Articles

10 ግራ-ገብ ዜናዎች

1/ “የተርባይኖች መቀነስ በሚመነጨው ኃይል ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም” የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ

በዚህ ዜና እና “ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ተርባይን ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው በሚለው ዜና መካከል ልዩነት የለም። ሁለቱም ዜና አይን ያወጣ ያፈጠጠ ውሸት ነው። ይሄን ለማረጋገጥ ከሃይስኩል ዕውቀት በላይ አይጠይቅም። በዚህ አካሄድ በቅርቡ እነዚህን ዜናዎች እንሰማለን።

–መንግስት አንዱን ኩላሊታችንን ያወጣውና…”የአንድ ኩላሊት መቀነስ በጤና ላይ የሚያመጣው አንዳችም ጉዳት የለም ተባለ”

—መንግስት ካሉን አውሮፕላኖች ላይ ከወጪ አንጻር አንዱን ሞተር ያወጣውና.…”የአንድ ሞተር መውጣት በተሳፋሪዎች ደህንነት ላይ የሚያስከትለው አንዳችም ስጋት የለም ተባለ”

…በቅርቡ መከላከያ የተኩስ ልምምድ የሚያደርገው መሀል አዲስ አበባ ላይ ይሆናል። ከዛ ዜናው ይቀጥላል…”የተኩስ ልምምዱ በነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት የደህንነት አያስከትልም ተባለ”

ዜናውን ሳነብ በርካታ መሀንዲሶች እሳት ጎርሰው..ለብሰው ፌስቡክን በፖስትና ኮሜንት ያጨናንቁታል ብዬ ገምቼ ነብር። በትክክል አልገመትኩም። በመቀጠል 3 አማራጭ ድምዳሜዎች ላይ ደርሻለው።

1/ የአገራችን መህንዲሶች ፌስ ቡክ አይጠቀሙም።

2/ ቢጠቀሙም ከራሳቸው ሙያ ይልቅ የሚመሰጡት በህግና የፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ ነው።

3/ ከስራቸው ባህርይ የተነሳ ሁሉም ኢንተርኔት የሌለበት ቦታ ፊልድ ወጥተው ዜናው ገና አልሰሙም።

ቢያንስ ቢያንስ “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ የሆነች ማብራሪያ ቢጤ ቢያክሉበት ኖሮ እኮ “የሶሻል” ተማሪዎችና ተመራቂዎች አርፈን እንቀምጥ ነበር። ለ”እንዴት?” በሚሰጠው ምላሽ ባለሞያዎች ሲከራከሩ እኛ ተመልካች እንሆናለን።

በአንድ ወቅት የመጨረሻ ዓመት የፊዚክስ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በመምህራቸው አንድ ከባድ assignment ተሰጣቸው። መምህሩ ተማሪዎቹን በጣም ብዙ በጎች የተሰማሩበት የግጦሽ ቦታ ነበር ያመጣቸው። የተሰጣቸው assignment የፊዚክስ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው የበጎቹን ቁጥር ፈጥኖ መናገር ነው። ሁሉም ተማሪዎች የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው ሲደናበሩ አንደኛው ተማሪ በቅጽበት እጁን አውጥቶ የበጎቹ ቁጥር ስንት እንደሆነ ተናገረ። “እንዴት አመጣኸው?” አሉት መምህሩ።

ተማሪውም በኩራት “እግራቸውን ቆጠርኩና ለአራት አካፈልኩት!!”

