Uncategorized

የ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሕገ-መንግስት ፈርሷል ወይስ ተጥሷል?

ኢሳያስ ኃይለማሪያም

የ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሕገ-መንግስት ፈርሷል ወይስ ተጥሷል?

በመጀመሪያ፣ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የመቀጠል (mutual continuity) ቃል-ኪዳን የሚገለፅበት ድንጋጌ ራሱ የሕገ-መንግስቱ መግቢያ (preamble) በመሆኑ፣ ሕገ-መንግስቱ ፈርሷል (dismantled) ወይስ ተጥሷል (violated) የሚለው ጥያቄም የሚገመገመው የተጣሰ ልዩ አንቀፅ (provision) በማጣቀስ ሳይሆን፣ የፖሊቲካና ማህበራዊ ውሉ፣ (ከነ ጉድለቶቹና ኣወዛጋቢነቱ)፣ እንደ ጥቁር ቀለም ሕግ (black letter law) ሃገሪቱ ለሃያ ስምንት ኣመታት ትመራበት ዘንድ የሕገ-መንግስቱ ኣላማዎች፣ መርሆዎች፣ የኣርቃቂዎቹ ሃሳብና (intent of the legislators) የተዋዋዮቹ የወደፊት እጣ መሰረት የተጣለበት ፅንሰ-ሃሳብ ይሄው መግቢያው ነበር።

“እኛ የ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች…. ከላይ ከዚ በላይ ለገለፅናቸው አላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው…አማካይነት…ዛሬ ህዳር 29 1987 አፅድቀነዋል።”

በመግቢያው ከተገለፁት ዝርዝር የቃልኪዳኑ ኣላማዎች ዋና ዋናዎቹ፥ “…ዘላቂ ዘላም፣ የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ  በጋራ መገንባትየጋራ አመለካከት አለን ብለን ስለምናንምን፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት…” ወዘተ… ተዘርዝረዋል።

ይህ ማህበራዊ ውል (social contract) ሶስት መስረታዊ ምንጮች ሊኖሩት ይችላል:-

፩) በጋራ ከመኖር ማህበራዊ ስነ-ልቦና፣

፪) በሰዎች መካከል ከሚፈፀም የፖሊካና ህግ ውል  (ሕገ-መንግስት የህግም የፖሊቲካም ሰነድ ነው የሚባለው ለዚህ ነው) ሲሆን፣

፫) “መንግስት የሚፈጠረው የዜጎቹን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳከት ነው” ለሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ተዛማች ሃሳብ የመንግስት ዜጎችን የመከላከል ሃላፊነት (responsibility to protect) የኣለም ኣቀፍ መርሆን ተስፋ በማድረግ  ነው።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ስርኣት “ስልጣን” በያዘ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ የፖሊቲካ አስተሳሰብ ልዩነትን መሰረት ያደረገ ሰፊ ተቋማዊ ብሄር-ተኮር ጥቃት በተለይ የትግራይ ተወላጆች ላይ ታወጀ። ወዲያው በሕገ-መንግስቱ የተገለፀውን የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት  ቃል-ኪዳን በመጣስ፣ ከወልዲያና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ወደ ትግራይ የሚደረግን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመግታት (economic embargo) ተሽከርካሪ እስከማገድ የሚደርስ ኣፀያፊ ተግባር በባለ-ስልጣናት ሳይቀር ትእዛዝ ተሰጠበት፤ “የጋራ የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት” የሚለውን መርሆ ወደጎን በማሽቀንጠር “ከ ብልፅግና የፖሊቲካ ኣስተሳሰብ ውጭ ላሳር” ብቻ ሳይሆን፣ የተለየ የፖሊቲካ ኣስተሳሰብ የያዙትን ከምድረገፅ የማጥፋት የህገኣራዊት ዘመቻ “በሕግ ማከበር” ስም በግላጭ ታወጀ፤ “የጋራ አመለካከት” ራዕዩ ተሽሮ፣ የፖሊቲካና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ለማስፈን ከመነጨ ራስ-ወዳድነት ሳቢያ በትግራይና ሌሎች ብሄሮች ላይ ግልፅ የዘር ማጥፋት አዋጁ “የቀን ጅብ”፣ “ፀጉረ-ልውጥ” በመሳሰሉ የዘር-ማጥፋት የመጀመሪያ (classification) እና ሁለተኛ (symbolization) ደረጃዎች (initial stages of genocide) ታጅቦ ተጀመረ፣ በርካታ የትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ቤኒሻንጉል፣ ቅማንትና ሌሎች ብሄሮች ላይ ግልፅ ጦርነት ታወጀ፤ ዘላቂ ሰላም ምኞት ሆኖ በሁለት አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ለመፍረስ ወደተቃረቡ (fragile states) ተርታ የመሰለፏ ውድቀትና ዝቅጠት “ከፍታ” የሚል የዳቦ ስም ተሰጠው::

