Articles

የሰበር ችሎት 11 የህግ አተረጓጎም ደንቦች

ህግ እንደማንኛውም የስነ ጽሑፍ ስራ ህግ ለማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል የሚጽፈው ድርሰት ነው። በመርህ ደረጃ ማንበብ የሚችል ዜጋ ሁሉ (በሙያው መመረቅና መሰልጠን ሳያስፈልገው) ይህን ህግ አንብቦ ይረዳዋል ተብሎ ይገመታል። ይሁን እንጂ የተጻፈ ህግ ከሌሎች ድርሰቶች በእጅጉ የሚለው የራሱ ባህርይ፣ ዘይቤና የአጻጻፍ ስርዓት አለው። ስለሆነም በሁሉም ዜጋ ይቅርና ህጉን በሚጽፈው፣ በሚያስፈጽመውና በሚተረጉመው አካል ወጥና ተመሳሳይ መረዳት አይኖርም። የህጉ ቋንቋ የሚፈጥረው የአረዳድ ልዩነት አንድ ቦታ ላይ ሊቋጭ ስለሚገባው አንደኛው የመንግስት አካል የሚሰጠው ትርጉም ባልተግባቡት ወገኖች መካከል አሳሪ ይሆን ዘንድ ፍርድ ቤት ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ ዕውቅናና ብቃት ያለው ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል።

ፍርድ ቤትም ቢሆን ግን አንድ ምላስ እንጂ አንድ ራስ የለውም። አንዲት ድንጋጌ በፌደራልና በክልል፣ በበላይና በበታች ፍ/ቤቶች ብሎም በውስጣቸው በሚገኙት ችሎቶች የተለያየ አንዳንዴም የተራራቀ መልዕክት ታስተላልፋለች። ሁልጊዜ ይህን መሰሉ አለመናበብ ባይኖርም ክስተቱ አይቀሬ ነው። አይቀሬነቱ የሚመነጨው ከአንባቢው (ዳኛው) ስህተትና ግድፈት ብቻ አይደለም፤ ከተነባቢው (ከተጻፈው ህግ) ልዩና ውስብስብ ባህርያት ጭምር እንጂ።

የአገራችን የመጨረሻ፤ የበላይ ህግ ተርጓሚ የሆነው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሚና በእያንዳንዱ በቀረበለት መዝገብ ላይ ህጉ ምን እንደሚል ትርጉም መስጠት ብቻ አይደለም። ከዚህ ባለፈ የስር ፍርድ ቤቶች ምን ዓይነት የህግ አተረጓጎም ስልት መከተል እንዳለባቸው ጭምር መመሪያ መስጠት ይጠበቅበታል። ይሄ ደግሞ ወጥነት ከማስፈኑ በላይ የችሎቱን ስራ በእጅጉ ያቀልለታል። ለምሳሌ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ለእያንዳንዱ ድንጋጌ ትርጉም ከመስጠት ባለፈ የስር ፍር ቤቶች ህጉን በምን ዓይነት የአተረጓጎም ስልት መተርጎም እንዳለባቸው አቅጣጭ ቢያስቀምጥ መሰረታዊ የህግ ስህተቶች ቁጥራቸው ይቀንሳል። በተለይ የህግ አተረጓጎም ስልትን የሚገዛ ዝርዝር ህግ በሌለበት /ከተወሰኑት ድንጋጌዎች በቀር/ በአገራችን የስር ፍርድ ቤቶች መከተል ስላለባቸው የህግ አተረጓጎም ስልት ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጥ ችሎት ዋነኛ ሚናው አድርጎ መውሰድ ይኖርበታል።

እስካሁን በሰበር ችሎት በተሰጡ ውሳኔዎች የህግ አተረጓጎም ስልትን በተመለከተ ጎልቶ የሚታይ ባናገኝም በተወሰኑ ውሳኔዎች ችሎቱ የተጠቀማቸው ስልቶች ጠቅለል ባለ አነጋገርም ቢሆን ተገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይታከልባቸው በውሳኔዎቹ ላይ እንደተጠቀሱ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

