Site icon Ethiopian Legal Brief

የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 6/2013

የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 6/2013 ዓ.ም.

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌ

አንቀፅ 1. አውጪው ባለሥልጣን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. አንቀፅ 163 ንዑስ አንቀፅ (2) እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀፅ 7 ንዑስ አንቀፅ (11) በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡

አንቀፅ 2. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ “የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 6  /2013 ዓ.ም.” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡  አንቀፅ 3. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ፤

 1. “ኢ.ፌ.ዲ.ሪ” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው::
 2. “ቦርድ” ማለት በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡
 3. “የፖለቲካ ፓርቲ” ማለት ዜጎች ተደራጅተው የሚመሠርቱት የፖለቲካ ፕሮግራም በማውጣት በሀገር አቀፍ፣ በክልል ወይም ከክልል በታች ባለ ደረጃ የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ ለመያዝ በምርጫ ሕጉ መሠረት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው።
 4. “ጠቅላላ ምርጫ” ማለት አግባብ ባለው ህግ መሠረት የሚካሄድ የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡
 5. “የአካባቢ ምርጫ” ማለት አግባብ ባለው ህግ መሠረት የሚካሄድ የብሔረሰብ ዞን፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው::
 6. “ድጋሚ ምርጫ” ማለት በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀፅ (16) በተሰጠው ስልጣን መሠረት ቦርዱ የምርጫ ውጤቱ እንዲሰረዝ ሲወስን፣ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 154 መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን፤ ወይም እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በማግኘታቸው ምክንያት አሸናፊውን ለመለየት የሚካሄድ ምርጫ ነው::
 7. “ማሟያ ምርጫ” ማለት በመራጮች ውሳኔ ከምክር ቤት መነሳትን ጨምሮ በማንኛውም ምክንያት በየደረጃው የሚገኙ የተጓደሉ የምክር ቤት አባላት መቀመጫዎችን ለመሙላት የሚካሄድ ምርጫ ነው::
 8. “ህዝበ ውሳኔ” ማለት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገመንግሥት ወይም አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት ሲወሰን የህዝብ ፍላጎትን ለመለካት እና የህዝብን ውሳኔ ለማወቅ ድምፅ የሚሰጥበት ስርዓት ነው::
 9. “የምርጫ ጣቢያ” ማለት በየደረጃው ለሚካሄዱ ምርጫዎች የመራጭ ምዝገባ የሚካሄድበት፣ መራጮች ድምፅ የሚሰጡበት እና የድምጽ ቆጠራ የሚካሄድበት ቦታ ነው::
 10. “የመራጮች መዝገብ” ማለት በየደረጃው ለሚካሄድ ምርጫ መራጩ ሕዝብ በምርጫ ጣቢያው በመራጭነት የሚመዘገብበት መዝገብ ነው::
 11. “የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ” ማለት አንድ ሰው በመራጭነት ስትመዘገብ ከመዘገባት የምርጫ ጣቢያ የሚሰጣት የመራጭነት ማረጋገጫ ነው::
 12. “የምርጫ አስፈፃሚ” ማለት በየደረጃው ምርጫን ለማስፈጸም በቦርዱ የምትመደብ ሰው ናት፡፡
 13. “የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ” ማለት የምርጫ ጣቢያውን በሰብሳቢነት የምትመራ በቦርዱ የምትመደብ የምርጫ አስፈጻሚ ናት፡፡
 14. “የመዝገብ ሹም” ማለት መራጮችን እንድትመዘግብ በምርጫ ጣቢያው ኃላፊ የተመደበች የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ናት፡፡
 15. “ሰልፍ አስከባሪ” ማለት በምርጫ ጣቢያው መግቢያ ላይ በመቆም መራጮች ለምዝገባ ሲመጡ በቅደም ተከተል የምታስተናግድ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናት፡
 16. “የፀጥታ አስከባሪ”፣ “የፀጥታ ኃይል” ወይም “የፀጥታ አካል” ማለት የምርጫ ጣቢያን ደህንነት ለማስከበር በምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ጥያቄ አማካኝነት የሚመደብ የፖሊስ ኃይል ነው፡፡
 17. “ልዩ የምዝገባ ቀን” ማለት ቦርዱ ለመራጮች ምዝገባ ባወጣው መደበኛ ጊዜ ውስጥ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሳይመዘገብ የቀረ ሰው እንዲመዘገብበት ቦርዱ የሚወስነው ቀን ነው።
 18. “የምርጫ ህግ” ማለት የኢትዮጵያ የምርጫ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. ነው::
 19. “ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ” ማለት በክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፤ በምርጫ ክልል እና በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ለሚነሱ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥ በአዋጁ መሰረት ለምርጫ ወቅት የሚቋቋም ኮሚቴ ነው፡፡
 20. “ሰው” ማለት ሕጋዊ ወይም የተፈጥሮ ሰው ነው፡፡
 21. በአዋጁ ላይ የተሰጡ ትርጓሜዎች እንደአግባብነታቸው ለዚህ መመሪያም ተፈጻሚ ይሆናሉ።

አንቀፅ 4. የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ ለጠቅላላ ፣ ለአካባቢ፣ ለማሟያ፣ ለድጋሚ ምርጫ እና በህገ መንግሥቱ መሠረት ለሚካሄድ ህዝበ ውሳኔ እንዲሁም አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች መሰረት በልዩ ሁኔታ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ በመደበኛ፣ በተንቀሳቃሽና በልዩ ሁኔታ በሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች በሚደረግ የመራጮች ምዝገባ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡  አንቀፅ 5. አላማ

የዚህ መመሪያ አላማ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በመጠቀም ተወካዮቻቸውን በእኩልነት የሚመርጡበት ትክክለኛ፣ አሳታፊ እና ግልጽ የመራጮች ምዝገባ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ነው::

አንቀፅ 6. የፆታ አገላለፅ

በዚህ መመሪያ ውስጥ በአንዱ ጾታ የተገለጸው አነጋገር ሌላኛውን ጾታም ያካትታል፡፡

ክፍል ሁለት የመራጮች ምዝገባ አደረጃጀት

አንቀፅ 7. የምርጫ ጣቢያ አካላት አደረጃጀት

 1. እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ በምርጫ ህጉ እንዲሁም አግባብ ባለው የቦርዱ መመሪያ መሠረት በቦርዱ የሚመለመሉ ቢያንስ አንድ ሴት የያዘ የምርጫ አስፈፃሚዎች ኮሚቴ ይኖረዋል፡፡
 2. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው ከምርጫ አስፈጻሚዎች ቢያንስ ሦስቱ በጣቢያው ሲገኙ ነው።
 3. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ከምርጫ አስፈፃሚ አባላት መካከል አንዷን የመዝገብ ሹም አድርጋ ትመድባለች።
 4. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው በተመደበችው የመዝገብ ሹም ይሆናል፡፡
 5. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ በየሳምንቱ የምርጫ ጣቢያውን ምርጫ አስፈጻሚዎች በመዝገብ ሹምነት በየተራ ትመድባለች፡፡
 6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (3) የተደነገገው ቢኖርም አንድ በመዝገብ ሹምነት የተመደበች የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር በሥራዋ ላይ መገኘት ካልቻለች የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዋ በምትሰጠው መመሪያ መሠረት ምዝገባው በሌላ የምርጫ ጣቢያው አስፈፃሚ አባል በጊዜያዊነት እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡
 7. አንድ የመዝገብ ሹም በቋሚነት በሥራዋ ላይ መገኘት ካልቻለች የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ወዲያውኑ በተጠባባቂነት ከተያዙት የምርጫ አስፈፃሚዎች መካከል በቋሚነት እንድትተካ ታደርጋለች፡፡
 8. በምርጫ ጣቢያው በተጠባባቂነት የተያዘች አስፈፃሚ ከሌለች በፍጥነት ለምርጫ ክልሉ በማሳወቅ እንድትተካ ታደርጋለች፡፡
 9. እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ በምርጫ ጣቢያ ኃላፊዋ በምትመደብ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሰብሳቢነት የሚመራና በምርጫ ክልሉ ከተመዘገቡ መራጮች መካከል የሚመረጡ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት አባል የሆኑበት የአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ይኖረዋል፡፡
 10. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል የሆኑ ሰዎች የማንም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና በመልካም ሥነ ምግባራቸውና ስብእናቸው የታወቁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ዝርዝር አሰራራቸውም ቦርዱ ባወጣው የአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ መመሪያ መሰረት የሚገዛ ይሆናል።

አንቀጽ 8. የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ስልጣንና ኃላፊነት

በምርጫ ሕጉ፤ በዚህ መመሪያ እና ቦርዱ በሚያወጣው የመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም ማንዋል መሠረት የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች የሚከተሉት ዋና ዋና ኃላፊነትና ስልጣኖች አሏቸው፡

