Directives

የመገናኛ ብዙሃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ ምግባር እና አሰራር መመሪያ ቁጥር 02 /2013

የመገናኛ ብዙሃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ ምግባር እና አሰራር መመሪያ ቁጥር 02 /2013

 

ምዕራፍ አንድ ጠቅላላ

አንቀጽ 1 አውጪ ባለስልጣን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 133/2011 አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ (1) እና በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. አንቀፅ 44 ንኡስ አንቀፅ (4) አንቀፅ 123 እና አንቀፅ 126 መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡

 

አንቀፅ 2   አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ « የመገናኛ ብዙሃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባር እና አሰራር መመሪያ ቁጥር 02/2013 ዓ.ም» ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

 

አንቀፅ 3 ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡-

 • “በአዋጅ” ማለት አዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በአዋጅ ቁጥር 1133/11  ላይ ያሉ ለዚህ መመሪያ አግባብነት ያላቸው ትርጓሜዎች እንደአግባብነቱ ተፈፃሚነት አላቸው፡፡
 • “የመገናኛ ብዙሃን” ማለት መጻሕፍትን፣ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን፣ ጦማሮችን እና በየጊዜው የሚወጣ ኅትመት አካል ያልሆኑ ፎቶ፣ ሥዕልና ካርቱንን ሳይጨምር በየጊዜው የሚወጣ ኅትመትን፣ የብሮድካስት አገልግሎትን እና የበይነመረብ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የዜና ወይም የፕሮግራም ወይም የዜና እና የፕሮግራም አገልግሎት ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ አካላት ሲሆኑ የዜና አገልግሎት ድርጅቶችንም እና የማህበረሰብ ሬዲዮዎችንም ያጠቃልላል፤

 

 • “በየጊዜው የሚወጣ ኅትመት” ማለት አንድ ቋሚ ስያሜ በመያዝ በመደበኛነት ሳይቋረጥ በተከታታይ እንዲወጣ ታቅዶ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም፤ ለጠቅላላው ኅብረተሰብ ወይም ለአንድ የተወሰነ የሕዝብ ክፍል እንዲደርስ ታስቦ የሚሰራጭ ጋዜጦችንና መፅሄቶችን የሚያካት የኅትመት ስራ ነው፤
 • “የብሮድካስት አገልግሎት” ማለት ዳታና የፅሁፍ መልዕክትን፣ የግል ድርጅት ወይም የመንግሥት አካል ውስጣዊ ግንኙነቶችን ሳይጨምር በምድር ለምድር አስተላላፊ፣ በሬዲዮ ሞገድ፣ በኬብል፣ በሳተላይት፣ ወይም እነዚህን በማቀናጀት ሥራ ላይ በሚውሉ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ወይም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫዎች አማካይነት አጠቃላይ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብን ክፍል ለማሳወቅ፣ ለማስተማር ወይም ለማዝናናት በድምጽ ወይም በምስል ወይም በድምጽና በምስል በክፍያ ወይም ያለክፍያ የሚተላለፍ ወይም የሚሰራጭ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሥርጭት አገልግሎት ነው፤
 • “የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን” ማለት በመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት አቅራቢው ይዘት ላይ የመወሰን ኃላፊነት ሥር ዋነኛ ሥራው ዜናና ፕሮግራምን መሰብሰብ፣ ማዘጋጀት፣ ማጠናቀርና ማሰራጨት በሆነ ድርጅት በበይነ መረብ/በኢንተርኔት አማካይነት የሚሰራጭ ምስል፣ ድምፅ፣ ቪድዮ እና የድረ-ገፅ ፅሁፍን በመጠቀም ወይም እነዚህን በማቀናጀት መረጃ የማስተላለፍ አገልግሎት ነው፤
 • “ምርጫ ነክ መልዕክት” ማለት ለምርጫ የሚወዳደር የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል እጩ ተወዳዳሪ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ለመራጮች የሚያቀርበው የአላማ፣ የፕሮግራምና የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ ሂስ፣ አስተያየት ወይም መሰል የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ነው፡፡
 • “የፖለቲካ ማስታወቂያ” ማለት ለምርጫ ውድድር የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል እጩ ተወዳዳሪ ገንዘብ በመክፈል ወይም ለመክፈል ቃል በመግባት በመገናኛ ብዙሃን የሚያስነግረው አጭር ማስታወቂያ ነው።
 • “የምርጫ ወቅት” ማለት ቦርዱ የሚወስነው የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ቦርዱ የምርጫ ውጤት ለህዝብ ይፋ ካደረገበት ቀን በኋላ ጀምሮ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያለው ጊዜ ነው፡፡
 • “ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት” ማለት በማንኛውም መደበኛ ሁኔታ ይደርሳሉ ተብሎ ያልተገመቱ እና ያልተጠበቁ፣ ከአመልካቹ ቁጥጥርና ምክንያታዊ ግምት ውጪ በሆነ ምክንያት የሚደርሱ እና እንዳይደርሱ መከላከል ወይም ማስቆም የማይቻሉ ክስተቶች ናቸው፡፡
 • “የጥቅም ግጭት” ማለት በጋዜጠኛው እና በእጩ ተወዳዳሪው መካካል ያለ ዝምድና፣ ማለትም አባቱን፣ እናቱን፣ ልጁን፣ አያቱን፣ እህቱን፣ ወንድሙን፣ አክስቱን፣ አጎቱን ወይም የትዳር አጋሩን፣ የትዳር አጋሩን ወንድም፣ እህት፣ እናትና አባትጋ የሚያያዝ ከሆነ እንዲሁም፣ ፣ ማንኛውም አይነት የጥቅም ግንኙነት ወይም የግጭት የንግድ ግንኙነት እና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
 • “ቦርድ” ማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነው።

