Directives

የፌዴራል የመንግስት መ/ቤቶች የህፃናት ማቆያ ማዕከል የአሰራር መመሪያ ቁጥር 47/2013

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 36(1)(ሐ) መሰረት ህፃናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን እንክብካቤ በተለይም የእናት ጡት ወተት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ ወላድ ሴት መንግስት ልጆቻቸውን በሚሰሩበት አካባቢ የሚያቆዩበትና ጡት የሚያጠቡበት ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣

ሴት የመንግስት ሰራተኞች በመውለዳቸው ምክንያት በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ ይፈጠርባቸው የነበረውን እንቅፋቶች በማስወገድ ያለምንም ስጋትና ሃሳብ ሙሉ ኃይላቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ፣

ሴት የመንግስት ሰራተኞች ትውልድን የመተካት ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ህጻን ልጃቸውን ለመንከባከብ በሚል ስራ የሚያቋርጡበት አጋጣሚዎች እየጨመረ በመምጣቱ በመንግስት መ/ቤቶች ህጻናት ልጆቻቸውን ማቆየት የሚችሉበትን ቦታ በማመቻቸት የስራ ዋስትናቸውን እንዳያጡ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ተሻሽሎ በወጣው የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 48(6) በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡

 ክፍል አንድ

 ጠቅላላ ድንጋጌዎች

1. አጭር ርእስ

ይህ መመሪያ “የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች የህፃናት ማቆያ የአሰራር መመሪያ ቁጥር 47/2013” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2. ትርጓሜ

በሌሎች ህጎ የተለየ ትርጓሜ የተሰጣቸው ቢሆንም ለዚህ መመሪያ አፈጻጸም ሲባል፣ (1) “ህጻን” ማለት የእናቱን ጡት የሚጠባና ከሦስት አመት በታች ያለ ሆኖ

የእናቱን የቅርብ ክትትል የሚፈልግ ልጅ ነው፡፡

(2) “የህጻናት ማቆያ” ማለት በፌዴራል መንግስት ሰራተኞ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀጽ 48(2) መሰረት በእያንዳንዱ የፌዴራል መንግስት መ/ቤት ውስጥ እንዲቋቋም የተደረገው የህጻናት ማቆያ ነው፡፡

(3) “ጨቅላ ህጻናት” ማለት እናቱ የወሊድ ፈቃድዋን ከምታጠናቅቅበት ከአራት ወር ጀምሮ እስከ 12 ወር እድሜ ያለው ህጻን ነው፡፡

(4) “የሚውተረተር ህጻን” ማለት ነገሮችን የማውቅ ፣ ስሜታዊና ማህበራዊ ሁኔታው ከፍተኛ እድገት የሚያሳይበበት ከ12 ወር እስከ 36 ወር እድሜ ያለው ህጻን ነው፡፡

(5) “የመንግስት መ/ቤት” ማለት በፌዴራል መንግስት ሰራተኞች በአዋጅ ቁጥር 1064/2010 መሰረት ሰራተኞቹን የሚያስተዳደርና ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር የፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡

3. የመመሪያው የአፈጻጸም ወሰን ይህ መመሪያ፣

(1) በፌዴራል መንግስት መ/ቤት ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው በሚሰሩ ሴት የመንግስት ሰራተኞች እና ከሦስት አመት በታች ባሉ ህጻናት ልጆቻቸው፣

(2) በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተቋቋሙ የህጻናት ማቆያዎችና የህጻናት ማቆያው ውስጥ ተመድበው በሚሰሩ ሰራተኞች፣ እና

(3) ለስብሰባና ለተለያዩ የመንግስትን ስራ ለማስፈጸም ከሶስት አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ይዘው ወደ መንግስት መ/ቤቱ የመጡ የክልል ሴት የመንግስት ሰራተኞች፣

ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

4. የመመሪያው አላማ

(1) ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከህፃን ልጆቻቸው ርቀው በሚሰሩበት ተቋም ውስጥ ሙሉ ትኩረታቸውንና አቅማቸውን በተሰማሩበትና በተመደቡበት የስራ መስክ ላይ አለማድረጋቸውና ከህፃን ልጆቻቸው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ከስራ ገበታቸው መቅረታቸው በራሳቸው ዕድገት፣ አቅም፣ ቅልጥፍና፣ ብቃትና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲሁም የራሳቸውን የኢኮኖሚ አቅም ከማሳደግና ራስን የመቻል እንቅስቃሴያቸው ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ፣

