Ethiopian Employment Law

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ‘ስውር’ ማሻሻያዎች

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 377/96 በማሻሻል ሂደት ውስጥ የሙከራ ጊዜ መጠን እንዲሁም የሥራ ሰዓት ባለማክበርና በመቅረት የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ስለሚቋረጥበት ሁኔታ አከራካሪ ምናልባትም አጨቃጫቂ በመሆን ጎልተው ወጥተዋል። የገነነ የንትርክ ርዕስ ባይሆኑም የዓመት ፈቃድ እና የወሊድ ፈቃድ መጠን እንዲሁም አዲስ የተጨመሩት ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በርካታ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሌሎች የማሻሻያ ነጥቦችም ከሠራተኛና አሠሪ ማህበራት እና ኮንፌዴሬሽን የድጋፍ ብሎም የተቃውሞ አስተያየት ቀርቦባቸዋል። የመጨረሻው ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ የረቂቁ ሐተታ ዘምክንያት /አጭር ማብራሪያ/ ከረቂቁ ጋር በምክር ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ ተለቋል።

ማብራሪያው በእያንዳንዱ ማሻሻያ በተደረገበት ጉዳይ ሰፊ ገለጻ መያዝ ባይጠበቅበትም የቃላት ማስተካከያም ቢሆን እያንዳንዱን ለውጥ ምንም ሳያስቀር መዘርዝር ይኖርበታል። ‘ዋና’ በሚላቸው ላይ ብቻ ራሱን የሚገድብ ማብራሪያ የ‘ሐተታ ዘምክንያት’ ን መስፈርት አያሟላም። ‘ዋና’ ያልተባሉ ተቆርጠው የቀሩ ለውጦች በአንባቢ በዋናነት ሊፈረጁ እንደሚችሉ መረሳት የለበትም።

አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ማሻሻያ በአዋጅ ቁ. 377/96 ላይ የተቀነሱ፤ የተጨመሩና የተለወጡ ድንጋጌዎችን ለብቻ በመለየት በሌላ ህግ ከማውጣት ይልቅ የተከተለው አቅጣጫ ነባሩን ህግ ‘ሽሮ’ እንደ አዲስ መጻፍ ነው። ሁሉም ማሻሻያዎች በአጭር ማብራሪያው ላይ ያልተዘረዘሩ በመሆኑ በተጨባጭ የተደረገውን እያንዳንዱን ለውጥ ለመለየት ነባሩንና አዲሱን አዋጅ ጎን ለጎን እያስተያዩ ማነጻጸር ይጠይቃል። አሰልቺና አድካሚ ቢሆንም በማሻሻል ሂደት ሆነ በምክር ቤቱ ውይይት ላይ ያልተነሳ ከዚህም አልፎ በማብራሪያው የተዘለለ ለውጥ መኖሩን ለማጣራት ከእንዲህ ዓይነት ንፅፅር የተሻለ አማራጭ የለም።

በንፅፅሩ አማካይነት የሚገኝ በማብራሪያው የተዘለለ ማሻሻያ እንደ ‘ስውር ማሻሻያ’ ይቆጠራል። በዚህ መልኩ ከተደረጉ ማሻሻያዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

ጡረታ እና የሥራ ጉዳት ካሣ

በአዋጅ ቁ. 377/96 ማስተካከያ ይፈልጉ ከነበሩ ኢ-ፍትሐዊ ድንጋጌዎች መካከል አንቀጽ 109/1/ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። አንቀጹ የጡረታ ተጠቃሚነትን ከሥራ ጉዳት ካሣ ጋር አላግባብ ያቆራኛል። ሆኖም አሉታዊ ውጤቱ በሁለት ምክንያቶች ገኖ አልወጣም። የተፈጻሚነት አድማሱ መጥበብ አንደኛው ምክንያት ነው። አንቀጹ የመንግስት የልማት ድርጅት ሠራተኞችን ብቻ ይጠቅሳል። እነዚህ ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው የሚያገኙት ካሣ የሚወሰነው በጡረታ ሽፋናቸው ወይም በመድን ሽፋናቸው ነው። የመድን ሽፋን ከሌላቸው ሆኖም በጡረታ ህግ ከተሸፈኑ ካሳውን በተመለከተ የጡረታ ህጉ ተፈጻሚነት ያገኛል።

