Draft Laws

በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር /ረቂቅ/ የወጣ አዋጅ

አዋጅ ቁጥር…/2011

በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ

በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ-ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እና ለሰብአዊ መብት ጥሰት እያገለጡ የሚገኙ ወንጀሎች መሆናቸውን በመገንዘብ ፤

በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2007 ግልጽነት የሚጎድለው፣ ከሌሎች ህጎች ጋር የማይጣጣምና ለችግሩ በቂ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ በመገኘቱ በአዲስና በተሟላ የሕግ ማዕቀፍ መተካት በማስፈለጉ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ድሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት አንቀጽ 18 መሰረት በማንኛውም መንገድ በሰው መነገድ በመከልከሉ እንዲሁም በሰው የመነገድ በተለይም በሴቶችና ሕጻናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት እና ሰውን  በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የሚያስችሉ ፕሮቶኮሎችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማውጣቱና ኢትዮጵያም ስምምነቱን ያጸደቀች በመሆኑ የማስፈጸሚያ ዝርዝር ህግ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤

መንግስት ሰዎች በተፈጥሮ እና በህግ የተጎናጸፉትን መብትና ጥቅም የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በወንጀል መከላከል፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ፣ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም በተለይም ለወንጀሎቹ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግና የተጎጂዎችን ዕድሜ፣ ጾታና ልዩ ፍላጎት ያማከል ተግባር መፈጸም እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማውጣት እና ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 (5) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

1.      አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር ——/2011” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጉም

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚሀ አዋጅ ውስጥ፡-

 • “የተደራጀ የወንጀል ቡድን” ማለት በዚህ አዋጅ የተመለከተ ወንጀልን ለመፈጸም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰውን የያዘ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌላ አገር የሚገኝ ወይም የሚንቀሳቀስ፤ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ሌላ ማንኛውንም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት የተዋቀረ ቡድን ነው፤
 • “ባርነት” ማለት የሌላ ሰው የባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እየተፈጸመበት ያለ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ ወይም አቋም ነው፤
 • “አገልጋይ ማድረግ” ማለት አንድ ሰው ሊያስቀረው፣ ሊከላከለው ወይም ሊቀይረው በማይችልበት ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ወይም ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ወይም ማስገደድ ነው፤
 • “በዝሙት አዳሪነትና መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ” ማለት አንድን ሰው ለዝሙት አገልግሎት ማሰማራት፣ ለግብረ ስጋ ግንኙነት አገልግሎት ማቅረብ ወይም መጠቀም ወይም ለመልካም ጸባይ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት በተለይም ገላን ወይም ህፍረት ሥጋ ለሌሎች እንዲያሳይ ማድረግ ሲሆን፤ እነዚህን ተግባራት በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምጽ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ መቅረጽና ማሰራጨት ወይም ለማሰራጨት ዓላማ መቅረጽን ያካትታል፡፡
 • “የህጻናት የጉልበት ብዝበዛ” ማለት ህፃንን በህግ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጭ ወይም ለህጻኑ አካል ወይም ዕድሜ በተጻረረ መልኩ ስራ እንዲሰራ ወይም አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፤
 • “ከባድ አካል ጉዳት” ማለት በወንጀል ህግ አንቀጽ 555 ስር የተመለከተው ሁኔታ ነው፤
 • “ተጎጂ” ማለት በዚህ አዋጅ ከተመለከቱት የወንጀል ድርጊቶች አንዱ ወይም ከአንድ በላይ የተፈጸመበት እና አካላዊ፣ ስነልቦናዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የደረሰበት ወይም የመብት ጥሰት የተፈጸመበት ወይም እነዚህ ጉዳቶች የደረሱበት ወይም የመብት ጥሰት የተፈጸመበት ባይሆንም ለወንጀሉ የተጋለጠ ወይም ሊጋለጥ የሚችል በመሆኑ በዚህ አዋጅ የተመለከተው ጥበቃ እና ድጋፍ እንደ አግባብነቱ የሚያስፈልገው ሰው ነው፤
 • “ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት” ማለት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3፣ 4፣ 8፣ 9፣ 10 ወይም 11 የተመለከተ ወንጀል መፈጸሚያነት የዋለ ንብረት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእነዚህ ወንጀል የተገኘ ንብረት፣ ከእነዚህ ወንጀል በተገኘው ንብረት የተፈራው ንብረት ወይም ለእነዚህ ወንጀል መፈጸሚያነት የዋለው ወይም ውጤት የሆነው ወይም የተፈራው ንብረት ያልተገኘ እንደሆነ ተመጣጣኝ ግምት ያለው የወንጀል ፈጻሚው ንብረትን ያጠቃልላል፤
 • “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 47 (1) የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም የአዲስ አበባንና የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደርን ይጨምራል፤
 • “ሕጻን” ማለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው፤
 • “የወንጀል ህግ” ማለት በአዋጅ ቁጥር 414/1996 ዓ.ም የወጣው የ1996 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ነው፤
 • “ፖሊስ” ማለት የፌዴራል ፖሊስ ወይም በፌዴራል ፖሊስ ውክልና የተሰጠው የክልል ፖሊስ ነው፤
 • “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤
 • ማንኛውም በወንድ ፆታ የተገለጸው አነጋገር ሴትንም ይጨምራል፡፡

 

ክፍል ሁለት

በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ 

መንገድ ድንበር የማሻገር፣ ህገ ወጥ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ወንጀሎች እና ተያያዥ ወንጀሎች