 1. የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ

ሀ) የምርጫ ጣቢያውን አስፈጻሚ ኮሚቴ በሰብሳቢነት መምራት፤

ለ) በምርጫ ሕጉ እና በዚህ መመሪያ የተደነገጉትን ጨምሮ በዚህ አንቀጽ የተዘረዘሩትን ሥልጣንና ኃላፊነቶች እንዲያከናውኑ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎችን መመደብ፣ ማቀያየር፣ እንዲሁም ሲጓደሉ ቦርዱ በምርጫ ክልሎች ካስቀመጣቸው ተጠባባቂ አስፈጻሚዎች ጠይቆ መተካት፤

ሐ) የመራጮች ምዝገባ ሰነድና ቁሳቁስ ከምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ወደ ምርጫ ጣቢያው መድረሳቸውን ማረጋገጥ፤ የምርጫ ጣቢያው በቂ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች እንዳሉት ማረጋገጥ እንዲሁም ሰነዶቹ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት  ቀናት የሚያልቁ ከሆነ ለምርጫ ክልሉ ፅሕፈት ቤት ማሳወቅ፤

መ) ሁሉም ሰነድና ቁሳቁስ ለመራጮች ምዝገባ በማይውሉበት ጊዜ ሁሉ በአግባቡ ተጠብቀው መቀመጣቸውን ማረጋገጥ፤

ሠ) የምርጫ ጣቢያው ለሥራ ምቹ የሆነ ክፍል እንዳለው እንዲሁም በአግባቡ መሰናዳቱን ማረጋገጥ፤

ረ) በምርጫ ህጉ መሰረት በምርጫ ጣቢያው ውስጥ መገኘት ያለባቸው ሰዎች ብቻ መገኘታቸውን ማረጋገጥ፤

ሰ) የምርጫ ቁሳቁስ በምርጫ ቁሳቁስ አስተዳደር መመሪያ መሰረት በአግባቡ መያዛቸውን መከታተል ስለአፈፃፀሙም በየእለቱ ለምርጫ ክልሉ ሪፖርት ማድረግ፤

ሸ) የምርጫ ጣቢያው ደህንነትና ሥርዓት መጠበቁን ማረጋገጥና ይህም እንዲከበር ማድረግ፤

ቀ) የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ደህንነትን የማስከበር ጥያቄ ካላቀረበች በስተቀር የፖሊስ ወይም የፀጥታ አካል ከምርጫ ጣቢያው ውጪ በተገቢው ርቀት ላይ መቆየታቸውን ማረጋገጥ፤

በ) በእያንዳንዱ የምዝገባ ቀን መጨረሻ ላይ የምዝገባ መረጃዎች ለምርጫ ክልል ጽ/ቤቱ ሪፖርት መደረጋቸውን ማረጋገጥ፤

ተ) በቦርዱ በሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ በ“የምርጫ ማስፈጸሚያና የድምጽ መስጫ መሳሪያዎች፣ ሰነዶች እና ቁሳቁስ ድልድል፣ ሥርጭት፣ አጠቃቀም፣ ርክክብና አወጋገድ መመሪያ”፣ በ“የምርጫ አስፈፃሚዎች የአሰራርና የስነምግባር መመሪያ”እና በአፈፃፀም መመሪያዎች መሰረት አስፈላጊ ቁሳቁሶች እና ሰነዶች ወደ የምርጫ ክልል ጽ/ቤት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መላካቸውን ማረጋገጥ፤

ቸ) እያንዳንዱ የመራጮች ካርድ መዝገብ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ወደ ምርጫ ክልሉ በፍጥነት መላኩን ማረጋገጥ፤

ነ) በቦርዱ ወይም በምርጫ ቦርዱ ስልጣን የተሰጣት ሰው የምትሰጣትን ተጨማሪ ተግባራት ማከናወን።=

 1. የመዝገብ ሹም የመዝገብ ሹም ሆና የተመደበች የምርጫ አስፈፃሚ፥

ሀ) የምዝገባ ቅጹን በመሙላት የመራጮች ምዝገባ ታካሂዳለች፤

ለ) ተመዝጋቢዋ የመታወቂያ ካርድ ባቀረበችበት ጊዜ ለመዝጋቢዋ ከምትሰጠው መረጃ ጋር በማመሳከር የተመዝጋቢዋ መረጃ በትክክል መስፈሩን ታረጋግጣለች፤

ሐ) ለመራጭነት ብቁ የሆነችን ሰው በተዘጋጀው የመራጮች መዝገብ ላይ በመመዝገብ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ ወዲያውኑ ለተመዝጋቢዋ ትሰጣለች፤

መ) በእስክሪቢቶ ወይም በጭቃ ቀለም ብቻ ሆኖ በግልፅ ሊነበብ በሚችል የእጅ ጽሑፍ እና ስርዝ ድልዝ በሌለበት ሁኔታ መራጮችን ትመዘግባለች፤

ሠ) የመራጮችን መዝገብና ቅጾች ምዝገባው እንዲከናወን በተወሰነበት የጊዜ ገደብ ሁሉ በሚገባ ትጠብቃለች፤

ረ) የመራጮች መዝገብን ጨምሮ ሌሎች የምዝገባ ሰነድና ቁሳቁስ በአግባቡ ተሰናድተው ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በማይደርሱበት ቦታ መቀመጣቸውን ታረጋግጣለች፤

ሰ) በምርጫ ጣቢያ ሃላፊዋ ወይም በምርጫ ቦርድ ስልጣን የተሰጣት ሰው የምትሰጣትን ተጨማሪ ተግባራት ታከናውናለች።

 1. የሰልፍ አስከባሪ

ሀ) በምርጫ ጣቢያው መግቢያ በር ላይ በመቆም መራጮች ለምዝገባ ሲመጡ የመራጭ ረዳት ከሆኑ ሰዎች በስተቀር በአንድ ወቅት አንድ ሰው ብቻ ወደ መዝገብ ሹሟ መሄዷን ማረጋገጥ፤

ለ) ለመመዝገብ የሚመጡ መራጮችን እየፈተሸች ታስገባለች፡፡ ወደ ምርጫ ጣቢያ ይዞ መግባት የተከለከሉ የጦር መሳሪያና ስለት ያላቸው ነገሮችን መራጮች ይዘው እንዳይገቡ ትከለክላለች፤

ሐ) ለመመዝገብ የሚጠባበቁ መራጮች በምርጫ ጣቢያው መግቢያ ላይ በአግባቡ መሰለፋቸውን እንዲሁም ከተመዘገቡ በኋላ ወዲያውኑ ከጣቢያው መውጣታቸውን ታረጋግጣለች፤ የምርጫ ጣቢያውን ስራ የሚያውክ ሁኔታ ሲፈጠር  ለምርጫ ጣቢያ ሃላፊዋ ወዲያውኑ ሪፖርት ታደርጋለች፤

መ) በምርጫ ጣቢያ ሃላፊዋ ወይም በምርጫ ቦርዱ ስልጣን የተሰጣት ሰው የምትሰጣትን ተጨማሪ ተግባራት ታከናውናለች፡፡

አንቀፅ 9. የምዝገባ የጊዜ ሠሌዳ

 1. የጠቅላላ ምርጫ ምዝገባ በአገር አቀፍ ደረጃ ቦርዱ በሚወስናቸው ቀናት የሚጀመርና የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
 2. ቦርዱ የሚመለከታቸውን ክልሎች ህገ መንግስት ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች መነሻ በማድረግ የአካባቢ ምርጫዎችን የምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ ያወጣል፡፡
 3. ቦርዱ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) እና (2) መሰረት የምዝገባ ቀናቱን ከመወሰኑ በፊት በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንደ አስፈላጊነቱም ከሲቪል ማህበራት፤ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይመካከራል፡፡
 4. ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምርበትን ዕለት በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው በማካተት ምዝገባው ከመጀመሩ 15 ቀን በፊት ጀምሮ ባሉት ቀናት በተከታታይ በመገናኛ ብዙሃንና በሌሎች የማስታወቂያ መንገዶች አማካኝነት የምዝገባውን ሰሌዳ ለህዝቡ ይገልፃል፡፡
 5. የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በፌደራል መንግስት ሕጎች የተደነገጉ የሕዝብ በዓላትን ሳይጨምር በመደበኛ የመንግሥት የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት መሰረት ይከናወናል፡፡
 6. የምርጫ አስፈጻሚዎቹ የየክልሉን መደበኛ የሥራ ሰዓት በመከተል ለአንድ ሰዓት ብቻ ለምሳ ይወጣሉ፡፡
 7. ቦርዱ በአንዳንድ ክልሎች ያለውን የመንግስት ስራ ሰአት አፈፃፀም ህጎች ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ ሆኖ ሲያገኘው የተለየ የስራ ሰአት ሊወስን ይችላል።

