Site icon Ethiopian Legal Brief

ዓለም ዓቀፍ የስንዴ ሽያጭ- ውል በተናጠል መሰረዝ የሰ/መ/ቁ 155880  አግሪኮም ኢንተርናሽናል ኩባንያ እና የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን እና

የሰ/መ/ቁ.155880

ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም.

ዳኞች –

መዓዛ አሸናፊ

ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)

ቀነአ ቂጣታ

ተሾመ ሽፈራው

ፀሐይ መንክር

አመልካች – አግሪኮም ኢንተርናሽናል ኩባንያ -ጠበቃ አለሙ ደነቀው ቀረቡ  ተጠሪ-የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን-ጠበቆች ሜሮን ሰለሞን እና ዶ/ር ዘውድነህ በየነ ቀረቡ

መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ

ጉዳዩ የስንዴ ግዢ ውልን መሰረት ያደረገ ሲሆን ክርክሩ የተደረገው ግራ ቀኙ እ.ኤ.አ ኖቨንበር 25/2011 ባደረጉት ስምምነት መሰረት አለመግባባታቸውን በኢትዮጵያ መሰረታዊ ህግ (Substantive Law) እንዲሁም በ Grain and Feeds Trading association (GAFTA)  የሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 125 (GAFTA Rules NO. 125) መሰረት በሚቋቋም የግልግል ዳኝነት አካል በእንግሊዝ ሃገር ለመቋጨት በተስማሙት መሰረት ነው፡፡

 1. የአሁን ተጠሪ ለግልግል ጉባኤው ባቀረበው ክስ 200,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማቅረብ አመልካች የውል ግዴታ ገብቶ ማቅረብ ባለመቻሉ ጥቅምት 9/2005 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ ሰጥቼ ውሉን በማቋረጥ ሌላ ግዢ ፈጽሜያለሁ፤ ስለሆነም በፈፀምኩት አዲስ ግዢ ምክንያት ለ 11,549,000.00 (አስራ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺህ) የአሜሪካ ዶላር ተጨማሪ ወጪ ተዳርጌያለሁ፤ ይህንኑ ገንዘብ እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው፡፡
 2. አመልካች ለቀረበበት ክስ በሰጠው መልስ ስንዴውን ለማቅረብ ያልቻልኩት ስንዴውን ለማቅረብ የሚያስፈልገውን የባንክ የመተማመኛ ሰነድ (L/C) ተጠሪ አስተካክሎ በወቅቱ ለማቅረብ ባለመቻሉ በራሱ ጥፋት ነው፤ የራሱን ግዴታ ባልተወጣበት ሁኔታ ውሉን ለማቋረጥም ሆነ ኪሳራ ለመጠየቅ አይችልም፤ ከዚህም ሌላ ውሉ በሚተዳደርበት በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ተገቢው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ተጠሪ ውሉን ሊያቋርጥ አይችልም፤ ስለሆነም ካሳ እንድከፍል ሊጠይቀኝ አይችልም፤ ይህ የሚታለፍ ቢሆንና የደረሰ ጉዳት አለ ከተባለ ተጠሪ ሊጠይቅ የሚችለው ለ200,000 ሜትሪክ ቶን የዋጋ መጠን በተሰጠው የመልካም ሥራ አፈፃፀም ሰነድ (Performance Bond) ማለትም 5,855,000.00 (አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ) የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡
 3. ጉዳዩ በዚህ መልኩ የቀረበለት የግልግል ጉባኤ ክርክርና ማስረጃውን መርምሮ ተጠሪ ውሉን ያቋረጠው በአግባቡ ነው፤ ውሉን ለማቋረጥ የተሰጠው ማስጠንቀቂያም የኢትዮጵያ ህግ የሚጠይቀውን የሚያሟላ ነው፤ እንዲሁም ተጠሪ የጠየቀውን የካሳ መጠን የማይከፍልበት ምክንያት የለም በማለት አመልካች ለተጠሪ 11,549,000.00 (አስራ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺህ) የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍል የካቲት 20/2010 ዓ.ም ባሳለፈው ፍርድ ወስኗል፡፡
 4. የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ አመልካች መጋቢት 18/2010 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር ማመልከቻ ውሳኔው የተሰጠው በኢትዮጵያ ህግ ላይ ተመስርቶ መሆኑንና ውሳኔውም የመጨረሻና በሁለቱ ወገኖች ላይ ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ መደንገጉን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 42239 ከሰጠው ውሳኔ አንጻር ጉዳዩን ተቀብሎ ለመዳኘት እንደሚችልና ህገመንግስታዊ ሥልጣን ያለው መሆኑን ጠቅሶ ማመልከቻውን አቅርቧል፡፡
 5. አመልካች በሰበር ማመልከቻው በ09/02/2005 ዓ.ም ተሰጠ የተባለው ማስጠንቀቂያ በ16/02/2005 ዓ.ም ከተጠሪ በተላከ መልዕክት የተነሳና የተሰረዘ በመሆኑ፤ ይህም ባይሆን ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ተጠሪ የራሱን ግዴታ ሳይወጣና በቂ ጊዜም ሳይሰጥ የፍትሐብሔር ህጉንና የሰበር ውሳኔዎች ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ሳያሟላ ስለሆነ በአግባቡ ባልተቋረጠ ውል ላይ ተመስርቶ አመልካች 11,5490,00.00 (አስራ አንድ ሺህ አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ) የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍል የተሰጠው የግልግል ጉባኤ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ ይህ የሚታለፍ ከሆነም ለደረሰው ጉዳት መከፈል ያለበት ለ 200,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግራቀኙ ካደረጓቸው ውሎች ተለይቶ በተሰጠው የፐርፎርማንስ ቦንድ ገንዘብ መጠን ማለትም 5,855,000.00 (አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ) የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው ተብሎ እንዲወሰን አመልክቷል፡፡
 6. የሰበር ማመልከቻው በአጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ የግልግል ጉባኤው የሰጠው ውሳኔ ተዋዋይ ወገኖች ውሉን

በተናጠል ለመሰረዝ (Unilateral Cancillation of Contract) ስለሚችሉበት አግባብ በሰበር መዝገብ ቁጥር 57280 ከተሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም አኳያ ተገቢነቱን መርምሮ ለመወሰን በሚል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ እና ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡

 1. ተጠሪ መስከረም 22/2011 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበውን ጉዳይ ለማየት ስልጣን የለውም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና በፍሬነገሩም መልስ ሰጥቷል፡፡
 2. ተጠሪ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የሌለው ስለመሆኑ ባቀረበው የመቃወሚያ ክርክር የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ባልሆነ የግልግል ዳኝነት የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲታይ የሚቀርብበት የህግ መሰረትም ልምድም የለም፤ የግልግል ዳኝነቱ ውሳኔ እንደ ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የመጨረሻ ውሳኔ ሆኖ እንዲቆጠር በተዋዋዮች መካከል የተደረገ ስምምነት ስለሌለ ውሳኔውን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደተሰጠ ውሳኔ ቆጥሮ በመሰረታዊ የህግ ስህተት ስም ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የሚደረግበት የህግ መሰረት የለም፤ ጉዳዩ በሰበር እንዲታይ የሚቀርብበት የህግ አግባብ የለም እንጂ አለ እንኳ ቢባል ሊቀርብ

ይገባ የነበረው የግልግል ዳኝነቱ ህጋዊ መቀመጫ ሆኖ በተመረጠውና በተዋዋይ ወገኖች ተቀባይነትን ባገኘው እ.ኤ.አ በ1996 በፀደቀው የዩናይትድ ኪንግደም የአርቢትሬሽን ህግ መሰረት ለለንደን የከፍተኛው ፍርድ ቤት የንግድ ችሎት ብቻ ነበር፤ አመልካች የግልግል ዳኝነት አካሉ የመጀመሪያ ጉባኤ (First Tier Tribunal) በሰጣቸው ውሳኔዎች ቅር በመሰኘት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የይግባኝ አቤቱታውን ለለንደን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ንግድ ችሎት አቅርቦ ውድቅ ተደርጎበታል፤ አመልካች እ.ኤ.አ. በፌብሪዋሪ 27 ቀን 2018 በአምስት ዳኞች የተላለፈውን የ GAFTA የግልግል ዳኝነት የይግባኝ ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ ቀሪ እንዲደረግ፣ እንዲሻር ወይም እንዳይፈፀም ለማድረግ አቤቱታውን ማቅረብ የነበረበት የግልግል ጉባኤው መቀመጫ ሀገር ህግ በሚፈቅደው መሰረት ሥልጣን ላለው ለለንደኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ንግድ ችሎት ነበር፤ ስለሆነም ይህ የሰበር አቤቱታ ስልጣን ለሌለው ፍ/ቤት የቀረበ በመሆኑ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡ አመልካች በሰ/መ/ቁ 42239 የተሰጠውን ውሳኔ በመጥቀስ አቤቱታውን ያቀረበ ቢሆንም በሁለቱ መዛግብት ክርክር ያስነሳው ጉዳይ፣ የውሉ ሁኔታዎች እና የግልግል ጉባኤው መቀመጫ ፈጽሞ የተለያየ በመሆኑ በሰ/መ/ቁ 42239 የተሰጠው ገዢ ትርጉም በዚህ መዝገብ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም፤ ሰበር ችሎቱ የመጨረሻና ይግባኝ የማይባልባቸው ናቸው የተባሉ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎችን ተቀብሎ ማየት የሚችለው የመጨረሻውን የግልግል ዳኝነት ወሳኔ ያስተላለፈው የግልግል ዳኝነት አካል ህጋዊ መቀመጫ (Juridical or Legal Seat) በኢትዮጵያ ከሆነ ብቻ ነው፤ ከዚህም ሌላ ተዋዋይ ወገኖች ውሳኔያቸውን የሚገዛው መሰረታዊ (የሥረ ነገር) ህግ (Substantive Law) የኢትዮጵያ ህግ በመሆኑና የኢትዮጵያ ህግ ሲተረጎም ደግሞ መሰረታዊ ስህተት ከተፈጸመበት ሊያቃና የሚችለው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ነው ከሚል ግንዛቤ የቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም፤ በግራቀኙ የተመረጠው መሰረታዊ ህግ የኢትዮጵያ ህግ ቢሆንም ክርክር ሂደቱን የሚገዛው የሥነ ሥርዓት ህግ ደግሞ የግልግል ዳኝነት አካሉ (የ GAFTA የአርቢትሬሽን የሥነ ሥርዓት ህግ) ህጋዊ መቀመጫ ሀገር ህግ በመሆኑ ይህ ሰበር ችሎት “መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል” የተባለውን የግልግል ዳኝነት ጉባኤ ውሳኔ የማየት ሥልጣን የለውም፡፡ በተዋዋይ ወገኖች የአርብትሬሽን የሥነ ሥርዓት ህጎች የሚወሰኑትም ከፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ለመራቅ ሲባል ነው፡፡ በሌላም በኩል አመልካች በአቤቱታው የገለፀው ጥቅምት 9/2005 ዓ.ም የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ጥቅምት 16/2005 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ተነስቷል? ወይስ አልተነሳም? የሚለው ክርክር ማስረጃን የሚመለከት በመሆኑና ውሳኔም የተሰጠው ማስረጃዎቹ ታይተው በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው ክርክር የህግ ክርክር አይደለም ለሰበር ችሎቱ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ሊታይ የሚችል አይደለም ተብሎ ውድቅ ይደረግልን በማለት መቃወሚያውን አቅርቧል፡፡