ንዑስ ክፍል አንድ

በሰው የመነገድ ወንጀል

3. በሰው የመነገድ ድርጊት

 • ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በባርነት ወይም በባርነት መሰል ተግባር፣ በአገልጋይነት ወይም ዕዳ መያዣነት የያዘው፤ አካሉን በማውጣት ወይም በዝሙት አዳሪነት ወይም መሰል የወሲብ ተግባር ብዝበዛ የፈጸመበት፤ በግዳጅ ሥራ ወይም አገልግሎት፣ በልመና፣ በወንጀል ተግባር፣ በግዳጅ ጋብቻ፣ ወይም በማህጸን ኪራይ ያሰማራ ወይም ህጻናትን በጉልበት ሥራ የበዘበዘ ወይም እነዚህን መሰል የብዝበዛ ተግባራት የፈጸመ እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • ማንኛውም ሰው በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) ለተመለከቱት የብዝበዛ ዓላማ በኢትዮጵያ ግዛትም ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ግዛት ውጭ መዳረሻ ቦታ ለማድረስ በዛቻ፣ በኃይል፣ በማገት፣ በመጥለፍ፣ ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ በመጠቀም፣ በማታለል፣ የተስፋ ቃል በስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ የሰውን ተጋላጭነት በመጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ሌላውን ሰው የመለመለ፣ ያጓጓዘ፣ ወደ ሌላ ሰው ያስተላለፈ፣ ያስጠለለ፣ የደበቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) ላይ የተጠቀሱት መንገዶች ጥቅም ላይ ባይውሉም ህጻናትን ለብዝበዛ ዓላማ መለመለ፣ ማጓጓዘ፣ ወደ ሌላ ሰው ማስተላፍ፣ ማስጠለል፣ መደበቅ ወይም መቀበል በሰው የመነገድ ድርጊት ነው፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2) ከተጠቀሱት መንገዶች ውስጥ አንዱ ያለ እንደሆነ ተጎጂው ብዝበዛው የሚፈጸምበት መሆኑን ማወቁ ወይም መስማማቱ የድርጊቱን ፈጻሚ ከወንጀል ተጠያቂነት የሚያስቀር አይሆንም፡
 • ለዚህ ንኡስ ክፍል አፈጻጸም “የተጠቀሱት መንገዶች” ማለት ኃይል መጠቀም፣ ማገት፣ መጥለፍ፣ ማስፈራራት ወይም ሌላ የማስገደጃ ዘዴ መጠቀም፣ ማታለል፣ የተስፋ ቃል መስጠት፣ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ የሰውን ተጋላጭነት መጠቀም ወይም ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት መደለያ ወይም ጥቅም መስጠት ወይም መቀበል ነው፡፡

4. ከባድ ሁኔታ

 • በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) ወይም (2) ላይ የተመለከተው የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው፦

ሀ) በሕጻንት፣ በአዕምሮ ህመምተኛ ወይም በአካል ጉዳተኛ ላይ ከሆነ፤

ለ) አደንዛዥ ዕፅ፣ መድሃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም እንደሆነ፤

ሐ) በመንግስት ሠራተኛ ወይም በባለሥልጣን ከሆነና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ ከሆነ፤ ወይም

መ) የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ፈቃድ ባለው አካል ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ፤

ከአስር ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሰላሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደረስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

 • በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) ወይም (2) የተመለከተው የወንጀል ድርጊት፡-

ሀ) የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር የተፈጸመ፤

ለ) በተጎጂው ላይ የማይድን በሽታ ያስከተለ፤ ወይም

ሐ) የተጎጂው ህይወት ወይም ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ ወይም በተጎጂው ላይ ከባድ  የአካል ጉዳት የደረሰበት ወይም ለኢ-ሰብአዊ አያያዝ የተዳረገ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሀምሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

መ) በተጎጂው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ወይም እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

 • የተፈጸመው ድርጊት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ በሚሆንበት ጊዜ በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) ፊደል (ሀ) ህጻናት የሚለው ማክበጃ ምክንያት በማክበጃነት ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

5. በሰው የመነገድ ድርጊትን መደገፍ

በወንጀል ህጉ ስለአባሪነት የተደነገገው እንደተጠበቀው ሆኖ ማንኛዉም ሰው በሰው ለመነገድ ዓላማ መጠቀምያ መሆኑን እያወቀ ፡-

 • የራሱንም ሆነ በይዞታው ስር የሚገኝ ቤት፣ ህንጻ ወይም ግቢ ያከራየ ወይም እንዲጠቀሙበት የፈቀደ፤ ወይም የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ወይም ተጊጂዎችን ያጓጓዘ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • የተጭበረበረ፣ ሃሰተኛ ወይም በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ ያዘጋጅ፣ የሰጠ፣ ያቀረበ ወይም ይዞ የተገኘ እንደሆነ ከአምስት ዓመት አስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ አስራትና ከአስ ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

6. የብዝበዛ ዓለማን ስለመገመት

አንድ ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ (2) ከተጠቀሱ መንገዶች አንዱን በመጠቀም ሰውን የመመልመል፣ የማጓጓዙ፣ ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፉ፣ የማስጠለል፣ የመደበቅ ወይም የመቀበል ተግባራት ማከናወኑ ወይም የተጠቀሱ መንገዶች ባይኖርም እነዚህን ተጋባራት በህጻናት ላይ ማከናወኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ይህን ድርጊት ለየትኛው የብዝበዛ ዓላማ እንደተፈጸመ በአከባቢ ማስረጃ ግምት ለመውሰድ ይቻላል፡፡

7. በሌሎች የዝሙት አዳሪነት መጠቀም

ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 እና 4 ከተመለከተው ሁኔታ ውጭ ሌሎች ሰዎች ከሚፈጽሙት የዝሙት አዳሪነት ተግባር ወይም የሥነ-ምግባር ብልሹነት ለመጠቀም ሲል ወይም የሌላውን ሰው ፍትወተ ስጋ ፍላጎት ለማርካት በማሰብ ሌላውን ሰው ለዝሙት ተግባር ያሰማራ፣ ያገናኘ፣ ያቀረበ፣ በዝሙት አዳሪ ቤት ያስቀመጠ፣ የሥራ ወይም የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለዚህ ተግባር ያዋለ ወይም ያከራየ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ የሌላውን ሰው የዝሙት ድርጊት ወይም የሥነ-ምግባር ብልሹነት መጠቀሚያ አድርጎ የያዘ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከአስር ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል

8.  በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር

 • ማንኛዉም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰዉን በሕገ- ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲገባ፣ ከኢትዮጲያ ግዛት እንዲወጣ፣ በኢትዮጵያ ግዛት እንዲተላለፍ ያደረገ ወይም ሰውን ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ዝግጅት ያደረገ፣ በሂደት ላይ የተገኘ፣ ያጓጓዘ ወይም የተቀበለ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከአስር ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው፦

ሀ) በሕጻናት፣ በአዕምሮ ህመምተኛ ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፤

ለ) አደንዛዥ ዕፅ፣ መድሃኒት ወይም የጦር መሣሪያ በመጠቀም ከሆነ፤

ሐ) በመንግስት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ ከሆነ እና ወንጀሉን የፈጸመው የተሰጠውን ኃላፊነት መከታ በማድረግ፤ ወይም

