ያልታተሙ የሰበር ውሳኔዎች

ዕቃዎችን በመርከብ ስለማጓጓዝና የቻርተርፓርቲ ስምምነት (ሰ/መ/ቁ. 21776 -ያልታተመ -3 ለ 2 አብላጫ ድምፅ የተወሰነ)

                                                          የሰ/መ/ቁ. 21776

መጋቢት 17 ቀን 2001 ዓ.ም

ዳኞች፡- ዓብዱልቃድር መሐመድ

       ታፈሰ ይርጋ

       ፀጋዬ አስማማው

       አልማው ወሌ

       ዓሊ መሐመድ

አመልቾች፡- 1. ኢኬንስለር ዲስ ቲካሬት ኤ.ኤ.ስ አልቀረቡም

2.  ቱሬ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር አልቀረቡም

ተጠሪ፡- ጉና የንግድ ስራዎች ድርጅት ኃ/የተ/የግል ማህበር ጠበቃ አቶ ይስሐቅ ተስፋዬ

      መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ነበር፡፡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥሰናል፡፡

ፍ ር ድ

      ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች ጥቅምት 15 ቀን 1998 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16/75 ሐምሌ 29 ቀን 1997 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ስላመለከቱ ነው፡፡

ክርክሩ በመጀመሪያ የታየው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በከፍተኛው ፍ/ቤት ተጠሪ በከሳሽነት ቀርቦ ከአንደኛው አመልካች አንድ ሺ ሜትሪክ ቶን፣(1000 ሜትሪክ ቶን) ብረት የገዛ መሆኑንና በቻርተርፓርቲ እቃውን ለመላክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት አሻሽዬ እንድከፈት ጠይቆኝ በዚሁ መሰረት “ሌተር ኦፍ ክሬዲቱን” ካሻሻልኩ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ(አመልካች) “ኤም.ቪ.ማርዋ” ከተባለ መርከብ አዛዥ ወይም የመርከብ ባለሐብት ጋር እቃውን በቻርተርፓርቲ ለማጓጓዠ ያደረገው ውል ሣይኖር እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም የቻርተርፓርቲ ውል የተዋዋለ በማስመሰል የቻርተርፓርቲ ቢል ኦፍሊዲንግ ለባንክ በማቅረብ የእቃውንና የማስጫኛውን ዋጋ ወስዷል፡፡ ስለሆነም እቃውን ጭኛለሁ ብሎ ገንዘብ የወሰደ ቢሆንም እቃውን ጫነች የተባለችው መርከብ ክሱን እስካቀረብንበት ጊዜ ድረስ የትእንዳለች ለማወቅ አልተቻለም፡፡ አንደኛ ተከሳሽ እቃውን ለመከታተልና ከአጓዡን ከመርከቡ ባለሐብት ጋር ያደረገውን ቻርተርፓርቲ ውል እንዲልክልን በተደጋጋሚ የጠይቀነው ቢሆንም ግንቦት 14 ቀን 1998 ዓ.ም በቴሌክስ በፃፈው ደብዳቤ ከመርከቡ ባሐብት ወይም ወኪል ጋር የተፈራረምኩት የቻርተርፓርቲ ውል የለንም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ አንደኛ ተከሳሽ (አመልካች) በሐሰት በተዘጋጀ የቻርተርፓርቲ ቢል ኦፍሌድንግ ለባንክ አቀርቦ የወሰደውን የእቃውን ዋጋና የማስጫኛ ዋጋ ለባንክ ለኢንሹራንስ ለፋክስ ያወጣነውንና ከእቃው የምናገኘው ትርፍ በድምሩ 372,269(ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ሺ ሁለት መቶ ስልሣ ዘጠኝ) የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ሁለተኛውም አመልካች የአንድነትና የነጠላ ሐላፊነት ስላለባቸው ከላይ የተገለፀውን ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍል እንዲወሰንልኝ በማለት ክስ አቅርቧል፡፡

አንደኛው አመልካች በተከሳሽነት ቀርቦ በሽያጭ ውሉ መሰረት አንድ ሺ ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት በቻርተር መርከብ በመጫን የመርከቡን የመጓጓዣያ ዋጋ በመክፈል እቃው በትክክል “ኬም.ቪ.ማረዋ.ኤም” ከተባለች መርከብ ያለጉድለት የተጫነ መሆኑን የሚያረጋግጥ በመርከቡ አዛዥ የፈረመው የጭነት ማስተወቂያ ደረሰኝ (clear on board bill of lading) ለከሳሽ (ተጠሪ) ልኬአለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ የቻርተርፓርቲ ውል የማቅረብ ግዴታ የለብኝም፡፡ የላኩለት የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ሐሰተኛ ስለመሆኑ ማስረጃ ያላቀረበ ስለሆነ በራሱ ድክመት ለደረሰበት ኪሣራ እኔ ላይ ያላቀረበው ክስ ተገቢነት የለውም በማለት ተከራክሯል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ (አመልካች) በበኩሉ አንደኛ ተከሳሽ (አመልካች) ውሉን ካልፈፀመ በአንድነትና በነጠላ ኃላፊ ለመሆን የገባሁት ግዴታ የሌለ በመሆኑ ተጠያቂ ልሆን አይገባኝም በማለት ተከራክሯል፡፡

የተጠሪንና የአመልካቾችን ክርክርና ማስረጃ በመጀመሪያ የሰማውና የመዘነው የከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ተከሳሽ(አመልካች) ከከሳሽ (ተጠሪ) ጋር በገባው የውል ግዴታ መሰረት የሸጠውን የአርማታ ብረት “የኤም ቪ ማሪዋ ኤም” ከተባለችው መርከብ ጉድለት በሌለበት ሁኔታ የጫነ መሆኑን በማረጋገጥ በመርከቡ ካፕቴን በባህር ህጉ አንቀጽ 187 ንኡስ አንቀጽ 3 መሰረት “የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ” (clean on bard bill of lading) ያቀረበ ስለሆነ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ የቻርተርፓርቲ ውል የማቅረብ ግዴታ የለበትም ስለዚህ ለቀረበው ክስ በሐላፊነት የሚጠየቅበት ምክንያት የለም በማለት የወሰነ ሲሆን ሁለተኛው ተከሳሽ (አመልካች) አንደኛው ተከሳሽ(አመልካች) ሐላፊነት የሌለበት በመሆኑ ከቀረበበት ክስ ነፃ ነው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