(2) ህጻናት እናቶቻቸው በስራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት ማግኘት የሚገባቸውን እንክብካቤ አለማግኘታቸው፣ በአመጋገባቸው፣ በጤንነታቸው፣ በደህንነታቸው፣ በአስተሳሰባቸው፣ በቅልጥፍናቸው፣ በፈጠራ ክህሎታቸው፣ በአካላዊና አዕምሯዊ ዕድገታቸውና ብስለታቸው፣ በትምህርት የመቀበል አቅማቸው፣ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅና የማዳመጥ ክህሎታቸውና የማገናዘብ ብቃታቸው ላይ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ፣

(3) የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች የህፃናት ማቆያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል በማቋቋም በተለይ በሴት ሰራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቀነስ፣ የሴቶችን ውጤታማነት ለማሳደግና ለህፃናት በቂ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያገኙ ማስቻል ነው፡፡

 ክፍል ሁለት

 የህጻናት ማቆያው አደረጃጀት

5. ህጻናት ማቆያን ስለማቋቋም

(1) ማንኛውም የመንግስት መ/ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ከሦስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩበትና ጡት የሚያጠቡበት የህጻናት ማቆያ የማቋቋም ሃላፊነት አለበት፡፡

(2) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ግቢ  ውስጥ ወይም በአንድ ህንጻ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ የሚገኙ የመንግስት መ/ቤቶች ተቀናጅተው አንድ የህጻናት ማቆያ ማእከል ማቋቋም ይችላሉ፡፡

(3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀት (2) መሰረት )የህጻናት ማቆያን በጋራ የሚያቋቀሙ የመንግስት መ/ቤቶች በጀት ፤የሰው ኃይልና እና ሌሎች ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በጋራ ይወሰናሉ፡፡

(4) የህጻናት ማቆያው ለማቋቋም የሚመረጠው ቦታ በህፃናቱ ጤናና አካል ላይ ጉዳት ሊያደርስ የማይችል፣ ከኬሚካሎች፣ ከብናኝ፣ ከጨረርና ከሽታ የፀዳ፣ የድምፅ ብክለት የሌለበት፣ ከመኪና መንገድ፣ ድምፅ ካላቸውና የማምረቻ ቦታዎች የራቀ፣ በቂ የፀሐይ ብርሃንና በቂ አየር ያለበት ቦታ መሆን አለበት፡፡

6. የሚቋቋመወው የህጻናት ማቆያ ውስጣዊ ይዘት

የህጻናት ማቆያው የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የመጫወቻ፣የመኝታና የማረፊያ ክፍል፣የምግብ ማዘጋጃና መመገቢያ ክፍል፣ የልብስና የመፀዳጃ ዕቃዎች ማስቀመጫና መቀየሪያ ክፍልን ያካተተ ሊሆን ይገባል፡፡

7. የመጫወቻ ክፍል

(1) የመጫወቻ ክፍል ህፃናቱ ጊዜያቸውን በጨዋታ የሚያሳልፉበት ክፍል በመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀና በህፃናት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች የፀዳ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም የመጫወቻ ክፍል በማንኛውም ሰዓት ተንከባካቢዎች በነፃነት ክትትል ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥርላቸው፣ አቀማመጡም ለህፃናት ነፃነት፣ ደህንነትና ምቾት ሊሰጣቸው የሚችል ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡

(2) የመጫወጫ ክፍሉ ለህፃናቱ በቂ የመዘዋወሪያ ቦታ እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀና አቀማመጡም በቂ የተፈጥሮ ብርሃን የሚያስገባና በጥላ የተጋረደ እንዲሁም ቀጥታ የፀሐይ ጨረር የማያስገባ መሆን አለበት፡፡

(3) የመጫወጫ ክፍሉ ሙቀት የተመጣጠነ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሰው ሰራሽ የሙቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያ መጠቀም ይቻላል፡፡ እንዲሁም ንፁህ አየር ሊዘዋወርበት የሚችልና የተፋፈነ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኝም የመጫወቻ ክፍሉ ወለል ለስላሳና በግጭት ወቅት ጉዳት ሊያስከትል የማይችል ሊሆን ይገባል፡፡

(4) አዋቂዎች ወደ ህፃናት መጫወቻ ክፍል ከመግባታቸው በፊት ንፅህናቸውን ስለመጠበቃቸውና ህፃናቱን ለበሽታ ከሚዳርጉ ነገሮች ስለመፅዳታቸው ማስጠንቀቂያና ጥቆማ የሚሰጥ ምልክት ከክፍሎቹ በተወሰነ ሜትር ርቀት ላይ በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡

(5)  ለጨቅላ ህፃናት (Infant Stage) የሚዘጋጁ የመጫወቻ ክፍል

(ሀ) በጨቅላ የዕድሜ ለሚገኙ ህፃናት የሚዘጋጁ የመጫወቻ ክፍሎች ደህንነታቸውና ምቾታቸው የተጠበቀ ሆነው መዘጋጀትና ክፍሎቹም ሞቃትና ለህፃናቱ ዕይታን የሚስቡ ሆነው መዘጋጀት አለባቸው፡፡

(ለ) አሻንጉሊቶችና ልዩ ልዩ የመጫወቻ ቁሳቁሶች ለህፃናቱ ግልፅና ምቹ የሆነ ክፍት ቦታ ላይ እንዲቀመጡ መደረግ አለበት፡፡

(ሐ) የክፍሉ ግድግዳዎች የሀገርን ባህላዊ እሴቶች የሚያሳዩ ሆነው ሊዘጋጁ ይገባቸዋል፡፡

(መ) ህፃናቱ በመዳህ ተነስተው ለመቆም በሚያደርጓቸው ጥረቶች በአካባቢያቸው ያሉትን ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎችና ሼልፎችን በመደገፍ በመሆኑ ህጻናቱ በሚደገፉበት ወቅት በመንሸራተት እንዳይከዷቸው ወይም አጋዥ እንዲሆኗቸው ለማድረግ በመጫወቻ ክፍሉ ውስጥ የሚዘጋጁ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎችና ሼልፎች የማይንቀሳቀሱና ከወለሉ ወይም ከግድግዳው ጋር የተያያዙ መሆን አለባቸው፡፡

(ሠ) አንድ የመጫወቻ ክፍል ከ10 ያልበለጡ ጨቅላ ህፃናትን ለማስተናገድ እንዲቻል እና ለአንድ ህፃን ነፃ የመጫወቻና የመንቀሳቀሻ ቦታ 2.8 ሜ2 ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት አለበት፡፡

 (6) ለሚውተረተሩ ህፃናት (Toddler Stage) የሚዘጋጁ የመጫወቻ ክፍል

ለእነዚህ ህፃናት የሚዘጋጁ የመጫወቻ ክፍሎች ለህፃናቱ ነፃነትን የሚሰጡና የሚያበረቷቷቸው ሆነው ከዚህ በታች የተመለከቱትን መስፈርቶች አሟልተው መዘጋጀት አለባቸው፡፡

(ሀ) ህጻናት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጡንቻዎቻቸው እንዲጠነክሩና እንዲበረቱ እገዛ የሚያደርጉ፣

(ለ) ለህፃናቱ የሚቀርቡት የመጫወቻ ቁሳቁሶችና አሻንጉሊቶች የህፃናቱን ዕውቀትና የአዕምሮ ደረጃ ሊያዳብሩ የሚችሉ ሆነው በቀላሉ ሊያገኟቸው በሚችሉባቸው ቅርብና ግልፅ በሆኑ ቦታዎች መቀጥ አለባቸው፡፡

(ሐ) ህፃናቱ የሚፈልጓቸውን ቦታዎችና እቃዎች ለመነካካትና ለመለማመድ፣ እንዲሁም አካባቢያቸውን ለማወቅ የሚጠመዱበትና ዕረፍት አልባ የሚሆኑበት የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን ለመጫወቻ የሚዘጋጅላቸው ቦታ ሰፊና ገላጣ መሆን አለበት፡፡

(መ) የክፍሉ ግድግዳዎች በመማሪያ ፊደላት በእንስሳትና በተክል ስዕሎች የተሞላና የህፃናቱን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ፣ የማወቅና የመማር ፍላጎታቸውን የሚያነሳሱና ዕውቀት የሚያስጨብጣቸው መሆን አለባቸው፡፡

(ሠ) ህጻናቱ ባሉበት የእድሜ ደረጃ ማህበራዊ መስተጋብርን እንዲለማመዱና ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ለማድረግ በክፍሉ ውስጥ በቡድን ሆነው እንዲጫወቱ የሚችሉበትን ሁኔታዎች መቻቸት አለባቸው፡፡

(ረ) አንድ የመጫወቻ ክፍል ከ15 ያልበለጡ የሚውተረተሩ ህፃናትን ለማስተናገድ እንዲቻል እና ለአንድ ህፃን ነፃ የመጫወቻና የመንቀሳቀሻ ቦታ 2.8 ሜ2 ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት አለበት፡፡