መ) የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ፈቃድ ያለው ሰው ፈቃዱን ሽፋን በማድረግ፤

ከሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ የተመለከተው የወንጀል ድርጊት፡-

ሀ) በተጎጂው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ የማይድን በሽታ ወይም ዘላቂ የአእምሮ ጉዳት ያስከተለ፤

ለ) ወንጀል አድራጊው ድርጊቱን የፈፀመው የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን፣ ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር፤ ወይም

ሐ) የተጎጂው ህይወት ወይም ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ ወይም ኢ-ሰብአዊ ለሆነ አያያዝ የተዳርገ፤

እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሰላሻ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

መ) በተጎጂው ላይ ሞትን ያስከተለ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ወይም የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም ሞት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

9. በህገወጥ መንገድ መቆየትን ስለመርዳት

 • ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ወይም ለመቆየት የሚያስችል የፀና ፈቃድ የሌለውን ሰው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዲቆይ ሀሰተኛ ሰነድ በመስራት፣ በማቅረብ ወይም በሌላ ማንኛውም ህገ-ወጥ መንገድ የረዳ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • በንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው ድርጊት የተፈጸመው ጥቅም ለማግኘት ያልሆነ እንደሆነ አግባብነት ያለው የወንጀል ህግ ድንጋጌ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

10.  በህገወጥ መንገድ ድንበር ለመሻገር መፈጸሚያነት ስለሚውል ስነድ  

ማንኛውም ሰው በቀጥታም  ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ወይም ሌላ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሰዉን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ለማሻገር ወንጀል መፈፀሚያነት እንዲዉል ሀሰተኛ የጉዞ ወይም የማንነት መታወቂያ ሰነድ ያዘጋጀ፣ ይዞ የተገኘ፣ ያቀረበ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ ከአምስት ዓመት አስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ አስራት እና ከአስር ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ንዑስ ክፍል ሶስት

የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ወንጀል

11.  በህገወጥ መንገድ ሰውን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ

 በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3 እና 8 ከተመለከቱት ሁኔታዎች ውጪ፡-

 • ማንኛም ሰው ወደ ውጭ አገር ሰውን ለሥራ ለመላክ ፈቃድ ሳይኖረው፣ ፈቃዱ ታግዶ ወይም ተሰርዞ እያለ ወይም እንዲልክ ፈቃድ ወዳልተሰጠው አገር ሰውን ለሥራ የላከ እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስር ሁለት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና ከሃያ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው ወንጀል የተፈጸመው የጉብኝት፣ የህክምና፣ የትምህርት ወይም የመሰል ጉዳዮች ቪዛን ሽፋን በማድረግ እንደሆነ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሰላሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ወይም (2) በተመለከተው የወንጀል ድርጊት ምክንያት የተላከው ሰው በሰብዓዊ መብቱ፣ በህይወቱ፣ በአካሉ ወይም በስነ-ልቦናው ላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ የላከው ሰው ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ወይም በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

12. የውጭ አገር ስራ ስምሪት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስለሚፈጸም ወንጀል

ማንኛውም የውጭ አገር ሥራና ሰራተኛ ማገናኘት ፈቃድ ያለው ሰው የሥራ ስምሪት አገልግሎቱን ምክንያት በማድረግ ከሰራተኛ ገንዘብ ወይም ቁስ የተቀበለ፤ የሠራተኛውን መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የጉዞ ሰነድ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰነድ ሰራተኛው ወደ ሥራ ከመሰማራቱ በፊትም ሆነ በኋላ ያለሰራተኛው ፈቃድ የያዘ ወይም የከለከለ፤  በማታለል ወይም በማንኛውም የማስገደጃ መንገድ ሰራተኛው ባለመብት የሆነበትን ጥቅም እንዲተው ያደረገ ፤ ወይም የሰራተኛውን ደሞዝ፣ ንብረት ወይም ሰራተኛው የሚልከውን ገንዘብ በሰራተኛው ፈቃድም ቢሆን እንኳን የያዘ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከሰላሳ ሺህ እስከ ሰባ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ንዑስ ክፍል አራት

ተያያዥ ወንጀሎች

13. ወንጀልን አለማስታወቅ

ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3፣ 4፣ 8 ወይም 11 ሥር የተመለከተው ወንጀል መፈፀሙን ወይም እየተፈጸመ መሆኑን ወይም የወንጀሉን ፈጻሚ ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ለፖሊስ ወይም አግባብነት ላለው የህግ አስከባሪ አካል ወዲያውኑ ያላሳወቀ ወይም ሐሰተኛ ማስረጃ የሰጠ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል፤ ድርጊቱ ከባድ ሲሆን ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡

14.     በጠቋሚዎች እና በምስክሮች ላይ የሚፈጸም ወንጀል

15. ማስረጃን ስለማጥፋት

 • ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ በተመለከተ ወንጀል በምርመራ ወይም በፍርድ ክርክር ሂደት ላይ ሊቀርብ የሚችልን ማስረጃን ሆን ብሎ ያጠፋ፣ ያበላሸ ወይም የደበቀ እንደሆነ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው ተግባር አፈጻጸም ከባድ በሆነ ጊዜ በተለይም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3፣ 4፣ 8 ወይም 11 የተመለከቱ ድርጊቶችን ለማስረዳት የሚውል እና የዋና ማስረጃ ይዘት ያለው እንደሆነ ቅጣቱ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይሆናል፡፡
 • የወንጀል የምርመራውን፣ የክርክሩን ወይም የፍርድ ሂደቱን ማከናወን የተቻለ ወይም ተከሳሽ በወንጀሉ ጥፋተኛ የተባለ ቢሆንም የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) ድንጋጌ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

16. ተጠርጣሪን እንዳይከሰስ ስለመርዳት

 • ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 3፣ 4፣ 5፣ 8፣ 9፣ 10 ወይም 11 በተመለከተ ድርጊት የተጠረጠረን ወይም የተከሰሰን ሰው አስቀድሞ በማስጠንቀቀም ሆነ በመደበቅ፣ ዱካውን በመሸሸግ ወይም በማጥፋት፣ የሚደረግ ምርመራን በማሳሳት ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ተከሶ እንዳይቀርብ የረዳ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሰራት ይቀጣል፡፡
 • የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተውን ድርጊት የፈጸመ ሰው የተከሳሽ መያዝ ወይም መከሰስ ወይም ምርመራው በአግባቡ መከናወንና መጠናቀቅ ከተጠያቂነት ነጻ አያደርገውም፡፡

