Articles

የክስ ምክንያት- የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

  1. አንድ ሰው አንድን ነገር ከአንድ ሰው ላይ ለማግኘት ፍ/ቤቱ እንዲወስንለት ክስ ለማቅረብና ዳኝነት ለማግኘት የሚያስችለው የፍሬ ነገር ሁኔታ

ማንም ሰው በህግ ችሎታ ኖሮት በሌላ ሰው ላይ ማናቸውንም ክስ ለማቅረብ እንዲችል አስቀድሞ ለክሱ መነሻ በሆነው ነገር ወይም ክሱ በተመሠረተበት ነገር ላይ ጥቅም ወይም መብት ያለው መሆኑ መረጋገጥ እንደሚገባው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 33 ይደነግጋል፡፡ በዚህም ከሣሽ ከተከሣሽ ላይ ሊፈፀም የሚችል መብት አለኝ ብሎ ለማለት አስቀድሞ ለመብቱ መገኘት መነሻ የሆነውን ነገር በማረጋገጥ የተጠየቀውን ዳኝነት ለማግኘት ከሣሹ በሕግ መብት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡

የክስ ምክንያት አለ ብሎ ለመወሰን የሚቻለው በክሱ ላይ የቀረበው ነገር ቢረጋገጥ ከሣሹ የጠየቀውን ዳኝነት ለማግኘት ሕግ ይፈቅድለታል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ሲቻል ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 16273 ቅጽ 2፣[1] ስለ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣ አዋጅ ቁ. 42/85 አንቀጽ 9፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 29፣ 80/2/፣ 224/2/፣ 23/1/ ሀ ፣ 224/2/፣ 23/1//ሀ/፣ 33፣ ሮበርት አለን ሴድለር በችሎቱ እንደተጠቀሰ

ሻጭ ከሽያጭ ውሉ በሚመነጭ ግዴታ የተሸጠውን ነገር ስመ ሀብትነት በሚመለከተው ክፍል ቀርቦ ለማዛወር እንደገባው ግዴታ ይፈጽምልኝ የሚል ክስ የክስ ምክንያት አለው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 82234 ቅጽ 15 [2]

አንድ ክስ ሊቀርብ የሚገባው የክስ ምክንያት ሲኖረው ሲሆን የክስ ምክንያትም ተከሣሽ ለከሣሽ ሊፈጽመው የሚገባው ግዴታ መኖሩ ጋር ተያይዞ ሊነሣ የሚችለውን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ሲረጋገጥ የሚታወቅ ነው፡፡

ሰ/መ/ቁ. 33945 ቅጽ 12፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 231(1) ሀ

  1. ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መነሻ ምክንያት

በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 231 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ፍርድ ቤት የክስ አቤቱታ ሲቀርብለት ተከሣሽ የሆነው ወገን ክሱን እንዲከላከል ከመጥራቱ በፊት ከሳሽ ክሱን ለማቅረብ የሚያስችል መነሻ ምክንያት ያለው ስለመሆኑና ፍ/ቤቱም አቤቱታውን ተቀብሎ ለማየት ስልጣን ያለው ስለመሆኑ መመርመር ይኖርበታል፡፡

ሰ/መ/ቁ. 32147 ቅጽ 6፣[4] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 231

አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች በአባቱ ብቻ ሳይሆን በአሳዳጊው ስም ጭምር ሊጠራ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ ሆኖ ባገኘው ጊዜ በአሳዳጊው ስም ጭምር መጠራቱ ቀሪ ሆኖ በፍትሐብሔር ሕጉ መሰረት በአባቱ ስም ብቻ እንዲጠራ የመወሰን መብት ያለው በመሆኑ ይህንኑ መብቱን በፍርድ ለማረጋገጥ የሚያቀርበው የዳኝነት ጥያቄ የክስ ምክንያት የለውም የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 95995 ቅጽ 15[5]

ከባዶ ቦታ ሽያጭ የመነጨ ግዴታ ለማስፈጸም የሚቀርብ አቤቱታ የክስ ምክንያት የለውም፡፡

ሰ/መ/ቁ. 27739 ቅጽ 6[6]

[1] አመልካች የኢት/ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ አቶ ገንታ ገምአ ጥቅምት 22 ቀን 1998 ዓ.ም. በተጨማሪ አመልካች አቶ ደጀኔ በላቸው እና ተጠሪ አቶ ነስሩ አወል ሰኔ 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ. 45247 ቅጽ 9 ይመለከቷል፡፡

[2] አመልካች አቶ አየለ መኮንን እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ ጦቢያው ወንድም ገዛው /6 ሰዎች/ የካቲት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

[3] አመልካች አቶ ሣልህ ሁሴን እና ተጠሪ ደግፌ ደርቤ ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም.

[4] አመልካች አቶ መሐመድ አብዲ እና ተጠሪ አቶ አብዱረህማን አብዲ መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም.

[5] አመልካች ወ/ት ሞሚና ሡልጣን ኮርዋላ እና ተጠሪ የለም የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

[6] አመልካች አቶ ድንቁ ገላው ተጠሪ ወ/ሮ ዋለ እሸቴ ጥቅምት 28 ቀን 2000 ዓ.ም.

2 replies »

  1. በጣም አመሰግናለሁ አብርሃም  በ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የህግ እውቀት እንዲኖረኝ ስላደረገኝ

     እባክህ  ውርስን በተመለከተ  ያንተን  ማብሪሪያፈልጌ ነው  ፡፡ 

    የ 3ኛ ትውልድ ማለትም የልጅ ልጅ  እናቱ ወይም አባቱ  የወላጆቻቸውን ወራሽነት  ሳያረጋግጡ በሞቱበት ሁኔታ  ከሟች አያቱ የማች እናቴን ወይም የአባቴን ድርሻ ላገኝ ይገባል ብሎ ሊጠይቅ ይችላል?  

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.