አንቀፅ 10. ልዩ የምዝገባ ቀን

 1. ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው መደበኛው የመራጮች ምዝገባ ቀናት ከመጠናቀቁ አንድ ሳምንት በፊት ተጨማሪ ልዩ የመራጮች ምዝገባ ቀን እንዲኖር ሊወስን ይችላል፡፡
 2. በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስችላትን መስፈርት የምታሟላ ሆና በመመራጭነት ከመመዝገብ የሚያግድ እክል ያጋጠማት መራጭ ቦርዱ በሚወስነው ልዩ የምዝገባ ቀን ለመመዝገብ ልትጠይቅ ትችላለች፡፡
 3. መራጯ ከመመዝገብ የሚያግድ እክል ገጥሟታል የሚባለው ከታች የተዘረዘሩት እና መሰል ያልታሰቡ ድንገተኛ ክስተቶች ሲፈጠሩ ነው፡-

ሀ) መራጯ ኃላፊ የማትሆንበት ያልታሰቡና በሦስተኛ ወገን ድርጊት የተከሰቱ ድንገተኛ ደራሽ ነገሮች፤

ለ) መራጯ ባልታሰበ ሁኔታ የሚደርስባት ከባድ አደጋ ወይም ጽኑ ሕመም፡፡

 1. ማንኛውም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ያጋጠማትና በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስችላትን መስፈርት የምታሟላ መራጭ ለምርጫ ጣቢያው ሃላፊ አስፈላጊውን የፅሁፍ ወይም የሰው ማስረጃ አቅርባ መመዝገብ ትችላለች፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚቀርብ አቤቱታ የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ቦርዱ በሚወስነው ቀን የሚስተናገድ ይሆናል፡፡
 3. ቦርዱ በዚህ አንቀፅ መሠረት ልዩ የምዝገባ ቀን ከወሰነ፤

ሀ) መራጮችን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት አመቺ በሆነ ማስታወቂያ ይገልፃል፡፡

ለ) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት ውሳኔው ሲደርሳቸው የምርጫ ጣቢያዎች

ቦርዱ ባወጣው መመሪያ መሠረት በልዩ የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ እንዲመዘገቡ የተፈቀደላቸው መራጮችን ከመራጮች መዝገብ መጨረሻ ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ወኪሎች ተፈራርመው ከተዘጋው ገጽ ቀጥሎ ባለው ገጽ ላይ ተመዘግበው የልዩ ምዝገባ ሰሌዳው ሲያልቅ አስፈፃሚዎቹ ተፈራርመውበት ይዘጋል።

ክፍል ሦስት የምዝገባ ቀሳቁስ ስርጭትና ጥበቃ

አንቀፅ 11. ስለሰነዶች ስርጭትና የመራጮች ምዝገባ ቅድመ ዝግጅት

 1. ቦርዱ ለመራጮች ምዝገባ የሚያገለግል ሰነድና ቁሳቁስ ከመራጮች ምዝገባ ከሚጀመርበት ዕለት አምስት ቀናት ቀደም ብሎ በየምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤቶች እንዲደርስ ያደርጋል፡፡
 2. የምርጫ ክልል ጽ/ቤት የመራጮች ምዝገባ ሰነዶችና ቁሳቁስ ቦርዱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከሚጀመርበት ዕለት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በየምርጫ ጣቢያ እንዲደርስ ማድረግ አለባቸው::
 3. ቦርዱ ስለመራጮች ምዝገባ በየደረጃው ላሉ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት በቂ ስልጠና ይሰጣል። አንቀፅ 12. ስለምርጫ ስነዶችና ቁሳቁሶች ርክክብ

እያንዳንዱ የምርጫ ክልል ለመራጮች ምዝገባ የተላኩ ሰነዶችን እና ሌሎች የምርጫ ቁሳቁሶችን ተረክቦ ቦርዱ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለየምርጫ ጣቢያዎቹ በጥንቃቄ እና በአግባቡ መድረሱን ያረጋግጣል፤ ርክክቡም በቦርዱ በተዘጋጀ የመረካከቢያ ቅፅ ይፈፀማል፡፡  አንቀፅ 13. ስለምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁስ ጥበቃ

 1. የምርጫ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ከቦርዱ ወደ የምርጫ ክልሉም ሆነ ወደ የምርጫ ጣቢያዎች ሲሰራጩ በየደረጃው የሚገኙ የምርጫ አስፈፃሚዎች ተገቢው የጥበቃና የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ::
 2. የምርጫ ክልል እና የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚዎች የመራጮች መዝገብ እንዲሁም የምርጫ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን ለመረከብ እና ለማስቀመጥ የሚያስችል ምቹ ቦታ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
 3. የምርጫ ክልል እና የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚዎች የመራጮች መዝገብ፣ እንዲሁም የምርጫ ሰነዶች እና ቁሳቁሶችን ያለፈቃድ እና አላግባብ እንዳይነካኩ፣ እንዳይበላሹ፣ እንዳይቃጠሉ፣ እንዳይሰረቁ እና እንዳይከፋፈቱ ጥበቃው አስተማማኝ በሆነ ቦታ በጥንቃቄ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
 4. የመዝገብ ሹሟ በኃላፊነቷ ሥር ያሉ ሁሉንም የምዝገባ ቁሳቁሶች በየቀኑ በአግባቡ በማሸግ እንዲቀመጡ ታደርጋለች፤
 5. የመራጮች ምዝገባና የመራጮች መዝገብ ለሕዝብ ግልጽ የማድረጊያ ጊዜ ሲጠናቀቅ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች በቦርዱ በተዘጋጀ መረካከቢያ ቅፅ መሰረት በምርጫ ጣቢያው ሃላፊና የምርጫ ክልል ሃላፊ ርክክብ ተደርጎ በምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡
 6. የምርጫ ምዝገባ ማስፈሚያ መሳሪያ፣ ቁሳቁስ፣ እንዲሁም ሰነዶች አያያዝ፣ ርክክብና አወጋገድ ዝርዝር ይህንኑ በተለይ በሚመለከተው የቦርዱ መመሪያ መሠረት ይፈጸማል፡፡

ክፍል አራት የምዝገባ ቅድመ ዝግጅት

አንቀፅ 14. የመራጮች ምዝገባ ቦታ

 1. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው የመራጮችን መደበኛ መኖሪያ መሰረት በማድረግ በምርጫ ህጉ መሠረት በቦርዱ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ነው::
 2. ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ቤት ለቤትም ሆነ በተመሳሳይ ቦታ እየተዘዋወሩ የመራጮች ምዝገባ ማከናወን የተከለከለ ነው::
 3. በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (2) የተደነገገው ቢኖርም ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የአርብቶ አደሩን አኗኗር መሰረት ያደረገ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያ ሊያቋቁም ወይም ቤት ለቤት በመሄድ የመራጮች ምዝገባ እንዲከናወን ሊወስን ይችላል፡፡
 4. የምርጫ ጣቢያዎች የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ሁኔታ፣ ለመራጮች ምዝገባ እና ለሌሎች የምርጫ ተግባራት ምቹነታቸው፣ አማካይ እና መራጩ በቀላሉ ሊያውቃቸው የሚችሉ መሆናቸውን ጨምሮ የተለያዩ ታሳቢዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ቦርዱ በሚወስነው ስፍራ በምርጫ አስፈጻሚዎች ተመቻችተው የሚቋቋሙ ይሆናል፡፡
 5. የመራጮች ምዝገባ የሚከናወንበት ቦታ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ 15 ቀናት አስቀድሞ ለመራጩ ህዝብ እና ለተወዳዳሪዎች ይፋ መደረግ አለበት::
 6. በማንኛውም ምርጫ አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ መብለጥ የለበትም::
 7. ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያዎችን በተመለከተ በምርጫ ሕጉና እነዚህን በሚመለከቱ መመሪያዎች ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ለአንድ የምርጫ ጣቢያ በተከለለ አካባቢ ከአንድ የምርጫ ጣቢያ በላይ ማቋቋም አይቻልም::
 8. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (7) ስር የተደነገገው ቢኖርም፣ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ መራጮች የተገኙ እንደሆነ አዲስ የምርጫ ጣቢያ ተቋቋሞ የመራጮች ምዝገባው ይቀጥላል፡፡
 9. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (7) ስር የተደነገገው ለልዩ የምርጫ ክልሎች በሚቋቋሙ እና በህግ በተለዩ ተቋማት በሚቋቋሙ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡
 10. ቦርዱ ለምርጫው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የምርጫ ጣቢያ ቦታዎችን ሊለውጥ ይችላል፤ ለውጡንም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት ለመራጩ ህዝብ፣ ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ታዛቢዎች፤ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ ሲቪክ ማህበራት እና ጋዜጠኞች ይፋ ማድረግ አለበት፡፡ ቦርዱ ይህንን የሚመለከት የአሰራር ስርአት ሊዘረጋ ይችላል ፡፡

አንቀፅ 15. የመራጮች ምዝገባ ቦታ በመሆን የማያገለግሉ ቦታዎች

በልዩ ሁኔታ የሚቋቋሙ ምርጫ ጣቢያዎች መመሪያ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በሚከተሉት ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ ጣቢያ ማቋቋም አይቻልም፤