አንቀፅ 4 የፆታ አገላለፅ

በዚህ መመሪያ ላይ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያጠቃልላል፡፡

አንቀጽ 5 አላማ

የመገናኛ ብዙሃን ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ እንዲሆን የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው በሚዘግቡበት ወቅት የሚኖራቸው መብት፣ የስነምግባር ሀላፊነት እና ግዴታዎችን መደንገግ ለምርጫ ሂደት መሳካት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህ መመሪያ ወጥቷል፡፡

አንቀፅ 6 የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ በምርጫ ወቅት ሀገሪቱ ውስጥ ምርጫን አስመልክቶ በሚከናወን ዜናን፣ ዘገባን፣ ሪፖርትን፣ ወይም ማናቸውም ሌላ መረጃን የማተም፣ የማሰራጨት እና የማቅረብ ተግባር ላይ የሚሳተፍ ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል።

 

ምዕራፍ ሁለት

የመዘገብ ፈቃድ ጥያቄ አቀራረብ እና አሰጣጥ

አንቀፅ 7 የምርጫ ሂደትን ለመከታተል ጥያቄ ማቅረብ ስለመቻሉ

 

 • ማናቸውም በተመዘገቡበት አገር ህግ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚሰሩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ የመገናኛ ብዙሃን በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ምርጫዎችን በምርጫ ጣቢያው ውስጥ በመገኘት በሚወክሏቸው ጋዜጠኞች አማካይነት ለመከታተል እና ለመዘገብ የእውቅና ጥያቄ ለቦርዱ ማቅረብ ይችላሉ።
 • ማንኛውም ምርጫን የሚዘግብ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ስራውን የሚገልፅ መታወቂያ በጉልህ ሊታይ በሚችል መልኩ ደረቱ ላይ ወይም አንገቱ ላይ በማንጠልጠል፣ ከሚሰራበት የመገናኛ ብዙሃን የተሰጠውን ማረጋገጫ በመያዝ በምርጭ ወቅት ከምርጫ ጣቢያ ከ200 ሜትር ርቀት ዙሪያ ውጪ በመሆን መዘገብ ይችላል፡፡

አንቀፅ 8   ስለ እውቅና ጥያቄ አቀራረብ እና አሰጣጥ

 • ማናቸውም የምርጫ ሂደት ከምርጫ ጣቢያው ውስጥ ተገኝቶ ስለሂደቱ በጋዜጠኞቹ አማካኝነት ለመዘገብ የሚፈልግ የመገናኛ ብዙሃን የእውቅና ካርድ እንዲሰጠው ጥያቄውን በፅሁፍ ለቦርዱ ማቅረብ ይችላል።
 • ማናቸውም የምርጫ ሂደትን ለመከታተል የሚቀርብ የእውቅና ጥያቄ ማመልከቻ በቦርዱ ለእውቅና ጥያቄ ማቅረቢያ ጊዜ ተብሎ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡ ፡ የጥያቄ ማቅረቢያ ጊዜው የመጨረሻ ቀን ድምፅ የሚሰጥበት ዕለት 15 ቀን ሲቀረው ይሆናል።
 • ቦርዱ ለቀረበለት የመዘገብ ፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻው ተሟልቶ በደረሰው በአምስት ቀናት ውስጥ በፅሁፍ ምላሽ ይሠጣል።
 • ቦርዱ የቀረበለትን የመዘገብ ፈቃድ ጥያቄ መርምሮ መመዘኛውን አሟልቶ ለተገኘ የመገናኛ ብዙሀን እና ጋዜጠኛ የእውቅና ካርድ ወይም የመታወቂያ ካርድ በአስራ አምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ይሰጣል።
 • ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እውቅና የመስጠት ሃላፊነቱን ለክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡

አንቀፅ 9 ቦርዱ በሚያዘጋጀው ቅፅ ላይ ስለሚሞሉ መረጃዎች

ቦርዱ ማመልከቻ የሚቀርብበትን ቅፅ  የሚያዘጋጅ ሲሆን፤ ቅጹ ምርጫን በምርጫ ጣቢያ ውስጥ በ200 ሜትር ዙርያ ውስጥ ገብቶ ለመዘገብ ጥያቄ የሚያቀርቡ የመገናኛ ብዙሀን የሚከተሉትን ማካተት ይኖርበታል።

