Draft Laws

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ  ረቂቅ አዋጅ

 

ጥቅምት 2010ዓ.ም

 

አዋጅ ቁጥር ——-/——

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐቭሊክ ህገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና የመንግስት ባለስልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በመመልከቱ፣

የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ያላቸው ቁርኝት ከመብታቸው ጋር በተሳሰረ ሁኔታ የሚኖራቸው የወሳኝነት ሥልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱና አስፈጻሚ አካላት ተግባራቸዉን ተፈጻሚ ህገ-መንግስታዊ ወሰንን ያላለፈ መሆኑን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፣

የአስተዳደር በደል እንዳይፈጸም አስቀድሞ በመከላከል ወይም ተፈጽሞ ሲገኝ በአፋጣኝ እንዲታረም በማድረግ በሀገራችን የመልካም የአስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ስኬታማ የሚሆነው ተቋማዊ  የአሠራር ነጻነቱ የተረጋገጠ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሲኖር መሆኑን በመረዳት፣

በአስፈጻሚ አካላት የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደሎች ወይም የሕግ ጥሰቶች እንዲታረሙ በተቋሙ የሚሰጥ የመፍትሔ ሐሳብ ለማስፈጸም መሰናክል የነበረን ክፍተት በማስወገድ በምርመራ እና ቁጥጥር ሥራዎቻችን ያዳበርናቸውን አዎንታዊና ገንቢ ልምዶች የመጠበቅንና ይበልጥ የማጠናከርን አስፈላጊነት በማመን፣

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንገስት አንቀጽ ፶፭(፩) እና (፲፭) መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ፤ ጠቅላላ

፩. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ  አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅቁጥር —/—”  ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ

፩. “ምክር ቤት” ማለት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሚክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማለት ነው፡፡

፪. “ተሿሚ” ማለትበምክር ቤት የሚሾም ዋና ዕንባ ጠባቂን፣ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ፣የሴቶች፣የህፃናትና የአካል ጉዳተኞች ዕንባ ጠባቂ እና የቅርንጫፍ ዕንባ ጠባቂ ነው፡፡

፫.  “ተቋም” ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማለት ነው፡፡

፬.  “የአስተዳደር በደል” ማለት ስልጣን ባለዉ አካል የወጣ እና በስራ ላይ ያለን ሕግን  በመፃረር በመንግስት አስፈፃሚ አካላት ወይም በመንግስት የልማት ድርጅቶች  የሚፈፀሙ ድርጊት ወይም የሚሰጥ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ማለት ሲሆን የተሰጠን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ አለመመፈጸምንይጨምራል፡፡

፭.  “ሕግ” ማለት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት፣የክልል መንግስታት ህገ መንግስት እና በፌደራል ወይም በክልል መንግስታት የሚወጡ ህጎች ማለት ነው፡፡

፮.  “መንግስት” ማለት የፌደራል ወይም የክልል መንግስት ነው፡፡

፯. “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ ፵፯(፩) ላይ የተመለከቱት ማለት ሲሆን ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የድሬደዋ አስተዳደርን ይጨምራል፤

፰. “የመንግስት መስሪያ ቤት” ማለት ሚኒስቴር፣ኮሚሽን፣ባለስልጣን፣ኤጀንሲ፣ኢንስቲቱት ወይም ማናቸውም ሌላ የመንግስት መስሪያ ቤት ነው፤

፱. “የመንግስት የልማት ድርጅት” ማለት በመንግስት ባለቤትነት ስር የሚገኝ የማምረቻ፣የማከፋፈያ፣አገልግሎት ሰጭ ወይም ሌላ አይነት ድርጅት ነው፤

፲. “አስፈፃሚ አካል” ማለት የመንግስት መስሪያ ቤትን  ወይም የመንግስት የልማት ድርጅትን እንዲሁም በዳኝነት ሰጭ ወይም በህግ አውጪው አካል ውስጥ የአስተዳደር ወይም የአስተዳደር ነክ አገልግሎት የሚሰጥ አካልን ይጨምራል፤

፲፩. “ባለስልጣን” ማለት የሕዝብ ተመራጭ ወይም የመንግስት አስፈጻሚ አካል ተሿሚ ወይም ኃላፊ ነው፤

፲፪. “ሠራተኛ” ማለት የተቋሙዳይሬክተሮችን፣የዋና ዕንባ ጠባቂ ጽ/ቤት ኃላፊን፣ ቡድን መሪዎች፣ ባለሙያዎችንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ይጨምራል ፤

፲፫. “መርማሪ” ማለት የምርመራ ስራ እንዲያካሂድ በዋና ዕንባ ጠባቂው ወይም በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ደረጃ ደግሞ በቅርንጫፍ ዕንባ ጠባቂው የተመደበ ሰራተኛ ነው፤