 1. ወታደራዊ ካምፖች፣
 2. የፖሊስ ጣቢያዎች፣
 3. ቤተክርስቲያናት፣
 4. መስጊዶች፣
 5. ሌሎች የእምነት ቦታዎች፣
 6. ሆስፒታሎችና በየደረጃው ያሉ ሌሎች የሕክምና ተቋማት፣
 7. ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች፣
 8. የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የሃይማኖት ድርጅቶች ህንፃዎች እና የግል መኖሪያ ቤቶች::

አንቀፅ 16. የምርጫ ጣቢያ ዝግጅት

 1. የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚዎች ለምርጫ ጣቢያነት የተመረጠውቦታ ለመራጮች ምዝገባ ምቹ እንዲሆን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ዝግጅት ያደርጋሉ፤

ሀ) መግቢያና መውጫው የተለያየ የመራጮች መመዝገቢያ ቤት ወይም ድንኳን ወይም ዳስ ያዘጋጃሉ::

ለ) የመዝገብ ሹም፣ ታዛቢዎች እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ  አባላት አቀማመጥ ፊት ለፊት ሆኖ ተመዝጋቢዎች ወደ መመዝገቢያው ቦታ ሲገቡ እና ከምዝገባ ቦታው ሲወጡ እንዲሁም የምዝገባውን ሂደት በግልፅ በማየትና በመስማት ሊታዘቡ የሚችሉበትን አቀማመጥ ያመቻቻሉ፡፡

ሐ) መራጮች ለመመዝገብ ሲመጡ ተራ የሚጠብቁበት ከፀሐይና ዝናብ መከለያ ቦታ ያዘጋጃሉ፡፡

 1. የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎች የመራጮች ምዝገባ ከሚጀመርበት ዕለት 3 ቀናት አስቀድመው፣

ሀ) የመራጮች ምዝገባ የሚካሄድበትን የምርጫ ጣቢያ በግልፅ ማወቅ ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ማስታወቂያ ለዚሁ በተዘጋጀ ወረቀት ላይ በጉልህ ተጽፎ በምርጫ ጣቢያው እንዲሰቀል ያደርጋሉ፤

ለ) ከዚህ በተጨማሪ በቦርዱ የመራጮች ትምህርት መርሀግብር አማካይነት ተጨማሪ መረጃ ለመራጮች እንዲደርስ ያደረጋሉ፡፡

 1. የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ የመራጮች መዝገብ፣ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እንዲሁም የማህተም መርገጫ እና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች በበቂ ሀኔታ መኖራቸውን ያረጋግጣሉ፤
 2. ያልተሟሉ ቁሳቁሶች ሲኖሩ የምርጫ ጣቢያው ሃላፊ ቁሳቁሶቹ እንዲሟሉ ጥያቄውን ለምርጫ ክልሉ ፅህፈት ቤት ወዲያውኑ ታቀርባለች፡፡

አንቀፅ 17. የመራጮች መዝገብ ዝግጅት

 1. እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ በምርጫ ህጉ መሠረት ለምርጫ አስፈጻሚዎች አያያዝና አጠቃቀም ቀላል የሆነ እንዲሁም ስህተቶች እንዳይፈጠሩ የሚያግዝ የመራጮች መዝገብ ይኖረዋል፤
 2. የመራጮች መዝገቡ በምርጫ ሕጉ የተጠየቁ መረጃዎችን ጨምሮ ቦርዱ ለምርጫ ሂደቱ ጠቃሚ የሚላቸውን ተጨማሪ መረጃዎች ያካተቱ ዐምዶች አስቀድሞ የታተሙበት ይሆናል፤
 3. የመራጮች መዝገብ ከመራጮች ምዝገባ መጀመሪያ ቀን በፊት መዘጋጀት አለበት፤
 4. የመዝገቡ የፊት ሸፋን ገፅ ላይ የክልሉ፣ የምርጫ ክልሉ፣ የወረዳው፣ የቀበሌው፣ የምርጫ ጣቢያው መጠሪያ እና የምርጫ ጣቢያው መለያ ቁጥር ይመዘገባል፤

አንቀፅ 18. በመራጮች ምዝገባ ቦታ መገኘት የሚችሉ ሰዎች

 1. በመራጮች ምዝገባ ቀናት የሚከተሉት ሰዎች በምርጫ ጣቢያው መገኘት ይችላሉ፤

ሀ) በቦርዱ እውቅና የተሰጣቸው ተዘዋዋሪ ወይም ተቀማጭ የምርጫ ታዛቢዎች፣

ለ) በቦርዱ እውቅና የተሰጠቸው የመገናኛ ብዙኃን አባላት፤

ሐ) የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት፤

መ) በቦርዱ የተመደቡ እና ማረጋገጫ ያላቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰራተኞች፤

ሠ) በቦርዱ እውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል እጩ ወኪሎች፤

ረ) በመራጭነት ለመመዝገብ የሚመጡ አካል ጉዳተኞችን የሚያግዙ ረዳቶች፤

 1. በንኡስ አንቀፅ አንድ መሰረት በመራጮች ምዝገባ ወቅት መገኘት የሚችሉ ሰዎች ባይገኙም የመራጮች ምዝገባ ሂደት በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይከናወናል::

ክፍል አምስት የመራጮች ምዝገባ አፈጻጸም

አንቀፅ 19. በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መመዘኛዎች

 1. ማንኛዋም ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 18 መሠረት የሚከተለውን ማሟላት ይኖርባታል፤

ሀ) ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነች፣

ለ) በምዝገባው ዕለት እድሜዋ 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ እና

ሐ) በምርጫ ክልሉ ቢያንስ ለ6 ወር የኖረች፡፡

አንቀፅ 20. በመራጭነት ለመመዝገብ የሚቀርቡ ማስረጃዎች

 1. አንድ በመራጭነት ለመመዝገብ ብቁ የሆነች ሰው እንደ ሁኔታው ከሚከተለው አንዱን ማስረጃ በምትኖርበት አካባቢ ለሚገኝ ምርጫ ጣቢያ በማቅረብ በመራጭነት መመዝገብ ትችላለች፤

ሀ) ተመዝጋቢዋ በምትኖርበት የምርጫ ጣቢያ ማንነቷን የሚገልፅ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት ፡፡

ለ) የቀበሌ መታወቂያ ካርዱ ወይም ፓስፖርቱ ያልታደሰ ቢሆንም እንኳን ለምዝገባ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ነገር ግን የካርዱ ዕድሳት ጊዜ  ከአምስት አመት በላይ ያለፈ ከሆነ ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

ሐ) የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት ማቅረብ ካልቻለች የቅርብ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ መንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለችበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ፣ የሰራተኛነት መታወቂያ የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስችሉ ሰነዶች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

 1. ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት፤

ሀ) ከምርጫ አስፈጻሚዎቹ ሁለቱ መራጯን ለይተው የሚያውቋት ከሆነ በአስፈጻሚዎቹ ምስክርነት ወይም፣

ለ) በገጠር አካባቢ ሲሆን በባሕላዊና በልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢዋን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ ባሕሉን የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ለምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ በሚሰጡት ምስክርነት ቃለ ጉባኤ ተይዞ እና በቃለ ጉባዔው ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ተፈራርመውበት ምዝገባው ይከናወናል፡፡

ሐ) የተመዝጋቢዋ እድሜ 18 ዓመት ስለመሆኑ የሚቀርብ ማስረጃ ሳይኖርና ወይም ጥርጣሬ ሲኖር በተመዝጋቢዋ ቤተሰብ አንጋፋ አባል ወይም ዘመድ፣ እነሱ ከሌሉ ስለግለሰቧ የሚያውቁ ሁለት ሰዎች ለምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ በሚሰጡት የምስክርነት ቃል በማረጋገጥ ሂደቱ በቃለ ጉባዔ ተይዞ ሊመዘገብ ይችላል፡፡

መ)የሚሰጠውን ምስክርነት የምርጫ ጣቢያው ሃላፊ ትሰማለች፤ በቃለ ጉባዔው ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ይፈራረሙበታል፡፡

 1. የምርጫ ጣቢያው በተቋቋመበት ቀበሌ ለረዥም ጊዜ በመደበኛነት መኖራቸው በሰነድ የተረጋገጠ ሦስት ግለሰቦች በሚሰጡት ምስክርነት የሰነድ ማስረጃ አልባዋን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ ሂደቱ ቦርዱ በሚያዘጋጀው የቃለ ጉባዔ ላይ የምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ተፈራርመውበት ምዝገባው ሊከናወን ይችላል፡፡
 2. ስለመራጭ ማንነት፣ ነዋሪነት ወይም ሌላ ሁኔታ ማንኛውም ዓይነት ምሥክርነት የምትሰጥ ሰው፡-

ሀ) በመራጭነት የተመዘገበች፣

ለ) እጩ ተወዳዳሪ  ወይም የእጩ ተወካይ ያልሆነች መሆን ይኖርባታል፡፡

 1. በዚህ አንቀጽ ከተመለከቱት ማረጋገጫዎች በአንዱ ብቻ የመራጩን ማንነትና የነዋሪነት ቆይታ ማረጋገጥ ያልተቻለ እንደሆነ መዝጋቢዎች ከአንድ በላይ መስፈርቶችን በመጠቀም ያረጋግጣሉ፡፡

