Site icon Ethiopian Legal Brief

ክሪሚናሊስቲክስ (criminalistics) ምንድነው?

ከ6 ወራት በፊት በመኪና /ባጃጅ/ አደጋ የተነሳ በእግሬ ላይ መጠነኛ ጉዳት ከደረሰ ወዲህ ብሎጌን update አላደረግኩም፡፡ አሁን አገግሜያለው፡፡ ለጠየቃችሁኝ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረስ፡፡

ከ6 ወራት ቆይታ በኋላ በዚህ ብሎግ ከሚዳሰሱ ጉዳዮች ትንሽ ወጣ ባለ ርዕስ ላይ የውይይት በር ለመክፈት ሀሳብ አለኝ፡፡ ለውይይት የመረጥኩት ርዕስ ክሪሚናሊስቲክ ወይም ደግሞ ሁላችንም በምናውቀው ቃል ፎረንሲክ ሳይንስ ነው፡፡ የዛሬው ጽሑፍ አጠቃላይ ስለ ሳይንሱ እና ለፍትሕ ስርዓቱ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ መልካም ንባብ!

ክሪሚናሊስቲክስ (criminalistics) ምንድነው?

       ትርጓሜውና ይዘቱ

       የፎረንሲክ ሳይንስ መሰረታዊ ዕውቀት አስፈላጊነት

       ተሳስቶ ላለማሳሳት-የአስፈላጊነቱ ማሳያ

            የባሩድ ቅሪት በእጥበት ይለቃል?

            ወንጀል የተፈጸመበት የጦር መሳሪያ እንዴት ይታወቃል?

           የፖሊስ መግለጫ- ጉዳት አድራሹ ሽጉጥ ተለይቷል? 

ፋይዳው- ‘ከማዕከላዊ ወደ ላቦራቶሪ’

ፎረንሲክ ፓቶሎጂ /Forensic Pathology/

       ሞተናል የሚባለው መቼ ነው?      

ዋቢ መጻህፍትና ጽሑፎች

ክሪሚናሊስቲክስ (criminalistics) ምንድነው?

ትርጓሜውና ይዘቱ

እ.ኤ.አ. በ1248 ቻይና ውስጥ በሩዝ ማሳ ውስጥ ይሰሩ ከነበሩ ሰራተኞች መካከል አንደኛው በስሎት ተወግቶ ተገደለ፡፡ የገዳዩን ማንነት ለማወቅ ሁሉም የማሳው ሰራተኞች ለስራ የተሰጣቸውን ማጭድ እንዲያመጡ ተደርጎ በረድፍ ተደረደሩ፡፡ ከተደረደሩት መካከል አንደኛዋን ማጭድ ዝንቦች ወረሯት፡፡ በዚህን ጊዜ ገዳዩ ወዲያውኑ ተናዘዘ፡፡ ዝንቦቹ ያረፉት ደም የነካው ማጭድ ላይ ነበር፡፡ (Bertino, 2012) በዚሁ ዓመት እዛው ቻይና ውስጥ የህክምና ዕውቀትን ለህግ ጉዳዮች ተፈጻሚ የሚያደርግ የመጀመሪያው መጽሐፍ ተጻፈ፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ በቻይንኛ Xi Yuan Ji Lu በእንግሊዝኛ ትርጉሙ The Washing Away of Wrongs and Collected Cases of Injustice Rectified  በሚል የሚታወቅ ሲሆን ጸሐፊው ሰንግ ትዙ (Sung Tz’u) ይባላል፡፡ ‘የማጭዱ ገዳይ’ ታሪክ በመጽሐፉ ውስጥ ከተዘገቡት ፎረንሲክ ጠቀስ ታሪኮች መካከል አንደኛው ነው፡፡ (Siegel & Mirakovits, 2010) ይህ መጽሐፍ በፎረንሲክ ሳይንስ ዕድገት ውስጥ የመጀመሪያው የተሟላ የፎረንሲክ ሳይንስ ማኑዋል /manual/ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ (Stefoff, 2011)

ክሪሚናሊስቲክስ የፎረንሲክ ሳይንስን ለወንጀል ጉዳዮች ተፈጻሚ የሚያደርግ ሳይንስ ነው፡፡ ቃሉ አንዳንዴ ከcriminology ጋር ይምታታል፡፡ ይሁን እንጂ criminology ወንጀል እና የወንጀል ባህርያትን የሚያጠና ማህበራዊ ሳይንስ እንደመሆኑ ሁለቱ ለየቅል ናቸው፡፡ (Fisher, Tilstone, & Woytowicz, 2009)

ለመሆኑ ፎረንሲክ ሳይንስ ምንድነው? ፎረንሲክ የሚለውን ቃል ብዙዎቻችን ሰምተነው እናውቃለን፡፡ ትክክለኛ ትርጓሜውን በተመለከተ ግን በብዙዎቻችን መረዳት ያለ አይመስልም፡፡ ለአንዳንዶች ፎረንሲክ ሳይንስ ሲባል የረቀቀና ጥቂት በሙያው የተካኑ ፖሊሶች ብቻ የሚረዱትና የሚጠቀሙበት ፖሊሳዊ ሳይንስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፎረንሲክ ሳይንቲስት ለመሆን ፖሊስ ወይም መርማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ እንዲያውም ሳይንሱ በእግሩ እንዲቆም ያደረጉት የዘርፉ ፈር-ቀዳጆች አብዛኛዎቹ በፖሊስነት ሞያ ውስጥ አላለፉም፡፡

