Ethiopian Employment Law

የሳምንት እረፍት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156-2011

እ.ኤ.አ በ1921 የወጣው የሳምንት እረፍት (ኢንዱስትሪ) ስምምነት ቁጥር 4 /Weekly Rest (Industry) Convention, 1921 (No. 14) የመጀመሪያው የሳምንት እረፍት ጊዜን የሚወስን የዓለም ዓቀፍ የሥራ ድርጅት ስምምነት ሲሆን የተፈጻሚነት ወሰኑ ከስያሜያው ለመረዳት እንደሚቻለው በማምረቻ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች ነው። በቀጣይ በንግድ፤ በቢሮ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለተሰማሩ ሠራተኞች የሳምንት እረፍት /ንግድ እና ቢሮ ሥራ/ ቁጥር 106 /Weekly Rest (Commerce and Offices) Convention, 1957 (No. 106)/ እ.ኤ.አ በ1957 ዓ.ም. ወጥቷል። ሁለቱ ስምምነቶች ተፈጻሚ ከሚሆኑበት የኢኮኖሚ ዘርፍ በስተቀር በመሰረታዊ ይዘታቸው ልዩነት አይታይባቸውም። ኢትዮጵያ ሁለቱንም ስምምነቶች እ.ኤ.አ በ 1991 ዓ.ም. አጽድቃለች።[1]

በስምምነቶቹ የተደነገጉት መሰረታዊ ደንቦች በአሠሪና ሠራተኛ ህጋችን ታቅፈዋል። የእረፍቱ መጠን በሰባት ቀናት ውስጥ ያልተቆራረጠ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ጊዜው ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከሚቀጥለው ንጋት 1 ሰዓት ያለውን ጊዜ እንዲጨምር ተደርጎ ይታሰባል።[2] ቀኑ የሚውለው ዕሁድ ላይ ሲሆን ለድርጅቱ ሠራተኞች በሙሉ በአንድ ላይና በአንድ ጊዜ ይሰጣል።[3] ከእረፍት መጠን እንዲሁም ከአቆጣጠሩ በስተቀር የሚውልበት ቀን እና አሰጣጡ በህብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ በተለየ አኳኋን ሊወሰን ይችላል።

ልዩ የሳምንት እረፍት ቀን

በህብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ በተለየ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር የሳምንት እረፍት ቀን እሁድ ላይ ይውላል።[4] የሥራ ደንብ በአሠሪው በተናጠል የሚዘጋጅ አስገዳጅ ደንብ ነው። ህጋዊ ውጤት እንዲያገኝ የሠራተኛው ሆነ የሠራተኛ ማህበር ይሁንታ አያስፈልገውም። ከዚህ አንጻር አሠሪው የሳምንት እረፍት የሚውልበትን ቀን ለመወሰን ያልተገደበ ስልጣን የተሰጠው ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህ ስልጣን በአንቀጽ 70 ላይ አሠሪው ድርጅት በሚያከናውነው ሥራ ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ጠባይ ተመስርቶ ገደብ ተበጅቶለታል። ስለሆነም የሳምንት እረፍት ቀን በእሁድ ምትክ በሌላ ቀን እንዲውል በሥራ ደንብ መወሰን የሚቻለው በሚከተሉት ሥራዎችና አግልግሎቶች ላይ ብቻ ነው።

  • ለጠቅላላው ሕዝብ ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎች ወይም ለጤንነት፣ ለመዝናኛ ወይም ለባህላዊ ጉዳይ የሚከናወኑ ሥራዎች
  • በአንቀጽ 137/2/ የተመለከቱት ለሕዝብ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች[5]
  • በሥራው ባሕርይ ወይም በቴክኒክ ምክንያት ቢቋረጥ ወይም ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍ ችግር ወይም ጉዳት የሚያስከትል ስራ

የማካካሻ የሳምንት እረፍት ቀን

አሠሪው የሳምንት እረፍት ቀን የሚውልበትን ቀን ከመቀየር በተጨማሪ የድርጅቱን መደበኛ ተግባር የሚያደናቅፉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሠራተኛው በሳምንት እረፍቱ ቀን ማሰራት ተፈቅዶለታል። አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች በአንቀጽ 71/1/ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፤

  • አደጋ ሲደርስ ወይም የሚደርስ መሆኑ ሲያሰጋ
  • ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ሲያጋጥም
  • በአስቸኳይ የሚሰራ ሥራ ሲያጋጥም

የተጠቀሱት ሁኔታዎች በማጋጠማቸው በሳምንት እረፍት ቀን ሥራ ሲሰራ የሚከፈል ተጨማሪ ክፍያ የለም። ሆኖም ‘በሌላ ጊዜ’ አሠሪው የማካካሻ የሳምንት እረፍት ቀን ለመስጠት ይገደዳል። ‘በሌላ ጊዜ’ የሚለው የህጉ አገላለጽ ‘ማካካሻ’ መቼ ሊሰጥ እንደሚገባ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ በአንደኛው ሳምንት ያልተወሰደ የሳምንት እረፍት መሰጠት ያለበት በቀጣዩ ሳምንት ወይስ ከአንድ ሳምንት በላይ ሊተላለፍ ይችላል? ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ አሠሪው በሳምንት እረፍት ቀን ሥራ ማሰራት የሚችለው ለምን ያህል ሳምንታት ነው?

ሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተ አንቀጽ 69/4/ በተዘዋዋሪም ቢሆን የመለሰው ይመስላል። ድንጋጌው በስራው ባህሪ ምክንያት ሠራተኛው የሳምንት ዕረፍቱን ለመጠቀም የማይችል እንደሆነ በወር ውስጥ ለ4 ቀናት ዕረፍት እንዲያገኝ በአሠሪው ላይ አስገዳጅ ግዴታ ይጥላል። ይህም ማለት በእረፍት ቀን ማሰራት አስፈላጊ የሚያደርጉ አስገዳጅ ሁኔታዎች እስከ አንድ ወር ድረስ ከዘለቁ ሠራተኛው ለሶስት ሳምንታት ያክል ያለ እረፍት የሚሰራበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በወር ውስጥ አራት የእረፍት ቀናት የህጉ አነስተኛው መጠን በመሆኑ አራተኛው ሳምንት ላይ ሠራተኛው ለአራት ቀናት ያክል ማረፍ አለበት።

 

[1]https://www.ilo.org/dyn/normlex/en/f?p=1000:11300:0::NO:11300:P11300_INSTRUMENT_ID:312251 እንዲሁም https://www.ilo.org/dyn/normlex/en/f?p=1000:11300:0::NO:11300:P11300_INSTRUMENT_ID:312159 በ13/13/2020 የተጎበኘ

[2] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 69/1/ እና /3/

[3] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 69/2/

[4] አዋጅ ቁ. 1156/2011 አንቀጽ 69/2/ ሀ

[5] በተጠቀሰው ድንጋጌ እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት ድርጅቶች የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፤

ሀ) የአየር መንገድ አገልግሎት፤

ለ) የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፤

ሐ) የውሃ አገልግሎት የሚሰጡ እና የከተማ ጽዳት የሚጠብቁ ድርጅቶች፤

መ) የከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፤

ሠ) ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድሃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶች እና የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች፤

ረ) የእሳት አደጋ አገልግሎት፤ እና

ሰ) የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት

1 reply »

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.