ሁለተኛው ምክንያት አብዛኞቹ የመንግስት የልማት ድርጅት ሠራተኞች የመድን ሽፋን ስላላቸው የጡረታ ህጉን ተፈጻሚነት በተግባር የተገደበ አድርጎታል። ለመሆኑ የጡረታ ህጉን ኢ-ፍትሐዊ ያሰኘው ምንድነው? በዚህ ነጥብ ላይ ዝርዝር ማብራሪያው ከዚህ በፊት በለጠፍኩት ‘የአካል ጉዳት ስሌት’፤ ‘በጡረታ ያልተሸፈነና የመድን ዋስትና ያልተገባለት ሠራተኛ’ በሚለው ስር ይገኛል። በአጭሩ ለማስቀመጥ ያክል የሥራ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የሚከፈለው ካሳ በጡረታ ህግ ሲሰላ በንፅፅር ከአሠሪና ሠራተኛ ህጉ ስሌት በእጅጉ ማነሱ ብቻ ሳይሆን የጡረታ መብትን ያሳጣል። በሌላ አነጋገር ለጉዳት ካሳ ከተከፈለ በጡረታ ዕድሜ መድረስ ምክንያት የሚከፈለው የጡረታ አበል አይኖርም።

የጡረታ መብትን ከሥራ ጉዳት ካሳ የሚቀላቅለው የአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 109/1/ በማሻሻያው መፍትሔ ይሰጠዋል ሲባል ጭራሽ አድማሱን አስፍቶ ሁሉንም በአዋጅ ቁ. 1156/2011 የሚገዙ ሠራተኞችን ጠቅልሎ በወሰኑ ስር ከቷቸዋል። በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ሁሉም ሠራተኞች የጡረታ ሽፋን አላቸው። የውይይት እና የክርክር ርዕስ ያልሆነው የአንቀጽ 109/1/ ማሻሻያ ድሮ ‘የመንግስት የልማት ድርጅት ሠራተኞች’ ይል የነበረውን በማውጣት ለሁሉም ሠራተኞች ተፈጻሚ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ በውጤቱ አሠሪውን በሥራ ላይ ለሚደርስ ጉዳት በአዋጅ ቁ. 1156/2011 የጉዳት ካሳ ከመክፈል ሀላፊነት ነጻ ሲያደርገው ሠራተኛውን ደግሞ ካሳውን ሲቀበል የጡረታ መብቱን ይነሳዋል።

የአዋጁ ሐተታ ዘምክንያት በአንቀጽ 109/1/ ላይ ስለተደረገው ስር-ነቀል ማሻሻያ ሳይናገር ሳይጋገር ያልፍና በቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ ማለትም 109(2) ስለተደረገው ማሻሻያ ማብራራት ይጀምራል።

ጡረታ እና የስንብት ክፍያ

ማሻሻያው ጡረታን ከሥራ ጉዳት ካሳ ጋር እንዳቆራኘው ሁሉ ከስንብት ክፍያ ጋርም አቆራኝቶታል። በዚህ ረገድ ስለተደረገው ማሻሻያ የአዋጁ ሐተታ ዘምክንያት የስንብት ክፍያ ለማግኘት የጡረታ አበል ለመቀበል ብቁ አለመሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ትኩረት ሰጥቶ በአጭሩ ካብራራ በኋላ ሌላውን ‘ስውር ማሻሻያ’ ግን አድበስብሶ አልፎታል። ለመጥቀስ ያክል፤

አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ በአንቀጽ 39 (1) ሥር የሥራ ስንብት ክፍያ የሚያስገኙ የቅጥር ውል ማቋረጫ ምክንያቶች ተዘርዝረው ተቀምጠዋል። ተመሳሳይ መብት የሚያስገኙ ተጨማሪ የቅጥር ውል ማቋረጫ ምክንያቶችም አዋጅ ቁጥር 494/1998 ይዞት በመጣ ማሻሻያ ተዘርዝረው ቀርበዋል። ረቂቁ ሌሎቹን አዋጆች የሚሽር ስለሆነ እነዚህ ተበታትነው የነበሩት ዝርዝሮች ለተደራሽነት ሲባል ወደ አንድ ሰነድ ማጠቃለል ስለሚገባው ይህንኑ ሥራ ተከናውኗል። አንዳንዶቹ የቅጥር ውል ማቋረጫ ምክንያቶችም ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።  (ሰረዝ የተጨመረ)