ፎረንሲክ ሳይንስ በአጭር አነጋገር ሳይንሳዊ ዘዴ በመጠቀም ከህግ አፈጻጸም የሚነጩ ጉዳዮችን ወይም ችግሮችን የሚፈታ ሳይንስ ማለት ነው፡፡ ሰፋ ባለ ትርጓሜው ለፍትሕ ስርዓት አገልግሎት የሚውል ማንኛውም ሳይንስ ሁሉ የፎረንሲክ ሳይንስ ነው፡፡ (Houck & Siegel, 2015) ከተፈጻሚነት አድማሱ አንጻር ሳይንሱ ለወንጀል ብቻ ሳይሆን ለፍትሐብሔር ጉዳዮችም ተግባር ላይ ይውላል፡፡ ሆኖም ሳይንሱ በጣም ጎልቶ የሚታየው ከወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ካየነው በክሪሚናሊስቲክስ እና ፎረንሲክ ሳይንስ መካከል የረባ ልዩነት የለም፡፡ እንዲያውም ለአንዳንዶች ሁለቱም ተመሳሳይ ስያሜዎች ናቸው፡፡ (Stefoff, 2011)

‘fornesic’ የሚለው ቃል የመጣው forum ከሚል የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉም ህዝባዊ ወይም የህዝብ ማለት ነው፡፡ በጥንታዊ ሮማ ሴኔቱ በፎረም /ህዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ/ እየተገናኘ በፖለቲካና በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ክርክር /debate/ ያካሂድ ነበር፡፡ አሁን ድረስ በተለይ በአሜሪካ በህዝባዊ ክርክር /debate/ የሚወዳደሩ ተከራካሪ ቡድኖች /teams/ “forensics.” እየተባሉ ነው የሚጠሩት፡፡ (Houck,, 2007)

በነገራችን ላይ የመጀመሪያው የፎረንሲክ የሬሳ ምርመራ የተካሄደው እዛው ሮማ ውስጥ ነው፡፡ ጁሊየስ ቄሳር በጠላቶቹ 23 ጊዜ ተወግቶ ሲገደል አንቲሺየስ የተባለ ሐኪም የሬ ምርመራ ካደረገ በኋላ ቄሳርን ለሞት ያበቃችው የትኛዋ እንደሆነች ለመለየት ችሏል፡፡ (Evans, 2004) በፈረሲክ ሳይንስ ስር የሚታቀፉ ዘርፎች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋና የሚባሉት እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፡፡

የፎረንሲክ ሳይንስ መሰረታዊ ዕውቀት አስፈላጊነት

የፎረንሲክ ሳይንስ መሰረታዊ ዕውቀት በተለይ በፍትሕ ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ዓቃቤ ህጎች፣ ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች በፀጥታ ማስከበር ስራ ውስጥ የተሰማሩ ባለሞያዎች መሰረታዊ የፎረንሲክ ሳይንስ ግንዛቤ ሊጨብጡ ግድ ይላቸዋል፡፡ በተለይ ፖሊስ ዘርፈ ብዙ ሳይንቲስቶችን ያቀፈ ዘመናዊ የፎረንሲክ ላቦራቶር ከሌለው ‘ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ’ የሚጠቀመው ማስረጃ አሁን ላይ በተግባር እያየን እንዳለነው እውነተኛና ሐሰተኛ ምስክሮች እንዲሁም በጥፊ በጡጫ የሚሰጥ የእምነት ቃል ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የፍትሕ ስርዓቱን ጥላሸት ከቀቡት ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ዳኞች መሰረታዊ የፎረንሲክ ሳይንስ ዕውቀት ከሌላቸው የባለሞያ ማስረጃ አግባብነትና ተዓማኒነት የሚመዝኑበት መለኪያ አይኖራቸውም፡፡ ወይ በጭፍን ይቀበሉታል፤ አሊያም በጭፍን ይጥሉታል፡፡ ለፎረንሲክ ሳይንስ አዲስ የሆነ ጠበቃ እንዲሁ የፎረንሲክ ማስረጃን እጅ ነስቶ ከመቀበል ውጭ በመስቀለኛ ጥያቄ ለማስተባበል አይዳዳውም፡፡ የጣት አሻራ finegerprint/፣ የዲ.ኤን.ኤ /DNA typing/፣ የሰነድ ምርመራ፣ /forensic document examination/ የሬሳ ምርመራ /Autopsy/ እና ሌላ ዓይነት በፎረንሲክ ምርመራ የተደረሰበት ግኝት በማስረጃነት ሲቀርብ ይብዛም ይነስም ባለሞያው  የሚሞገትበት መስቀለኛ ጥያቄ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም አንዳንዱ ሳይንስ የጋራ ባህርያት /class/ እንጂ ነጠላ ባህርያት /individualization/ መለየት ያቅተዋል፡፡ እንበልና በወንጀል ስፍራ የሸበተ ከርዳዳ ፀጉር ተገኘ፡፡ ከዚያም ከተጠርጣሪው ላይ የፀጉር ናሙና ተወስዶ የፎረንሲክ የፀጉር ምርመራ ሲደረግ ተጠርጣሪውም የሸበተ ከርዳዳ ፀጉር እንዳለው ተረጋገጠ፡፡ ይህ የምርመራ ውጤት በወንጀል ስፍራ የተገኘው ፀጉር የተጠርጣሪው እንደሆነ አያሳይም፡፡ ምክንያቱም እጅግ በርካታ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ፀጉር አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ተዳብሎ ሲቀርብ ጠንካራ አካባቢያዊ ማስረጃ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ሊጋራው የሚችል ባህርያትን የሚወስን የፎረንሲክ ማስረጃ /ተጨማሪ ምሳሌ ለመስጠት ያክል የደም ምርመራ (serology)፣ የፋይበር (fiber) ምርመራ/ በተዓማኒነቱና በሳይንሳዊ የምርመራና ትንተና ዘዴው ላይ ብዙ መስቀለኛ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ከወንጀል ስፍራ የተገኘው የማስረጃ ምንጭ ከአንድ ግለሰብ ጋር ብቻ በሚያዛምዱና ጠቅለል ባለ አነጋገር መስቀለኛ ሆነ ሌላ ጥያቄ ለማንሳት ክፍተት በማይተዉ ዘርፎች /ለምሳሌ የጣት አሻራ finegerprint/ እና የዲ.ኤን.ኤ /DNA typing/ ምርመራዎች እንዲሁ በተገኘው አጋጣሚ ማስረጃውን ለመሞገት ጥቂትም ቢሆን ስለ አሻራ እና ዲ.ኤን.ኤ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የወንጀል ስፍራ በአግባቡ ካልተጠበቀ፣ ካልተዘገበ /crime scene documentation/ ብሎም ካልተሰበሰበ በፎረንሲክ የሚመረመረው ማስረጃ ጥራት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለምርመራ በቂ ናሙና በሌለበት ምርመራ ተካሂዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ምርመራው የተካሄደበት መንገድ እና የባለሞያው የሞያና ዕውቀት ደረጃ በመስቀለኛ ጥያቄ ሊፈተኑ ይገባል፡፡