፲፬. “ስልታዊ ምርመራ” ማለት በመንግስት የአስተዳደር መዋቅር ላይ የተከሰቱ የአስተዳደር ችግሮችን የሚመለከቱ ሲሆን በባህሪያቸዉ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጉዳት ሊያከትል በሚችል ጉዳዮች ላይ የሚካሄድ ምርመራ ማለት ነዉ፡፡

፲፭. “ቤተ ዘመድ” ማለት በክልል የቤተሰብ ህግ ወይም በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ መሰረት የስጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው ሰው ነው፣

፲፮. “ሶስተኛ ወገን” ማለት አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን የሚወክል የሕዝብ ተመራጭ ወይም ማህበር ወይም “የመብት ተሟጋች” ድርጅት ማለት ነዉ፡፡

፲፯ “ሰው” ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤

፫.ስለ ፆታ አገላለፅ

በዚህ አዋጅ በወንድ ፆታ የተደነገገው ለሴት ፆታም ያገለግላል፡፡

.የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎችና ባለስልጣኖች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

ክፍል ሁለት

ስለኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

፭. እንደገና መቋቋም

፩.  የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም (ከዚህ በኋላ “ተቋሙ” እየተባለ የሚጠራ) በኢትዩጰያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ ፶፭(፩) እና (፲፭) በተደነገገው መሠረት የሕግ ሰውነት ያለው ሆኖ ራሱን ችሎ በዚህ አዋጅ እንደገና ተቋቁሟል፡

፪. የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ሆኖ ጉባዔዉ በሚወስነው በማናቸውም ቦታ ቅርንጫፍጽ/ቤት ሊከፍት ይችላል፡፡

፮. ዓላማ

የተቋሙ ዓላማ በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈፃሚው አካላትመከበራቸውን በማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ይሆናል፡፡

፯. ስለ ተቋሙ ሥልጣንና ተግባር

ተቋሙ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ ሆኖ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

፩. አስፈፃሚ አካላት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና  አሠራሮቻቸው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዲሁምሌሎች ህጎችን የማይቃረኑ መሆናቸውን የመቆጣጠር፤

፪.  የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ ወይም በራስ ተነሳሽነት ወይም በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ስልታዊ ምርመራ  የማካሂድ፤

፫. አስተዳደራዊ በደል መፈፀሙን ሲያረጋግጥ ተገቢዉን የመፍትሄ ሃሳብ የማቅረብ፤

፬. አስፈፃሚው አካል ሥራውን በህግ መሰረት የሚያከናውን መሆኑን ለማረጋገጥና አስተዳደራዊ በደሎች እንዳይፈፀሙ ለመከላከል ቁጥጥር የማድረግ፤

፭. አስተዳደራዊ በደሎች የሚቀረፉበትን ሁኔታ የማጥናትና ምክረ ሀሳብ የማቅረብ፤

፮.  የተሻለ የመንግስት አስተዳደርን ለማስገኘት ነባር ሕጎች ወይም አሰራሮች ወይም መመሪያዎች እንዲሻሻሉ፣አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ወይም ፖሊሲዎች እንዲቀየሱ የማሳሰብ፤

፯.  በመልካም የመንግስት አስተዳደር ጉዳዩች ላይ ለመንግስት የምክር አገልግሎት የመስጠት፤

፰. ሕብረተሰቡ ስለመልካም አስተዳደር እና ስለ አስተዳደራዊ ፍትህ ግንዛቤ እንዲኖረው የተለየዩዘዴዎችን በመጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር፤

፱.  በዓለም አቀፍ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በሚመለከት ስብሰባዎች ኮንፍረንሶች ሲምፖዚየም ላይ መሳተፍ፣

፲. ዓላማዉን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን የማከናወን

፰. የሥልጣን ገደብ

ተቋሙ የሚከተሉትን ጉዳዩች የመመርመር ሥልጣን የለዉም ፡-

፩. በሕዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በሕግ አውጭነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎችን፤

፪. በፍርድ ቤቶች ወይም በህግ የመዳኘት ስልጣን በተሰጣቸው አካላት በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዩች

ወይም የታዩና ውሳኔ የተሰጠባቸውጉዳዩችን ፤

፫.በፌደራል ዋና ኦዲተር ወይም በክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በመታየት ላይ ያሉ እና የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙጉዳዮችን፤ወይም

፬.  በመከላከያ ሠራዊትና በፖሊስ ክፍሎች የሚሰጡ የፀጥታ ወይም የሀገር መከላከል ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎችን ፡፡

