Directives

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይት ጊዜ አመዳደብ እና የተናጋሪ  አመራረጥ የሚመራበትን አሠራር ለመወሰን  የወጣ መመሪያ ቁጥር 6/2000 ዓ.ም

 ምዕራፍ አንድ

 ጠቅላላ

 አንቀፅ 1

 አውጪው ባለስልጣን

የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 ዓ.ም. አንቀፅ 143 ንዑስ አንቀጽ 7 እና አንቀፅ 191 መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል።

 አንቀፅ 2

 አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ «የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይት ጊዜ አመዳደብ እና የተናጋሪ አመራረጥ መመሪያ ቁጥር 6/2000 ዓ.ም» ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል።

 አንቀፅ 3

 ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሠጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ፡- 1) «ኢ.ፌ.ዲ.ሪ.» ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው።

2) «ምክር ቤት» ማለት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡

3) «ደንብ» ማለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 ዓ.ም ነው።

4) «አፈ-ጉባኤ» ማለት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ነው።

5) «የቀድሞ አፈጉባኤ» ማለት የስራ ዘመኑን ከጀመረው ምክር ቤት በፊት በነበረው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ሰው ነው።

6) «ኮሚቴ» ማለት የምክር ቤቱን ተግባር ለማከናወን እንደሁኔታው በምክር ቤቱ የተቋቋመ የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ወይም አስተባባሪ ወይም ቋሚ ወይም ጊዚያዊ ኮሚቴ ነው።

7) «አማካሪ ኮሚቴ» ማለት በምክር ቤቱ ደንብ አንቀፅ 142 መሠረት የተደራጀው የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ነው።

8) «የፓርላማ ቡድን» ማለት አንድ ፓርቲ ወይም በምርጫ ክልሎች እርስ በርሳቸው ያልተወዳደሩ፣ በአንድ ፖለቲካ ፕሮግራም የተወዳደሩ ፓርቲዎች አባላት ስብስብ ሆኖ

ከ10 የማያንስ መቀመጫ ያለውን ወይም ያላቸውን ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የያዘ ነው።

9) «የመንግሥት አጀንዳ» ማለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ለምክር ቤት የሚቀርብ ማንኛውም አጀንዳ ነው፡፡

10) «አባል» ማለት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነው፡፡

11)«ሰው» ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሠጠው አካል ነው።

 አንቀፅ 4

 አላማ

የአባላትን እና የፓርላማ ቡድኖችን ንቁ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ፍትሃዊ የውይይት ጊዜ የሚመድብበት እና ተናጋሪዎች የሚመረጡበት ግልፅ አሠራር በመዘርጋት ምክር ቤቱ የተጣለበትን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ማስቻል ነው፡፡

 ምዕራፍ ሁለት

 ለምክር ቤቱ አጀንዳ ስለሚመደብ የውይይት ጊዜ

 አንቀጽ 5

 የውይይት ጊዜ አመዳደብ

 1. በደንቡ አንቀፅ 34 ንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት ለእያንዳንዱ አጀንዳ የሚያስፈልግ የውይይት ጊዜ የሚመደበው በምክር ቤቱ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ስምምነት ይሆናል።
 2. ከላይ በንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ስምምነት ያልተደረሰበት የጊዜ አመዳደብ ሀ. በአፈ-ጉባኤ አማካኝነት ሁሉም አማራጮች ለምክር ቤቱ ይቀርባሉ፡፡

ለ. በጉዳዩ ላይ ልዩነት ያላቸው አካላት ሀሳባቸውን በአጭሩ እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ይወሰናል።

 1. አፈ-ጉባኤው፤ በም/ቤቱ የተወሰነውን የውይይት ጊዜ በአንቀፅ 13 መሠረት ተፈፃሚ ያደርጋል።

 አንቀፅ 6

 የውይይት ጊዜ መነሻ ሃሳብ ስለማቅረብ

 

 1. ማንኛውም ረቂቅ አጀንዳ አቅራቢ ለአጀንዳው የሚያስፈልገውን የመወያያ ጊዜ ለአማካሪ

ኮሚቴው በመነሻነት ማቅረብ አለበት፡፡

 1. ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1 መሠረት በቀረበ የመወያያ ጊዜ ላይ አጭር አስተያየት እንዲሠጥ ይደረጋል፡፡ አፈጉባኤው፤ በጉዳዩ ላይ በቂ ውይይት ተደርጓል ብሎ ሲያምን የአባላትን ስምምነት ይጠይቃል፡፡ መግባባት የተደረሠበትን ሃሳብ መሠረት በማድረግም የንግግር ጊዜ ይመድባል።
 2. የኮሚቴው አባላት ከስምምነት ካልደረሱ ጉዳዩ በዚህ መመሪያ አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት ይወሰናል።