 1. ተጠሪ ከዚህም ሌላ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ዝርዝር መልስ ሰጥቷል፡፡ የመልሱ ይዘት ባጭሩ ሲታይ በተጠሪ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ አልተነሳም፤ በግራ ቀኙ መካከል በተገባው ውልና የውል ማራዘሚያ መሰረት አመልካች ሥንዴውን ማቅረብና ማጠናቀቅ የነበረበት ጊዜ ባለማቅረቡ ተጠሪ ጥቅምት 13/2005 ዓ.ም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፤ ከዚህ በኃላ በአመልካች በቀረበ ጥያቄ መሰረት ተጠሪ ጥቅምት 16/2005 ዓ.ም የጻፈው ደብዳቤም ማስጠንቀቂያውን ያለቅድመ ሁኔታ አንስቻለሁ የሚል ሳይሆን ቅድመ ሁኔታዎችን በግልጽ አስቀምጦ ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ማስጠንቀቂያው ሊቀር እንደሚችል ገልጾ ነው፤ አመልካች ሁኔታዎችን ያላሟላ መሆኑንና ጥቅምት 13/2005 ዓ.ም የተሰጠው ማስጠንቀቂያ የፀና ስለመሆኑ የግልግል ዳኝነት ጉባኤው አጣርቶ ውሳኔ ሰጥቶበታል፤ ስለሆነም ማስጠንቀቂያው ተነስቷል ወይም ተሰርዟል በማለት ያቀረበው ክርክር የውልም ሆነ የህግ መሰረት የሌለው ነው፡፡ የተሰጠው ማስጠንቀቂያም በፍትሐብሔር ህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች እንዲሁም በሰ/መ/ቁ 57280 የተሰጠውን የህግ ትርጉም ባሟላ መልኩ የተደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ ተጠሪ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ህጋዊ ግዴታ ባይኖርበትም ተጠሪ በአግባቡ ህጉን የተከተለ ማስጠንቀቂያ የሰጠ በመሆኑና የግልግል ዳኝነት ጉባኤው ማስረጃዎችን መርምሮ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ያልተነሳ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲሁም ተጠሪ የሚጠበቅበትን የውል ግዴታ ቢወጣም አመልካች ግን ግዴታውን ያልተወጣ መሆኑን በማስረጃ አረጋግጦ የወሰነ በመሆኑ ቅሬታው ውድቅ ይደረግ፡፡ የመልካም ሥራ አፈጻፀም ዋስትና (ቦንዱ) በተመለከተም በአመልካች አቤቱታ የተጠቀሰው መጠን ስህተት ነው፤ በውሉ አንቀጽ 13 እንደተቀመጠው የመልካም ሥራ አፈጻፀም ዋስትናው የሚገባው የውሉን ዋጋ 10% መሆኑን ስለሚደነግግ ይህ ሲሰላ 14,637,500.00 የአሜሪካ ዶላር ይሆናል፤ አመልካች የ200,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ዋጋን መሰረት በማድረግ ያስቀመጠው የዋስትና ገንዘብ መጠን የተሳሳተ እና የውል መሰረት የሌለው ነው፤ ውሉ የመልካም ሥራ አፈጻፀም ዋስትና (ቦንድ) መጠኑን ሲያስቀምጥ የዋሱን ኃላፊነት መጠን ለመገደብ እንጂ የጉዳቱን መጠን ለመገደብ እንደሆነ ያስቀመጠው ነገር የለም፤ ከቦንዱ በላይ ጉዳት ቢደርስ ተጨማሪ ካሳ መጠየቅ አይቻልም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ ነገርም የለም፤ በተጨማሪም በውሉ አንቀጽ 17 ላይ liquidated damage የተቀመጠ ሲሆን ይህም በአንቀጽ 13 ላይ የተቀመጠው የጉዳት ካሳ የመልካም ሥራ አፈጻፀም ዋስትና ሰነድ የጉዳት መጠኑን በአጠቃላይ ለመገደብ የተቀመጠ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ የግልግል ጉባኤው ውሳኔ እንዲፀና በማለት ተከራክሯል፡፡
 2. አምልካች ጥቅምት 23/2011 ዓ.ም በተጻፈ የመልስ መልስ በመቃወሚያው ላይ የበኩሉን ክርክር አቅርቧል፡፡ በዚህም መሰረት የጋፍታ የግልግል ጉባኤ (ቦርድ) የሰጠው ውሳኔ ጉዳዩ የሚዳኝበትን የኢትዮጵያ ህግ የጣሰ ነው በማለት የቀረበን ቅሬታ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 80 እና በአዋጅ ቁጥር 454/97 መሰረት ለማየት ሥልጣን ያለው ሰበር ሰሚው ችሎት ነው፤ ሁለቱ ወገኖች ጉዳያቸውን በኢትዮጵያ መሰረታዊ ህግ (substantive law) መሰረት ለመገዛት ፈቃደኛነታቸውን በውል ከገለፁ የኢትዮጵያን ህግ አስመልክቶ ክርክር ቢነሳ ጉዳዩ ከሰበር ሰሚው ስልጣን ውጪ የሚሆንበት የህግ መሰረት የለም፤ ይህ ያልተገደበ የሰበር ስልጣን ፍርዱ በየትም ቦታ ቢሰጥ ወይም ውሳኔ የሰጠው አካል የተከተለው ሥርዓት (Procedure) ምንም ይሁን የተሰጠው ውሳኔ የኢትዮጵያ የህግ መስፈርቶችን አያሟላም የሚል ጥያቄ ከተነሳ ውሳኔ የሚሰጠው በህግ ስልጣን የተሰጠው ሰበር ሰሚ ችሎት ብቻ ነው፤ ተዋዋዮች በአንድ የግልግል ተቋም አማካኝነት በተወሰነ ሃገር ለመዳኘት ፈቃድ መስጠታቸው የግልግል ተቋሙ የሚመራበትን ሥርዓት (procedure) መቀበላቸውን ከሚያረጋግጥ በቀር መሰረታዊውን ህግ በተመለከተ ያላቸውን መብት ተነፍገዋል ማለት አይደለም፡፡ አመልካች በተለያዩ ጊዜያት ይግባኝ ሲያቀርብ የነበረው ለለንደኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው አሁንም በዚያው መሰረት ሊያቀርብ ይገባል ተብሎ በተጠሪ በኩል የቀረበውን ክርክር በተመለከተም ፍሬ ነገርን ወይም መሰረታዊ (የስረ ነገር) የህግ ስህተትን አስመልክቶ ለለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረብነው አንዳችም ይግባኝ የለም፤ በርግጥ ጉዳዩ በግልግል ጉባኤ በመታየት ላይ እያለ ሁለት የሥነ ሥርዓት ጥያቄዎች ላይ በመመስረት አቤቱታ ለለንደን ፍርድ ቤት አቅርበናል፡- ይኸውም በመጀመሪያ ጉዳዩ ለግልግል ጉባኤ በቀረበበት ወቅት የአቤቱታ ማቅረቢያው ጊዜ አልፏል በማለት፣ ሁለተኛ ደግሞ ክርክሩ አልቆ ውሳኔውን ከመስማታችን በፊት ተዋዋይና ከሳሽ ወገን የነበረው የኢትዮጵያ አህል ንግድ ድርጅት አስቀድሞ ፈርሶ እያለ በፈረሰው ድርጅት ሥም ሲካሄድ የነበረው ክርክር እንደተካሄደ ሊቆጠር አይገባም በማለት የቀረበ የሥነ ሥርዓት ተቃውሞ ነው፤ የዚህ አይነት የሥነ ሥርዓት ተቃውሞ ደግሞ ክርክሩ የሚካሄድበትን ሥርዓት መሰረት በማድረግ በይግባኝ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መቅረቡ በአግባቡ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠሪ ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ብሏል፡፡ ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም አመልካች የቀደመ ክርክሩን በማጠናከር ውሉ የተቋረጠው ያላግባብ ስለሆነ የግልግል ጉባኤው ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግ፤ ይህ የሚታለፍ ከሆነም የካሳው መጠን በመልካም ሥራ አፈጻፀም ቦንዱ ላይ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን 5,855,000.00 (አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አምስት ሸህ) የአሜሪካን ዶላር ነው ተብሎ እንዲወሰን ጠይቋል፡፡
 3. የጉዳዩ አመጣጥና የግራቀኙ የጽሁፍ ክርክር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያው ላይ ክርክራቸውን በቃል ሰምቷል፡፡ ጉዳዩንም የሠበር አቤቱታ ከቀረበበት ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምረናል፡፡
 4. እንደመረመርነው በሰበር አጣሪ ችሎቱ እንዲታይ የተያዘው ጭብጥ ፍሬ ጉዳዩን የተመለከተ ቢሆንም ከዚህ በፊት የችሎቱን ምላሽ የሚጠይቀው ነጥብ የአሁን ተጠሪ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ተቀብሎ ለመወሰን ስልጣን የለውም በማለት ያቀረበው ክርክር ነው፡፡ ይህን ጭብጥ ለመመለስ ግራቀኙ በገቡት ስምምነት መሰረት ጉዳዩ በግልግል ጉባኤ ውሳኔ ያገኘበትን አግባብ እና የተሰጠውን ውሳኔ ተፈጥሮ፤ መሰል የአማራጭ ሙግት መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች አቤቱታ የሚቀርብበትን ሁኔታ፤ እንዲሁም በሀገራችን የተዘረጋው የሰበር ስርዓት አላማና የህጉን ማእቀፍ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡
 5. በሀገር ውስጥ የግልግል ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ተከራካሪዎቹ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይግባኝ የሚሉበትና ውሳኔው እንዲሻር ማመልከቻ የሚቀርብበት ሂደት በሥነ ሥርዓት ህጉ ተመልክቷል፡፡ ከፍትሐብሄር ሥነ ሥርዓት ህጉ ግልጽ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ መረዳት እንደሚቻለው የግልግል ውሳኔው እንዲሻር የሚቀርበውን ማመልከቻ በመቀበል እንዲሁም የአፈፃፀም ክርክሩን በመወሰን ፍርድ ቤቶች የግልግል ዳኝነት ሂደትን ይቆጣጠራሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች የግልግል ዳኛ በመሾም፣ በመሻር፣ ጉዳይን ወደ ግልግል በመምራት እንዲሁም ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ፍርዱን ሊመረምሩ የሚችሉበት ሁኔታ በህጉ ተደንግጓል፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህጉ ከአንቀጽ 350 እስከ 354 ስለ ይግባኝ፤ ከአንቀጽ 355 እስከ 356 ብይኑ ስለሚሻርበት እና ማመልከቻው ስለሚቀርብበት ሁኔታ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ፍርድ ቤቶች የግልግል ዳኝነቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ማሳካቱና እና