ክፍል ሶስት

የተቋሙ አቋምና ሥልጣንና ተግባር

፱. የተቋሙ አቋም

ተቋሙ፡-

፩.  የዕንባ ጠባቂጉባኤ ፤

፪.  አንድ ዋና ዕንባ ጠባቂ፤

፫.አንድ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ፤

፬. አንድ የሴቶች ፣የሕጻናት እና አካል ጉዳኞች ዕንባ ጠባቂ ፤

፭. የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዕንባ ጠባቂ እና

፮. ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞች ይሆናል፡፡

፲.የጉባዔ አባላት                       

፩.  የተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎች ጉባዔ (ከዚህ በኋላ “ጉባዔ” እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ እንደገና ተቋቁሟል፣

፪.  ጉባዔው የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል፡-

ሀ/ ዋና ዕንባ ጠባቂ …………………………………………ሰብሳቢ

ለ/  ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ..…………………………… ምክትል ሰብሳቢ

ሐ/ የሴቶች፣ ህጻናት እና አካልጉዳተኞች ዕንባ ጠባቂ………….. አባል

መ/ የቅርንጫፍ ዕንባ ጠባቂዎች………………………………….. አባል

፫.  ጉባዔው የራሱን ፀሐፊ ከአባላቱ መካከል ይመርጣል፣

፬.  ጉባዔው የራሱን የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡

፲፩.የጉባዔው ሥልጣንና ተግባር

ጉባዔው ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሥልጣንና ተግባርይኖሩታል፡-

፩. ይህን አዋጅ ሥራ ላይ  ለማዋል መመሪያዎችን እና የውስጥ ደንቦችን የማፅደቅ፣

፪.  በተቋሙ ረቂቅ በጀት ላይ የመምከር፣

፫.  የመንግስት ሠራተኞች ሕግ ቢኖርም ጉባኤዉ ፡-

ሀ. ለተቋሙ ስራ አመቺ የሆነ አደረጃጀትና መዋቅር አጥንቶ በስራ ላይ ያዉላል

ለ. ለተቋሙ ሠራተኞች ልዩ የደመወዝና ስኬል ስርዓት አጥንቶ ለምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ተግባራዊነቱን ይከታተላል፣

ሐ. የተቋሙ ሠራተኞች የሚተዳደሩበትን የአስተዳደር መመሪያ ያወጣል፣

መ. ለተቋሙ ሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም ክፍያ አስመልክቶ ዉሳኔ ይሰጣል፡፡

፬. የተቋሙን ዳይሬክተሮች የመመደብ፤

፭.የዳይሬክተሮችን የዲሲፕሊን ጉዳይመርምሮ ዉሳኔ መስጠት፣

፮. የሚቀርቡለትን የሰራተኛ አስተዳደር ጉዳዮች ወይም አቤቱታዎች መርምሮ ውሳኔ የመስጠት፡

፲፪. የዋና ዕንባ ጠባቂው ሥልጣንና ተግባር

፩.  ዋናው ዕንባ ጠባቂ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ ሆኖ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ በመሆን በዚህ አዋጅ ለተቋሙ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር በሥራ ላይ ያውላል፡፡

፪.   የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው ዕንባ ጠባቂ፤

ሀ/ የተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎች ጉባዔ በሚያጸድቀው መመሪያ መሠረት ሠራተኞችን ይቀጥራል ፣ ያስተዳድራል፤

ለ/ በተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎች ጉባኤ የተመከረበት ረቂቅ በጀት አዘጋጅቶ በቀጥታ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ሥራ ላይ ያውላል፤

ሐ/  በቂ ምክንያት ሲኖረው አንድ ጉዳይ ከአንድ የምርመራ ክፍል ወይም መርማሪ ወደ ሌላ የምርመራ ክፍል ወይም መርማሪ ያዛውራል፤ወይም በራሱ ይመረምራል፤

መ/  ተደጋጋሚ የአስተዳደር በደሎችን አጥንቶ ከመፍትሔ ሀሳብ ጋር ለምክር ቤቱ ያቀርባል፤

ሠ/አስተዳደራዊ ጉዳዩችን የሚመለከቱ ረቂቅ ህጎችን አዘጋጅቶያቀርባል፤በሌሎች አካላት በተዘጋጁ ላይ አስተያየት ይሰጣል፤

ረ/ አስተዳደራዊ በደሎችንና የተቋሙን የስራ አካሂድ አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፤

ሰ/  ተቋሙን በመወከል በስብሰባዎች ይካፈላል፣ከፌደራሉና ከክልል መንግስታት አካላት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የስራ ግንኙነት ያደርጋል፤

ሸ/ ቅርንጫፍ  ጽ/ቤቶችንያደራጃል፣  ያስተባብራል፣   ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤

ቀ/ በምክር ቤቱ የሚሠጡትን ሌሎች ተግባራት የማከናወን፣

፫.  ለተቋሙ የቀረበ አቤቱታ በአቤቱታ አቅራቢ ላይ የማይመለስ ወይም የማይተካ ጉዳት ያደርሳል ብሎ ዋና ዕንባ ጠባቂ ካመነ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዕግድ ትዕዛዝ የመስጠት፤

