Courts

በኮሮና ቫይረስ (COVID 19) መከሰት ምክንያት የተከሰተውን ሀገራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ፍርድ ቤቶች ሊመሩበት የሚገባ አጠቃላይ መመሪያ (Comprehensive Guideline)

በኮሮና ቫይረስ (COVID 19) መከሰት ምክንያት የተከሰተውን ሀገራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ፍርድ ቤቶች ሊመሩበት የሚገባ አጠቃላይ መመሪያ (Comprehensive Guideline)

DOWNLOAD .pdf

1. መግቢያ

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የተከሰተውና የሕዝብን ጤንነትና አጠቃላይ የኑሮ ዘይቤ እየተፈታተነ የሚገኘው የኮቪድ 19 (ኮሮና) ወረርሺኝ የእያንዳንዱ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የማሕበረሰብ፣ የሀገር ብሎም የዓለም ስጋት በመሆን በሰው ልጅ ሕልውና ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡ ወረርሺኙ ዓለምን በሙሉ ያዳረሰና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ቀጥፏል፡፡ በዚህም ሳያበቃ በዓለማችን ላይ በአጠቃላይ ሊባል በሚችል ሁኔታ የማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፈጠሯል፡፡ እየፈጠረም ነው፡፡
ሀገራት አሁን ያለውን የወረርሽኙን እንቅስቃሴ ለመግታት ያስቻላቸው ዘንድ የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱና እይወሰዱ የሚገኙ ሲሆን በዚህ ረገድ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የፊት መሸፈኛ ማድረግ፣ እጅን መታጠብ፣ በጣም አስፈላጊ ወሳኝ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት ዋና ዋና ሊባሉ የሚችሉ የሕዝብን ጤንነት መጠበቂያ መንገዶች ሆነው ተወስደዋል፡፡ እነዚህን የጤንነት መጠበቂያ መንገዶችን ለማረጋገጥ ደግሞ ጥቂት በማይባሉ ሀገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ይህም ጥብቅ በሆነ መልኩ በሽታውን ለመከላከልና ጉዳቱንም ለመቀነስ በማሰብ ነው፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአንፃራዊነት ትንሽ ዘግይቶ ቢሆንም ቫይረሱ መኖሩ መጀመሪያ ከታወቀበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና በሕብረተሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በአግባቡ ለመቀነስ በርካታ ርምጃዎች በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተወስደዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሕዝብ ሊሰበሰብባቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎች ላይ የተለያዪ ዓይነት ገደቦች የተደረጉ ሲሆን በሕገ-መንግስቱም መሠረት በአንዳንድ መብቶች ላይ ዕቀባ ተደርጓል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለዚሁ ችግር መፍትሔ ከማበጀት አንፃር የራሱን ርምጃዎች የወሰደ ሲሆን ከዚህ አኳያ ፍርድ ቤቶች ሊሠሩ ስለሚገባበት ሁኔታና አሠራር አሳውቋል፡፡ በዚህም መሠረት
ከመጋቢት 10 ቀን እስከ መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚቆይና በጣም አስቸኳይ የሆኑ ጉዳዮችን ከሚያዩ ተረኛ ችሎቶች በስተቀር ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ተወስኗል፤
ይሄው ውሳኔ ከመጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላም እየተራዘመ የቆየ ሲሆን አሁንም የፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ የመሆን አሠራር እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡
ይህ መመሪያ የወጣውም የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሐምሌ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ላይ መፍትሔ ይኖረዋል ተብሎ ስለማይገመትና ይልቁንም በሽታው እየተባባሰ የመጣ በመሆኑ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚቆይና በኮሮና ቫይረስ (COVID 19) መከሰት ምክንያት የተከሰተውን ሀገራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ፍርድ ቤቶች ሊመሩበት የሚገባ አጠቃላይ መመሪያ (Comprehensive Guideline) ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡

2. የአጠቃላይ መመሪያው ዓላማ

ይህ መመሪያ ሶስት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን እነርሱም

ፍርድ ቤቶች ያስፈለጉበትን ዓላማና የተቋቋሙበትን ግብ መምታት ይችሉ ዘንድ በዚህ ፈታኝ ወቅት ማረጋገጥ ለማስቻል
ለዜጎች የፍትሕ ተደራሽነትን (access to justice) ሳይጓደል አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ መዘርጋት ለማስቻል፤
የፍርድ ሥርዓቱ የሚጠበቅበትን ማበርከት ይችል ዘንድ በፍርድ ቤት የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን የዳኝነት ሰጪ እና የድጋፍ ሰጪ አካላትን ሕይወትና ጤንነት ማረጋገጥ ለማስቻል፤
የመጣ አጠቃላይ መመሪያ (Comprehensive Guideline) ነው፡፡

3. የአጠቃላይ መመሪያው የሕግ ማዕቀፍና

ይህ አጠቃላይ መመሪያ በሕግ በአስገዳጅነት የተደነገጉ የ ሕግ ሥነ-ሥርዓቶችን የመጣስም ሆነ የማሻሻል ዓላማ የለውም፡፡ ሆኖም ግን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተገልጋዩንም ሆነ የዳኝነት ሥርዓቱን ጤንነትና ፍትሕ አሰጣጥ በተጣጣመ መልኩ መምራት ይቻል ዘንድ የወጣ መመሪያ ነው፡፡ መመሪያው የዳኝነት ነፃነትን በማንኛውም ሁኔታ የመንካት ዓላማ የለውም፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የዳኝነት ተቋማዊ ሥርዓቱን ከበሽታ ለመከላከል በሚል ሐሳብ የፍትሕ ተደረሽነትን የመገደብ ሚናም አይኖረውም፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱንም ባከበረ መልኩና አሁን ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የመሥራት ሚና ይኖረዋል፡፡
4. መመሪያውን በአግባቡ ለመፈፀም ታሳቢ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች

የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ድንገተኛ መሆኑና የተለመደውን መደበኛ አሠራር ብቻ በመከተል መከላከል የማይቻል በመሆኑ ብዙ ልዩ ልዩ ርምጃዎችን ይጠይቃል፡፡ በዚህም መሠረት የፍትሕ አካሉን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ማንቀሳቀስ የሚቻለው አስፈላጊውን የመከላከያ መንገዶች በማመቻቸት ነው ፡፡ ከዚህ አንፃር የሚከተለውን ሪሶርስ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል
በየችሎቱ ተገልጋዮችን የሚያስተናግዱ በጎፈቃደኛ ግለሰቦች
በየችሎቱ ያሉ ውዝፍ የመዝገብ ሥራዎችን ለማንቀሳቀስና ወደፊትም በዚህ ችግር ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ውዝፍ ሥራዎችን ለማንቀሳቀስ የሚረዱ በጎፈቃደኛ የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ተመራቂዎች
የዳኞችን፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞችን እና ተገልጋዮችን ባማከለ መልኩ የጥንቃቄ ርምጃ መውሰጃ መንገዶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት
በየምድብ ችሎቱ ለስድስት ወራት የሚቀጠሩ የጤና ባለሙያዎችና በምድብ ችሎቱ የሚገኝ ግብረ ሐይል ማቋቋም፡፡ (በኮቪድ 19 የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን አቅራቢያ ካለ የጤና ተቋም ጋር በመነጋገር የሚልክ)
በየምድብ ችሎቱ የሙቀት መለኪያ እንዲኖር ማድረግና ይህንኑ የሚያከናውን የሥራ መደብ በመነጋገር በተደራቢነት መፍጠር
በየሳምንቱ የፍርድ ቤቶችን የመድሐኒት ርጭት ማከናወን ማስቻል
5. የመመሪያው አፈፃፀም
5.1. የፍትሐ ብሔር ፍትሕ (Civil Justice) በተመለከተ
5.1.1. ክስ መመስረት
ማንኛውም የፍተሐብሄር ክስ በመጣበት አግባብ ይስተናገዳል ይስተናገዳል፤
ማንኛውም ክስ ለመመስረት ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ተገልጋዮች የፊት መሸፈኛ ማድረግ ያለባቸው ሲሆን በፍርድ ቤቱ አስተዳደር የተቀመጡ የጥንቃቄ ርምጃዎችን የመተግበር ግዴታ አለባቸው
ክስ ለመመስረት የሚመጡ ተገልጋዮችንና የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ጤንነት በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ ይቻል ዘንድ ፍርድ ቤቶቹ አካላዊ ርቀትን የሚያሳዩ ምልክቶችን የማድረግ ሐላፊነት አለባቸው
በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተገልጋዮችና ከጠበቆች ውጪ መግባት ክልክል ነው፤ ይህንንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
በፍርድ ቤት ውስጥ ለመገልገል የሚደረጉ መስተንግዶዎች በሰልፍ የሚፈፀሙ ሲሆን ይህንንም አካላዊ ርቀትን በጠበቁ መልኩ ማድረግ ይቻል ዘንድ ተገላጋዮች ቆመው የሚጠብቁበትን ርቀት በምልክት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
ክስ የመሠረቱ ተገልጋዮች መጥሪያ የሚወስዱበትን ጊዜ መዝገቡን በከፈቱበት ቀን መንገርና ይህንንም በወቅቱ መፈፀም ይገባል፡፡
5.1.2. መጥሪያ
ማንኛውም ተገልጋይ መጥሪያን በወቅቱ የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ሊነገረው ይገባል፡፡
5.1.3. ምስክሮች አጠራርና አቀራረብ
5.1.3.1. ምስክሮችን መስማት በጣም አፋጣኝ እስካልሆነ ድረስ በተቻለ መጠን ራቅ ያለ ቀጠሮ ይሰጣል
5.1.3.2. የምስክር መስማት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በፕላዝማ ማከናወን ከተቻለ አማራጩን የምስክር መስሚያ ጊዜ በማቀናጀት ማከናወን ያስፈልጋል
5.1.3.3. የባለሙያ ምስክር ያለበትን ፋይል ባለሙያውን በአካል ለመስማት በጣም አስፈላጊ መሆኑ በችሎቱ ካልታመነ በቀር በጽሑፍ መቀበል ይረጣል
5.1.4. ጊዜያዊ ትእዛዞች
5.1.4.1. ማንኛውም ጊዜያዊ ትዕዛዞች ሲሰጡ የወቅቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩና የሚኖረውን ተፅዕኖ ከግምት ባስገባ መልኩ ሊሆን ይገባል
5.1.4.2. የዕግድ ትዕዛዞች ለመስጠት አሳማኝ የሆነ ምክንያትን ታሳቢ በማድረግና ከሚጠየቀው ዳኝነት አንፃር በማገናዘብ ሊሆን ይገባል
5.1.5. ቀጠሮ
5.1.5.1. በቀጠሮ ቀን አለመገኘት ወይም መዘግየት በተከራካሪዎች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስለሚሆን የቀረው ተከራካሪ በቂ የሚለውን ምክንያት አቅርቦ የተዘጋውን መዝገብ ለማስከፈት የሚኖረው ሥርዓት ግርግር እንዳይፈጥር የተከራካሪዎች መብት ከመታለፉ በፊት ሌሎች አማራጮችን መውሰድ ይገባል፡፡
5.1.5.2. ቀጠሮዎች ሲለወጡም ሆነ ሲፃፉ የተለያዩ የቀጠሮ መለጠፊያ ቦታዎችን ማዘጋጀት የተገልጋዮችን መጨናነቅ ያቀንሳል
5.1.6. ክስ መስማት

