የባንክ ህግ

ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ገብተው በባንክ በመያዣ ለተያዘ ህንፃ ግብዓትነት ስለሚሉ ዕቃዎች የቀዳሚነት መብት

ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ገብተው በባንክ በመያዣ ለተያዘ ህንፃ ግብዓትነት ስለሚሉ ዕቃዎች የቀዳሚነት መብት

ከግብር እና ቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ግብር እና ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነባን ለምሳሌ ሆቴልን አንድ አበዳሪ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ የሆቴሉን ህንፃ ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደ ራሱ ሳያዞር (before it is acquired by the bank ) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹ ቀረጥና ታክስ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል ወይስ አይችልም?

ጥያቄውን ለመመለስ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የጉምሩክ ህጎች (Law of Customs) ፣ የፎርክሎዠር ህግ (Foreclosure laws) ፣ የንብረት ህግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) እና ሌለችንም መፈተሸ ያለባቸው ህግጋቶች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ህጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006ን ስንመለከት የአዋጁ አንቀፅ 130 (6) “ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ወደ አገር የገባን ዕቃ በዋስትና ማስያዝ የሚቻለው ከባለሥልጣኑ ጋር በቀረጥና ታክስ አከፋፈል ረገድ ላይ ስምምነት ሲደረስ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል ይህ ማለት የዕቃው ባለቤት ቀረጥና ታክሱን የሚከፍል መሆኑንና ስለአከፋፈሉ ሁኔታ ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ ዕቃው ለዕዳ መክፈያነት በመያዣ መስጠት አይችልም ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር አብሮ መነሣት ያለበት ጉዳዩ “ዕቃ” ማለት ምን ማለት ወይም አዋጁ ይህን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ለየትኞቹ ዕቃዎች ነው የሚለው ነው ፡፡ የአዋጁ የትርጓሜ አንቀፅ የሆነው አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ (1) “ዕቃ ማለት ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆን ግዙፍነት የሌላቸው በሕግ እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የሚታወቁትን ንብረቶች ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን በአገልግሎት ላይ የዋሉ የተፈጥሮ ኃይልንና ሀብቶችን የሚያካትት ሲሆን ገንዘብን ይጨምራል” ይላል ፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 130 (6) የተገለፀው ቅድመ ሁኔታ ከቀረጥ ነፃ በገቡ ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል ፡፡ ይህ ማለት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ለሆቴል ግንባታ ፕሮጀክት የሚገቡ ዕቃዎችን ባንኮች በዋስትና የሚይዙ ከሆነ ተበዳሪው ዕቃዎቹን ለማስያዝ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ አለበት ፡፡

ባንኮች ከላይ የተጠቀሰውን ፈቃድ በተበዳሪው ሳይቀርብላቸው ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎቹን በመያዣ ይዘው ቢገኙ እና ደንበኛው ዕዳውን በውሉ መሠረት ባይከፍል ምን ይሆናል ? ባለሥልጣኑ በቁጥር 5.0/269/02 ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቅርንጫፍ ፅ/ቤቶቹ በፃፈው እና በግልባጭ ለሁሉም ባንኮች ባሳወቀበት ደብዳቤ ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎች በዕዳ ሲያዙ ተበዳሪው አስቀድሞ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ ያለበት መሆኑን እንዲሁም ባንኮቹ ዕቃዎቹን በመያዣ መያዛቸውን ለባለሥልጣኑ መግለፅ ያለባቸው መሆኑን ይገልፃል ፡፡ ነገር ግን ይህ ተሟልቶ ብድሩ ከተለቀቀ በኋላ ተበዳሪው በውሉ መሠረት ግዴታውን ካልተወጣ ባለሥልጣኑ ቀረጥና ታክሱን መያዣው በባንኩ ከተሸጠ በኋላ ሥመ ሀብቱ ለገዢ ሳይዘዋወር የሚከፈለው መሆኑን በደብዳቤው ተ.ቁ. 3 ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው በባንኮች ፋይናንስ ለተደረጉ ፕሮጀክቶች ግብዓትነት ወደ ሃገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎችም ጭምር ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ባንኮችን ተበዳሪው ባለሥልጣኑ ዕቃዎቹ ለዋስትና እንዲያዙ ፈቃድ ሳያቀርብላቸው ዕቃዎቹ በመያዣ መያዣቸው አዋጁን የሚጥስ ተግባር በመሆኑ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደ ራሱ ሳያዞር (acquired by the bank ) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን (ዕቃዎቹን) ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል ፡፡

ጥያቅውን ለመመለስ ከሚያስፈልጉን ህጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ ህግን የተመለከትን ቢሆንም አዋጁ የማይመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ እነዚህን ጥያቄዎች ከየፎርክሎዠር ህግ (Foreclosure laws) እና የንብረት ህግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ድንጋጌ አንፃር መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ባንኮች በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 98/90 መሠረት የማይንቀሳቀስ ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት ፣ ንግድ መደብርን (Bussiness) ወይም ዕቃን (Merchandise) በመያዣ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ባንኮች ከቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዥ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አለባቸው ወይስ የለባቸውም ? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡት ዕቃዎች ግንባት ላይ ከመዋላቸው በፊት እና ከዋሉ በኋላ ከንብረት ህግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) አንፃር እንዴት ይታያሉ የሚለውን መመለስ የቀደመውን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳል፡፡