አንቀፅ 7

 በጊዜ አመዳደብ ከግምት ውስጥ መግባት

 የሚገባቸው ጉዳዮች

 

 1. ለማንኛውም የህግ ረቂቅ ለእያንዳንዱ  ንባብ  ደረጃ  የሚያስፈልገው የውይይት ጊዜ እንደየአስፈላጊነቱ ይመደባል።
 2. በማንኛውም አካል ወደ  ምክር  ቤቱ  የሚቀርብ  ሪፖርት  ወይም  የውሳኔ   ሀሳብ እንዳስፈላጊነቱ የማቅረቢያና የውይይት ጊዜ ይመደባል።
 3. የ ፕ ሬ ዚ ዳ ን ቱ አ መ ታ ዊ የ መ ክ ፈ ቻ ን ግ ግ ር እ ን ዲ ሁ ም የ ጠ ቅ ላ ይ ሚኒስትሩ ሪፖርት የጊዜ ገደብ  አይደረግበትም።  ሆኖም  በቀረበው ጉዳይ ላይ ለሚደረገው ውይይት አስፈላጊው ጊዜ ይመደባል።
 4. በፌደራል መንግስት በሚቀርብ አመታዊ  ረቂቅ  በጀት  ላይ  ለሚደረግ አጠቃላይና ዝርዝር ውይይት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት አፀዳደቅ ሂደትን ለመወሰን በወጣው መመሪያ መሠረት በቂ ጊዜ ይመደብለታል።
 5. ወደ ምክር ቤቱ የሚቀርብ ሌላ ማንኛውም ጉዳይ እንደሁኔታው አስፈላጊው ጊዜ ይመደብለታል።

 

 አንቀፅ 8

 ለቃል መልስ ስለሚመደብ የውይይት ጊዜ

 

 1. አፈ-ጉባኤው በሌላ ሁኔታ ካልወሰነ በስተቀር ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትሮች በቃል መልስ የሚሰጡበት በየሳምንቱ ሀሙስ የአንድ ሰዓት የጥያቄ ጊዜ (Question hour) ይኖረዋል።
 2. የዚህ አንቀፅ ዝርዝር አፈፃፀም ስለ ጥያቄ አቀራረብ በወጣው መመሪያ ቁጥር 2/2000 መሠረት ይመራል።

አንቀፅ 9

 ለበጀት ውይይት ስለሚመደብ ጊዜ

 1. አፈጉባኤው፤ በረቂቅ በጀት ላይ ለሚደረግ አጠቃላይ እና ዝርዝር ውይይት የሚያስፈልገውን ጊዜ ከምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ ጋር በመመካከር ይመደባል።
 2. ከላይ በንዑስ 2 መሠረት በረቂቅ በጀቱ ላይ ለሚደረግ ውይይት የሚመደበው ጊዜ ከሁለት ቀን ማነስ የለበትም፡፡
 3. የዚህ አንቀፅ ዝርዝር አፈፃፀም በም/ቤቱ የበጀት አፀዳደቅ ሂደትን ለመወሰን በወጣው መመሪያ መሠረት ይመራል።

 አንቀፅ 10

 ለተቃዋሚዎች ቀን ስለሚመደብ

 የውይይት ጊዜ

ምክር ቤቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት አጀንዳ ላይ በየወሩ ለአንድ ሰዓት ውይይት ያደርጋል፡፡ ዝርዝር አፈፃፀሙ የአማካሪ ኮሚቴ የተቃዋሚዎች ቀንን አስመልክቶ በአወጣው መመሪያ መሠረት የሚመራ ይሆናል።

 አንቀፅ 11

 ለምክር ቤቱ የመክፈቻ ስነስርዓት ስለሚመደብ

 የውይይት ጊዜ

 

በደንቡ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀፅ 2 ለተዘረዘሩት በምክር ቤቱ የመክፈቻ ስነስርዓት ለሚከናወኑ ጉዳዮች የሚያስፈልግ የውይይት ጊዜ የሚመደበው በቀድሞው አፈጉባኤ ነው።

 አንቀፅ 12

 ለሌሎች ጉዳዮች ስለሚመደብ የውይይት ጊዜ

አፈ-ጉባኤው፦

 1. በደንቡ አንቀፅ 11/1/ ስር በተደነገገው በፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ላይ ለሚደረገው ውይይት የሚያስፈልገው ጊዜ ከመንግስት ተጠሪ ጋር በመመካከር ይመድባል፡፡
 2. በእለታዊ አጀንዳ ያልተቀረፀ ጉዳይ እንዲታይ ሞሽን ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ጊዜ ይመድባል።
 3. ም/ቤቱ በውይይት ላይ እያለ ለሚቀርቡ የተለያዩ ሞሽኖችና የማሻሻያ ሞሽኖች የሚያስፈልገው የውይይት ጊዜ በአፈጉባኤው ይወሰናል።
 4. የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የውይይት ጊዜ አመዳደብ በሚከተለው አኳኋን ይፈፀማል፡፡