ሊሆን ይችላል። በበኩሌ በተማሪው መልስ መሳቅ ቢዳዳኝም አላደርገውም። ምክንያቱም ለ”እንዴት?” በሚሰጥ ምላሽ ከፊዚክስ ተመራቂ  በላይ አላውቅም።

“የተርባይኖች መቀነስ በሚመነጨው ኃይል ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም” የሚለው መግለጫ የፊዚክስ ተማሪውን ያክል እንኳን ማብራሪያ የለውም። በነገራችን ላይ ይሄን ዜና “ግራ-ገብ” ብቻ ሳይሆን “እጥፍ ግራ-ገብ” የሚያደርገው ሌላ ነገር አለ። ከወር በፊት /1 September 2019/ የዚህን ነገር ዳር-ዳርታ የሚያሳይ ዜና ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ተዘግቦ ነበር።

“ከህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮች ውስጥ አምስቱ ግድቡ ተጠናቆ ውኃ ከተሞላ በኋላ እንዲተከሉ ተወሰነ”

በዜናው ላይ ካነበብኩት ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ እያሳቀችኝ ያለች አንዲት አስተያየት አለች። ዜናው ይወርድ ይወርድና ሰባተኛ አንቀጽ ላይ “አንድ የኃይል ማመንጫን አቅም ያመነጫል በተባለው አጠቃላይ ሜጋ ዋት ኃይል የመለካት የተሳሳተ ግንዛቤ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደተዛመተ የሚገልጹት ኢንጂነሩ…” ብላ ትቀጥላለች። ሲጀመር አብዛኛው ህብረተሰብ ስለ ሜጋ ዋት፤ የኃይል ማመንጫ፤ ኃይል መለካት .…ምኑን አውቆት ነው? “የተሳሳተ ግንዛቤ በኢትዮጵያ..” የተባለው? እንኳንስ “የተሳሳተ” እና ከነጭራሹ ከባለሞያው ውጭ ያለው ‘ኢትዮጵያ’ ምን ግንዛቤ አለውና ነው? ወይስ መሀንዲሶች ናቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የያዙት? ደሞስ መቼ ነው ይሄ የተሳሳተ ግንዛቤ ሲንጸባረቅ የነበረው? “አንድ የኃይል ማመንጫን አቅም ያመነጫል በተባለው አጠቃላይ ሜጋ ዋት ኃይል የመለካት የተሳሳተ ግንዛቤ” ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ከእሳቸው አፍ ነው የወጣው። ለምሳሌ ስለ deoxyribonucleic acid, nameplate capacity, Francis turbine-generators, capacity factor “የተሳሳተ ግንዛቤ በኢትዮጵያ” ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ግንዛቤው ራሱ የለም፤ ከጥቂት የመስኩ ባለሞያዎች ውጭ። ስለሆነም በቅጡ ግንዛቤ እንኳን በሌለበት “የተሳሳተ ግንዛቤ በኢትዮጵያ..” ብሎ መግለጫ መስጠት የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ሊበሏት ያሰቧትን ጅግራ..ዓይነት ነገር..ቀድሞም የታቀደበት ነገር መሆኑን ማሳያ ነው።

እስቲ አሁን ደግሞ ትንሽ መረጃ እንለዋወጥ

ስለ ህዳሴው ግድብ በአጠቃላይ እና አሁን እየተባለ ስላለው ነገር መነሻ ለማግኘት የሲቪል ግንባታውን የሚያከናውነው ሳሊኒ በድረ-ገጹ ላይ ስለ ፕሮጀክቱ ያሰፈረውን አጭር መረጃ /በተለይ MAIN TECHNICAL DATA/ ተመልክቱት። በድረ-ገጹ ላይ እንደሚነበበው፤

The project involves the construction of a main dam in Roller Compacted Concrete (RCC), with 2 power stations installed at the foot of the dam. The power stations are positioned on the right and left banks of the river and comprise 16 Francis turbines with a total installed power of 6,000 MW and estimated production of 15,000 GWh per year.

6000 / installed power/ እና 15,000 GWh per year / estimated production/ ምንድነው የሚያመለክቱት?

በዚህ ነጥብ ላይ U.S. Department of Energy’s Office of Energy Efficiency and Renewable Energy (EERE) ለእኛ በሚገባን መልኩ U.S. Energy Information Administration (EIA) ጠቅሶ መልሱን ይሰጠናል።

በዚህ መሰረት Capacity / installed power/ ማለት The maximum output of electricity that a generator can produce under ideal conditions. Capacity levels are normally determined as a result of performance tests and allow utilities to project the maximum electricity load that a generator can support. Capacity is generally measured in megawatts or kilowatts.