ከፍተኛው ፍ/ቤት በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት ተጠሪ ይግባኝ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ፣ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ፣አግባብነት አላቸው የሚላቸውን የፍታብሔር ሕጐች ከተነተነ በኋላ አንደኛ መልስ ሰጭ (አመልካች) በባህር ሕግ ቁጥር 187 ንኡስ አንቀጽ 1 መሰረት የጭነት ማስታወቂያ በማቅረብ ከሐላፊነት ነፃ የሚሆነው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኙ ታዓማኒነት ያለውና ሕጋዊ አካሄድ ተከትሎ የተሰራ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ አንደኛ መልስ ሰጭ(አመልካች) ካቀረበው ክርክርና ማስረጃ ሲመዘኑ እቃው አልተጫነም ወይም አልተላከም ከሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም አንደኛ መልስ ሰጭ በገባው የሺያጭ ውል መሰረት ግዴታውን ያልተወጣ በመሆኑ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሁለተኛ መ/ሰጪ(አመልካች) ሐላፊነት የሌለበት መሆኑን አንስቶ ቢከራከሩም የአንድነትና የነጠላ ሐላፊነት ያለበት መሆኑን የቀረቡት ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም አንደኛው መልስ ሰጭ (አመልካች) እና ሁለተኛ መልስ ሰጭ በአንድነትና በነጠላ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ብር 2,593,970.30(ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ሶስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ብር ከሰላሣ ሣንቲም) እና ለዳኝነት የተከፈለውን ብር 43,184.56(አርባ ሦስት ሺ አንድ መቶ ሰማኒያ አራት ብር ከሐምሣ ስድስት ሣንቲም) እንዲከፍሉ በማለት ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

አመልካቾች የጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ (C&F seal contract) ማጓጓዝን የሚጨምር የሽያጭ ውል አቃውን ለባለመርከቡ ከማስረከብ አልፎ እቃው ገዥ እጅ እስኪረከብ ድረስ ኃላፊነት አለበት በማለት የፍታሐብሔር ድንጋጌዎችን በመጥቀስ መሰረታዊ የህግ ስህተት ፈጽሟል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የማጓጓዝ ግዴታን የሚጨምር የሽያጭ ውልን አስመልክቶ የዓለም የንግድ ምክር ቤት ባወጣቸው ቃሎችን (ICC INCOTERMS) በማዛባት የሰጠው ውሳኔ ሊታረም ይገባዋል፡፡ እቃው በመርከብ ላይ የተጫነ መሆኑን በመርከቡ ካፕቴን የተፈረመ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (bill of lading) አቅርቦ እያለና ይህም ሰነድ በባህር ሕግ ድንጋጌዎች አንቀጽ 181 እና 187/3/ በመተላለፍ የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 2301/3/ በመጥቀስ ለጉዳዩ ተፈፃሚ መሆን ያለበትን የባህር ሕግ ልዩ ድንጋጌዎች ውጤት ማሳጣቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው፡፡ ሁለተኛው አመልካች የገባው የውል ግዴታ ሣይኖር በአንድነትና በነጠላ ሐላፊ ነህ መባሉ የፍታብሔር ሕግ ቁጥር 1952/1/ የሚጥስ ነው፡፡ ሁለተኛው አመልካች የመጓጓዥያ ውሉ ሲቀየር ያልተሰማማ በመሆኑ የፍርድ ቤቱ ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት አመልክተዋል፡፡

ተጠሪ በበኩሉ አመልካቾች በባህር ሕጉ መሰረት አንደኛ አመልካች እቃዎቹን ያለጐድለት በመርከብ ላይ በመጫን የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (ቢል ኦፍ ሌዲንግ) ያቀረበ ስለሆነ ግዴታውን ተወጥቷል በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ተገቢነት የለውም፡ አንደኛ አመልካች ለእኛ የላከልን የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ሐሰተኛ ሰነድ ነው፡፡ አንደኛ አመልካች የላከልን የጭነት ማስትወቂያ ደረሰኝ (ቢል ኦፍ ሌዲንግ) በአንደኛ አመልካችና በመርከቧ ባለንብረት መካከል ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም በተደረገው የቻርተርፓርቲ የእቃ ማጓጓዥያ ውል መሰረት እቃው በመርከብ ላይ የጫነ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ሆኖም አንደኛ አመልካች ከመርከቡ ባለሐብት ወይም ወኪሉ ጋር ግንቦት 29 ቀን 1998 ያደረገው የቻርተርፓርቲ የእቃ ማጓጓዣ ውል የሌለ መሆኑን አንደኛው አመልካች ግንቦት 14 ቀን 1999 በቴሌክስ በፃፈው ደብዳቤ አረጋግጦልናል፡፡ ይህንን ትክክለኛ ያልሆነ ሐሰተኛና ያልተደረገ የቻርተርፓርቲ ውል የሚጠቅስ ሐሰተኛ ሰነድ ይዘን በአጓዡ ላይ ክስ ለማቅረብ የምንችልበት ሁኔታ የለም፡፡ አመልካቾች የጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍታብሔር ህግ በመጠቀስ ወሰነብን የሚሉት ተገቢ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱ ኃላፊ ያላቸው ያቀረቡት የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ታዓማኒነት የሌለውና አጠራጣሪ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ በመድረሱ ነው፡፡ ሁለተኛው አመልካች በዋናው ውል እቃውን ለማስረከብ ግዴታ የገቡ ሲሆን ኤልሲው እንዲሻሻል ጥያቄውን ያቀረበው የአንደኛው አመልካች ወኪል ሆኖ ራሱ ነው፡፡ ስለዚህ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረትዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡

አመልካቾች የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ነሐሴ 13 ቀን 1999 ዓ.ም የተጻፈ አራት ገጽ የመልስ መልስ ያቀረቡ ሲሆን የሰበር ችሎቱም የአመልካቾችንና የተጠሪን ጠበቆች ያቀረቡትን የቃል ክርክር ሰምቷል፡፡ የክርክሩ መሰረታዊ ፍሬ ጉዳይ፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔና በሰበር የተደረገው ክርክር ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩን መርምረናል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ባቀረበው የክስ ማመልከቻ የጠየቀውን ገንዘብ አመልካቾች በአንድነትና በነጠላ የመክፈል ኃላፊነት አለባቸው በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ የክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከላይ የያዝነውን ጭብጥ ለመወሰን በመጀመሪያ በተጠሪና በአንደኛ አመልካች መካከል ያለውን ግንኙነት፣ ተጠሪ አንደኛ አመልካች በገባው የውል ግዴታ መሰረት አልፈፀመም በማለት የሚያቀርበውን ክርክርና ማስረጃ አንደኛ አመልካች በመከላከያነት የሚያነሣቸውን የመከራከሪያ ነጥቦችና ያቀረባቸውን ማስረጃ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የመሰረቱትን ጭብጥና የሰጡትን ውሣኔ አግባብነት ካላቸው ድንግጌዎች ጋር በማገናዘብ መመርመሩ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