 • የተቋሙን በህግ የተመዘገበ ስምና አድራሻ፣
 • ተቋሙ መከታተል የሚፈልገው የምርጫ ሂደት ወይም አይነት፣ የሚሸፍነው አካባቢ
 • ምርጫውን የሚከታተሉለት ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር፣
 • የጋዜጠኞች ቡድን ሲሆን ቡድኑን የሚመራው ጋዜጠኛ ስም እና አድራሻ እና፣
 • የውጭ ጋዜጠኞች ከሆኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ወይም የገቡበት ቀን መገለጽ ይኖርበታል፡፡

አንቀፅ 10 ከፍቃድ ጥያቄው ጋር ተያይዘው ስለሚቀርቡ ሰነዶች

የመገናኛ ብዙሃኑ ከሚያቀርቡት ማመልከቻ ጋር፡-

 • ከሚመለከተው አካል በመገናኛ ብዙሃንነት እንዲሰራ የተሰጠው ፍቃድ ቅጂ፣
 • ምርጫውን እንዲዘግቡለት የሚልካቸው ጋዜጠኞች በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በእጩነት የቀረቡ ያለመሆናቸውን ወይም በግል ለመወዳደር ያልተመዘገቡ እንደሆነ እና ይህን የስነምግባር መመሪያ እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው የአገሪቷ ህጎች አክብሮ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ መሆኑን የሚገልፅ የተቋሙ የበላይ ሃላፊ ፊርማ እና የተቋሙ ማህተም ያለው ማረጋጋጫ ደብዳቤ፤
 • መገናኛ ብዙሃኑ ሂደቱን እንዲከታተሉ የሚያቀርበው የጋዜጠኞች ዝርዝር ላይ ያለው የእያንዳንዱ ጋዜጠኛ ሙሉ ስም፣ የጋዜጠኛው የቅርብ ጊዜ የፓስፖርት መጠን ፎቶግራፍ፣ የጋዜጠኛው ማንኛውም አይነት የመታወቂያ ካርድ ቅጂ/ኮፒ ተያይዞ መቅረብ አለበት።
 • ፍቃድ ጠያቂው የውጪ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ሲሆን ከላይ ከተመለከቱት ሰነዶች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተሰጠውን የዘገባ ፍቃድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
 • እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ይህንን የስነ-ምግባር መመሪያ እና ሌሎች የአገሪቱ ህጎችን ለማክበር ፍቃደኛ መሆኑን ቦርዱ በሚያዘጋጀው የጥያቄ ማቅረቢያ እና የስነ-ምግባር መመሪያ ቅፅ ላይ አረጋግጦ መፈረም ይኖርበታል፡፡

 

አንቀፅ 11 የፍቃድ ጥያቄው ውድቅ የሚሆንባቸው ምክንያቶች

አንድ የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ እንደ አግባብነቱ በሚከተሉት ምክንያቶች ምርጫን የመዘገብ ፈቃድ ጥያቄው ውድቅ ሊደረግበት ይችላል፡-

 • በአንቀጽ 10 ሥር የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ያላሟላ ከሆነ
 • ምርጫውን እንዲዘግቡለት ያቀረባቸው ጋዜጠኞች በፖለቲካ ድርጅት እጩነት ወይም በግል እጩነት ለመወዳደር የተመዘገቡ ሲሆኑ፣
 • የማመልከቻ ማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ በኋላ የሚቀርብ የእውቅና ጥያቄ ሲሆን፣
 • የእውቅና ጥያቄ ለማቅረብ መብት ወይም ስልጣን በሌለው ሰው የቀረበ ማመልከቻ ሲሆን፣
 • ጥያቄውን ያቀረበው ተቋም ህጋዊ እውቅና የሌለው ከሆነ፡፡

አንቀፅ 12 ውድቅ የተደረገ ጥያቄ ላይ ስለሚቀርብ ቅሬታ

 • ያቀረበው ማማልከቻ ውድቅ የተደረገበት የመገናኛ ብዙሃን ውሳኔው በተሰጠው በአምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ቅሬታውን ለቦርዱ ማቅረብ ይችላል፡፡
 • በአንቀጽ 11 (3) መሰረት ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት አመልካች የጊዜ ገደቡን ያሳለፈበት ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት እንዳለው ሲያስረዳ እና ቦርዱ ሲያምንበት ፍቃድ የሚሰጠው ይሆናል፡፡
 • ከላይ በንኡስ ቁጥር (2) ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ እውቅና ጥያቄ በማንኛውም መልኩ የድምፅ መስጫ ቀን አምስት ቀን ከቀረው በኋላ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡
 • ቦርዱ ቅሬታውን ከአስፈላጊ ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ ቅሬታው ከቀረበለት ጊዜ ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡
 • ቦርዱ በአምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ ወይም ቦርዱ በሰጠው ምላሽ ቅር የተሰኘ ሰው ቅሬታውን ቦርዱ መልስ መስጠት ከነበረበት ቀን ወይም ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በአስር ቀናት ጊዜ ገደብ ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡

 

