ያልታተሙ የሰበር ውሳኔዎች

የወንጀል ህግ አንቀጽ 23 -የዐቃቤ ህግ የወንጀል ተጠያቂነት (ምርጥ የሰበር ውሳኔ)

የሰበር መ/ቁ 40687[1]

ሀምሌ 19 ቀን 2002 ዓ.ም

 

ዳኞች፡ ሐጎስ ወልዱ

                  ሂሩት መለሰ

                  ብርሀኑ አመነው

                  አልማው ወሌ

                  ዓሊ መሐመድ

አመልካች፡ አቶ ዮሐንስ ወልደገብኤል – አልቀረቡም

ተጠሪ፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን – አልቀረቡም

                መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

                ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 42486 መስከረም 29 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው የጥፋተኝነት ውሣኔና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 33771 ሰኔ 27 ቀን 2001 ዓ.ም የከፍተኛውን ፍርድ ቤት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በማፅናት የሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት የሰበር አቤቱታ ስላቀረቡ ነው፡፡

ክርክሩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በአመልካችና በሥር ፍርድ ቤት ሁለተኛ ተከሳሽ በነበረው አቶ ወርቁ በረደድ ላይ ጥር 16 ቀን 1998 ዓ.ም ባቀረበው የወንጀል ክስ አመልካችን ሁለት የወንጀል ክስ አቅርቦባቸው የነበረ መሆኑን መዝገቡ ያሣያል፡፡ ተጠሪ አመልካችና በሥር ፍርድ ቤት ሁለተኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ ወርቁ በረደድ በአዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 1(ሀ)(ለ) እና 2 የተመለከተውን በመተላለፍ ከፍትህ ሚኒስትር ከተሰጣቸው ውክልና ውጭ በኤግዚቢትነት የተያዘው እና በማስረጃነት ለፍርድ ቤቱ መቅረብ የሚገባውን ወርቅ እንዲሰጥ አስተያየት በመስጠት ወርቁ ከተሸጠ በኋላ በኤግዚቢትነት ያለ አስመስለው በማስረጃ ዝርዝር በመጥቀስ በስልጣን አላግባብ የመገልገል ወንጀል ፈፅመዋል በማለት ያቀረበውን ሁለተኛ የወንጀል ክስ የተጠሪ የሰውና የፅሑፍ ማስረጃዎች እንደ ክሱ አቀራረብ ያላስረዱባቸው መሆኑን በመግለፅ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 141 መሠረት በነፃ እንዲሰናበቱ ውሣኔ የሰጠበት በመሆኑ በሰበር የመከራከሪያ ጭብጥ ሆኖ አልተያዘም፡፡

በሰበር የመከራከሪያ ጭብጥ ሆኖ የተያዘው ተጠሪ በአመልካችና የወንጀል ተካፋይ ነበር በማለት ባቀረበው ሰው ላይ ያቀረበውን የመጀመሪያው የወንጀል ክስ በተመለከተ በግራ ቀኙ የቀረበውን ክርክርና ማስረጃ በመስማት የከፍተኛው ፍርድ ቤትና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት የተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በአግባቡ መሆን አለመሆኑ ነው፡፡ የክርክሩ መነሻ ተጠሪ በአመልካች ላይ ጥር 16 ቀን 1998 ዓ.ም አሻሽሎ ያቀረበው አንደኛው የወንጀል ክስ ነው፡፡ የክሱ መሠረታዊ ይዘት አመልካች በአዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀፅ 23(1)ሀ(ለ) እና 2 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የጉምሩክ ባለሥልጣን የህግ መምሪያ ኃላፊ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ ህገ ወጥ ጥቅም ለአቶ ዳንኤል መኮንን ለማስገኘትና የጉምሩክ ባለሥልጣን ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው የተሰጣቸውን የሥልጣን ችሎታ አሳልፈው በመገልገልና የመንግስትና የህዝብ ጥቅም በሚጎዳ አኳኋን በመሥራት ነሐሴ 22 ቀን 1996 ዓ.ም የተያዘው 46.096 ኪሎ ግራም ወርቅ ባለቤትና ሶስተኛ ተከሳሽ የነበረውን ዳንኤል መኮንን ከወንጀሉ ነፃ ለማውጣትና በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረው ወርቅ በመንግስት እንዳይወረስ በማቀድና በማቀነባበር አቶ ዳንኤል መኮንን የጉምሩክ ዐቃቤ ህግ ነፃ አድርጎኛል ብሎ ወርቁ እንዲመለሰለት ወለድ እንዲከፈለው በፍታብሔር ክስ አቅርቦ እንዲረታ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አቶ ዳንኤል መኮንን ጨምሮ በእነ በጅጋ ዲጋሣ (አራት ሰዎች) ላይ የተጠሪው የምርመራ መዝገብ ሲቀርብላቸው