እንዲሁ እንደዋዛ ‘ማስተካከያ ተደርጓል’ በሚል ተድበስብሶ የታለፈው ማሻሻያ በይዘቱ ነባር መብትን ከህጉ የፋቀ መሰረታዊ ማሻሻያ ነው። በአዋጅ ቁ. 494/1998 በጡረታ መገለል (የጡረታ ዕድሚ በመድረሱ) ለስንብት ክፍያ ከሚያበቁ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል። ሆኖም መብቱ የሚሰራው የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ወይም የጡረታ ለሌለው ሠራተኛ ብቻ ነው። በማሻሻያው ይህ ተቆርጦ ወጥቷል። በማሻሻያው የተነሳ የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ሆነ የጡረታ መብት የሌለው ሠራተኛ በጡረታ ሲገለል የስንብት ክፍያ የማግኘት መብት ያጣል። እንዲህ ዓይነት ግዙፍ የመብት ማሳጣት ውጤት ያለውን ማሻሻያ ሐተታ ዘምክንያቱ ‘ማስተካከያ’ በሚል አድበስብሶ ያለፈው ለምን ይሆን?

የመብት እና ግዴታዎች መታገድን ተከትሎ የውሉ መቋረጥ

ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች መታገድን በሚገዛው የህጉ ክፍል /አንቀጽ 17-22/ ላይ መጠነኛ እና መሰረታዊ የሚባሉ በድምሩ አራት ማሻሻያዎች የተደረጉ ቢሆንም ሀተታ ዘምክንያቱ አንደኛውን ብቻ በመምዘዝ በአንድ ዓረፍተ ነገር ለማብራራት ሞክሯል። ሰነዱ በአንቀጽ 22 ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ይጠቅሳል፤ ‘አሠሪውም ለሥራ የሚቀርበውን ሠራተኛ ወደ ሥራ መመለስ አለበት’ ይል የነበረው ተቀይሮ ‘አሠሪውም ለሥራ የሚቀርበውን ሠራተኛ ከሙያው ጋር አግባብነት ባለው የሥራ መደብ ላይ ቀድሞ ሲከፈለው የነበረውን ደመወዙን በመጠበቅ ወደ ሥራው መመለስ አለበት።’ በሚል ተሻሽሏል።

ከአንቀጽ 17-22 ከተደረጉት ማሻሻያዎች ውስጥ በመሰረታዊነት ገዝፎ የሚወጣው የአንቀጽ 21/2/ ማሽሻያ ነው። ይህ አንቀጽ ቀድሞም ቢሆን በችግር የተተበተበ ነበር። ማሻሻያው ሌላ ትብታብ ጨምሮበት የማይፈታ ቋጠሮ አድርጎታል። በአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 21/2/ አሠሪው በተፈቀደለት የዕገዳ ጊዜ ወይም በህጉ በተወሰነ ከፍተኛው የ90 ቀናት የዕገዳ ጊዜ ውስጥ ሥራውን እንደገና ለመቀጠል የማይችል መሆኑን የሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ካመነ ሠራተኛው በአንቀጽ 39 እና 44 የተመለከቱትን ጥቅሞች የማግኘት መብቱን ይጠብቅለታል። የአዋጅ ቁ. 1156/2011 ማሻሻያ ‘ካመነ’ ከሚለው ለጥቆ ‘ሠራተኛው የቅጥር ውሉ ተቋርጦ’ የሚል ሐረግ ጨምሮበታል።

የዚህ ስውር ማሻሻያ እንደምታ እንደሚከተለው ተዳሷል።

የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት

የዕገዳ ጊዜ ማብቃት የዕገዳ ምክንያት ማብቃትን አያሳይም። አሠሪውን የሚመለከቱ የማገድ ምክንያቶች አሠሪው ከተፈቀደለት ወይም በህጉ ከተቀመጠው የዘጠና ቀናት ጊዜ በላይ ሊዘልቁ ይችላሉ። ይህ ሲሆን የአዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 21(2) ሠራተኛውን የስንብት ክፍያ እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ የማግኘት መብቱን ይጠብቅለታል። ክፍያዎቹ የሥራ ውል መቋረጥ ውጤቶች እንደመሆናቸው ውሉ የሚቋረጥበት መንገድ ሳይታወቅ ስለክፍያ ማውራት ከማደናገር የዘለለ ፋይዳ የለውም። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚወስነው ወይም በህጉ ከተቀመጠው የዘጠና ቀናት ማብቃት በኋላ የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት (መቀጠል) በራሱ የሥራ ውልን የሚያቋርጥ በቂ ምክንያት አይደለም። ይህ ፈጦ የወጣ የህጉ ግድፈት በማሻሻያው መስተካከል ቢኖርበትም ከመስተካከል ይልቅ ችግሩ ገዝፎ እንዲባባስ ተደርጓል።

