Ethiopian Employment Law

የህዝብ በዓላት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156-2011

ከ195 አገራት ውስጥ ኢራን በ30 የህዝብ በዓላት በአንደኛነት ትመራለች።[1] አዘርባጃን፤ ቡልጋሪያ እና ማሌዢያ በ19 በዓላት በሁለተኛ ደረጃ ተሰልፈዋል።[2] በደረጃው መጨረሻ ላይ የምትገኘው ኖርዌይ ስትሆን ያላት ሁለት የህዝብ በዓላት ብቻ ነው።[3] ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው የ195 አገራት አማካይ ሲወሰድ አስራ አንድ ላይ ይወድቃል።

ከአሠሪና ሠራተኛ ህግ አንጻር ሲቃኝ ቁምነገሩ የበዓላት ቁጥር ሳይሆን የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ ነው። በዚህ ረገድ አሜሪካ ያላት ደመወዝ የሚከፈልባቸው የህዝብ በዓላት ዜሮ ነው። ይህም ማለት ምንም እንኳን በአሜሪካ አስር በህግ የታወቁ የህዝብ በዓላት ቢኖሩም[4] አሠሪው በእነዚህ ሥራ ባልተሰራባቸው የበዓላት ቀናት ደመወዝ ለመቀነስ የሚከለክለው ህግ የለም። ሆኖም በአሜሪካ በርካታ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ጉዳዮች ለሥራ ውል እና ለህብረት ስምምነት የተተዉ እንደመሆናቸው አብዛኛው ሠራተኛ በስምምነት በሚወሰነው መሰረት ሥራ በማይሰራባቸው የህዝብ በዓላት ክፍያ ያገኛል።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ምን ያህል በህግ የታወቁ የህዝብ በዓላት አሉ? ለዚህ ቀጥተኛ መልሱ አስራ ሶስት ቢሆንም በህጉ እና በአተገባበሩ መካከል ያለውን ልዩነት መጠቆም ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ የሚከበሩ በዓላትን የሚወስነው የፀና ህግ በ1967 ዓ.ም. በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የወጣው ‘የሕዝብ  በዓላትና የእረፍት ቀን አዋጅ ቁ. 16/1967’ ሲሆን በዛው ዓመት የታወጀው ‘የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ ቁ.  28/1967 ደግሞ የአከባባር ስርዓታቸውን ይወስናል። ቀዳሚው አዋጅ የህዝብ በዓላትንና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 29/1988 ተሻሽሏል። ማሻሻያው ግን ‘የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል’ በሚል የካቲት 23 ቀን ሲከበር የነበረውን በዓል ‘የድል ቀን’ ተብሎ ሚያዝያ 27 እንዲከበር ከማድረግ ውጭ የነበሩትን የበዓላት ቁጥር አልጨመረም፤ አልቀነሰም።

በአዋጅ ቁ. 16/1967 ላይ ያሉትን የህዝብ በዓላት ዝርዝር ስንቆጥር ከላይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሻችን አስራ ሶስት መሆኑ ትክክል ነው። ሆኖም በዚህ አዋጅ ላይ መስከረም 2 ቀን ላይ እንደሚውል የተጠቀሰው ‘የሕዝብ ንቅናቄ (ሬቮሎሽን) ቀን መታሰቢያ’ ከደርግ መውደቅ በኋላ በተግባር እየተከበረ አይደለም። ህግን ከአተገባበሩ ጋር ስናስታርቅ የበዓላት ቁጥር ወደ አስራ ሁለት ይወርዳል። ይሁን እንጂ የማስታረቁ ሥራ በዚህ አይቆምም። ህግ ባያወቀውም በየዓመቱ ግንቦት 20 ላይ ‘ደርግ የወደቀበት /የተደመሰሰበት/’ በሚል በአማራጭ ‘ግንቦት 20’ የሚል ስያሜ ይዞ ላለፉት 30 ዓመታት ሲከበር ቆይቷል። ይሄ ደግሞ ቁጥራቸውን በተጨባጭ ወደ አስራ ሶስት ያሳድገዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ይሄ በዓል ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የድሮ ድምቀቱንና አገር አቀፋዊ መልኩን ይዞ እየተከበረ አይደለም። ወደፊት የሚኖረው ቦታ ማለትም እንደ ህዝባዊ በዓል ይከበራል? ወይስ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በህግ ሳይደነገግ ታስቦ ይውላል? ወይስ ከነጭራሹ ይረሳል? ለሚሉት ጥያቄዎች ግምታዊ መልስ መስጠት ሳያስፈልግ ጉዳዩን በአሠሪና ሠራተኛ ህግ መነጽር ካየነው በአሁኑ ወቅት አሠሪው ከአስራ ሁለት ህዝባዊ በዓላት ውጭ ላሉ ሌሎች (ግንቦት 20 ን ጨምሮ) በዓላት ሥራ ሳይሰራ ደመወዝ ለመክፈል አይገደድም።

