Ethiopian Employment Law

አሠሪና ሠራተኛ ህግ፡ መደበኛ የሥራ ሰዓት እና የሥራ ሰዓት ድልድል

የዓለም የሥራ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ 1919 ዓ.ም. ሲቋቋም በጊዜው ስር ሰዶ የነበረውንና ለበርካታ ሰራተኞች የጤና ቀውስ /ሞት ጭምር/ መንስዔ የነበረውን ገደብ አልባ የስራ ሰዓት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ቀዳሚና አንገብጋቢ አጀንዳው ነበር።[1] በዚሁ መሰረት የቀን የሥራ ሰዓትን በስምንት ሰዓት፤ ሳምንታዊ የስራ ሰዓትን ደግሞ በአርባ ስምንት ሰዓት የሚገድበው የሥራ ሰዓት ስምምነት /Hours of Work (Industry) Convention, 1919 (No. 1) ድርጅቱ በተቋቋመ በዚያው ዓመት የወጣ የመጀመሪያ የሥራ ስምምነት ሆኗል። የስምምነቱ ተፈጻሚነት ወሰን በፋብሪካና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች ሲሆን በንግድ ሥራ፤ በቢሮ እና በአገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች እ.ኤ.አ በ1930 ዓ.ም. የሥራ ሰዓት ስምምነት ቁጥር 30 /Hours of Work (Commerce and Offices) Convention, 1930 (No. 30) ወጥቷል።

አርባ ስምንት ሰዓትን ለመቀነስ በተደረጉ በርካታ ጥረቶች እ.ኤ.አ. በ1935 ዓ.ም. የአርባ የሥራ ሰዓት ስምምነት Forty-Hour Week Convention, 1935 (No. 47) ወጥቷል። ስምምነቱ እንደ ባለፉት ስምምነቶች አስገዳጅ ጣሪያ የሚወስን አይደለም። የስምምነቱን ዋና ይዘት የሚወስነው አንቀጽ አንድ እንደሚከተለው ይነበባል፤

Each Member of the International Labour Organisation which ratifies this Convention declares its approval of–

(a) the principle of a forty-hour week applied in such a manner that the standard of living is not reduced in consequence; and

(b) the taking or facilitating of such measures as may be judged appropriate to secure this end;

and undertakes to apply this principle to classes of employment in accordance with the detailed provision to be prescribed by such separate Conventions as are ratified by that Member.

ከምንባቡ እንደሚታየው ስምምነቱን የተቀበሉ አገራት አርባ የሥራ ሰዓት በመርህ ደረጃ ከመቀበል እና በዚህም ሳቢያ የኑሮ ደረጃ እንዳይቀንስ ከማረጋገጥ ያለፈ ግዴታ አልተጣለባቸውም። ሆኖም በመርህ ደረጃ የተቀበሉት የሥራ ሰዓት በተጨባጭ እንዲታይ ተገቢ ተብለው የሚገመቱ እርምጃዎችን መውሰድ እና በሌላ በሚያፀድቁት ስምምነት በሚወሰኑ ዝርዝር ድንጋጌዎች መሰረት መርሁን በተወሰኑ የሥራ ዘርፎች ተፈጻሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጠቅለል ያለ ተፈጻሚነት ካላቸው ሶስቱ ስምምነቶች በተጨማሪ በልዩ የሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች /ለምሳሌ ማዕድን ማውጣት፤ ትራንስፖርት፤ መርከበኞች ወዘተ/ በርካታ ዓለም ዓቀፍ የሥራ ስምምነቶች ወጥተዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1923 ዓ.ም. ድርጅቱን በአባልነት ስትቀላቀል ከአፍሪካ ሶስተኛዋ አገር ናት።[2] ለአባልነት እንደመፍጠኗ ግን የድርጅቱን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ለማጽደቅ ተንቀርፍፋለች። ጥቂት የማይባሉ ዓበይት ስምምነቶችንም አሁን ድረስ አልፈረመችም። ከእነዚህ ውስጥ የሥራ ሰዓት ላይ ገደብ የሚያስቀምጠውና የመጀመሪያው የድርጅቱ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት Hours of Work (Industry) Convention, 1919 (No. 1) ጨምሮ የስምምነት ቁጥር 30 እና 47 ይጠቀሳሉ። አሁን ድረስ ኢትዮጵያ የነዚህ ስምምነቶች ፈራሚ አገር አይደለችም።