  1. በመጀመሪያ ተጠሪ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበውን ክስ ይዘትና የመከራከሪያ ነጥብ አንደኛ አመልካች የሰጠውን የመከላከያ መልስና ያቀረበውን ማስረጃ፣ ፍርድ ቤቱ የመሰረተውን ጭብጥና የሰጠውን ውሣኔ መመልከቱ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ተገቢነት ለመመርመር የጐላ ጠቀሜታ አለው፡፡ ተጠሪ ከአንደኛ አመልካች መጠኑ አንድ ሺ ሜትሪክ ቶን የሆነ “የሆት ፎሊድ የማጠናከሪያ ብረት ዘንጐች” እንደ አውሮፖ አቆጣጠር መጋቢት 18 ቀን 1998 ዓ.ም በተፈራረሙት የሽያጭ ውል የገዛ መሆኑ በአንደኛ አመልካችም ሆነ በተጠሪ የተካደ አይደለም፡፡ ተጠሪና አንደኛ አመልካች ባደረጉት የሽያጭ ውል ስምምነት አንደኛ አመልካች እቃውን “በሎይድ ወይም ተመሣሣይ” በሆነ መንገድ በተመዘገበ መርከብ ያለምንም ጉድለት የመጫንና የመጓጓዥያ ገንዘቡን ለአጓጓዙ የማስረከብ ግዴታ እንዳለበት በውሉ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ 3 የተመለከተ መሆኑንና ከዚህ በኋላ አንደኛ አመልካች እንደአውሮፓ አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 1998 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ ተጠሪ የከፈተው “ኤልሲ” ላይ እቃው የሚላከው “በተራ ሎይድ” በተመዘገበ የጭነት ማጓጓዥያ መሆኑ ቀርቶ “በቻርተርፓርቲ ስምምነት” መሰረት እደሆነ፣ የተከፈተው “ኤልሲ” ቻርተርፓርቲ ተብሎ ተሻሽሎ እንዲከፈት የጠየቀ መሆኑንና ተጠሪ አንደኛ አመልካች ያቀረበውን የማሻሻያ ጥያቄ በመቀበል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤል ሲውን በቻርተርፓርቲ አሻሽሎ እንዲከፍትለት የጠየቀ መሆኑና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ኤልሲውን አሻሽሎ የከፈተ ስለመሆኑ በአንደኛ አመልካችና እና በተጠሪ መካከል የተፈጠረ ልዩነት የለም፡፡

አንደኛ አመልካች ከዚህ በኋላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም “ኤም ቪ ማርዋ” ከተባለ የመርከብ ድርጅት ጋር እቃውን በቀጥታ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማጓጓዝ የሚያስችል የቻርተርፓርቲ ስምምነት ያደረገ መሆኑን የሚገልጽና በተደረገው የቻርተርፓርቲ ስምምነት መሰረት አንደኛ አመልካች 40,912.67(አርባ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ ሁለት የአሜሪካን ዶላር ከስልሣ ሰባት የአሜሪካን ሣንቲም) “ለኤም ቪ ማርዋ” ከፍሎ እቃውን ያለምንምን ጉድለት እንደ አውሮፓ አቶጣጣር ሰኔ 3 ቀን 1998 ዓ.ም ከመርከብ ላይ የጫነ መሆኑን የሚገልጽ “የኤም ቪ ማርዋ” ካፕቴን የፈረመበት የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (“ክሊን ኦን ቦርድ ቢል ኦፍ ሌዲንግ”) ነው በማለት ሰነዱን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላክ የእቃውንና ለእቃ መጓጓዥያ መከፈል የሚገባውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የወሰደ ስለመሆኑ አንደኛ አመልካች እና ተጠሪ አልተካካዱም፡፡

ተጠሪና አንደኛ አመልካች የሚካካዱበት ነጥብ ተጠሪ ለአንደኛ አመልካች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውና ለእኔ የሰጠኝ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ( ክሊን ኦን ቦርድ ቢል ኦፍ ሌዲንግ) ትክክለኛ እና አንደኛ አመልካች እቃውን መርከብ ላይ የጫነ መሆኑን የሚያስረዳ ሰነድ አይደለም፡፡ ይኸ ሰነድ በሐሰት ተዘጋጅቶ በአንደኛው አመልካች የቀረበ ሰነድ ነው፣ በማለት በክስ ማመልከቻው የገለፀ ሲሆን አንደኛ አመልካች በበኩሉ ሰነዱ እቃውን “ኤም ቪ ማርዋ” ከተባለች መርከብ ላይ የጫንኩ መሆኑን የሚያረጋግጥና የሚያስረዳ ትክክለኛ ሰነድ ነው በማለት የመከላከያ መልሱን አቅርቧል፡፡ በአንድ ጉዳይ ጭብጥ የሚመሰረተው አንደኛው ተከራካሪ የገለፀውን ነገር ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በማስተባበል የካደ እንደሆነ መሆኑን ከፍታብሔር ስነ ስርአት ሕግ ቁጥር 247 ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚቻል ሲሆን ፍርድ ቤቱ የክርክሩን ጭብጥ መመስረት ያለበት በክሱና በመከላከያ መልስ የተገለፁ ነገሮችን፣ በተከራካሪዎቹ የቀረቡለትን የጽሑፍ ማስረጃ እና በፍታብሔር ሰነ ስርአት ሕግ ቁጥር 241 መሰረት የቃል ምርመራ ሲያደርግ ተከራካሪዎች ከሰጡት ምላሽ መሰረት በማድረግ መሆን እንዳለበት ከፍታብሔር ስነ ስርአት ሕግ ቁጥር 248 ድንግጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ተጠሪና አንደኛ አመልካች በስር ፍርድ ቤት በይግባኝና በሰበር ካደረጉት የጽሑፍና የቃል ክርክር ለመረዳት የሚቻለው አከራካሪው ጭብጥ አንደኛ አመልካች “ኤም ቪ ማርዋ” በተባለችው መርከብ ካፕቴን የተፈረመ ነው በማለት ያቀረበው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (clean on board bill of lading)ትክክለኛና አንደኛ አመልካች እቃውን ከመርከብ ላይ የጫነ ለመሆኑ ለማስረዳት የሚችል ታአማኒነት ያለው ሰነድ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው፡፡ አከራካሪው ነጥብ የዚህ ሰነድ ታአማኒነት እና ትክክለኛነት ሆኖ አያለ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተጠሪና አንደኛ አመልካች የሚካካዱበትን ይህንን መሰረታዊ ነጥብ በጭብጥነት ሣይዝ አልፎታል፡፡ የባህር ሕግ አንቀጽ 181 እና የባህር ሕግ አንቀጽ 187 በጉዳዩ ተፈፃሚ የሚሆኑት በመጀመሪያ አንደኛ አመልካች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀረበውና ለተጠሪ የላከው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ታአማኒነት ያለውና ትክክለኛ ሰነድ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጭብጥ ተመርምሮ ሰነዱ ትክክለኛ ነው በሚል መደምደሚያ ላይ ሲደርስ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ስናየው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤት የክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥ አድርጐ መያዝ የሚገባውን ነገር ግን በጭብጥነት ሣይዘው ያለፈውን ነጥብ በመሰረታዊ ጭብጥነት በመያዝ የአንደኛ አመልካችንና የተጠሪን ማስረጀና ክርክር መመዘኑ ከፍታብሔር ስነ ስርአት ሕግ ቁጥር 182 ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት ያከናወነው ተግባር በመሆኑ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