1. የቃላት ዝርያ /ማራባት/

ሰ/መ/ቁ. 79476 ቅጽ 18

ከድንጋጌው ውስጥ “…የሌሎችም ክፍያዎች..” ወይም “.. Other payments…” የሚለው ሐረግ ጠቅላላ ቃል መሆኑ ግልጽ ሲሆን እንዲህ በሆነ ጊዜ ቃሉን ሕግ አውጪው የተጠቀመው ምንን ለማመላከት ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሣቱ ተገቢ ሲሆን የሕግ አተረጓጎም መርሆዎችን መሠረት በማድረግም ምላሹን ማግኘት ይቻላል። በዚህም መሠረት ከጠቅላላው ቃል በፊት የተዘረዘሩት የቃላት ዝርያ የሚያሣዩትን ሁኔታ በመመልከት ጠቅላላ ቃል ሌሎች ያልተዘረዘሩትን ተመሣሣይ ዝርያ ያላቸውን ቃላት ለመጠቀም ታስቦ የተቀመጠ ነው በሚል እንደሚተረጎም ተቀባይነት ያላቸው የሕግ አተረጓጎም መርሆዎች ያስገነዝባሉ።

2. ጥብቅ የሕግ አተረጓጐም መርህ

ሰ/መ/ቁ. 98263 ቅጽ 17

በፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ አፈፃፀም ለማስቀረት የፍርድ ባለመብት እና የፍርድ ባለዕዳ የሚያደርጉት የዕርቅ ውል፣ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 276 እና በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 277/1/ የተደነገገውን ጥብቅ መስፈርት የሚያሟላ ባልሆነበት ጊዜ፣ ህጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት እንደማይኖረው የሚያረጋግጥ፣ ጥብቅ የሆነ የሕግ አተረጓጐም መርህ መከተል የፍርድ አፈፃፀም ስርዓቱን ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ እንዲከናወን ለማድረግ አስፈላጊ ነው።

3. ህጉን በጠባቡ መተርጎም

ሰ/መ/ቁ. 50985 ቅጽ 13

የውክልና ስልጣን የሚተረጎመው ሳይስፋፋ በጠባቡ ነው፡፡

4. የቃል በቃል ንባብ /የተናጠል ንባብ/

ሰ/መ/ቁ. 57632 ቅጽ 12

የ2 ዳኞች የልዩነት ሀሳብ

ከላይ ከደረስንበት መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ከዚህ በፊት ከላይ ከገለፅናቸው ምክንያቶች በተጨማሪ የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 አቀራረፅ እና የቃል በቃል ንባብ መገናዘብ አለበት የሚል እምነት አለን።

ሰ/መ/ቁ 101271 ቅጽ 16

የአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 44 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረታዊ ባህሪና ዓላማ እንደዚሁም ድንጋጌው በአካዳሚክ ሰራተኞች የይግባኝ መብት ላይ የሚኖረውን ሕጋዊ ውጤት ለመረዳት የድንጋጌውን የተናጠል የቃል በቃል ንባብ ማየት ብቻዉን በቂ አይደለም።

5. ዓላማ

ሰ/መ/ቁ. 93137 ቅጽ 15

የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 6 ዓይነተኛ ዓላማ ተገቢ ሁኔታዎችና ፍሬ ነገሮች ተሟልተው መገኘታቸው ሲረጋገጥ በሀሰተኛ ማስረጃ፣ በመደለያና በመሰል ወንጀል ጠቀስ ድርጊቶች ምክንያት የተዛነፈውን ፍትሕ ወደነበረበት መመለስ ነው።

6. ተቃራኒ ንባብ

የሰ/መ/ቁጥር 46386 ቅጽ 13

በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ ውሣኔ በዚያው ጉዳይ በፍታብሔር በማስረጃነት አግባብነት እና ብቃት የሚኖረው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2149 ተቃራኒው ንባብ ያስገነዝበናል።