መደበኛ የሥራ ሰዓት

በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 63/2/ ‘የማንኛውም ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን ከስምንት፤ በሳምንት ከአርባ ስምንት ሰዓት’ እንደማይበልጥ ተደንግጓል። ‘መደበኛ የሥራ ሰዓት’ ሲባል ሠራተኛው ሥራውን በማከናወን የሚያጠፋው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሥራ ዝግጁ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜንም ይጨምራል።[3]

ምንም እንኳን አገራችን የሥራ ሰዓትን የሚመለከቱ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ባታጸድቅም በአሁኑ ሆነ በፊት በነበሩ የአሠሪና ሠራተኛ ህጎች የተወሰነው መደበኛ የቀን እና ሳምንታዊ የሥራ ሰዓት ከስምምነቶቹ መሰረታዊ ይዘት አላፈነገጠም። አንድ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው የሥራ ሰዓት ስምምነት ቁጥር 1 /Hours of Work (Industry) Convention, 1919 (No. 1) እና ቀጥሎ እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም. በወጣው ስምምነት ቁጥር 30 /Hours of Work (Commerce and Offices) Convention, 1930 (No. 30) የተሰመረው በቀን ስምንት ሰዓት፤ በሳምንት አርባ ስምንት ሰዓት ከፍተኛው ጣሪያ አገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ከደነገገችበት ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ በግሉ ዘርፍ ተፈጻሚነት ያገኘ መደበኛ የሥራ ሰዓት ሆኗል።

ለመንግስት ሠራተኞች የተወሰነው የሥራ ሰዓት ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነጻጻር በጣም ዝቅ ይላል። በፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁ. 1064/2010 ለሚተዳደሩ ሠራተኞች ሳምንታዊው የሥራ ሰዓት ከ39 ሰዓት አይበልጥም።[4] ከፍተኛው የቀን የሥራ ሰዓት ግን በአዋጁ አልተወሰነም። ይህ የሥራ ሰዓት ለፌደራል ዓቃብያነ ህግ መደበኛው የሥራ ሰዓት ነው።[5] ከፍተኛው የ39 ሰዓት ጣሪያ በልዩ ህግ በሚተዳደሩ የመንግስት ሠራተኞች ላይ መዋዥቅ ይታይበታል። ለምሳሌ ለብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች የተወሰነው በቀን 8 በሳምንት 39 ሲሆን[6] አሁን የጉምሩክ ኮሚሽን እና የገቢዎች ሚኒስቴር በሚል ለሁለት የተከፈለው የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን 8 በሳምንት 43 ሰዓት ነው።[7]

የሥራ ሰዓት ድልድል

ምንም እንኳን በበርካታ አገራት መደበኛ የሥራ ሰዓት በሳምንት በአርባ[8] እና አርባ ስምንት ሰዓት መካከል ቢዋዥቅም በህግ በሚወሰኑት ልዩ ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ልዩነት ይታያል። እነዚህ ሁኔታዎች መደበኛውን የሥራ ሰዓት የማሳጠር ወይም የማስረዘም ውጤት አላቸው። በተወሰኑ የሠራተኛ መደቦች ላይ ደግሞ መደበኛው ራሱ ተፈጻሚ አይሆንም።