፬. በዚህ አንቀጽ በንዑስ  አንቀጽ ፪ ፊደል ተራ (ለ፣ሠ፣ረ) እና በአንቀፅ ፵፪ ከተጠቀሱት በስተቀር ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ዋና ዕንባ ጠባቂው ለተቋሙ የሥራ ቅልጥፍና ባስፈለገ መጠን ሥልጣንና ተግባሩን በከፊል ለዕንባ ጠባቂዎች ወይም ለሌሎች ኃላፊዎች ወይም ሌሎች ሰራተኞች በውክልና ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

፲፫. የምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ ሥልጣንና ተግባር

፩. ተጠሪነቱ ለዋና ዕንባ ጠበቂ ሆኖየተቋሙን ተግባራት በማቀድ፣ በማደራጀት፣ በመምራት እና በማስተባበር ዋና ዕንባ ጠባቂውን የመርደት፣

፪. ዋና ዕንባ ጠባቂው በማይኖርበት ጊዜ ለዋና ዕንባ ጠባቂው የተሰጡትን ስራዎች የማከናወን፣

፫. በዋና ዕንባ ጠባቂው የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት የማከናወን፣

፲፬.የሴቶች፣የሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች ዕንባ ጠባቂ ሥልጣንና ተግባር

፩. ተጠሪነቱ ለዋና ዕንባ ጠበቂ ሆኖሴቶችን፣ ሕፃናትን እና አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ተግባራትን በማቀድ፣በማደራጀት፣ በመምራት እና በማስተባበር ዋና ዕንባ ጠባቂውን የመርዳት፣

፪. በዋናው ዕንባ ጠባቂዉ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራትየማከናወን፡፡

፲፭.የቅርንጫፍ  ዕንባ ጠባቂ ሥልጣንና ተግባር

ዕንባ ጠባቂው ተጠሪነቱ ለዋና ዕንባ ጠበቂ ሆኖየቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ የበላይ ኃላፊ በመሆን በዚህ አዋጅ በአንቀፅ ፭ (፪) በተቋቋመበት ስፍራ ውስጥ ለተቋሙ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በስራ ላይ ከማዋል በተጨማሪ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባሮች ይኖሩታል፡-

፩. የመንግስት አስተዳደር ሕጎች እና ሌሎች ሕጎች ደንቦችና መመሪያዎች መከበራቸውን የማረጋገጥ፣

፪. በቂ ምክንያት ሲኖረው አንድ የአስተዳደር ጉዳይ ከአንድ የምርመራ ክፍል ወይም ከአንድ መርማሪ ወደ ሌላ የማዛወር ወይም እራሱ ምርመራ የማካሄድ ፤

፫. አስተዳደራዊ በደሎችን በተመለከተ ለዋና ዕንባ ጠባቂ ዝርዝር ሪፖርት የማቅረብ፤እንዲሁም በተቋቋመበት ስፍራ ለሚገኝ ክልል ምክር ቤት በጽሁፍ የማሳወቅ፤

፬. ከመልካም አስተዳደር መርህ ጋር የማይጣጣሙ ህጎችና የአሰራር ልምዶች እንዲሻሻሉ ሐሳብ የማቅረብ፤

፭. በተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎች ጉባዔ በሚወጣዉ መመሪያ መሰረት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን የመምራት፣

፮. ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በተፈቀደው በጀት መሰረት ክፍያዎችን የመፈጸም፤

፯. ቅርንጫፍጽህፈት ቤቱንበመወከልከክልልመንግስትአካላትናበተቋቋመበትሥፍራውስጥከሚሰሩመንግስታዊካልሆኑድርጅቶችጋርየስራግንኙነትየማድረግ፤

፰. በዋና ዕንባ ጠባቂ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት የማከናወን፡፡

ክፍል አራት

ስለ ዕምባ ጠበቂዎች አሻሻምና መመዘኛዎች

፲፮. አሿሿም

፩.  የተቋሙ ተሿሚዎች በምክር ቤቱ ይሾማሉ፡፡

፪.  የተቋሙተሿሚዎች አሿሿም የሚከተለው የአመራረጥ ሥርዓት ይኖረዋል፡-

ሀ/  ተሿሚዎች በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፯ መሰረት በሚቋቋመው የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ  ይመለመላሉ

ለ/   ዕጩዎቹም በኮሚቴው ሁለት ሶስተኛ  ድምፅ  የተደገፉ መሆን አለባቸው ፤

ሐ/  ዕጩዎቹ  በምክር ቤቱ  አፈ-ጉባዔ አማካኝነት ለምክር ቤቱ ቀርበው ድምጽ የሚሰጥባቸው ይሆናል ፤

መ/  የቀረቡት ዕጩዎች በምክር ቤቱ ሁለት ሶስተኛ  ድምፅ ሲደገፉ ይሾማሉ፡፡

፲፯. የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጥንቅር

የዕጩ ተሿሚ አቅራቢ ኮሚቴ የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል፡-

፩. የምክር ቤቱ አፈጉባዔ……………………………………………    ሰብሳቢ

፪. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ…………………………………    አባል

፫. ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የሚመረጡ አምስት አባላት…………. አባል

፬.በምክር ቤቱ መቀመጫ ካላቸው ተፎካካሪየፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በጋራ