በሌላ መልኩ Electricity generation /estimated production/ ማለት The amount of electricity that IS produced over a specific period of time እንደሆነ ይነግረናል።የዚህን ስሌትና አለካክ በተመለከተም ወደ የተወሳሰበ ቀመር ሳይገባ በአጭር ምሳሌ እንደሚከተለው ያስረዳናል።

consider a wind turbine with a capacity of 1.5 megawatts that is running at its maximum capacity for 2 hours. In this scenario, at the end of the second hour, the turbine would have generated 3 megawatt-hours of energy (i.e. 1.5 megawatts X 2 hours).

https://www.energy.gov/eere/articles/whats-difference-between-installed-capacity-and-electricity-generation

አሁን እየተነገረን ያለው ግድቡ ያመነጫል ተብሎ የተሰላው በዓመት በአማካይ 15760 ጊጋ ዋት (Gigawatt hours) የኢነርጂ (ኃይል) መጠን ላይ የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነው።  አምስት ተርባይን ሲቀነስ የግድቡ Capacity / installed power/ 4700 MW ይሆናል። ስለሆነም በመግለጫው መሰረት 4700 MW ሆነ 6,000 MW 15,000 GWh per year / estimated production/ ይሰጣል እንደማለት ነው። ይሄኔ ነው “ዘይመስል ነገር!” ማለት።

በተጨማሪም የውሀ ሀይል ማመንጫ እንዴት እንደሚሰራ በአሜሪካ በሀይል እና የአየር ንብረት ላይ የመንግስትን ፖሊሲ በመቅረጽ፤ በማመንጭትና አንዳንዴም በማስለወጥ የሚታወቀውና ከተቋቋመ 50 ዓመት በላይ ከሆነው የሳይንቲስቶች ስብስብ The Union of Concerned Scientists ድረ-ገጽ ላይ How Hydroelectric Energy Works በሚል ከቀረበው ጽሁፍ አንዲት መስመር ላካፍላቹ። ቀሪውን ሊንኩን በመጠቀም አንብቡት።

In order to generate electricity from the kinetic energy in moving water, the water has to move with sufficient speed and volume to spin a propeller-like device called a turbine, which in turn rotates a generator to generate electricity.

https://www.ucsusa.org/resources/how-hydroelectric-energy-works

በተጨማሪ ደግሞ በሚከተለው ሊንክ ላይ ያለውን መረጃ አንብቡት።

http://www.wvic.com/content/how_hydropower_works.cfm

How Hydropower Works

Parts of a Hydroelectric Plant

Most conventional hydroelectric plants include four major components (see graphic below):

  1. Dam. Raises the water level of the river to create falling water. Also controls the flow of water. The reservoir that is formed is, in effect, stored energy.
  2. Turbine. The force of falling water pushing against the turbine’s blades causes the turbine to spin. A water turbine is much like a windmill, except the energy is provided by falling water instead of wind. The turbine converts the kinetic energy of falling water into mechanical energy.
  3. Generator. Connected to the turbine by shafts and possibly gears so when the turbine spins it causes the generator to spin also. Converts the mechanical energy from the turbine into electric energy. Generators in hydropower plants work just like the generators in other types of power plants.
  4. Transmission lines. Conduct electricity from the hydropower plant to homes and business.

በላይኛው መረጃ ላይ በመንተራስ “ብዙ ጀነሬተር ብንደርድር…” በሚል የቀረበውን ማብራሪያ መዳኘት አይከብድም።

ከመግለጫው በጣም አሳሳቢው ክፍል የተርባይን እና ጄኔሬተር ቁጥር በምን እንደሚወሰን የሚያወሳው ሙያዊ ትንተና ነው። እንደሚከተለው ይነበባል።

“የተርባይን እና ጄነሬተር ቁጥር የሚወሰነው፤ ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን፣ ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ላይ በምን ያክል ፍጥነት ተርባይኑን ይመታል፣ የኃይል ፍላጎት፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ እና የመሳሰሉት ላይ ነው ይላሉ”

ጭራሽ ግድቡ የሚይዘው የውሀ መጠን ሳይታወቅ ነው ወደ ግንባታ የተገባው? ውሃው ከምን ያክል ከፍታ ላይ በምን ያክል ፍጥነት ተርባይኑን እንደሚመታውም ገና እርግጠኛ አይደላችሁም? የኃይል ፍላጎት እና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱን በተመለከተም You have no idea?