አንቀፅ 13 የመዘገብ ፈቃድ መታወቂያ ካርድ ስለመስጠት

 • ቦርዱ ፈቃድ ለሰጣቸው ጋዜጠኞች መታወቂያ ካርድ ያዘጋጃል፣ ይህንንም ለተቋሙ ወይም ለህጋዊ ወኪሉ እንዲሁም እንዳግባብነቱ ለጋዜጠኛው ለራሱ ይሰጣል፡፡
 • የመታወቂያ ካርዱ የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ይሆናል፣

ሀ. የቦርዱ አርማ፣

ለ. ጋዜጠኛ የሚል ከቅርብ ርቀት ሊለይ የሚችል ቀለም ያለው ፅሁፍ

ሐ. የወከለውን ተቋም ስም፣ ፣

መ. የጋዜጠኛውን ስም እና ፎቶግራፍ ፣

ሠ.  የቦርዱን ማህተም፣

ረ.  መታወቂያው ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ፣

ሰ.   የመታወቂያ ቁጥር፣

ሸ.   ፈቃዱን የሠጠው ኃላፊ ፊርማ እና፣

ቀ.   የባለመታወቂያው ፊርማ፡፡

 • ቦርዱ ለእያንዳንዱ ተቋም የሚሰጠውን የመታወቂያ ካርድ ቁጥር፣ በአመልካቶቹ ብዛት፣ በመገናኛ ብዙሃኑ የሽፋን መጠን፣ ስርጭት ቋንቋቸው እና በሌሎች ከምርጫ አፈጻጸምና ጸጥታ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች መሰረት አድርጎ ይወስናል፡፡

 

ምዕራፍ ሶስት

የመገናኛ ብዙሀንና የጋዜጠኞች መብቶች፣ ግዴታዎች እና ሃላፊነቶች

አንቀፅ 14 የምርጫ ሂደትን ለመዘገብ ፈቃድ የተሰጠው ጋዜጠኛ መብት ማናቸውም ምርጫን ለመከታተል ፈቃድ የተሰጣቸው የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኞች እንደአግባብነቱ የሚከተሉት መብቶች ይኖራቸዋል፣

 • ከጋዜጠኛው ያለቅድሚያ ማስታወቂያ መከታተል በሚፈልግበት ማንኛውም ምርጫ ጣቢያ እና ሂደት ምርጫን የመከታተልና የመዘገብ፤
 • ማንኛውም የምርጫ ሂደት ማለትም የመራጮች ምዝገባን፣ የእጩ ምዝገባን፣ የምርጫ ቅስቀሳን፣ የድምፅ አሰጣጥን፣ የቆጠራ ሂደትን እና የውጤት አገላለጽን የመከታተል እና የመዘገብ፤
 • ከመንግስት፣ ከቦርዱና ከሌላ ከማንኛውም ሰው ተፅእኖ ውጪ በገለልተኛነት ሥራውን የማከናወን፤
 • ከቦርዱና በየደረጃው ከሚገኙ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት መረጃና ትብብር የማግኘት፤
 • በድምፅ ሰጪነት የሚመዘገቡትን፣ ድምፅ ሰጪዎችን ወይም የምርጫ አስፈፃሚዎችን ሥራ የሚያውክ ወይም የሚያደናቅፍ እስካልሆነ ድረስ በምርጫ ጣቢያው ውስጥ የመዘዋወር፣
 • በድምፅ ሰጪነት ለሚመዘገቡ፣ ለድምፅ ሰጪዎች፣ ለዕጩዎች ወኪሎች ወይም ለታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ ቃለመጠይቅ የማድረግ

አንቀፅ 15) የምርጫ ሂደትን ለመዘገብ ፈቃድ የተሰጠው ጋዜጠኛ ግዴታዎች  ማንኛውም ምርጫን ለመከታተል የእውቅና ካርድ የተሰጠው የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኛ የሚከተሉትን ግዴታዎች ማክበር ይጠበቅበታል፤