አዋጅ ቁ. 1156/2011 በአንቀጽ 21(2) ላይ ‘ካመነ’ ከሚለው ቀጥሎ ‘ሠራተኛው የቅጥር ውሉ ተቋርጦ’ የሚል ሐረግ ጨምሮበታል። ‘ካመነ’ በሚል ልኩ የማይታወቅ ተለጣጭ ስልጣን (discretion) የሚያጎናጽፈው ማሻሻያ ስልጣኑ የተሰጠው አካል ይህን ስልጣን በመገልገል ስለሚሰወደው እርምጃ ወይም ውሳኔ በዝምታ አልፎታል። ‘ሠራተኛው በአንቀጽ 39 እና 44 የተመለከቱትን ጥቅሞች የማግኘት መብት አለው።’ የሚለው የቀድሞው አዋጅ ሆነ ‘ሠራተኛው የቅጥር ውሉ ተቋርጦ በአንቀጽ 39 እና 44 የተመለከቱትን ጥቅሞች የማግኘት መብት አለው።’ የሚለው አዲሱ አዋጅ ሁለቱም በውሉ ዕጣ ፈንታ ላይ ማን ወሳኝ እንደሚሆን ግልጽ አላደረጉትም። ውሉ የሚቋረጠው በህግ በተደነገገው መንገድ? በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን ውሳኔ? ወይስ በአሠሪው አነሳሽነት?

ከሥራ ውል የሚመነጭ መብትና ግዴታ ለጊዜው መታገድና የዕገዳው ምክንያት አለማብቃት በቀጥታ ወደ ሥራ ውል መቋረጥ ያመራበት ምክንያት ሐተታ ዘምክንያቱ ሊመልሰው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ አሠሪው ሥራውን እንደገና ለመቀጠል የማይችል ከሆነ በአንድ ተቋም ዕምነት ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጥ ይገባል። ማረጋገጫ ከተገኘ ደግሞ የሥራ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው በአንቀጽ 24/4/ (ድርጅቱ በመዘጋቱ) ወይም በአሠሪው አነሳሽነት በአንቀጽ 28(2) ሀ (በቅነሳ) ነው። ዕገዳ መኖሩ የሁለቱን ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ሊያስቀር እንደማይገባ ግልጽ ነው።

የዕገዳ ጊዜ ማብቃትን ተከትሎ አሠሪው ምን ማድረግ አለበት? ወይም ውሉን በየትኛው ድንጋጌ መሰረት ማቋረጥ አለበት? የሚለው ጥያቄ ሊያስጨንቅ የሚገባው አሠሪውን እንጂ አስፈጻሚውን አካል አይደለም። ለዕገዳው ምክንያት የሆነው ነገር ከዕገዳ ጊዜው በላይ ቢቀጥልም ባይቀጥልም የዕገዳ ምክንያት አለማብቃት ህጋዊ ውጤቱ በአንቀጽ 22 ላይ ከተቀመጠው ውጪ አይወጣም። የዕገዳ ጊዜው እስካበቃ ድረስ የዕገዳው ምክንያት አበቃም አላበቃም ለጊዜው ታግደው የነበሩት መብትና ግዴታዎች ውጤት ማግኘት ይጀምራሉ። ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ‘ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ካመነ’ የሚወስነው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ከዕገዳው ማብቃት በኋላ ከአቅም በላይ የሆነው ምክንያት ወይም ያልታሰበ የገንዘብ ችግር ካልተወገደ የመዋቅር ለውጥ ማድረግ፣ የቅነሳ እርምጃ መውሰድ፣ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ብሎም መፍትሔ ሊሆን የሚችል የተለየ ዕቅድ መቀየስና መተግበር በአጠቃላይ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አይቶ ይበጀኛል የሚለውን መወሰን የአሠሪው ስልጣን ነው።

1 reply »

  1. ጥሩ እይታ ነው አብርሽ ፣ በተለይ አንደኛውን ሃሳብ/ የጡረታ እና የስንብት ክፍያ መቀላቀልን / በተመለከተ አንድ ክርክር ጀምሬያለሁ ውጤቱን አብረን እናያለን።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.