5.1.6.1. ክሶችን መስማት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በፕላዝማ ማከናወን ከተቻለ አማራጭ የክስ መስሚያ ጊዜ በማቀናጀት ማከናወን ያስፈልጋል
5.1.6.2. ዳኞች ክስ ሲሰሙ በተቻለ መጠን ጊዜን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ ረጅም ጊዜ በመውሰድ ሊከሰት የሚችለውን ወረፋና የሰው መጨናነቅ ሊቀንሱ ይገባል፡፡
5.1.7. ፍርድ
5.1.7.1. ፍርድ ሲሰጥ በኮሮና ምክንያት ያልተጠሩ ተብሎ በመመዝገብ ፍርዱ ሊሠራ ይችላል፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ባሉበት መነበብ አለበት ብሎ የሚያምን ችሎት ግን ይህንኑ ከመፈጸም አይከለከልም፡፡
5.1.7.2. የፍርድ ውሳኔዎች በመዝገብ ላይ የተሰጠ መሆኑንና ይህንኑ እንዲወስዱ ለተከራካሪ ወገኖች በስልክ ወይም በሌላ አመቺ መንገድ ሊገለጽላቸው ይችላል፡፡ ይህንንም መፈጸም ይቻል ዘንድ ፍርድ ቤቶች ዝግጅት ያከናውናሉ፡፡
5.1.8. ፍርድ አፈጻጸም
5.1.8.1. ማንኛውም የፍርድ አፈፃፀም መፈፀም የሚቻል ቢሆንም የአፈፃፀሙ መንገድ አሁን ያለውን የሕዝብ ጤና ችግር አደጋ ላይ እንዳይጥል ፍርድ ቤቶች ወቅቱን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታና የፍትሕ ተደረራሽነትን ባማከለ መልኩ ይፈጽማሉ፡፡

5.2. የወንጀል ፍትሕ (Criminal Justice) በተመለከተ
5.2.1. ክስ መመስረት
ማንኛውም የወንጀል ክስ በመጣበት አግባብ ይስተናገዳል፤
ማንኛውም ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ተገልጋዮች የፊት መሸፈኛ ማድረግ ያለባቸው ሲሆን በፍርድ ቤቱ አስተዳደር የተቀመጡ የጥንቃቄ ርምጃዎችን የመተግበር ግዴታ አለባቸው
ማንኛውም ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ተገልጋዮችንና የፍርድ ቤት ሠራተኞችን ጤንነት በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ ይቻል ዘንድ ፍርድ ቤቶቹ አካላዊ ርቀትን የሚያሳዩ ምልክቶችን የማድረግ ሐላፊነት አለባቸው
በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፖሊሶች፤ ከተገልጋዮችና ከጠበቆች ውጪ መግባት ክልክል ነው፤ ይህንንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
በፍርድ ቤት ውስጥ ለመገልገል የሚደረጉ መስተንግዶዎች በሰልፍ የሚፈፀሙ ሲሆን ይህንንም አካላዊ ርቀትን በጠበቁ መልኩ ማድረግ ይቻል ዘንድ ተገላጋዮች ቆመው የሚጠብቁበትን ርቀት በምልክት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
ይህ የጥንቃቄ ርምጃ ከማረሚ ቤቶች የሚመጡ ተገልጋዮችንም ይመለከታል፡፡
ማንኛውም ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ የሚመጡ ተገልጋዮች፣ ፖሊሶችና ዐቃቤ ሕጎች ከፍርድ ቤት መጥሪያ የሚወስዱበትን ጊዜ መዝገቡን በከፈቱበት ቀን መንገርና ይህንንም በወቅቱ መፈፀም ይገባል፡፡
5.2.2. መጥሪያ
ማንኛውም ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚመጡ ተገልጋዮች፣ ፖሊሶችና ዐቃቤ ሕጎች መጥሪያን በወቅቱ የመውሰድ ግዴታ እንዳለባቸው ሊነገራቸው ይገባል፡፡
5.2.3. ምስክሮች አጠራርና አቀራረብ
5.2.3.1. ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ ምስክሮችን መስማት በጣም አፋጣኝ እስካልሆነ ድረስ በተቻለ መጠን ራቅ ያለ ቀጠሮ ይሰጣል
5.2.3.2. የምስክር መስማት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በፕላዝማ ማከናወን ከተቻለ አማራጩን የምስክር መስሚያ ጊዜ በማቀናጀት ማከናወን ያስፈልጋል