  1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አንደኛ አመልካች የቃረበው “የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ” ታአማኒነትና ትክክለኛነት አስመልክቶ በጭብጥነት በመያዝ ማስረጃው ታዓማኒነት የሌለው ነው፡፡ አንደኛ አመልካች ያቀረበው ክርክርና ማስረጃ፣ አንደኛ አመልካች እቃውን በመርከብ ላይ አልጫነም ከሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ናቸው በማለት ወስኗል፡፡

አመልካቾች ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው አግባብነት የሌላቸው የፍታብሔር ህግ ድንጋጌዎች በመጥቀስና መሰረት በማድረግ ነው በማለት የሚከራከሩ በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካችን ማስረጃ ታአማኒነት የለውም በማለት የደረሰበት መደምደሚያ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ይግባኝ ሰሚው ችሎት ማስረጃው ታዓማኒነት የለውም ያለው የማስረጃውን ይዘት እና ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ተጣምሮ ሲታይ የሚያሣየውን ሁኔታ በመመርመር ነው ወይስ የፍታብሔር ሕግ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ የሚሉትን ነጥቦች መመዘኑ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

የአንድ ማስረጃ ታአማኒነት (credibility) አስመልክቶ የሚነሣ ክርክር ማስረጃው ትክክለኛ እውነተኛ ሰነድ ነው ወይስ አይደለም በሚለው አንፃር የሚታይ ነው፡፡ አንደኛ አመልካች “ኤም ቪ ማርዋ” የተባለችው መርከብ ካፕቴን ፈርሞ የሰጠኝ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (ክሌን ኦን ቦርድ ቢል ኦፍ ሌዲንግ) ነው በማለት ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ትክክለኛ ሣይሆን በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው በማለት ተጠሪ አጥብቆ ይከራከራል፡፡ አንድ የሰነድ ማስረጃ ትክክለኛነት(ታአማኒነት) ለመመዘን በመጀመሪያ ሰነዱ ውስጥ የተገለፁት ፍሬ ጉዳዮች ትክክለኛና በእርግጠኝነት የተከናወኑ ተግባራትና ፍሬ ጉዳዮችን የሚገልፁ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሰነድ ማስረጃው ውስጥ የተገለጹት ፍሬ ጉዳዮች እና ተከራካሪው በፃፏቸውና ባቀረቧቸው ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች ይዘት እርስ በርሱ የማይቃረን (contradictory evidence) አለመሆናቸውንና በአንፃሩ የሰነድ ማስረጃዎቹ ተደጋጋፊነት ያላቸውና የአንድን ፍሬ ጉዳይ መከሰት ወይም መኖር የሚያስረዱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

አንደኛ አመልካች እቃዎቹ “በኤም ቪ ማርዋ” የተጫኑ መሆኑን በመርከቡ ካፔቴን ተፈርሞ ተሰጥቶኛል የሚለው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (clean on board bill of lading) በይዘቱ ሲመረመር ሙሉ በሙሉ የተፈፀሙና የተከናወኑ ፍሬ ጉዳዮችን በትክክለኛው መንገድ የሚገልጽ ሰነድ አይደለም፡፡ ሰነዱ ያልተፈፀመና ሐሰተኛ የሆነ መግለጫ አካትቶ የያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ተጠሪ ያቀረበው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ በባለመርከቡ ድርጅትና በአንደኛ አመልካች መካከል እንደአውሮፓ አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን 1998 በተደረገው የቻርተርፓርቲ ስምምነት መሰረት እቃው ሰኔ 3 ቀን 1998 ዓ.ም  “ኤም ቪ ማርዋ” ከተባለችው መርከብ አመልካች የጫነና የማጓጓዥያ ሒሳብ የከፈለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሆኖም አንደኛ አመልካች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 14 ቀን 1999 ዓ.ም በቴሌክስ ባስተላለፈው ደብዳቤ ከመርከብ ድርጅቱ ወይም ወኪሉ ጋር እንደአውሮፓ አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም ያደረገው የቻርተርፓርቲ ውል የሌለና ውሉ በተዋዋይ ወገኖች ያልተፈረመ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ከዚህም የምንረዳው አንደኛ አመልካች በመርከቡ ካፕቴን ተፈርሞ የተሰጠኝ ነው የሚለው “የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ” በይዘቱ ያልተከናወነና ልተፈፀመ ፍሬ ጉዳይ እንደተከናወነ አድርጐ የሚጥቅስ ሐሰተኛ ቃልና መግለጫ ያለበት ሰነድ ነው፡፡ አንድ ሰነድ ከያዛቸው ፍሬ ጉዳዮች ከፊሉ ሐሰተኛ እና ትክክለኛ አለመሆኑ ከተረጋገጠ፤ ሰነዱ ታዓሚኒነት የሌለው ሰነድ እንደሚሆንና እቃው ተጭኗል የማጓጓዥያ ዋጋ ተከፍሏል ተብሎ በሰነዱ የተጠቀሰውን ፍሬ ጉዳይ እውነተኛ መግለጫ ነው ብሎ ለመቀበል የሚከብድና የማይቻል  በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ይኸ ሰነድ ታዓማኒነት የለውም በማለት የደረሰበት መደምደሚያ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንደኛ አመልካች “ኤም ቪ ማርዋ” በተባለችው መርከብ ካፐቴን ተፈርሞ ተሰጥቶኛል በማለት ያቀረበው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (ክሊን ኦን ቦርድ ቢል ኦፍ ሌዲንግ) እና አንደኛ አመልካች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 14 ቀን 1999 ዓ.ም በቴሌክስ የፃፈው ደብዳቤ በይዘታቸው እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ማስረጃዎች(contradictory evidence) ናቸው፡፡ እንደዚሁም አንደኛ አመልካች እቃውን የጫነችው መርከብ ዝርዝር ሁኔታ እንደገለፁለት በተጠሪ በኩል በቀረበለት ጥያቄ በቴሌክስ የሰጠው ምላሽና የፃፋቸው ደብዳቤዎች የድርጅቱ የፐሮተኮል ቁጥር የሌላቸው፣ አግባብ ባለው ባለስልጣን ያልተፈረሙና በድርጅቱ ማህተም ያልተረጋገጡ በአጠቃላይ ተጠሪ እቃውን አጓዥ ነው ከተባለው ድርጅት ላይ ለማስመለስ በማስረጃነት አቀርቦ ሊጠቀምባቸው በሚችል መንገድ ተዘጋጅተውና በሚገባ በአንደኛ አመልካች ተረጋግጠው ያልተላኩ ናቸው ከዚህ በተጨማሪ አንደኛ አመልካች ከመርከቡ ባለሐብት ጋር ተስማምቸበታለሁ የሚለው የቻርተርፓርቲ ስምምነት በአመለካችም ሆነ የመርከቡ ድርጅት ወይም ወኪል ያልተፈረመ ረቂቅ ሰነድ መሆኑ ሲመዘን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደኛ አመልካች እቃውን በመርከብ ላይ አልጫነም ከሚለው መደምደሚያ ላይ መድረስ የቀረቡለትን ማስረጃዎች ታዓማኒነት ተቀባይነት ባላቸው መስፈርቶች መሰረት በመመዘን የደረሰበት መደምደሚያ በመሆኑ ጉድለት ያለበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡

  1. አንደኛ አመልካች “ኤም ቪ ማርዋ” በተባችው መርከብ ላይ እቃው ሰኔ 3 ቀን 1998 ዓ.ም ጉድለት በሌለበት ሁኔታ የተጫነ መሆኑን ያስረዳል በማለት ያቀረበው “ክሊን ኦን ቦርድ ቢል ኦፍ ሌዲንግ” ከዚህ ሰነድ በተጨማሪ ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም በባለመርከቡ ድርጅት በአንደኛ አመልካች መካከል የተደረገ የቻርተርፓርቲ ስምምነት ያለ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው አንደኛ አመልካች እቃዎቹን የጫነ መሆኑን እና ከአጓጓዙ የመርከብ ድርጅት ጋር የቻርተርፓርቲ ስምምነት ያለ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሁለት የተለያዩ ሰነዶች እንዳሉ አንደኛ አመልካች የውል ግዴታየን ለመፈፀሜ አይነተኛ ማስረጃ ነው በማለት ያቀረበው ሰነድ ያሣያል፡፡

በአጓጓዥ የመርከብ ድርጅቱና በእቃ ላኪው መካከል የተደረገ የቻርተርፓርቲ ስምምነት በሚደረግበት ጊዜ፣ስምምነቱ በባህር ህግ ቁጥር 134 የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች በግልጽ በሚያሳይ መንገድ መደረግ ያለበት ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እቃው ከመጫኑ በፊት የተደረገ የቻርተር ፓርቲ የመጫን ኪራይ ውልና እቃው ሲጫን በመርከቡ ካፕቴን የሚሰጥ የቻርታርፓርቲ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ (ቻርተርፓርቲ ቢል ኦፍ ሌዲንግ) ሁል ጊዜ በይዞታቸውም ሆነ በውጤታቸው አንድና ተመሣሣይ ሰነዶች ናቸው ተብሎ ለመደምደም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በቻርተርፓርቲ ስምምነትና በጭነት ማስታወቂያ መካከል ልዩነት የሚያጋጥምበት ሁኔታ እንዳለና የዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ተዋዋይ ወገኖች የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ የተገለፀው ቃል ተፈፃሚ እንዲሆን ካልተስማሙ በስተቀር በላጭነት ያለውና ሊፈፀም የሚገባው በቻርተርፓርቲ ስምምነቱ የተገለፀው ቃል እንደሆነ የባህር ሕግ አንቀጽ 194 ንኡስ አንቀጽ 1 “ተዋዋይ ወገኖች በዚሁ አይነት እንዲፈፀም የተስማሙበት መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር በጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ላይ የተፃፈው የውል ቃል ስለመርከቡ መከራየት ጉዳይ ከተደረገው ውል ላይ ቀዳሚ ብልጫ አይሰጠውም” በማለት ደንግጓል፡፡

ከዚህ አንፃር ስናየው አንደኛ አመልካች “በኤም ቪ ማርዋ” የመርከብ ካፕቴን ተፈርሞ የተሰጠኝ ነው የሚለው የሰነድ ማስረጃ የቻርተርፓርቲ ውል ከዚያ በፊት ከመርከቡ ድርጅት ጋር ለማድረጌም እቃውን በመርከብ ላይ የጫንኩ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው በማለት የሚያቀርበው ክርክር ማስረጃው ታዓማኒነት የለውም በማለት ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከደረሰበት መደምደሚያ በተጨማሪ ክርክሩ በባህር ሕግ ቁጥር 134 እና የባህር ሕግ ቁጥር 194 ድንጋጌዎችን ከግንዛቤ ውስጥ የማያስገባ በመሆኑ ተቀባይነት ያለው የህግ ክርክር ሆኖ አላገኘነውም፡፡

  1. አንደኛ አመልካች ዓለም አቀፍ የንግድ ቸንበር ያወጣቸውን የንግድ ቃላቶች (Incoterms) በመጥቀስና ስለ መርከብ ማጓጓዝ ኪራይ ውል በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡ ስምምነቶችን በማጣቀስ የሰበር ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ ሆኖም አመልካቾች የጠቀሱት (C and F) የመጫኛና የመጓጓዥያ ዋጋ የተከፈለበት የሚለው የዓለም አቀፍ የንግድ ቃልም ሆነ ስለ መርከብ መጓጓዥያ የወጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሊጠቀሱና ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉት በመጀመሪያ አንደኛ አመልካች በገባው የውል ግዴታ መሰረት በቻርተርፓርቲ መርከብ ተከራይቶ እቃውን ጉድለት በሌለበት ሁኔታ መርከብ ላይ የጫነ መሆኑን ትክክለኛና ታዓማኒነት ያለው ማስረጃ በማቅረብ ለማስረዳት ሲችል ነው፡፡ በያዝው ጉዳይ አንደኛ አመልካች በተሻሻለው ውል መሰረት የቻርተርፓርቲ የመርከብ ኪራይ ውል ከፍሎ እቃዎቹን ያለምንም ጉድለት መርከብ ላይ የጫነ ስለመሆኑ ታዓማኒነት ያለው ትክክለኛ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ስለሆነም እቃውን በውሉ መሰረት ከመርከብ ላይ አልጫነም በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ወስኖበታል፡፡ አንደኛ አመልካች እቃውን በቻርተርፓርቲ በተደረገው የመርከብ ኪራይ ውል መሰረት የመርከብ ኪራይ ከፍሎ የጫነ ስለመሆኑ ታዓማኒነት ያለው ማስረጃ ባላቀረበበት ሁኔታ እቃው በአግባቡ በመርከብ ላይ ከተጫነ በኋላ ለሚደርሰው ጉዳት ማን ኃላፊ ይሆናል በሚለው ነጥብ ተፈፃሚና ተጠቃሽ የሚሆኑትን ዓለም አቀፍ የንግድ ቃላቶችና(Inconterms) እና አለም አቀፍ ስምምነት እያጣቀሰ ያቀረበው ክርክር ተገቢ ሆኖ አላገኘውም፡፡