  • የወርቁ ባለቤት የሆነውና አንደኛ ተከሳሽ የነበረው ዳንኤል መኮንን ህዳር 10 ቀን 1997 ዓ.ም በመሠረቱት የይስሙላ ክስ ክስ ስሙን በተከሳሽነት ጠቅሰው አቶ ዳንኤል መኮንን በወንጀሉ ያለውን ተካፋይነትና ተሣትፎ ሣይዘረዝሩ በዝምታ በማለፍ ተከሳሽ የወንጀል ክስ መቃወሚያ እንዲያቀርብ በማመቻቻት
  • ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት የወንጀል ክሱ የአቶ ዳንኤል መኮንን የወንጀል ተሣትፎ በሚያሣይ መልኩ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጥር 19 ቀን 1997 ዓ.ም በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት አሻሽለው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በሌሎቹ ተከሳሶች ላይ ብቻ የተሻሻለ የወንጀል ክስ ሲያቀርቡ አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ከፍትህ ሚኒስትር ከተሰጣቸው ውክልና ውጭ በአቶ ዳንኤል መኮንን የወንጀል ክስ በማንሣት አቶ ዳንኤል መኮንን የሰጠውን የዕምነት ቃል በሌሎች ተከሳሾች ላይ ማስረጃ አድርገው አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም ክሱ በቀጠለባቸው ሌሎቹ ተከሳሾች ላይ ፍርድ ቤቱ ምስክር ለመስማት መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም የሰጠውን ቀነ ቀጠሮ በማሣሣት ለመጋቢት 22 ቀን 1997 ዓ.ም እንዲቀርቡ የሚል ደብዳቤ ለኢንዶርስመንት መምሪያና ለዐቃቤ ህግ ዋና ክፍል አስተላልፏል፡፡
  • በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ ወርቁ የተያዘው ነሐሴ 22 ቀን 1996 ዓ.ም መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ እያለ ነሐሴ 12 ቀን 1996 ዓ.ም ወንጀሉ የተፈፀመ አስመስሎ ሁለተኛ ተከሳሽ ያዘጋጀውን ክስ በመፈረም የወንጀል ክሱ እንዲኮላሽ ለማድረግና በወቅቱ ተከሳሽ የነበረው አቶ በጅጋ ድጋሣ ሲጠይቀው በአቶ ዳንኤል መኮንን ክስ መነሣት ማንንም አይጎዳም አንተም በቀጠሮው ቀን ብትቀርብ የሚያስከትለው ችግር የለም በማለት አግባብቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የነበሩት እነ በጅጋ ድጋሣ ለሚያዝያ 7 ቀን 1997 ዓ.ም ታስረው እንዲቀርቡ መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም የሰጠውን ትዕዛዝ እስከ ሚያዝያ 6 ቀን 1997 ዓ.ም ድረስ በእጁ አቆይቶ ለምርመራ ክፍል ኃላፊው በመስጠት ተከሳሾች አላገኘሁም ብለህ ለፍርድ ቤት ፃፍ የሚል አስገዳጅ ትዕዛዝ ሰጥቷል የሚል ነው፡፡