አንቀፅ 21. በመራጭነት ሊመዘገቡ ስለማይችሉ ሰዎች  ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰዎች በመራጭነት ሊመዘገቡ አይችሉም፤

 1. ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያልሆነች፣
 2. በምዝገባው ዕለት ዕድሜዋ ከ18 ዓመት በታች የሆነች፣
 3. በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌላት ስለመሆኑ በታወቀ ሕክምና ተቋም ወይም በፍርድ ቤት የተረጋገጠባት ሰው፣
 4. የመምረጥ መብቷ በህግ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበባት ሰው::

አንቀፅ 22. የአመዘጋገብ ስርዓት

 1. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (3) ስር ከተጠቀሱት መራጮች በስተቀር ለመራጭነት ብቁ የሆነች ሰው እንደ አመጣጧ ተራዋን ጠብቃ መዝገብ ሹሟ ፊት በመቅረብ በመራጮች መዝገብ ላይ በጥንቃቄ እንድትመዘገብ ይደረጋል::
 2. ለምዝገባ የቀረበች ሰው መዝጋቢዎች ግላዊ መረጃዋን በተመለከተ የሚጠይቋትን ጥያቄ በትክክል መመለስ አለባት:: የሰጠችው እያንዳንዱ መረጃም በተዘጋጀው የመራጮች መዝገብ ላይ በጥንቃቄ ይሰፍራል፡፡
 3. ለመመዝገብ ብቁ የሆኑና አቅም ደካሞች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ የሚያጠቡ እንዲሁም ጨቅላ ሕፃናት የያዙ ወላጆች እራሳቸው በወሰኑት ረዳት አማካኝነት በአካል ተገኝተው ተራ ሳይጠብቁ ለምርጫ ጣቢያው ሀላፊ በማሳወቅ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይመዘገባሉ::
 4. ለአቅመ ደካሞች፣ ለዓይነ ስውራን ወይም ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ሰዎች ረዳት የሆነች ሰው፤

ሀ) እድሜዋ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ እና

ለ) እጩ ተወዳዳሪ፣ የእጩ ተወካይ ወይም የምርጫ ታዛቢ ያልሆነች መሆን ይኖርባታል፡፡

ሐ) ረዳት የሚፈልጉ ሰዎች የራሳቸውን ረዳት ሳይዙ የመጡ ከሆነ የምርጫ አስፈጻሚዋ ለመመዝገብ ከመጡ መራጮች መካከል ፈቃደኛ የሆነች ሰው ጠይቃ እንድታግዝ ታደርጋለች፡፡

 1. የመዝገብ ሹሟ መራጯን ስትመዘግብ በምርጫ ጣቢያው የሚገኙ ታዛቢዎች እና ተመዝጋቢዋ ለመስማት በሚችሉበት ሁኔታ ድምጹዋን ከፍ አድርጋ መረጃዎቹን አንድ በአንድ ደግማ በመናገር ዝርዝሩን በመራጮች መዝገብ ላይ ታሰፍራለች፡፡
 2. መራጮች ከተመዘገቡ በኋላ በመራጮች መዝገቡ ላይ በስማቸው ትይዩ እንደ ችሎታቸው በጽሁፍ ወይም በጣት አሻራ እንዲፈርሙ ወይም ጣቶች የሌሏት ሰው ከሆነች መዝጋቢዋ በመራጮች መዝገቡ ልዩ አስተያየት አምድ ላይ ይህንኑ ትጽፋለች፡፡

አንቀፅ 23. አንድ ጊዜ እና አንድ ቦታ ብቻ በግንባር ስለመመዝገብ

 1. ማንኛዋም መራጭ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ጊዜ በላይ ወይም በሌላ የምርጫ ጣቢያ ድጋሚ መመዝገብ የለባትም፡፡
 2. የመራጭነት ምዝገባ ልዩ የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ የሚካሄደው በግንባር በመቅረብ ብቻ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 24. ስለመራጮች የምዝገባ መታወቂያ ካርድ  በመራጭነት የተመዘገበች ሰው፤

 1. የመራጭነት ምዝገባ መታወቂያ ካርድ ይሰጣታል::
 2. እያንዳንዱ የመራጭነት ምዝገባ መታወቂያ ካርድ መራጮች በመራጮች በመዝገብ ላይ ከተመዘገቡ በኋላ ከመዝገቡ ጋር እየተገናዘቡ የሚሞሉ የሚከተሉት አምዶች ይኖሩታል፤

ሀ) የመራጯ ስም ከነአያቷ፣

ለ) የምትኖርበት ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ፣ ምርጫ ጣቢያ፣ የቤት ቁጥር፣ መንደር ወይም ጎጥ፤

ሐ) የመዝገብ ቁጥር፣ የመዝገብ ተራ ቁጥር፣ የመራጭ መለያ ቁጥር እና የመዝገብ ገጽ፤

መ) የመራጯ ዕድሜ፤

ሠ) የመራጯ የምልክት ወይም የአውራ ጣት ፊርማ፣ የመዝጋቢዋ ፊርማ እና

ረ) የተመዘገበችበት ቀን፡፡

 1. አንድ መራጭ አንድ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ ብቻ ይኖረዋል፡፡
 2. ለምርጫ የተመዘገበች ሰው በድምፅ መስጫው ዕለት የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርዷን ይዛ ወደ ምርጫ ጣቢያ መምጣት አለባት፡፡
 3. የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ የጠፋባት መሆኑን በማስረጃ ያረጋገጠች ወይም የተበላሸባት መራጭ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደበት ባለበት ጊዜ፣ የመራጮች መዝገብ ለሕዝብ ግልጽ በሚደረግበት ጊዜ ወይም በምርጫው ቀን በማንኛውም የምርጫ ጣቢያው የሥራ ጊዜ የምርጫ ጣቢያው ምትክ ካርድ እንዲሰጣት ማመልከት ትችላለች።
 4. መመዝገቧ ከምርጫ ጣቢያው መዝገብ ከተረጋገጠ በኋላ በቃለ ጉባዔ ተይዞ በምትኩ ሌላ ካርድ ይሰጣታል ወይም አቤቱታው የቀረበው በምርጫው ቀን ሲሆን ድምጽ እንድትሰጥ ይደረጋል፡፡ በመራጮች መዝገብ ላይ ቀድሞ የተሰጣት ካርድ ቀሪ ኮፒ ላይ ውድቅ የተደረገ ተብሎ ምልክት ይደረግበታል፡፡ የተበላሸውን ካርድ ይዛ ከቀረበችም እንድትመልስ ይደረጋል።

አንቀፅ 25. የመራጮች መዝገብ ይዘት

 1. የመራጮች መዝገብ የሚከተሉትን መረጃዎች ለመሙላት የሚያስችሉ አምዶች ይኖሩታል፤

ሀ) የመዝገብ ተራ ቁጥር፣

ለ) የመራጭ መለያ ቁጥር፣

ሐ) የምዝገባ ቀን፣

መ) የተመዝጋቢዋ ሙሉ ስም ከነአያት፣

ሠ) የምስክርነት ቃል የተሰጠ እንደሆነ፣

ረ) የተመዝጋቢዋ ፆታ፣

ሰ) የተመዝጋቢዋ ዕድሜ፣

ሸ) የተመዝጋቢዋ የትውልድ ቀን እና ዓ.ም፣

ቀ) አካል ጉዳተኝነት፣

በ) የአካል ጉዳተኝነት ዓይነት፣

ተ) የቤት ቁጥር፣ መንደር ወይም ጎጥ፣

ቸ) በምርጫ ክልሉ የኖረበት ጊዜ፣

ኀ) የምዝገባው ዕለት የጽሕፈት ወይም የአውራ ጣት ወይም በሌላ ምልክት ፊርማ፣

ነ) የምርጫው ዕለት የጽሕፈት ወይም የአውራ ጣት ወይም በሌላ ምልክት ፊርማ፣

እና

ኘ) ልዩ አስተያየት፡፡

 1. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1)(መ)፣ (ረ)፣ (ሰ)፣ (ሸ)፣ (ቀ)፣ (በ)፣ (ተ) እና (ቸ) የተደነገገው በመራጮች ምዝገባ ወቅት ለመመዝገብ የመጣችን ነዋሪ በመጠየቅ እና ማስረጃውን በማየት የሚሞላ ይሆናል፡፡
 2. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1(ነ) የተደነገገው በድምፅ መስጫው ዕለት መራጯ የምትፈርምበት አምድ ነው፡፡

አንቀፅ 26. በምርጫ ጣቢያው በየዕለቱ ምዝገባ ማጠናቀቂያ ላይ ስለሚያዝ ቃለ ጉባዔ

 1. የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ለምሳ ሲወጡና ሲመለሱ እንዲሁም የቀኑ የመራጮች ምዝገባ ሥራ እንደተጠናቀቀ የመራጮች መዝገብ፤