በተለይ፣ የአንድ ስርኣት ዜጎችን የመጠበቅና ህጋዊ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ መርሆዎችን እና ቃል-ኪዳን በመሻር የአብይ አህመድ ስርኣት ኤርትራን  (የውጭ ሃገር) በግላጭ በመጋበዝ በትግራይና ኦሮሞ ህዝቦች ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ኣሳፋሪ ክህደት ፈፀመ፤ የ ሕገ-መህግስቱ ቁልፍ መርሆ ተጣሰ፣ ቃል-ኪዳኑ በመጣሱና ውሉ በመፍረሱ የክህደቱ ሰለባ የሆነው የትግራይ ህዝብ በፓርላማና የፌደረሽን ምክርቤት እንዲሁም  ትግራይንና ኢትዮጵያን ወክለው ሲያገለግሉ የነበሩ ሌሎች የፌደራል ሃላፊዎችን በግልፅ ወደትግራይ በመጥራት (recall) የውክልና ስልጣኑን (delegated power) በማንሳት ውሉን በጠሰ፣ ገመዱ ተቆረጠ፤ ትግራይ በማህበራዊ  ውሉ ለማእከላዊው ስርኣት ሰጥታ የነበረውን የውክልና ስልጣን አስመልሳ ራሷን  ከጥፋት ለማዳን በመሰለፍ የራሷን ጉዳይ በራሷ የምትወሰንበት ሁኔታ መስመር ያዘ።

ሕገ-መንግስቱ ተጥሷል እንጂ አልፈረሰም” የሚሉት ኣካላት ሶስት መከራከርያዎችና ምክኒያቶች ኣሏቸው:-

፩) የሕገ-መንግስቱ መፍረስና የኢትዮጵያ መፍረስ ተመሳሳይ ውጤትና ኣንድምታ ስላለው፣ “ኢትዮጵያ አትፈስርም” የሚለውን የቆዬ ትርክት (rhetoric) በማጠናከር የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ማህበረስብ መፍረስ የማይዋጥለት ቡድን መከራከሪያ፣

፪) ሌላኛው አስተሳሰብ ደግሞ፣ በተለይ በቅርብ፣ በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች መካከል የሰላም ስምምነት (negotiation) ለማድረግ በታሰበበት ዋዜማ፣ “ሕገ-መንግስቱ ፈርሷል ካልን በምን ገዢ ህግ ድርድር ጠረጼዛ ላይ ልንቀመጥ እንችላለን” ከሚል ፍራቻና ጥርጣሬ የሚመነጨው እሳቤ  (የህግና የፍትሃዊነት ሳይሆን የፖሊቲካ ስሌት) ነው። ሕገ-መንግስቱ ፈርሷል ካልን፣ ድርድር ሊደረግባቸው የሚቻልባቸው ኣለማቀፍ መርሆዎችና የልማዳዊ ኣለማቀፋዊ ህጎች (customary international law) ኣስተሳሰቦችን ጨምሮ በርካታ ፖለቲካዊ የመፍትሄ አማራጮችን በሌላ ፅሁፍ እንመለስበታለን።