ከቁጥር ባሻገር የፌደራል ስርዓት አወቃቀር በአሠሪና ሠራተኛ ህጉ የህዝብ በዓላት ድንጋጌዎች ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ያስነሳል። ‘ደመወዝ የሚከፈልባቸው የህዝብ በዓላት የማግኘት መብት’ ህገ-መንግስታዊ ዕውቅና አግኝቶ አፈጻጸሙ በህግ ቢወሰንም ‘የህዝብ በዓላት’ ትርጓሜ በህገ-መንግስቱ ሆነ በህጉ አልተካተተም። ባለመካተቱም አጥብቆ ጠያቂ ጥያቄ ያነሳል፤ ‘የህዝብ በዓላት ሲባል በክልል ደረጃ የሚከበሩ በህግ የታወቁ በዓላትን ይጨምራል? ወይስ ወሰኑ በመላ አገሪቱ በሚከበሩ የፌደራል በዓላት ብቻ ነው?’ በፌደራል እና በክልል መንግስታት የስልጣን ሽንሽን የአሠሪና ሠራተኛ ህግን መደነገግ ከክልሎች ‘የስልጣን ክበብ’ ቢወጣም በከልላቸው ብቻ የሚከበሩ በዓላትን በህግ የመደንገግ ስልጣን አላቸው። ይሄኔ ከአሠሪና ሠራተኛ ህጉ አንጻር ተጨማሪ ጥያቄ ይከተለላል። በክልሎች ህዝባዊ በዓላት ቀን ሥራ አይኖርም፤ ደመወዝስ? አሠሪው ሥራ ሳይሰራ ደመወዝ ለመክፈል የምገደደው በመላ አገሪቱ ለሚከበሩ ‘የፌደራል በዓላት’ ብቻ ነው ማለት ይችላል?

ለጥያቄዎቹ ቀጥተኛ ምላሽ ባናገኝም የአዋጁ አንቀጽ 73 አሉታዊ ምላሽ እንደ አቋም ለመያዝ አሳማኝ መከራካሪያ ሆኖ ቢቀርብ ያስኬዳል። የድንጋጌው ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

አግባብ  ባለው  ሕግ  መሠረት  የሚከበሩ  የሕዝብ  በዓላት  ደመወዝ  የሚከፈልባቸው ይሆናሉ።

የድንጋጌው ይዘት በጥሞና ሲታይ ‘በፌደራል መንግስት ህግ የታወቁ የህዝብ በዓላትን ብቻ’ ነቅሶ ለማውጣት ፍላጎት ያለው አይመስልም። ይህን የሚቃረን እይታ ያለው ሞጋች ‘የክልል ህግ’ ለምን ‘አግባብ ያለው ህግ’ ሆኖ እንደማይቆጠር ሚዛን የሚደፋ ሀሳብ መሰንዘር ይጠበቅበታል። ከድንጋጌው አወቃቀር አንጻር ‘ሀሳብ መሰንዘር’ የማይቻል ባይሆንም ቅሉ ሚዛን መድፋቱ ግን ‘እንደሚያጠራጥር አያጠራጥርም።’ ሲጠቃለል በበህገ-መንግስቱ ሆነ በአዋጁ ‘ደመወዝ የሚከፈልባቸው የህዝብ በዓላት’ በፌደራል መንግስቱ እና በክልል መንግስታት በህግ የታወቁ በዓላትን ይጨምራል።