ሀ) መጨረሻ የተመዘገበው መራጭ መለያ ቁጥር፣

 

ለ) ቀን፣ ወር እና ዓመተ ምህረት

 

ሐ) ክልል፣

 

መ) የምርጫ ክልል፣

 

ሠ) ወረዳ፣

 

ረ) ቀበሌ፣

 

ሰ) የምርጫ ጣቢያ ስም፣

 

ሸ) የምርጫ ጣቢያ መለያ ቁጥር፣

 

ቀ) የማሸጊያው ቁጥሮች፣

በ) የመዝጊያ ሰዓት እና

 

ተ) የመክፈቻ ሰዓት በመመዝገብ ቦርዱ በሚያዘጋጀው የመፈራረሚያ ቅፅ ላይ ይሞላል፡፡

 1. በቅፁ ላይ የምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈጻሚዎች በየቀኑ ይፈራረሙበታል፡፡
 2. በዚህ አንቀፅ መሠረት የተያዘና የተፈረመው ቅፅ በምርጫ ጣቢያው በጥንቃቄ ይያዛል፡፡
 3. ምርጫ አስፈፃሚዎች ለምሳ ሲወጡና ከምሳ ሲመለሱ የምርጫ ጣቢያውንና የምርጫ ሰነዶች ባሉበት ሁኔታ አሽገው ይወጣሉ፤ ሲመለሱ እሽጉን ከፍተው ቃለ ጉባኤ ይፈራረማሉ፡፡
 4. በዚህ መሰረት የምርጫ አስፈፃሚዎች፤ ታዛቢዎችና የተወዳዳሪዎች ወኪሎች የምርጫ ጣቢያው ሲከፈት፤ ለምሳ ሲወጡ፤ ከምሳ ሲመለሱ እና ምዝገባ ሲጠናቀቅ በቦርዱ በተዘጋጀ የቃለጉባኤ መያዣ ቅፅ ላይ ይፈራረማሉ፡፡ በቃለ ጉባኤው ይዘት የተለየ ሃሳብ ያለው ሰው ልዩነቱን መዝግቦ ፊርማውን ያሰፍራል፡፡

አንቀፅ 27. የመደበኛው የመራጮች መዝገብ አዘጋግ

 1. በመራጮች መደበኛ ምዝገባ ማጠናቀቂያ ዕለት እና የመራጮች ምዝገባ ሰዓት እንዳበቃ፤ በመራጮች መዝገብ ላይ የሚካሄደው ምዝገባ ይቆማል፡፡
 2. መዝገቡ ከዚህ ቀጥሎ በቅደም ተከተል የተዘረዘረው ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ወዲያውኑ ይዘጋል፤
 3. የመራጮች ምዝገባ ሲጠናቀቅ በመዝገቡ ላይ በመጨረሻ ተራ ቁጥር ከተመዘገበው ስም ቀጥሎ ያሉትን መመዝገቢያ መስመሮች ከግራ ወደቀኝ በዚግዛግ መስመር በማያያዝ ይዘጋል፡፡
 4. በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት መዝገቡ ከተዘጋ በኋላ፦

ሀ) ጠቅላላ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር፣

 

ለ) የተመዘገቡ ሴት መራጮች ቁጥር፣

 

ሐ) የተመዘገቡ ወንድ መራጮች ቁጥር፣

 

መ) ክልል፣

 

ሠ) የምርጫ ክልል፣

 

ረ) ወረዳ፣

 

ሰ) ቀበሌ፣

 

ሸ) የምርጫ ጣቢያ ስም፣

 

ቀ) የምርጫ ጣቢያ መለያ ቁጥር፣

 

በ) ቀን፥ወር እና ዓመተ ምህረት፣

 

ተ) መጨረሻ የተመዘገበው መራጭ መለያ ቁጥር፣

 

ቸ) የተበላሹ የመራጭ መታወቂያ ካርዶች ብዛት፣

 

ኀ) የምስክርነቶች ቁጥር፣

 

ነ) የአቤቱታዎች ቁጥርን

 

በመለየት ቦርዱ በሚያዘጋጀው የመተማመኛ ቅፅ  ላይ ይሰፍራል፤ የምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ ስምና ፊርማ ያርፍበታል።

 1. በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (3)መሠረት የተለየውን መራጭ ብዛት በዚግዛግ ከተዘጋው መዝገብ መጨረሻ ገፅ ጀርባ ላይ “ወንድ____ ሴት____ ድምር ____” በሚል በመመዝገብ እና በቃለ ጉባኤው ላይ በመሙላት የምርጫ አስፈፃሚዎች ይፈራረሙበታል፡፡
 2. ቦርዱ በተለየ ሁኔታ ካልወሰነና አመቺ በሆነ ማስታወቂያ ለሚመለከታቸው ምርጫ ጣቢያዎች ካልገለፀላቸው በስተቀር በዚህ አንቀፅ መሠረት ተዘግቶ የምርጫ አስፈፃሚዎች ከፈረሙበት በኋላ በመራጮች መዝገብ ላይ አዲስ መራጮች አይመዘገቡም፣ የሚሰፍር ወይም የሚፃፍ ነገር አይኖርም::
 3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (6) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የመራጭ ምዝገባን በተመለከተ በሚነሱ ክርክሮች ላይ የምርጫ ጣቢያ ወይም የምርጫ ክልል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት እንደ አግባብነቱ የምርጫ ጣቢያ ወይም የምርጫ ክልል ፅህፈት ቤት የመሰረዝ ወይም የመመዝገብ ስራውን ያከናውናል፡፡
 4. የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ የፍርድ ቤት ውሳኔ ቅጂ ይዞ የቀረበ መራጭ የድምፅ አሰጣጥ ቆጠራና ውጤት አፈፃፀም መመሪያ ላይ በተቀመጠው መሰረት በቀጥታ ድምጽ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡
 5. የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀበት ዕለት በአንቀፅ 27 ንኡስ አንቀዕ (4) መሰረት ከሚያዘው መተማመኛ በተጨማሪ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (5) መሠረት በየመዝገቡ ላይ ከተሞላው ማጠቃለያ ድምር ቀጥሎ የምርጫ አስፈፃሚዎች ይፈራረሙበታል፡፡
 6. የግል እጩዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ወኪሎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች፣ እንዲሁም ታዛቢዎች የመራጮች መዝገብ አዘጋግ ሂደትን ጨምሮ መታዘብ ይችላሉ፡፡

 

 

አንቀፅ 28. የመራጮች ልዩ መዝገብ አዘጋግ

በዚህ መመሪያ አንቀፅ 11 መሠረት ቦርዱ በወሰነው ልዩ የመራጮች ምዝገባ ቀን መራጮች ከተመዘገቡ በኋላ የመራጮች ልዩ መዝገብ በሚከተለው ሁኔታ ይዘጋል፤

 1. ልዩ ምዝገባው የሚጠናቀቀው እና መዝገቡ የሚዘጋው ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በልዩ ምዝገባ ማጠናቀቂያ ዕለትና ሰዓት ይሆናል፡፡
 2. የልዩ ምዝገባ መራጮች መዝገብ አዘጋግ በዚህ መመሪያ አንቀፅ 27 ለመራጮች መደበኛ መዝገብ አዘጋግ በተደነገገው መሠረት ይሆናል::

አንቀፅ 29. የመራጮችን መዝገብ ለህዝብ ግልፅ ስለማድረግ

 1. የመራጮች ምዝገባ እንደተጠናቀቀ የመራጮች መዝገብ በምርጫ ጣቢያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለተከታታይ 10 ቀናት ይፋ ሆኖ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ይደረጋል፡፡
 2. የመራጮችን መዝገብ ለመመልከት የምትቀርብ ሰው የመራጭነት ምዝገባ ካርዷን እና የማንነት መታወቂያ ካርድ ወይም ማንነቱዋን የሚያውቅ ምስክር ማቅረብ  አለባት::
 3. የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው የሚደረገው በሚከተለው አሰራር ይሆናል፤

ሀ) የመራጮችን መዝገብ ህዝቡ በግልፅ እንዲያይ የሚያደርጉት በምርጫ ጣቢያው የመዝገብ ሹም ሆነው የተመደቡት የምርጫ አስፈፃሚ አባላት ናቸው::

 

ለ) የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ መዝገቡን ለመመልከት የሚፈልጉትን ሰዎች  እንዳመጣጣቸው ተራ በተራ ወደ መዝገቡ እየቀረቡ እንዲመለከቱ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ታመቻቻለች፣ ታስፈፅማለች፡፡

 

ሐ) የመራጮችን መዝገብ መመልከት የምትፈልግ ሰው ወደመዝገብ ሹም በመቅረብ የምትፈልገውን መረጃ ከመዝገቡ ለማየት የመዝገብ ሹሟን ትጠይቃለች፡፡ የመዝገብ ሹሟም የተጠየቀውን መረጃ ለሚመለከታት ሰው መዝገቡን በመግለፅ ታሳያለች፡፡