ተሳስቶ ላለማሳሳት-የአስፈላጊነቱ ማሳያ

የታላቁ ግድብ ታላቁ ሰው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞትን ተከትሎ ሰሞነኛ መላምቶች፣ ግምቶችና አስተያየቶች ፌስቡክን ወረውት ነበር፡፡ የፖሊስ ሪፖርት ይፋ ከመደረጉ በፊት ማን ገደላቸው? ለሚለው ጥያቄ ወንጀሉን ማን ሊፈጽመው እንደሚችል ሁሉም በየፊናው መላምት አቅርቧል፡፡ ከሪፖርቱ በኋላ ደግሞ ራሳቸውን አጠፉ? ወይስ ተገደሉ? የሚለው ጥያቄ ትልቅ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ ማስረጃ በአግባቡ ተሰብስቦ በተሟላ መልኩ የፎረንሲክ ምርመራ በብቁ ባለሞያ ሳይካሄድ ስለ አሟሟት ሆነ ስለ ገዳይ ማንነት የተረጋገጠ ነገር ማውራት አይሞከርም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ላይ ከተለያየ አቅጣጫ አስተያየትና ትችት መሰንዘር ትክክለኛና ገንቢ ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም በሪፖርቱ ላይ በግልጽ ከሚታዩ ግዙፍ ጉድለቶችና አደናጋሪ ብሎም እርስ በእርስ ከሚጣረሱ ገለጻዎች ገሚሱ ያክል እንኳ የመወያያ ርዕስ አልሆኑም፡፡

በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ፎረንሲክ ጠቀስ አስተያየቶች በማህበራዊ ሚዲያ ቀርበዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ትክክል እና አስተማሪ ናቸው፡፡ በግሌ ካነበብኳቸው ውስጥ ሁለት ነጥቦች ነጋሪት ጋዜጣ ላይ እንዳለው ዓይነት ‘ማረሚያ’ ያስፈልጋቸዋል፡፡

የባሩድ ቅሪት በእጥበት ይለቃል?

የመተኮስ ሂደትን ተከትሎ አብዛኛውን ጊዜ የባሩድ ቅሪት (Gun Shot Residue) በተኳሹ እጅ እና በከፊልም ልብስ ላይ ይገኛል፡፡ በወንጀል ምርመራ ሂደት የዚህ ቅሪቱ የማስረጃ ፋይዳ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅሪቱ የተገኘበት ሰው ወንጀሉ የተፈጸመበትን መሳሪያ ይዞት እንደነበር ያረጋግጣል፡፡ ቅሪት የበርካታ Organic እና Inorganic ኬሚካላዊ ውህዶች ድምር ውጤት ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛዎቹ በአካባቢያችን ስለሚገኙ ምንጫቸው የጦር መሳሪያ ተኩስ ላይሆን ይችላል፡፡ አብዛኛዎቹ ኬሚካላዊ ቅሪቶች ከአካባቢያችን ጋር ባለን ንክኪ የተነሳ እጃችን ላይ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የፎረንሲክ ሳይንቲስቶች ከአካባቢያዊ ንክኪ የማይተላለፉና የጦር መሳሪያ ተኩስ ውጤት የሆኑትን ሶስቱን ብቻ ለይተዋል፡፡ እነዚህም፤

ስለሆነም በፎረንሲክ ሳይንስ የባሩድ ቅሪት (Gun Shot Residue) የሚለው አገላለጽ እነዚህን ሶስት ኬሚካላዊ ቅሪቶች እንደሚያመለክት ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡

የባሩድ ቀሪትን አስመልከቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በቀረበ አስተያየት መሰረት ቅሪቱ ያለበት እጅ ቢታጠብ ወይም በአልኮል ቢፀዳ ቅሪቱ አይጠፋም፡፡ እውነታው ግን ፍጹም የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የዘርፉ ባለሞያ የሚሉትን እስቲ እንመልከት፤

GSR [Gun Shot Residue] evidence can be lost or destroyed if evidence connected to the incident is not properly preserved. The simple act of washing one’s hands or clothing may remove important GSR evidence. (Kling, 2009)

የባሩድ ቅሪት ድራሹ እንዲጠፋ አልኮና እጥበት አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ ቅሪት የነካውን እጅ ኪስ ውስጥ በመክተት እንዲሁም በላብ ይለቃል፡፡ ከዚያም አልፎ በንክኪ ይተላለፋል፡፡ የቆይታ ጊዜውም በጣም አጭር ነው፡፡