አመልካች የተጠሪ የወንጀል ክስ ግልባጭ ከደረሰው በኋላ ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክሯል፡፡ ተጠሪ ክሱን ለማስረዳት አስራሰባት የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን በሰነድ ማስረጃነት ካቀረባቸው ውስጥ ህዳር 10 ቀን 1997 በእነ አቶ በጅጋ ድጋሣ ላይ የቀረበና የወርቁ መኮንን የወንጀል ተሣትፎ ያልተገለፀበት የክስ ማመልከቻ የወርቁ መኮንን ስም የሌለበትና ጥር 19 ቀን 1997 ዓ.ም ተሻሽሎ የቀረበው ክስ በወርቁ መኮንን ክስ አመልካች አላግባብ ያነሣና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሣይሆን ሌላ ቀን ህዳር 12 ቀን 1996 መጠቀሱን ለማስረዳት አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አመልካች ምስክሮች ለመጋቢት 22 ቀን 1997 ዓ.ም እንዲቀርቡ በማለት የፃፈው ደብዳቤ እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች ተጠሪ እንዳቀረበ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ወሣኔ ተገልጿል፡፡ የሰው ምስክሮችን በተመለከተ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘው ወርቅ ነሐሴ 22 ቀን 1996 ዓ.ም በመያዝ በሞዴል 265 ገቢ ማድረጋቸውንና በባንክ የተቀመጠው የወርቅ ክምችት በመብዛቱ አመልካች የህግ አስተያየት ተጠይቆ ወርቁ ተሽጦ ግማሹ በባንክ በጉምሩክ እንዲቀመጥ የተደረገ መሆኑን የመሰከሩ ምስክሮች አቅርቦ ያሰማ መሆኑን፣ አመልካች የፍርድ ቤቱን የማሠሪያ ትዕዛዝ ቀጠሮው አንድ ቀን ሲቀረው ለምርመራ ክፍል ኃላፊው ሰጥቶ ተከሳሾችን አላገኘኋቸውም የሚል ደብዳቤ እንድፅፍ አስገዳጅ ትዕዛዝ መስጠቱን አመልካች የምርመራ ክፍል ኃላፊው የሰጠው ምስክርነትና አመልካች የምስክሮች መቅረቢያ ቀን አሣሥቶ የፃፈ መሆኑንና ለተጠሪ አራተኛ ምስክር ለነበረውና አንደኛ ተከሳሽ ለነበረው አቶ በጅጋ ድጋሣ አመልካች ለምስክሮቹ መቅረብ ላይ ብዙም ትኩረት እንደሌለውና ዋናው አላማው ዕቃውን(ወርቁን) ማስወረስ መሆኑን እንደገለፀለት በመግለፅ የምስክርነት ቃል የሰጠ መሆኑንና አመልካች በወቅቱ የፍትህ ሚኒስትር የነበሩ አቶ ሀርቀሀሮያ ስሙን ከሚያውቁት ሰው ጋር ከቢሯቸው ድረስ በመሄድ ወርቅ በኮንትሮባንድ ወደ ጅቡቲ ሊወጣ ሲል መያዙን ክሱን ለመቀጠል ጠቋሚዎች ተከሳሾች በመሆናቸው ማስረጃ ማጣታቸውን ሲገልፁላቸው በወንጀሉ ዝቅተኛ ተሣትፎ ያላቸውን ተከሳሾች ማስረጃ በማድረግ ከፍተኛ ተሣትፎ ያላቸውን ለመጠየቀ እንደሚችሉና ከፀረሙስና ጋር ተነጋግራችሁ ግፉበት በማለት በቃል ምክር የለገሷቸው መሆኑን በመግለፅ የተጠሪ ተጨማሪ ምስክር በመሆን ቀርበው እንደመሠከሩ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በውሣኔው ውስጥ አስፍሯል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት አመልካች መከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት አመልካች አምስት የመከላከያ ምስክሮች አቅርበው አሰምተዋል፡፡ የመጀመሪያው የአመልካች የመከላከያ ምስክር በወቅቱ የጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩ መሆናቸውን ገልፀው 46.09 ኪሎ ግራም ወርቅ እንደተያዘ አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን መክሰስ የወርቁ ባለቤት ነህ የሚል ማረጋገጫ መስጠት ስለሆነብኝ ክሱን ቀሪ ላደርገው ብሎ አማክሮት እንደነበር ምስክሩ አመልካች ከፍትህ ሚኒስትር በተሰጠው ውክልና መሠረት የሚሠራ ቢሆንም አመልካች ምክር ስለጠየቀው ጥሩ አስበሀል ብሎ ያለው መሆኑን ከዚህ በኋላ ትንሽ ቆይቶ አመልካች ሌሎቹን ተከሳሾች ምስክር በማድረግ አቶ ዳንኤል መኮንን መክሰስ አለበት ብሎ እንዳማከረውና በዚህ ሀሳብም መስማማቱን ሲገልፅለት አመልካች ይህንን ለማድረግ ከፍትህ ሚኒስትሩ መመሪያ መቀበል ይኖርብናል ስላለው አብረው ከሚኒስትሩ ዘንድ ሄደው ሚኒስትሩ በቃል የወርቅ ኮንትሮባንድ እየተስፋፋ በመሆኑ የኮንትሮባንድ ወርቅ አውጭና ተቀባይ ለማወቅ እንዲቻል ምርመራችሁን ቀጥሉ ብለው መመሪያ በመስጠታቸው የጉምሩክ ፖሊስ አቅም ስላልነበረው ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ተፅፎ ሁለት መርማሪዎች መጥተው ምርመራውን ጀምረው እንደነበር ከዚያ በኋላ ጉዳዩም ፍትህ ሚኒስትር እንዳይዘው መደረጉን መሥክረዋል፡፡ ሁለተኛው የመከላከያ ምስክር ሀርቀሀሮያ አመልካች ከማያውቁት ሰው ጋር ስለ ወርቁ ያናገራቸው መሆኑን ዳንኤል መኮንን ስለተባለ ተከሳሽ እንዳልሰሙ የመሠከሩ መሆናቸው በውሣኔው የተመዘገበ ሲሆን ሶስተኛው የመከላከያ ምስክር በወቅቱ የጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ መሆናቸውን ገልፀው አመልካች ምርመራ እንዲቀጥል ከፍትህ ማኒስትሩ መመሪያ ተቀብለው መምጣታቸውን ገልፀው ፌዴራል ፖሊስ መርማሪ እንዲመድብላቸው የትብብር ደብዳቤ እንዲፃፍ አመልካች ስለገለፀላቸው መርማሪዎች እንዲመደቡ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ መፃፉን የመሠከሩ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ሁለት ምስክሮች ከጉምሩክ ባለሥልጣን በተፃፈው ደብዳቤ መሠረት ከፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ለማጣራት የተላኩ ሁለት መርማሪ ፖሊሶች ሲሆኑ በዚህ ወቅቱ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ እንደ አዲስ ምርመራ እንዲጀምሩ አመልካች ጋር የተነጋገሩ መሆኑንና አቶ ዳንኤል መኮንን ለጉምሩክ ፖሊሶች ወርቁ የእኔ ነው ብሎ ቃሉን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በእኛ ግን ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም አመልካች ምርመራውን ስናከናውን አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላላቸው መሆኑን የመሰከሩ መሆኑን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሣኔ ተገልጿል፡፡ አመልካች በተጨማሪ የመከላከያ ማስረጃነት የፍትህ ሚኒስትር የበላይ አመራሮች የካቲት 9 ቀን 1998 ዓ.ም ስለ ጉዳዩ ተወያይተው የደረሱበትን የውሣኔ ሀሳብ የሚያሣይ ስድስት ገፅ ቃለጉባኤ ፍርድ ቤቱ እንዲቀርብላቸው በመጠየቃቸው የሰነድ ማስረጃውን በተጨማሪ የመከላከያ ማስረጃነት ተቀብሎ ፍርድ ቤቱ የመዘነው መሆኑ ከሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ ለመገንዘብ ችለናል፡፡

