁ. 108/1/ ከአንድ እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚያስቀጣውን መደበኛውን ጽኑ እስራት  ከዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት በግልጽ ይለያል፡፡ ድንጋጌው የጽኑ እሥራት ቅጣት ግቡ ተቀጪው እንዲታረምና ወደ ማህበራዊ ኑሮ እንዲመለስ ከማድረግ በተጨማሪ በተለይ ለኀብረተሰቡ ደህንነት በጥብቅ ቁጥጥር ሥር እንዲቆይ ለማድረግ እንደሆነ ከደነገገ በኋላ የጽኑ እስራት ቅጣት ጊዜው ከአንድ ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት እንደሚደርስ ሆኖም በሕጉ ተገልጾ የተደነገገ ሲሆን ጽኑ እስራት እስከ ዕድሜ ልክ እንደሚዘልቅ ይናገራል፡፡ በግልጽ አማርኛ ስናስቀምጠው የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተወሰነበት ሰው ዕድሜ ልኩን እስኪሞት ድረስ በእስር ይቆያል፡፡

የህጉ መልዕክት አሻሚነት ባይኖረውም የዕድሜ ልክ እስራትን በ25 ዓመት የሚገድቡ አስተያየቶች ከህግ ባለሞያው ዘንድ ሲሰነዘር ይታያል፡፡ የወንጀል ህጉ መግቢያ ሳይቀር ተመሳሳይ የተዛባ ሀሳብ ይንጸባረቅበታል፡፡ በመግቢያው ላይ የሚከተለው ዓረፍተ ነገር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በተወሰኑ ወንጀሎች ረገድ የእስራት ወይም የሞት ቅጣት ተፈፃሚ ቢሆንም ዋናው አስተሳሰብ ጥፋተኞቹ ለጊዜው ወይም ለዘለቄታው በኀብረተሰቡ ላይ ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈጽሙበት ለመከልከል ነው፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜም ከሞት ቅጣት በቀር የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ጥፋተኞች እንኳ ቅጣታቸውን ሳይጨርሱ በአመክሮ ሊለቀቁ ይችላሉ፡፡

ቅጣታቸውን ሳይጨርሱ? ዕድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው ከፊቱ የሚጠብቀው ዕለተ ሞቱን ነው፡፡ እናም የሚጨርሰው ቅጣት የለም፡፡ ዕድሜ ልክ አያልቅም፡፡ ስለሆነም በመግቢያው ላይ የሰፈረው ዓረፍተ ነገር ጣዕም ያለው ይዘት የሚኖረው ቅጣታቸውን ሳይጨርሱ የሚለው ሐረግ ተቆረጦ ሲወጣ ነው፡፡

የዕድሜ ልክ እስራትን ከ25 ዓመት ጽኑ እስራት ጋር በማቀላቀል የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ባብዛኛው ምንጫቸው በአመክሮ መፈታትን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ አግባብነት ያለው ድንጋጌ የወንጀል ህጉ ቁ. 202 ሲሆን ሙሉ ይዘቱ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

አንቀጽ ፪፻፪ ለመለቀቅ የሚያበቁ ሁኔታዎች 

፩  ተቀጪው ከተወሰነበት የእሥራት ጊዜ ከሦስት  እጅ ሁለቱን እጅ ወይም ፍርዱ የዕድሜ ልክ እሥራት ሲሆን ሃያ ዓመት በፈፀመ ጊዜ አግባብ ባለው አካል ወይም በጥፋተኛው አሳሳቢነት ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው በአመክሮ እንዲፈታ መወሰን የሚችለው ጥፋተኛው፡-

ሀ/ አስፈላጊ የሆነውን ነፃነት የሚያሳጣ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ በመፈፀም ላይ ሳለ በሥራውና በጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ፣

ለ/ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ሊከፍል የሚጠበቅበትን በፍርድ ቤት በተወሰነው መሠረት ወይም ከተበዳዩ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ካሣ ለመክፈሉ ማረጋገጫ አቅርቦ እንደሆነ፣ እና

ሐ/ አመሉና ጠባዩ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለው እና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ፣ ነው፡፡

ከድንጋጌው ምንባብ እንደምንረዳው የዕድሜ ልክ እስራት የተወሰነበት ሰው ሃያ ዓመት ከታሰረ በኋላ በአመክሮ ሊፈታ ይችላል፡፡ አመክሮ በልዩ ሁኔታ የሚፈቀድ እንጂ መብት አይደለም፡፡ የወንጀል ህግ ቁ. 201 በደነገገው መርህ መሰረት ለአመክሮ በተወሰነ ገደብ መፈታት የተቀጪውን ጠባይ ማሻሻያና ወደ ደንበኛው ማህበራዊ ኑሮ መመለሻ ሆኖ ሊቆጠር ይገባዋል፡፡ ተቀጪው ለዚሁ ተገቢ ካልሆነና በተወሰነ ገደብ መፈታቱ ተፈላጊውን ውጤት የሚያስገኝ መሆኑ ካልታመነበት በቀር ሊፈቀድ አይቻልም፡፡ ህጉ ያስቀመጠው መርህ በተግባር እንዲረጋገጥ በቁ. 202 ላይ የተዘረዘሩት ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል፡፡

የተነሳንበትን ርዕስ ስናጠቃልል ዕድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው በአመክሮ ሊፈታ የሚችልበት ዕድል መኖሩ የቅጣቱን ዓይነት መሰረታዊ ይዘት አይቀይረውም፡፡ መሰረታዊ ይዘቱ ተቀጪው ዕድሜ ልኩን እንደሚታሰር፣ ህይወቱን በሙሉ እስረኛ ሆኖ እንደሚቆይ ነው የሚያስገነዝበን፡፡ ህጉም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡

Categories: Articles

Tagged as:

6 replies »

  • የፌዴራል የይቅርታ ህግ ማዕቀፍ ይቅርታ የሚቀርብበቸዉን አማራጮች ከመዘርዘር ባለፈ የይቅርታ ይደረግልኝ ጥያቄዉ የሚቀርብበትን የጥያቄዉ ማቅረቢያ ጊዜም በዝርዝር ደንግጓል፡፡በዚሁ መሰረት የይቅርታ ጥያቄ የሚያቀርብ ማንኛዉም ታራሚ ጥያቄዉን የቅጣት ፍርድ ከተሰጠበት በኋላ በማናቸዉም ጊዜ ዉስጥ ማቅረብ እንደሚችል በመርህ ደረጃ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ ለይቅርታ አሰጣጥ አስፈላጊ የሆኑና ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ መስፈርቶችን እንዲያወጣ በአዋጁ አንቀጽ 9(1)(ለ) በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ባወጣው የአሰራር መመሪያ ላይ የቅጣትንና የይቅርታ አዋጁን ዓላማ መሰረት በማድረግ የይቅርታ ማቅረቢያ ጊዜ ከዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ዉጭ ባሉ ፅኑ እና ቀላል እስራቶች የቅጣቱ 1/3ኛ ከተፈፀመ በኋላ እንዲሁም ለዕድሜ ልክ ፍርደኞች 12 ዓመት ከሞላቸው በኋላ መሆን እንዳለበት ወስኗል፡፡ …..

 1. Thank you Abrish,
  It was my question and confusion.
  Now it becomes clear.

  With best regards,

 2. This is good comment. Bevause there are so many instances where provisions are erroneiously percieved and leads to grave fault. Nice of you to digout such simingly common mistakes.

 3. Thank you very much for your clarification, because people always confused me about this issue.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.