 

መ) የመራጮችን መዝገብ የምትመለከት ሰው በመዝገብ ሹሟ አማካኝነት የምትፈልገው መረጃ ያለበትን ገጽ /ገፆች/ በዓይን ከማየት ወይም መረጃው ሲነበብላት ከማዳመጥና ማስታወሻ ከመያዝ ውጪ በእጇ መንካት፣ መዝገቡ ላይ መፃፍ፣ ምልክት ማድረግ፣ ወይም ፎቶግራፍ ማንሳት የተከለከለ ነው::

 

 1. የመራጮች መዝገብ ህዝብ በግልፅ እንዲያየው ሲደረግ የምርጫ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎች እና የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊገኙ ይችላሉ፡፡
 2. የመራጮች መዝገብ ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ይፋ ወጥቶ ቅዳሜ እና እሁድን እንዲሁም በዓላትን ጨምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት ህዝቡ በግልፅ እንዲያየው የሚደረገው በየዕለቱ በመንግሥት የሥራ ሰዓት ይሆናል::

 

 

 1. የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የሚሆንባቸው ቀናት ሲጠናቀቅ፤

ሀ) መዝገቡ ለ10 ተከታታይ ቀናት ህዝቡ እንዲያየው ስለመደረጉ፣

 

ለ) ህዝቡ መዝገቡን ሲመለከት የጠየቀውን መረጃ ይዘት እና መረጃውን ስለማግኘት እና አለማግኘቱ በአጭሩ፣

 

ሐ) የአካባቢው ነዋሪ የሆነች ሰው መዝገቡን አይታ ለአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረበችው አቤቱታ ካለ እና ስለተሰጠው መልስ በአጭሩ እንዲሁም መዝገቡ ለሕዝብ ግልፅ በሆነባቸው ቀናት የተገኙ ታዛቢዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የግል እጩ ወኪሎችን የሚመለከቱ መረጃዎች መተማመኛ ይዘጋጃል፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች ከተፈራረሙበት በኋላ በሰነድነት ይያዛል፡፡

አንቀጽ 30.  በመራጭ አመዘጋገብ ሂደት የተፈፀመ ስህተት የሚስተካከልበት አግባብ

 1. በመራጭነት የተመዘገበች ሰው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ በሆነበት ጊዜ የግል መረጃዋን በተመለከተ ስህተት አለ የሚል ቅሬታ ካላት እንዲስተካከልላት ለምርጫ ጣቢያው ማመልከት ትችላለች፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) ስር የተጠቀሰው ማመልከቻ ለዚሁ አላማ በተዘጋጀ ቅጽ ላይ ተሞልቶ ከመራጯ የምዝገባ መታወቂያ ካርድ እና በመራጮች መዝገብ ላይ የሰፈረው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ ከሚያስረዳ ማንኛውም ሰነድ ጋር ተያይዞ መቅረብ አለበት፡፡
 3. ማመልከቻው ተቀባይነት ካገኘ የምርጫ አስፈጻሚዋ ለምርጫ አስፈጻሚዎች በተዘጋጀው ምዝገባ ማኑዋል ላይ በተገለጸው አግባብ ማስተካከያውን ታደርጋለች፡፡

አንቀፅ 31. ከምዝገባ ስለመሰረዝ

 1. በመራጭነት የተመዘገበች ሰው በአዕምሮ ህመም ምክንያት ለመወሰን ብቃት የሌላት መሆኑ በባለሙያ ካልተረጋገጠ፣ ወይም በማጭበርበር የተመዘገበች፣ በድጋሚ የተመዘገበች፣ የሞተች ወይም አግባብ ባለው ህግ መሠረት በተሰጠ የፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ መብቷ የተገደበ መሆኑን የሚመለከት በማስረጃ የተረጋገጠ ተቃውሞ ካልቀረበባት በስተቀር ከመራጮች መዝገብ አትሰረዝም::
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሲከሰት ወይም ሲታወቅ እንደ የአግባብነቱ ፍርድ ቤቶች፣ የወሳኝ ኩነት ቢሮዎች፣ ሆስፒታሎች፣ እድሮች ወይም ሌሎች ስለጉዳዩ ዕውቀት ያላቸው የህብረተሰቡ አባላት ወዲያውኑ ለሚመለከተው፤

ሀ) የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወይም

ለ) የምርጫ ክልል ወይም

ሐ) የምርጫ ጣቢያ

መ) መራጯ የተመዘገበችበትን የምርጫ ክልልና ጣቢያ ለይቶ በመግለፅ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለባቸው::

 1. የእጩ ስረዛ የሚከናወነው በምርጫ ጣቢያ ሲሆን፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት መረጃ የደረሰው የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ወይም የምርጫ ክልል መረጃውን በተቻለ ፍጥነት ለምርጫ ጣቢያ እንዲደርስ ማድረግ አለበት፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2) እና (3) መሰረት መረጃ የደረሰው ምርጫ ጣቢያ፦

ሀ) ተመዝጋቢውን ወዲያውኑ ከመራጮች መዝገብ ላይ ይሰርዘዋል፡፡

ለ) ለተሰረዘው መራጭ ከመራጮች መዝገብ መሰረዙን እና ተቃውሞ ካለው ለምርጫ ጣቢያው የአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ማቅረብ እንደሚችል ገልጾ በጽሁፍ ያስታውቀዋል፡፡

ሐ) ከላይ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ “ሀ” መሠረት የተሰረዘው መራጭ ለመሠረዙ የቀረበበትን ማስረጃ በመጥቀስ ቃለ ጉባኤ ይይዛል፡፡

መ ) ከላይ በዚህ ንዑስ አንቀፅ “ሐ” መሠረት የተያዘ ቃለጉባዔ የምርጫ አስፈፃሚዎች ይፈራረሙበታል፡፡

 1. በዚህ አንቀፅ መሠረት አንድ ሰው ከመራጮች መዝገብ የምትሰረዘው የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ እስከሚያበቃ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ክፍል ስድስት

ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የመራጮች ምዝገባ እና የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደት ስለሚቋረጥበት ሁኔታ

አንቀፅ 32. የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደት መቋረጥ

 1. የምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ የምርጫ ጣቢያው በሁከት፣ ግጭት፣ በአውሎ ነፋስ፣ በጎርፍ፣ በእሳት ወይም በማንኛውም አስገዳጅ ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ የማይቻልበት ከአቅም በላይ የሆነ አስገዳጅ ሁኔታ ካጋጠመው የመራጮችን ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደት ሊያቆም ይችላል።
 2. የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደት በደህንነት ችግር ምክንያት ከማቋረጡ በፊት የምርጫ ጣቢያው ሰብሳቢ ከሚመለከተው የፀጥታ አስከባሪ ጋር መማከር ይኖርበታል ፡፡
 3. በዚህ አንቀጽ በተቀመጠው አግባብ የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ የማድረግ ሂደት ከመቋረጡ በፊት፤ በተቻለ መጠን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ከምርጫ ክልል ጽ/ቤት ጋር መማከር ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነ የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮችን መዝገብ ለህዝብ ግልፅ የማድረግ ሂደቱ እንደተቋረጠ በተቻለ ፍጥነት ለምርጫ ክልል ጽ/ቤት ማሳወቅ አለበት ፡፡
 4. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ሂደቱን እንዲያቋርጥ ከምርጫ ክልሉ ጽ/ቤት ወይም ከምርጫ የፀጥታ አስከባሪዎች የቅርብ ኃላፊ ሃሳብ ከተሰጠው የመራጮችን ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ የማድረግን ሂደት ማቋረጥ አለበት።
 5. በዚህ አንቀጽ አግባብ የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ የማድረግ ሂደት የተቋረጠ ከሆነ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ልዩ ጥበቃ የሚሹ ቁሳቁሶችን፤

ሀ) መራጮች ምዝገባ መቋረጥ በተመለከተ ሲሆን የመራጮች መዝገብ እና የመራጮች ካርድ መዝገብ፣ ህጋዊ የምርጫ ጣቢያው ማህተም እና የተጠናቀቁ ቅጾች፣

ለ) የመራጮችን መዝገብ ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ሂደት መቋረጥን በተመለከተ ሲሆን የመራጮች መዝገብ፣ የምርጫ ጣቢያው ህጋዊ ማህተም እና የተጠናቀቁ ቅጾች ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ መታሸጋቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡

 1. የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ የማድረግ ሂደት እስከሚቀጥል ድረስ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ልዩ ጥበቃ የሚሹ ቁሳቁሶች በጊዜያዊነት የሚቀመጡበትን ቦታ ለመወሰን ከምርጫ ክልል ጽ/ቤት ጋር ይመክራል፡፡ በጊዜያዊነት የሚቀመጡበት ቦታ ከተወሰነ በኋላ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ልዩ ጥበቃ የሚሹ ቁሳቁሶች ታሽገውና በተቆለፈ ክፍል ውስጥ ተገቢውን የደህንነት ጥበቃ ተደርጎላቸው መቀመጣቸውን ያረጋግጣል፡፡
 2. በምርጫ ጣቢያው የተገኙ ፈቃድ ያላቸው ወኪሎች፣ ታዛቢዎች እና ጋዜጠኞች ልዩ ጥበቃ የሚሹ ቁሳቁሶች ሲታሸጉና ወደ ጊዜያዊ ማስቀመጫ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ ሂደቱን እንዲመለከቱ ይደረጋል፡፡
 3. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ሂደቱ የተቋረጠበትን ጊዜ እና ምክንያት በምርጫ ጣቢያው ቃለጉባዔ ላይ መያዙን አስፈፃሚዎቹም እንደፈረሙበት ያረጋግጣል፡፡

አንቀፅ 33. የተቋረጠ የመራጮች ምዝገባ ወይም የመራጮች መዝገብ ለህዝብ ይፋ ማድረግ  ሂደት ዳግም ስለመጀመር

 1. የተቋረጠው እንቅስቃሴ በምርጫ ጣቢያው እንደገና ሊጀመር ይችል እንደሆነ ለመወሰን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ከምርጫ ክልል ጽ/ቤት እና በፀጥታ ምክንያት ከተቋረጠ ደግሞ ከምርጫ ጣቢያው የጸጥታ አስከባሪዎች ሀላፊ ጋር ምክክር ማድረግ አለበት፡፡
 2. በተፈጠረው ችግር ምክንያት የምርጫ ጣቢያውን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የማይቻል ከሆነ፣ ሌላ የምርጫ ጣቢያ ቦታ በአቅራቢያው እንዲቋቋም ለመወሰን ወይም በአቅራቢያው ባለ ሌላ የምርጫ ጣቢያ ሂደቱን ለማስቀጠል የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ከምርጫ ክልል ጽ/ቤት ጋር ወይም ከሚመለከተው የቦርዱ ጽ/ቤት ጋር መማከር አለበት፡፡
 3. በምርጫ ጣቢያው የተቋረጠው እንቅስቃሴ በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት፣ ሂደቱ ተቋርጦ ለቆየበት ጊዜ ያህል ይራዘማል።
 4. እንቅስቃሴው የሚጀመርበት ቦታ እና ጊዜ ከተወሰነ በኋላ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊና የምርጫ ክልሉ ጽ/ቤት ይህንን መረጃ ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው፡፡
 5. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ እንቅስቃሴው የሚጀመርበትን ቦታና ሰዓት ፈቃድ ለተሰጣቸው ወኪሎች፣ ታዛቢዎች እና ጋዜጠኞች ያሳውቃል፡፡
 6. የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ እንቅስቃሴው እንደገና የሚጀመርበትን ቦታ እና ሰዓት በምርጫ ጣቢያው ቃለጉባኤ ላይ ያሰፍራል፡፡

 

ክፍል ሰባት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

አንቀፅ 34. በመራጮች ምዝገባ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት

 1. በመራጮች ምዝገባ ሂደት የሚከተሉትን የተከለከሉ ተግባራት ፈፅማ የተገኘች በህግ ተጠያቂ ትሆናለች፤

ሀ) ተመዝጋቢዋ መመዘኛውን አለማሟላቷን እያወቀች በመራጭነት መዝግባ የተገኘች የመዝገብ ሹም፣

 

ለ) በምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሠሌዳ መሠረት እና ለመራጮች ምዝገባ ከተወሰኑት ቦታ፣ ቀን እና ሰዓት ውጪ ማንኛውንም ዓይነት ምዝገባ ስታከናውን የተገኘች የመዝገብ ሹም፣

 

ሐ) ለመራጭነት ከአንድ ጊዜ በላይ ወይም ከአንድ ምርጫ ጣቢያ በላይ ተመዝግባ የተገኘች እንደሆነ ወይም ከአንድ በላይ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ ይዛ የተገኘች፣

 

መ) በመራጭነት ለመመዝገብ ስትል የሀሰት መግለጫ፣ ወይም ማስረጃ የሰጠች ወይም የሀሰት ሰነድ ለሚመለከተው አካል አቅርባ የተገኘች፣

ሠ) መራጮች እንዳይመዘገቡ ወይም እንዲመዘገቡ በማንኛውም መንገድ ያስፈራራች ወይም የሀሰት መረጃ ወይም ማስረጃ የሰጠች፣

 

ረ) የሌላውን በመራጭነት የመመዝገብ ወይም አቤቱታ የማቅረብ መብት

እንዳይጠቀምበት የከለከለች፥ የገደበች ወይም ያወከች፣

 

ሰ) የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ የለወጠች፣ የሠረዘች፣ የደለዘች፣ ወይም አስመስላ የሰራች፣

 

ሸ) በህጋዊ መንገድ የተመዘገበን መራጭ ከማንኛውም የምርጫ ሰነድ የሠረዘች ወይም የደለዘች፡፡

 

ቀ) ከመዝገብ ሹሟ ውጪ የመራጮች ምዝገባ አከናውና የተገኘች።

 

 1. የምርጫ ጣቢያ ሃላፊዋ በዚህ አንቀጽ የተከለከሉ ሌሎች ተግባራት በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 157 እንዲሁም አግባብነት ባለው የወንጀል ህግ መሠረት የተፈፀሙ ጥሰቶች ሲኖሩ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጉዳዮቹን ለፖሊስ ትመራለች፣ ትከታተላለች፡፡
 2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ስር የተደነገገው እደተጠበቀ ሆኖ፤

ሀ) የተመዘገበች መራጭ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል እጩ ወኪል  በመራጮች ምዝገባ ላይ ተቃውሞ ካላት ተቃውሞውን ከነምክንያቱ በቦርዱ በተዘጋጀ ቅጽ አማካኝነት ለምርጫ ጣቢያው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ታቀርባለች፡፡

 

ለ) በምርጫ ሕጉ በተፈቀደላቸው የአምስት  ቀን ጊዜ ገደብ ውሳኔ ካልተሰጠ ወይም በተሰጠው ውሳኔ ያልተስማማች እንደሆነ በአምስት ቀን ገደብ ውስጥ በየደረጃው ላሉ የቦርዱ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ኮሚቴዎች አልፎም ስልጣን ላላቸው በየደረጃው ላሉ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት አቅርባ ውሳኔውን በጽሑፍ የማግኘት መብት አላት፡፡

 

ሐ) የምርጫ ጣቢያው የጣቢያው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፥ የምርጫ ክልሉ አቤቱታ ሰሚ

ኮሚቴ ወይም ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ስራውን ያከናውናል፡፡

 

 1. የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዋ አንድ መራጭ በዚህ መመሪያ መሰረት ከአንድ ጊዜ በላይ ወይም በሌላ የምርጫ ጣቢያ ድጋሚ መመዝገቧን ወይም እየተመዘገበች መሆኑን አልያም ከአንድ በላይ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ ይዛ እንደተገኘች ስታውቅ ወይም በመረጃ የተደገፈ አቤቱታ ሲደርሳት በምርጫ ሕጉ እና በዚህ መመሪያ መሰረት መራጯን ከመራጮች መዝገብ ላይ ወዲያውኑ ትሰርዛለች፡፡
 2. በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 152 ንዑስ አንቀፅ (2) መሠረት በቀረበ አቤቱታ መነሻነት አግባብ ያለው የቦርዱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ድጋሚ ምዝገባ ተግባሩ የተፈጸመው ሆን ብሎ ለማጭበርበር እንዳልሆነ ከወሰነ የመራጯ ድጋሚ ምዝገባ እንዲሰረዝ ሁለተኛው የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድም እንዲወገድ ውሳኔውን ለምርጫ ጣቢያው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስተላልፋል፡፡ የምርጫ ጣቢያው ፅሕፈት ቤትም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ስራውን ያከናውናል፡፡

አንቀፅ 35. በመራጮች ምዝገባ ሂደት ሥራ ላይ ስለሚውሉ ቅፆች እና ስለ ሪፖርት አቀራረብ

 1. በየደረጃው የተቋቋሙ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት የመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ለበላይ የምርጫ አስፈፃሚ አካል ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው::
 2. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) መሠረት የሚቀርብ ሪፖርት ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ እና መመሪያዎች መሰረት ይከናወናል፡፡

አንቀፅ 36. የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው ወይም አካል የዚህን መመሪያ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ በምርጫ ክልል ኃላፊ በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት የመተባበር ግዴታ አለበት::

አንቀፅ 37. ስለቅጣት

ይህን መመሪያ የጣሰች ወይም ሆን ብላ የምርጫውን ሂደት የሚያሰናክል ጥፋት ፈፅማ ከተገኘች አግባብ ባለው ሕግ መሰረት ትጠየቃለች፡፡  አንቀፅ 38. የተሻሩ መመሪያዎችና አሰራሮች

ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም አሠራር በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም::

አንቀፅ 39. መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ  ከታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ብርቱካን ሚደቅሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ

Exit mobile version