COVID_19

የኮቪ-ድ 19 ወረርሽኝና የኢትዮጵያ 2012 ምርጫ መተላልፍን በሚመለከት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ የጋራ አቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እና ክልከላዎች፣ የቦርዱን የምራጫ 2012 እቅድና የግዜ ሰሌዳ በታቀደለት መሰረት እንዳይከናወን አግዷል ሲል መጋቢት 22 ቀን 2012 ባወጣው መግለጫ ኣሳውቋል። ቦርዱ ከአሁን ቀድም ባወጣው የግዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫውን ማካሄድ የማይችል መሆኑን፣ የወጣውን የግዜ ሰሌዳ መሰርዙንና በግዜ ሰሌዳዉ መከናወን የሚገባቸው ዋና ዋና ተግባራት እንድቆሙ መወሰኑን ገልጿል። ባጠቃላይ ቦርዱ ምርጫውን ማካሄድ የማይችል መሆኑን የደረሰበትን ወሳኔ ከዳሰሳ ጥናቱ ጋር አያይዞ ውሳኔ እንድሰጥበት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማስተላለፉን በመግለጫው አትቷል።
የምርጫ ቦርዱ ከዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር ማድረጉን በዚሁ መጋቢት 22 ቀን 2012 ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። በርግጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ ም ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ የተገኙበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብስባ አዘጋጅቶ ምክክር ተደርጓል። ግን በስብሰባዉ መጨረሻ ላይ ‘የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ሌላ ዙር ስብሰባ እንደሚጠራና በዚህ ጉዳይ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይ ውይይትና ክርክር’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር። ነገር ግን ለሌላ ዙር የታቀደው ስብሰባ ሳይደርግ ቀርቶ ቦርዱ ሌላው ቢቀር በውስጥ መስመር እንኳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያሳውቅ ነበር መግለጫውን ያወጣው።
አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በለዉጡ ማግስት ከተቋቋሙት የዲሞክራሲ ተቁማት ሁሉ የተሻለና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረው ትብብር አበረታች እንደነበር ሳንጠቅስ አናልፍም። ይሁንና በዚህ አጋጣሚ የቦርዱን አንዳንድ ጉድለቶች ማንሳት እንፈልጋለን ። እነዚህም
አንደኛ፥  የክልል ዕጩ የምርጫ አስፈጻሚ አባላት ምልመላና ቅጥርን በሚመለከት ስም ዝርዝርራቸው ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚላከው ለመቅጠር ጥቂት ቀናት ስቀሩ ነበር።
ሁለተኛ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባትና ለመንከባከብ እንዲሁም ለነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሃላፍነቱ መሆኑ የምርጫ ቦርድን መልሶ ለማቋቋም የወጣው ህግ ስልጣን ይሰጠዋል ።  ሆኖም ግን ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በመንግስት የሚደርሱ ተጽዕኖዎችን በሚመለከት  መረጃዎችን ማሰባሰብ እና የሚቀርቡለትን ሪፖርቶችንም ለመከተታል ሃላፍነቱን አልተወጣም ብለን እናምናለን። በመንግስትና በገዢው ፓርቲ በአባሎቻችን ላይ የሚደርስ ወከባና እስራትን ማስቆም አልቻለም። የተፎካካሪ ፓርቲዎችን መብቶች ለማስከበር ደፍሮ ስሟገትና እርምጃ ሲወስድ አልተስተዋለም።
ወደ ፍሬ ነገሩ ስንመለስ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 3 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመንን ይገድባል። የሄውም አንቀጽ 58(3) “ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፣ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል” ይላል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብልክ ህገ መንግስት በወረርሽኝ በሽታም ሆነ በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ለአምስት ዓምት የስራ ዘመን ብቻ የተመረጠ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ካለቀ በኋላ ምርጫን ማራዛም ወይም ማቆየት የሚችልበትን ስልጣን አልሰጠውም። የትኛውም የመንግስት አካል የስልጣን ዘመኑ ካለቀ በኋላ ምርጫን እንዲያራዝም ህገ መንግስቱ አይፈቅድለትም።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት፣ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የዲሞክራሲ ተቋማትን ለመግንባት የገባዉን ቃል በማፍረስ ወደ ሃይል እርምጃና ራስን በስልጣን ለመደላደል ዞሮ በከፍተኛ ወታደራዊ ግንባታና በፋይናንስ ጡንቻዉን በማፈርጠም ላይ የገኛል። ፖለቲካውንም ወደ ንግድ ወይም ብዝነስ ቀይሮታል። ሰብሃዊ መብቶችን ክፉኛ እየረገጠ መሁኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።