7. ግልባጭ ንባብ

ሰ/መ/ቁ. 49635 ቅጽ 12

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2278 እንደተመለከተው የተሸጠን ነገር የተረከበ ገዥ የሽያጩን ዋጋ ወዲያውኑ የመክፈል ግዳታ ያለበት በመሆኑና የሽያጩ ዋጋ ያልተከፈለው ሻጭ የተሸጠውን ነገር ሳያስረክብ በእጁ የማቆየት መብት የሚሰጠው ለመሆኑ የዚሁ ድንጋጌ ግልባጭ ንባብ ስለሚያስረዳ…

8. የተቃርኖ ንባብ

ሰ/መ/ቁ. 54129 ቅጽ 11

የአስተዳደር መስሪያ ቤት መብቱን የሚጠይቀውም ሆነ ግዴታውን የሚወጣው ለሥራ ተቋራጩ ሲሆን የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ግንኙነት ከሥራ ተቋራጩ ጋር ብቻ የሚወሰን መሆኑን ከፍታብሔር ህግ ቁጥር 3205 እና ከፍታብሔር ህግ ቁጥር 3206 የተቃርኖ ንባብና ትርጉም ‛Acontrario reading and Interpretation‛ ለመገንዘብ ይቻላል።

9. ጣምራ ንባብ

ሰ/መ/ቁ. 86398 ቅጽ 17

የመቃወም አቤቱታው እና የማስረጃው ቅጂ የመቃወም ተጠሪ ለሆነው ወገን እንዲደርስ መደረግ የሚገባው መሆኑን ከመግለጽ በስተቀር የመቃወም ተጠሪው የጽሁፍ መልስ እና የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚገባው በእነዚህ ድንጋጌዎች ላይ በግልጽ የተጻፈ ባይሆንም የመቃወም ተጠሪ የሆነው ወገን በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 234 ድንጋጌ መሰረት ለቀረበበት የመቃወም አቤቱታ ያለውን የመከላከያ መልስ እና ማስረጃ ማቅረብ የሚገባው ስለመሆኑ ከቁጥር 360(1) እና (2) ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ መገንዘብ ይቻላል።

10.   አውድ ንባብ

ሰ/መ/ቁ. 67280 ቅጽ 11

ሕግ አውጪው የትምህርት ዝግጅትንና የሥራ ልምድን ለያይቶ እኩል ዋጋ በአንድ አንቀፅ ከሰጠ በኋላ በተከታዩ ድንጋጌ ተመሣሣይ መንፈስ ያለው አንቀፅ ያስቀምጣል ማለት ትርጉም አልባ ከመሆኑም በላይ የሕጎችን አውድ ንባብ (contextual interpretation) ትርጓሜ ያልተከተለ፤ አዋጁ ውጤት እንዲኖረውና በአዎንታዊ መንገድ ታይቶ ሥራ ሊይ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የአተረጓጎም መንገድ ሆኖ አይገኝም።

11.   ጠቅላላ እና ልዩ ህግ

ሰ/መ/ቁ. 39803 ቅጽ 8

ይሁንና የማይንቀሳቀስ ንብረትን ስጦታ በተመለከተ በተለይ በሚገዛው ከፍ ብሎ በተጠቀሰው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2443 እና 881 ዴንጋጌ መሠረት ይህ ሥርዓት መከናወን እንዳለበት አልተመለከተም። በጠቅላላ ሕግና በልዩ ሕግ መካከል አለመጣጣም ወይንም ልዩነት በሚኖርበት ጊዜ ልዩ ሕግ የበላይ ሆኖ ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደሚችል /The Special prevail over the general/ ከሕግ አተረጓጎም መርህ መገንዘብ ይቻላል።

ሰ/መ/ቁ. 24703 ቅጽ 7 የግራ ቀኙን ግንኙነት በተለይ የሚገዛው ልዩ ሕግ የሆነው የንግድ ሕጉ ስለሆነና በጠቅላላ ሕግና በልዩ ሕግ መካከል አለመጣጣም በሚኖርበት ጊዜ ልዩ ሕግ የበላይነት እንደሚኖረው /The special prevails over the general/ ከሕግ አተረጓጐም መርህ መገንዘብ የሚቻል እንደመሆኑ…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.