በመቀጠል የህዝብ በዓላት ከሠራተኛው መብት አንጻር ህጋዊ ውጤታቸውን እንቃኛለን።

በበዓል ቀን አለመስራት

ደመወዝ እና ሥራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በመሆናቸው ሥራ ካልተሰራ ደመወዝ አይከፈልም። ይህ የአንቀጽ 54/1/ ጠቅላላ መርህ በህዝብ በዓላት ቀናት ላልተሰራ ተፈጻሚ አይሆንም። ስለሆነም የህዝብ በዓላት ደመወዝ ይከፈልባቸዋል።[5] በሌላ አነጋገር በእነዚህ ቀናት ሥራ ባለመሰራቱ ምክንያት ከሠራተኛው ላይ ደመወዝ አይቀነስም።[6] ይህ ጠንካራ የህጉ አቋም ግን ወርሃዊ ደመወዝተኛ ላልሆነ ሠራተኛ አይሠራም። በቁርጥ፤ በኮሚሽን፤ በሥራ መጠን ብሎም በሌላ ወርሃዊ ባልሆነ መንገድ ደመወዝ የሚያገኝ ሠራተኛ በህዝብ በዓላት ቀን ክፍያ የማግኘት ዕጣ ፈንታው ለሥራ ውሉ ወይም ለህብረት ስምምነት ተትቷል።[7]

በበዓል ቀን መስራት

በህዝብ በዓላት ቀን ሥራ መስራት አስፈላጊ በሚሆኑባቸው ሁኔታዎች በመደበኛው 8 ሰዓት ሥራ ከተሠራ ከደመወዝ በተጨማሪ የአንድ ሰዓት ደመወዝ በሁለት ተባዝቶ በበዓሉ ቀን ለተሰራው እያንዳንዱ ሰዓት ይከፈላል።[8] ክፍያው ወርሃዊ ደመወዝተኛ ያልሆኑ ሠራተኞችን ማጠቃለሉ ግልጽ አይደለም። በሥራ ውላቸው ወይም በህብረት ስምምነታቸው ደመወዝ የማይቀነስባቸው ከሆነ በበዓል ቀን የሚሰራ ስራ ተጨማሪ እንደመሆኑ ተጨማሪ ክፍያ ሊከፈላቸው ይገባል። በተቃራኒው ደመወዝ የሚቀነስ ከሆነ ግን በበዓል ቀን መስራት ተጨማሪ ክፍያ አያስገኝም፤ መደበኛው /ደመወዝ/ በሌለበት ‘ተጨማሪ’ አይኖርምና።

በበዓል ቀን ትርፍ ሰዓት መስራት

በሕዝብ  በዓላት  ቀን  ለሚሠራ  የትርፍ  ሰዓት  ሥራ  ለመደበኛ ሥራ በሰዓት የሚከፈለው ደመወዝ  በሁለት  ተኩል ተባዝቶ ይከፈላል።[9] የድንጋጌው ይዘት ግልጽነት ቢኖረውም በአንቀጽ 68/1/ መ ላይ ‘ሁለት ተኩል’ ከሚለው ለጥቆ በቅንፍ (በአንድ  ነጥብ አምስት) በሚል የተሰነቀረው አገላለጽ የማሻሻያው የህግ ማርቀቅ እና ህግ አወጣጥ ቸልተኝነት ተጨማሪ ማሳያ ሆኗል። ስህተቱ የተፈጠረው በፊደል የተገለፀን መጠን እንደገና በፊደል ለመግለጽ መሆኑ ደግሞ ቸልተኝነቱን አግዝፎታል።

[1] https://www.qppstudio.net/ በ 14/12/2020 የተጎበኘ

[2] https://www.hrdive.com/press-release/20190625-ranking-of-the-countries-with-the-most-public-holidays-1/ በ 14/12/2020 የተጎበኘ

[3] ዝኒ ከማሁ

[4] https://www.opm.gov/policy-data-oversight/pay-leave/federal-holidays/#url=2020 በ 14/12/2020 የተጎበኘ

[5] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 73

[6] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 74/1/

[7] ዝኒ ከማሁ

[8] አዋጅ ቁ. ቅ1156/2011 አንቀጽ 75/1/

[9] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 68/1/ መ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.