Courts

በክርክርና በቀጠሮ ላይ ያሉ የክስ መዛግብት ለሚቀጥለው ዓመት እንዲቀጠሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

በክርክርና በቀጠሮ ላይ ያሉ የክስ መዛግብት ለሚቀጥለው ዓመት እንዲቀጠሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

 

ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ

በዳኝነት ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባት እንዳይሆን ተሠግቷል

የፍትሐ ብሔር ውሳኔዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳይገለጹ ታገደ

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ከሚታዩ የክስ መዝገቦች ውስጥ በክርክርና በቀጠሮ ላይ ያሉ መዛግብት፣ ከመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ጊዜያት እንዲቀጠሩ ለየምድብ ችሎቶቹ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ተጠቆመ፡፡ ማሳሰቢያው የተሰጠው በፍርድ ቤቱ አመራሮች በመሆኑ፣ በዳኝነት ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባት እንዳይሆን የሕግ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በክርክር ላይ ያሉ ወይም ክርክራቸው የተወሰነ ጊዜ የሚወስድ መዛግብት ለቀጣዩ ዓመት ከመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ እንዲቀጠሩ አመራሩ የገለጸ ቢሆንም፣ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ያለው ሥርጭት ከተቃለለ፣ የቀጠሮ ጊዜ ተሰብሮ በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ሊሠራ እንደሚችልም አማራጭ ሐሳብ አስቀምጧል፡፡

የፍርድ ቤቱ አመራር ያስተላለፈውን ማሳሰቢያ በሚመለከት አስተያየታቸውን የሚሰጡ የሕግ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ አመራሩ የሰጠውን ማሳሰቢያ በሁለት ከፍለውታል፡፡ የመጀመርያው ከተከሳሹ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት አንፃር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሠራጭቶ ከሚገኘው ኮሮና ቫይረስ አደገኛ ሁኔታ አንፃር ነው፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ቤተሰቦችና ሌላ የችሎት ታዳሚዎች በሌሉበት ርቀታቸውን በጠበቀ ሁኔታ ክርክር በማድረግ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ እየቻሉ፣ ሙሉ በሙሉ መከልከል ግን የመብት ጥሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የፍርድ ቤቱ አመራር በወረርሽኙ ይከሰታል ብሎ የሚሠጋበትን ጉዳት የሚያሳይ በመሆኑ፣ ማሳሰቢያው ተገቢ መሆኑንም የሚደግፉ የሕግ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል አንድ ዳኛ በያዘው መዝገብ ላይ የመወሰንና የማዘዝ ሥልጣኑ የዳኛው ሆኖ ሳለ፣ ‹‹ይህንን አድርግ›› ማለት በዳኝነት ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባት በመሆኑ እንዳሳሰባቸውም ገልጸዋል፡፡

የሕግ ባለሙያዎቹ ከመብት ጥሰትና በዳኞች ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባት ላይ ባነሱት ጥያቄ፣ ፍርድ ቤቱ የክርክርና የቀጠሮ መዛግብትን ከመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለምን መቅጠር እንደፈለገ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪ፣ ፍርድ ቤት አልተዘጋም ብለዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ ፍትሕ ማግኘት አለበት፡፡ ፍትሕ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውኃና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ነው፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፉ ኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያም በመከሰቱ፣ የሕዝብ መሰባሰብን ማለትም ችሎት ለመከታተል፣ ዋስ ለመሆን፣ ለዋስትና ያስያዙትን ገንዘብ ለመውሰድ፣ የውሳኔ ግልባጭ ለመውሰድና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣውን ማኅበረሰብ ለማስቀረት ፍርድ ቤት በከፊል እንዲዘጋ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