 (ሰ) የመቻወቻ ክፍል የመማሪያና የመጫወቻ ቁሳቁስ፣ ቴሌቪዥን፣ አሻንጉሊት፣ የህፃናት ወንበርና ጠረጴዛ፣ የፊደል ገበታ፣ ለህፃናት የተዘጋጁ ባህላዊ ስዕሎችና ቅርፃ ቅርፆች እንዲሁም ሌሎች ለህፃናት የሚሆኑ የመጫወቻ ቁሳቁሶች መያዝ ይኖርበታል፡፡

(7) በዚህ አንቀጽ (6) የተመለከተው ቢኖርም ከመጫወቻ ክፍል ውጭ መጫወት የሚገባቸው ህጻናት ካጋጠሙ በመንግስት መስሪያ ቤቱ አጥር ግቢ ውስጥ የመጫወቻ ቦታ ሊዘጋጅላችው ይገባል፡፡

8. የመኝታ ክፍል

(1) የመኝታ ክፍል ከህፃናቱ የመጫወቻ ክፍል ጋር ተጎራባች ሆኖ በመጫወቻ ክፍሉ ውስጥ በሚፈጠረው የህፃናት ጩኸት እንዳይረበሽ ድምፅ በማያሳልፍ ቁስ (ማቴሪያል) የተሰራና በከፊል በመስታወት የተከለለ መሆን አለበት፡፡

(2) የመኝታ ክፍሉ ለተንከባካቢዎች ዕይታ አመቺ ሆኖ በተመሳሳይ ጊዜ የመኝታና የመጫወቻ ክፍሎቹን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡

(3) የመኝታ ክፍል በቂ የተፈጥሮ ብርሃን የሚያስገባና በጥላ የተጋረደና ቀጥታ የፀሐይ ጨረር የማያስገባ መሆን አለበት፡፡

(4) የመኝታ ክፍል የሙቀት መጠን የተመጣጠነ ፣ ንፁህ አየር ሊዘዋወርበት የሚችልና የተፋፈነ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ሆኖ ከ10 ያልበለጡ ጨቅላ ህፃናትን የሚይዝ ሆኖ መዘጋጀት አለበት፡፡

(5) አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሰው ሰራሽ የሙቀት መቆጣጠሪያ መጠቀም ይቻላል፡፡

(6) የመኝታ ክፍል በህጻናቱ ቁጥር ልክ የህፃናት አልጋና ፍራሽ፣ የተለያዩ ተንጠልጣይ ቅርፃ ቅርፆች፣ የሙቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ (Heater & Air conditioner) አካቶ መያዝ አለበት፡፡

(7) የህፃናቱ አልጋ ስፋት ከ75 ሳ.ሜ በ 135 ሳ.ሜ ያልበለጠ፣ የተንከባካቢዎች የመተላለፊያ ቦታ ከ90 ሳ.ሜ ያላነሰ እና በአልጋዎቹ መካከል የሚኖረው ስፋት ከ45 ሳ.ሜ ያላነሰ መሆን አለበት፡፡

9. የንፅህና መጠበቂያ ክፍል

(1) ይህ ክፍል ለህፃናቱ መፀዳጃና መታጠቢያ የሚያገለግል ሆኖ፣ ህጻናቱ ከተፀዳዱ በኋላ ልብሳቸውን የሚቀይሩበትና የመፀዳጃ ቁሳቁሶችና አልባሳቶቻቸው የሚቀመጡበት ክፍል ነው፡፡ ክፍሉ በቂ አየር የሚዘዋወርበት ሆኖ ከቀጥታ የፀሐይ ጨረርና ንፋስ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡

(2) የንጽህና መጠበቂያ ክፍል የዕቃ መደርደሪያ ሳጥን፣ የልብስ መቀየሪያ ጠረጴዛ፣ የህፃናት ማጠቢያ ገንዳ፣ የኤሌክትሪክ ውሃ ማሞቂያ፣ የህፃናት መፀዳጃ ፖፖ፣ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ ሳጥን፣ የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ዳይፐር፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት እና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን መያዘ አለበት፡፡

10. የምግብ ማዘጋጃና መመገቢያ ክፍል

(1) ይህ ክፍል ጡት የሚጠቡ ህፃናት እናቶቻቸው ለማጥባት በሚመጡበት ወቅት አረፍ ብለው ሊያጠቡ የሚችሉበት ቦታና ተጨማሪ ምግብ የሚጠቀሙ ህፃናት ምግባቸው የሚዘጋጅበትና ከተዘጋጀም በኋላ በወላጅ እናቶቻቸው ወይም በተንከባካቢያቸው አማካኝነት ሊመገቡበት የሚያስችላቸው ቦታ ሊኖረው ይገባል፡፡