ይግባኝ ሰሚው ችሎት በዋነኛነት የአንደኛ አመልካች የሰነድ ማስረጃዎች በመመርመር ማስረጃዎቹ ታዓማኒነት የላቸውም፡፡ እቃው ከመርከብ ላይ አልተጫነም ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው የቀረበውን ማስረጃ ታዓማኒነት በመመርመር እንጅ ለፍታብሔር ህግ ድንጋጌዎች የተዛባ ትርጉም በመስጠት አይደለም፡፡ ስለሆነም የሻጭ ግዴታ አስመልክቶ ለመዘርዘር እንደ መንደርደሪያ የፍታብሔር ድንግጌዎችን ይግባኝ ሰሚው ችሎት መጥቀሱ፤ የአንደኛ አመልካች ማስረጃዎች ተዓማኒነት የለውም እቃዎቹም አልተጫኑም ከሚለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ያቀረበው መሰረታዊ ምክንያት ባለመሆኑና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ከደረሰበት መደምደሚያና ውሣኔ ላይ የደረሰው በዋነኛነት የፍታብሔር ሕግ ድንጋጌዎችን በተርጐም ሣይሆን አንደኛ አመልካች እቃዎቹን በቻርተርፓርቲ የጫንኩ መሆኑን ያስረዱልኛል በማለት ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ተዓማኒነት በመመርመር በመሆኑ በዚህ በኩል አመልካቾች ያቀረቡትን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የባህር ሕግ አንቀጽ 181 እና አንቀጽ 187 ተፈፃሚነት የሚኖራቸው በመጀመሪያ አመልካች ያቀረበው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ትክክለኛና ታዓማኒነት ያለው ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ በአንደኛ አመልካች እቃውን በጫነችው “ኤም ቪ ማርዋ” በተባለችው መርከብ ካፕቴን ተፈርሞ የተሰጠኝ ነው በማለት አንደኛ አመልካች ያቀረበው የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ሐሰተኛ ፍሬ ጉዳዮችን የያዘ አመልካች ከፃፋቸው ሌሎች ሰነዶች ጋር የሚቃረን ተዓማኒነት የሌለው ሰነድ ነው የተባለ በመሆኑ ትክክለኛ ያልሆነ የእቃ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ በማቅረብ ሻጭ የባህር ህግ አንቀጽ 181 እና አንቀጽ 187 መሰረት የውል ግዴታውን ተወጥቷል ሊባል የማይችል በመሆኑ በዚህ በኩል ያቀረቡት ክርክርም ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም፡

5.ሁለተኛው አመልካች አንደኛ አመልካችና ተጠሪ ያደረጉት፣የሽያጭ ውል እሱ ያልፈረመበትና የማይመለከተው መሆኑን በመግለጽ በስርና በሰበር ባቀረበው ክርክር ተከራክሯል፡፡ ሁለተኛ አመልካች አንደኛ አመልካችና ተጠሪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 18 ቀን 1998 ዓ.ም ባደረጉት የሽያጭ ውሉ የአንደኛ አመልካች ወኪል ለመሆኑና እቃውን ተጠሪ እስኪረከብ እንደ አንደኛ አመልካች ሆኖ ኃላፊነቱን ለመወጣት በውሉ በአንቀጽ 16 የተስማማ ሲሆን፣ ውሉ ካልተፈፀመ ወይም ባአግባቡ ባለመፈፀሙ ለሚደርሰው ጉዳት አንደኛው አመልካች ጋር በአንድነትና በነጠላ ሐላፊ ለመሆን በአንቀጽ 17 በግልጽ የውል ግዴታ ገብቷል፡፡ ስለሆነም ሁለተኛ አመልካች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ በአንድነትና በነጠላ የመክፈል ሐላፊነት አለበት በማለት ይግባኝ ሰሚው  ችሎት የሰጠው ውሣኔ ተገቢና ምንም አይነት የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት ነው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ከተራ ቁጥር ከአንድ እስከ አምስት በዘረዘርናቸው ምክንያቶች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አንደኛ አመልካችና ሁለተኛ አመልካች ተጠሪ ላቀረበው ክስ በአንድነትና በነጠላ ሐላፊዎች ናቸው በማለት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የሌለበት በመሆኑ በፍታብሔር ሕግ ቁጥር 348/1/ መሰረት ሙሉ በሙሉ ሊፀና ይገባል በማለት በድምጽ ብልጫ ወሰነናል፡፡

ው ሣ ኔ

  1. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16175 ሐምሌ 29 ቀን 1997 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ሙሉ በሙሉ በድምጽ ብልጫ ጸንቷል፡፡ ይፃፍ፡፡
  2. አመልካቾች በአንድነትና በነጠላ ክስ የቀረበበትን ብር 2,593,970.30 /ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ብር ከሰላ ሣንቲም/ ክሱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ዘጠኝ ፐርሰንት(9%) ወለድ ጋር ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡
  3. አመልካቾች በአንድነትና በነጠላ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የወሰነውን ብር 43,184.56(አርባ ሶስት ሺ አንድ መቶ ሰማኒያ አራት ብር/ ከሐምሳ ስድስት ሳንቲም) የዳኝነት ገንዘብ ለተጠሪ ይክፈሉ ብለናል፡፡ ይፃፍ፡፡
  4. በትውስት የመጣው የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዘገብ ይመለስ
  5. በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ አመልካቾችና ተጠሪ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

ይህ ፍርድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት መጋቢት 17 ቀን 2001 ዓ.ም በጽምጽ ብልጫ ተሰጠ፡፡

የማይነበብ የሦስት ዳኞች ፊርማ አለበት

የልዩነት ሐሳብ

      ሰብሳቢው ዳኛና 2ኛው ዳኛ በዚህ ጉዳይ በአበላጫ ድምጽ ከተሰጠው ውሳኔ በሚከተለው አኳኋን በሐሳብ ተለይተናል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክርና እንደዚሁም ጉዳዩን በየደረጃው የተመለከቱት ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ከፍ ብሎ በአብላጫ ድምጽ በተሰጠው ውሳኔ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡

ተጠሪና 1ኛ አመልካች እ.ኤ.አ. መጋቢት 18 1998 ባደረጉት ውል የዋጋ ግምቱ 280 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሆነ 1 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአርማታ ብረት 1ኛ አመልካች ለተጠሪ ለመሸጥ እንደዚሁም 1ኛ አመልካች በውሉ ላይ የተመለከተውን ግዴተ ሳይወጣ ቢቀር 2ኛ አመልካች ከ1ኛ አመልካች ጋር በአንድነትና በነጠላ ሐላፊ እንደሚሆኑ በዚህ መልኩ ውሉ የተፈረመ ስለመሆኑ ከውሉ መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በዚህ ረግድ ግራ ቀኙ ክርክር የላቸውም፡፡