ስምምነት የሚመረጡ ሁለት የምክር ቤቱ አባላት …………………………አባል

፭.  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት………………………….  አባል

 

፰.ለሹመት የሚያበቁ መመዘኛዎች

ከዚህ በታች የተመለከቱትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ሆኖ ሊሾም ይችላል፡-

፩.  ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ

፪.  ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ተገዥ የሆነ፤

፫. በህግ ወይም በአስተዳደር ወይም በተዛማጅ የትምህርት መስክ ከታወቀ ዩኒቨርስቲ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በዘርፉ በቂ የስራ ልምድ ያለው፤

፬. ከማንኛውም  የፖለቲካ ፓርቲ  ገለልተኛ የሆነ ፣

፭.  በታታሪነቱ፣ በታማኝነቱ እና በሥነ-ምግባሩ መልካም ስም ያተረፈ

፮. ከደንብ መተላለፍ ውጪ  በሌላ የወንጀል ጥፋት ተከሶ ያልተፈረደበት ፤

፯. ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል  ጤንነት ያለው እና

፰. ዕድሜው ከ፴፭ ዓመት በላይ የሆነ ፡፡

፲፱.  የሥራ ዘመን

፩.የተሿሚዎች የስራ ዘመን ስድስት ዓመት ይሆናል፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተዉየስራ ዘመን ሲያበቃ ለአንድ ተጨማሪ ስድስት ዓመት ብቻ ሊሾሙ ይችላሉ፡፡

፳.የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ

፩.የተሿሚ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የመንግስት ተሿሚዎች ጥቅማ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ሕግ መሰረት ይፈጸማል፡፡

፪.በአንቀጽ ፳፩ (፩) መሰረት ሹመቱ ቀሪ የተደረገበት ወይም ከኃላፊነት የተነሳ ተሿሚ እንደገና         ካልተሾመ በስተቀር ያገኙት የነበረው ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ተጠብቆ ለስድስት ወራት ያህል በሕግ አውጪ ፣በህግ አስፈጻሚ  ወይም በዳኝነት አካላት ውስጥ የኃላፊነት ቦታ አይሰጠውም፣

፳፩.ተሿሚው ከኃላፊነት የሚነሳበት ምክንያት

፩. አንድ ተሿሚ በሚከተሉት ምክንያቶችከኃላፊነት እንዲነሳ ወይም ሹመቱ ቀሪ እንዲሆን ሊደረግ ይችላል፡፡

ሀ/ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ ሲፈልግና አስቀድሞ የሦስት ወር ማስጠንቀቂያ  በጽሑፍ ሲሰጥ ፣ ወይም

ለ/ በህመም ምክንያት ሥራውን በሚገባ ለማከናወን የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ወይም

ሐ/  ሙስና መፈፀሙ ወይም ሕግን የሚጻረር ሌላ ድርጊት መፈጸሙ ሲረጋገጥ፣ ወይም

መ/ ግልጽ የሆነ የሥራ ችሎታ ማነስ መኖሩ ሲረጋገጥ ፣ወይም

ሠ/  የሥራ ዘመኑ ሲያበቃ ፡፡

፪. አንድ ተሿሚ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ መሠረት ከኃላፊነት ከተነሳበት ወይም ሹመቱ  ቀሪ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በሌላ ተሿሚ መተካት ይኖርበታል፡፡

፳፪.ተሿሚው ከኃላፊነት የሚነሳበት ሥነ-ሥርዓት

፩. በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፳፩ንዑስ አንቀጽ ፩ ከፊደል ተራ (ለ) እስከ (መ) በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሹመቱ ቀሪ እንዲሆን የሚደረገው ጉዳዩ በአንቀጽ ፳፫ መሰረት በሚቋቋመው ልዩ አጣሪ ጉባኤ ከተመረመረ በኋላ ይሆናል፡፡

፪.  ምክር ቤቱ በልዩ አጣሪ ጉባዔው አብላጫ ድምጽ ተደግፎ የቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ሲያምንበት እና በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ሲደግፈው ተሿሚው ከኃላፊነት እንዲነሳ ይደረጋል፡፡