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ከግራ ቀኙ በኩል የቀረበውን ክርክር ከሰማና ማስረጃውን ከመዘነ በኋላ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀፅ 1(ሀ)(ለ) እና (2) የተመለከተውን በመተላለፍ በስልጣን አላግባብ የመገልገል ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ነው ብሎ በሶስት ዓመት ፅኑ እስራትና በብር 1000 /አንድ ሺህ ብር/ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡ አመልካች በዚህ ፍርድ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት አቅርበው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀፅ 2-ለ-2 መሠረት አፅንቶታል፡፡

አመልካች የከፍተኛው ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት የሰጡት ፍርድ የህግ መሠረት የሌለውና የህግ አፈፃፀምና አተረጓጎም ስህተት ያለባቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፍትህ ሚኒስትር በተሰጠኝ የዐቃቤ ህግነት የውክልና ሥልጣን በሰጠሁት ማናቸውም አይነት ውሣኔ የመሻርና የመለወጥ ወይም በወንጀል እንድጠየቅ የማድረግ ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 74/1986 እና ደንብ ቁጥር 44/92 የፍትህ ሚኒስትር ሆኖ እያለ የወንጀል ክሱን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ማስተናገዱ ተገቢ አይደለም፡፡ ይኸም ቢታለፍ በወቅቱ የሰጠሁት ውሣኔ ትክክለኛ ውሣኔ መሆኑን ወካዩ የፍትህ ሚኒስትር ባረጋገጠበት ሁኔታ ወንጀል ፈፅሟል ተብዬ ጥፋተኛ መባሌ ተገቢ አይደለም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከእኔ ጋር ተከስሶ ጥፋተኛ የተባለውን የሥራ ባልደረባዬን በነፃ አሰናብቶ በእኔ ላይ የጥፋተኝነት ውሣኔ ማፅናቱ ተገቢ አይደለም፡፡ በተከሰስኩበት እንድከላከል ብይን የተሰጠበትና የተፈረደብኝ ጭብጥ የተለያየ በወንጀል ህግ ያልተጠቀሰና የሌለ የህጋዊነት መስፈርት የማያሟላ ነው፡፡ እኔ በተከሰስኩበት ጉዳይ በወሰድኩት እርምጃ መንግስት መጠቀሙንና ጉዳት ያልደረሰበት መሆኑ በተጠሪ ማስረጃ ጭምር ተረጋግጧል ተጠሪ ክስ ማቋረጥና ክስ ማንሣት የሚሉ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦችን በክሳቸው በመጥቀስ ያቀረቡት ክስ ተገቢነት የለውም፡፡ በወቅቱ የፍትህ ሚኒስትሩን ፈቃድ በማግኘት በተጠናከረ መንገድ ምርመራው እንዲቀጥል ማድረጌ በማስረጃ ተረጋግጦ እያለ ጥፋተኛ ነህ መባሌ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል፡፡