17. ንብረት ስለመሰወር

 • ማንኛውም ሰው ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረትን እንዳይወረስ ለማድረግ በማሰብ የደበቀ፣ ጉዳት ያደረሰበት ወይም በማናቸውም መልኩ እንዳይታወቅ ያደረገ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
 • የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ቢኖርም ድርጊቱ የተፈጸመው ንብረቱን ህጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ እንደሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

18.     የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት የወንጀል ተጠያቂነት

 • የወንጀል ሕግ አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ (1)፣ (3)፣ እና (4) ላይ የተደነገገው ቢኖርም በዚህ አዋጅ የተደነገገው ወንጀል የተፈፀመው የሕግ ሰውነት በተሰጠው ድርጅት እንደሆነ ለወንጀሉ የሚጣለው ቅጣት፡-

(ሀ) በቀላል እስራት ወይም እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ከሆነ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር

(ለ) ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ከሆነ ከአምስት መቶ ሺህ እስከ  አንድ ሚሊዮን ብር፤

(ሐ) ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ከሆነ ከአንድ ሚልዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር፤

(መ) ከሃያ  ዓመት በላይ በሆነ እስራት ወይም በሞት ከሆነ ከሁለት ሚልዮን ብር እስከ ሶስት ሚሊዮን ብር፤

በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ከተደነገገው ቅጣት በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ ጠያቂነት ወይም በራሱ አነሳሽነት ድርጅቱ እንዲፈርስ ወይም ንብረቱ እንዲወረስ ሊወስን ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው ቅጣት በድርጅቱ ስም ወይም ለድርጅቱ ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ በድርጊቱ የተሳተፈውን የድርጅቱን ባለቤት፣ ሥራ አስኪያጅ፣ የድርጅቱን ሠራተኛ ወይም ሌላ ማንኛውንም ሰው የወንጀል ተጠያቂነት አያስቀረውም፡፡

ክፍል ሦስት

ስለወንጀል መከላከል እና ንብረት መውረስ

19.  ለአደጋ የተጋለጡ ሰውን ሰለማዳን

 • ፖሊስ በሰው የመነገድ ወይም ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የተፈጸመ፣ እየተፈፀመ ወይም ሊፈፀም የተቃረበ ለመሆኑ በበቂ ምክንያት የጠረጠረ እንደሆነ፦

ሀ) ማንኛውንም ማጓጓዣ፣ ቤት፣ ስፍራ ወይም ይዞታ በመፈተሸ ለድርጊቱ የተጋለጡ ወይም በድርጊቱ የተጎዱ ሰውን ለማዳን ይችላል፡፡

ለ) ድንበር እያቋረጡ ወይም ድንበር ለማቋረጥ በሂደት ላይ ያሉ ሰውን ለማስቆምና ለማጣራት ይችላል፤ ሆኖም የማጣራቱን ተግባር ወዲያውኑ የማከናወን እና ተጎጂ ወይም ተጠርጣሪ ያልሆኑ ሰውን ወዲያው የመልቀቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

 • ፖሊስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) (ሀ) መሰረት ቤት እና ይዞታን መፈተሸ የሚችለው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ነው፡፡ አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር ፖሊስ ፍተሻውን ያለ ፍርድ ቤት ማድረግ የሚችል ሲሆን በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም አስቸኳይ ሁኔታ የነበረ መሆኑን ጭምር በመመርመር ተገቢ ነው የሚለውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
 • ፖሊስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተውን ተግባር ሲፈጽም ተጎጂዎችን ያገኘ እንደሆነ ተገቢው እንክብካቤና ድጋፍ ወደሚያገኙበት ማዕከል ያደርሳል፡፡
 • ፖሊስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተውን ተግባር ሲፈጽም የህመም ስቃይ ወይም ጉዳት ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች ባጋጠሙት ጊዜ በማናቸውም የመንግስት ወይም የግል የህክምና ተቋም እርዳታ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ለለመስጠት ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (4) በተገለጸው ተግባር ምክንያት የህክምና አገልግሎት የሰጠ ተቋም ለአገልግሎቱ ወጪ ከፈንዱ የሚከፈለው ይሆናል፤ የአከፋፈሉ ሁኔታ ስርዓት ስለፈንዱ አስተዳደር በሚወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡

20. ከወንጀል ጋር የተገናኘን ንብረት ስለማገድና መያዝ

 • በሌላ ህግ ስለማይታገዱ እና ስለማይወረሱ ንብረቶች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት፣ በዐቃቤ ህግ ወይም በፖሊስ አመልካችነት በዚህ አዋጅ መሰረት ሊወረስ የሚችል ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጊዜያዊ እርምጃዎችን ጨምሮ የማገድ ወይም የመያዝ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
 • ፖሊስ የወንጀል ክሱ ከመመስረቱ በፊት ወይም ዐቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ከተመሰረተ በኋላ ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት እንዲታገድ ወይም እንዲያዝ በቃለ መሀላ በተደገፈ ማመልከቻ ፍርድ ቤትን ለመጠየቅ ይችላል፡፡
 • ተከሳሹ በሌለበት የእግድ ወይም የመያዙ ትእዛዝ ከተሰጠ ፖሊስ ወይም ዐቃቤ ህግ ትእዛዙንና ቃለ መሀላውን ለተከሳሹ ወይም በንብረቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም አለኝ ለሚል ሰው ያደርሳል፡፡ ተከሳሽን ማግኘት ያልተቻለ እንደሆነ በቋሚ አድራሻው ትዕዛዙን ይለጥፋል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት የተወሰነን ማንኛውም ጊዜያዊ እርምጃ፤ ውሳኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት በራሱ ተነሳሽነት ወይም በዐቃቤ ሕግ፣ በወንጀሉ ተጠርጣሪ ወይም በንብረቱ ላይ መብት አለኝ በሚል ሰው አመልካችነት በማናቸውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ቢኖርም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር የወንጀል ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን ያለው ዐቃቤ ህግ ተቋም ኃላፊ ለሰባ ሁለት ሰዓት የሚፀና ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ዐቃቤ ህግ ጊዜያዊ እግድ መስጠት ያስፈለገበትን ምክንያት በመግለጽ ሰባ ሁለት ሰዓቱ ከማለፉ በፊት ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት፤ ፍርድ ቤቱም ተገቢነት ያለውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
 • ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “ማገድ” ማለት በንብረት ላይ በፍርድ ቤት በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ጸንቶ ለሚቆይበት ጊዜ ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሰረት ለሰባ ሁለት ሰዓት ወደ ሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ፣ እንዳይለወጥ፣ እንዳይወገድ ወይም እንዳይንቀሳቀስ መከልከል ነው፡፡
 • ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም “መያዝ” ማለት በንብረት ላይ ታግዶ ያለ ንብረት በፍርድ ቤት በተሾመና ቁጥጥር በሚደረግበት ንብረት አስተዳዳሪ ስር እንዲተዳደር ማድረግ ነው፡፡