1.  ኮቪድ-19 በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ማህበረስብ በተለይም በኢትዮጵያ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምራጫ 2012 እቅድና የግዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮቶችን ደቅኖ ቦርዱን እየተፈታተነ መሆኑን እንረዳለን። ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለሌላ ዙር የታቀደው ስብሰባ ሳይደርግ ቀርቶ ቦርዱ ሌላው ቢቀር በውስጥ መስመር እንኳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያሳውቅ መጋቢት 22 ቀን 2012 ያወጣው መግለጫና ውሳኔ አግባብ አልነበረም እንላለን።
2. ወረርሽኙ በአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት፣ በኢኮኖሚው እና ማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም በሰው ህይወት ላይ የሚያስከትለውና እያስከተለ ያለውን ችግሮች ለማስወገድ ቅድሚያ በመስጠት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያንና ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ሆነን የበኩላችን ድርሻ እንወጣለን። በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረሱ ወረርሽኝን እየተዋጋን በዚህም ሳንዘናጋ በሌላ በኩል ደግም የአለም ጤና ድርጅትን በማማከር ለቀጣዩ ምርጫ ለመዘጋጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድናደርግ ለሁሉም ፖለቲካ ፓርትዎች ጥሪ እናስተላልፋለን።
3. ምርጫውን ለማራዘምም ሆነ ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ሁሉን ባለድርሻ አካላት ሳያማክር መንግስትም ሆነ የትኛውም አካል አንዳች ውሳኔ እንዳያስተላልፍ አጥብቀን እናሳስባለን። የአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተናል፣ ያገባናል ከሚሉት ባለድርሻ አካላት ጋር ወይይት፣ ክርክር፣ ምክክር እና ስምምነት ላይ ሳይደረስ  በመንግስት አካል ውሳኔ ብቻ (unilateral decision ) ምርጫውን ማራዘምና ቀጣዩ የአገሪቱን ዕጣ ፋንታ ለመወሰን መሞከር የባሰ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለን እንሰጋለን። የመንግስት ስልጣን በአንድ ወገን እጅ ብቻ እንድቆይ ማድርግ ኢ- ህገመንግስታዊ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራር ከመሆኑም በላይ ህገ መንግስታዊ ቀውስን ከማስከተሉ በላይ ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል ብለን እንሰጋለን። በዚህ አይነት መንገድ ስልጣን ላይ የሚቆይ መንግስት ቀጣዩንም ምርጫ በፈለገው መንገድ መዘወር ይችላል ብለን እናምናለን።
4. ዲሞክራሲን ማስፈን ፣ግጭቶችን ማስወገድ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቆጣጠር ባልተቻለበት ስርዓት ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተሽመደመደበት እና ማህበራዊ ቀወሶች በተንሰራፉበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን የማራዘም ውሳኔም ሆነ ከመስከረም 2013 በኋላ ሊኖር የሚችል መንግስትን ለመወሰን አሁን ላለው መንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለን እናምናለን።
5. ወረርሽኙን ለመግታት ተብለው በመንግስት የሚወጡ ሁጎች፣ ደንቦችና ውሳኔዎች እየጠበበ የመጣውን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የባሰ ለማጥበብ መንግስት እንዳይጠቀምበት ቁጥጥር ማድረግና መንግስት አላስፈላጊ የሆኑ ህጎችን ከማውጣት ተቆጥቦ የኮሮና ቫይረሱ ወረርሽኝን የሚመለከቱ መመሪያዎችና መልዕክቶችን በዋናነት ለህዝብ ጤና ጥበቃ ተቋማትና ባለሙያዎች እንድተው እናሳስባለን።
6. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ውስብስብ ሁኔታ ለማለፍና የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ግንባታን ለማጠናከር በመንግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርስውን ተጽዕኖ ተከታትሎ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ታሪካዊና ህጋዊ ሃላፍነቱን እንድወጣ እንጠይቃለን። ምንም እንኳ ቦርዱ ለውጥ ለማምጣት ያደርጋቸው እንቅስቃሲዎች የሚያስመሰግኑት ቢሆንም ግልጽነት የጎደላቸው አንዳንድ አሰራሮች በቦርዱ ላይ ያለንን እምነት እየሸረሸረ መሆኑን ቅሬታችንን መግለጽ እንወዳለን።
7. የ2012 የኢትዮጵያ ምርጫን ለማራዘምም ሆነ ባጠቃላይ ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን አለበት ወይም ምን መደረግ አለበት (what is to be done) በሚለው ላይ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቭክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተለይም መንግስትና የፖለትካ ፓርቲዎች ተገናኝተን ተከታታይ ውይይት እና ምክክር እንድናደርግና ሁላችንም ያሉንን አማራጭ ሃሳቦች ማቅረብ እንድንችል መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች አጥብቀን እንጠይቃለን።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ
መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ ም
ፊንፍኔ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.