ተጠሪ በበኩሉ አመልካች ፍርድ ቤቶቹ የትኛውን ህግ ሲተረጉሙ መሠረታዊ የህግ ስህተት እንደፈፀሙ በሰበር አቤቱታቸው በግልፅ አልዘረዘሩም፡፡ አመልካች የተከሰሱት የወርቁን ባለቤትና ዋና ወንጀል አድራጊ ዳንኤል መኮንን በክሱ ላይ ለይስሙላ ብቻ ስማቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ እንዲያሻሽሉ ሲጠይቅ በተሻሻለው ክስ ሣያካትቱ በመቅረታቸው ምስክሮችና ተከሳሾች እንዳይቀርቡ በማድረጋቸው በዚህም በወንጀልና በፍታብሔር አቶ ዳንኤል መኮንን አሸናፊ ሆነው የሚወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸታቸው ነው አመልካች ውሣኔ በፍትህ ሚኒስትር ተሽሯል፡፡ ይህንን በወቅቱ ፍትህ ሚኒስትር የነበሩት ሰው በምስክርነት ቀርበው አስረድተዋል፡፡ አመልካች ፍትህ ሚኒስትር በአግባቡ ነው የሠራው ብሏል የሚሉት ክርክር የህግ መሠረትና ተቀባይነት የሌለው ነው የከፍተኛው ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የለበትም የሚል የቃል ክርክር አቅርቧል፡፡ አመልካች በቃል የመልስ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በሥር ያቀረበው የወንጀል ክስ ክሱን ለማስረዳትና ለመከላከል በግራቀኙ በኩል የቀረበው ማስረጃ መሠረታዊ ይዘትና የከፍተኛው ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ችሎት የሰጡት ፍርድ ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም መዝገቡን መርምረናል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው ተጠሪ በአመልካች ላይ የወንጀል ክስ የመሠረተው 46.096 ኪሎ ግራም ወርቅ የተያዘበትንና በዋና ወንጀል አድራጊነት መከሰስ የሚገባውን አቶ ዳንኤል መኮንን በህገ ወጥ መንገድ ለመጥቀምና በመንግስትና ህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የወንጀል ክስ አዘጋጅቶ ሲያቀርብ የተከሳሾችና የምስክሮች ፍርድ ቤት የሚቀርቡበትን ቀን ለሚመለከታቸው ክፍሎች ሲገልፅ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቀን ሲገለፅ የተሣሣቱ መረጃዎችን በመስጠት አቶ ዳንኤል መኮንን ከወንጀል ነፃ እንዲሆንና የተያዘውን ወርቅም በፍታብሔር ተከራክሮ ለማስመለስ እንዲችል ሁኔታዎች አመቻችቷል የሚል ነው፡፡

ተጠሪ አመልካች በመጀመሪያ ባቀረበው ክስ አሻሽሎ ባቀረበው ክስና ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን መቅረብና የምስክሮችን መቅረብ የሰጠውን ቀነ ቀጠሮ በተመለከተ በክሱ ውስጥ የጠቀሳቸው ድርጊቶች የተፈፀሙ መሆኑን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ሆኖም አመልካች ተጠሪ በአንደኛው ክስ የጠቀሳቸውን ድርጊቶች የፈፀመው እንደ ተጠሪ የክስ አቀራረብ 46.096 ኪሎ ግራም ወርቅ የተያዘበትን አቶ ዳንኤል መኮንን አላግባብ ለመጥቀም ዳንኤል መኮንን የተያዘበትን ወርቅ በፍታብሔር ተከራክሮ ወርቁን እንዲያስመልስ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እና በህዝብና የመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጭብጥ አመልካች ወርቁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በተጠሪ በቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ጊዜ ድረስ አከናውኗቸዋል ተብለው በተጠሪና በአመልካች ማስረጃ የተገለፀ ተግባራትን አግባብነት ካላቸው የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መመርመር  ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

  1. ተጠሪ አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ህዳር 10 ቀን 1997 ዓ.ም በቀረበው ክስ የወንጀል ተካፋይነቱን አለመዘርዘሩ ክሱን አሻሽሎ ሲያቀርብ አቶ ዳንኤል መኮንን ከክሱ ሣያካትት መቅረቱ በሰነድና በሰው ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ሆኖም አመልካች ይህንን ባደረገው በምርመራ መዝገቡ ጠንካራ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ መሆኑንና አቶ ዳንኤል መክሰስ የወርቁ ባለቤት እሱ መሆኑን ማረጋገጫ እንደመስጠት በመቁጠሩ መሆኑን ይህንንም ከማድረጉ በፊት የጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጋር መማከሩን ትንሽ ቆይቶ አመልካች ሌሎቹን ተከሳሾች ምስክር በማድረግ አቶ ዳንኤል መኮንን መክሰስ እንደሚሻል ለምክትል ሥራ አስኪያጁ የገለፀላቸው መሆኑንና ይህንን ለማድረግ የፍትህ ሚኒስትሩን ፈቃድ ስለሚያስፈልግ አብረን ሄደን እንጠይቃቸው ብሎኝ አብረን ሄደን የፍትህ ሚኒስትሩን ወደ ጅቡቲ በኮንትሮባንድ ሲወጣ 46.096 ኪሎ ግራም ወርቅ መያዙን ጠቋሚዎች ተከሳሾች በመሆናቸው እንዴት መቀጠል እንዳለበት የተቸገረ መሆኑን ሲገልፅላቸው ሚኒስትሩ የወርቅ ኮንትሮባንድ አውጭና ተቀባይ ለማወቅ ምርመራው ተጠናክሮ ይቀጥል ዝቅተኛ ተሣትፎ ያላቸውን ምስክር አድርጎ ከፍተኛ ተሣትፎ ያላቸውን ወንጀለኞች መክሰስ ነው በሚል መንገድ በቃል እንደነገሯቸው በአመልካች አንደኛ የመከላከያ ምስክር የመሠከረ መሆኑን ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሣኔ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ አመልካች ከፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች እንደላኩ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በደብዳቤ እንዲጠይቅለት ነግሯቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪዎች እንዲመድብላቸው ደብዳቤ መፃፋቸውንና በዚያ መሠረት ሁለት መርማሪዎች ተመድበው መጥተው በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ምርመራ ከጀመሩ በኋላ አመልካች በተጠሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በመከላከያ ማስረጃነት ቀርበው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር አመልካች ስሙን ከማያውቁት ሰው ጋር መጥቶ ወርቅ በኮንትሮባንድ ወደ ጅቡቲ ሲሄድ መያዙን እንደነገረላቸውና አነስተኛ የወንጀል ተሣትፎ ያላቸውን ምስክር በማድረግ ከፍተኛ የወንጀል ተሣትፎ ባላቸው ላይ ክሱን እንዲቀጥል በቃል እንዳማከሩት መስክረዋል፡፡ እንደዚሁም ከፌዴራል ፖሊስ ተመድበው የመጡት ሁለት መርማሪ ፖሊሶች አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ሰፋ ያለ ምርመራ እንዳያደርጉ እንደነገራቸውና ለምርመራ ሥራቸው አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዳደረሳቸው መሥክረዋል፡፡