21. ንብረት ስለመውረስ

 • በዚህ አዋጅ የተመለከተ ወንጀል ጉዳይን ለማየት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት፡-

ሀ) በተከሳሽ ላይ የወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰጠ እንደሆነ፤ ወይም

ለ) የወንጀሉ ፈጻሚ ባለመታወቁ፣ በመሰወሩ፣ በመሞቱ፣ በተለያየ ምክንያት ምርመራ ወይም ክስ በመቋረጡ ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ባይሰጥም ንብረቱ ከወንጀሉ ጋር የተገናኘ መሆኑን ሲያረጋገጥ፤

ንብረቱ እንዲወረስ ይወስናል፡፡

 • ፍርድ ቤቱ በዚህ አንቀጽ መሰረት ከወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት እንዲወረስ ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት በንብረቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም አለኝ ለሚል ማንኛውም ሰው የመሰማት እድል መስጠት አለበት፡፡
 • በዚህ አንቀጽ መሰረት የተወረሰው ንብረት በዚህ አዋጅ መሰረት ወደ ተቋቋመው ፈንድ ገቢ ይደረጋል፡፡

22. የንብረት አስተዳደሪ  ስለመሾም

 • ፍርድ ቤት ከወንጀሉ ጋር የተገናኘውን ንብረት ወደ ፈንዱ ገቢ እንዲሆን ከመወሰኑ በፊት፡-

ሀ) ንብረቱን የሚያስተዳደር አስተዳዳሪ መሾም፣

ለ) ንብረቱን በይዞታው ወይም በአደራ አስቀማጭነት ወይም በጠባቂነት የያዘን ሰው ንብረቱን እንዲያስረክብ ለማዘዝ፣

ሐ) አስተዳዳሪው ንብረቱን በይዞታው ስር እንዲያደርግ፣ እንዲጠብቅና እንዲያስተዳድር ለማዘዝ፤

መ) አስተዳዳሪው በአስተዳዳሪነት የተሾመበትን ንብረት ለመጠበቅ፣ ለማስተዳደር እና ለማሻሻል የሚያስችለውን ስልጣን ለመስጠት፤

ሠ) ንብረት አስተዳዳሪው በአስተዳዳሪነት የተሾመበትን ንብረት በተመለከተ የመክሰስና መከሰስ መብት እንዲኖረው፤ ከንብረቱ የሚገኝ ኪራይ፣ ትርፍ ወይም ሌላ ማንኛውንም ገቢ ለመሰብሰብ እና የሰበሰበውንም ገንዘብ ንብረቱን ለማስተዳደር ጠቃሚ ለሚሆን ጉዳይ ለማዋል እንዲችል ወይም ተገቢ መስሎ የታየውን ሌላ ስልጣን ለመስጠት፤

ይችላል፡፡

 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ -አንቀጽ (1) መሰረት ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ትእዛዝ ንብረቱን ለማስተዳደር የሚያስፈልገውን ወጪ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውም ሹመቱን ከመስጠቱ በፊት የሂሳብ ማጣራት እንዲደረግ ለማዘዝ ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት በአስተዳዳሪነት የሚሾመው የተፈጥሮ ሰው የሆነ እንደሆነ መልካም ሥነ-ምግባርና ችሎታ ያለው፣ በንብረቱ ላይ የጥቅም ግጭት የሌለው፣ ከተከሳሽ ወይም በንብረቱ ላይ መብት ወይም ጥቅም ካለው ሰው ጋር ዝምድና ወይም የጥቅም ግንኙነት የሌለው መሆን ይኖርበታል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት በአስተዳዳሪነት የሚሾመው የህግ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ፤ ድርጅቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት የኦዲት ግኝት የሌለበት፣ መልካም የሂሳብ አያያዝ ስርዓት ያለው መሆኑን እና የጥቅም ግጭት የሌለው መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡
 • በዚህ አንቀጽ መሰረት ንብረት አስተዳዳሪን ፍርድ ቤት የሚሾመው በራሱ ተነሳሽነት፣ በፖሊስ ወይም በዐቃቤ ህጉ አመልካችነት ሊሆን ይችላል፡፡

ክፍል አራት

ስለተጎጂዎች ጥበቃ፣ መልሶ ማቋቋም እና ካሣ

23. ተጎጂዎችን ስለመመለስ

 • የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተጎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
 • ተጎጂው የታሰረ ወይም የተያዘ እንደሆነ ተጎጂው ባለበት አገር የሚገኝ ወይም በቅርበት የሚሰራ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ተጎጂው እንዲለቀቅ እና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡
 • በየደረጃው ያሉ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋማት አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር በሀገር ውስጥ የሚገኙ እንዲሁም ከወጪ አገር የተመለሱ ተጎጂዎችን ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡
 • ስለቪዛ፣ ስለጉዞ ሰነድ እና ሌሎች ሁኔታዎች በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የውጭ አገር ዜጋ የሆነ ተጎጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ እንደሆነ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት እና ከሚመለከተው አገር ዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ጋር በመተባበር ተጎጂው ወደ አገሩ እንዲመለስ ያደርጋል፡፡

24. የተጎጂዎች ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋም

 • ተጎጂዎች፡-

ሀ) አስፈላጊው ጥበቃ እና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፤ የሚደረገው ጥበቃ እና ድጋፍ የተጎጂዎቹን ሁኔታ ያማከለ በተለይም የሴቶች፣ ህጻናት፣ የአዕምሮ ህመምተኛ እና አካል ጉዳተኖችን ለአደጋ ተጋላጭነትና ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤

ለ) ግላዊ ሚስጥራቸው እና ሰብዓዊ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ መያዝ እና ተገቢው የጤና፣ የማህበራዊ አገልግሎት፣ የህግና ሥነ-ልቦና ምክርና ድጋፍ፣ ጊዚያዊ መጠለያ እና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይደረጋል፤