፫) ቀድሞውኑም “ፈርሷል” የተባለ ሕገ-መንግስትን ተንተርሶ የተመሰረተ ስርኣተ-መንግስት የቅቡልነት (legitimacy) እና ህጋዊነት (legality) ጥያቄ ሊያጋጥመው ስለሚችል የሕገ-መንግስቱን መፍረስ “በመጣስ” ኣይን ብቻ ኣቅልሎ የማየት አዝማሚያ ሊኖር ይችላል።

እንግዲህ፣ “ሕገ-መንግስቱ ኣልፈረሰም፣ ተጥሷል እንጂ” ማለት:-

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይና ሌሎች ህዝቦች የዘር ማጥፋት እልቂት ከተፈፀመና የዘር ማጥፋቱ የተፈፀመበት ማህበረሰብ በተፈፀመበት ክህደት ሳቢያ ከማህበራዊ ውሉ ራሱን ባገለለበት ሁኔታ የሕገ-መንግስቱ “የመጣስ ኣደጋ (violation) ብቻ ነው ያጋጠመው” ማለት፣ የዘር ማጥፋት ሰለባ በሆኑት ንፁሃን ማፌዝ ብቻ ሳይሆን፣ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋው ዘር-ማጥፋ ከተፈፀመ በሗላ ሳይቀር ማህበራዊ ስርኣት (social order) እንደማይናጋ፣ ዘር-ማጥፋት ከሌሎች ወንጀሎች የተለየ የተጠያቂነት ክብደት እንደሌለው በማመላከት እጅግ የተሳሳተ መልእክት ያስተላልፋል።

ለምሳሌ፣ የሰዎች የመሰብሰብ መብት፣ የፆታና ኢኮኖሚያዊ እኩልነት፣ በህግ ፊት እኩል የመታየትና ሌሎች መብቶች በሰልጣን ላይ ባለ አካል ከተገደቡ፣ ወይም መብቶች በሌላ ኣካል ሲገደቡ “ህግ የማስከበር ሃላፊነት አለብኝ” የሚለው አካል ከለላ መስጠት ካልቻለ ወይም ካልፈለገ (unable or unwilling to protect) “ህግ ተጣሰ” (violation) ሊባል ይችላል። በሌላ መልኩ፣ ከላይ ለተቀሱት መብቶች መሰረት የሆነው ማሰሪያ ቃል-ኪዳን (የሕገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ የተቀሰው የፖለቲካና ማህበራዊ ውል [political and social contract]) ሲጣስ፣ መብት ብቻ ሳይሆን የሚጣሰው ለመብቶቹ መስረት የጣለው፣ የመተማመኛ ቃል-ኪዳን ራሱ ይሆናል ማለት ነው።  የሕገ-መንግስቱ ቃል-ኪዳን ተንዶ ሕገ-መንግስት የማይፈርስ ከሆነ፣ በኣለም ውስጥ፣ “ምንም ይፈፀም ምን፣ የሚፈርስ ሕገ-መንግስት የለም” እንደማለት ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየዩ ኣካባቢዎች ዘግናኝ የጅምላ ወንጀሎች በተለያዬ ደረጃና ኣይነት በተለይ ስልጣን ላይ ባለው ኣካል ይሁንታና ትእዛዝ ተፈፅመዋል፤ በ ትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ግን እጅግ የከፋ፣ ለንፅፅር የማይቀርብ ነበር። እንደ ድህረ-ዘር ማጥፋት ማህበረሰብ (post-genocide society) ትግራይ ከፈረሰው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትና የፈረሰው ሕገ-መንግስት ከወለደው ህገወጥ  (illegitimate) ስርኣት ባሻገር  የራሷን ኣዲስ የፖሊቲካ ማህበረስብ በራሷ መንገድ እና ፍቃድ መቀየስ አስፈላጊ ነው።

Esayas Hailemariam [University of California, Berkeley School of Law; Haramaya University, College of the Law], July 2, 2022

Categories: Uncategorized

1 reply »

  1. It is a nice View. From my point of view the constitution is already teardown. And Tigray is by now an independent Nation

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.