ተጠሪ በጉምሩክ ፖሊስ ተመርምሮ ለአመልካች ያቀረበለት የምርመራ መዝገብ አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ የተሟላ የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ማስረጃ የነበረው መሆኑ አላረጋገጠም፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች በተሻሻለው ክስ ውስጥ ዳንኤል መኮንን ሣይካተት የወንጀል ክስ መቅረብን እንደ ጥፋት የወሰደው የምርመራ መዝገቡን በማስቀረብ በወቅቱ የዳንኤል መኮንን የወንጀል ተሣትፎ በተሟላ ሁኔታ ዘርዝሮና ክሱን አሻሽሎ ለማቅረብ የሚያስችለው ማስረጃ የነበረ መሆኑን በማረጋገጥ አይደለም፡፡ አመልካች በምርመራ መዝገቡ ያለው የማስረጃ ክፍተት በተለይም ተከሳሽ የነበሩትን ሰዎች በዳንኤል መኮንን ላይ ምስክር በማድረግ እስካልተጠቀመ ድረስ ውጤታማ እንደማይሆን በመገንዘብ ለቅርብ የሥራ ኃላፊው የጉምሩክ ምክትል ስራ አስኪያጅ ጋር በመመካከር በመጨረሻም ከፍትህ ሚኒስትሩ ጋር ስለ ጉዳዩ ከተወያየ በኋላ ምርመራው በፌዴራል ፖሊስ ተይዞ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ እያለ በተጠሪ በቁጥጥር ሥር የዋለ መሆኑን በመዝገቡ በግራ ቀኙ በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ያሣያሉ፡፡ አመልካች የሠራቸው እነዚህ ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃዎች አመልካች ምርመራው በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሎና ሌሎች ተከሳሾችን ምስክር በማድረግ አቶ ዳንኤል መኮንን በወንጀል ተጠያቂ እንደሆኑ ፍላጎትና ሀሳብ የነበረው መሆኑን የሚያስረዱ እንጂ አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ለማውጣት ሃሳብና ፍላጎት የነረው መሆኑን የማያስረዱ በመሆናቸው የከፍተኛው ፍርድ ቤት አመልካች በወንጀል ህግ አንቀፅ 403 የተደነገገውን ጥቅም የማስገኘትና የመጉዳት የህግ ግምት በበቂ ማስረጃ ያስተባበለና አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን ከወንጀል ነፃ ለማድረግ በማሰብ በክስ የተጠቀሱትን ተግባራት የፈፀማቸው መሆኑን ዐቃቤ ህግ ሣያስረዳበት፤ የወንጀሉ ሞራላዊ ፍሬ ነገር ሣይሟላ አመልካች ላይ የሰጠው የጥፋተኝነት ውሣኔ በወንጀል ህግ አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 2 የሚጥስና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