፳፫. የልዩ አጣሪ ጉባዔው ጥንቅር

ልዩ አጣሪ ጉባኤው  የሚከተሉት አባላት ይኖሩታል ፡-

፩.  የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ …………………………….  ሰብሳቢ፤

፪.  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ …………………   አባል፤

፫.  ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የሚመረጡ ሦስት አባላት……. አባል፤

፬.  በምክር ቤቱ መቀመጫ ካላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ

ስምምነት የሚመረጥ አንድ የምክር ቤቱ አባል  ………………አባል ፤

፭. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ኘሬዚዳንት …………… አባል፡፡

፳፬. በሌላ ሥራ መሰማራት ስለመከልከሉ

፩. ተሿሚው በሥራ ዘመኑ ክፍያን በሚያስገኝ በሌላ የመንግሥት ሆነ የግል ቅጥር ሥራ ላይ እንዲሰማራ አይፈቀድለትም ፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፩ የተመለከተው ቢኖርም ተሿሚው አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚፈለግበት የተለየ የሙያ መስክ ከግምት ውሰጥ ገብቶ በምክር ቤቱ ሊፈቀድለት ይችላል፡፡

 

ክፍል አምስት

የአቤቱታ አቀራረብና የምርመራ ሥነ-ሥርዓት

፳፭.  አቤቱታ የማቅረብ መብት

፩. አቤቱታ የሚቀርበው መብቴ ተጥሶብኛል በሚል ሰው ወይምበሶስተኛ ወገን  ሊሆን ይችላል፡፡

፪. እንደተፈጸመው የአስተዳደር በደል ክብደት ተቋሙ የአመልካቹ ማንነት ሳይገልፅ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ሊቀበል ይችላል፡፡

፫. ማንኛውም ሰው ለደረሰበት የአስተዳደር በደል ለተቋሙ አቤቱታ ከማቅረቡ በፊትአግባብነት ላላቸው አካላት ደረጃውን ጠብቆ ቅሬታውን የማቅረብ እና ዉሳኔ ማግኘት ወይም በተወሰነዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ ዉሳኔ ያላገኘ መሆን ይኖርበታል፡፡

፬. በአንቀጽ፰የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ መሰረት አቤቱታ የማቅረብ መብት በጉዳዩ የወንጀል ወይም የፍትሐብሄር ክስ መመስረትን አይከለክልም፡፡

፭. ተቋሙ አቤቱታዎችን ተቀብሎ የሚመረምረው ያለምንም ክፍያ ነው፡፡

፳፮.ስለ አቤቱታ አቀራረብ

፩. አቤቱታ በቃል ወይም በጽሁፍ ወይም በማንኛውም ሌላ መንገድ ለተቋሙ ሊቀርብ ይችላል፡፡

፪. አቤቱታ በተቻለ መጠን ከደጋፊ ማስረጃዎች ጋር መቅረብ ይኖርበታል፡፡

፫. አቤቱታ እንደሁኔታው በፌዴራል ወይም በክልሉ የስራ ቋንቋ ሊቀርብ ይችላል፡፡

፳፯. ማስረጃዎች እንዲቀርቡስለማድረግ

ተቋሙ አስፈላጊ ማጣሪያዎችን ለማካሄድ በቂ በሆነ ጊዜ ውስጥ ፡-

፩.ተመርማሪዎች ለጥያቄ እንዲቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ ፣

፪. ምስክሮች ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ፣

፫. ለጉዳዩ ጠቃሚ የሆነ ማስረጃ የያዘ ማንኛውም ሰው ይህንን ማስረጃ እንዲያቀርብ፣

ለማድረግ ይችላል፡፡

፳፰. መፍትሔ ስለመስጠት

፩. ተቋሙ የቀረበለትን አቤቱታ በስምምነት ለመጨረስ የተቻለውን ሁሉ ማድርግ አለበት፡፡

፪. የምርመራውን ውጤት ከነመፍትሔ ሀሳቡ ለሚመለከተው አካል የበላይ ኃላፊ በጽሁፍ ያቀርባል፡፡

፫. ተቋሙ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ፪ መሰረት የሚሰጠው የመፍትሔ ሐሳብ ለተፈፀመው  አስተዳደር በደል ምክንያት የሆነው ድርጊት ወይም አሰራር እንዲቆም ወይም ለበደሉ  ምክንያት የሆነው መመሪያ ተፈፃሚነቱ ቀሪ እንዲሆንና የተፈፀመው የአስተዳደር በደል እንዲታረም ወይም ተገቢ የሆነ ማንኛውም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድ በግልፅ የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡

፬. ተቋሙ የምርመራ ዉጤት ለአቤቱታ አቅራቢዉ በጽሁፍ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

፭.ለተቋሙ የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡

፳፱.የአስፈጻሚ አካላት ግዴታ

፩. ተቋሙ አግባብነት ያላቸዉን ሰነዶች ወይም ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ የተጠየቀው አካል በተሟላ አኳኋን የማቅረብ ግዴታ አለበት፤