ለወረርሽኙ መስፋፊያ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ መሰባሰብ በመሆኑ፣ ያንን ለማስቀረትና የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለው አክለዋል፡፡ በጣም አስፈላጊና አስቸኳይ የሆኑ የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተረኛ ችሎቶች እንደሚታዩ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ የወንጀል ክስ ኖሮባቸው በማረሚያ ቤት ያሉ ተጠርጣሪ ታሳሪዎች ጉዳይ ባሉበት ቦታ በቴሌ ኮንፈረንስ ለማከራከር ዝግጅቶች እየተሟሉ መሆኑን፣ አቶ ብርሃነ መስቀል ተናግረዋል፡፡ እንደ ወረርሽኙ ሁኔታ ፍርድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የሚዘጉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ መታሰብ ያለበት ግን ሲከፈት ምን ያህል ባለጉዳይ ፍርድ ቤቶችን ሊያጥለቀልቅ እንደሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ሳይዘጉ እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው ከችሎት አስተባባሪ ዳኞች ጋር በተደረገ ውይይት አንድ የውሳኔ  ሐሳብ ላይ መደረሱን ጠቁመው፣ የችሎት አስተባባሪ ዳኞች ከችሎት ዳኞች ጋር በመወያየትና የዳኞቹን ውሳኔ በማወቅ፣ ችሎቶች ሳይሠሩ የሚቀጥሉበትን ማመቻቸት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የችሎት ዳኞችን ባገኙት መገናኛ ዘዴ ያነጋገሩት የችሎት አስተባባሪዎች ያገኙት ምላሽ፣ ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመርያ አካባቢ ወረርሽኙ በስፋት ይሠራጫል የሚል ሥጋት ስላለ፣ እስከዚያው ድረስ የክርክርና የቀጠሮ መዝገቦችን ረዘም አድርጎ በመቅጠር ጊዜው በሰላም ካለፈ፣ ነሐሴ 2012 ዓ.ም. እና መስከረም ወር 2013 ዓ.ም. ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚያዩዋቸው ጉዳዮች ከባድና ትልልቅ በመሆናቸው፣ እንዲሁም ዳኞቹ ከፍተኛ የሆነ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ እነሱ ያልመከሩበት ውሳኔ ሊተላለፍ እንደማይችል የገለጹት አቶ ብርሃነ መስቀል፣ አንድ ዳኛን እንኳን ‹‹ይህን መዝገብ ሥራ፣ ያንን መዝገብ ተው›› ብሎ ጣልቃ በመግባትና ማዘዝ ቀርቶ ስለያዘው መዝገብ እንኳን ማንሳት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡ ማንም አካል በዳኝነት ነፃነት ላይ ሊገባ እንደማይችልም አክለዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ አመራር ባደረገው ውይይት የደረሰበት ስምምነት፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ጋር ተያይዞ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚቀርቡ ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑን የፍርድ ቤቱ አመራሮች ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተረኛ ችሎት ዳኞችን ቁጥር በመጨመር በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም በሌሎች መዝገቦች ማለትም ለውሳኔ፣ ለብይንና ለትዕዛዝ የተቀጠሩ በርካታ የወንጀል መዛግብትና ውስን የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን ሥራ ማቃለል እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የፍርድ ቤቱ አመራር ሌላው ያስተላለፈው ሐሳብ፣ ፍርድ ቤቱ በከፊል ዝግ ከተደረገ በኋላ የፍትሐ ብሔር የውሳኔ መዝገቦች በፍርድ ቤቱ ማኅበራዊ የትስስር ገጽ ላይ እንዲወጡ የተወሰነ ቢሆንም፣ አመራሩ እንዲቆም ወስኗል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የተወሰነበት ወገን በወቅቱ ይግባኝ ማለት ስለማይችልና የፍርዱን ግልባጭ ማግኘት ስለሚቸገር፣ ሁሉም ሰው ማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ማግኘት ስለማይችል፣ የተወሰነለትም በወረርሽኙ ምክንያት ማስፈጸም ስለማይችል መታገዱን አቶ ብርሃነ መስቀል አስረድተዋል፡፡

ውሳኔ ያረፈባቸው መዛግብት በዳኞች እጅ በመሆናቸው ሰብስቦ ወደ መረጃ ቋት (ዳታ) ማስገባትም ስለማይቻል መሆኑን፣ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም አክለዋል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የልጅ፣ የቤተሰብ ቀለብ፣ የአሠሪና የሠራተኛ ጉዳይ፣ የጉዳት ካሳ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አንድምታ ያላቸው ጉዳዮችና አስቸኳይ ጉዳዮች ከሆኑ ሊታዩ እንደሚችሉ የፍርድ ቤቱ አመራር ስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

በማረሚያ ቤት ሆነው የጥፋተኝነት ፍርድም ሆነ ወይም የቅጣት ውሳኔ፣ በነፃ የሚለቀቁ ወይም እንዲከላከሉ ብይን የመሥራት ሥራ በሚገባ እንዲሠራና ውጤቱ እንዲነገራቸውም አመራሩ ተስማምቷል፡፡ በክርክር ሒደት ላይ ያሉት ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ክርክር እንዲያደርጉና ፍትሕ እንዲያገኙ ለማድረግ አመራሩ ተስማምቷል፡፡ ስምምነቱ በቂሊንጦ፣ ቃሊቲ፣ ድሬዳዋና በክልል ያሉ ተዘዋዋሪ ችሎቶችን ያካተተ ነው፡፡ ከማረሚያ ቤት ውጪ በዋስትና ያሉ መደበኛ ችሎቶች እስከሚጀምሩ ድረስ ባሉበት እንደሚቆዩም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ መዛግብት በትብብር ተሠርተው እንዲጠናቀቁ፣ ለግንቦት ወር 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበሩ በከፊል ዝግ መሆኑን ያልሰሙ ባለጉዳዮችን፣ ዳኞች ከቻሉና ከፈለጉ ርቀታቸውን ጠብቀው ፍርዱን መንገር እንደሚችሉም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ የዋስትና ገንዘብ ተመላሽ ማድረግ በሚመለከት በጣም የተቸገሩ ከሆነ እንደ ሁኔታው ዳኞች በሚሰጡት ትዕዛዝ እንዲፈጸምላቸው ተስማምተዋል፡፡ የየራሳቸውን ውዝፍ መዝገብ ሠርተው ያጠናቀቁ ዳኞች በፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ፊት ዕውቅና እንደሚሰጣቸው፣ ያላጠናቀቁ ደግሞ የየራሳቸው ምክንያት ስለሚኖራቸው ሪፖርት እንዲያደርጉ አመራሩ መስማማቱ ታውቋል፡፡

Categories: Courts

3 replies »

  1. Not only your contents but also the way you present the issue is awesome. Particularly this one is articulating the sense of the discussion.

  2. የዳኝነት ስልጣን ነፃነትን ጣልቃ ገብነትን ከተያዙት መዝገቦች አንፃርና ከፍ/ቤት አስተዳደር አሰራሮች ለይተን ማየት የለብንም እንዴ??

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.