በአገራችን ‘የማንኛውም ሠራተኛ…’ ብሎ የሚጀምረው የአዋጁ አንቀጽ 63/2/ ጠቅላላ መርህ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሲታይ ተጨባጩን እውነታን ያንፀባርቃል። እስካሁን ድረስ ከወጣት ሠራተኞች[9] በስተቀር የ ‘ሠራተኛ’ ን ትርጓሜ እስካሟላ ድረስ በአዋጁ ወይም በሌላ ህግ ከሥራ ሰዓት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ውጭ የተገለለ፤ የሥራ ሰዓቱ በልዩ ሁኔታ የረዘመ ወይም ያጠረ ሠራተኛ የለም። የተለየ የሥራ ሁኔታዎች ያሉበት ክፍለ ኢኮኖሚ፤ ኢንዱስትሪ ወይም ሙያ ላይ መደበኛውን የሥራ ሰዓት መመሪያ በማውጣት መቀነስ እንዲችል ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስልጣን ቢሰጠውም[10] እስካሁን በዚህ ስልጣኑ ያወጣው መመሪያ የለም።

ከማግለያ፤ መደበኛ የሥራ ሰዓት ከማሳጠር እና ከማስረዘም በተለየ መልኩ የሥራ ሰዓት ድልድል በዓለም ዓቀፍ የሥራ ስምምነቶች ተቀባይነት አግኝቶ በበርካታ አገራት በስፋት ሲተገበር ይታያል። ይህም የተለዩ የሥራ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት አሠሪው ስራውን ለመምራት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የተዘየደ አማራጭ ነው። በመደበኛው ሁኔታ ሠራተኛው በየቀኑ ለስምንት ሰዓት፤ በሳምንት ለስድስት ቀናት እንዲሰራ ይጠበቅበታል። በዚህ መልክ የቀኑ እና የሳምንቱ የስራ ጊዜ እኩል ተደልድለዋል።

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከአሠሪው የሥራ ፀባይ ወይም ድንገት በሚከሰቱ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች የተነሳ የእኩል የሥራ ሰዓት ድልድል በአሠሪው ድርጅት ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህን ጫና ለመቀነስ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአማካዩ መደበኛ የሥራ ሰዓት ሳያፈነግጥ ተለዋዋጭ የሥራ ሰዓት ድልድል ተፈጻሚ እንዲሆን አዋጁ በልዩ ሁኔታ ይፈቅዳል።

ድልድል፡ ለአንድ ሳምንት

ከመደበኛው የተለየ የሥራ ሰዓት ድልድል በሁለት ዓይነት መልክ ይተገበራል። የመጀመሪያውና በአንቀጽ 63 የተመለከተው በቀን የሥራ ሰዓት ላይ የሚደረግ ድልድል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአንቀጽ 64 የሚገኘው ሳምንታዊ የሥራ ሰዓት ላይ የሚደረግ ድልድል ነው። አጠር ባለ መልኩ ግልጽ ለማድረግ ያክል የመጀመሪያው በአንድ ሳምንት ውስጥ መደበኛውን ስምንት ሰዓት የማሳጠር እና የማስረዘም ውጤት ያለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአራት /ወይም ከዚያ በታች/ ሳምንት ውስጥ የአርባ ስምንት ሰዓቱን የማስረዘም እና የማሳጠር ውጤት አለው። የድልድል አስፈላጊነት አሠሪው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሳይከፍል ከስምንት ሰዓት በላይ ማሰራት የሚችልበት (አማካዩን ሳይለቅ) አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደመሆኑ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ሊነሳ የሚችለው በምን ያህል ሰዓት ማራዘም ሊፈቀድለት ይገባል? የሚለው ጥያቄ ነው። ከላይ በተጠቀሰው ዓለም ዓቀፉ የሥራ ስምምነት ቁጥር 1 በቀን ማራዘም እንዲቻል የሚፈቅደው ለአንድ ሰዓት ያክል በቁጥር ነው። ስምምነት ቁ. 30 በሁለት ሰዓት ማስረዘም ይፈቅዳል። በበርካታ አገራት ሁለት ሰዓት በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል።

