Site icon Ethiopian Legal Brief

ህጋዊነትና ካርታ ማምከን

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የባለቤትነት ማረጋገጫ የመስጠት ስልጣን ያላቸው አካላት ‘ካርታ ማምከን’ የሚሉት አዲስ ፈሊጥ አምጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ቃሉን በተውሶ እያዘወተሩት ወደ ህግ ቃል እየቀየሩት ነው፡፡ ይህ የማምከን እርምጃ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ በተደጋገሚ ሲስተዋል የነበረ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ ንብረት የማፍራት መብትን አደጋ ውስጥ የከተተው ‘ከመሬት ተነስቶ’ ካርታ የማምከን ተግባር በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠረው በመጥፋቱ የተነሳ አስተዳደሩ ከህገ ወጥነት ወደ ጋጠ ወጥነት ተሸጋግሯል፡፡ በአስረጂነት ከሚጠቀሱ የሰበር ችሎት መዝገቦች መካከል የሰ/መ/ቁ 17712 አንደኛው ነው፡፡ በዚህ መዝገብ አመልካች ሆኖ የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ሲሆን ተጠሪ የወሮ ሳድያ እስማኤል ወራሾች ናቸው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥና በሰበር የተሰጠው ውሳኔ በአጭሩ እንዲህ ይተረካል፡፡

ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪዎች በውርስ የተላለፉላቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት የንግድ ቤቶችን ተከራይተው የሚሰሩባቸው ግለሰብ ቤቶቹን እንዲያስረክቧቸውና ያልተከፈለ ኪራይም እንዲከፍሉ በማለት ክስ ያቀርባሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም መብታቸውን በማረጋገጥ ወሰነላቸው፡፡ ከውሳኔ በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳደር ቤቶቹ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሱና ከዚህ ቀደም ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ የተሰረዘ መሆኑን በመግለፅ በክርክሩ ውስጥ በተቃውሞ ገብቶ የባለቤትነት ጥያቄ ያነሳል፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ ያዩት የስር ፍ/ቤቶች ‘ቤቶቹ ስለመወረሳቸው የሚያረጋግጥ የመረካከቢያ ቅፅ አልቀረበም’ በሚል የአስተዳደሩን ጥያቄ ውድቅ አደረጉት፡፡ አስተዳደሩ የሥር ፍርድ ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ስላለባቸው ይታረምልኝ በማለት የሰበር አቤቱታ በማቅረቡ የሰበር ችሎት የሚከተለውን ውሳኔ በድምፅ ብልጫ ሰጠ፡፡

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍል ለአንድ ሰው የተሰጠ የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት ማስረጃ ለተሰጠው ሰው ለዚሁ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብት እንደሆነ እንደሚያስቆጥረው ተመልክቷል፡፡ በአንፃሩ ማስረጃው የተሰጠው ከደንብ ውጭ በሆነ አሰራር መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ከፍ ብሎ በፍትሐብሔር ቁጥር 1195 ላይ የተመለከተው የሕሊና ግምት ፈራሸ እንደሚሆን የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) ይደነግጋል፡፡ በያዝነው ጉዳይ በሕግ አግባብ ስልጣን ተሰጥቶት ይህን መሰሉን የባለሃብትነት ማስረጃ የሚሰጠው ክፍል ቁጥር 5127386 የሆነው የባለሃብትነት የምስክር ወረቀት የሰረዘው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተሰረዘ የባለሃብትነት ምስክር ወረቀት ደግሞ የሚገኝ የባለሃብትነት መብት አይኖርም፡፡ የተጠሪ ወራሾችም አውራሻቸው ያልነበራቸውን መብት ሊወርሱ አይችሉም፡፡

ለንፅፅር እንዲረዳ በሓሳብ ልዩነት የተሰጠውን አስተያየትና ምክንያት ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

አመልካች የአዲስ አበባ መስተዳደር በቤቶቹ ላይ መብት አለኝ የሚለው በመንግስት የተወረሱ ናቸው በሚል መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ቤቶቹ በመንግስት የተወረሱ መሆናቸውን የሚያሳይለት ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ለተጠሪዎች አውራሸ ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ደብተር ተሰርዟል ማለቱ ብቻውን ለእርሱ መብት የሚሰጠውና አቤቱታውም በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 አግባብ እንዲሰተናገድለት ለማድረግ የሚያስችል አይደለም፡፡ በኔ እምነት የሥር ፍርድ ቤቶች ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰው ክርክሩን እንደገና መመርመር ሳያስፈልጋቸው አመልካቹን ወደ ክርክሩ ለመግባት የሚያስችልህ መብት መኖሩን አላስረዳህም በሚል ከወዲሁ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው የፈፀሙት የሕግ ስህተት የለም፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1195 ግምት በፍ/ሕ/ቁ 1196 በተደነገገው መሠረት ማለትም በሕጉ መሠረት ፈራሸ ሊሆን ይችላል፡፡ የባለቤትነት ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ ከሆነ መሰረዙን ህግ ይፈቅዳል፡፡ ሆኖም የመሰረዝ ስልጣን ያለው አካል የካርታው አሰጣጥ ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ የማስረዳት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የቤቶች ጉዳይ መምሪያ ካርታውን ሲሰርዝ ካርታው ከደንብ ውጭ የተሰጠ መሆኑን የማሳየትና የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ካላደረገ እርምጃው ከሥልጣን በላይ እንደመሆኑ በሕግ ፊት ዋጋ አይኖረውም፡፡ አመልካች ካርታው ከደንብ ውጭ ስለመሆኑ ወይም ቤቱ በአዋጅ ስለመወረሱ በክርክሩ ቢጠቅስም ከአባባል ያለፈ በተጨባጭ ማስረዳት አልቻለም፡፡ ስለሆነም የመሰረዝ ድርጊቱ የሕጋዊነት መርህን የሚጥስ፣ የሕግ የበላይነትን የሚጻረር፣ ከሥልጣን በላይ የሆነ ድርጊት ነው፡፡