ሐ) ስለሚደረግላቸው ጥበቃና ድጋፍ፣ እና በምርመራና በፍርድ ሂደት ወቅት ጉዳዩ ስለደረሰበት ደረጃ መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

መ) በማንኛውም ሁኔታ በፖሊስ ጣቢያ፣ በማረፊያ ቤት ወይም በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረግ የለባቸውም፡፡

 • የተጎጂው ሁኔታ ካላስምገደደ ወይም ተጎጂው ለምርመራ ወይም ለክርክር ሂደት አስፈላጊ የሆነና ለመመስከር ፈቃደኛ የሆነ ካልሆነ በስተቀር በጊዜያዊ መጠለያ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ መደረግ የለበትም፡፡
 • በዚህ አዋጅ የተመለከቱ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለመመርመር፣ ክስ ለማቅረብ ወይም የዳኝነት ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ተጎጂን በሚያገኙበት ወቅት የተጎጂውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተሻለ ድጋፍ እና እንክብካቤ ወደሚያገኝበት ተቋማት ተጎጂውን የመላክ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
 • የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስት ኤጀንሲ መኖሪያቸው በከተማ ለሆኑ ተጎጅዎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ያደርጋል፡፡
 • የገጠር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ መኖሪያቸው በገጠር ለሆኑ ተጎጅዎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ያደርጋል፡፡
 • ስለስደተኞች በሌላ ህግ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የሌለው የውጭ አገር ዜጋ ተጎጂ ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ እንደሆነ ተጎጂዎች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ከሚፈጸመው የመልሶ ማቋቋም አገልግሎት በስተቀር ተገቢው ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ እንደነገሩ ሁኔታም ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኝ ሊደረግ ይችላል፡፡

25.      የምስክሮች ጥበቃ

በዚህ አዋጅ በተመለከተ ወንጀል ምስክር ወይም ጠቋሚ የሆነ ሰው በዚሁ ምክንያት የእርሱ ወይም የቤተሰቡ ህይወት ወይም ንብረት ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነ በምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ተገቢ ጥበቃ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

26. ስለካሣ

 • ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ በተመለከተው ወንጀል በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት ከሚወስነው ቅጣትና መቀጮ በተጨማሪ የሕክምና፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው ወጭዎችን ጨምሮ ተጎጂው ላይ ለደረሰው የጉዳት ካሳ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ተጎጂውን ለማዳንና ለመንከባከብ ያወጡትን ወጪ እንዲከፈል ሊወስን ይችላል፡፡
 • ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ በተመለከተ ወንጀል ምክንያት የህሊና ጉዳት ለደረሰበት ሰው ከአንድ ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ ብር የሚደርስ የህሊና ጉዳት ካሳ ለመወሰን ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚወሰን ካሳ በማናቸውም ሁኔታ ተጎጂው ለወንጀል ፈጻሚው ከከፈለው ገንዘብ፣ ካስገኘው ጥቅም ወይም በወንጀል ድርጊቱ ምክንያት ተጎጂው ካጣው ወይም ሊያጣው ከሚችለው ገቢ ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
 • ፍርድ ቤት በራሱ አነሳሽነት ወይም በዐቃቤ ህግ አመልካችነት የካሳ ጉዳይን ከወንጀል መዝገቡ ጋር በማጣመር ወይም ከወንጀል መዝገቡ በመነጠል ለማየት ይችላል፡፡
 • ፍርድ ቤት በዚህ አንቀጽ መሰረት ካሳን የወሰነ እና ተከሳሽ መክፈል የማይችል መሆኑ የተረጋገጠ እደሆነ ለተጎጂው ወይም ስለተጎጂው ወጪ ላወጣው ሌሎች ሰዎች የሚንስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ በተመለከተው መጠንና ሁኔታ መሰረት ከፈንዱ እንዲከፈል ሊወስን ይችላል፡፡
 • በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት ፍርድ ቤት ከፈንዱ እንዲከፈለው የወሰነው የካሳ መጠን ለተጎጂው የወሰነው አጠቃላይ ካሳ መጠን ያልሆነ እንደሆነ፤ ቀሪውን የጉዳት ካሳ ተጎጂው የድርጊቱ ፈጻሚ የመክፈል አቅም ሲኖረው ለመጠየቅ ይችላል፡፡ መንግስትም ከፈንዱ ለተጎጂው ለከፈለው መጠን ተከሳሽን ለመጠየቅ ይችላል፡፡

ክፍል አምስት

ስለፈንድ መቋቋም

27. መቋቋም

በሰው የመነገድ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ (ከዚህ በኋላ “ፈንድ” እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

28. የገቢ ምንጭ

የፈንዱ የገቢ ምንጭ፡-

 • ከመንግስት ከሚመደብ በጀት፣
 • በዚህ አዋጅ መሠረት የሚወረሱ ንብረቶችና የሚሰበሰቡ መቀጮዎች፣
 • ከግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚገኝ ልገሳ እና እርዳታ፣ እና
 • ከሌሎች የገንዘብ ሚኒስቴር ከሚያፀድቃቸው የገንዘብ ምንጮች ከሚገኙ ገቢዎች፣

ይሆናል፡፡

29. ዓላማ

የፈንዱ ዓላማ፦

 • የተጎጂዎች የህክምና፣ የስነ-ልቦናና የህግ ምክር፣ የትራንስፖርት እና መሰል አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚወጣ ወጪን ለመሸፍን፤
 • ለተጎጂዎች ቁሳዊ እርዳታን ለማድረግ፤
 • ለተጎጂዎች የሙያ ሥልጠና እና በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ ለማድረግ፤
 • የተጎጂዎችን ቤተሰብ ማፈላለግ እና ከቤተሰብና ከማሕበረሰቡ ጋር ለማቀላቀል የሚደረገውን ጥረት ድጋፍ ለማድረግ፤
 • ለተጎጂዎች ጊዜያዊ መጠለያ ግንባታን ለማከናወን እና
 • በፍርድ ቤት የሚወሰን ካሳን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ መሰረት ለመክፈል፤