ጥያቄውን ወደ አገራችን አሠሪና ሠራተኛ ህግ ስናመጣው ‘ግዙፍ በሆነ የህግ ማርቀቅ ግድፈት’ የተነሳ ምላሹ በውዥንብር ታጅቧል። በአንቀጽ 63 የአማርኛው እና እንግሊዝኛው ቅጂ መካከል የሚታየው የጎላ ልዩነት አማርኛውን ‘ምላሽ አልባ’ አድርጎታል። አማርኛው ‘…የሳምንቱን የሥራ ቀኖች የሥራ ሰዓቶችን ማሳጠርና ልዩነቱን ለተቀሩት ቀናት ማደላደል ይቻላል።’ ብሎ በማብቃት ‘ለምን ያህል ሰዓት’ ማሳጠር እንደሚቻል ሳይጠቁም በዝምታ ያልፈዋል። የእንግሊዝኛው ቅጂ ግን በአማርኛው ላይ ያለውን የድልድል መሰረተ ሀሳብ ከተረጎመ በኋላ ‘…without extending the daily limits of eight hours by more than two hours’ የሚል ሐረግ በመጨመር ድንጋጌውን የተሟላ ይዘት እንዲላበስ ያደርገዋል። በእንግሊዝኛው ቅጂ መሰረት የቀን የሥራ ሰዓት ሊራዘም የሚችለው እስከ ሁለት ሰዓት ያክል ነው። ይህ የቅጂ አለመናበብ በቀድሞው አዋጅ ቁ. 377/96 ላይ አልነበረም።

የእንግሊዝኛውን ሀሳብ ይዘን አንቀጽ የ63 ን መልዕክት በቀላሉ ለመረዳት ድልድሉን በምሳሌ እንመልከት። ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ባለው የአንድ ሳምንት የሥራ ሰዓት መደበኛውን ስምንት ሰዓት በቀን እስከ ሁለት ሰዓት ድረስ ማራዘም ሲቻል አሠሪው ካሉት በርካታ አማራጮች ውስጥ የሥራ ሰዓቱን እንደሚከተለው ሊደለድል ይችላል።

  • ሰኞ- 10፤
  • ማክሰኞ 10፤
  • እሮብ 10፤
  • ሐሙስ 6፤
  • አርብ 6፤
  • ቅዳሜ 6 ሰዓት

ስሌቱን ስንሰራው የየቀኑ የስራ ሰዓት መዋዥቅ ቢታይበትም ሁሉም ሲደመሩ አርባ ስምንት ሰዓት ይሰጡናል። አሠሪው ከፈለገ ዘጠኝ ወይም ሰባት እያደረገ መደልደል ይችላል። መሰረታዊው ቁምነገር በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን በቀን ከአስር ሰዓት በሳምንት ደግሞ በአማካይ ከአርባ ስምንት ሰዓት በላይ ማሰራት አይፈቀድለትም። እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው ግን የእንግሊዝኛውን ቅጂ ይዘት የተከተልን እንደሆነ ነው።

ድልድል፡ ከአንድ ሳምንት በላይ

ሁለተኛው ዓይነት የሥራ ሰዓት ድልድል በአንቀጽ 64 የተጠቀሰው ሳምንታዊ ድልድል ሲሆን አማካዩን ለማስላት የተፈቀደው ከፍተኛ ጊዜ አራት ሳምንት ነው። በዚህ ድንጋጌ አሠሪው በሳምንት ከአርባ ስምንት ሰዓት ለበለጠ ጊዜ ለማሰራት አመቺ ሁኔታ ይፈጥርለታል። በዚህ ዓይነቱ ድልድል ሳምንታዊው የሥራ ሰዓት ከፍ ባለው መጠን በሌላ ሳምንት ደግሞ ዝቅ እያለ እስከ አራት ሳምንታት ይዘልቃል። በምሳሌ ለማስረዳት ያክል፤