ሌላው መረሳት የሌለበት መሰረታዊ ነጥብ የባሩድ ቅሪት መኖሩ በእይታ አይረጋገጥም፡፡ ማስረጃዎቹን መሰብሰብ እንዲሁም የባሩድ ቅሪት መሆናቸውን በቤተ ሙከራ ለማረጋገጥ ጥልቅ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ቅሪት መኖሩን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ሙከራዎች /tests/ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ አካባቢ ሰፊ ተቀባይነት አግኝተው ይሰራባቸው የነበሩ የሙከራ ዘዴዎች ሶስት ናቸው፡፡ እነሱም፤

FAAS እና SEM-EDX አሁንም ድረስ ተመራጭ ሆነው እየተሰራባቸው ሲሆን neutron activation ግን ከሶስቱ የቅሪት ዓይነቶች መካከል ሊድ / lead/ በደንብ መለየት ባለመቻሉና ሙከራውን ለማካሄድ ደግሞ የኒክሌር ማብለያ / nuclear reactor/ ስለሚያስፈልግ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ አንጻር እ.አ.አ ከ1990 ወዲህ ቀርቷል፡፡ (Schwoeble & Exline, 2000)

ወንጀል የተፈጸመበት የጦር መሳሪያ እንዴት ይታወቃል?

በጦር መሳሪያ አማካይነት ወንጀል ሲፈጸም የባለስቲክ ኤክሰፐርት ከሚያከናውናቸው በርካታ የፎረንሲክ ምርመራዎች መካከል ወንጀሉ የተፈጸመበትን መሳሪያ መለየት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ እንዴት ይታወቃል? ለሚለው ጥያቄ ጥይቱን እንዲሁም ቀለሀውን ከመሳሪያው ጋር በማዛመድ ማወቅ እንደሚቻል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምላሽ የቀረበ ሲሆን ተመሳሳይ ሀሳብ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሟሟትን አስመልከቶ በተሰጠው ፖሊሳዊ መግለጫ ላይ ቀርቧል፡፡

በጠብመንጃ /rifle/ ወይም በሽጉጥ /handgun/ የመተኮስ ተገባር ሲፈጸም ጠብመንጃውና ሽጉጡ በጥይቱና በቀለሀው ላይ የራሱን ልዩ አሻራ /ምልክት/ ያሳርፋል፡፡ እነዚህን ምልክቶች በመጠቀም የሚደረግ ምርመራ እንደሁኔታው ሁለት ዓይነት ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡

የጦር መሳሪያው በወንጀሉ ስፍራ ካልተገኝ

በወንጀሉ ስፍራ ላይ ወንጀል የተፈጸመበት መሳሪያ ካልተገኘ የባለስቲክ ኤክስፐርቶች በጥይትና ቀለሀ ላይ ያረፉትን ምልክቶችና ጭረቶች በመጠቀም ወንጀል የተፈጸመበትን መሳሪያ ዓይነት ከነሞዴሉ ጭምር ይለያሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሚደረግ ምርመራ የጋራ ባህርይ /class/ የሚጋሩ የጦር መሳሪያ ዓይነቶችን ከመለየት በላይ ሊዘልቅ አይችልም፡፡ ጥይቱ የተተኮሰበት የጦር መሳሪያ ጠብመንጃ ወይም ሽጉጥ? ለሚለው ጥያቄ የቀለሀ እና የጥይት ምርመራው ውጤት ሽጉጥ መሆኑን ካሳየ ሽጉጥ ሁሉም በአንድ እጅ የሚተኩሱ በዓለማችን ላይ የሚገኙ ሽጉጦች ሁሉ የሚጋሩትና የሚታወቁበት የመደብ ስያሜ ነው፡፡ በቀጣይ ምን ዓይነት ሽጉጥ? ሪቮልቨር /revolver/ ወይስ ፒስትል /pistol/? ፒስትል ከሆነ ሙሉ ወይስ ከፊል አውቶማቲክ? እያለ እያለ ካሊበሩ፤ ሞዴሉ፤ አምራቹ…እና ሌሎች በርካታ መለያ ባህርያትን በመጠቀም በተቻለ መጠን ጥቂት ሽጉጦች በጋራ በሚታወቁበት መደብ ውስጥ ላይ ይደረሳል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በወንጀሉ ስፍራ የተገኘው ጥይትና ቀለሀ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሽጉጦች መካከል በየትኛው አማካይነት ወንጀሉ እንደተፈጸመ በላያቸው ላይ ያለው ምልክት አያሳይም፡፡

የጦር መሳሪያው በወንጀሉ ስፍራ ከተገኘ

እስካሁን ስናወራ የነበረው በወንጀሉ ስፍራ ጥይት እና/ወይም ቀለሀ ተገኝቶ የተተኮሰበት መሳሪያ ግን በማይገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ሶስቱም በወንጀሉ ቦታ የተገኙ እንደሆነ ግን ሟች ጉዳት የደረሰበት በወንጀሉ ስፍራ በተገኘው መሳሪያ አማካይነት መሆኑ የሚታወቀው በጥይቱና ቀለሀው ላይ ያለውን ምልክት ከመሳሪያው ጋር በማስተያያት አይደለም፡፡ ንጽጽሩ የሚካሄደው በመሳሪያው አማካይነት ለሙከራ በመተኮስ በወንጀል ስፍራ የተገኘውን ጥይት እና ቀለሀ በሙከራ ተኩስ ከሚገኘው ጥይትና ቀለሀ ጋር በንጽጽር ማይክሮስኮፕ በማስተያየት ነው፡፡

የንጽጽሩ ውጤት ተመሳሳይ ምልክቶችን ካሳየ በወንጀሉ ስፍራ የተገኘው የጦር መሳሪያ ወንጀሉ የተፈጸመበት መሳሪያ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ከላይ የተገለጹትን ሀሳቦች ሪቻርድ ሳፍረስቴን Criminalistics: An Introduction to Forensic Science በሚለው መጽሐፉ እንደሚከተለው ያጠቃልላቸዋል፡፡

The inner surface of the barrel of a gun leaves its markings on a bullet passing through it. These markings are peculiar to each gun. Hence, if one bullet found at the scene of a crime and another test-fired from a suspect’s gun show the same markings, the suspect is linked to the crime. (Saferstein, 2015)

የፖሊስ መግለጫ- ጉዳት አድራሹ ሽጉጥ ተለይቷል?

ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በመኪናቸው ውስጥ በተገኘውና የእርሳቸው በሆነው ሽጉጥ በተተኮሰ ጥይት ህይታቸው እንዳለፈ በፎረንሲክ ምርመራ መረጋገጡን ፖሊስ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው? መግለጫውን ልብ ብላችሁ ስታዳምጡት ይህ የተረጋገጠበት መንገድ በመኪና ውስጥ የተገኘውን ጥይት እና ቀለሀ እዛው መኪና ውስጥ ከተገኘው ሽጉጥ ጋር በማዛመድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማዛመድ ግን ኢንጅነሩ በመኪና ውስጥ በተገኘው ሽጉጥ በተተኮሰ ጥይት መሞታቸውን የማረጋገጥ ብቃት የለውም፡፡ ከላይ ግልጽ ለማድረግ እንደተሞከረው በዚህ መልኩ የሚከናወን የባለስቲክ ምርመራ ጉዳት አድራሹ የጦር መሳሪያ በወንጀሉ ስፍራ ሳይገኝ ሆኖም ግን ጥይት እና/ወይም ቀለሀው በስፍራው ከተገኘ ከጥይቱ እና ቀለሀው በመነሳት የጦር መሳሪያውን ዓይነት የሚታወቅበት ዘዴ ነው፡፡ ጥይት እና ጥይት እና/ወይም ቀለሀ እና ቀለሀ ሳይነጻጸር ወንጀል የተፈጸመበትን የጦር መሳሪያ ማወቅ አይቻልም፡፡ የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ሪቻርድ ሳፍረስቴን በዚህ ነጥብ ያሰፈረውን ሀሳብ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡

Because there is no practical way of making a direct comparison between the markings on the fired bullet and those found within a barrel, the examiner must obtain test bullets fired through the suspect barrel for comparison. (Saferstein, 2015)

ስለሆነም ፖሊስ የሙከራ ተኩስ ሳያደርግ /በነገራችን የሙከራ ተኩስ /test fire/ በራሱ ዕውቀት የሚጠይቅ ከመሆኑም ለዚህ ተግባር የተዘጋጀ መሳሪያ ሊኖር ይገባል፡፡/ አረጋግጫለው ቢልም መግለጫው እንዳላረጋገጠ ማረጋገጫ ነው፡፡ ጥይትና ቀለሀ ከሽጉጡ ጋር በማዛመድ ሟች በዛው ሽጉጥ በተተኮሰ ጥይት መሞቱን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

ፋይዳው- ‘ከማዕከላዊ ወደ ላቦራቶሪ’

በፎረንሲክ ሳይንስ ወደ ኋላ በቀረ እንደ እኛ ባለ አገር ውስጥ ፖሊስ ወንጀለኞችን በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚጠቀምበት ዘዴ ኋላ ቀር ብቻ ሳይሆን በከፊል ከወንጀል የጸዳ አይሆንም፡፡ ሳይንሳዊ ያልሆነ የወንጀል ምርመራ ከምስክሮች ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃ አይደገፍም፡፡ ሆኖም ምስክር እና ወንጀል ሁልጊዜ አብረው አይገኙም፡፡ በዚህ ጊዜ ዛቻ፣ ማስፈራራት፣ ድብደባ በመጠቀም ተጠርጣሪው እንዲያምን ማስገደድ አማራጭ ፖሊሳዊ የምርመራ ታክቲክ ይሆናል፡፡

እስከ 19ነኛው ክፍለዘመን ድረስ አሁን ላይ የስልጣኔ ጫፍ በደረሰው በምዕራቡ ዓለም ሳይቀር በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን ለይቶ ለማወቅ ከምስክሮች ከሚሰበሰብ ማስረጃ እና ተጠርጣሪውን በማሰቃየት ከሚገኝ የእምነት ቃል በስተቀር ተዓማኒነት ያለው ሳይንሳዊ መንገድ የሚከተል የምርመራ ዘዴ አልነበረም፡፡ ‘እውነቱን አውጣ!’ እያሉ ተጠርጣሪን ማሰቃየት የአንዲትን አገር የፍትሕ እና የወንጀል ስርዓት ያቀጭጨዋል እንጂ አያጎለብተውም፡፡ (Ramsland, 2007) በአንድ በኩል ያለጥፋታቸው የሚቀጡ ንጹሀን ስለሚኖሩ ኢ-ፍትሐዊነት ይነግሳል፡፡ በሌላ በኩል እውተኛው የወንጀል ፈጻሚ ስለማይደረስበት ወንጀል ይስፋፋል፡፡ የዚህ ችግር ስፋትና ጥልቀት በሳይንሳዊ ዕውቀት የታገዘ የወንጀል ምርመራ ስርዓት አስፈላጊነት በጊዜ ሂደት ዕውቅና እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህንን ሐቅ በፎረንሲክ ሳይንስ ዕድገት ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረገውና ከፖሊስነት ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ በመሸጋገር የእንግሊዙን የዜና ማሰራጫ ቢቢሲ (BBC) በመቀላቀል በስራው ዝናን ያተረፈው ኒገል ማክሬሪ (Nigel McCrery) Silent Witnesses: The Often Gruesome but Always Fascinating History of Forensic Science በሚለው መጽሐፉ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡

[I]t wasn’t until the nineteenth century that the need for a reliable, systematized method of identifying the people involved in a crime was recognized. Prior to then, the most common ways of doing so were eyewitness accounts and information extracted by torture. (McCrery, 2014)

በአውሮፓ እስከ 19ነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀው ችግር በ21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ በአገራችን በገሀድ ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ወንጀል እንዳይፈጸም የመከላከል ግቡን ለማሳካት ሁለት ስልቶችን ዘርግቷል፡፡ አንደኛው ስለወንጀሎችና ቅጣታቸው በቅድሚያ ለህብረተሰቡ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሲሆን ማስጠንቀቂያ ያልገተቸው ወንጀል አድራጊዎችን መቅጣት ደግኖ ሁለተኛው ነው፡፡ በወንጀል አድራጊዎችና በንጽሀን ዜጎች መካከል ያለው መለያ ክር ማስረጃ ነው፡፡ ማስረጃው ደግሞ ከበቂ ጥርጣሬ በላይ የሚያረጋግጥና ተዓማኒነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡

በአገራችን የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ሲካሄድ የፍትሕ ስርዓቱን ችግሮች በማጥናት የዳሰሳ ሪፖርት ያቀረቡ አማካሪዎች ጥናቱ በተጠናበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ በግኝታቸው ላይ በአጽንኦት እንደዘገቡት በወንጀል ጉዳዮች በአብዛኛው ለፍርድ ቤት የሚቀርበው ማስረጃ የሰዎች ምስክርነት ነው፡፡ በእርግጥ ችግሩን አለሳልሰው ‘በአብዛኛው’ አሉት እንጂ ‘ሁሉም’ የሚለውን ቃል ቢጠቀሙ ስህተት አይሆንባቸውም ነበር፡፡

አማካሪዎቹ በአገሪቱ በፎረንሲክ ሳይንስ ዘርፍ ያለውን ችግር እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡

Ethiopia has one Federal Forensic Laboratory. Only one or two experts are working at this laboratory. They have been covering the various areas of the needed forensic expertise. The infrastructure of the laboratory is limited and backward. (Center for International Legal Cooperation , 2005)

የሪፖርቱ ዕድሜ አሁን ላይ ከአስራ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ምን ለውጥ መጣ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ የችግሩን መግዘፍ እንጂ መቀረፍ አይጠቁምም፡፡ በምስክሮች ላይ የተንጠለጠለ የፍትሕ ስርዓት መሰረታዊ ችግር በሪፖረቱ ላይ ከተመለከተው በላይ ሌሎች አሉታዊ ጎኖች አሉት፡፡ እስቲ አስቡት! ምንም ዓይነት ቀላል ሆነ ውስብስብ ወንጀል ቢፈጸም ዓቃቤ ህግ ምስክር አጥቶ አያውቅም፡፡ ወንጀል ካለ ምስክር አለ! ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ እንኳስ ታዛቢ፤ ከሳሽና መርማሪ የፍትሕ አካላት ሳይቀር በልባቸው ይረዱታል፡፡ ስለሆነም ሀቁን እናውራ ከተባለ በወንጀል ጉዳይ የሚቀርቡ ምስክሮች ስለጉዳዩ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያውቁ ብቻ ሳይሆኑ ‘በምስክርነት ኢንስቲትዩት’ የአጭር ጊዜ ስልጠና ተሰጥቷቸው ስለጉዳዩ ያወቁ ጭምር ናቸው፡፡

ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በፎረንሲክ ሳይንስ ኋላ በቀረ የወንጀል ፍትሕ ስርዓት ወንጀለኞችን ከንፁሐን ለመለየት ከምስክሮች በተጨማሪ በውድ ይሁን በግድ ከተጠርጣሪው የእምነት ቃል መቀበል አይቀሬ አማራጭ ይሆናል፡፡ የዚህ አማራጭ ውጤቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ህገ-መንግስታዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ ዜጎች ባልሰሩት ጥፋት እንዲያምኑ ይንገላታሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይሰቃያሉ፡፡ የስልጣን አለአግባብ መገልገል ይሰፍናል፡፡ ቀስ በቀስ በስልጣን መባለጉ ከግላዊ አልፎ ተቋማዊ መልክ መያዝ ይጀምራል፡፡ ስለሆነም የፎረንሲክ ሳይንስ ፋይዳ ከማስረጃ ብቃት እና ተዓማኒነት ባለፈ ሰብዓዊ እና ህገ-መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻርም ልንቃኘው ይገባል፡፡

‘ህግ በመጣስ ህግ ማስከበር!’ የወንጀል ህጉን ግብ አያሳካም፡፡ የማዕከላዊ እስር ቤትን መዘጋት ሁላችንም ሰበር ዜናውን ሰምተናል፡፡ በእርግጥ ተዘጋ የሚባለው ግን ቤቱ ሲዘጋ ሳይሆን በውስጡ ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የወንጀል ምርመራ ስልቱ ‘ከማዕከላዊ እስር ቤት’ ወደ ‘ፎረንሲክ ላቦራቶሪ ምርምር ቤት’ ሊሸጋገር ይገባዋል፡፡