በህጉ አግባብ ጉዳዩን መርቶ መወሰኑን እንዲያረጋግጡ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በአንፃሩ እነዚህ ድንጋጌዎች በውጪ ሀገራት የተሰጡ የግልግል ዳኝነቶችን በቀጥታ ይመለከታሉ ባይባልም የሥነ ሥርዓት ህጉ ከአንቀጽ 456 እስከ 461 ድረስ ከውጪ አገር ስለሚመጡ የግልግል ውሳኔዎች አፈፃፀም ሂደትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

 1. በሌላ በኩሉ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ያለው ልምድ እና የዳበረ የግልግል ዳኝነት ህግጋት ያላቸው የበርካታ ሀገራት ህጎች እንዲሁም አለማቀፍ ስምምነቶች እንደሚያረጋግጡት የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እንደመደበኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተቆጥረው የግልግል ውሳኔዎችን በፍርድ ውሳኔ ለማስቀረት (seating aside) ወይም ለማሰረዝ (annulment) አቤቱታ ሊቀርብ የሚችለው በተዋዋይ ወገኖች መካከል ይኸው በስምምነት ሲደገፍ፣ ተዋዋይ ወገኖች በመረጡት የግልግል ዳኝነት የሥነ ሥርዓት ህግ (Institutional Arbitration Rule) ይኸው ሲደገፍ፣ እንዲሁም የግልግል ዳኝነቱ ህጋዊ መቀመጫ ሀገር (Juridical or Legal Seat) ህግ ይህንኑ የሚደግፍ ሲሆን ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫ በእንግሊዝ ሀገር መሆኑ እንዲሁም ግራቀኙ ባደረጉት ስምምነት ውስጥ የግልግል ዳኝነቱ ውሳኔ እንደ ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ሆኖ እንዲቆጠር የተደረገ ስምምነት አለመኖሩ አላከራከረም፡፡ የተመረጠው የግልግል ዳኝነት መቀመጫ ሀገር ህግም ቢሆን በግልግል ጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ በዚያው ሀገር ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ እንዲቀርብ የሚፈቅድ ነው፡፡ ስለሆነም የግልግል ጉባኤው ውሳኔ እንዲሻር/እንዲሻሻል አቤቱታው ለዚህ ፍርድ ቤት በቀጥታ የቀረበው ይህን የሚፈቅድ ህግ እንዲሁም የተዋዋይ ወገኖች ሥምምነት በሌለበት ነው፡፡
 2. ከዚህ ጋር በተያያዘ አመልካች የግልግል ዳኝነት አካሉ የመጀመሪያ ጉባኤ (First Tier Tribunal) በሰጣቸው ውሳኔዎች ቅር በመሰኘት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የይግባኝ አቤቱታውን ለለንደን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ንግድ ችሎት አቅርቦ ውድቅ ተደርጎበታል፤ በመጨረሻው ውሳኔ ላይም ቅሬታው ሊቀርብ የሚገባ በዚሁ አግባብ ነው በማለት ተጠሪ የተከራከረ ሲሆን አመልካች በሰጠው መልስ ሁለት ጊዜ የይግባኝ አቤቱታ ለለንደን የከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርቦ እንደነበር ሳይክድ ያቀረበው ይግባኝ የስነ ሥርዓት ጉዳዮችን በተመለከተ ብቻ እንደነበርና ፍሬ ነገርን ወይም መሰረታዊ (የስረ ነገር) የህግ ስህተትን አስመልክቶ ለለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ እንደሌለ ተከራክሯል፡፡ እንደሚታወቀው በአንድ በተሰጠ ውሳኔ ላይ ይግባኝ የማለት መብት መሰረታዊ መብት ሆኖ የሚቆጠር ሲሆን የይግባኝ መብቱ ዝርዝር አፈፃፀም ግን የሚወሰነው በሥነ ሥርዓት ህጎች ነው፡፡ ስህተቱ የሥነ ሥርዓትም ሆነ የፍሬ ነገር ቢሆን ሊሰማና ሊታረም የሚችለው ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ባለው የሥነ ሥርዓት ደንብ እየተመራ ነው፡፡ ስለሆነም የግልግል ዳኝነቱ አካል የሚመራበት ሥነ ሥርዓት ላይ ግራ ቀኙ ስምምነት አድርገው በዚሁ አግባብ ሁለት ጊዜ የይግባኝ አቤቱታ ለለንደኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረቡ ባላከራከረበት ሁኔታ አመልካች ፍሬ ነገርን ወይም መሰረታዊ የህግ ስህተትን አስመልክቶ ለመደበኛው ፍርድ ቤት ያቀረብኩት ቅሬታ የለም በማለት ያቀረበው ክርክር የሥምምነታቸውን ይዘት እና ጉዳዩ የሚገዛበትን ህግና ልምድ የተከተለ ባለመሆኑ