ሳምንት 1፤ 52

ሳምንት 2፡ 54

ሳምንት 3፡ 44

ሳምንት 4፡ 42

የአራቱ ሳምንታት ጠቅላላ የሥራ ሰዓት 192 ሲሆን ይህ ለአራት ሲካፈል አማካዩን 48 ሰዓት ይሰጠናል።

የድንጋጌው መሰረታዊ ችግር የቀን አማካዩ ላይ ነው። የድንጋጌው ይዘት ጠቅላላው የሥራ ሰዓት ለጠቅላላው የሥራ ቀናት ሲካፈል /በላይኛው ምሳሌ 192 ሰዓት ለ 24 ቀናት ሲካፈል/ አማካዩ በቀን ከስምንት ሰዓት፤ በሳምንት ከአርባ ስምንት ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት ብቻ ነው የሚናገረው። የአንድ ሳምንት ከፍተኛው የቀን የሥራ ሰዓት በድንጋጌው አልተወሰነም። ስለሆነም ያለው አማራጭ የአንቀጽ 63 የሁለት ሰዓት ገደብ ተፈጻሚ ማድረግ ይሆናል። በዚህ ስሌት የአንድ ሳምንት ከፍተኛው መጠን እስከ 60 ሰዓት ይዘልቃል። በምሳሌ ለማየት ያክል በአራት ሳምንት ውስጥ ሳምንታዊው የሥራ ሰዓት እንደሚከተለው ሊደለደል ይችላል።

ሳምንት 1፤ 60 ሰዓት

ሳምንት 2፡ 60 ሰዓት

ሳምንት 3፡ 36 ሰዓት

ሳምንት 4፡ 36 ሰዓት

የምሽት ሽፍት ሥራ

የአገራችን አሠሪና ሠራተኛ ህግ መደበኛውን የቀን እና ሳምንታዊ የሥራ ሰዓት ጣሪያ ሲወስን አፈጻጸሙን በቀን እና በማታ አልለየም። የምሽት ሥራ ጠባይ በአንድ በኩል አድካሚ ሲሆን በሌላ በኩል ቤተሰባዊ ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከባድ እንደመሆኑ የተለየ የህግ ማዕቀፍ ይፈልጋል። ህግ ሊወስናቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የምሽት ሥራ ትርጓሜ (የሰዓት ገደቡ ስንት ሰዓት ጀምሮ ስንት ሰዓት ላይ እንደሚያበቃ)፤ የአሠሪው ትራንስፖርት የማቅረብ ግዴታ፤ በምሽት ሥራ የትርፍ ሰዓት ማሰራት ስለመቻሉ እንዲሁም በአንቀጽ 63 እና 64 ላይ የተመለከተው አማካይ የሰዓት ድልድል ለምሽት ሥራም ተፈጻሚ ስለመሆኑ በዋናነት ይነሳሉ።

 

[1] Prof. N. Valticos, International Labour Law (Springer-Science+ Business Media, 1979) ገፅ 134

[2] ላይቤሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ1919 ዓ.ም. ሲመሰረት ጀምሮ አባል ሆነዋል።

[3] አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 61/1/

[4] የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁ. 1064/2010 አንቀጽ 33

[5] የፌደራል ዐቃብያነ ሕግ መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ. 44/1991 አንቀጽ 16

[6] ደንብ ቁ. 157/2001 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አንቀጽ 16

[7] የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስተዳደር ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ. 155/2000  አንቀጽ 16

[8] በጥቂት አገራት ሳምንታዊ የሥራ ሰዓት ከአርባ ዝቅ ይላል። ለምሳሌ ቤልጅየም እና ፈረንሳይ Sangheon Lee, Deirdre McCann and Jon C. Messenger, Working Time Around the World፡ Trends in working hours, laws and policies in a global comparative perspective (Switzerland: International Labour Office, 2007) ገፅ 16

[9] ዕድሚያቸው ከ15 እስከ 18 የሆኑ ወጣት ሠራተኞች መደበኛው የቀን የሥራ ሰዓት በቀን ከ7 ሰዓት መብለጥ የለበትም። አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 93

[10] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 62/1/

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.