 • የህዝብን ሰብአዊ መብትና መሠረታዊ ነፃነቶች ማክበር፣
 • የቦርዱን፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችን፣ የፀጥታና ደህንነት እንደዚሁም የሌሎች የመንግስት አካላትን ሚና እና ስልጣን ማክበር፣
 • ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስለ ኃላፊነታቸው ምክር ወይም መመሪያ አለመስጠት፣
 • መራጩ ድምፁን ለማን እንደሰጠ አለመጠየቅ፣
 • የህግ ጉዳዮችን በራስ አለመተርጐም እና የምርጫ ሂደትን የሚመለከት ህጋዊ ያልሆነ መረጃ ወይም መመሪያ አለማስተላለፍ፣
 • መራጭ በሚስጢር ድምፅ በሚሰጥበት ክፍል ወይም ለድምፅ መስጫ የተከለለ ቦታ ካሜራም ሆነ ሌላ የድምፅ ወይም የምስል መቅረጫ መሳሪያ አለመጠቀም፣
 • ከአድልዎና ከወገንተኝነት በፀዳ አኳኋን ተግባራትን ማከናወን፣
 • የሀገሪቱን እና የአካባቢውን ባህልና ልምድ ማክበር፣
 • በቦርዱ የተሰጠውን የመታወቂያ ካርድ በሚታይ መልኩ በመያዝ መንቀሳቀስ
 • የመራጭ ምዝገባ መረጃዎች በሰነድ ላይ ሲሰፍሩ ወይም መራጩ በድምፅ መስጫው ወረቀት ላይ የምርጫ ምልክት ሲያደርግ፣ በፊልም አለመቅረፅ ወይም ፎቶግራፍ አለማንሳት ፣
 • ግለሰቡ በግልፅ እየተቃወመው በምርጫ ጣቢያ ወይም ምርጫ ክልል ውስጥ ያሉ ምርጫ አስፈፃሚዎችን፣ ታዛቢዎችን እና የግል የእጩ ወኪሎችን ወይንም እጩዎችን ሳይጨምር መራጮችን እና ሌላ ማንኛውም ሰው ፎቶ ወይም በተንቀሳቃሽ ምስል አለመቅረፅ እና ቃለመጠይቅ አለማድረግ እና፣
 • የመራጮች ማንነትን ግላዊነት በሚነካ አኳኋን የመራጮችን መዝገብ፣ የመራጮችን ምዝገባ መታወቂያ ወይም ማንኛውንም ተመሳሳይ ሰነድ በፊልም አለመቅረጽ፣ ፎቶግራፍ አለማንሳት ወይም ኮፒ አለማድረግ ናቸው፡፡

አንቀፅ 16- የመገናኛ ብዙሀን በምርጫ ነክ ጉዳዮች ላይ ያለባቸው ግዴታዎች

 • የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሁሉም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውን ለመራጭ ህዝቡ ለማቅረብ፣ ፍትሃዊ እድል እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው
 • መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቧቸው ከምርጫ ጋር የተያያዙ ዜናዎች፣ ዘገባዎች፣ ሪፖርቶች እና ወቅታዊ ፕሮግራሞች ማንኛውንም ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከማጥላላት የተቆጠቡ ከሕትመቱ ወይም ከፕሮግራሙ አዘጋጆች የግል አቋም የፀዱ ወቅታዊ፣ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ መሆን አለባቸው፣
 • የመገናኛ ብዙሃን በምርጫ ወቅት በሚሰሩት ስራ ሴቶችን ወይም ወንዶችን በሚሰጣቸው የተሳሳተ ባህላዊ እምነት ላይ የተመሰረተ ሚናቸውን የሚጠቁም መሆን የለበትም፡፡
 • ማንኛውም ምርጫ ነክ ዘገባዎች ወይም ሪፖርቶች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው፡፡
 • የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች ከሚከተሉት አካላት የሚደርስባቸውን ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና ማስወገድ አለባቸው፣ ሀ/ የመገናኛ ብዙሀኑ ባለቤት፣ ለ/ ከመንግስት፣ ሐ/ ከማስታወቂያ ድርጅት፣

መ/  ገንዘብ ወይም ድጋፍ ከሚሰጠው ሰው ወይም ከደንበኛው ወይም፣ ሠ/   ከሌላ ማንኛውም ድርጅት ወይም ሰው፡፡

 • የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በምርጫ ወቅት ለሚዘጋጁ የውይይትና የክርክር ፕሮግራሞች እንደዚሁም ለሚካሄዱ ቃለ ምልልሶች ተገቢውን የዜና ሽፋን መስጠት አለባቸው።

አንቀፅ 17 የመገናኛ ብዙሀንና የጋዜጠኞች የምርጫ ሂደትን የመከታተል እና የመዘገብ ሃላፊነቶች

 • ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ምርጫውን ከሚያደናቅፍ ማንኛውም ተግባር እንደዚሁም በምርጫው ሂደት ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው።
 • ምርጫን የሚከታተሉ ጋዜጠኞች ወጪ የሚሸፈነው በራሳቸው ወይም በወከላቸው ተቋም ይሆናል። የቦርዱን ተሽከርካሪ ወይም ሌላ ሀብት የመጠቀም መብት የላቸውም።
 • ማንኛውም የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት የወከሏቸው ጋዜጠኞች ተግባራቸውን ከመጀመራቸው በፊት፡-

ሀ. ስለ ምርጫ ሂደቶች፣

ለ. በምርጫ ህጐች እና አሠራሮች

ሐ. በዚህ የስነ-ምግባር መመሪያ ድንጋጌዎች ላይ

የተሟላ ስልጠና እንዲያገኙ እና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ አለባቸው።

 • ማንኛውም ጋዜጠኛ የታዘበውን ጉዳይ ወይም ግድፈት በየደረጃው ለሚገኙ የምርጫ አስፈፃሚ አካላት በማቅረብ ማሳወቅ ይችላል።
 • ማንኛውም የእውቅና ካርድ የተሰጣቸው የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኞች ከፍተኛ የሙያ ስነምግባር ሊኖራቸው ይገባል።
 • የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት የወከሏቸው ጋዜጠኞች ይህንን የስነ-ምግባር መመሪያ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