(2) ክፍሉ በቂ የተፈጥሮ ብርሃን የሚገባበት፣ ንፁህ አየር የሚዘዋወርበትና ቀጥታ የፀሐይ ጨረር የማይገባበት ክፍል ሊሆን ይገባል፡፡ የማብሰያ ክፍሉም ከመመገቢያ ክፍሉ ጋር የተያያዘ ሆኖ ህፃናቱ ሊደርሱበት የማይችሉበትና ለብቻው የተከለለ መሆን አለበት፡፡

(3) በማብሰያና መመገቢያ ክፍል የምግብ ማብሰያ ምድጃ (የኤሌክትሪክ እና ሲሊንደር)፣ ፍሪጅ፣ የውሃ ማጣሪያና ማሞቂያ፣ የማብሰያና የመመገቢያ ቁሳቁሶችን ማጠቢያ ቦታ (ሲንክ) እና እቃ ማስቀመጫ/መደርደሪያ ሳጥን እንዲሁም፣ የህፃናት መመገቢያ ጠረጴዛና ወንበር እና የአዋቂ ወንበር የያዘ መሆን አለበት፡፡

 ክፍል 3

 ለህጻናት ማቆያው የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና የሚጠበቅ ስነ-ምግባር

11. የሰው ኃይል

(1) የህጻናት ማቆያው እንደሚያስተናግደው ህጻናት ብዛትና የተቋሙ ስፋት አንጻር የሰው ሀይሉ ቁጥር የሚወሰን ሆኖ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችለው በበቂ የሰው ኃይል መደራጀት ይኖርበታል፡፡

(2) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ህጻናት ማቆያው ከዚህ በታች የተመለከቱት የሰው ሃይል አሟልቶ መያዝ አለበት፣

(ሀ) በህፃናት አያያዝና እንክብካቤ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና 10+3 ያጠናቀቀች፣

 የህጻናት ማቆያ ስልጠና የወሰደች፣ በመጀመሪያ ዕርዳታ አስፈላጊውን ስልጠና

 የወሰደች   ፣  በባህሪዋ፣   በፀባይዋና    በሥራዋ    ምስጉን   የሆነች   ሴት   የህጻናት

 ተንከባካቢ፤

(ለ) በህጻናት ማቆያው የሚገለገሉት ህፃናት እንደመሆናቸው መጠን ህፃናቱ በሚያደርጓቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ችግር እንዳይገጥማቸው የማዕከሉን ፅዳት እየተከታተለችና ከተንከባካቢዎች የሚሰጧትን ጥቆማዎች ባለመሰልቸት ተቀብላ ለመተግበር ፈቃደኛ የሆነች፣ በባህሪዋ፣ በፀባይዋና በሥራዋ ምስጉን የሆነች ሴት የጽዳት ሰራተኛ ፣

(ሐ) ህጻናት ማቆያው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናትን የሚያስተናግድ ከሆነ አንድ ነርስ ሊኖሩት ይገባል፡፡

(3) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ(2) የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ የህጻን ተንከባካቢ(ሞግዚት) ከ5 በላይ ህጻናት መንከባከብ የለባትም፡፡

12. የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ሃላፊነት

(1) የህጻናት ማቆያ ተጠሪነት በመንግስት መ/ቤቱ ውስጥ ለተቋቋመው የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ይሆናል፡፡

(2) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) መሰረት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከህጻናት መቆያው ስራዎች ጋር በተያያዘ የሚከተሉት ሀላፊነት ይኖሩታል፣

(ሀ) በዚህ መመሪያ በተመለከተው መስፈርት መሰረት የህጻናት ማቆያ በመንግስት መ/ቤቱ ውስጥ እንዲቋቋም የማድረግ፣

(ለ) የመንግስት መ/ቤቱ ለህጻናት ማቆያው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና የሰው ሃይል እንዲሟላ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን በጀት እንዲያዝ ክትትል የማድረግና መነሻ ጥኖቶችን የማቅረብ፣

(ሐ) የህጻናት ማቆያው የአካባቢ ፀጥታና ንፅህና መጠበቁን የማረጋገጥ፣

(መ) የህጻናት ማቆያ በመወከል አስፈላጊ የሆኑ ስምምነቶችን ማከናወንና ኃላፊነቶችን የመቀበል፡፡

13.    በህጻናት ማቆያው የሚመደቡ ሰራተኞች ሃላፊነትና ተጠያቂነት

(1) የመንግስት መስሪያ ቤቱ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ህጻናትን ለመንከባከብ የሚመደቡ ሰራተኞች ከተላላፊ በሽታዎች ነጻ ስለመሆናቸው እንዲመረመሩ ለማድረግ ይችላል፡፡ በህጻናት ማቆያው የሚመደቡ ሰራተኞችም ምርመራ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ለምርመራ የመቅረብ ሃላፊነት አለባቸው፡፡