ነው፡፡

30. የፈንዱ አስተዳደር እና አጠቃቀም

ፈንዱ ስለሚተዳደርበት፣ ለተጎጂዎች አገልግሎት ስለሚውልበት፣ ፍርድ ቤት ለተጎጂዎች ካሳ ከፈንዱ እንዲከፈላቸው ስለሚወስንበት ሁኔታና መጠን እና ተያያዥ ጉዳዮች ስለሚፈጸሙበት አግባብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይወሰናል፡፡

31. የፈንዱ የሂሳብ መዝገብና ኦዲት

 • የፈንዱ የሂሳብ መዛግብትና ገንዘብ ነክ ሰነዶች በየዓመቱ በዋናው ኦዲተር ወይም ዋናው ኦዲተር በሚሰይመው ኦዲተር ይመረመራሉ፡፡
 • ፈንዱን የሚያስተዳድረው አካል የኦዲት ሪፖርቱን የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠሪ ለሆነለት አካል ማቅረብ አለበት፡፡

32. የበጀት ዓመት

የፈንዱ የበጀት ዓመት የመንግስት የበጀት ዓመት ይሆናል፡፡

ክፍል ስድስት

ስለብሔራዊ ምክር ቤት፣ የተቋማት ሚና እና ትብብር

33. ስለብሔራዊ ምክር ቤት መቋቋም

 • በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ መላክ ወንጀል መከላከልና መቆጣጠር በብሔራዊ ደረጃ አስተባባሪ ምክር ቤት (ከዚህ በኋላ “ብሔራዊ ምክር ቤት” እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡
 • የብሔራዊ ምክር ቤቱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡
 • ብሔራዊ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ፣ የሴቶች፣ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ባንክ፣ የማዕክላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ ክልሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ እና እንደ አግባብነቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲካተቱ የሚደረጉ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ ይሆናል፡፡
 • የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት በተቋማቱ ኃላፊዎች ወይም ምክትል ኃፊዎች የሚወከሉ ይሆናል፡፡
 • ክልሎች አግባብነት ያላቸውን የክልሉ ተቋማትን ያቀፈና ተጠሪነቱ ለክልሉ ፕሬዝዳንት የሆነ መሰል ምክር ቤት ሊኖራቸው ይችላሉ፡፡

34. የብሔራዊ ምክር ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት

ብሔራዊ ምክር ቤቱ፡-

 • በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲ፣ ህግ እና ስትራቴጂ ያመነጫል፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሌላ ህግ በግልጽ ፖሊሲ፣ ህግ እና ስትራቴጂ እንዲያመነጭ ስልጣን የተሰጠው አካል ሲኖር ያስተባብራል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤
 • ተጎጂዎችን ማዳን፣ መልሶ ማቋቋም፣ ልዩ ልዩ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ሁኔታ፣ ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከተ አገር አቀፍ የቅብብሎሽ ስርዓት መመሪያ ያወጣል፤
 • ስለአገር ውስጥ መፈናቀል፣ ስደት እና ፍልሰት በህግ ተግባርና ኃላፊነት የተሰጣቸውን አካላት በማስተባበር የፖሊሲ፣ የህግ ወይም ስትራቴጂ ማዕቀፍ እንዲወጣ ያደርጋል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤
 • ለስድትና ፍልሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና ምላሽ ስለሚደረግበት፣ የስራ ዕድል ስለሚፈጠርበትና መሰል ጉዳዮች ተግባራዊ ስለሚደረጉበት ሁኔታ ምክረ-ሀሳብ ያቀርባል፣ እነዚህ ጉዳዮች ተግባራ የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋሞች ተግራን ስለመፈጸማቸው ይከታተላል፣ አስፈላጊውን ድጋ ያደርጋል፡፡
 • ለብሔራዊ የትብብር ጥምረት የሥራ መመሪያ ይሰጣል፣ የጥምረቱን መርሀ ግብር ያጸድቃል፣ አፈጻጸሙን ይከታተላል፣ ጉድለቶች እንዲስተካከሉ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
 • የውስጥ አስራሩን እና ከብሔራዊ አስተባባሪ ጥምረቱ ጋር ስለሚኖረው የአሰራር ግንኙነት በተመለከተ መመሪያ ያወጣል፡፡

35. ስለብሔራዊ አስተባባሪ ጥምረት መቋቋም

 • በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክወንጀሎች ተከላካይ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት (ከዚህ በኋላ “ብሔራዊ የትብብር ጥምረት” እየተባለ የሚጠራ) በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡
 • የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ተጠሪነት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ይሆናል፡፡
 • ጥምረቱ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚመራ ሆኖ ክልሎችን ሳይጨምር በዚህ አዋጅ አንቀፅ 33 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የተመለከቱትን አካላት ያካተተ ይሆናል፡፡
 • የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ የውስጥ አደረጃጃት እና አሰራር ብሔራዊ ምክር ቤቱ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡
 • ክልሎች ይህን ህግ ለማስፈፀም እንደየክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አግባብነት ያላቸውን አካላትን ያቀፈ እና በዐቃቤ ህግ ተቋም የሚመራ የክልል የትብብር ጥምረት ማቋቋም አለባቸው፡፡

36. የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ተግባርና ኃላፊነት

የብሔራዊ የትብብር ጥምረት፡-

 • በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ጥናቶችን በማጥናት፣ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ህጎችን በማዘጋጀት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ያቀርባል፤ አግባብ ባለው አካል ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ያስተባብራል፤
 • ተጎጂዎችን ማዳን፣ መልሶ ማቋቋም፣ ልዩ ልዩ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ሁኔታ፣ ከህብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ስለሚችሉበት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከተ አገር አቀፍ የቅብብሎሽ ስርዓት መመሪያ እና የአሰራር ስርዓት ያዘጋጃል፤ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ሲጸድቅ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፡፡
 • ስለአገር ውስጥ መፈናቀል፣ ስደትና ፍልሰት፤ የስራ ዕድል ፈጠራና መሰል ጉዳዮችን የተመለከተ የፖሊሲ፣ የህግ ወይም የስትራቴጂ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓት እንዲዘጋጅ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፣ በሚመለከተው አካል ሲጸድቅም አፈጻጸሙን ይከታተላል፤
 • የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድና የድርጊት መረሐ-ግብር ያዘጋጃል፤ ለብሔራዊ ምክር ቤቱ በማቅረብ ሲጸድቅ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
 • በዚህ አዋጅ የተሸፈኑ ጉዳዮች ተግባርና ኃላፊነት በተናጥል የተሰጣቸው ተቋማት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሰልመወጣታቸው ይከታተላል፣ አፈጻጸሙን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
 • ለብሔራዊ ምክር ቤቱ በየወቅቱ ሪፖርት ያቀርባል፣ የሚሰጡ ግብረ መልሶችን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
 • በአዋጅ ቁጥር 923/2008 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተውን ተግባራት ያከናውናል፤
 • ሌሎች በብሔራዊ ኮሚቴው የሚሰጡ ልዩ ልዩ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

