Articles

በአስተዳደር ህግ ‘የመጨረሻ ማሰሪያ ድንጋጌ’ (finality clause) ተፈጻሚነትና ውጤት

የኮመን ሎው የአስተዳደር ህግ ስርዓትን በሚከተሉ አገራት (በተለይ በእንግሊዝ) ህግ አውጪው የፍርድ ቤቶችን ስልጣን በህግ ከሚገድብባቸው መንገዶች ዋነኛው በአስተዳደር መስሪያ ቤት ወይም በአስተዳደር ጉባዔ የተሰጠን ውሳኔ የመጨረሻ አድርጎ በማሰር ሲሆን ይህም መደበኛ ፍ/ቤቶች ጥያቄ የተነሳበትን ጉዳይ ድጋሚ እንዳያዩት ስልጣናቸውን ይገድባል፡፡ ያም ሆኖ ግን የእንግሊዝ ፍ/ቤቶች እንደ ማሰሪያ ድንጋጌው (Finality clause) አገላለጽ ከፊል የአቋም ልዩነት ቢያሳዩም በመርህ ደረጃ ግን በህግ የበላይነት ላይ እንደተደረገ ገደብ በመቁጠር የመጨረሻ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ህጋዊነት ከማጣራትና ከመመርመር አልተቆጠቡም፡፡[1]

ህግ አውጪው አንዳንድ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የመጨረሻ እንዲሆኑ ሲደነገግ በህጉ ላይ የተለያዩ አገላለጾችይጠቀማል፡፡ የአገላለጽ መንገዱ መለያየት በተለይ በእንግሊዝ የተለመደ ሲሆን የፍ/ቤቶች ምላሽና ትርጓሜም የህጉን የቋንቋ አጠቃቀም መሰረት ያደርጋል፡፡ በጣም የተለመደው አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የመጨረሻ እንዲሆኑ የማድረግ ዘዴ ‘ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል’ (Shall be final) ወይም ‘ውሳኔው የመጨረሻና የጸና ይሆናል’ (Shall be final and conlusive) የሚል ማሰሪያ ድንጋጌ በማስቀመጥ ነው፡፡

በእንግሊዝ ፍ/ቤቶች ይህን መሰሉ የመጨረሻ ድንጋጌ በአፈፃፀም ወይም በአተረጓጎም ረገድ ቀላል እና የማያሻማ ስለመሆኑ ወጥ ተቋም ተይዞበታል፡፡ በዚህ መሰረት ‘የመጨረሻ’ የሚል ማሰሪያ ድንጋጌ ውጤት የይግባኝ መብትን ከማስቀረት ባለፈ የውሳኔውን ህጋዊነት ከመመርመር አያግድም፡፡ ይህም ማለት ውሳኔው ከይዘት አንፃር እንጂ ህጋዊነቱን በተመለከተ የመጨረሻ ሊሆን አይችልም፡፡

ይህን ሀሳብ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ከአገራችን ህግ ጋር በማነጻጸር እናያለን፡፡ በመንግስትና የግል ሠራተኞች የጡረታ አዋጆች ላይ እንደተመለከተው የመንግስት እና የግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲዎች ከጡረታ መበትና ጥቅም ጋር በተያያዘ በየፊናቸው በሚሰጡት ውሣኔ ቅር የተሰኘ ሠራተኛ ቅሬታውን ለማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ የማቅረብ መብት አለው፡፡ የጉባኤው ውሣኔ በፍሬ ነገር ረገድ የመጨረሻ ሲሆን በውሣኔው መሠረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ቅሬታ ያለው ሠራተኛ የይግባኝ አቤቱታ የሚያቀርበው ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ነው፡፡[2]