5.2.3.3. የባለሙያ ምስክር ያለበትን ፋይል ባለሙያውን በአካል ለመስማት በጣም አስፈላጊ መሆኑ በችሎቱ ካልታመነ በቀር በጽሑፍ መቀበል ይረጣል
5.2.4. ጊዜያዊ ትእዛዞች
5.2.4.1. ማንኛውም ጊዜያዊ ትዕዛዞች ሲሰጡ የወቅቱን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩና የሚኖረውን ተፅዕኖ ከግምት ባስገባ መልኩ ሊሆን ይገባል
5.2.4.2. የእስር ትዕዛዞች ለመስጠት አሳማኝ የሆነ ምክንያትን ታሳቢ በማድረግና ከሚጠየቀው ዳኝነት አንፃር በማገናዘብ ቢሆን ይመከራል፡፡
5.2.5. ቀጠሮ
5.2.5.1. ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘበቀጠሮ ቀን አለመገኘት ወይም መዘግየት በተከራካሪዎች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስለሚሆን የቀረው ተከራካሪ በቂ የሚለውን ምክንያት ለማቅረብ የሚኖረው ሥርዓት ግርግር እንዳይፈጥር የተከራካሪዎች መብት ከመታለፉ በፊት ሌሎች አማራጮችን መውሰድ ይገባል፡፡
5.2.5.2. ፍርድ ቤቶች ውስጥ ከወንጀል ክስ ጋር በተገናኘ ቀጠሮዎች ሲለወጡም ሆነ ሲፃፉ የተለያዩ የቀጠሮ መለጠፊያ ቦታዎችን ማዘጋጀት የተገልጋዮችን መጨናነቅ ለመቀነስ ይረዳል፡፡
5.2.6. ክስ መስማት
5.2.6.1. የወንጀል ክሶችን መስማት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በፕላዝማ ማከናወን ከተቻለ አማራጭ የክስ መስሚያ ጊዜ በማቀናጀት ማከናወን ያስፈልጋል
5.2.6.2. ዳኞች ክስ ሲሰሙ በተቻለ መጠን ጊዜን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ ረጅም ጊዜ በመውሰድ ሊከሰት የሚችለውን ወረፋና የሰው መጨናነቅ ሊቀንሱ ይገባል፡፡
5.2.7. ፍርድ
5.2.7.1. በወንጀል ጉዳይ ላይ ፍርድ ሲሰጥ በኮሮና ምክንያት ያልተጠሩ ተብሎ በመመዝገብ ፍርዱ ሊሠራ ይችላል፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ባሉበት መነበብ አለበት ብሎ የሚያምን ችሎት ግን ይህንኑ ከመፈጸም አይከለከልም፡፡
5.2.7.2. የወንጀል ፍርዶችን መስጠት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወይም በፕላዝማ ማከናወን ከተቻለ አማራጭ የክስ መስሚያ ጊዜ በማቀናጀት ማከናወን ያስፈልጋል
5.2.8. ፍርድ አፈጻጸም
5.2.8.1. ማንኛውም የፍርድ አፈፃፀም መፈፀም የሚቻል ቢሆንም የአፈፃፀሙ መንገድ አሁን ያለውን የሕዝብ ጤና ችግር አደጋ ላይ እንዳይጥል ፍርድ ቤቶች ወቅቱን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታና የፍትሕ ተደራሽነትን ባማከለ መልኩ እንዲፈፀሙ ማድረግ ይመከራል፡፡
6. የተፈፃሚነት ጊዜ

ይህ መመሪያ ከሐምሌ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

Categories: Courts

Tagged as: ,

3 replies »

  1. The federel supreme court should enact procedural regulations that how the lower courts entertain cases that are seen by emergency proclamation ;that’s proc no 213/12 & cases that are not seen by regular procedural codes.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.