፪. አስፈጻሚ አካላትበተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤትና የመፍትሄ ሀሳብ ላይ በ፴ ቀናት ውስጥ የእርምት እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት፣ የወሰዱትን ዕርምጃ እና ለመውሰድ ካልተቻለ በቂ ምክንያት ካላቸዉይህንኑ በመግለፅ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸዉ፡፡

፴.ይግባኝ የማቅረብ መብት

፩. ማንኛውም አቤቱታ አቅራቢ ወይም አስፈጻሚ አካልየተቋሙ ኃላፊወይም መርማሪ በሰጠው የምርመራ ዉጤትና መፍትሔ ሀሳብ ወይም ዉሳኔላይ ቅሬታያለው ከሆነ የምርመራ ዉጤትና የመፍትሔ ሐሳብ ወይም ዉሳኔዉ በጽሁፍ ከደረሰው ጊዜ አንስቶ በ፴ ቀናት ውስጥ በደረጃው ቀጥሎ ለሚገኘው የተቋሙ ኃላፊ ወይም ዳይሬክተር ቅሬታውን የማቅረብ መብት አለው፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (፩) መሰረት ቅሬታው የቀረበለት ተሿሚ ወይም ኃላፊ ወይም ዳይሬክተር የተሰጠውን የምርመራ ዉጤትና መፍትሔ ሐሳብ ወይም ዉሳኔ ማሻሻል፣ ማገድ፣ መሻር ወይም ማፅናት ይችላል፡፡

፫. ዋና ዕንባ ጠባቂው በ፴ ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፤ የሚሰጠው ውሳኔምየመጨረሻ ይሆናል፡፡

፴፩. ቅጣት

፩.ማንኛውም ሰው፡-

ሀ/በተቋሙ መጥሪያ ደርሶት ወይም በሌላ ሁኔታ ተጠርቶ ካልቀረበ፣ ወይም

ለ/ ለምርመራ ወይም ለቁጥጥር ስራ ማስረጃዎችን ወይም ሰነዶችን እንዲያቀረብ ተጠይቆ ተቋሙ በጠየቀው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማያቀርብ ፣ ወይም

ሐ/ የምርመራ ወይም የቁጥጥር ሥራ እንዳይሰራ እንቅፋት የሆነ፣ ወይም

መ/ ምስክሮች ወይም አቤቱታ አቅራቢዎች ወይም ለተቋሙ ሥራ በማናቸውም መንገድ በተባበሩ ወገኖች ላይ ጥቃት ያደረሰ ፣ ወይም

ሠ/ ያለ በቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ዉጤትና መፍትሄ ወይም የቁጥጥር ውጤትመሰረት የእርምት ዕርምጃ በ፴ ቀናት ውስጥ ያልወሰደ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም ብር ሺ(አስር ሺ ብር) የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ከፊደል ተራ (ሀ) እስከ (ሠ) የተዘረዘሩትን ጥፋቶች የፈጸመ ማንኛውም ሰው በሕግ እንዲጠየቅ ተቋሙ በቀጥታ ጉዳዩ ለሚመለከተው ዓቃቤ-ሕግ መስሪያ ቤት የድርጊቱን ሪፖርት ከደጋፊ ማስረጃዎች ጋር ያቀርባል፡ ከተቋሙ ትዕዛዝ የደረሰው ዓቃቤ ህግ መስሪያ ቤት አግባብ ባለው ሕግ መሰረት የወንጀል ክስ ይመሰርታል፡፡

፴፪. የማሳወቅ ግዴታ

ተቋሙ የምርመራ ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ወንጀል ስለመፈፀሙ ያመነ እንደሆነ ለሚመለከተው አካል ወይም ኃላፊ ወዲያውኑ በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

መወሰን ካልተቻለ አስቀድሞ የቀረበለት አካል ይመረምራል፡፡

፴፫.የስልጣን መደራረብ

፩.  በተቋሙና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን  ሥልጣን ሥር የሚወድቁ ጉዳዮች በሚያጋጥሙ ጊዜ በማንኛቸው እንደሚመረመሩ በሁለቱ የጋራ ምክክር ይወሰናል፡፡

፪. አንድን ጉዳይ የትኛው አካል እንደሚመረመር በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሰረት መወሰን ካልተቻለ አስቀድሞ የቀረበለት አካል ይመረምራል፡፡

፴፬.የመተባበር ግዴታ     

ተቋሙ ሥልጣንና ተግባሩን ሥራ ላይ ለማዋል እንዲችል ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠትና የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

፴፭.መግለጫ ስለመስጠት

፩. ተቋሙ እንደአስፈላጊነቱ የምርመራ፣የቁጥጥር እና የጥናት ውጤቶችን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሀን ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡

፪. ተቋሙ መደበኛ ሪፖርትን ለምክር ቤት የማቅረብና አሰራሩን በሙሉ ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