ጎበዝ እዚህ ላይ ይበቃል። እዛው civil code ምናምን ባገላብጥ ይሻላል። ስለ ግድቡ ሰፋ ያለ መረጃ ከፈለጋችሁ ዊኪፒዲያን ጎብኙት። /https://en.wikipedia.org/wiki/Grand_Ethiopian_Renaissance_Dam/

2/ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን የዜጎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ እየተጠቀመችበት መሆኑ ተገለፀ

http://tiny.cc/iz0kez

የኑውክሌር ቴክኖሎጂ? እንዴት ደስ ይላል። የኑክሌር ቴክኖሎጂ መጠቀም ከቻልን ከአሁን በኋላ “ኋላ ቀር” የሚለው ቅጥያ ይፋቅልናል። ከድህነት ለመውጣትም ረጅም ጊዜ አይፈጅብንም።

በዚህ ዜና ብዙዎች እንደኔ ተደስተዋል። ሌሎች መናፍቃን ደግሞ ኢትዮጵያ የኑክሌር መሳሪያ እንዳላት ጠርጥረዋል።

ግን ግን ምንድነው የኒውክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀም? የዜናው ይዘት ለዚህ መልስ አይሰጥም። ትንሽ ፍንጭ የምትሰጥ ዓረፍተ ነገር ግን አለች። “የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከል ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጌታቸው ቴክኖሎጂውን ለካንስር ህክምና፤ ለቆላ ዝንብ ማምከኛ እና ለመንገድ ስራ በአግባቡ እየተጠቀመችበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡” ልክ ነው፤ የኑክሌር ቴክኖሎጂ በእነዚህ ብቻ ሳይሆን በግብርና እንዲሁም በምግብ ማምረት ሂደት ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህ ረገድ በጣም ተጠቃሽ “የጭስ መለያ” /smoke detector/ ነው። ይህንን ከዜናው ጋር አዛምዱት፤ እንበልና smoke detector በአገራችን ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች ላይ ቢገጠም መባል ያለበት “ኢትዮጵያ የኑክሌር ቴክኖሎጂን እየተጠቀመችበት መሆኑ ተገለፀ” ነው? በፍጹም!

መባል የነበረበት፤

“ኢትዮጵያ የኑክሌር ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ምርቶች እየተጠቀመች መሆኑ ተገለፀ”

3/ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቸርነት ሳይሆን ህልውና ነው ተባለ

http://www.dbu.edu.et/index.php/latest/news/2-dbu-articles/181-2019-03-13-06-35-21

ይሄ የተባለው በሴቶች ቀን ነው። የህልውና ጉዳይ በሆነ ጉዳይ ላይ በየዓመቱ የሴቶች ቀን እስኪመጣ መጠበቅ ለምን አስፈለገ? ማህበራዊ ችግሮች በተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ብቻ አይፈቱም። ትኩረት ለማግኘት “ህልውና” ስለተባለ ጠብ የሚል ለውጥ አይመጣም። ሁሉም ነገር  የህልውና ጉዳይ ከሆነ “ህልውና” ትርጉም ያጣል።

ኮንዶሚኒየም ህልውና ነው ተባለ፡ ትራንፖርት ህልውና መሆኑ ተነገረ፤ የከተማ ጽዳት ህልውና መሆኑ ተነገረ…በዚህ አያያዝ በቀጣይ የምንሰማቸው ዜማዎች፤

Samsung S10 ህልውና ነው ተባለ

ዱባይ ደርሶ መምጣት ህልውና መሆኑ ተገለጸ

ቪትዝ መኪና ህልውና መሆኑ ተነገረ..