አንቀፅ 18 የእውቅና ካርድ ስለመሠረዝ ወይም ስለማገድ

ቦርዱ አንድ የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኛ የምርጫ ሂደትን እንዲከታተል የተሰጠውን በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ እና በዚህ መመሪያ የተደነገጉትን ግዴታዎች ወይም ሀላፊነቶች ጥሶ ሲገኝ ቦርዱ እስኪያጣራ ድረስ የሰጠውን ፈቃድ ሊያግድ ወይም ጥሰቱን ሲያረጋግጥ ሊሰርዝ ይችላል፡፡

 • ቦርዱ ለመገናኛ ብዙሃን ወይም ለጋዜጠኛ የሰጠውን የእውቅና ካርድ ሲሰርዝ ወይም ሲያግድ ውሳኔውን የወሰደበትን ምክንያት በመጥቀስ ለሚመለከተው ጋዜጠኛ እና መገናኛ ብዙሃን በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት።
 • የመገናኛ ብዙሀኑ ወይም ጋዜጠኛው ምርጫን እንዲዘግብ የተሰጠውን የእውቅና ፈቃድ በቦርዱ ከተሰረዘ የተሰጠውን የመዘገብ መታወቂያ ካርድ ወዲያውኑ ለቦርዱ መመለስ አለበት።
 • ቦርዱ እንደ አስፈላጊነቱ የእውቅና ፍቃዳቸው የተሰረዘባቸውን መገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኞች ዝርዝር ለህዝብ እና ለምርጫ አስፈፃሚዎች ይፋ ማድረግ ይችላል፡፡

 

አንቀፅ 19 ስለምርጫ ነክ መልዕክቶችና የፓለቲካ ማስታወቂያ

 • ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ ለስርጭት የቀረበለትን የምርጫ ነክ መልዕክት ከስርጭቱ በፊትም ሆነ በኋላ ፓርቲውን ወይም የግል እጩ ተወዳዳሪውን ሳያማክር ምንም አይነት ማስተካከያ ማድረግ አይችልም፡፡
 • የመገናኛ ብዙሃኑ ከፓርቲው ቅድሚያ ፈቃድ አግኝቶ ያሰራጨውን የምርጫ ነክ መልእክት ፓርቲው ድጋሚ እንዳይተላልፍ ወይም ስርጭቱ እንዲቋረጥ የጠየቀው እንደሆነ በባለመልእክቱ ፓርቲ ጥያቄ መሰረት ወዲያውኑ ስርጭቱን ማቆም አለበት፡፡
 • ማንኛውም የፖለቲካ ማስታወቂያ በፕሮግራም ጣልቃ አይሠራጭም።
 • ማናቸውም የፓለቲካ ማስታወቂያ ይዘት ህጋዊነትና ትክክለኛ ስለመሆኑ ፓርቲው ወይም እጨው ማረጋገጡን የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡
 • ፍትሀዊ፣ ሚዛናዊ እና ከወገንተኝነትና ከአድልዎ የፀዳ ሁሉ አቀፍ የሆነ ትክክለኛ ሪፖርት ወይም ዘገባ ማቅረብ አለባቸው።
 • የፓርቲዎችን እና የእጩ ተወዳዳሪዎችን አመለካከት በተቻለ መጠን በራሳቸው ቃላት የተነገረውን በቀጥታ ሪፖርት ማድረግ ወይም መዘገብ አለባቸው።
 • የፖለቲካ ፓርቲን ወይም የእጩ ተወዳዳሪን መረጃ ሆን ብሎ ማዛባት፣ መደበቅ፣ እውነቱን ሀሰት ወይም ሀሰቱን እውነት አስመስሎ ማቅረብ የለባቸውም፡፡
 • የማንኛውንም ፓርቲ ወይም እጩ አርማ ወይም ሌላ መለያና መቀስቀሻ ምልክት አድርገው ስራቸውን ማከናወን የለባቸውም፡፡
 • የመገናኛ ብዙሀን ወይም ጋዜጠኞች በምርጫ ዘመቻ ወቅት በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል ስለተፈጠረ አከራካሪ ጉዳይ ሲዘግቡ በማስረጃ ተደግፈው አድልዎን በማስወገድ የሁሉንም ወገን አቋም ባካተተ መልክ በሚዛናዊነት የቀረቡ መሆን አለባቸው፡፡

 

አንቀፅ 20 በምርጫ ሂደቶች ላይ ትምህርት እና ገለፃ ስለማስተላለፍ መገናኛ ብዙሀን ቦርዱ በሚሰጠው መረጃ መሠረት ገለልተኛ በመሆን በሚከተሉት የምርጫ ሂደቶች ላይ ያተኮሩ ትክክለኛ የመራጮች ትምህርት ማስተላለፍ  ይችላሉ፣

 