(2) ህጻናትን ለመከባከብ የተቀጠሩ ሰራተኞች ሆን ብለው ወይም በቸልተኝነት  በህጻናት ማቆያው ውስጥ ባለ ህጻን ላይ ጉዳት ካደረሱ በወንጀልና በፍትሃ ብሔር ያለባቸው ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ በከባድ የዲስፕሊን ጥፋት እንዲከሰሱ ይደረጋል፡፡

(3) የመስሪያ ቤቱ የስራ አካባቢና ደህንነት ባለሙያ በተጨማሪ የህጻናቱ ደህንነት ስለመጠበቁ በየሳምንቱ መጨረሻ ክትትል በማድረግ ለሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት የማቅረብ ሃላፊነት አለበት፡፡

(4) በዚህ መመሪያ ክፍል ሶስት የተመለከቱትን አሰራሮች  የማክበር  ግዴታ  አለበት፡፡

 ክፍል አራት

 በህጻናት ማቆያ ስለሚሰጡ የአገልግሎት አይነትና የአሰጣጥ ሁኔታ

14. በየህጻናት ማቆያ የሚሰጡ አገልግሎቶች

በማእከሉ ከዚህ በታች ያሉ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ ይኖርበታል (1) የመኝታና የማረፊያ ቦታ አቅርቦትና አገልግሎት፣

(2) የመጫወቻ ቦታ አቅርቦትና አገልግሎት፣

(3) የምግብ ማብሰያ ቦታ አቅርቦትና አገልግሎት፣

(4 የመመገቢያ ቦታ አቅርቦትና አገልግሎት፣

(5) የንፅህና መጠበቂያና ለህፃናት የመፀዳጃ ቦታ አቅርቦትና አገልግሎት፣ (6) የእንክብካቤና የቅርብ ክትትል አገልግሎት፣

(7) የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት፣

15. የህጻናት ማቆያው የስራ ሰዓት

(1) ህፃናት ማቆያ አገልግሎት መስጫ ቀናት ከሰኞ እስከ አርብ ሆኖ በመንግስት የስራ ሰአት ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 11፡30 ብቻ የሚሰጥ ይሆናል፣

(2) በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስት የስራ ሰዓት የምሳ ሰዓትን ይጨምራል፡፡

(3) በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ (1) ቢኖርም የተለየ የስራ ቀናትና የስራ ሰዓታት ያሉዋቸው የመንግስት መ/ቤቶች ካሉ በህግ የተወሰነውን የራሳቸውን የስራ ቀናትና የስራ ሰዓት መሠረት በማድረግ የህጻናት ማቆያው አገልግሎት የሚሰጥበትን የስራ ቀናትንና ሰዓት ሊወስኑ ሊያስተካክሉ ይችላሉ፡፡

16.የህጻናት ማቆያው ተገልጋዮች ሃላፊነት

ማንኛውም በህጻናት ማቆያው ህጻን ልጁን ለማምጣትና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በዚህ መመሪያ የተፈቀደላት ሴት የመንግስት ሰራተኛ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በቅድሚያ ከዚህ በታች የተቀመጡትን ዝርዝር ሁኔታዎች ሟላት ይኖርባታል፡፡

(1) አገልግሎቱን ለማግኘት ህጻን ልጇን የማስመዝገብ፣

(2) ለምዝገባ ሲትቀርብ የህጻን ልጇን የልደት የምስክር ወረቀት፣ ልጇ ተገቢውን ክትባት መውዷን/መውሰዱን የሚያረጋግጥ የሃኪም ማስረጃ፣

(3) የህጻኗንና የመንግስት ሰራተኛዋ የራሷን ሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፍ የማቅረብና ለዚሁ አገልግሎት የሚል መታወቂያ የመወሰድ፡፡

17. የህጻናት ማቆያው ተገልጋዮች ግዴታ ማንናውም የህጻናት ማቆያው ተገልጋይ፣

(1) በዚህ መመሪያ የተመከቱትን አሰራሮችና መ/ቤቱ አገልግሎቱን የበለጠ ለማጠናከር የሚወጣቸውን ተጨማሪ አሰራሮች የማክበር ፣

 (2) የማእከሉ የስራ ሰዓት መሰረት ባደረገ ህፃናትን ይዘው የመምጣትና ለተንከባካቢዎች የማስረከብ፣ እንዲሁም በስራ መውጫ ሰዓት ላይ ሰዓት ላይ የተሰጣቸው ልዩ መታወቂያ ህጻኑን/ህጻኗን የመረከብ፣