ሀ.   አፈ-ጉባኤው ለጉዳዩ የሚያስፈልገውን የጊዜ መጠን አስመልክቶ መነሻ ሀሳብ ያዘጋጃል፤

ለ.   አፈ-ጉባኤው፤ ባዘጋጀው የመነሻ ሀሳብ ዙሪያ ከመንግስት ዋና ተጠሪ ጋር ይመካከራል፤ ከስምምነት የደረሱበት የውይይት ጊዜም ለአባላት ይገለፃል፡፡

ሐ.   ከላይ በ “ለ” መሠረት ከስምምነት መድረስ ካልቻለ፤ አፈ-ጉባኤው የሚወስነው የውይይት ጊዜ ለአባላት ይገለፃል፡፡

 ምዕራፍ ሶስት

 ስለምክር ቤቱ የንግግር ጊዜ

 እና የተናጋሪ አመራረጥ

 አንቀፅ 13

 የንግግር ጊዜ አመዳደብ

 1. አፈጉባኤው፤ ለምክር ቤቱ አጀንዳ የተወሰነውን የውይይት ጊዜ መሠረት በማድረግ የንግግር ጊዜ ይመድባል።
 2. የፓርላማ ቡድኖች፤ በምክር ቤት ውስጥ ያላቸውን መቀመጫ መሰረት በማድረግ ለሚያቀርቡት ሃሳብ ለአጀንዳው ከተያዘው ጠቅላላ ጊዜ ውስጥ ይመደብላቸዋል፤
 3. አባላት ሃሳባቸውን ለመግለፅ እንዲችሉ ለአጀንዳው ከተመደበው ጠቅላላ ጊዜ ውስጥ እንደአስፈላጊነቱ የንግግር ጊዜ ይመደብላቸዋል፤
 4. አፈጉባኤው፤ ከላይ በንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት የተመደበን የንግግር ጊዜ በምክር ቤቱ ጽ/ቤት በኩል የፓርላማ ቡድኖች እንዲያውቁት እና የተናጋሪ አባላትን ስም ዝርዝር እንዲልኩ /እንዲያቀርቡ/ ያደርጋል።
 5. በአንቀፅ 13(2) መሠረት ለፓርቲ የተመደበው የጊዜ አጠቃቀም በፓርቲው /በፓርላማ ቡድኑ/ ይወሰናል።
 6. በቀረበ አጀንዳ ዙሪያ በሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የሚመለከተው አካል መልስ ወይም አስተያየት ለመስጠት የሚያስፈልገው ጊዜ ለጉዳዩ ከተመደበው አጠቃላይ ጊዜ ውስጥ የሚመደብ ይሆናል።
 7. አፈጉባኤው፤ የሚሰጣቸው ገለፃዎች እንዲሁም በማንኛውም አካል ወይም ግለሰብ ለምክር ቤቱ እንዲሰጥ የተፈለገ ማብራሪያ ወይም ምስክርነት የንግግር የጊዜ ገደብ አይደረግበትም።
 8. አፈጉባኤው ለጥያቄ በተመደበው ጊዜ ውስጥ በሚኒስትሮች የተሰጠን መልስ መነሻ በማድረግ ተጨማሪ የማብራሪያ ጥያቄ በአቅራቢው ወይም በሌላ አባል እንዲቀርብ ሊያደርግ ይችላል።

አንቀጽ 14

 ስለተናጋሪ አመራረጥ /እድል አሰጣጥ/

 1. አፈጉባኤው ማንኛውንም ስብሰባ በሚመራበት ወቅት ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ የሆነ መርህን መከተል ይገባዋል።
 2. አፈጉባኤው፦

ሀ. ለመጀመሪያ  ንባብ  በቀረበ  ረቂቅ  ህግ  ላይ  ውይይት  ከመደረጉ  በፊት ረቂቁን ባመነጨው አካል አጭር ማብራሪያ እንዲሰጥ ያደርጋል።

ለ. ለምክር ቤቱ በቀረበ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት ከማድረጉ  በፊት የሚመለከተው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በቅድሚያ እንዲያቀርብ ያደርጋል።

ሐ. ምክር ቤቱ በቀረበለት የመንግስት ሪፖርት ወይም ሌላ አጀንዳ ላይ ከመወያየቱ በፊት የሚመለከተው ኃላፊ አስፈላጊውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ያደርጋል።

