Draft Laws

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣ /ረቂቅ/ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር —–/2011

አስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋየወጣ አዋጅ

የፌዴራል ስርዓቱን በማጠናከር እየተገነባ የመጣውን የብሔር ብሔረሰብ እና ህዝብ ብዝሃነት ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙርያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮችን አገራዊ በሆነና በማያዳግም መንገድ መፍታት በማስፈለጉ፣

ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውዝግቦች በተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሃል የቅራኔ ምንጭ መሆናቸውን በመገንዘብ፣

ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ለሆነ አለመረጋጋት መንስዔ በመሆናቸው፣ ለነዚህ ችግሮች ገለልተኛ በሆነ፣ ከፍተኛ ሞያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ማፈላለግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

 1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ‹‹ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅቁጥር ——–/2ዐ11›› ተብሎሊጠቀስይችላል፡፡

 1. ትርጓሜ

1/     “የአስተዳደር ወሰን” ማለት ራስን በራስ ማስተዳደር ፣ ከማንነት ጥያቄ እና ከሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር በተያይዘ የሚነሱ የወሰን ጉዳዮች ነው

2/     “ኮሚሽን” ማለት በዚህ አዋጅ አንቀፅ 3(1) መሰረት የተቋቋመ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጥያቄ ጉዳዮች ኮሚሽን ነው፡፡

 1. መቋቋም

1/    የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን (ከዚህ በኋላ ‘ኮሚሽን’ እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

2/    ኮሚሽኑ የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደር  እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፣ ጽህፈት ቤት እና   አስፈላጊ ሰራተኞች፣ ይኖሩታል፡፡

3/    የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡

 1. የኮሚሽኑ ዓላማ

ኮሚሽኑ አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደር  እና ከማንነት ጋር የተያይዙ ግጭቶችንና መንስኤያቸውን በመተንተን የመፍትሄ ሃሳቦችን ለህዝብ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  እና ለአስፈጻሚው አካል  ማቅረብ ነው።

 1. የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር

ኮሚሽኑ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1/    ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲሁም ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችንና ግጭቶችን በጥናት ለይቶ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት  ሪፖርት ያቀርባል፤

2/    በህዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሰረት አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ማሻሻያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሃሳቦችን ያቀርባል፤

3/    አስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወሰኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ በተመለከት አግባብነት ያላቸውን ህገ-መንግስታዊ መርህዎች ያገናዘበ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ስርዓትወይም የህግ ማሻሻያ እንዲዘረጋ ጥናት በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፤

4/    ጎልተው የወጡና በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴራል መንግስት የሚመሩለትን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦችን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ  እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፤

5/    ከአስተዳደራዊ ወሰኖች ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶች ተፈተው፣ በአጎራባች ክልሎች መሃከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚታደስበትና የሚጠናከርበትን መንገድ ያመቻቻል፤

6/    በቀጣይነት አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ለፌዴሬሽን ምክር ቤትእና ለሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፤

7/    አስተዳደራዊ ወሰኖችና አካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው የልማትና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሂድባቸው እንዲሆኑ አስተዳደራዊ ወሰኖችን የተመለከተ የፖሊሲ ማእቀፍ ያመነጫል፤

8/    የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮችን በተመለከት የህዝብ አስተያየት ይሰበስባል፤

9/    ጉዳዮ ከሚመልከታቸው የክልልና የፌደራል የስራ ሃላፊዎች፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ እንዲሁም ሌሎች ባላድርሻ አካላት አሰትያየትና ለጥናቱ የሚሆን ግብዐት ይሰብስባል፤

10/   ከህዝብ ግብዐትና አስተያየት የሚሰበሰብበትን አካሄድ የሚያሳይ፣ ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ መሆኑን የሚያረጋገጥ ስትራትጂና ዝርዝር እቅድ ያዘጋጃል።

 1. የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች

ማንኛውም የአስተዳደር ወሰን ውሳኔ፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በኮሚሽኑ ተጠንቶ አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ እልባት ያገኛል፡፡

 1. ኮሚሽን አባላት አሰያየም

1/    የኮሚሽኑ አባላት ቁጥር በመንግስት የሚወሰን ይሆናል፡፡

2/    በኮሚሽኑ አባል ተደርገው የሚሰየሙ ግለሰቦች በስነ ምግባራቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በስራ ልምዳቸው በማህበረሰቡ የተመሰገኑና መልካም ስም ያተረፉ ይሆናሉ፡፡

3/    የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ሌሎች አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማሉ።

 1. ኮሚሽኑ ስብሰባ

1/    የኮሚሽኑ መደበኛ ስብሰባ በየአስራ አምስት ቀኑ ይካሄዳል፣ ሆኖም እንደየ አስፈላጊነቱ በማናቸውም ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ ሊደረግ ይችላል፡፡