4/ የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ የተቀናጀ ድጋፋዊ ጉብኝት ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ

https://ehia.gov.et/node/306

“የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋናው መስሪያ ቤት ሀላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለሞያዎች የኤጀንሲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጆች የክልል ጤና ቢሮ አሰተባባሪዎች የዞንና የወረዳ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪዎች እንዲሁም ከክሊንተን ሄልዝ ኢኒሸቲቭ የተውጣጡ ባለሞያዎችን ያሳተፈ በዘጠኝ ቡድን በመደራጀት ከታህሳስ 27/2011 ጀምሮ በአራቱ ክልሎች የሚገኙ የጤና መድህን ዝግጅት ስራዎችን ለመደገፍ እንደሚንቀሳቀስ ታውቋል፡፡”

ምንድነው “ድጋፋዊ ጉብኝት?” እየዞሩ “አይዟችሁ! በርቱ!” ሊሉ ነው?

5/ የመብራት ፈረቃው ሰኔ 30 ድረስም ላይቆይ ይችላል ተባለ

http://tiny.cc/g90kez

“በመላው ሀገሪቱ በተከሰተው የሃይል እጥረት ምክንያት የመብራት አገልግሎት በፈረቃ መሰጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ግድቦች ይሞላሉ ተብሎ ስለሚታመን እስከ ሰኔ 30 ድረስ ላይቆይም እንደሚችልና መብራት በመደበኛነት የ24 ሰአት አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል አቶ ሰለሞን ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልፀዋል፡፡”

ብድር ወስደህ አበዳሪው “በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መልስልኝ! ከአንድ ወር በላይ አልታገስህም” ሲልህ ” ኧረ! አንድ ወር ድረስም አይቆይም! በእኔ ተማመን” ትልና ታረጋጋዋለህ። /ልቦናህ እያወቀው…የገቢ ምንጭ እንደሌለህ!/

የኃላፊውና የተበዳሪው ምላሽ አንድ አይነት ነው። “ይሞላሉ ተብሎ ስለሚታመን..!”—ምንም ዓይነት የሜትሮሎጂ መረጃ የለም እኮ!

6/ መልካም እሴቶች ይዳብሩ ተባለ

http://tiny.cc/wc1kez

ይዳብሩዋ ታዲያ! ማን አይዳብሩ አለ? አይዳብሩ የሚል ደፋር ካለ ዜና ነው። “ይዳብሩ ተባለ” ግን ጭራሽ ዜና አይደለም።

7/ የቅድመ መደበኛ መምህራንን አቅም መገንባት ወሳኝ ነው ተባለ

http://tiny.cc/sf1kez

ይሄንን ገና ያልተወለደ ልጅም ጠንቅቆ ያውቃል። አቅም መገንባት ሲጀመር ዜና ይሆናል። እስከዛው ድረስ ግን.…አይባልም…ዜና አይሰራለትም።

8/ ህብርተሰቡ የፓልም ዘይትን በተመጠነ መልኩ መጠቀም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ህብርተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ

http://tiny.cc/kq1kez

ሙሉ ዜናው እንደሚከተለው ይነበባል።

“አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህብርተሰቡ ለምግብነት የሚጠቀመውን የፓልም ዘይት በተመጠነ መልኩ መጠቀም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ህብርተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገባውን ፓልም ዘይት እና ሌሎች በሀገሪቱ የሚመርቱ ዘይቶች ደርጃቸውን ጠብቀው እንዲመርቱ በሚል የጥናት ውጤት ማሳወቁን አስታውቋል።

ሆኖም በወቅቱ ህብርተሰቡ ጋር የደርሰው መርጃ መደናገርን መፍጠሩን ገልጾ፥ ህብርተሰቡ የፓልም ዘይትን እንዳይጠቀም ሳይሆን በተመጠነ ምልኩ እንዲጠቀም ነው መልዕክቴን ያስተላለፍኩት ብሏል።