ተቀባይነት የለውም፡፡

 1. በሌላ በኩል አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ሁለቱ ወገኖች ጉዳያቸውን በኢትዮጵያ መሰረታዊ ህግ

(substantive law) መሰረት ለመገዛት ፈቃደኛነታቸውን በውል ከገለፁ የኢትዮጵያን ህግ አስመልክቶ ክርክር ቢነሳ ጉዳዩ ከሰበር ሰሚው ስልጣን ውጪ የሚሆንበት የህግ መሰረት የለም፤ ይህ የሰበር ስልጣን ፍርዱ በየትም ቦታ ቢሰጥ ወይም ውሳኔ የሰጠው አካል የተከተለው ሥርዓት (Procedure) ምንም ይሁን የተሰጠው ውሳኔ የኢትዮጵያ የህግ መስፈርቶችን አያሟላም የሚል ጥያቄ ከተነሳ ውሳኔ የሚሰጠው ሰበር ሰሚ ችሎቱ ብቻ ነው በሚል ነው፡፡ ለዚህ ክርክራቸው መሰረት የሚያደርጉትም በሰ/መ/ቁ 42239 የተሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም እና የህገ መንግስቱን አንቀጽ 80 እንዲሁም የአዋጅ ቁጥር 454/97 ድንጋጌን ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ሁኔታ በግልግል ጉባኤ የሚሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ አስገዳጅና ይግባኝ የማይባልበት ስለመሆኑ በተከራካሪዎች ስምምነት የተደረገበት ቢሆን ጉዳዩ በሰበር ችሎት ሊታይ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለው ነጥብ አከራካሪ ሆኖ ይታያል፡፡ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በጉዳዩ ላይ አስቀግሞ ሰጥቶት የነበረውን አስገዳጅ ትርጉም በፓናል ችሎት በመለወጥ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ 42239 ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ኃ/የተ/የግል ኩባንያ እና ዳኒ ድሪሊንግ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ መካከል በተደረገው ክርክር ሰበር ችሎቱ የግልግል ውሳኔን የመጨረሻነት እንዲሁም በግልግል ዳኝነት አካላት የተሰጡ ውሳኔዎችን በተመለከተ ፍርድ ቤቶች ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና አስመልክቶ አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቶ ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት “…… አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች በኢትዮጵያ የህግ ስርዓት ውስጥ ተካተው የሚገኙ ሲሆን እነዚህን የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ፍርድ ቤቶች የሚያበረታቱበት አጋጣሚ እንዳለ ሁሉ የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ መኖሩን…………፤ ከዚህ አኳያ አንድ ጉዳይ ለሰበር የመቅረቡ ሁኔታ በህገ መንግስቱ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ ሥልጣን በመሆኑ የሰበር ስርዓቱ ሊጫወተው ከተፈለገው ዐቢይ ዓላማ አንፃር ሲታይ ጉዳያቸው በግልግል ዳኝነት እንዲታይላቸው የተስማሙ ወገኖች የግልግል ዳኝነቱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው በማለት ስለተስማሙ ብቻ ጉዳዩ በሰበር ሥርዓቱ እንዳይታይ ፍላጎት አሳይተዋል ተብሎ መሰረታዊውን የህግ ስህተት ላለማሳረም ምክንያት ሊሆን የሚችል አይደለም….” በማለት የኢፌዴሪ ህገ

መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ)፣ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10፣ እና አዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በማድረግ ወስኗል፡፡ ነገር ግን ሊታይ የሚገባው ይህ ውሳኔ ለተያዘው ጉዳይ ያለው ተገቢነትና አስገዳጅነት ነው፡፡ ከውሳኔው መገንዘብ እንደሚቻለው በጉዳዩ ላይ በሰበር ችሎቱ ውሳኔ የተሰጠው የግልግል ችሎቱ መቀመጫ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ተከትሎ በመሆኑ አሁን በእጃችን ካለው ጉዳይ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ በተያዘው ጉዳይ ግራቀኙ ባደረጉት የግዥ እና ሽያጭ ውል የግልግል ዳኝነት መቀመጫውን በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ያደረገ የግልግል ተቋም የመረጡ ሲሆን በ Grain and Feeds Trading association (GAFTA)  የሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 125 (GAFTA Rules NO. 125) መሰረት ለመዳኛትም ተስማምተዋል፡፡ በሰ/መ/ቁ 42239 የተሰጠው ውሳኔ ደግሞ ይህን መሰረት አድርጎ የተሰጠ ባለመሆኑ ከተያዘው ጉዳይ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ የፍሬ ነገር ወይም የህግ ክርክሮች በሌሉበት ሁኔታ አስቀድሞ የተሰጠ የሰበር ውሳኔ በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚደረግበት የህግ አግባብ እንደሌለም ከአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) ግልጽ ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 1. በሌላ በኩል የሰበር አቤቱታ የቀረበበት የግልግል ጉባኤ ውሳኔ (APPEAL AWARD NO: 4496 & 4515) መግቢያ ላይ በተራ ቁጥር 1.4 ሥር የሚከተለው ተመልክቷል፡-