የአብላጫው ድምፅ ይህን መሠረታዊ ጭብጥ አላነሳውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካርታው በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1196 (1) መሠረት ተሰርዞ በምትኩ ለሌላ 3ኛ ወገን ሲተላለፍ ያ ሶስተኛ ወገን የቤቱ ሕጋዊ ባለቤት ስለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ባለቤትነቱ የተሰረዘውን የንግድ ቤት የራሱ ሃብት ሲያደርገው በሕጉ መሠረት የባለቤትነት መብት የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በአዋጅ ቁ 47/67 ተወርሷል የሚል ከሆነ እንደተወረሰ በበቂ ማስረጃ ማሳየት አለበት፡፡ አመልካች የቤቱ ባለቤት ስለመሆኑ አሁንም በአብላጫው ድምፅ ላይ ጭብጥ ሆኖ ተነስቶ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰበትም፡፡ በእርግጥ በተሰረዘ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት የሚገኝ የባለሀብትነት መብት አይኖርም፡፡ ከዚህ ድምዳሜ በፊት ግን የህግ የበላይነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡

ተጠሪዎች እየሞገቱ ያሉት የመሰረዙን ሕጋዊነት ነው፡፡ የተጠሪዎች ሙግት በአብላጫው ድምፅ ሰሚ አላገኘም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ካርታው ከደንብ ውጭ ለአመልካች እንደተሰጠ ስላላስረዳ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ወይም ከሥልጣን በላይ ነው፡፡ በቤቱ ላይ በሕጉ መሠረት ባለቤት እንደሆነ ስላላስረዳም ‘ከመሬት ተነስቶ በሌላ ሰው መብት ባለቤትነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህን ሀሳብ በአነስተኛ ድምፅ አስተያየት ስንቋጨው፤

አመልካች እንኳንስ መብት ሊኖረው ቀድሞውኑ በተቃውሞ ወደ ክርክር ውስጥ እንዲገባ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር፡፡

በሌላ ተመሳሳይ መዝገብ እንዲሁ ፍርድ ያረፈበት የባለቤትነት መብት አስተዳደሩ ስላመከነው መና ሆነ ቀርቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 22719[1] ተጠሪ በሁለት የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር /ካርታ/ የተመዘገቡ ሶስት የቤት ቁጥር የተሰጣቸው ቤቶች የራሳቸው መሆናቸው ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ውሳኔ አርፎባቸው በአፈጻጸም መዝገብ ቤቶቹን ተረክበዋል፡፡ የፍርድ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ አመልካች የቤት ማረጋገጫ ደብተሮቹን በመሰረዙ ተጠሪ ክስ አቀረቡ፡፡ በሰበር ችሎት በነበረው ክርክር ችሎቱ ተጠሪ መብታቸውን በፍርድ ቤት አስከብረውና አረጋግጠው የተፈጸመባቸው ዓይን ያወጣ ህገ ወጥ ተግባር ከማረምና የህግ የበላይነትን ከማስከበር ይልቅ ክስ የማቅረብ መብታቸውን ነፍጓቸዋል፡፡ ችሎቱ ለማመዛን እንደሞከረው፡

አመልካች የተጠሪን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶች ከሰረዘ ተጠሪ አስቀድሞ በተጠቀሱት ቤቶች ላይ ባለመብት መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን በእጁ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ ይህ መሠረታዊ ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ማስረጃ ሳይኖረው ፍ/ቤት ሰነድ እንዲሰጠው እንዲወሰንለት መጠየቅ አይቻልም፡፡

በአጭር አነጋገር ቤቱን በአስተዳደሩ ህገ ወጥ ተግባር የተነጠቀ ሰው ቤቱ እንዲመለስለት የመጠየቅ መብት እንኳን የለውም፡፡

የሰበር ችሎት ዘግይቶም ቢሆን የሰ/መ/ቁ 17712 እና 22719 ውሳኔ ካገኙ ከሰባትና አምስት ዓመታት በኋላ ፍጹማዊ በሆነውና ፍጹማዊነቱንም ችሎቱ ይሁንታ በሰጠው የአስተዳደሩ ካርታ የማምከን ስልጣን ላይ ገደብ ለማበጀት ተገዷል፡፡ በሰ/መ/ቁ. 42501[2] ፍርድ ባረፈበት ጉዳይ ካርታ ማምከን ህገ ወጥነቱን ጠንከር ባሉ ቃላት እንደሚከተለው ገስጾታል፡፡

አንድ የአስተዳደር አካል በፍርድ ቤት ክርክር መረታቱን ከተረዳ በኃላ በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መነሻ በማድረግ ለፍርዱ መሰጠት መሠረት የሆነውን ማስረጃ ዋጋ በማሣጣቱ ምክንያት የፍርድ አፈፃፀም ዋጋ እንዲያጣ የማድረግ ውጤት በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 78/1/ እና 79/1/ እና /4/ ስር የተረጋገጠውንና የተከበረውን የነፃ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነት ስልጣን ትርጉም አልባ የሚያደርገው ነው፡፡

[1] አመልካች የአ/አ/ ከተማ አስተዳደር ስራ ከተማ ልማት ቢሮ ተተኪ የመሬት ልማትና አስተዳደር ባለስልጣን እና ተጠሪ አቶ ነጋሽ ዱባለ ጥር 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ቅጽ 6

[2] አመልካች የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እና ተጠሪ የአስር አለቃ ደምሴ ዳምጤ ወራሾች /3 ሰዎች/ የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ.ም.

Exit mobile version