  1. ተጠሪ አመልካች ህዳር 10 ቀን 1997 ዓ.ም በቀረበው የወንጀል ክስና ጥር 19 ቀን 1997 ዓ.ም ተሻሽሎ በቀረበው የወንጀል ክስ አንደኛ ተከሳሽ የነበረው አቶ በጅጋ ዲጋሣ ለምን አቶ ዳንኤል መኮንን ክስ እንደተነሣ ሲጠይቀው የእሱ ክስ መቋረጥ ማንንም አይጎዳም አንተም በቀጠሮው ቀን አትቅረብ ብሎ አግባብቷል፡፡ የተከሳሾችና ምስክሮች እንዳይቀርቡ የተለያዩ መሰናክሎችን ፈጥሯል በማለት በአመልካች ላይ ባቀረበው የወንጀል ክስ ገልጿል፡፡ አመልካች በፊት አንደኛ ተከሳሽ የነበረውና ለሶስተኛ ጊዜ በፍትህ ሚኒስትር በኩል ክሱ ተሻሽሎና በአማራጭ ተዘጋጅቶ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ሲቀርብ የዐቃቤ ህግ አንደኛ ምስክር ሆኖ ጠቃሚ የምስክርነት ቃል በሰጠው አቶ በጅጋ ዲጋሣና ሌሎቹ ተከሳሾች ላይ ተጀምሮ የነበረውን ክስ እንዲቀጥል ማድረግ ዋናውን ወንጀል ሠሪ አቶ ዳንአል መኮንን ተጠያቂ ማድረግ እንደማያስችለው በመረዳት ለሎቹን ተከሳሾች ምስክር በማድረግ አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ክስ የማቅረብ ሀሳብ ያለው መሆኑን ለጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ የገለፁለት መሆኑንና ይህንን ለማድረግ የፍትህ ሚኒስትሩን በአካል አግኝተው ካወያያቸው በኋላ ከፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች በትብብር በመጠየቅ ምርመራው በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ እንዲቀጥል ማድረጉን በአመልካች የመከላከያ ምስክሮች ተረጋግጧል፡፡ አመልካች በፊት ተከሳሽ በኋላ ጠቃሚ የዐቃቤ ህግ ምስክር የነበረው አቶ በጅጋ ዲጋሣ በተከሳሽነት በክርክርሩ እንደማይዘልቅ ከወዲሁ መንገር ነበረበት ሊባል አይገባም፡፡ አመልካች ተከሳሾችን ምስክር ማቅረብና ማስቀጣት ዋናው ዓላማው እንዳልሆነና ዋናው አላማው ዕቃውን (የተያዘውን ወርቅ) ማስወረስ መሆኑን ገልፆልኛል በማለት አቶ በጅጋ ዲጋሣ የተጠሪ ምስክር በመሆን ቀርቦ አስረድቷል፡፡ ይኸም አመልካች ተከሳሽ የነበሩትን ሰዎች ምስክር በማድረግና በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ በተጠናከረ ምርመራ ተጨማሪ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ክርክሩን ለመቀጠልና በተለይም የተያዘው ወርቅ ለመንግስት ገቢ እንዲሆንና እንዲወረስ ጠንካራ ፍላጎትና ሀሳበ የነበረው መሆኑ በተጠሪ ምስክር ጭምር የተረጋገጠ መሆኑን የሚያሣይ እንጂ የወንጀል ምርመራና ክስ ሂደቱን በማኮላሸት አቶ ዳንኤል መኮንን ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ ለማውጣትና የተያዘውን ወርቅ በፍታብሔር ተከራክሮ እንዲወሰድ ሀሳብና ፍላጎት የነበራቸው መሆኑን የሚያስረዳ አይደለም፡፡

የፍትህ ሚኒስትር በፊት የተጀመረውን ክስ በመተውና በተለይ በአቶ በጅጋ ድጋሣና ሌሎች ተከሳሾች ላይ አቅርቦት የነበረውን ክስ በማቋረጥ አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ አማራጭ የወንጀል ክሶችን በማቅረብና በመከራከር በኋላም ጉዳዩን የጉምሩከ ዐቃቤ ሕግ በመያዝ እስከ ሰበር ችሎት ድረሰ በመከራከር አቶ ዳንኤል መኮንን ጥፋተኛ ለማሰኘት ውጤታማ ለመሆን የቻለው በፊት ተከሳሽ የነበሩትን አቶ በጅጋ ድጋሣና ሌሎች ተከሳሾች በምስክርነት በመጠቀም እንደሆነ በሰበር መዝገብ ቁጥር 43781 ከተሰጠው ውሣኔ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች በአቶ በጅጋ ድጋሣና ሌሎች ተከሳሾች ላይ የተጀመረው ክርክር እንዳይቀጥልና ምስክሮች እንዳይሰሙ ያደረገው እነዚህን ሰዎች በምስክርነት ተጠቅሞ የተጠናከረ ክስ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ለማቅረብ በማሰብ መሆኑ በጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ የጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተመድበው የነበሩት መርማሪ ፖሊሶችና በውቅቱ የፍትህ ሚኒስትሩ በሰጡት የምስክርነት ቃል ተረጋግጦ እያለ አቶ ዳንኤል መኮንን ጥፋተኛ ለማስባል ጠቃሚ የምስክርነት ቃል በሰጡት በእነ በጅጋ ድጋሣ ላይ ምስክሮች እንዳይቀርቡ ያደረግኸው አቶ ዳንኤል መኮንን ከወንጀሉ ነፃ እንዲሆን ለማድረግና በፍታብሔር ክርክር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው የጥፋተኝነት ውሣኔ በመዝገቡ የተረጋገጠውን ዕውነታ መሠረት ያላደረገና በመዝገቡ የተረጋገጠውን ፍሬ ጉዳይ ከወንጀል ህግ አንቀፅ 403 እና አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 2 ጋር ያላገናዘበ በጉዳዩ የሞራላዊ ፍሬ ጉዳይ መሟላቱን ሣያረጋግጥ የተሰጠና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