የስር ከሳሽ የአሁን ተጠሪ አጥበቆ የሚከራከረው ከ1ኛ ከአመልካች ጋር እ.ኤ.አ መጋቢት 18 ቀን 1998 ዓ.ም የሽያጭ ውሉ ከተፈረመ በኋላ የመርከብ ማስጫኛው ሰነደ መደበኛው መሆኑ ቀርቶ እቃው በተለየ መርከብ(ቻርተርፓርቲ) መላክ እንዲችል አስቀድሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የተከፈተውን ሌተር ኦፍ ክሬዲት አሻሽልልኝ በማለት 1ኛ አመልካች ጠይቆኝ አሰቀድሞ የተከፈተው ኤ.ል.ሲ.ተሻሽሉ የተላከለት ሲሆን በዚሁ መሰረት የቻርተርፓርቲ ውል ከባለመርከቡ ጋር ተዋውሎ ውለታውን ለገዢ ማስተላለፍ ሲገባው አላስተላለፈም፡፡ እቃውንም ኤም.ቪ.ማርዋ ኤም ከተባለ የመርከብ አዛዥ ወይም ባለንብረት ጋር እ.ኤ.አ ግንቦት 29 ቀን 1998 ዓ.ም የተዋዋል በማስመሰል ይህንኑ ሰነድ ለባንክ አቅርቦ የእቃውን ጠቅላላ ዋጋ ከነማስጫኛው ከወሰደ በኋላ እ.ኤ.አ ሰኔ 3 ቀን 1998 ዓ.ም እቃው ተጭኖባታል የተባለችው ኤም.ቪ.ማርዋ ኤም መርከብ የት እንዳለች አልታወቀም፡፡ ከሳሽ አጓዡን ለመጠየቅ እንዲያስችለው ቻርተርፓርቲ ኮንትራቱን 1ኛ ተከሳሽ  እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ቢጠይቅም መጨረሻ ላይ ከአጓዡ ጋር የተፈራረመው ቻርተርፓርቲ እንደሌለ በመግለጽ ለከሳሽ በቴሌክስ አሳውቋል፡፡

ስለሆነም 1ኛ ተከሳሽ በውሉ የገባውን ግዴታ ያልተወጣ ስለሆነና 2ኛ ተከሳሽም ለውሉ አፈፃፀም የአንድነትና የነጠላ ግዴታ የገባ ስለሆነ በክስ የተጠየቀውን ገንዘብ ባለተነጣጠለ ኃላፊነት እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ነው፡፡

ተከሳሾችም በበኩላቸው ለከሱ ምክንያት የሆነውን የአርማታ ብረት 1ኛ ተከሳሽ ኤም.ቪ.ማርዋ.ኤም በተሰኙት ቻርተር መርከብ የማስጫኛ ዋጋ በመክፈል አስጭኖ እቃው በትክክል ለመጫኑም የመርከብ አዛዡ ክሊን ኦን ቦርድ (clean on board) የሚል የፈረመበት የባህር ጭነት ማጓጓዣ ሰነድ (Bill of Lading) በመቀበል ለከሳሽ ያስተላለፉት መሆኑን ገለጸው ከባህር ሕግና በግራ ቀኙ መካከል ከተፈረመው ውል አንቀጽ 8 አኳያ 1ኛ ተከሳሽ ግዴታውን በሚገባ የተወጣ በመሆኑ ክሱ ከበቂ ኪሳራ ጋር ሊሰረዝ ይገባለል በማለት መከራከራቸውን መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ግራ ቀኙ እየተከራከሩ ያሉት በውሉ አፈፃፀም ረገድ ስለሆነ ውሉ ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለው የክርክሩ ጭብጥ የግራ ቀኙን ንግኙነት በተለይ ከሚገዛው የባህር ሕጉ፣ግራ ቀኙ ካቋቋሙት ውል ከዚህ ጋር ተያይዞም ተስማምተንበታል ካሉት የዓለም ንግድ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ንግድ ስነ ቃሎች(International chamber of commerce/ICC/ international commercial terms/incoterms/) አንፃር መታየት እንዳለበት እናመናለን፡፡

በዚህም መሰረት የግራ ቀኙን ግንኙነት በተለይ በሚገዛው የባህር ሕግ የጭንት ማስታወቂያ ደረሰኝ (Bill of lading)  የአመላላሹን ስምና አድራሻ፣የጫኙ ስምና አድራሻ የመርከቡ ስምና ዜግነቱ፣ ለእቃው መድረሻ የተመደበውን ስፍራ ወይም የጭነት ማስታወቂያው ደረሰኝ በሰው ስም ተጽፎ እንደሆነ የእቃ ተቀባዩን ስም፣አመላላሹ የተረከባቸውን የንግድ እቃዎች፣ዕቃው የተጫነበትን ስፍራና ቀን እንደዚሁም የጭነቱ ዋጋ ልክ መጠቀስ እንዳለበትና በጭነቱ ማስታወቂያ ደረሰኝ ላይ አመላላሹ ወይም እንደራሴው ቀኑን መጻፍና መፈረም እንዳለበት በአንቀጽ 182 ስር ተዘርዝሯል፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ክርክር ሲደረግ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኙን ግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች በአስረጂነት ያቀረቡት ሲሆን ከፍ ብሎ በተጠቀሰው የባህር ሕግ ቁጥር 182 ስር የተመለከቱትንም ዝርዝር ሁኔታዎች ሰነዱ የሚያሟላ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ተጠሪ ሰነዱ በንግድ ሕግ ቁጥር 182 መሰረት የተዘጋጀ መሆኑን ሳይክድ ነገር ግን በዚህ ሰነድ ዓማካይነት እቃው ተጭኖበታል የተባለችውን ኤም.ቪ.ማርዋ.ኤም የተባለችውን መርከብ ማግኘት ስላልቻልኩ ሰነዱ የተጭበረበረ ነው ብሏል፡፡

ይሁንና በባህር ሕግ ቁጥር 182 መሰረት የተዘጋጀ የጭነት ማስታወቂያ ደረሰኝ ተጠሪ መቀበሉ ከተረጋገጠ 1ኛ አመልካች በሕጉ የተጣለበትን ግዴታ እንደተወጣ ይቆጠራል፡፡

በዚህ ሰነድ ዓማካይነት ተጠሪ መርከቧን ማግኘት አለመቻሉና እቃውንም እንዳልተረከበ መገንዘብ ቢቻልም 1ኛ አመልካች እቃውን ለባለመርከቡ ማስረከቡ እስከተረጋገጠ ድረስ በጉዞ ላይ በእቃው ላይ ለሚደርስ ጉዳትም ሆነ መጥፋት ተጠሪ አስቀድሞ መላ ሊያበጅለት ይገባ ነበር፡፡ ይህንን ሳያደርግ ቀርቶ እቃውን ሳይረከብ መቅረቱ የተረከበው ሰነድ የተጭበረበረ ነው ወደሚል መደመደሚያ ሊያደርስ አይችልም፡፡

ተጠሪና 1ኛ አመልካች እ.ኤ.አ መጋቢት 18 ቀን 1998 ባደረጉት ውል አንቀጽ 8 ላይ 1ኛ አመልካች እቃው በመርከብ የተጫነ መሆኑን የሚያረጋግጥ ንጹሕ የተፈረመ የባህር ማጓጓዣ ሰነድ ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህንን ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ ተጠሪም ይህንኑ ሰነድ ስለመረከቡ ለ1ኛ አመልካች ማረጋገጫ(Receipt) በመላኩ 1ኛ አመልካች ይህንኑ ሰነድ ለባንክ በማቅረብ የእቃውን ዋጋ ከነማስጫኛው ወስዷል፡፡