ለሆቴል ፕሮጀክት ግንባት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ስለንብረቶች አከፋፈል (classification of goods) በሚደነግገው የፍ/ህጉ አንቀፅ 1126 መሠረት ከተንቀሳቃሽ ዕቃዎች ተርታ የሚመደቡ ናቸው ፡፡ እነዚህ ዕቃዎች ለሆቴል በተሠራ ህንፃ ላይ መጥተው ግብዓት በሚሆኑበት ወቅት እንደየሁኔታቸው የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በልማድ የሆቴል አካል ተብለው የሚታሰቡ ፣ ከሆቴሉ ህንፃ ጋር በግዙፍነት የተያያዙት እና ህንፃው ሳይጎዳ መነጠል የማይቻለውን የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ሲባል በቋሚነት ለሆቴል አገልግሎት የተቀመጡ እና በግዙፍነት ያልተያያዙት ደባል ክፍሎች (Accessory) ይባላሉ (የፍ/ህግ ቁጥር 1132 እና 1136ን ይመለከቷል)፡፡ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) አንድ ከማይቀሳቀስ ንብረት ጋር የተቀላቀሉ እንደሆነ እራሳቸው እንደቻሉ ንብረቶች መቆጠራቸው ይቀራል (they cease to exist) እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በእነዚህ ዕቃዎች ላይ ያሏቸው መብቶች ቀሪ ይሆናሉ የፍ/ህግ ቁጥር 1134 (1) እና (2)ን ይመለከቷል፡፡ የባለቤትነት መብት ጉዳይ አሻሚ በሚሆን ወቅት የዋናው ንብረት ወይም የሆቴሉ ህንፃ ላይ የተቋቋመ መብት ደባል ክፍሎች (Accessory goods)ን ይጨምራል (የፍ/ህግ አንቀፅ 1135) ፡፡ ሰለዚህም የሶስተኛ ወገኞች መብት የማይኖርና ከሆነ ( cease to exist) ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዥ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አያስፈልግም፡፡ የሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ላይ መብት የነበራቸው ሶስተኛ ወገኖችን መብታቸውን ስለጉዳት ኃላፊነት ወይም አላግባብ መበልፀግ የተደገጉትን ድንጋጌዎች በመጠቀም መጠየቅ ይችላሉ (የፍ/ህጉን አንቀፅ 1134 (3) እና 1138 (1)ን ይመለከቷል) ፡፡ ይህን የፎርክሎዠር ህግ (Foreclosure laws) እና ንብረት ህግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ትንታኔ ስንከተል ባንኮች የሆቴል ህንፃን በመያዣ ከያዙ የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) የሆኑ ዕቃዎች ላይ ጭምር የመያዣ መብት ያቋቁማሉ ፡፡ በመያዣውን በመሸጥ ዕዳቸውን ማስመለስ ይችላሉ ፡፡ ባለሥልጣኑ እንደ ሶስተኛ ወገን ዕዳ ጠያቂ በመቅረብ በጉምሩክ አዋጁ አሊያም በፍ/ህጉ ከተበዳሪው ቀረጥና ታክሱን ሊጠይቅ ይችላል ወደሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡

ነገር ግን ለአንድ ጉዳይ ሁለት የህግ ዘርፎች ወይም ድንጋጌዎች አተረጓጎም የተለያየ ውጤት የሚኖራቸው ከሆነ ከጠቅላላው ህግ ልዩ ህግ ቀዳሚነት ሊኖረው የሚገባ ስለመሆኑ the special law prevails over the general የሚለው የህግ አተረጓጎም መርህ (rules of interpretation) ያስረዳል፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ለጉዳዩ የጉምሩክ አዋጁ ላይ የተሠጠውን ትንታኔ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጉምሩክ አዋጁ ለዕቃ የተሠጠው ትርጓሜ ሰፊ በመሆኑ የግንባታ ግብዓቶችንም ስለሚጨምር ከላይ ከጉምሩክ አዋጅ አንፃር በቀረበው ሃሳብ መሠረት አንድ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ ከቀረጥ ነፃ በሆኑ ዕቃዎች የተገነባ ሆቴል ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደ ራሱ ሳያዞር (acquired by the bank ) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ባንኮች ብድር በሚሠጡበት ወቅት ግንባታው ከቀረጥ ነፃ በገቡ ዕቃዎች ግብዓትነት የተሠራ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጥበት አሠራር በባንኮች ማህበር እና ባለስልጣኑ መካከል በሚደረግ ውይይት ሊዘረጋ ይገባል፡፡


Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.