አብርሃም ዮሃንስ

አሠሪና ሠራተኛ ህግ መጽሐፍ 2ኛ የተሻሻለ ዕትም

አሠሪና ሠራተኛ ህግ መጽሐፍ 2ኛ የተሻሻለ ዕትም ከ10 ቀናት በኋላ አራት ኪሎ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት በሚገኘው አንከቡት መጽሐፍት መደብር በገበያ ላይ ይውላል።

መጽሐፍ 3 አዲስ ምዕራፎች የተጨመሩበት ሲሆን የአዲሱ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156 ማሻሻያዎችን እንዲሁም ተጨማሪ የሰበር ውሳኔዎችን አካቷል።

ከዚህ በታች ያለው የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ጽሑፍ ነው።

የዓለም ዓቀፉ የሥራ ድርጅት የተቋቋመበት ሰነድ ‘ጉልበት ሸቀጥ አይደለም’ በማለት መሪ መርህ አድርጎ ያውጃል።አሠሪና ሠራተኛን የሚያገናኘው ድልድይ የሥራ ውል ቢሆንም በቅጥር ግንኑነት የውል ህግ ሚና ኢሚንት ነው፤ ምክንያቱም ጉልበት ሸቀጥ አይደለምና። ይህ መሰረታዊ መርህ ግንኙነቱን ሰብዓዊ መልክ ያለብሰዋል። የአሠሪና ሠራተኛ ህግ በሁለቱ ጎራዎች መካከል ገዝፎ የሚታየውን የመደራደር አቅም ልዩነት በማስታረቅ ሠራተኛው ሰብዓዊ ክብሩ፤ ደህንነቱና ጤናው ተጠብቆ ለራሱ፤ ለቀጣሪው ብሎም ለአገሩ የሚተርፍ አምራች ዜጋ እንዲሆን በስምምነት የማይቀየሩ አነስተኛ ደንቦችን ይደነግጋል። በዚህ ገፅታው ህጉ ለሠራተኛው ከለላ ይሰጣል፤ ጥበቃ ያደርጋል። ከለላውና ጥበቃው የአንድ ወገን ቢመስልም ተጨባጩ እውነታ የሚሳየን ግን አሠሪውም የህጉን ጥላ ከለላ ያገኛል። አሠሪና ሠራተኛ ህግ ባይኖር የኢንዱስትሪ ሰላም አይኖርም። ግንኙነቱ ይሻክራል። በሥራ ቦታ ቀውስ ይነግሳል። ትርፍ ለኪሳራ ቦታውን ያስረክባል። በዚህ መልኩ ሰፋ አድርገን ካየነው የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ለአንዲት አገር ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

የዚህ መጽሐፍ 2ኛ የተሻሻለ ዕትም የተሻሻለውን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 1156/2011 እንዲሁም ተጨማሪ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን በማካተት ሶስት ምዕራፎች ተጨምሮበት ይዘቱና አቀራረቡ ተሻሽሎ ለአንባቢያን ቀርቧል። ሠራተኞች፤ አሠሪዎች፤ የህግ ባለሞያዎችና ሌሎችም ህጉን በጥልቀት ለማወቅ ፍላጎቱ ያላቸው አንባቢያን ይህ መጽሐፍ ግንዛቤያቸውን የሚያሰፋ ጠቃሚ ምንጭ ይሆናቸዋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

ፀሐፊው (አብርሃም ዮሐንስ ሐይሉ)

 

 

 

 

አንከቡት አሳታሚ ፥ አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ

ankebootpublishing@gmail.com

+251966215342

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.