ፎረንሲክ ፓቶሎጂ /Forensic Pathology/

ፓቶሎጂ ስለ በሽታዎች የሚያጠናና ሳይንስ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ፎረንሲክ ፓቶሎጂ ማለት በሬሳ ምርምራ አማካይነት የሞት መንስዔና የአሟሟት ሁኔታ የሚወስን የፎረንሲክ ዘርፍ ነው፡፡ አውቶፕሲ (Autopsy) ቃሉ የመጣው ከግሪክ ሲሆን auto ራስ እና opsy ደግሞ መመልከት ማለት ነው፡፡ ስናገጣጥመው ራስን መመልከት (to look at one’s self) የሚል ትርጓሜ ይሰጠናል፡፡ ከሟች ጋር ካዛመድነው ትርጓሜው ትክክለኛ መልዕክት አያስተላልፍም፡፡ የተሻለ ገላጭ ቃል የሚሆነው ኔክሮስኮፒ “necropsy” (necro በግሪክ ሞት opsy መመልከት) ነው፡፡ (Eckert & Wright, 1997) የፎረንሲክ ፓቶሊጂስቱ ከሞት ይጀምራል፡፡ በዚህ የፎረንሲክ ሳይንስ ከሚዳሰሱ በርካታ ጉዳዮች መካከል የሞትን ትርጓሜ እንመለከታለን፡፡

ሞተናል የሚባለው መቼ ነው?

ስቴዝስኮፕ (stethoscope) ከመፈልሰፉ በፊት በ17ኛው ክፍለ-ዘመን አካባቢ ሰዎች የልብ ምታቸው ሲደክም ወይም ኮማ ውስጥ ሲገቡ ሞተዋል በሚል ግምት ይቀበሩ ነበር፡፡ ኮማ ውስጥ የገባ ሰው ሞቷል ተብሎ ከተቀበረ በኋላ አንድ ቀን በሬሳ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ሲነቃ፤ በጨለማ ውስጥ መውጫ አጥቶ ሲንፈራገጥ፤ ባለችው አቅሙ ሳጥኑን ደብድቦ ምላሽ ሲያጣ፤ በመጨረሻም የሚደርስለት ጠፍቶ በረሀብ እና በውሀ ጥም በቀስታ እስከወዲያኛው ‘እንደገና ሲሞት’…በቁም ላለ ሰው ሀሳቡ እንዴት እንደሚያስፈራ አስቡት፡፡ ከዚህ ፍርሀት ለመገላገል የ17ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አንድ መላ ዘየዱ፤ ሬሳ ሳጥን ውስጥ ደወል ማንጠልጥል፡፡ በስህተት ሳይሞት የተቀበረ ሰው ድንገት ከነቃ አጠገቡ ያለውን ደወል ይደውላል፡፡ ማን ይሰማዋል? ካላችሁ ለዚህ ሲባል የመቃብር ቦታዎች ‘ሬሳ ጠባቂዎች’ ነበሯቸው ፡፡ (Bertino, 2012)

ለመሆኑ በህይወት የመቀበር አጋጣሚ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር እንደማይችል እርግጠኛ መሆን እንችላለን? የጤና ሽፋን በሌለበት አካባቢ ሰዎች ከነህይወታቸው እንደማይቀበሩ እርግጠኛ መሆን ይከብዳል፡፡ በከተማም ቢሆን ቆም ብሎ ያሰበው የለም እንጂ የእኛ አገር ሀኪም እና ህክምና አያስተማምንም፡፡ በሐኪሞች ስህተት የሚሞተው ሰው ቁጥር ሲታይ በስህተት ሞትን የሚያውጅ ሐኪም አይጠፋም፡፡

ለመሆኑ አንድ ሰው በእርግጠኝነት ሞቷል የሚባለው መቼ ነው? ነብሱ ስትወጣ? ልክ ነው፤ አንድ ሰው ነብሱ ከወጣች ሞቷል ማለት ነው፡፡ ነብሱ ከወጣች በህይወት የለም፡፡ በህይወት ከሌለ ነብሱ ወጥታለች፡፡ ሆኖም የነብስ መውጣት ወይም በህይወት አለመኖር የሞት አቻ መገለጫዎች እንጂ ማረጋገጫዎች አይደሉም፡፡ አንቶኒ ጄ. በርቲኖ እንደሚነግረን ሰውነቱ እንደ በረዶ የሚቀዘቅዝ አሊያም ራሱን የሳተ ሰው (comatose) በእርግጥም ሞቷል ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ምልክቶች በህይወት ያለ ሰው ላይም ይታያሉ፡፡ (Bertino, 2012)

It is…some-times difficult to tell if a person is dead or not. The outward signs of death, such as being cold to the touch and comatose, can be present even though a person is still alive.

የህክምና ባለሞያዎች በሞት ትክክለኛ ትርጓሜ ላይ ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ በብዙዎች ተቀባይነት ባገኘው ትርጓሜ መሰረት ሞት ማለት “ወደ ኋላ የማይመለስ የደም ዝውውር መቋረጥ” (“irreversible cessation of circulation of blood.”) ነው፡፡ ይህም ማለት ልብ መምታቱን ያቆማል፡፡ ከማቆም አልፎ እንደገና መምታት አይጀምርም፡፡ አንጎል እንቅስቃሴውን ሲያቆም እንዲሁ የሞት ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም ይህኛው ሀሳብ ሁሉንም ባለሞያዎች እኩል አያስማማም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ልቡ እየመታች አንጎሉ ስራውን ቢያቆም ሞቷል ማለት ነው? (Bertino, 2012)