፫. በተቋሙ የቀረበ የምርመራ ዉጤትና መፍትሄ ሀሳብ ለመፈፀም ተባባሪ ያልሆነ አስፈጻሚ አካላት ዝርዝር በተመለከተ ልዩ ሪፖርት ለምክር ቤቱ ማቅረብ፤ ምክር ቤቱም ተገቢዉን እርምጃ ይወሰዳል፡፡

፬. በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (፩) ፣ (፪) እና (፫) የተደነገገው ቢኖርም የአገሪቱ የፀጥታና ደኅንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለማድረግ ወይም የግለሰቦችን የግል ህይወት መብት ለመጠበቅ ሲባል በሚስጢር ሊያዙ በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ ተቋሙ ጥንቃቄ የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡

፴፮. በስም ማጥፋት ስላለመጠየቅ

፩. በዚህ አዋጅ መሠረት የቀርበ አቤቱታ በስም ማጥፋት አያስጠይቅም፡፡

፪. ተቋሙ ስለሚያካሂደው ምርመራ ውጤት ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው ሪፖርት ወይም በመገናኛ ብዙሃን በሚሰጠው ይፋዊ መግለጫ ወይም ሥራውን በማስመልከት በሚያደርገው ሌላ ዓይነት መፃፃፍ በስም ማጥፋት የሚያስጠይቅ አይሆንም፡፡

፴፯. ልዩ መብት   

ማንኛውም የተቋሙ፡-

፩.  ተሿሚ ከሆነ ምክር ቤቱ፣

፪.  መርማሪ ፣ ምርመራ ስራ የሚያከናውን ባለሙያ ወይም የምርመራ ዳይሬክቶሬት ከሆነ ዋና ዕንባ ጠባቂው  ሳይፈቅድ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እንጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር አይያዝም ፣አይከሰስም፣አይታሰርም ፡፡

ክፍል ስድስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

፴፰.በጀት

፩.  የተቋሙ በጀት ከሚከተሉት ምንጮች የሚገኝይሆናል፡-

ሀ/  በምክር ቤቱ በሚመደብ በጀት ፣

ለ/  ከዕርዳታ፣ ከስጦታና ከማናቸውም ሌላ ምንጭ፡፡

፪.  ለተቋሙ ከተፈቀደው በጀት ውስጥ የየሦስት ወሩ ድርሻ የሆነ የሥራ ማስኬጃ በቅድሚያ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ስም በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ውስጥ በአንድ ጊዜ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

፴፱. የሂሣብ መዛግብት

፩.  ተቋሙ የተሟላና ትክክለኛ የሆኑ የሂሣብ መዛግብት ይይዛል፡፡

፪.  የተቋሙ ሂሣብ ምክር ቤቱ በሚሰይመው አካል በየዓመቱ ይመረመራል፡፡

፵. ይግባኝ

፩. ጉባኤው በሚሰጠው የአስተዳደር ውሳኔ ቅር የተሰኘ የተቋሙ ዳይሬክተር ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ በ፴ ቀናት ውስጥ የይግባኝ ቅሬታውን ለምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማቅረብ ይችላል፡፡

፪. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሰረት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡

፵፩. በሌሎች ባለሙያዎች ስለመገልገል

ተቋሙ ለተለየ ሥራና ለተወሰነ ጊዜ ተገቢ የሆነውን ክፍያ በመፈፀም ለሥራ የሚያስፈልጉትን  የራሱ ያልሆኑ ባለሙያዎችን መድቦ ሊያሠራ ይችላል፡፡

፵፪.ሚስጥር ስለመጠበቅ

በፍርድ ቤት ካልታዘዘ ወይም በዋና ዕንባ ጠባቂው ካልተፈቀደ በስተቀር ማንኛውም የተቋሙ ተሿሚ ወይም ሠራተኛ ወይም በአንቀጽ ፵፩ መሠረት የተመደበ ባለሙያ በሥራው አጋጣሚ ያወቀውን ምስጢር በማንኛውም ጊዜ የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡

፵፫. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን              

፩.  ምክር ቤቱ ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም አስፈላጊ የሆኑ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

፪. ጉባኤዉ ለዚህ አዋጅ እና ደንቦች አፈፃፀም አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

፵፬. የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች

ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በተቋሙ በምርመራ፣ በቁጥጥርና ጥናት ላይ የሚገኙ ጉዳዮች በቀድሞው ህግ መሠረት መታየታቸው ይቀጥላል፡፡

፵፭.የተሻሩና ተፈፃሚነት ስለማይኖረቸው ህጎች

፩.የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለመቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር ፪፻፲፩/፲፱፻፺፪በዚህ አዋጅ ተሸሯል፡፡

፪. ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ ወይም የተለመደ አሰራር በዚህ አዋጅ ውስጥ በተጠቀሱ ጉዳዩች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

፵፮. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

2 replies »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.