37. ስለጥምረቱ  ጽህፈት ቤት

 • የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ተግባርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚደግፍና የሚያስተባብር ፅህፈት ቤት ያደራጃል፡፡
 • የክልል ዐቃቤ ህግ ተቋማት የክልል የትብብር ጥምረትን የሚደግፍና የሚያስተባበር ፅ/ቤት ያደራጃሉ፡፡

38. የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ኃላፊነት

በሌላ ህግ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር እንደተጠበቀ

በዚህ አዋጅ የተመለከቱትን ወንጀሎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሕግ አስከባሪ አካላትን ሚና፣ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ ህጎችን፣ ወንጀለኞች ስለሚጠቀሟቸው የመመልመያ ዘዴዎች፣ ስለብዝበዛ ዓይነቶች እና የአፈጻጸም ስልቶች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለህብረተሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ይፈጥራል፤ ሆኖ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ:-

 • ለፌዴራልና ክልል ፖሊሲ፣ ዐቃቤያነ ህግና ዳኞች የወንጀል መከላከል፣ የምርመራ ስራዎችን፣ ማስረጃ ምዘናን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የአቅም ግምባታ ስራ ያከናውናል፡፡

39. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፦

 • ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተጎጂዎችን መረጃ፣ የሚገኙበትን አገር፣ ያሉበትን ሁኔታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ መረጃ ያጠናቅራል፣ ለሚመለከታቸው አካላት ያደርሳል፤
 • በውጪ ሀገር የሚገኙ የተለዩ ተጎጂዎችን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስረክባል፤
 • በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰውን ለስራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል መዳረሻ በሆኑ አገራት ለሚገኙ ዜጎች የየአገራቱን የስጋት ደረጃ በመለየት በየወቅቱ በተለያዩ የግንኙነት ዘዴዎች እንዲያውቁት ያደርጋል፤ የየራሳቸውን ማህበረሰብ እንዲያቋቁሙ፣ በማህበረሰቡ አደረጃጀት መሠረት በየአገራቱ መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡

40. የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነት

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ፣ ከክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋማት እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በሀገር ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎችን መረጃ፣ ያሉበትን ሁኔታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ መረጃ ያጠናቅራል፣ ለሚመለከታቸው አካላት ያደርሳል፤

41. የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊነት

የፌዴራል ፖሊስ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አግልግሎት፣ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዚህ አዋጅ የተደነገጉ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንደነገሩ ሁኔታ በምርመራ፣ መረጃ በመለዋወጥ፣ በአቅም ግንባታ እና በመሳሰሉ ጉዳዮች በጋራ ይሰራል፡፡

42. የዳኝነት ሥልጣን

 • የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ በተደነገጉ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
 • በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ (2) እና አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ (3) የተመለከቱት ጉዳዮች የሚታዩት ሶስት ዳኛ በተሰየመበት ችሎት ይሆናል፡፡

43. የዓለም አቀፍ ትብብር

 • የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፡-

ሀ) በዚህ አዋጅ በተመለከቱ ወንጀሎች ምርመራ፣ ወንጀለኛ አሳልፎ መስጠትን፣ መረጃ ልውውጥ እና ሌሎች የጋራ ትብብር የህግ ድጋፍ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሌላ ሀገር አግባብ ካለው ባለሥልጣን ጋር እንካ በእንካ መርህን፣ ኢትዮጵያ ተዋዋይ ወገን በሆነችበት ስምምነት እና የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት በትብብር ይሰራል፣ እንዲሁም ማዕከላዊ ባለስልጣን ሆኖ ያገለግላል፡፡

ለ) እንደአስፈጊነቱ ወንጀሎቹን ለመከላከል እና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከሌሎች አገራት ጋር ልዩ ልዩ የትብብር ማዕቀፎችን ሊፈራረም ይችላል፡፡

 • የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እንደተጠበቀ ሆኖ የፌዴራል ፖሊስ ተመሳሳይ ተልዕኮ ካለው መሰል የሌላ ሀገር ተቋም ጋር በህግ ተቋሙ ከተሰጠው ስልጣን ጋር በተያያዘ እንካ በእንካ መርህ እና በኢትዮጵያ የህግ ማቀፍ መሰረት የመረጃ ልውውጥና የጋራ ትብብር ሊያደርግ እና የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ይችላል፡፡

ክፍል ሰባት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

44. የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች

 1. ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች ይህ አዋጅ ለተከሳሸ የተሻለ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2007 ወይም በሌሎች አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት ፍፃሜ ያገኛሉ፡፡
 2. ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 909/2007 መሰረት አድርገው የወጡ መመሪያዎች በሌሎች መመሪያዎች እስከሚተኩ ድረስ ከዚህ አዋጅ ጋር በሚጣጣም መልኩ ተፈጻሚነታቸው ይቀጥላል፡፡

45. ስለተሻረ እና ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ድንጋጌዎች

 • “ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2007” በዚህ አዋጅ ተሽሯል፡፡
 • የወንጀል ሕግ አንቀጽ 243 ንዑስ አንቀጽ (2)፣ (3)፣ ከአንቀጽ 596 እስከ አንቀጽ 599 እና ከአንቀጽ 634 እስከ አንቀጽ 638 የተመለከቱ ድንጋጌዎች በዚህ አዋጅ ተሽረዋል፡፡
 • የወንጀል ሕግ አንቀጽ 243 ንዑስ አንቀጽ (1) ፊደል (ለ) እና የኢሜግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995 አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ (2) በኢትዮጵያ እንዲቆይ መርዳቱ የተፈጸመው የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በሚሆንበት ጊዜ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

46. ደንብና መመሪያ የማውጣት ስልጣን

 • የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚያስፈልግ ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡
 • የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ይህን አዋጅ ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የሚወጣውን ደንብ ለማስፈፀም መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡

47. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ——– ቀን 2011 ዓ.ም

ሳህለወርቅ ዘውዴ

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት

 

 

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.