ሀ. የመራጮች ምዝገባ መቼ እንደሚካሄድ፣

ለ. መቼ፣ የት እና እንዴት ድምፅ እንደሚሰጥ፣

ሐ. ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሚስጥር እንደሚካሄድ፣

መ. መራጩ ህዝብ ከምርጫ ተሣትፎው ጋር በተያያዘ ከማንኛውም ተፅእኖ የተጠበቀ መሆኑን፣

ሠ. የድምፅ መስጠትን አስፈላጊነት፣

ረ. ስለተለያዩ አካላት ሚና እና

ሰ. በምርጫ ህጉ በተካተቱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ።

አንቀፅ 21 አካታችነት

ማናቸውም ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሀን በሚያደርጓቸው የምርጫ ዘገባዎች፡-

 • በሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ሌሎች እኩል ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ላይ አድሏዊ የሆነ ወይም የጥላቻ እና የእምነት ማጣት አመለካከትን ለሚፈጥሩ ወይም ለሚያንፀባርቁ መረጃዎች ሽፋን መስጠት የለባቸውም።
 • ከላይ በንኡስ አንቀፅ (1) ላይ የተዘረዘሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ ወቅት ማሳተፍ የሚኖረውን ጠቀሜታ በማስተማርና የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ የዚህን ማህበረሰብ ክፍል የሚወክሉ እጩ ተወዳዳሪዎችን ማስተዋወቅ እና ማበረታታት አለባቸው።

አንቀፅ 22 ስለ ክፍያ

 • የቦርዱ ማንኛውም የምርጫ መረጃ፣ ትምህርት ወይም ማስታወቂያ እና ፕሮግራም በመገናኛ ብዙሀን ይተላለፋል። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መልእክቶቹን በነፃ የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ መልእክቱ የሚተላለፈው በግል የመገኛኛ ብዙሃን ከሆነ እንደየሁኔታው በነፃ ወይም በክፍያ ይተላለፋል፡፡ በነፃ የሚመደበውን የአየር ሰአት ወይም የጋዜጣ አምድ ቦርዱ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመመካከር ይወስናል፡፡
 • የመገናኛ ብዙሀኑ ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ ለተመሳሳይ ጊዜ ወይም የሽፋን አይነት የሚጠይቁት የማስታወቂያ ክፍያ መጠን እኩል መሆን አለበት።
 • ማናቸውም የመገናኛ ብዙሀን የፖለቲካ ማስታወቂያ ያለ ክፍያ ማስተናገድ አይችሉም።
 • ለፖለቲካ ማስታወቂያ የሚጠየቀው ክፍያ ለንግድ ክፍያ ከሚጠየቀው ክፍያ መብለጥ የለበትም።

አንቀፅ 23 የምርጫ ቅስቀሳን ማስተናገድ ወይም ማስተላለፍ የማይፈቀድበት ወቅት ማናቸውም የመገናኛ ብዙሀን እና ጋዜጠኛ ድምፅ የሚሰጥበት ቀን አራት ቀን ከቀረው በኋላ የእጩ ተወዳዳሪ ወይም የፖለቲካ ድርጅት የምርጫ ቅስቀሳን ማተም ወይም ማሰራጨት ወይም መዘገብ የለበትም።

አንቀፅ 24 ምርጫ ትንበያ እና ውጤት   ማናቸውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ የምርጫ ውጤት ትንበያ ማድረግ አይችልም፡፡ ነገር ግን በምርጫ ጣቢያ እንዲሁም በምርጫ ክልል ደረጃ ውጤቶች ይፋ ስለሆኑ ውጤቶች ዘገባ መስራት ይችላሉ፡፡

አንቀፅ 25 ስጦታ መቀበል የተከለከለ ስለመሆኑ

1) ማንኛውም ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙሀን

ሀ.    በጉቦ፣

ለ.    በስጦታ፣

ሐ.    በጥቅማጥቅም

መ. በማንኛውም ሁኔታ በመደለል የምርጫ ዘገባ ወይም ሪፖርት ማቅረብ የለበትም።

ሠ. ማንኛውም ጋዜጠኛ ወይም የመገናኛ ብዙሀን ትራንስፖርትም ሆነ ሌላ ምንም              አይነት መደለያ ከፓርቲዎች፣ ከፖለቲከኞች ወይም ከእጩዎች መቀበል              የለባቸውም።

አንቀፅ 26 ጥቅም ግጭትን ማስወገድ

ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ የምርጫ ዘገባ በሚሰራበት ወቅት የጥቅም ግጭትን ማስወገድ አለበት፡፡

አንቀፅ 27 ስለፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩ ተወዳዳሪዎች ኃላፊነት ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ፣

