Cassation Decisions

አለአግባብ መበልፀግ-የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም

የሌላውን ሰው የሥራ ድካም ወይም በሌላው ሰው ሀብት በመገልገል በቂ ባልሆነ ምክንያት ጥቅም ማግኘት

አንድ ሰው የሌላውን ሰው የሥራ ድካም ወይም በሌላው ሰው ሀብት በመገልገል በቂ ባልሆነ ምክንያት ጥቅም ያገኘ እንደሆነ አላግባብ ባገኘው ጥቅም መጠን ለባለሀብቱ ወይም በጉልበቱ ለደከመው ሰው የመመለስና የመካስ ግዴታ ያለበት መሆኑ በፍታብሔር ህግ ቁጥር 2162 በመሠረታዊ መርህነት ተደንግጓል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ሲታይ የሚከፈለው የካሳ መጠን የሚወሰነው ተከሳሹ ያገኘው ጥቅምና ከሳሹ የደረሰበት ኪሳራ ተመዛዝነው በመታየት ስለመሆኑ ያስገነዝባል፡፡ በመሆኑም ለከሳሹ የሚወሰንለት ካሳ ተከሳሹ ካገኘው ጥቅምም ሆነ ከሳሹ ከደረሰበት ኪሳራ ሊበልጥ እንደማይገባ ሕጉ ያሳያል፡፡ ሕጉ ተከሳሹ የሚያገኘው ጥቅም በንብረት ላይ የተቋቋመ ግዙፍ መብት ወይም ከአንድ ሰው ላይ የሚጠየቅ መብት ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ተከሳሹ የነበረበት እዳ ተሰርዞለት ወይም ግዴታው ቀርቶለት ወይም ኪሳራ ሳይደርስበት ቀርቶ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በተከሳሹ በኩል የተገኘው ጥቅም መኖር ብቻ ሳይሆን የተገኘው ጥቅም የሕሊና እርካታን የሚያስገኝና በገንዘብ ሊተመን የሚችል መሆን አለበት፡፡

ሰ/መ/ቁ. 93104 ቅጽ 16፣[1] ሰ/መ/ቁ. 90529 ቅጽ 18፣[2] ፍ/ህ/ቁ.  2162

በክፉ ልቦና የተደረገ ወጪ

አንድ ሰው ለተወሰነ ጊዜ በእጁ ያቆየውን እቃ እንዲመልስ የተገደደ እንደሆነ ለሕግ ወይም ለውል ተቃራኒ የሚሆን ድንጋጌ ከሌለ በቀር የተባለውን እቃ ከመለዋወጥ የተነሳ ያሉት መብቶችና ግዴታዎች ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2168 ቀጥለው ባሉት ደንቦች መሰረት የሚወሰን ሲሆን በዚሁ ድንጋጌ ስር ከሰፈሩት ደንቦች መካከል አንዱ የሆነው በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2169 ስር የተቀመጠው ደግሞ የያዘውን እቃ እንዲመልስ የተገደደ ሰው በእቃው ላይ ያደረገው ወጪ ሊመለስለት የሚገባው ወጪው የግድ አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ስለመሆኑና ወጪው አስፈላጊ ሳይሆን ከቀረ ወይም ወጪው እቃውን እንዲመልስ በተገደደው ሰው ወይም ተገዳጁ ኃላፊ በሚሆንበት ሰው ጥፋት ምክንያት ከሆነ ወጪው ሊመለስ የማይችል መሆኑን ያሳያል፡፡

ሕጉ በአንቀጽ 2171(1) ስርም ለእቃው የተደረገው ወጪ የእቃውን ዋጋ ግምት ከፍ አድርጎት እንደሆነም እቃውን ለመመለስ የተገደደው ሰው ስለዚሁ ጉዳይ ያወጣው ገንዘብ ሊመልስለት እንደሚገባ የደነገገ ሲሆን ይህ ወጪ በክፉ ልቦና ስለመደረጉ የተረጋገጠ ወይም ርትዕም የሚያስገድድ ከሆነ ደግሞ ዳኞች ወጪውን ለመቀነስ ወይም ጭራሹን ለማስቀረት የሚችሉበት አግባብ መኖሩንን የተጠቃሹ ድንጋጌ ቀጣይ የሆነው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2172((1) ይዘት ያሳያል፡፡ ይህ ድንጋጌ አንድን ወጪ በክፉ ልቦና የተደረገ ነው ለማለት የሚቻልበት አግባብም ወጪው በተደረገበት ጊዜ ወጪውን የሚጠይቅ ሰው እቃውን ለመመለስ ግዴታ ያለበት መሆኑን ያውቅ እንደነበረ ወይም ማወቅ ይገባው የነበረና ርትዕም ሲያስገድድ መሆኑን በመለኪያነት አስቀምጧል፡፡

ስለሆነም እነዚህ ድንጋጌዎች ሲታዩ አንድ ሰው የሌላ ሰው ንብረት ይዞ ሲጠቀም ከቆየና ንብረቱን በሚጠቀምበት ጊዜ ንብረቱን ከጥፋት ወይም ከብልሽት ለማዳን ሲል ተገቢውን ወጪ ቢያወጣ ይኼው ወጪ በሕጋዊ ባለሃብቱ እንዲተካለት መጠየቅ የሚችልበት አግባብ የሚኖረው ወጪው የግድ አስፈላጊ ከሆነና በቅን ልቦና የተደረገ መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡ ሲሆን በክፉ ልቦና የተደረገ ስለመሆኑ የተረጋገጠውን ወጪ ግን እቃውን እንዲመልስ የተደረገ ሰው ሊቀነስበት ወይም ጭራሹንም ዳኞች ሊያስቀሩት የሚችሉ ስለመሆኑ ሕግ ስልጣን የሰጣቸው መሆኑን ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡

ሰ/መ/ ቁ. 81081 ቅጽ 14፣[3] ፍ/ህ/ቁ. 2168፣ 2169 2171(1)፣ 2171(2)


[1] አመልካች ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና ተጠሪ አቶ ደስታ ጁላ ቤካሎ ሚያዚያ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

[2] አመልካች አቶ ኃይለየሱስ መንግስቴ ይግዛው እና ተጠሪ አማኑኤሌ ፀጋ የከተማ ሱቅ ቤቶች ልማት አክሲዮን ማህበር ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም.

[3] አመልካች ወ/ሮ ፍሬ ሕይወት መብራህቱ ገ/መድህን እና ተጠሪ እነ አቶ መብራህቱ ገ/መድህን /2 ሰዎች/ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.