ከዚህም በውሉ በገባው ግዴታ መሰረት በመርከቡ ካፒቴን የተፈረመ የባህር ማጓጓዣ ሰነድ (Clean on board charter party bill of lading) 1ኛ አመልካች ለተጠሪ ማስረከቡን መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በባህር ሕግ ቁጥር 187/3/ መሰረትም ለጫኙ የሚሰጠው ደረሰኝ አመላላሹ ወይም እንደራሴው ፈርሞበት ሕጋዊ ለሆነው የደረሰኙ ያዥ እቃውን የመረከብና በእቃውም የማዘዝ መብት እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡

ስለሆነም ተጠሪ ከ1ኛ አመልካች ማግኘት የሚገባውን ተገቢ ሰነድ ካገኘ በኋላ እቃውን ማግኘት ካልቻለ ከፍ ብሎ ከተጠሰቀሰው የባህር ሕግ ቁጥር 187/3/ አኳያ ጥያቄው መቅረብ ያለበት ለ1ኛ አመልካች ሳይሆን ለባለመርከቡ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ተጠሪ ጥያቄውን በ1ኛ አመልካች ላይ ማቅረቡ የውልም ሆነ የሕግ ድጋፍ ያለው አይደለም፡፡

በመጨረሻም 1ኛ አመልካችና ተጠሪ እ.ኤ.አ መጋቢት 8 ቀን 1998 የተፈራረሙት ውል የዓለም ንግድ ምክር ቤት /ICC/ በሚመራበትና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ድንጋጌዎች (Incoterms) መሰረት ውሉ ፍጻሜ እንደሚያገኝ ግራ ቀኙ ስለመስማማታቸው ተማምነውበታል፡፡

በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ውለታውን ያደረጉት ተጠሪ የእቃውን ዋጋ ማስጫኛውን ጨምሮ Cost and freight/C&F/ በሚል ቃል (Incoterm) ለመክፈል በመስማማት እንደተዋዋሉ ተገንዝበናል፡፡

ይህንኑ ግራ ቀኙ የተስማሙበትን የዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ድንግጌ እንደተመለከትነውም፡፡ C&F means ”Cost and right” The seller must pay the costs and freight necessary to bring the goods to the named destination but the risk of loss of or damage to the goods as well as any cost increase is transferred from the seller to the buyer when the goods pass the ships rail in port of shipment.

ይህ ወደ አማርኛ ሲተረጐምም “ሲ” እና “ኤፍ” ማለት ወጭና የማስጫኛ ዋጋ ማለት ነው፡፡ ሻጭ እቃውን ወደ ተጠቀሰው መዳረሻ  ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭና ማስጫኛ ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ ነገር ግን እቃው ወደብ ላይ እንደተጫነ በእቃው ላይ ለሚደረስ መጥፋትም ሆነ ጉዳት እንደዚሁም የወጭ መጨመር ኃላፊነት ወደ ገዢው ይዛወራል፡፡ የሚል ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት (ICC) ድንጋጌ መሰረት ዓለምአቀፍ ንግድ የሚከናወነው ይህንን ስርአት ተከትሎ እስከሆነ ድረስ ሻጭ የሸጠውን እቃ መርከብ ላይ ከጫነ ርክክብ እንደተፈጸመ እንደሚቆጠር ከዚህ በኋላም በንብረቱ ላይ ለሚደርስ ጉዳት፣መጥፋትም ሆነ የዋጋ መጨመር የአደጋ ኃላፊነቱ ወደ ገዢው እንዲተላለፍ የሚቆጠር ሲሆን በእኛም በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2397 ላይም በባህር ለማጓጓዝ መርከብ በማስረከብ ስራ የሚፈጸመው እቃውን ለአጓጓዥ መርከብ በማስረከብ ነው ተብሎ የተደነገገውም ይህንኑ የአለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት (ICC) ድንጋጌን የሚያጠናክር ነው፡፡

በመሆኑም 1ኛ አመልካች ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን የአርማታ ብረት ወደ ተጠቀሰው መዳረሻ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭና ማስጫኛ ዋጋ በአግባቡ ተከፍሎ እቃው ወደብ ላይ ስለመጫኑ የተረጋገጠ ስለሆነ ከዚህ በኋላ እቃው በመጥፋቱ ወይንም በሌላ ምክንያት ተጠሪ አልተረከበም ቢባልም የአደጋው ኃላፊነት ወደ እራሱ የተዛወረ ስለሆነ እቃው በጉዞ ላይ ቢጠፋ ወይም ጉዳት ቢደርስበት ይህንን ጉዳት ለማስቀረት ተጠሪ ውሉን ከ1ኛ አመልካች በተዋዋለ ጊዜ በ”C” & “F” ሁኔታ (term) መሆኑ ቀርቶ ኢንሹራንስንም በሚያካትት መልኩ በCIF/cost,insurance and freight/ በሚለው የዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የንግድ ስነ-ቃል/incoterm/ መሰረት ተዋውሎ ቢሆን ኖሮ 1ኛ አመልካች ከኢንሹራንስ ድርጅት ጋር የመዋዋል ግዴታ ስለሚኖርበት ጉዳቱን በመካስ ረገድ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ኃላፊነቱን ይወሰድ ነበር፡፡ ይህም ካለሆነ ተጠሪ በእራሱ በኩል ለንብረቱ የመድን ሽፋን ውል በመግባት ጉዳቱን ሊታደግ ሲችል ይህንን ዓይነት መላ ባላበጀበትና የጉዳት ኃላፊነቱም ወደ አራሱ በተዛወረበት ሁኔታ አመልካቾች በክስ የተጠየቀውን ገንዘብ ባልተነጣጠለ ሁኔታ ኃላፊነት ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት በክስ መጠየቁ ከዓለም አቀፍ ንግድ ም/ቤት (ICC) የዓለም አቀፍ ንግድ ስነ ቃሎች(incoterms) አኳያም ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረበው ክስ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የሕግም ሆነ የውል ድጋፍ የሌለው በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን የግራ ቀኙን ግንኙነት በተለይ ከሚገዛው ከባህር ሕጉ፣ከውላቸውና ከዓለም አቀፍ ንግድ ም/ቤት የዓለም አቀፍ ንግድ ስነ-ቃል አኳያ ተመልክቶ መወሰን ሲገባው በፍ/ብሔር ሕጉ ጠቅላላ ስለ ውሎች በሚለው ስር የውል አፈፃፀም ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ 1ኛ አመልካች በወሉ የተጣለበትን ግዴታ ያልተወጣ ስለሆነ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ አመልካቾች ለተጠሪ ሊከፍሉ ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ በእኛ እምነት መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ ይኼው ውሳኔ ተሽሮ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ሊጸና ይገባል በማለት በሐሳብ ተለይተናል፡፡

የማይነበብ የሁለት ዳኞች ፊርማ አለበት

ቤ/ኃ

2 replies »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.