“As the seat of the arbitration is in England and an Award subject to English procedural and Ethiopian substantive law, it therefore follows that it is an English Award for the purpose of recognition and enforcement under the terms of the 1958

New York Convention on the Recognition and Enforcement of Foreign Arbitral

Awards”

የዚህ የአማርኛ ትርጉምም እንደሚከተለው ይነበባል፡-

“የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫ ቦታ እንግሊዝ ሀገር በመሆኑና የዳኝነቱ ሂደት የሚመራው በእንግሊዝ የሥነ ስርዓት ህግ፣ የውሉን ይዘት በተመለከተ ግን ተፈፃሚው የኢትዮጵያ ህግ በመሆኑ፤ የግልግል ውሳኔው እንደ እንግሊዝ አገር ውሳኔ ተቆጥሮ ውሳኔው ዕውቅና የሚያገኘውና ተፈፃሚም የሚሆነው ከአንድ አግር ውጪ የተሰጠን ውሳኔ አፈፃፀም በተመለከተ በ1958 የወጣው የኒዮርክ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ነው”

 1. ከዚህ የግልግል ጉባኤ ውሳኔ ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው የግልግል ውሳኔው ከአንድ አገር ውጪ የተሰጠ ውሳኔ (በእንግሊዝ) ተደርጎ የሚወሰድና ውሳኔው ዕውቅና የሚያገኘውና ተፈፃሚም የሚሆነው በ1958 የወጣው የኒዮርክ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን መሰረት ስለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ለሰበር ክርክሩ አወሳሰን ሲባል ይህ የግልግል ጉባኤው ውሳኔ ተፈጥሮና በ1958 የወጣው የኒዮርክ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን በሀገራችን የህግ ሥርዓት ያለውን ቦታ በአግባቡ መመርመር ይጠይቃል፡፡
 2. ከሀገር ውጪ የሚሰጡ የግልግል ውሳኔዎችን በሃገራት ውስጥ በማስፈፀም ረገድ እ.ኤ.አ በ1958 የወጣው ለግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች ዕውቅና መስጠትና ማስፈፀምን የሚመለከት የኒውዮርክ ኮንቬንሽን (The New York Convention on the Recognition and Enforcement of Arbitral Awards) እንደ ትልቅ ስኬትና እመርታ

ይወሰዳል፡፡ በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚመሰክሩለትም ከሁሉም ሃገራት ፍላጎት ጋር በሚስማማ መልኩ የግልግል ውሳኔዎች በቀላሉ የሚፈፀሙበትን መንገድ ዘርግቷል ተብሎ ይታመናል፡፡ በሃገራችንም ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ተያይዞ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጦች እየተጠናከሩ በመሆኑና ግዙፍ ኩባንያዎች የገበያ አድማሳቸውን በማስፋት ወደ ሃገራችን በማቅናት መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ በመሆኑ ይህን ዘላቂ ለማድረግ፤ በተለይም ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የንግድ ማህበር (World Trade Organization) አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት አንዱ መመዘኛ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፤ እንዲሁም አለመግባባቶች በግልግል መቋጨታቸው ከሚኖረው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር ሃገራችን የኒውዮርኩን ኮንቬንሽን ለማጽደቅ በሂደት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡

 1. የኒዮርኩ ኮንቬንሽን እስካሁን በሃገራችን አልፀደቀም ማለት ግን በህግ ሥርዓታችን ውስጥ ምንም ቦታ አልተሰጠውም ማለት እንዳልሆነ ተገቢነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሀገራችን ውስጥ በግልግል ጉባኤዎች የሚሰጡ ውሳኔዎች የሚፈፀሙት የፍርድ ውሳኔዎች በሚፈፀሙበት መንገድ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 319 በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል ከውጪ ሀገር የሚመጡ የግልግል ውሳኔዎች የሚፈፀሙበት ራሱን የቻለ ሥርዓት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ህጉ ከአንቀጽ 456 እስከ 461 ተደንግጎ ይገኛል፡፡
 2. ከኒዮርኩ ስምምነት ይዘትና ከሃገራችን ህጎች መገንዘብ እንደሚቻለው በውጭ ሃገራት የሚሰጡ የግልግል ውሳኔዎችን በማስፈፀም ረገድ የኢትዮጵያ ህግ ከኒዮርክ ስምምነት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ መመሳሰሉን ለማሳየት የሚከተሉትን ነጥቦች በማነፃፀር ማንሳት ይቻላል፡-
  • የስምምነቱ አንቀጽ 1(3) ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 458(ሀ) እና 461(1)(ሀ)
  • የስምምነቱ አንቀጽ 3 ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 461(1) ይዘት ጋር
  • ከኒውዮርኩ ስምምነት በዋናነት የሚጠቀሱት በአንቀጽ 5 ሥር የተጠቀመጡት ሁኔታዎች ሲሆኑ እነዚህ ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ ህግ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰሉ መሆኑን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 461(1)(ለ)-(ሠ) ከተዘረዘሩት ጋር በማነፃፀር መረዳት ይቻላል፡፡
 3. በዚህ መልኩ በኒውዮርክ ስምምነት እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 461 መካከል የቃል በቃል መመሳሰል እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለውን በአግባቡ ማየትም ያስፈልጋል፡፡ በኒውዮርክ ስምምነት እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህጉ መካከል ላለው መመሳሰል በምክንያትነት የሚጠቀሰው የሥነሥርዓት ህጉ የወጣው የኒውዮርኩ ስምምነት በወጣ በጥቂት አመታት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ የሥነ ሥርዓት ህጉ እ.ኤ.አ በ08/10/1965 የወጣ ሲሆን የኒዮርክ ስምምነት ለፊርማ ክፍት የሆነው እ.ኤ.አ በ31/12/1958 ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ህግ አውጭው በውጪ ሃገራት የተሰጡ የግልግል ውሳኔዎችን ለማስፈፀም እንዲሁም አፈፃፀሙን ለመቃወም ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶችን ከኒዮርክ ስምምነት ሊወስድ መቻሉ ይታመናል፡፡
 4. ስለሆነም በተያዘው ጉዳይ ግራቀኙ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ የግልግል ጉባኤው የሰጠው ውሳኔ እንደ እንግሊዝ አገር ውሳኔ የተቆጠረ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ለማሳረም በሚል ለዚህ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተገቢ ባይሆንም ውሳኔው ዕውቅና የሚያገኘውና ተፈፃሚም የሚሆነው ከአንድ አገር ውጪ የተሰጠን ውሳኔ አፈፃፀም በተመለከተ በ1958 በወጣው የኒዮርክ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን መሰረት በመሆኑ በዚህ አግባብ አቤቱታ ሊቀርብና ሊስተናገድ አይገባም ማለት ግን አይሆንም፡፡
 5. በአጠቃላይ ግራቀኙ ወገኖች በ Grain and Feeds Trading association (GAFTA) የሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 125 (GAFTA Rules NO. 125) መሰረት በሚቋቋም የግልግል ዳኝነት አካል በእንግሊዝ ሃገር ክርክራቸውን ለመቋጨት የተስማሙ በመሆኑና የግልግል ዳኝነቱ ውሳኔ የተሰጠውም ይህን ስርዓት ተከትሎ በመሆኑ፤ አመልካቹም በግልግል ጉባኤው ውሳኔ ላይ የይግባኝ ቅሬታውን በውል ስምምነታቸው እና በህግ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ለንደን ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቅሬታውን በየጊዜው ያቀርብ እንደነበር የተረጋገጠ በመሆኑ፤ አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ሰበር ችሎት ለማቅረብ በዋቢነት በጠቀሰው የሰ/መ/ቁ 42239 የተሰጠው የህግ ትርጉም የግልግል ጉባኤው መቀመጫ በተዋዋዮች በስምምነት ወይም ከህግ በተሰጠ ስልጣን በውጪ ሀገር እንዲሆን ተደርጎ በውጪ ሀገር የተሰጠ ፍርድን የሚመለከት ባለመሆኑ፤ እንዲሁም ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 (በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2 እንደተሻሻለ) የተሰጠው መሰረታዊ የህግ ስህተትን የማረም ስልጣን የተያዘውን ጉዳይ የሚመለከት ባለመሆኑ አመልካች ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት

የለውም ብለናል፡፡ ተከታዩንም ወስነናል፡፡

ው ሣ ኔ

 1. አመልካችና ተጠሪ እ.ኤ.አ ኖቨንበር 25/2011 ባደረጉት ስምምነት መሰረት አለመግባባታቸውን በ Grain and Feeds Trading association (GAFTA) የሥነ ሥርዓት ህግ 125 (GAFTA Rules NO. 125) መሰረት

በሚቋቋም የግልግል ዳኝነት አካል በእንግሊዝ ሃገር ለመቋጨት በተስማሙት መሰረት የተቋቋመው ጉባኤ የሰጠው ውሳኔ (APPEAL AWARD NO: 4496 & 4515) በኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ታይቶ እንዲታረም የቀረበው የሰበር ማመልከቻ በግራቀኙ የተደረገውን ስምምነት እና ህጉን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 244(2)(ሀ) እና 245(2) መሰረት ወስነናል፡፡

 1. አመልካች ለዳኝነት ከከፈለው ብር 1,605,760.10 (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰምስት ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ብር ከአስር ሳንቲም) ላይ በደንቡ መሰረት የሚቀነሰው ሂሳብ ከተቀነሰ በኃላ ቀሪው ገንዘብ ለአመልካች እንዲመለስ ብለናል፡፡ የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ይህን ተከታትሎ ያስፈጽም፡፡
 2. ውሳኔው ሀምሌ 5/2011 ዓ.ም በችሎት ተነቧል፡፡
 3. በዚህ ችሎት ስለተደረገው ክርክር ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡ የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የልዩነት ሀሳብ

ውል የተዋዋዩ ወገኖችን ነፃነት የሚያሳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ተዋዋይ ወገኖች ውል በሚያደርጉበት ጊዜ ውሉ ህግን እና ሞራልን የሚቃረን መሆን ሊቃረን አይገባም፡፡

አመልካችና ተጠሪ ጉዳያቸውን በግልግል ለማሳየት መስማማታቸው የዳኝነቱ አገር እና የስነ ስርአት ህግ መምረጣቸው ጤናማ የውል ስምምነት ሲሆን ነገር ግን ከተዋዋዩች   አንዱ የኢትዮጵያ መንግስት መ/ቤት ሆኖ የተዋዋሉበት ነገር ለኢትዩጵያ  ሆኖ የተዋዋሉበት ነገር ለኢትዩጵያ እና ህዝቦቿ ጥቅም እንዲሰጥ መሆኑ ተረጋግጦ አለ እንዲሁም የሚፈፀመውም በኢትዮጵያ ሆኖ አመልካችን እንደ አንድ ተዋዋይ ግለሰብ በማሰብ የኢትዮጵያ ፍ/ቤት በማንኛውም ደረጃ ገዳዩ ቢቀርብለት የማየት ስልጣን እንደሌለው አድርጎ መዋዋል ህግን እና ሞራልን የሚጋፋ እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅምን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በውጭ አገር የተሰጠው ፍርድ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ህግ ግድፈት በተፈፀመበት ጊዜ በኢትዮጵያ ፍ/ቤት አይታይም አይልም እንጂ የግልግል ዳኝነቱ መቀመጫም ሆነ የሚመራበት ስነ ስርአት ህግ በኢትዮጵያ ባለመሆኑ እና የሚሰጠው ፍርድም የለንደን ፍርድ እንደሆነ መቆጠሩ በኢትዮጵያ ፍ/ቤት ፍርዱ ላይ መሰረታዊ  የህግ ጥሰት ተፈጽሟል የሚል ወገን አቤቱታ ሲያቀርብ ፍ/ቤቱ የማየት ስልጣን የለውም የሚባል  ከሆነ ኢትዮጵያን በራሷ ጥቅም ላይ ጉዳይዋን እንዳታይ ያገለለ ከመሆኑ አንፃር ውሉ በራሱ ለህግና ለሞራል ተቃራኒ  የሆነ ውል በመሆኑ ከመነሻው ተቀባይነት ማግኘት ያልነበረበት ውል ነው ባይ ነኝ፡፡

በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ጉዳዩ በግልግል እንዲታይ፣ መስማማታቸው በስምምነታቸው  መሰረትም የግልግል ዳኝነቱ ህጋዊ መቀመጫ አገር ለንደን መሆኑን እና ግልግሉ ሚመራበትን የስነ ስርአት ህግ የመረጡ መሆኑ እና ውሳኔው በኢትዮጵያ እንደተሰጠ ፍርድ እንደማይቆጠር በመስማማታቸው ላይ ልዩነት እንደሌላቸው ተረድቻለሁ፡፡

ነገር ግን በዚህ መልኩ ተዋዋይ ወገኖች የተዋዋሉ መሆኑ እና በተለይ መንግስት በሚያስተዳድረው መ/ቤት የተወከሉ የስራ ኃላፋዎች ጉዳዩ በውጭ አገር እንዲታይ እና በውጭ አገር ህግም እንዲመራ የተስማሙበትን ልዩ ምክንያት ሳያስቀምጡ በአገር ጥቅም ላይ ስምምነት በማድረጋቸው ብቻ የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች በተለይም የሰበር ሰሚ ችሎቱ ስልጣን የለውም ለማለት የሚቻልበት አግባብ ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡

ግራ ቀኙ  የስነ ስርአት ግድፈት ሲፈጽም ለለንደን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ማለት የሚችሉ መሆኑ የተዋዋሉ በመሆኑ አመልካች በለንደን በስነ ስርአት ጉዳይ ላይ ይግባኝ ማለቱን አልካደም፣ ተጠሪም በስነ ስርአት ጉድለት ብቻ ሳይሆን በፍሬ ነገር ላይም ይግባኝ ብሏል ቢልም በምን አይነት ፍሬ ነገር ላይ ይግባኝ እንዳለ ባልገለፀበት እና በአብብላጫው ድምጽ እንደተገለጸው ሁለት ጊዜ ለለንደን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ የተባለው በስነ ስርአት ግድፈት ላይ መሆኑ የሚያስረዳ ሆኖ እያለ በፍሬ ጉዳይ ላይ ይግባኝ እንዳለ በመቁጠር በስምምነቱ መሰረት ጉዳዩ የሚታየው በለንደን አገር እና በለንደን ፍ/ቤት ብቻ ነው መባሉ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

እንዲሁም ክርክር ያስነሳው ጉዳይ ሰንዴን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመጣት ሆኖ ስንዴውን የሚጠቀሙት ኢትዮጵያውያን ሆነው እያለ እንዲሁም የግልግል ጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ለዛው አገር ከፍተኛ ፍ/ቤት አቤቱታ የሚቀርብ መሆኑን ይግለጽ እንጂ በኢትዮጵያ ፍ/ቤት የሰበር ስልጣንን በሚያስቀር መልኩ ስለመዋዋላቸው የሚያሳይ ነገር ሳይኖር አመልካች ቀደም ሲል በስነ ስርአት ግድፈት ምክንያት ለከፍተኛ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ያቀረበ ሲሆን ለዛው ይግባኙን ላየው ፍ/ቤት ደግሞ አቤቱታ እንዲያቀርብ ስምምነቱን ማድረጉ በራሱ ኢትዮጵያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳይኖራት ተደርጎ ውል የተደረገ መሆኑን ከማሳየቱም በላይ አመልካች በኢትዮጵያ የሚገኝ የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ መሰረታዊ የሆኑ ህጎች የመዳኘት መብት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እና አመልካች ውል ውስጥ ሲገባ ማንኛውንም መብት የተወ መሆኑን ባልገለጸበት ሁኔታ የአመልካቾች ጥያቄም የኢትዮጵያ መሰረታዊ ህግ ተጥሶብናል በሚል አቤቱታ አቅረበው ባለበት፣ በስምምነታቸውም የስነ ስርኣት ግድፈት ሲኖር ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ እንጂ መሰረታዊ ህግ ሲጣስ ለለንደን ፍ/ቤት ይግባኝ ይላሉ ተብሎ ውል ባልተገባበት ሁኔታ በተለይ ተዋዋይ ወገኖች መንግስታዊ አካላት ከሆኑ የሚዋዋሉትን ውሎች የመንግስትን እና የአገሪቱን  ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ መዋዋል ያለባቸው መሆኑ ስለታመነበት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግን ለማቋቋም እና ስልጣኑን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6/4/ለ/ መሰረት የፌዴራል ጠ/ዐቃቤ ህግ ውሎችን እንዲመረምር መደረጉ ከብሄራዊ ጥቅም አንፃር በራሱ በዚህ መልኩ የሚፈፀሙ ውሎች በአገር ጥቅም ላይ ጉዳትሊያድርሱ የሚችሉ ከመሆኑ አኳያም ሲታሰብ የአገሪቱ የመጨረሻ የሆነው ፍ/ቤት በውጭ አገር የተሰጠን ፍርድ የግልግል ዳኝነቱ አገር በመመረጡ እና የስነ ስርአት ህጉ በመመረጡ እንዲሁም ፍርዱ በኢትዮጵያ እንደተሰጠ ፍርድ ይቆጠራል በሚል በውሉ ባለመገለፁ መሰረታዊ የህግ ጥሰት  እንዲታረም የቀረበን አቤቱታ ባለመቀበል ፍ/ቤቱ ስልጣን የለውም ተብሎ በአብላጫው የተሰጠው ፍርድ ተገቢ አይደለም በማለት ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው ተብሎ ብይን ተሰጥቶ ወደ ዋናው ጉዳይ ተገብቶ ሊመረመር ይገባ ነበር በማለት ስሜ በተራ ቁጥር 5 ስር የተሰየምኩት የችሎት ዳኛ በአብላጫው ድምጽ በሃሳብ ተለይቻለሁ፡፡

የማይነበብ የአንድ ዳኛ ፊርማ አለበት፡፡

ፋ/ዘ

Exit mobile version