 1. አፈጉባኤው፤ የፓርቲ ወይም የፓርላማ ቡድን መሪዎች ወይም ተጠሪዎች ወይም ተወካዮች ፓርቲያቸውን በመወከል ሀሳብ እንዲያቀርቡ ቅድሚያ እድል ይሰጣቸዋል። በመቀጠል ሌሎች በፓርላማ ቡድን ስማቸው የተላለፈ የምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ እንዲያቀርቡ እድል ሊሰጣቸው ይችላል።
 2. በመጨረሻም ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንዲቀርቡ በአንቀፅ 13(3) መሰረት አፈጉባኤው እድል ይሰጣል።
 3. አፈጉባኤው በምክር ቤቱ ስብሰባ ሂደት የስነስርዓት ጥያቄ ለሚያነሳ አባል የቅድሚያ እድል መስጠት ይጠበቅበታል።

ንቀፅ 15

 የባከነ ጊዜን ስለማካካስ

 

 1. አፈጉባኤው ለእያንዳንዱ ንግግር የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ማለቁን ሲያውቅ ንግግሩን ማስቆም ይጠበቅበታል።
 2. ማንኛውም አባል ሀሳቡን በሚገልጽበት ጊዜ በደንቡ አንቀፅ 29 እና ሌሎች ድንጋጌዎች የተመለከቱትን ሥነ-ምግባሮችና ሥነ-ሥርዓቶች ካልተላለፈ በስተቀር አፈጉባኤው ጣልቃ በመግባት ማቋረጥ የለበትም።
 3. ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በስነ-ስርዓት ጥያቄ ወይም የእራሱ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ንግግሩ የተቋረጠበት አባል የተጓደለበት (የባከነበት) ጊዜ በአፈጉባኤው ይካካስለታል፡፡

አንቀጽ 16

 የንግግር እድል በድጋሚ ማግኘት

 የሚቻልበት ሁኔታ

 1. አንድ አባል በአንድ ጉዳይ ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ የመናገር እድል አይኖረውም። ሆኖም አፈጉባኤው አስፈላጊ መስሎ ከታየው ተጨማሪ የንግግር ጊዜ ሊሰጥ ይችላል።
 2. አፈጉባኤው፤ አንድ ተናጋሪ አዲስ ሀሳብ ሳይጨምር ቀደም ብሎ በተናገረው ጉዳይ ሀሳቡን ለማስተካከል ወይም በሀሳቡ ዙሪያ የእርምት አስተያየት ለማቅረብ ሲፈልግ ድጋሚ የንግግር እድል ሊሰጠው ይችላል።
 3. አፈጉባኤው፤ በራሱ አስተያየት የተለየ የመናገር እድል ወይም ተጨማሪ የንግግር ጊዜ ለአባላት መስጠት ሲፈልግ የሁሉንም ወገኖች ተሳትፎን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት።

ንቀፅ 17

 የተናጋሪ ዝርዝር ቀድሞ ስለማስተላለፍ

 

 1. ፓርቲውን ወይም የፓርላማ ቡድኑን በመወከል ሀሳቡን ለመግለፅ የፈለገ ማንኛውም አባል በፓርቲው ወይም በፓርላማ ቡድኑ ተጠሪ ወይም ወኪል በኩል ስሙ ለአፈጉባኤው መተላለፍ አለበት።
 2. ማንኛውም በግሉ ሃሳብ ማቅረብ የሚፈልግ አባል ስሙን ለአፈጉባኤው ቀድሞ ማስተላለፍ አለበት።
 3. በዚሁ አንቀፅ መሠረት የሚተላለፍ የስም ዝርዝር የምክር ቤቱ ስብሰባ ከመጀመሩ ከ30 ደቂቃ በፊት ለአፈጉባኤው መቅረብ አለበት።
 4. በምክር ቤቱ ስብሰባ ወቅት ሃሳብ መስጠት የሚፈልግ ወይም የስነስርዓት ጥያቄ ያለው ማንኛውም አባል ለአፈጉባኤው በሚታይ መልኩ እጁን በማውጣት የንግግር እድል ማግኘት ይችላል።

 ምዕራፍ አራት

 ልዩ ልዩ ድንጋጌ

 አንቀፅ 18

 የሌሎች መመሪያዎች ተፈፃሚነት

ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ እና አሠራር በዚህ መመሪያ ውስጥ በተሸፈኑ (በተመለከቱ) ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።

አንቀፅ 19

 መመሪያው የሚፀናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ  በምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ  ኮሚቴ ከፀደቀበት ከመጋቢት 13 ቀን/2000 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል።

 

 

ተሾመ ቶጋ /አምባሳደር/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አፈ-ጉባኤ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.