በአሜሪካም ኢሊዮኒስ ግዛት በኪርካም እና ዊል (Kirkham Vs. Will) መካከል በታየ አንድ የይግባኝ ክርክር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በጉዳዩ የተነሳው ጭብጭ የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያን በመጠቀም እልባት ሰጥቶበታል፡፡ ክሱ የተጀመረው “የተከሳሽ ውሻ በንክሻ ላደረሰብኝ ጉዳት የውሻው ባለቤት የሆነው ተከሳሽ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል፡፡” በሚል ከሳሽ ባቀረበው ክስ ሲሆን ተከሳሹም በበኩሉ ከሳሽ የተነከሰው ውሻውን በመተናኮሉ ስለሆነ በራሱ ጥፋት ለደረሰበት ጉዳት ልጠየቅ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡
ክሱ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በይግባኝ ክርክሩ ላይ በዋነኛነት የተነሳው ጭብጥ “መተናኮል አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ ይህንን ጭብጥ ለመወሰን እንደመመዘኛ ወይም መስፈርት የተጠቀሙት የተለመደውን የአስተዋይ ሰው ሚዛን ሳይሆን የአንድ አስተዋይ ውሻ መለኪያ ነበር፡ በዚህ ሚዛን ወይም መለኪያ መሠረት መተናኮል አለ ወይስ የለም? የሚለውን ጥያቄ ለመወሰን በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ‘አንድ አስተዋይ ውሻ’ ከሳሽ ካሳየው እንቅስቃሴ አንጻር ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል? የሚል መላምታዊ ጥያቄ አንስቶ ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተፈጻሚ ባደረግው መለኪያ መሰረት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶታል፡፡