የጉባኤው የፍሬ ነገር ውሳኔ የመጨረሻ ተብሎ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት የማይመረመረው በህጉ የስልጣን ገደብ ውስጥ የተሰጠ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሚስትነት/ባልነት አስመልክቶ ኤጀንሲው ሆነ ጉባኤው የሚደርስበት መደምደሚያ ከስልጣን በላይ እንደመሆኑ የመጨረሻ አሳሪ ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከባልነት/ ሚስትነት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ለማሳለፍ ህጉ ስልጣን አልሰጣቸውም፡፡ ይህ የሚያደርሰን ድምዳሜ ‘የመጨረሻ ይሆናል’ የሚል ድንጋጌ ውሳኔው በህግ ከተሰመረው የስልጣን ገደብ ስላለማለፉ ከመመርመር አያግድም፡፡

በአገራችን የመጨረሻ የሚያደርጉ ማሰሪያ አንቀጾች በስፋት የተለመዱ ናቸው፡፡ ለአብነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡

  • የደህንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን የውጭ አገር ዜጋንከአገር ለማስወጣት በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ ቅሬታ የሚቀርበው የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ እና የባለስልጣኑ ተወካዮች ለሚገኙበት አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ሲሆን ኮሚቴው ቅሬታውን መርምሮ ለባለስልጣኑ የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበ በኋላ ባለስልጣኑ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[3]
  • በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቁ. 847/2006የተቋቋመው ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ክስ ሰሚዎች (Hearing Examiners) የሚሰጡትን ውሳኔ በይግባኝ አይቶ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[4]
  • የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን አሠሪ፣ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ወኪል ወይም ሠራተኛ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁ. 923/2008እንዲሁም በአዋጁ መሠረት የወጣ ደንብና መመሪያ በመጣሳቸው ምክንያት የሚነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመስማትና የመወሰን ሥልጣን ያለው ሲሆን በውሳኔው ቅሬታ ያደረበት ወገን ይግባኙን የሚያቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[5]
  • የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የምስክር ጥበቃ ተጠቃሚ የሆነ ወይም ያመለከተ ሰው የሚያቀርበውን ቅሬታ ሰምቶ የሚሰጠው ውሳኔ ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማይቀርብበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው፡፡[6]
  • የራሱንና የቤተሰቡን የገቢ ምንጭ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ ያለበት ሰው የምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምለት ለስነ ምግባር መከታተያ ክፍል አቤቱታ አቅርቦ ውድቅ ከተደረገበት ቅሬታውን ለስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስናኮሚሽን ማቅረብ የሚችል ሲሆን ኮሚሽኑ በቅሬታው ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[7]
  • የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የሚወስደውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመቃወም አቤቱታ የሚቀርበው ለትራንስፖርት ሚኒስቴርሲሆን የሚኒስቴሩ ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[8] ይኸው ሚኒስቴር መ/ቤት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ በፈቃድ ሰጪው አካል በመታገዱ ወይም በመሰረዙ ምክንያት የሚቀርብለትን አቤቱታ ምርምሮ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡[9] በማሪታይም ዘርፍ አስተዳደር ማፅደቂያ አዋጅ ቁ. 549/199 አንቀጽ 16/ሀ/ ላይ እንዲሁ የሚኒስቴሩ ውሳኔ የመጨረሻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡[10]
  • ለማንኛውም እንቅስቃሴ ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት (advance informed agreement) በመከልከሉ ምክንያት እንደገና እንዲታይ የሚቀርብ ማመልከቻ በአዲስ ሳይንሳዊ መረጃ ከተደገፈ እንደ አዲስ ማመልከቻ በድጋሚ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ክልከላው የፀና (በእንግሊዝኛው ቅጂ final) ይሆናል፡፡[11]
  • የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲዋና ዳይሬክተር በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበውን ቅሬታ ሰምቶ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው አካል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ቦርድ ሲሆን የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ጉዳዩ በይግባኝ እንዲታይለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህን መብት በሚፈቅደው አዋጅ ላይ የውጭ አገር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተነጥለው ቀርተዋል፡፡[12] ስለሆነም እነዚህን አካላት በተመለከተ የቦርዱ ውሳኔ በዝምታ የመጨረሻ ስለተደረገ ወደ ፍርድ ቤት የመሄጃውን መንገድ ተዘግቷል፡፡