በቀጣይም ከአጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሊደርጉ ይገባል ያላቸውን ጥንቃቄዎችን ገልጿል።

በተለይም ሰውነት ከሚያቃጥለው በላይ ይህንን ዘይት ሰዎች የሚጠቀሙ ከሆነ የደም ቧንቧ ላይ እየተጋገረ እንደሚመጣ ያነሳው ተቋሙ፥ አጠቃቀማችን የተመጠነ መሆን አለበት ሲል አሳስቧል”

በተመጠነ? ለአምስት ሰው የሚበቃ ሽሮ ለማዘጋጀት ስንት ማንኪያ ፓልም ዘይት እንጠቀም? “በተለይም ሰውነት ከሚያቃጥለው በላይ.…???” ሰውነቴ የሚያቃጥለው ፓልም ዘይት ምን ያህል ነው?

ይልቅ እናንተም ከሚያቃጥለን በላይ መግለጫ ባትሰጡን? ማለቴ..እስቲ የተመጠነ አርጉት

9/ ኢትዮጵያ በመጪው ታህሳስ ወር መጀመሪያ የራሷን ሳተላይት እንደምታመጥቅ ተነገረ

https://shegerfm.com/2013-05-11-16-19-47/5425-ethiopia-to-launch-satellite-in-the-coming-tahsas

ይኼኛውም ልክ እንደ “ኒውክሌር ቴክኖሎጂ..” ደስታችሁን ያንረውና ወደ ዝርዝሩ ስትገቡ..

“…ሙሉ ወጪዋ በቻይና መንግስት የተሸፈነው ሳተላይቷ ወደ ህዋ የምትመጥቀው ከቻይና ምድር ነው”

ለኢትዮጵያ ጥቅም የምትውል ሳተላይት ወደ ህዋ መምጠቋ እስየው ነው። ግን ዜናው በእንዲህ መልኩ አስተካክሉት።

“ቻይና ለኢትዮጵያ ጥቅም የምትውል ሳተላይት በራሷ ቴክኖሎጂና ወጪ ሰርታ እንደምታመጥቅላት ተነገረ።”

10 /የክረምቱ ዝናብ ለሳምንታት ከተለመደው በላይ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ

https://amharic.voanews.com/a/ethiopia-meteorology-forcast-08-26-10-101594063/1461047.html

“የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዲሬክተር አቶ ኪዳኔ አሰፋ የዚህ ክረምት የዝናብ ሁኔታ ከመደኛው ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀው ሕዝቡ ከባድ ዝናብና ጎርፍ፣ በገደላማ አካባቢ የሚኖረውም ሰው የመሬት መንሸራተት እንደሚኖር አውቆ ሕይወቱን፣ ቤተሰቡን፣ እንስሣቱንና ንብረቱን ከአደጋ መጠበቅ እንዲችል በእንቅስቃሴው ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሣስበዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በማከልም ምንም እንኳ እንኳ ኤጀንሲያቸው ስፋት ያላቸውንና ተአማኒነታቸውም ከፍተኛ የሆነ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ቢሰጥም በአካባቢ የተወሰኑ ልዩ ትንበያዎችን ለማድረግ ግን የአቅም ውሱንነት እንዳለው ገልፀዋል፡፡”

ይሄ ጥንቆላ ነው። ሳይንስም ሜትሮሎጂም አይደለም። “…በአካባቢ የተወሰኑ ልዩ ትንበያዎችን ለማድረግ ግን የአቅም ውሱንነት እንዳለው ገልፀዋል።” የእናንተ ሜትሮሎጂ “ምስራቅ፤ ምዕራብ፤ ደቡብ፤ ሰሜን” ብሎ ነው የሚያሳየው። ደግሞስ ቦታውን ካላወቃችሁት ምን አርጉ ነው? እንዴት እንጠንቀቅ? በጊዜ ወደ ቤታችን እንግባ? ሰፈር እንቀይር?

Categories: Articles

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.