የትርጓሜ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰው በእርግጠኝነት ሞቷል የሚባልበትን ቅጽበት በትክክል ማመልከት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ሞት ሂደት እንጂ ልክ እንደ አምፖል መብራትና መጥፋት  በተወሰነች ቅጽበት የሚከሰት ሁኔታ (event) አይደለም፡፡ ፎረንሲክ ፓቶሎጂሰቶች በሞት ትርጓሜ ላይ የሚፈጠረውን አተካራ ለማስወገድ ሞትን በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚያስፈልግ ያሰምሩበታል፡፡ የመጀመሪያው የአንዲት ነጠላ ሴል መሞት (cellular death) ሲሆን ሁለተኛው somatic death የሚባለው የሰውነት ተግባራት መቆም ነው፡፡ cellular death በአንድ በኩል የእስትንፋስ (respiration) መቆም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መደበኛው የቲሹዎችና ሴሎች ሜታቦሊክ እንቀስቃሴ መቆም (cessation of the normal metabolic activity in the body tissues and cells) ነው፡፡ በዚህ ሂደት ለሰውነታችን የሚደርሰው የኦክስጅን አቅርቦት ይቋረጣል፡፡ ከዛም ቀስ በቀስ ሴሎች መፈረካከስ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሂደት autolysis ተብሎ ይጠራል፡፡ በቀጣይ ሰውነት መበስበስ ይጀምራል፡፡ ከዚህ በኋላ በህይወት የመኖር አጋጣሚ አይኖርም፡፡ somatic death ሲኖር ግለሰቡ እስከወዲያኛው (irreversibly) ራሱንና አካባቢውን አያውቅም፡፡ መለኪያው ሂደቱ ወደ ኋላ የማይመለስ (irreversible) መሆኑ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ላይመለስ የማይነቃው ሰው መተንፈስ ካላቆመ እንዲሁም ልቡ መምታቷን ከቀጠለች ሞቷል ብሎ መፈረጅ አስቸጋሪ ነው፡፡ (Shepherd, 2003)

ከላይ የተገለፀው ሀሳብ ከኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሟሟት ጋር በተያያዘ   በርካታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ እና በሌሎች የክሪሚናሊስቲክ ወጎች ቀጣይ ጽሑፍ በሚቀጥለው ሳምንት ይቀርባል፡፡

ዋቢ መጻህፍትና ጽሑፎች

Bertino, A. J. (2012). Forensic Science: Fundamentals and Investigations. Cengage Learning.

Bevel, T., & Gardner, R. M. (2008). Bloodstain Pattern Analysis with an Introduction to Crime Scene Reconstruction (3rd ed.). CRC Press Taylor & Francis Group.

Center for International Legal Cooperation . (2005). Comprehensive Justice System Reform Program: BASELINE STUDY REPORT. Ministry of Capacity Building, Justice System Reform Program Office. Ministry of Capacity Building.

Eckert, W. G., & Wright, R. K. (1997). Forensic Pathology. In W. G. Eckert (Ed.), Introduction to Forensic Sciences. CRC Press.

Embar-Seddon, A., & Pass, A. D. (Eds.). (2009). Forensic science (Vols. 1-3). Salem Press, Inc.

Evans, C. (2004). Murder two : the second casebook of forensic detection. John Wiley & Sons, Inc.

Evans, C. (2007). The casebook of forensic detection : how science solved 100 of the world’s most baffling crimes. Penguin Group (USA) Inc. .

Fisher, B. A., Tilstone, W. J., & Woytowicz, C. (2009). Introduction to Criminalistics: The Foundation of Forensic Science . Elsevier Inc.

Houck, M. M. (2007). FORENSIC SCIENCE: Modern Methods of Solving Crime. Praeger Publishers.

Houck, M. M., & Siegel, J. A. (2015). Fundamentals of Forensic Science (3rd ed.). Academic Press.

Jackson, G. (2009). Understanding forensic science opinions. In J. Fraser, & R. Williams (Eds.), Handbook of Forensic Science. Willan Publishing.

Jamieson, A., & oenssens, A. M. (Eds.). (2009). Wiley encyclopedia of forensic science (Vols. Volume 1 A-B). John Wiley & S ons L t d.

Kiely, T. F. (2001). Forensic evidence : science and the criminal law. CRC Press.

Kling, A. A. (2009). Ballistics . Gale, Cengage Learning .

Maio, V. J. (1999). Gunshot Wounds: Practical Aspects of Firearms, Ballistics, and Forensic Techniques (2nd ed.). CRC Press.

McCrery, N. (2014). silent witnesses: The Often Gruesome but Always Fascinating History of Forensic Science. Chicago Review Press Incorporated.

Newton, M. (2008). THE ENCYCLOPEDIA OF CRIME SCENE INVESTIGATION. Facts On File, Inc.

Ramsland, K. (2007). BEATING THE DEVIL’S GAME: A History of Forensic Science AND Criminal Investigation. Penguin Group.

Rose, P. (2002 ). Forensic Speaker Identification. Taylor & Francis.

Rothschild, M. A. (2011). Wound ballistics and forensic medicine. In B. P. Kneubuehl (Ed.), Wound Ballistics: Basics and Applications (S. Rawcliffe, Trans.). Springer.

Saferstein, R. (2015). Criminalistics: An Introduction to Forensic Science (11th ed.). Pearson Education Limited.

Schwoeble, A. J., & Exline, D. L. (2000). Current methods in forensic gunshot residue analysis. CRC Press LLC.

Shepherd, R. (2003). Simpson’s Forensic Medicine (12 ed.). Arnold.

Siegel, J., & Mirakovits, K. (2010). FORENSIC SCIENCE: the basics (2nd ed.). CRC Press.

Stefoff, R. (2011). Criminal profiling . Marshall Cavendish Benchmark.

Tilstone, W. J., Savage, K. A., & Clark, L. A. (2006). FORENSIC SCIENCE: An Encyclopedia of History, Methods, and Techniques. ABC-CLIO.

Waggoner, K. (Ed.). (2007). Handbook of Forensic Services. FBI Laboratory Publication.

Yount, L. (2007). FORENSIC SCIENCE: From Fibers to Fingerprints. Chelsea House.

Exit mobile version