የመጨረሻ የሚለው ቃል በተለያዩ ህጎች ላይ መካተቱ ብቻውን ወደ ፍርድ ቤት ወይም የአስተዳደር ጉባዔ አቤቱታ እንዳይቀርብ አይከለክልም፡፡ የቃሉ አጠቃቀምና አገባብ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቦርድ ከስልጣንና ተግባራቱ መካከል አንዱ በተቋሙ ውሳኔ (ለምሳሌ በመምህራን ላይ የሚወሰድ የዲሲፕሊን እርምጃ) ላይ ቅሬታ ሲቀርብ መመርመርና የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ነው፡፡[13] የመጨረሻ መሆኑ ግን ውሳኔው በመንግስት ሠራተኞች የአስተዳደር ፍርድ ቤት እንዳይታይ አይገድበውም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 78945[14] ተጠሪ በዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት የተወሰደበትን የዲሲፕሊን እርምጃ ቅድሚያ ለቦርድ ሳያቀርብ ለመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቅ እንደማይችል የህግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ የትርጉሙ እንደምታ በቦርዱ የታየ የተቋሙ ውሳኔ በአስተዳደር ፍርድ ቤቱ መስተናገድ እንደሚችል ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ የመጨረሻ በሚል በተለያዩ ህጎች ላይ የሚጨመረው ማሰሪያ ቃል በይዘቱ በህግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መብት አለመጠየቅ የሚያስከትለውን ውጤት ከመንገር የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የክፍያ መፈጸሚያ የግብይት ፈጻሚ ዕውቅናን በመሰረዝ ወይም በማገድ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የሚቀርበው ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ይግባኝ ካልቀረበ ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል፡፡[15] እዚህ ላይ የመጨረሻ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በጊዜ ገደቡ አቤቱታ ካልቀረበ መብቱ ቀሪ እንደሚሆን ነው፡፡

 

[1] Diane Longley and Rhoda James, ADMINISTRATIVE JUSTICE: CENTRAL ISSUES IN UK AND EUROPEAN ADMINISTRATIVE LAW (Cavendish Publishing Limited, 1999) ገፅ 160

[2] የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 አንቀጽ 56/4/ እና የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁ. 715/2003 አንቀጽ 55/2/

[3] የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁ. 354/1995 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2

[4] አንቀጽ 48/5/ እና 49/3/

[5] የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ 923/2008 አንቀጽ 52 እና 59

[6] የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁ. 699/2003 አንቀጽ 25/2/

[7] የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁ. 668/2002 አንቀጽ 8/3/

[8] የሲቪል አቪየሽን አዋጅ ቁ. 616/2001 አንቀጽ 80/1/

[9] የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አዋጅ ቁ. 600/2000 አንቀጽ 20/4/

[10] በእርግጥ በአዋጁ የአማርኛ ቅጂ ላይ ውሳኔው የመጨረሻ እንደሚሆን ያልተመለከተ ቢሆንም በእንግሊዝኛው ቅጂ ላይ ግን በግልጽ ‘final decision’ በሚል አገላለጽ ተቀምጧል፡፡

[11] የደህንነተ ሕይወት አዋጅ ቁ. 665/2002 አንቀጽ 15/2/

[12] የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁ. 621/2001 አንቀጽ 104/2/

[13] የከፍተኛ ትምህር አዋጅ ቁ. 650/2001 አንቀጽ 44/1/ ኀ

[14] አመልካች ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ እና ተጠሪ መምህር ባዬ ዋናያ የዳ መስከረም 25 ቀን 2005 ዓ.ም.  ቅጽ  14

[15] የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁ. 551/1999 አንቀጽ 19/3/

2 replies »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.