(3) ለዕለቱ የሚስፈልገውን በቂ፣ የተመጣጠነ፣ ጤናማና የአስተሻሸግ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ የታሸገ/የተያዘ ምግብ ከመመገቢያ ቁሳቁስ ጋር ለተንከባካቢዎች የማስረካብ፣

(4) ተዘጋጅቶ ለህፃኑ የሚቀርብ ምግብ ከሆነ ከበቂ የምግብ ዕይነቶቹ ዝርዝርና የአዘገጃጀት ማብራሪያ ፅሁፍ ጋር አያይዞ የማቅረብ ፣

(5) ለዕለቱ የአየር ሁኔታ የሚስማማና ለአንድ ቀን የሚበቃ ንፁህ ቅያሪ ልብስ፣ ጫማና ካልሲ፣አንሶላና ብርድ እንዲሁም የቆሸሹና የተቀየሩ ልብሶችን መያዣ የሚሆን ቦርሳ/ከረጢት የማቅረብ፣

(6) የህጻናት ማቆያው ተገልጋዮች ህጻን ልጃቸውን ይዘው ሲመጡ የህጻናቱን ንጽህና ጠብቀውና የታጡ ልብሶቸችን አልብሰው የማስረከብ፣ እንዲሁም አቅሙ በፈቀደ መጠን ለህጻኑ/ኗ ለቀኑ የሚያገለግል በቂ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አዘጋጅተው የማቅረብ፣

(7) ወደ ህጻናት ማቆያው አገግሎት ፈልገው የሚመጡ ወላጆችና ህፃናት ለተላላፊ በሽታዎች የተጋለጡ አለመሆናቸውን የማረጋገጥ፣

(8) ህጻናቱ በእድሚያቸው የሚሰጠውን ክትባትና የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ የማቅረብ ፣ሃላፊነት አለባቸው፡፡

18.የህጻናት ማቆያው የአሰራር ስርዓት

(1) የህጻናት ማቆያውን አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ወላጆች አገልግሎቱን ከማግኘታቸው በፊት በማቆያው ሰራተኞች እንዲመዘገቡ መደረግ አለበት፡፡

(2) የህጻናት ማቆያው ተገልጋይና የህፃኑ ወላጅ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ በመንግስት መ/ቤቱ የተዘጋጀ ልዩ መታወቂያ ካርድ ለተገልጋይዋ ሰራተኛ መሰጠት አለበት፡፡

(3) ለተገልጋይዋ የሚሰጠው ልዩ መታወቂያ የወላጅና የህፃኑ/ኗ ፎቶግራፍ የተለጠፈበት መሆን አለበት፡፡

 (4) በህጻናት ማቆያ ውስጥ ተመድቦ የሚሰራ ሰራተኞች በማቆያው ለመገልገል የሚመጡ ህጻናት በቅድሚያ የመንግስት መ/ቤቱ ባዘጋጀው የመመዝገቢያ  ቅጽ የተመዘገቡ መሆኑንና የተሰጣቸውን ልዩ መታወቂያ መያዛቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡

(5) ወላጆችም ልጆቻቸውን ለማስረከብ በሚመጡበት ወቅት የተሰጣቸውን ልዩ የመታወቂያ ካርድ ይዘው በመቅረብ አስመዝግበው ማስረከብ አለባቸው፡፡

(6) ልጆቻቸውን ለመረከብ በሚመጡበት ወቅትም ይህንኑ መታወቂያ ካርድ ይዘውና ልጆቻቸውን መረከብና ስለመረከባቸውም በፊርማቸው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

(7) ባለመታወቂያው ወላጅ መገኘት በማይችሉበት ወቅት ሁለተኛ ወላጅ ማንነትን የሚገልፅ ከህጋዊ የመንግስት አካል የተሰጣቸውን መታወቂያ ካርድ እና መ/ቤቱ የተሰጣቸውን ልዩ መታወቂያ ካርድ አያይዘው በማቅረብ ልጃቸውን መውሰድና ስለመውሰዳቸው በፊርማቸው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

(8) የተቋሙ ሠራተኛ ከሆኑት ውጪ የህጻናት ማቆያውን አገልግሎት ለማግኘት በተቋሙ ለተለያዩ የስብሰባ፣ የስልጠናና መሰል ፕሮግራሞች የሚመጡና ከተቋሙ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ተገልጋዮች የህጻናት ማቆያውን አገልግሎት ፈልገው በሚመጡበት ወቅት ህጋዊ ከሆነ የመንግስት አካል የተሰጣቸውን ማንነታቸውን የሚገልፅ የመታወቂያ ካርድ ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡

(9) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (8) የተገለጹት ተገልጋዮች አገልግሎቱን በጊዜያዊነት ፈልገው የመጡ ቢሆኑም ልጆቻቸውን ህጻናት ማቆያው ለማቆየት ይዘው በሚመጡበት ወቅት በመታወቂያ ካርዳቸው አማካኝነት ምዝገባ እንዲከናወንና ለልጃቸውም ልዩ መለያ (ኮድ) እንዲሰጥ ተደርጎ ለወላጆቻቸው መሰጥት አለበት ፡፡ በተጨማሪም ለህጻኑ/ኗ የሚያስፈልጉ በዚህ መመሪያ የተመለከቱትን አልባሳትና ምግቦችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

(10) በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (8) የተገለጹት ተገልጋዮች ልጃቸውን ለመረከብም በሚመጡበት ወቅት በምዝገባ ጊዜ የተሰጠቸውን ልዩ መለያ (ኮድ) እና የመታወቂያ ካርዳቸውን በማመሳከር ልጆቻቸውን እንዲረከቡ

መደረግ አለበት፡፡ በህጻናት መቆያው ውስጥ የተመደቡ ሰራተኞችም የቀረበው ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን አጣርተው ህጻናቱን ማስረካብና ወላጆችም ስለመረከባቸው በፊርማ እንዲያረጋግጡ ማድረግ አለባቸው፡፡

19.     የመጓጓዣ ትራንስፖርት

 ክፍል አራት

 ልዩ ልዩ ሁኔታዎች

1. በዚህ መመሪያ መሰረት በመንግስት መስሪያ ቤቱ ውስጥ በሚቋቋመው የህጻናት ማቆያ ተጠቃሚ እንድትሆን የተፈቃደላት የመንግስት ሰራተኛ ጠዋት ወደ ስራ ስትመጣና ማታ ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇን ይዛ በፐብሊክ ትራንስፖት አገልግሎት የመጠቀም መብት አላት፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ(1) መሰረት ተጠቃሚ የሚሆኑ ሴት የመንግስት ሰራተኞችና ህጻናት በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎትን በተለየ መንገድ ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት ሁኔታ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትርራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሚያወጣው ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ የሚወሰን ይሆናል፡፡

20. ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናትን በተመለከተ

ልዩ ፍጎት ያላቸው ህጻናት በህጻናት ማቆያው ለመገልገል ከመጡ ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤቱ እንደ ህጻናቱ ፍላጎት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸት ሃላፊነት አለበት፡፡

21. በጀት

(1) ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ለህጻናት ማቆያው የሚያስፈልጉ በዚህ መመሪያ የተመለከቱ ቁሳቁሶች ለማሟላትና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ወጪ በመንግስት እንዲመደብ ያደርጋል፡፡

(2) በዚህ መመመሪያ አንቀጽ (5) ንኡስ አንቀጽ (3) መሰረት የተቋቋመ የህጻናት ማቆያ የሚስፈልገውን በጀትና የሰው ሃይል መስሪያ ቤቶቹ በጋር እንዲሸፍኑ መደረግ ይኖርበታል አለበት፡፡

22.  የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት

(1) የህጻናት ማቆያ ማዕከል አገልግሎት ከፍተኛ ጥንቃቄና  ጥብቅ  ክትትል  የሚጠይቅ አገልግሎት በመሆኑ የመ/ቤቱ የስራ አካባቢና ደህንነት ባለሙያ በሳምንት አንድ ቀን በማእከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት፣ ጊዜውን ጠብቀው አገልግሎቱን እያገኙ ስለመሆኑ፣ የአካባቢውን እና የህጻናትን ንጽህና በአግባቡ መጠበቁን፣ በህጻናት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፣ የህጻናት ጤናና ሌሎች በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ጥብቅና ተከታታይ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሪፖርት ማቅረብ ይኖበታል፡፡

(2) በተጨማሪም የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በየጊዜው  የማዕከሉን ይዘት፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የቁሳቁስ አቅርቦት፣ የአካባቢውን ደህንነትና ሰላም የመገምግም፣ የመከታተልና የመደገፍ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ በአካል በማዕከሉ በመሄድ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡

23.መመሪያው የሚጸናበት ጊዜ

ይህ መመሪያ ከሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

ያለም ፀጋይ

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.