 • የመገናኛ ብዙሀን ነፃነት ማክበር አለበት
 • ጋዜጠኞችን ማዋከብ፣ ሙያዊ ተግባራቸውን ማደናቀፍ ወይም ማወክ የለበትም፡፡
 • የያዘውን የስራ ኃላፊነት ወይም ስልጣን ተጠቅመው ፍትሀዊ ያልሆነ የመገናኛ ብዙሀን ተጠቃሚ ከመሆን መቆጠብ አለበት።
 • ለመገናኛ ብዙሀንም ሆነ ለጋዜጠኛ ምንም አይነት ስጦታ፣ ጉቦ ወይም የተስፋ ቃል መስጠት የለበትም።
 • የሌላ ፓርቲን ወይም እጩን አስመልክቶ የተገለፀ አቋምን እና መረጃዎችን አዛብቶ ማቅረብ የለበትም።
 • መገናኛ ብዙሃን በምርጫው ሂደት ተገቢ ሚናቸውን እንዲጫወቱ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለበት፤
 • ወኪሎቹ ወይም ደጋፊዎቹ በጋዜጠኞች ላይ ጥቃት፣ ማስፈራራት፣ አደጋ፣ ጫና እና ድብደባ እንዳያደርሱ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አለበት።
 • በምርጫ ዘመቻ ወቅት መቻቻልና ነፃ ክርክር እንዲረጋገጥ ተገቢውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።

አንቀፅ 28 ስለ ምርጫ አስፈፃሚ አካል ኃላፊነት

 • ቦርዱ፦

ሀ. የመገናኛ ብዙሃን፣ የጋዜጠኞች፣ የፓርቲዎችን እና የእጩ ተወዳዳሪዎች የመናገር ነፃነት ማክበር እና በህግ መሠረት ስራዎቹን ለመገናኛ ብዙሀን ተደራሽ ማድረግ አለበት።

ለ.  መረጃ እና የእውቅና መታወቂያ በመስጠት ረገድ በመገናኛ ብዙሀን መካከል ልዩነት መፍጠር የለበትም።

 • ምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ስራው ሳይረበሽ ሊያስተናግዱ የሚችሉትን የጋዜጠኛ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ጣቢያው ውስጥ ሊገኙ የሚገቡ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር ወይም ጋዜጠኞች ቁጥር ሊወስኑ እና የመስተናገድ ተራ ሊያወጡ ይችላል፡፡
 • ቦርዱ አቅም በፈቀደው እና በህግ መሠረት ትብብር ማድረግ እና በየደረጃው የሚገኙ የምርጫ አስፈፃሚ አካላትም ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ ማድረግ አለበት።
 • የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚዎች ሃላፊ ከመረጃ ጋር ለተያያዙ አጠቃላይ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም በመረጃው ላይ ትንታኔና አስተያየት ማቅረብ ወይም መስጠት የለበትም፡፡
 • የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚች ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን እና ሌሎች ተመሳሳይ አጠቃላይ የመረጃ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ፣ቃለመጠይቅ ማድረግ ግን አይፈቀድላቸውም፡፡

ሀ. የመራጮችን ምዝገባ፣ የመራጮችን መዝገብ ለሕዝብ ክፍት ማድረግና የድምፅ አሰጣጡን ሥነ ሥርዓት፤

ለ.  በምርጫ ጣቢያው የተመዘገበውን እና ድምፅ የሰጠውን ሕዝብ ብዛት፤

ሐ.  የምርጫ አስፈፃሚዎችን ተግባራትና የተሰጣቸውን ሥልጠና እና

መ.  በሥራ ላይ ያሉ የሥነ ምግባር መመሪያዎችንና የአሠራር ደንቦችን  በተመለከተ ሊሆን ይችላል፡፡

 • የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ከዚህ በታች ያሉትን እና የመሳሰሉ ትንታኔዎችን ወይም አስተያየቶችን መስጠት አይኖርባቸውም፣

ሀ. የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት፤ በምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ክልል ወይም በክልል ደረጃ በታየው ውጤት ላይ ተመስርቶ መተንበይ፤

ለ. ድምፅ አሰጣጡ ስለሚያመላክተው አዝማሚያ ወይም ከድምፅ አሰጣጡ ስለሚጠበቀው ውጤት አስተያየት መስጠት፤

ሐ. ስለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ስለዕጩዎች ወይም ስለምርጫው የፖለቲካ ሃሳብ መሰንዘር፤

መ. በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ፣ ተገቢው ሥርዓት ስለመከበሩ አስተያየት መስጠትን፤ በሌሎች አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ግምታዊ አስተያየት መስጠት ወይም ማቅረብ እና

ሠ. አሉባልታዎችን በተመለከተ አስተያየት መስጠት የለባቸውም፡፡

 

 • የምርጫ ክልል ምርጫ አስፈጻሚዎች ወይም የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊዎች በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (4)፣ (5) እና (6) ስር የተመለከቱትን ግዴታዎች ማክበር አለባቸው::

 

ክፍል አምስት  ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

አንቀፅ 27 ስለ መመሪያ መጣስ  ማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ የዚህ መመሪያ ድንጋጌዎች ተላልፎ ሲገኝ ቦርዱ ከሚመለከተው አካል ጋር በትብብር በመስራት አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ሊያደርግ ይችላል፡፡

 

አንቀፅ 28 የተሻሩ መመሪያዎች

ይህንን መመሪያ የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ እና ልማዳዊ አሰራር በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

 

አንቀፅ 29 መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ ቦርዱ ካፀደቀበት ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል።

 

 

ብርቱካን ሚደቅሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰብሳቢ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.