2/    ከኮሚሽኑ አባላት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከተገኙ ምልዓተ-ጉባኤ ይሆናል፡፡

3/    የኮሚሽኑ ምክረሃ ሳቦች በስምምነት ያልፋሉ፡፡

4/    የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ኮሚሽኑ የራሱን የስብሰባሥነ-ሥርዓት ደንብ ሊያወጣይችላል፡፡

 1. የሰብሳቢ ስልጣንና ተግባር

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፡-

1/    አጠቃላይ የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፤

2/    ለኮሚሽኑ አስፈላጊ የሆኑ የድጋፍ ሰጭ ሠራተኞችንይመድባል፤

3/    ኮሚሽኑን በመወከል ከሌሎች አካላት ጋር ግንኙነት ያደርጋል፡፡

 1. የምክትል ሰብሳቢ ስልጣንና ተግባር

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ፡-

1/    ሰብሳቢው በማይኖርበት ጊዜ ሰብሳቢዉን ተክቶ ይሰራል

2/    በሰብሳቢው የሚሰጡትንተግባራትይፈጽማል፡፡

 1. የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት

1/የኮሚሽኑ ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፍ ሊኖረው ይችላል፡፡

2/    የኮሚሽኑ ጽ/ቤት በመንግስት የሚመደብ የጽ/ቤት ሃላፊ ይኖረዋል፡፡

 1. የጽህፈት ቤትስልጣንናተግባር

የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤቱ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

1/    ለኮሚሽኑ አጠቃላይ የአስተዳደርና ፋይናንስ አገልግሎት ይሰጣል፤

2/    ለኮሚሽኑ የምርምርና ጥናት አገልግሎት ይሰጣል፤

3/    ለኮሚሽኑ የህዝብ ተሳትፎና ምክክር መድረኮችን የሎጅስቲክስ ድጋፍ ይሰጣል፤

4/    የኮሚሽኑን ቃለ ጉባኤዎችን፣ ውሳኔዎችንና ሰነዶችን አጠናቅሮ ይይዛል፤

5/    የኮሚሽኑን ስራ ለማሳለጥ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል።

 1. የጽህፈት ቤት ሃላፊ

1/    የጽ/ቤቱን ሰራተኞች እናሃ ብትያስተዳድራል፡፡

2/    ለኮሚሽኑ አባላት የሚሰጡትን የሴክሪታሪያል እና ሎጅስቲክ ድጋፎች በበላይነት ይመራል፡፡

3/    የኮሚሽኑ እቅድና በጀት ያዘጋጀል በኮሚሽኑ ሲጸድቅም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

4/    ጽ/ቤቱን በመወከል ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ግንኙነት ያደርጋል፡፡

 1. የኮሚሽኑ ገለልተኝነት

ኮሚሽኑ ስራውን በነፃነትና በገለልተኝነት ያከናውናል።

 1. የኮሚሽኑየሥራ ዘመን

1/    የኮሚሽኑ አባላት የስራ ዘመን እስከ እስከ 3 ዓመት ነው።

2/    በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ(1) የተጠቀሰው ቢኖርም የኮሚሽኑ የስራ ዘመንን እንደ ሁኔታው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊያራዝመው ይችላል።

 1. የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው ኮሚሽኑ በዚህ አዋጅ የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚያቀርበው ማንኛውም ህጋዊ እንቅስቃሴ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

 1. ጠቋሚዎችና ምስክሮችን ስለመጠበቅ

1/    ማንኛዉም ሰው በኮሚሽኑ ፊትቀርቦ በሚሰጠው ቃል መሰረት ክስ ሊመሰረትበት እንደዚሁም የሰጠው ቃል በእርሱ ላይ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብበት አይችልም፡፡

2/    ለጠቋሚዎችና ለምስክሮች ጥበቃ ለማድረግ የወጣ ሕግ ለኮሚሽኑ ቃላቸው እና መረጃ ለሚሰጡሰዎችም ተግባራዊ ይሆናል፡፡

 1. በጀት

የኮሚሽኑ በጀት በመንግስት ይመደባል፡፡

 1. ስለሂሳብ መዛግብት

1/    የኮሚሽኑ ጽ/ቤት የተሟላና ትክክለኛ የሆኑ የሂሳብ መዛግብት ይይዛል፡፡

2/    የኮሚሽኑ የሂሳብ መዛግብት እና ገንዘብ ነክ ሰነዶች በዋናው ኦዲተር ወይም ዋናው ኦዲተር በሚሰይማቸው ኦዲተሮች በየዓመቱ ይመረመራሉ፡፡

 1. ደንብና መመሪያ የማውጣትሥልጣን

1/    የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

2/    ኮሚሽኑ ይህንን አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የወጡ ደንቦችን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

 1. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የጸናይሆናል።

አዲስ አበባ፤  ….. ቀን 2011 ዓ.ም.

ሳህለወርቅ ዘውዴ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት

 

3 replies »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.