  1. አመልካች በክሱ የተገለፁትን ተግባራት የፈፀመው አቶ ዳንኤል በቀለ በፍታብሔር በሚያቀርበው ክርክር ወርቁን ለማስመለስ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በማሰብ ነው በማለት ተጠሪ በክሱ ውስጥ በሰፊው ዘርዝሯል፡፡ ሆኖም አመልካች የተያዘው ወረቅ 46.096 ኪሎ ግራም ወርቅ በብሔራዊ ባንክ በኩል ተሽጦ ገንዘቡ በባንክና በጉምሩክ ሒሳብ እንደተቀመጠ አስተያየት በሰጠው መሠረት የተያዘው ወርቅ የተሸጠ መሆኑን ተጠሪ ያቀረባቸው ወርቁን ይዘውና አጅበው የመጡት ፖሊሶች በሰጡት የምስክርነት ቃል ያረጋገጡ መሆናቸው የተጠሪ ምስክር የነበረው አቶ በጅጋ ድጋሣ አመልካች ዋና ዓላማው የተያዘው ወርቅ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን የገለፁለት መሆኑን በሰጠው ምሰክርነት ማረጋገጡንና አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን የፍታብሔር ክስ ቢያቀርብ ውጤቱ ምን ይሆናል ለሚለው የጉምሩከ ባለሥልጣን የፋይናንስ መምሪያ ደብዳቤ ማንም ሰው የብሔራዊ ባንክ ካልፈቀደ በቀር ወርቆችን መያዝም ሆነ መግዛት የማይችል በመሆኑ የተያዘው ወርቅ ለአቶ ዳንኤል መኮንን ተመላሽ ሊሆን እንደማይችል በመግለፅ ደብዳቤ የፃፈ መሆኑ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትርና ሚኒስትር ዲኤታዎች በያዙት ቃለ ጉባኤ ያረጋገጡ መሆናቸውን መግለፃቸው ሲታይ አመልካች የተያዘው ወርቅ ለአቶ ዳንኤል መኮንን ከፍታብሔር ክርክር እንዲመለስ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሀሳብ ነበረው የሚለው በተጠሪ ክስ የገለፀው ሣይሆን አመልካች ወርቁን የማስወረስና ለአቶ ዳንኤል በቀለ እንዳይመለስ አስፈላጊ የሆኑ የህግ አስተያየቶችን እንደሰጠና የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረከተ መሆኑን የሚያረጋግጡ በመሆኑ አመልካች ወርቁ ለአቶ ዳንኤል መኮንን እንዲመለስ የሚያደርግ ግዙፍ ተግባር ያልፈፀሙና ይህንንም የማድረግ ሀሳብ የሌላቸው ሆኖ እያለ የከፍተኛውና ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካቹ ሀሳብና ፍላጎት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዱ ተያያዥነት ያላቸውን የአመልካች ተግባራት ሣይመረምሩ ተጠሪ በክሱ የጠቀሳቸው ድርጊቶች መፈፀማቸውን ብቻ በመመልከት የሰጡት ውሣኔ በወንጀል ህግ ቁጥር 403 እና የወንጀል ህግ አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 2 ድንጋጌዎችን ተፈፃሚነትና አተረጓጎም ያላገናዘበና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከላይ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 በተዘረዘሩት ምክንያቶች ተጠሪ አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን አላግባብ ለመጥቀምና በመንግስት ላይ ጉዳት እንደደረሰ በማሰብና አቶ ዳንኤል መኮንን በፍታብሔር ተከራክሮ የተያዘውን ወርቅ ለማስመለስ የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ የሠራው የወንጀል ተግባር መኖሩን ተጠሪ በበቂ አላስረዳም፡፡ በአንፃሩ አመልካች አቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ምርመራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግና ሌሎች ተከሳሾችን ከወንጀል ክስ ነፃ በማድረግ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ምስክር አድርጎ ለማቅረብ ከፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጋርና ከበላይ ኃላፊዎቹ ጋር ከተወያየና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪዎች በትብብር እንደላኩለት ደብዳቤ አፅፎ መርማሪዎቹ በአቶ ዳንኤል መኮንን ላይ ምርመራ ከጀመሩ በኋላ በተጠሪ በቁጥጥር ሥር የዋለ መሆኑን በመከላከያ ማስረጃው አስረድቷል፡፡ ስለሆነም የሞራላዊ ፍሬ ነገር ባልተሟላበት አመልካች በወንጀል ህግ ቁጥር 403 የተደነገገውን የህግ ግምት በአጥጋቢ ማስረጃ ባስተባበለበት ሁኔታ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 214/74 አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 1(ሀ)(ለ) እና 2 የተመለከተውን በመተላለፍ በሥልጣን አላግባብ የመገልገል ወንጀል የፈፀመ ነው በማለት የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ችሎት ሣያርም ማፅናቱ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀፅ 2 የሚደነግገውን መሠረታዊ ሁኔታዎች የሚጥስና መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል፡፡

  1. የከፍተኛው ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ይግባኝ ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195(2)(ለ-1) መሠረት ተሽሯል፡፡
  2. አመልካች የተከሰሱበትን በሥልጣን አላግባብ የመገልገል ወንጀል ያልፈፀሙ ስለሆነ በነፃ ይሰናበቱ ብለናል፡፡

ይኸ ፍርድ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በሙሉ ድምፅ ተሰጠ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

ራ/ታ

 

[1] ያልታተመ

6 replies »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.